04/06/2026
7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የተምሳሌት ጉዞ ማሳያ!
ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ታሪኳ ውስጥ አዲስና ብሩህ ምዕራፍ የከፈተችበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው። ይህ ምርጫ ተራ የድምፅ መስጠት ሂደት ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በነፃነት፣ በሰላምና በብስለት የራሱን ዕድል በራሱ መወሰን እንደሚችል ለዓለም ያስመሰከረበት ታላቅ ሁነት ነው።
ምርጫው ኢትዮጵያ ማንኛውንም የውስጥ እና የውጭ ፈተናዎች እየተሻገረች ወደ ከፍታ የምታደርገው ግስጋሴ ለአፍታም እንደማይገታ ዳግም ያረጋገጠችበት ሲሆን፤ ለሀገራችን ሉዓላዊነት ተጠብቆ መዝለቅ የተጣሉ ፅኑ መሰረቶችን ጥንካሬም ማሳየት ችሏል፡፡
ይህ ታሪካዊ ምርጫ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድና በአጠቃላይ በአህጉሩ የእውነተኛ ዴሞክራሲ ተምሳሌት ለመሆን የምታደርገውን ጉዞ በተግባር ያበሰረ ነው። የምርጫው ሂደት በሰላማዊ መንገድ መከናወኑ፣ የዜጎች በነፃነት የመሳተፍ መብት መረጋገጡ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰለጠነ እና ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ሃሳባቸውን የሚያቀርቡበት አውድ መፈጠሩ የፖለቲካ ባህል ግንባታ ጉዞአችንን ከፍ አድርጎታል።
ኢትዮጵያውያን የሀሳብ ልዩነቶቻቸውን በግጭት እና በጦርነት ሳይሆን በንግግር፣ በውይይትና በህዝባዊ ውሳኔ መፍታት የሚችሉባቸው እሴቶች እንዳሏቸው ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳየት በኩልም 7 ኛው ሀገራዊ ምርጫ ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡
03/06/2026
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ በመጠናቀቁ እንኳን ደስ አለን - የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ በመጠናቀቁ የተሰማውን ደስታ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ገልጿል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፀጥታ ኃይል አካላት እንዲሁም ሕዝቡ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሙሉ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ለተወጡት ሀገራዊ ኃላፊነት እና ላሳዩት ፅናትም ምክር ቤቱ ያለውን ምስጋና እና አድናቆት ገልጿል።
ምክር ቤቱ በመግለጫው፣ “ልዩነቶቻችንን እና ችግሮቻችንን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመፈታት በምርጫው የታየውን ሰላም በማስቀጠል የበኩላችንን ሚና እንወጣ፤ ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም በጋራ እንቁም” ሲል ጥሪውን አቅርቧል።
03/06/2026
በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለማጎልበት የተሠሩ ሥራዎች አበረታች ናቸው - የአፍሪካ ኅብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን
የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ እና የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የቡድኑን የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመጀመሪያ ግምገማ ውጤትን በተመለከተ መግለጫ በሰጡበት ውቅት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ዴሞክራሲን ለማጎልበት የሠራውን ሥራ እንደሚያደንቁ ገልጸዋል።
አጠቃላይ የምርጫው ሂደትም የኢትዮጵያን እና የዓለም አቀፍ ሕጎች ማዕቀፍን በተከተለ መልኩ መካሄዱን በግምገማው ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል።
ከቅድመ ምርጫው ጀምሮ የነበረው ሂደት አበረታች እንደነበር የገለጹት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የአፍሪካ ኅብረት ከምርጫው ዋዜማ አንሥቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ ውይይቶችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
የመራጮች ትምህርት አሰጣጥ በተመለከተም ሕዝቡ እንዴት መምረጥ እንዳለበት ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲያገኝ መደረጉን እና በምርጫው ዕለት የነበረው የተቀናጀ መናበብ ለመራጮች ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን አስረድተዋል።
በምርጫው ሂደት ጥቅም ላይ የዋለው ቴክኖሎጂ በተለይም ለወጣቶች የፈጠረው ዕድል ከፍተኛ መሆኑን የታዛቢ ቡድኑ መሪ በመግለጫቸው አብራርተዋል።
የድምፅ መስጫ ሰዓት መራዘሙ ለመራጮች ተጨማሪ ዕድል መፍጠሩን፣ እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች እና ለአረጋውያን በድምፅ አሰጣጡ ሂደት ቅድሚያ መሰጠቱ የዜጎችን ተሳትፎ በእጅጉ ማነቃቃቱንም ጠቁመዋል።
በመላው ኢትዮጵያ የምርጫ አስፈፃሚዎች እና የፀጥታ አካላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በጥሩ ሁኔታ መወጣታቸውን፣ የመገናኛ ብዙኃንም በተመሳሳይ በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት ሥራቸውን ማከናወናቸውን አድንቀዋል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ በምርጫው ያሳየው ተሳትፎ እና ትልቁን ኃላፊነቱን በጀግንነት መወጣቱ እጅግ የሚያስመሰግን መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ኡሁሩ ኬንያታ አስታውቀዋል።
03/06/2026
የአውሮፓ ኅብረትና አጋር ሀገራት የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ሒደት አደነቁ
የአውሮፓ ኅብረት እና አጋር ሀገራት ግንቦት 24/2018 ዓ.ም የተካሄደውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አድንቋል፡፡
ምርጫውን አስመልክቶ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ የኅብረቱ አባል ሀገራትና በኢትዮጵያ የካናዳ፣ የኖርዌይ እና ስዊዘርላንድ ኤምባሲዎች የጋራ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
ሀገራቱ በመግለጫቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እጩዎችና የሲቪል ተቋማት ጠቅላላ ምርጫው በስኬት እንዲካሄድ ያደረጉትን አስተዋጽኦ አድንቀዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በምርጫው ላይ ለነበራቸው የታዛቢነት ሚና እውቅና እንደሚሰጡም ሀገራቱ አረጋግጠዋል፡፡
02/06/2026
7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት ዳግም አረጋግጧል!
ህዝባችን በነቂስ ወጥቶ ድምጹን በመስጠት የሀገራችንን የዲሞክራሲ ጉዞ ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሯል። ይህ ምርጫ የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ የህዝብ ነፃ ፍላጎትና ውሳኔ ብቻ መሆኑን በተግባር የታየበት ደማቅ የታሪክ አጋጣሚ ነው።
የኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወሰነው በህዝቦቿ ድምፅ መሆኑን በግልጽ አስመስክሯል። የ7ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሂደትም ተቋማትን በማጠናከርና የሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ባህልን በማሳደግ ረገድ ትልቅ እመርታ የታየበት ነው።
የሀገራችንን ሰላም፣ ልማትና አንድነት የምናረጋግጠው በጋራ በመቆምና የህዝባችንን የሉዓላዊነት ድምፅ በማክበር ነው!
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት
02/06/2026
ኢትዮጵያ መርጣለች ፤ አሸንፋለች!
ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተደመረ የመራጮች ድምፅ በየምርጫ ጣቢያዎች መለጠፍ መጀመሩን ተከትሎ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ውጤቱን እየተመለከቱ ይገኛሉ።
7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ በድምጹ የሚመራውን ሕጋዊ መንግሥት ለማቋቋም ያለው ጉጉት እጅግ በጣም የላቀ መሆኑን ትልቅ አስረጅ ሆኖ በፖለቲካ ታሪካችን ውስጥ ተመዝግቧል።
የፖለቲካ ሀሳብን በሰላማዊ መንገድና በሕዝበ ውሳኔ መዳኘት የሰለጠነ ፖለቲካ ነው።
02/06/2026
ኢትዮጵያ መርጣለች፤ አሸንፋለች!
7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነትን ዳግም በተግባር ያረጋገጠበት ብቻ ሳይሆን፣ ሀገራችን በአፍሪካ ቀንድና በአጠቃላይ በአህጉሪቱ የዴሞክራሲ ተምሳሌት ወደ መሆን የምታደርገውን ታሪካዊ ሽግግር በይፋ ያበሰረ ታላቅ ሁነት ነው።
ምርጫው ዜጎች በነፃነትና በሰላማዊ መንገድ ሉዓላዊ መብታቸውን ያረጋገጡበት፣ የሀሳብ ልዩነቶች በጠረጴዛ ዙሪያና በድምፅ መስጫ ሳጥን ምላሽ እንደሚያገኙ የተረጋገጠበት ነው፡፡
ውጤቱ ምንም ይሁን ምን፣ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሀዊና ተዓማኒ ሆኖ መጠናቀቁ ለሀገራችን የዴሞክራሲ ጉዞ ትልቅ እርምጃ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህ ሂደት የመንግሥት ሥልጣን ምንጭና መሠረት የሕዝብ ነፃ ፍላጎትና ቀጥተኛ ተሳትፎ ብቻ መሆኑን ለዓለም ያስመሰከረ ከመሆኑም በላይ፣ የሀገራችንን የዴሞክራሲ ተቋማት ተቋማዊ ጥንካሬ ያረጋገጠ እውነታ ነው።
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት
01/06/2026
የመራጩ ህዝብ ሌሊት በነቂስ ወጥቶ መምረጥ በአገሩ ጉዳይ ላይ ያለዉን የእኔነት ስሜት የሚገልጽ ነው - ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
የመራጩ ህዝብ በለሊት በነቂስ ወጥቶ መምረጥ በአገሩ ጉዳይ ላይ ያለዉን የእኔነት ስሜት የሚገልጽ መሆኑን ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገለጹ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማሕበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በምርጫ ክልል 28 በዛጎል ትምህርት ቤት አካባቢ የምርጫ ጣቢያ ተገኝቸዉ ድምጽ ሰጥተዋል።
ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በዚሁ ወቅት እንደገለጹት መራጩ ህዝብ ከለሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ተሰልፎ እና ወረፋ ጠብቆ በመምረጥ ለምርጫዉ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት አሳይቷል።
የመራጩ ህዝብ በለሊት በነቂስ ወጥቶ መምረጥ በአገሩ ጉዳይ ላይ ያለውን የእኔነት ስሜት የሚገልጽ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ህዝቡ ለመምረጥ የማንም ቅስቀሳ እንደማያስፈልገው ያሳየ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ምርጫ አገር የምናስቀጥልበት የምናጸናበት እንዲሁም ዲሞክራሲ የምንለማመድበት ነው ያሉት ሙዓዘ ጥበባት ዳንኤል፣ ለአገር ዋጋ የሚከፍለው እና የማይከፍለው የሚለይበትም ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል።
01/06/2026
ኢትዮጵያ እየመረጠች ነው!
ለፈተናዎች የማትንበረከከው፣ አይበገሬነቷን ያፀናችው ኢትዮጵያ ዛሬም እንደ ትናንቱ ከሩቅም ከቅርብም የተደቀኑባትን ተግዳሮቶች እየተሻገረች ዴሞክራሲያዊ ባህልን መገንባት እንደምትችል በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ተግባራዊ ምላሽ ሰጥታለች፡፡
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት