10/09/2026
አገው ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (ፍትህ) ለመላው የአገው ህዝብና ለኢትዮጵያ ብሔረሰቦች እንኳን ለ2019 ዓ/ም በሠላም አደረሳችሁ!!! ፤ አደረሰን ይላል!፦
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
ድርጅታችን ፍትህ ለመላው የአገው ህዝብና ለኢትዮጵያ ብሔረሰቦች መጪው ዘመን ከሰቆቃ የምንፈወስበት ፣ ከተጋረጠብን የሠላም ዕጦት እረፍት የምናገኝበት ፣ የኑሮ ውድነት የሚቀንስበት እና ከመሰደድ የምንታደግበት ዓመት እንዲሆን ይመኛል።
ይህ ዓመት ለህዝባችን እና ለኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የተስፋ፣ የሠላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነት፣ የአንድነት፣ የመሰባሰብ፣ የመረዳዳት፣ የመቻቻል እና የስኬት ዘመን እንዲሆን የአገው ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ከልብ እየተመኘ የጀመረውን አገዋዊ እና ኢትዮጵያን የመታደግ ትግል በመጪው ዓመት ከምን ጊዜም በላይ አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
ፍትህ ፓርቲ የተመሠረተበት ዋናው ምሰሶ የአገው ህዝብ ለ800 ዓመታት የተነፈገበትን ነፃነትና ፍትህ ለማስፈን መሆኑ ግልፅ ሲሆን የአገው ህዝብ ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተከበሩ ማለት የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች መብት ያለ አንዳች ገደብ እንደሚከበር ድርጅታችን የምናል ማለት ነው።
ይህ ማለት የአገው ህዝብ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች አካል በመሆኑ የህዝባችን መብት ሲከበር የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች መብትም አብሮ እንደሚከበር ስለምንገነዘብ ነው። ድርጅታችን ፍትህ የሀገራችን ህዝብ ማህበራዊ ስሪቱ እንደ ማግና ድር የተጋመደና የተሳሰረ መሆኑን ስለሚረዳ አንዳችን ለአንዳችን ጌጥም፣ መከታም፣ ጠበቃም መሆን እንደሚገባን ያስገነዝባል።
2019 ዓ/ም የአገው ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲን (ፍትህ) የተለየ የሚያደርገው ከምን ጊዜም በላይ ለህዝባችን ድምፅ የምንሆንበት፣ ህዝበችን በ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ውክልና እንዲያገኝ በቂ ዝግጅትና ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጉ የሚታወቅ ቢሆንም ስልጣኑን እናጣለን በሚሉ ደካማዎችና ከህዝባችን በተገለሉ ድኩማን የቀበሌ፣ የወረዳ፣የከተማ አስተዳደር ፣ የዞን እና በክልል 3 ግልገል አምባገነን ካድሬች አማካይነት በክልል እና በህዝብ ተወካይ ም/ቤቶች አሸንፈን የአገው ህዝብን የስልጣን ባለቤት ለማድረግና ትክክለኛ ተወካይ ለመሆን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ያደረግን ቢሆንም በተላላኪዎችና በሆድ አደር ካድሬዎች ህዝባችን የሰጠን ድምፅ በአደባባይ ቢዘረፍብንም አሁንም ቢሆን ለህዝባችን ድምፅ፣ መከታ፣ ጠበቃና ተከራካሪ ለመሆን ከምን ጊዜም በላይ አገዋዊ ትግላችንን ጠንክረን የምንቀጥልበት ዓመት ይሆናል።
የ2019 ዓ/ም አንኳር አጀንዳችን ከሐምሌ 08/11/2018 እስከ ነሐሴ 16/12/2018 ዓ/ም በነበረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በእልህ አስጨራሽ ተጋድሎ ያስፀደቅነውን "የአገው ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት" አጀንዳን በብቃት፣ በቁርጠኝነት፣ በፅናት እና በአገዋዊ ፍቅር በታጀበ ጠንካራ ክትትል ተፈፃሚ ማስደረግ ይሆናል።
ሌላው የ2019 ዓ/ም የቤት ስራችን ዘርፈ ብዙ ከሆኑ የአገው ህዝብን ህልውና ከሚፈታተኑ የህልውና ጥያቄዎቻችን ውስጥ የተለዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት፣ እውነተኛ ዴሞክራሲን ማስፈን፣ ለህዝባችን ፍትህ ማጎናፀፍ፣ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በዘላቂነት ማስከበር፣ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እና የማህበራዊ ፍትህ ጥማቶች በጠንካራ አገዋዊ ትግላችን መልስ የሚያገኙበት ዓመት እንደሚሆን ድርጅታችን ፍትህ ከምን ጊዜውም በላይ ታግሎ የሚያታግል ይሆናል።
በመጨረሻ መላው የአገው ህዝብ ጉልበት ያለው በጉልበት፤ ሃሳብ ያለው በሃሳብ፤ ዕውቀት ያለው በዕውቀት፤ ገንዘብ ያለው በገንዘብ ከአገው ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ጎን በመሠለፍ ትግሉን እንዲደግፍ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
በድጋሜ ድርጅታችን ፍትህ ለመላው የአገው ህዝብና ለኢትዮጵያ ብሔረሰቦች አዲሱ ዓመት የሠላም፣ የደስታ፣የስኬት እና የድል ዘመን እንዲሆንልዎ ይመኛል። መልካም አዲስ ዓመት !!! ፤ መልካም በዓል!!!
==== አገው ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (ፍትህ)====
=========== ጷግሜ 05/13/2018 ዓ/ም======
============= አዲስ አበባ ፤ ኢትዮጵያ=======