12/04/2026
በመዲናችን አዲስ አበባ እውን እየሆኑ ባሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች 24/7 ያለእረፍት የበዓልን ቀን ጭምር በስራ ላይ ካሉ የአቃቂ ኢንዱስትሪ ክለሳተር ባለሙያዎች እና ሠራተኞች ጋር በመሆን ማዕድ በመቋደስ የትንሳዔ በዓልን አብረን አክብረናል።
መስራት ያስከብራል ድህነት ያዋርዳል ፣ በዓላችን ሙሉ የሚሆነው ሰርተን ስንበለፅግ ነው ብላችሁ ቀን ከሌሊት ሳትሉ ዛሬም ስራ ላይ የምታሳልፉ ሁሉ እንኳን አደረሳችሁ ማለት እወዳለሁ።
በዓሉን በጋራ ሆነን ማዕድ ስንቋደስ ለህዝባችሁ እንዲሁም ለከተማችሁ እድገት የምታደርጉትን አስተዋፅኦ እንዲሁም ድካማችሁ እውቅና እንዲሆንና በርቱ ለማለት ነው ።
መልካም የትንሳዔ በዓል
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦችዋን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
12/04/2026
“በበዓላት ወቅት ድጋፍ ከሚያሻቸው ወገኖቻችን ጋር አብሮ ማሳለፍ ሰው ተኮርና የህሊና እርካታ የሚያጎናፅፍ ተግባር ነው!”
አቶ ሞገስ ባልቻ
የአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ
የአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ የተከበሩ አቶ ሞገስ ባልቻን ጨምሮ የኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሌሊሴ ነሜ፣ የአዲስ አበባ የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ጥላሁን፣ የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍፁም ኃይሌ፣ የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍፁም ኃይሌ እንዲሁም የከተማ፣ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች ተገኝተው መርሃ ግብሩን በደመቀ ሁኔታ አከናውነዋል።
በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 በሚገኘው 14ኛው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል በመገኘት ለአቅመ ደካማ ነዋሪዎች የትንሳኤ በዓልን አስመልክቶ የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ያካሃዱት
የአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ የተከበሩ አቶ ሞገስ ባልቻ እንደገለፁት ኢትዮጵያ የብዙ ሀይማኖቶች ታሪክና ባህል ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው ሁሌም በበዓላት ወቅት ድጋፍ ከሚያሻቸው ወገኖቻችን ጋር አብሮ ማሳፍ ሰው ተኮርና የህሊና እርካታ የሚያጎናፅፍ ተግባር ነው ብለዋል።
አቶ ሞገስ አክለውም እንደዚህ ያሉ መርሃ ግብሮች በከተማ ደረጃ ከ26 በላይ በሆኑ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት በመገንባት በቀን አንድ ጊዜ መመገብ ለማይችሉ ወገኖች መመገብ መቻሉን ጠቅሰው በበዓል ወቅት ከአቅመ ደካማ ዜጎች ጋር መሆን የማህበራዊ አብሮነትን የሚያጠናክር መሆኑንና የመደጋገፍ ባህልን በቀጣይነት ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍፁም ኃይሌ በበኩላቸው በዓላትን ከአቅመ ደካማ ዜጎች ጋር በመካፈል ማክበር የሰብአዊነትና የብልፅግና እሴቶችን የሚያንጸባርቅ መሆኑንና አስተዳደሩ ማህበራዊ አብሮነትን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።
መርሃ ግብሩ ዋና ዓላማ በበዓል ወቅት ደስታን አብሮ መጋራትና ማህበራዊ አብሮነትን ማጠናከር ሲሆን ተሳታፊዎችም ከፍተኛ የደስታ ስሜት እንዳሳዩ ተገልጿል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሌሊሴ ነሜ፣ የአዲስ አበባ የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ጥላሁን፣ እንዲሁም የከተማ፣ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች ተገኝተው መርሃ ግብሩን በደመቀ ሁኔታ አከናውነዋል።
12/04/2026
እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበረውን የትንሳኤ በዓል በማስመልከት፣ የየካ ክፍለ ከተማ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለመላው የእምነቱ ተከታዮች መልካም ምኞቱን ይገልጻል።
የትንሳኤ በዓል የድል፣ የሰላም፣ የፍቅር እና የይቅርታ በዓል ነው፣ይህን ታላቅ በዓል ስናከብር ካለን ላይ ለሌላቸው በማካፈል፣ የታመሙትን በመጠየቅ እና አቅመ ደካሞችን በመርዳት ሊሆን ይገባል።
በበዓሉ ወቅት ልናስታውሳቸው የሚገቡ እሴቶች፡
አብሮነት፡፣መረዳዳት፡ ሰላም፣ለሀገራችን ሰላም እና ብልፅግና በጋራ መቆምን ነው።በዓሉ የሰላም፣ የጤና እና የደስታ እንዲሆንላችሁ ከልብ እንመኛለን።
መልካም የትንሳኤ በዓል!
በብልፅግና ፓርቲ የየካ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት
11/04/2026
እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው በሠላም በደስታ አደረሳችሁ !
ጌታችንና መድዓኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፍፁም ትህትና ፣ በፍፁም ፍቅር የሰው ልጆችን መከራ እሱ ተቀብሎ ፣ በሞቱ ሞትን ድል አድርጎ ከሞት ወደ ህይወት አሸጋግሮናል።
ትህትናን እና ፍቅርን ገንዘባችን ካደረግን ከችግሮች አሻግረን ከተመለከትን ከፊታችን ብሩህ ተስፋ እንደሚጠብቀን ከትንሳኤው እንረዳለን።
በትንሣኤው በዓል ከፈጣሪያችን የተማርነው ትህትናንና ፍቅርን በመሆኑ እኛ በዓሉን ስናከብር ያለንን አካፍለን ከሁሉም ወገኖቻችን ጋር በአብሮነትና በፍቅር ልናከብር ይገባል።
መልካም የትንሳኤ በዓል ለሁንላችንም!
11/04/2026
የከንቲባ አዳነች አቤቤ የትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት...!!
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ፤ እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
የትንሣኤ በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ መዳን ያለውን ፍቅር እስከ መስቀል ሞት የገለጸበትና የሞት ድል የተበሰረበት ታላቅ ዕለት ነው። በመሆኑም በዓሉን ስናከብር በታላቅ ፍቅር፣ በትሕትና እና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባል።
ድጋፍ ለሚሹ ወገኖቻችን ያለንን አጋርነት በተግባር የምንገልጽበት፣ አንዳችን ለሌላችን የደስታ፣ የሰላም እና የአብሮነት ምክንያት የምንሆንበት በዓል እንዲሆንልን እመኛለሁ።
መልካም በዓል!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
11/04/2026
ብልፅግና በተግባር!
የብልፅግና ፓርቲ ዋነኛ መገለጫ የሆነውን ሰው ተኮር ተግባር በተግባር ለማዋልና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት፣ የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በየካ ክፍለ ከተማ የታደሱ ቤቶች ለባለቤቶቹ ተላለፉ።
በቤት ምርቃትመርሃ ግብሩ ላይ አቶ ጃንጥራር አባይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ፣አቶ ፍፁም ኃይሌ የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ፣አቶ መገርሣ ገላና የየካ ክፍለ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ቅ/ፅ/ቤት ኃላፊ ተገኝተዋል።
በዕለቱ በነበረው መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ የቤት እድሳቱ ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች እንዲተላለፍ ያደረጉ ሲሆን ይህ ተግባር በከተማዋ የሚገኙ አቅመ ደካሞችንና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ከታቀዱት ዘርፈ ብዙ የሰው ተኮር ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ጃንጥራር አባይ በንግግራቸው እንደገለጹት፣ ቤቶቹ የታደሱት የትንሣኤን በዓል ምክንያት በማድረግ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹ በዓሉን በታደሰና ለኑሮ ምቹ በሆነ ቤት ውስጥ እንዲያሳልፉ ታስቦ የተከናወነና የብልፅግና ጉዟችን ዋና ዓላማ ሰው በመሆኑ፤ ሰውን ማዕከል ያደረገ ልማት ደግሞ ዜጎች የሚገባቸውን ክብርና ማረፊያ እንዲያገኙ ማድረግን ይጨምራል በለዋል።"
የክፍለ አተማው ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፍፁም ኃይሌ እንደገለፁት መንግስት ከሚሠራቸው በርካታ ሰው ተኮር ተግባራቶች ውስጥ አንዱ በሆነው የቤት እድሳት መርሃግብር በተያዘው በጀት አመት 8 ወራት ውስጥ ለመኖር የማይመቹና የፈራረሱ ከ500 በላይ የአረጋውያንን ቤቶችን አድሰው ያስረከቡ መሆናቸውን ገልፀው ዘወትር ከመንግስት ጎን ሆነው እገዛ የሚያደርጉ ልበቀና ባለሐብቶችን አመስግነዋል።
ቤቶቻቸውን የተረከቡት እናቶችና አባቶች በሰጡት አስተያየት፣ ቀደም ሲል ቤቶቻቸው በዝናብና በፀሐይ ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶት በመታደሱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸውና ለበዓሉ ትልቅ ስጦታ እንደሆነላቸው ገልጸዋል።
11/04/2026
በየካ ክፍለ ከተማ የትንሳኤ በዓል ግብይት በከፍተኛ ግርግር እና ድምቀት እየተከናወነ ይገኛል። በተመጣጣኝ ዋጋ ፣ የህብረተሰቡ የመግዛት አቅም እንደየደረጃው ገበያውን ሲያሞቀው ይታያል። ሸማቾች ግብይታቸውን ሲያከናውኑ ዋጋ በማነፃፀር እና በህጋዊ የገበያ ማዕከላት እንዲጠቀሙ ይመከራል።
መልካም የትንሳኤ በዓል!
11/04/2026
እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን!
የትንሣኤ በዓል በክርስቲያኖች ዘንድ ልዩ ቦታ ያለው በዓል ነው። ሞት የተሻረበትና ሕይወት ዋስትና ያገኘበት ነው። ከሞት ባሻገር ሕይወት፣ ከመቃብር ባሻገር ትንሣኤ መኖሩ የታወጀበት ነው። ሞት መጨረሻ መቃብር መዳረሻ አለመሆናቸው የተረጋገጠበት ነው። በአዳም ምክንያት ወደ ምድር የወረደው ሰው፣ በክርስቶስ ምክንያት ወደላይ የወጣበት ነው።
የዘንድሮውን ትንሣኤ የምናከብረው ሀገራችን ኢትዮጵያ በሚያልፍ ፈተና ውስጥ እንዳለች እያሰብን ነው። መንገዳችን ረጅም፣ ጉዟችን ፈታኝ መሆኑን እናውቃለን። ብርሃን እንዳናይ የሚጋርዱ፣ በጥልቁ ጨለማ ጠፍተን እንድንቀር አሥረው ለመያዝ የሚሞክሩ ወጥመዶች ብዙ ናቸው። ወደ ተስፋ ምድር እንዳንሻገር የሚጎትቱ ሰበቦች ሞልተዋል። ዳሩ ግን ከሕማማቱ ወዲያ ትንሣኤ፣ ከዕንቅፋቱ ባሻገር ስኬት እንደሚጠብቀን አምነን እንታገላለን።
በትንሣኤው ዋዜማ - ርግጠኞች፣ ተስፈኞች፣ ተስፋ ቆራጮች፣ ወሬኞች፣ ተስፋ አስቆራጮች፣ ተጠራጣሪዎች ነበሩ። ርግጠኞቹ የሕማማቱ ፈተና እንደሚያልፍ ርግጠኞች ነበሩ። የዕለተ ስቅለት መከራ፣ለዕለተ ትንሣኤ ዋዜማ ለመሆኑ ርግጠኞች ነበሩ። የድንጋዩ በር፣ የበሩ ማኅተም እና የመቃብሩ ጠባቂዎች ትንሣኤውን እንደማያስቀሩት ርግጠኞች ነበሩ። የሚናፈሰው ወሬ እና የሚሠራጨው አሉባልታ እድሜው አጭር መሆኑን ርግጠኞች ነበሩ። ርግጠኞችም ስለሆኑ መሥዋዕትነትን ለመክፈል ዝግጁዎች ነበሩ። እውነቱን ለመመስከር ቆራጦች ነበሩ። በመስቀሉ ሥር ለመገኘት ደፋሮች ነበሩ።
ተስፈኞቹ የርግጠኞቹን ያህል ሳያዩ የሚያምኑ አልነበሩም። ግን አንዳች መልካም ነገር ይጠብቁ ነበር። የተሰጠውን ትምህርት፣ የተደረገውን ተአምራት ሰምተዋል፤ አይተዋል፤ አንዳች ነገርም ጠብቀዋል። ነገር ግን ተገቢውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁዎች አልነበሩም። እውነትን ለመድፈር ቆራጦች አልነበሩም። ሐሰቱን ለመጋፈጥ ዐቅም አላገኙም። ቢያንስ ግን አንደበታቸውን ከክፉ ከልክለዋል።
ተጠራጣሪዎች አጥር ላይ የነበሩ ናቸው። በጥብርያዶስ ይበላሉ፣ በጎልጎታ ይክዳሉ። በሆሳዕና ይዘምራሉ፣ በሊቶስጥራ ይሸሻሉ፡፡ ተአምር ለማየት ይመጣሉ፣መከራ ለማየት ይሳቀቃሉ፡፡ ከደስታው አውጡልኝ፣ ከመከራው ጦመኛ ነኝ የሚሉ ናቸው።
ተስፋ ቆራጮች በሚያዩትና በሚሰሙት ቶሎ የሚወሰዱ ናቸው። በእውነትና በሐሰት፣ በፍርሃትና በጽናት መካከል ያለው ድንበር የጠፋባቸው ናቸው። ሕማማቱ ሲመጣ በቶሎ ወደ ትዝታ ገቡ። ሁሉንም ነገር የትናንት ታሪክ ብቻ አድርገው ወሰዱት። ሁሉንም ነገር “ልጡ የተራሰ፣ መቃብሩ የተማሰ” አድርገው ቆጠሩት። ከግራ ከቀኝ የሚሰሙት አሉባልታ፣ ከፊት ከኋላ የሚመጣው ጫጫታ፤ ከወዲህ ከወዲያ የሚማጣው እሳት፣ ከዚህም ከዚያም የሚያዩት መዓት አስፈራቸው። ነገን አስረሳቸው። በዚህ የተነሣ ተስፋ ቆርጠው ወደ ኋላ ተመለሱ።
ወሬኞች ድሮም ወሬ ስቧቸው የመጡ ናቸው። ምን አለ ምን ተባለ ብለው የተሰባሰቡ ናቸው። የሰሙትንም ያልሰሙትንም፤ የሚያውቁትንም የማያውቁትንም፤ እውነቱንም ሐሰቱንም እያደባለቁ ኢየሩሳሌምን በወሬ ሞሏት። ቢያንስ ከትንሣኤው 15 ዓመት በኋላ ወንጌሉን የጻፈው ማቴዎስ፣ እስከዚያ ዘመን ድረስ ወሬው ብዙ ተቀባይ እንደነበረው ገልጧል።
ተስፋ አስቆራጮች ዓላማቸው ሰውን ሁሉ ከትንሣኤ መንገድ ማራቅ ነበር። እነርሱም አይሄዱ፣ ሰውም አያስኬዱ። ከመጀመሪያው አልተቀበሉትም፤ በኋላም አልፈለጉትም። ብዙ ሰዎች እንደተከተሉት ሲያውቁ ደግሞ ቅናት አቃጠላቸው፤ ክፋት አንገበገባቸው። ክርስቶስን ከሰሱ፤ ራሳቸው ምስክር ሆኑ፤ በመጨረሻም ራሳቸው ፈረዱ። መቃብሩን ዘጉ፤ ጠባቂ አስቀመጡ። በማኅተም አሸጉ። ነገር፣ ያለቀና የተቆረጠ መሰላቸው።
የትንሣኤ በዓል የእነዚህን ሁሉ እውነተኛ ማንነት የገለጠ ነው። ርግጠኞች የቆራጥነታቸው ውጤት በትንሣኤ አገኙ። ተስፈኞች እንዲህ ለሚያልፍ ጊዜ ባለመጽናታቸው አዘኑ። ተስፋ ቆራጮች አሻግሮ ማየት አቅቷቸው ከቦታቸው በመጥፋታቸው ተፀፀቱ። ወሬኞች በትንሣኤው እውነት የተነሣ ያ ሁሉ ወሬ እንደ ናቡከደነፆር ሐውልት ሲፈረካከስ አዩት። ተስፋ አስቆራጮች የገደሉት ክርስቶስ ሲነሣ፣ የዘጉት መቃብር ሲከፈት፣ ያተሙት ማኅተም ሲቀደድ፣ የመደቧቸው ጠባቂዎች ሲሸሹ በዓይናቸው በብረቱ አዩ። ትንሣኤው የሚነገር ሐቅ፣ የሚታይ እውነት ሆነ። ተጠራጣሪዎች ግን አሁንም አጥራቸው ላይ ሆነው ከግራም ከቀኝም ሳይሆኑ ቀሩ።
የኢትዮጵያችንም ነገር እንዲሁ ነው። በኢትዮጵያ ለውጥ ርግጠኞች የሆኑት ዋጋ ይከፍላሉ፤ ርግጠኝነትን ፈርተው ተስፈኞች የሆኑት ቢያንስ አንደበታቸውን ከክፉ ይጠብቃሉ፡፡ ተስፋ ቆራጮች ነገን ማየት ስለሚሳናቸው መንገዳቸውን ይቀይራሉ፡፡ ወሬኞች አውርቶ አዳሪዎች በመሆናቸው የወሬ እንጀራ ይጋግራሉ። ተስፋ አስቆራጮች “ወተቱን አጥቁረው፣ ማሩን አምርረው” የዋሖችን አታለሏቸው፡፡ ተጠራጣሪዎች አንዴ ትኩስ አንዴ ቀዝቃዛ ሲሆኑ፣ ለብ ብለው ቀሩ።
ኢትዮጵያችን ግን ትንሣኤዋን እያየች ነው። መግነዙን ፈትታዋለች፣ መቃብሩን ከፍታዋለች፤ ማኅተሙን ቀዳዋለች። ወሬኞች ከመቃብር ጠባቂዎች ጋር ተማክረው የሚያወሩትን ወሬ የምትሰማበት ጆሮ የላትም። ትንሣኤዋን አይለውጠውምና። እሷ ከዚህ በኋላ የምትጠብቀው ዕርገትን ነው። የምትጓዘው ኃይል እንደሚወርድላት አረጋግጣ ነው። ወደኋላ መመለስ የለም። ሕማማት አልፏል፤ዓርብም አልፏል፤ ቅዳሜም አልፏል። ትንሣኤ መጥቷል። በትንሣኤ ሌሊት የተኙ አልሰሙ ይሆናል። በተስፋ አስቆራጮች ተታለው የሄዱ ዜናው አልደረሳቸው ይሆናል። ትንሣኤ ግን እውን ሆኗል።
ከቻላችሁ አጥር ላይ ያላችሁ ውረዱ። ተስፈኞች ርግጠኞች ሁኑ። ተጠራጣሪዎች እመኑ። ወሬኞች ከአፍ ወደ መዳፍ ተለወጡ። ምክንያቱም - ኢትዮጵያ ወደ ትንሣኤ ተቃርባለች።
የኢትዮጵያ ትንሣኤ ከሚበሰርባቸው ምዕራፎች አንዱ ግንቦት ላይ የሚካሄደው ምርጫ ነው። ትንሣኤን ያለ ሕማማት እንደማናስበው ሁሉ ዴሞክራሲንም ከውጣ ውረድ ነጥሎ ማየት አይቻልም። በዓለም ላይ በደልዳላ መንገድ ተጉዞ ዴሞክራሲን የገነባ ሀገር የለም። ዴሞክራሲና ብልጽግና ያለ ጽናት አይሳኩም። ከእኛ በፊት ዐመጻውን በትዕግሥት የመከቱ ተሻግረዋል፤ ሑካታውን በጽናት ያለፉ አሳክተዋል። ብንመኝም ፈተናውን አናስቀርም፤ መጽናት ግን እንችላለን። ከድህነት መውጫው ብርታታችን፣ ወደ ዴሞክራሲ መድረሻችው ትዕግሥታችን እንደሆነ አምነን ለኢትዮጵያ ትንሣኤ በሙሉ ልባችን እንትጋ!!
በድጋሚ መልካም የትንሣኤ በዓል ይሁንልን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ሚያዝያ 03 ቀን 2018 ዓ.ም
፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ
11/04/2026
“የሰንበት ገበያዎች በቅርበት በማግኘታችን ድካም ቀንሶልናል፤ ገንዘባችንም ጊዜአችንም ቆጥቦልናል”
ነዋሪዎች!
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ የሰንበት ገበያዎች በተከተማዋ በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ነዋሪው ባለበት መንደሮች ሁሉ፣ በቅርበት በመኖራቸው፣ ፍጆታዎችን ለመሸመት ይባክን የነበረውን ጊዜና ጉልበት ቀንሶልናል ሲሉ ምስክርነታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
በተለይም እነዚህ ገበያዎች በአቅራቢያቸው በማግኘታቸው የተለያዩ ምርቶችን ከአንድ ቦታ ሸምቶ ለመሄድ አስችሎልናል፣ ድካም ቀንሶልናል፣ የትራንስፖርት ወጪ አስቀርቶልናል፣ ከምንም በላይ ጥራት ያለው ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንድናገኝ አስችሎናል ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
መንግስትም ለኑሮ ውድነት መባባስ መንስኤ የሆኑትን የምርት አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ ፣ የፍጆታ እና የሰብል ምርቶች በቀጥታ ከአርሶ አደሮች እና ከባለሀብቶች ጋር በማስተሳሰር ምርት በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ከተማ እንዲገባ በማድረግ ሸማቹ ማህበረሰብ ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡
በዚህ ውጤታማ ስራ ለዋጋ ንረትና ለንግድ ሚዛን መዛባት ምክንያት የሆኑ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች እና ደላሎች ላይ ህጋዊ እርምጃዎችን በመውሰድ በገበያው ላይ ይታይ የነበረውን የዋጋ ንረት ማረጋጋት ተችሏል፡፡