19/11/2022
ማዕከሉ ከአፋር የማዕድን ልማት አክሲዮን ማህበር ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ
***************************************************************
የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ከአፋር የማዕድን ልማት አክሲዮን ማህበር ጋር በክሎርአልካሊ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ፡፡
በክሎርአልካሊ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ላይ ቴክኒካል እና ቅድመ የአዋጭነት ጥናት ማካሄድ ለስራው አስፈላጊ የሰው ሀይል መመደብ፣ ወቅታዊ ሪፖርት አዘጋጅቶ መላክ፣ ከተቋማት የተሻለ ተሞክሮ መቀመርና የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ስራ መስራት ለማዕከሉ ተሰጡ የስራ ሀላፊነቶች ሲሆኑ አስተዳደራዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ፣ ለፕሮጀክቱ ስራ ጥበቃና አማካሪዎችን መመደብና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ደግሞ በአክሲዮን ማህበሩ በኩል የሚተገበሩ እንደሆኑ በስምምነቱ ላይ ተመላክተዋል፡፡
06/11/2022
በማዕከሉ የዘርፉን ኢንዱስትሪ ችግር መፍታት የሚችሉ 17 የጥናትና ምርምር ፕሮፖዛሎች ተገምግመው 15ቱ ወደ ተግባር መግባት የሚያስችላቸውን ውጤት አገኙ!
*****************************************************
የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በዘርፉ የተሰሩ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ወደ ተግባር ለማስገባት በስሩ ከሚገኙ የምርምር ማዕከላት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የዘርፍ ማህበራት ጋር የግምገማና የውይይት መድረክ ከጥቅምት 25 እስከ 26/2015 ዓ.ም በአዳማ ከተማ አካሄዷል፡፡
በውይይት መድረኩ ከ6ቱም የምርምር ማዕከላት 78 የጥናትና ምርምር ፕሮፖዛሎች ቀርበው ውይይትና ግምገማ ተካሂዶባቸዋል፡፡
የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል 7 የምርምር ፕሮፖዛሎች በዩኒቨርሲቲ መምህራን 10 የምርምር ፕሮፖዛሎች ደግሞ በማዕከሉ ተመራማሪዎች በድምሩ 17 የጥናትና ምርምር ፕሮፖዛሎች ቀርበው በዩኒቨርሲቲ መምህራንና በውስጥ ፈታኞች ተገምግመው 15ቱ ወደ ቀጣዩ የትግበራ ምዕራፍ መግባት የሚያስችላቸውን ውጤት አግኝተዋል፡፡
የዘርፉን ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማድረግ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት፤ የጂዲፒ ድርሻና የውጭ ምንዛሬ ማሳደግ እንዲሁም ምርት ማምረትና በሀገር ውስጥ መተካትና ተጨማሪ የስራ ዕድል መፍጠር የዘርፉ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሆኑ በስራ ሀላፊዎች ተገልጸዋል፡፡
17/10/2022
የማዕከሉ አመራሮችና ሰራተኞች15ኛውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን አከበሩ!
**********************************************
የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ሰራተኞችና አመራሮች 15ኛውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን የብዝሃነታችን መገለጫ የሉዓላዊነታችን ምሰሶ ነው!” በሚል መሪ ቃል በልየ ልዩ ፕሮግራም አከበሩ፡፡
የማዕከሉ ዋና ስራ አስኪያጂ አቶ ሀብታሙ አራጌ ቀኑን ስናከብር ለሀገር ክብርና ጥቅም ሁላችንም እንደዜጋ የበኩላችንን ለመወጣት በሰንደቅ ዓላማ ፊት ዳግም ቃላችንን የምናድስበት ዕለት እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡
ለሰንደቅ ዓላማ የምንሰጠው ክብር እና ፍቅር ከእናት አባቶቻችን በክብር ወርሰን በክብር ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፈው በልባችን ውስጥ ታትሞ የሚቆይ የብዝኃነታችን፣ የአንድነታችን እና የሉዓላዊነታችን መገለጫ ታላቅ ሀገራዊ እሴት እንደሆነም አቶ ህብታሙ አክለው ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም የማዕከሉ አመራሮችና ሰራተኞች ሰንደቅ ዓለማ በመስቀልና በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ በመፈፀም ስነ-ስርዓት የፕሮግራሙ ፍጻሜ ሆኗል፡፡
23/09/2022
የማዕከሉ አመራሮችና ሰራተኞች የማዕድ ማጋራትና የሽኝት ፕሮግራም አካሄዱ!
********************************************
የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል አመራሮችና ሰራተኞች የማዕድ ማጋራትና የሽኝት ፕሮግራም መስከረም 12/2015 ዓ.ም አካሄደዋል፡፡
በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ የማዕከሉ ዋና ስራ አስኪያጂ አቶ ሃብታሙ አራጌ የዕለቱን ፕሮግራም ያዘጋጁትን የማዕከሉ ሶሻል ኮሜቴ አባላት አመስግነው እንደተቋም ከተከናወኑ የክረምት የበጎ አድራጎት ስራዎች መካከል ለአረጋዊያን ቤት እድሳት ከአራት ሚሊዮን በላይ ድጋፍ እንደተደረገ ገልጸዋል፡፡ ስራ አስኪያጁ አክለውም በአረንጓዴ አሻራ ከ16000 በላይ ችግኞችን በመትከል ከዕቅድ በላይ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም በአካባቢው ላሉ አቅመ ደካሞች የዱቄትና ማካሮኒ ስጦታ በማበርከት ማዕድ የማጋራትና ወደ ተለያየ ተቋም ለተመደቡ ሰራተኞችና አመራሮች የሽኝት ፕሮግራም በማካሄድ የዕለቱ ፕሮግራም ፍጻሜ ሆኗል፡፡
08/09/2022
ማዕከሉ ከዘርፉ አምራቾች ጋር የውይይት መድረክ አካሄደ
*************************************
የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ከዘርፉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በ2014 በጀት ዓመት የዕቅድ ክንውን እና በ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ጳጉሜ 3/ 2014 ዓ.ም በማዕከሉ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት አካሄደ፡፡
የማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሃብታሙ አራጌ በመክፈቻ ንግግራቸው በ2014 በጀት ዓመት ያልተፈቱ የኢንዱስትሪ ችግሮችን መሰረት አድርገን በቀጣይ ትኩረት ሰጥተን ለማሻሻል እንሰራለን ብለዋል፡፡
ዋና ስራ አስኪያጁ አክለውም እንደ ምርምር ማዕከል የጥናትና ምርምር፣ የአቅም ግንባታና የማማከር አገልግሎት ስራዎች የቀጣይ ዕቅድ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡
በውይይቱ የ2014 በጀት ዓመት የዕቅድ ክንውንና የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ በዕቅድና በጀት ክፍል ሀላፊ አቶ ማስተር መርሀዊ ቀርቦ ውይይትና ግምገማ ተካሂዶበታል፡፡ በተጨማሪም የዘርፍ ማህበራት የስራ እንቅስቃሴ በየዘርፍ ማህበራቸው ተወካዮች በኩል የቀረበ ሲሆን በቀጣይ ማህበራቶቻቸውን በማጠናከር የዘርፉን ዕድገት ማረጋገጥ እንዳለባቸው በመድረኩ ተመላክቷል፡፡
በመጨረሻም የኢንዱስትሪ ተወካዮችና ባለቤቶች በቀረበው ሪፖርት እና ዕቅድ ላይ ጥያቄና አስተያየት ያቀረቡ ሲሆን ለተነሱ ጥያቄዎች በማዕከሉ አመራሮች ምላሽ ተሰጥቶባቸው የውይይቱ ፍጻሜ ሆኗል፡፡
01/09/2022
በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሄደ
****************************************
የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል አመራሮች ከሰራተኞች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አካሔዱ፡፡
ውይይቱን የመሩት የማዕከሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ አራጌ አሸባሪው ህውሀት በከፈተው የሰሜኑ ጦርነት በሚነሱ አሉባልታዎች ሳንዘናጋ መደበኛ ስራችን ላይ በማተኮር የተሰጠንን ግዴታ መወጣት እንደሚገባ ገልጸው ማነኛውንም አስተዋጾ ለሀገር፣ ለህዝብና ለመከላከያ ማበርከት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም የጠራ መረጃ በመያዝ አንድነታችንን አጠናክረን ከሀገራችን ጎን በመሰለፍ አስፈላጊውን መስዋትነት ለመክፈል መዘጋጀት እንደሚገባ ከሰራተኞችና አመራሮች ሀሳብና አስተያየቶች ቀርበው ምላሽ ከተሰጠባቸው በኋላ የውይይቱ ፍጻሜ ሆኗል፡፡
25/08/2022
የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ባዮማስን ለሀይል ምንጭነት ለማዋል ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ተገለጸ!
**********************************************************
ነሐሴ 19/2014 ዓ.ም የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ አመራሮች ከኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል አመራሮች ጋር የፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ ባዮማስን ለሃይል ምንጭነት ለማዋል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።
የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ኤግዝኤል ብዙአየሁ የፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ ባዮማስን በ40 ፐርሰንት ለሀይል ግብዓትነት መጠቀም የሚያስችል የፊዲንግ ሲስተም እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
ስራ አስኪያጁ አክለውም የዲዛይን ስራው ተጠናቆ የማሽነሪ ግዥ ሰምምነት ከሀገር ውስጥና ከቻይና ሀገር ኩባንያዎች ጋር እንደተካሄደ ገልጸው በቀጣይ መስከረም ወር አጋማሽ ስራው ተጠናቆ ወደ ትግበራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሃብታሙ አራጌ የፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ ባዮማስ ፕሮጀክት ያለው ጠቀሜታ እንደሀገር ዘርፈ ብዙ እንደሆነ ገልጸው ፋብሪካው ፈጥኖ ወደ ተግባር እንዲገባ አሳስበዋል።
በማዕከሉ የአካባቢ ጥበቃ ሙያ ደህንነትና ኢነርጂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳዊት አለሙ ባዮማስን ለኢነርጂ ምንጭነት መጠቀሙ የውጭ ምንዛሬ ከማዳን በተጨማሪ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ ያለው ድርሻ ትልቅ በመሆኑ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
24/08/2022
የፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ ባዮማስ ፕሮጀክት የትግበራ ሂደትን መገምገም የሚያስችል ጉብኝት ተካሔደ
***************************************************
ከኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብኣቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል፣ ከኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስቴር እና ከአውሮፓ ህብረት የተውጣጣ የልዑካን ቡድን በአፋር ክልል እየተተገበረ የሚገኘውን የፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ ባዮማስ ፕሮጀክት ላይ ጉብኝትና ግምገማ አደረገ።
በማዕከሉ የአካባቢ ጥበቃ፣ ሙያ ደህንነትና ኢነርጂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳዊት አለሙ በጉብኝቱ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት በፕሮጀክት ትግበራው እስከአሁን ከ20 ሄክታር መሬት በላይ የፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ ወራሪ አረም እንደ ተጸዳ ገልጸው የጸዳውን መሬት ለማልማትና የተፈጨውን የወራሪ አረም ባዮማስ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሀይል ምንጭ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
በመጨረሻም በፕሮጀክቱ ትግበራ ላይ የሚያጋጥሙ የፋይናንስና ሎጀስቲክስ ችግሮችን ለመፍታት የልዑካን ቡድኑ ከስምምነት ላይ በመድረስ የጉብኝቱ ፍጻሜ ሆኗል።
የፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ ወራሪ አረም የባዮማስ ፕሮጀክት የማስጀመሪያ ፕሮግራም የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት በተገኙበት ሰኔ 16/2014 ዓ.ም መካሔዱ ይታወሳል።
23/08/2022
የማዕከሉ ሰራተኞችና አመራሮች የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም አካሔዱ
************************************************
የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ሰራተኞችና አመራሮች በኦሮሚያ ክልል አደአ ወረዳ ሂዲ ቀበሌ ልዩ ቦታው ሆራ ኪሎሌ በተባለ ኮረብታማ ስፍራ ነሐሴ 17/2014 ዓ.ም ለአራተኛ ጊዜ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም አካሔዱ፡፡
መረሀግብሩ "በትውልዶች መደጋገፋ ለሁሉም እድሜ ክልል የምትሆን አለም መፋጠር" በሚል መሪ ቃል በአለም ለ23ኛ በሀገራችን ለ18ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአለም ወጣቶች ቀንን በማስመልከት የተዘጋጀ ነው።
የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጂ አቶ ሃብታሙ አራጌ በዕለቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ5000 በላይ ችግኞች እንደተተከሉ ገልጸው በያዝነው የክረምት ወራት የማዕከሉ ሰራተኞች በተለያዩ ቦታዎች ከ16600 በላይ ችግኞችን በመትከል የዕቅዱን 120% በማከናወን ለአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ተጠሪ ከሆኑ ስድስት ማዕከላት ቀዳሚ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ዋና ስራ አስኪያጁ አክለውም እንደ ተቋም በአረንጓዴ አሻራ ያሳካነውን ግብ በምርምር ስራችንም በመድገም አራኣያ መሆን እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
18/08/2022
ነሀሴ 12/2014 የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ማዕከል ሰራተኞችና አመራሮች የደም ልገሳ መርሃ ግብር አከናወኑ።
16/08/2022
የማዕከሉ ሰራተኞችና አመራሮች የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር አከናወኑ።
**********************
የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ማዕከል ሰራተኞችና አመራሮች ከፈርኒቸር አምራቾች ዘርፍ ማህበራት ጋር በመሆን እንጦጦ ፓርክ በመገኘት የችግኝ ተከላ መርሃግብር አከናውነዋል።
የማዕከሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ አራጌ መረሀ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት ሀገራዊ ጥሪውን በመከተል ችግኝ መትከላችን ከፋተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልፀው በቀጣይ ከዚህ ቀደም በተከልንባቸው ቦታወችም ሆነ በዛሬው ችግኞቹ የደረሱበትን እየተከታተልን የምንከባከብ ይሆናል ብለዋል።