Yeka Woreda 09 Prosperity Party ብልጽግና

Yeka Woreda 09 Prosperity Party ብልጽግና

Share

This page is yeka woreda-09 prosperity party media and communication official face book page

06/06/2026
06/06/2026

ኢትዮጵያ መርጣለች፤ የነገውን ትውልድ አሻራ ዛሬ እያኖረች!

ኢትዮጵያ የታሪክ ባለቤት ሀገር ናት የዛሬው ትውልድም ለነገው ትውልድ የሚተላለፍ የክብር፣ የልማት እና የተስፋ አሻራ የማኖር ሀላፊነት አለበት። ስለዚህ ዛሬ የምናደርገው ምርጫ ከአንድ ወቅት ወይም ከአንድ ትውልድ ፍላጎት በላይ ትርጉም ያለው ሲሆን፣ የመጪዎቹን ትውልዶች ዕጣ ፈንታ የሚወስን ታሪካዊ ውሳኔ ነው።

ኢትዮጵያ ዛሬ የምትመርጠው ለልጆቿ የተሻለ ነገን ለመገንባት ነው። የተረጋጋ ሰላም፣ ዘላቂ ልማት፣ ጠንካራ ኢኮኖሚ፣ የተስፋፋ የሥራ ዕድል፣ የተሻለ ትምህርት እና የዜጎች ክብርና ተጠቃሚነት የሚረጋገጥባት ሀገር ለመፍጠር ነው።

የዛሬው ምርጫ የድምፅ መስጠት ብቻ ሳይሆን ለሀገር የሚኖረንን እምነት፣ ለወደፊቱ ያለንን ራዕይ እና ለትውልድ ያለንን ኃላፊነት የምንገልጽበት መድረክ ነው። ዛሬ የምናሳየው ተሳትፎ የነገውን የሀገራችን አቅጣጫ የሚቀርጽ ሲሆን፣ ለልጆቻችን እና ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፍ ታሪካዊ አሻራ ይሆናል።

ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሲቆሙ፣ በራዕይ ሲመሩ እና ለጋራ ጥቅም ሲወስኑ የማይሳካ ግብ የለም። ስለዚህ ዛሬ የምንመርጠው ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድ፣ ለሀገራችን ክብር እና ለኢትዮጵያ ዘላቂ ብልፅግና ነው።

ኢትዮጵያ መርጣለች! የተሻለ ነገን ለመገንባት፣ የልማት ጉዞዋን ለማስቀጠል፣ ለትውልድ የሚታወስ አሻራ ለማኖር መርጣለች። ዛሬ የተሰጠው ውሳኔ የነገው ታሪክ ይሆናል፤ ዛሬ የተጣለው መሠረት የነገው ከፍታ ይሆናል።




yekawrd09pp

06/06/2026

የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ አህጉራዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

በአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራን በተግባራዊ ፖሊሲዎች ለመደገፍ ያለመ አህጉራዊ ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰኔ 4 እና 5 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ያዘጋጀው ይህ ጉባኤ በአካዳሚክ ምርምሮች እና በፖሊሲ አፈጻጸሞች መካከል ያለውን ክፍተት መሙላትን ታሳቢ ያደረገ ነው።

የአፍሪካ ልማትና የተግባራዊ መፍትሄዎች መድረክ (ADIF 2026) የሚል ስያሜ ያለው ጉባኤ “በአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ የሚረዱ ምርጥ ተሞክሮዎችና የፈጠራ መፍትሔዎች” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ነው።

ጉባኤው በአፍሪካ በፍጥነት እያደገ የሚገኘውን የወጣት ማኅበረሰብ፣ በዓመት ከ15 ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድል በመፍጠር አህጉራዊው ፍላጎትን ለመመለስ ከተያዘው ውጥን ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው።

ይህ አዲስ መድረክ ከተለመዱ አህጉራዊ ስብሰባዎች በተለየ፤ የፖሊሲ አፈጻጸምን በማፋጠን በዘርፉ ያለውን የፖሊሲ እና የአሰራር ሂደት ለማቀለጣፈ ያለመ መሆኑን ኢዜአ ከኢሲኤ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በዚህም መሠረት የኢኮኖሚክ ኮሚሽኑ በገንዘብ እጥረት ምክንያት መሬት ያልወረዱ ጥናታዊ ምርምሮችን ወደ ተግባር ለመለወጥ፣ በጥቂት አካባቢዎች ተሞክረው ስኬታማ የሆኑ አነስተኛ የሙከራ ፕሮጀክቶችን ለማስፋት እንዲሁም አህጉር በቀል ምርጥ ተሞክሮዎችን በአገራት አጠቃላይ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ውስጥ በቀጥታ ለማካተት አቅዷል።

አሠራሩ በልማት ላይ የሚፈሱ የአህጉሪቱ ኢንቨስትመንቶች አስተማማኝና ዘላቂ ውጤት እንዲያመጡ ለማድረግ ትልቅ እገዛ ይኖረዋል ተብሏል።

የፎረሙን ውጤታማነትና ተጠያቂነት በተረጋገጠ መልኩ ለመከታተልም፣ ከጉባኤው በፊት፣ በጉባኤው ወቅትና ከጉባኤው በኋላ የሚተገበር የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቷል።

የመድረኩን ቀጣይነትና ትስስር አስተማማኝ ለማድረግ፣ የየዓመቱ መሪ ሀሳቦችን አንዱ ከሌላው ጋር በማስተሳሰር እና ተመጋጋቢ በማድረግ እንደሚዘጋጁ ኮሚሽኑ አስታውቋል።

በቀጣይ የሚካሄዱት ፎረሞች፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ትግበራን ከአህጉራዊ የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂዎች ጋር ማስተሳሰር ጨምሮ ሌሎች የልማት የትኩረት መስኮችን ታሳቢ በማድረግ እንደሚካሄድ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።

06/06/2026

‎7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያ የወሰነችው የዴሞክራሲ ጉዞ!

‎የኢትዮጵያ 7ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሀገሪቱን የፖለቲካ አቅጣጫ የሚወስን፣ የሕዝብን ሉዓላዊነት የሚያረጋግጥ እና የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ለማጠናከር የተከናወነ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው። ይህ ምርጫ ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳናዋ ላይ ያሳየችው የቁርጠኝነት መገለጫ ነው።

‎በዚህ ምርጫ የታየው የሕዝብ ተሳትፎ ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው የወደፊት ዕጣ ፈንታ ያላቸውን ከፍተኛ ክብር እና ኃላፊነት የሚያሳይ ነው። በመራጮች የምዝገባ ወቅት እንዲሁም በምርጫው ቀን የነበረው የሕዝብ መጉረፍ፣ ዜጎች በየደረጃው ባሉ የአስተዳደር መዋቅሮች ላይ የራሳቸውን ውክልና የመስጠት መብታቸውን በንቃት እየተጠቀሙበት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

‎7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች በሰላማዊ መንገድ የሀሳብ ልውውጥ የሚያደርጉበት፣ አማራጮች የሚቀርቡበት እና ሕዝቡ በነፃነት የሚወስንበት አጋጣሚ ሆኗል። የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ክርክሮች እና መድረኮች አማካኝነት የየራሳቸውን ፕሮግራም ለሕዝብ በማቅረብ፣ የዴሞክራሲን ባህል በማዳበር ረገድ ሚናቸውን ተወጥተዋል።

‎7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሰላም፣ ለፍትሕ እና ለጋራ ዕድገት ያለውን የቆራጥነት ስሜት የሚያሳይ ነው። ውጤቱ ምንም ይሁን ምን፣ በምርጫው መሳተፍ ለሀገር ግንባታ የታየ ታላቅ አሻራ ነው። ኢትዮጵያ አሁን በመረጠችው መንገድ፣ የዴሞክራሲን እሴቶች እያረጋገጠች ወደ ብሩህ ተስፋ የምታመራበት ምዕራፍ ተከፍቷል።



#ምርጫ

Photos from Yeka Woreda 09 Prosperity Party ብልጽግና's post 05/06/2026

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ 5ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ በዛሬው ዕለት አካሄደ።

ለካቢኔው በዛሬው በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡

በዚህ መሰረት፡-
1ኛ. የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ አስተዳደር ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ ተፈፃሚ እንዲሆን አፅድቋል።

2ኛ. የመሬት ይዞታ ማስለቀቅና ካሳ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ እንደገና ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ አፅድቋል።

3ኛ. በግል ዘርፍ ለህክምና ተቋማት ግንባታ እና ማስፉፍያ የሚውል መሬት ለማስተላለፍ የቀረበ የዉሳኔ ሀሳብ ላይ ተወያይቶ፣ ተፈፃሚ እንዲሆን አድፅድቋል።

05/06/2026

ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የተሰጠ መግለጫ

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ማለዳ ላይ፤ የመጀመሪያው የወገግታ ጭላንጭል በከፍታማዎቹ የኢትዮጵያ ተራሮች ላይ ፈንጥቆ ጨለማውን ሳይቀድ በፊት ኢትዮጵያውያን ረጃጅም ሰልፍ ተሰልፈዋል። በጅማ፣ በድሬዳዋ፣ በሐዋሳ፣ በባሕር ዳር እንዲሁም ስማቸው በዓለም አቀፍ የዜና ጋዜጣዎች ላይ ፈጽሞ ሊወጣ በማይችሉ ከተሞችና መንደሮች ውስጥ ያሉ ወንዶችና ሴቶች፤ ወሳኝ ተግባር ለመፈጸም በሰልፍ ቆሙ። ድምፅ ሰጡ! ይህንን ታሪካዊ ኃላፊነት ለመወጣት ከሃምሳ አራት ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ተመዝግበው ነበር። ይህ ቁጥር ከአንዳንድ ሀገሮች አጠቃላይ ሕዝብ ቁጥር በላይ ነው። ይህ ምርጫ እውነተኛ ስለመሆኑ ጥያቄ ለሚያነሣ ለማንኛውም አካል ግልጽ እና የማያሻማ ምላሽ ሰጥቷል!

‎የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት
‎የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከ52,000 ምርጫ ጣቢያዎች መካከል ከ50,188 በላይ የሚሆኑት በሰዓቱ ተከፍተው ቀኑን ሙሉ መራጮችን ሲያስተናግዱ እንደነበር አረጋግጧል። ከ42 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወጣጡ ከ10,438 በላይ ዕጩዎች እና 80 የግል እጩዎች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤት ወንበሮችን ለማሸነፍ ተወዳድረዋል። ይህ በማንኛውም ሊለካ በሚችል መሥፈርት በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቁ እና በውሳኔ አሰጣጥም ሆነ በአስተዳደራዊ ረገድ እጅግ በረቀቀ ሁኔታ ተግባራዊ የተደረገ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ የታየበት ኩነት ነበር።

የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ክቡር ኡሁሩ ኬንያታ የሚመሩትና ከ37 የአፍሪካ ሀገሮች የተወጣጡ 83 ታዛቢዎችን ያቀፈው የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ምርጫውን “ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን በሰፊው በሚደግፍ ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ ውስጥ የተካሄደ” ሲል ገምግሞታል። በቀድሞዋ የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ክብርት ዶክተር ስፔሲዮዛ ዋንዲራ ካዚብዌ የሚመራው የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት፥ በታዘቡባቸው ጣቢያዎች ሁሉ የምርጫ ሳጥኖች በትክክል የታሸጉ መሆናቸውን፣ የፓርቲ ወኪሎች በሂደቱ በሙሉ መገኘታቸውን እንዲሁም ምርጫው አስደናቂ ተቋማዊ፣ አስተዳደራዊና የቴክኖሎጂ ዕድገትን ያሳየ መሆኑን አረጋግጧል። የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ይሄንን ምርጫ «የበርካታ አዳዲስ ምዕራፎች ምርጫ» ሲል ሰይሞታል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በድምፅ መስጠት ሂደት ውስጥ ምንም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳልተመለከተ አረጋግጧል። የሲቪክ ማኅበረሰብ ታዛቢዎች ጥምረት በምርጫ ቦርድ እውቅና ከተሰጣቸው 55 ድርጅቶች 65,299 የታዛቢዎችን በመላ ሀገሪቱ ያሠማራ ሲሆን፥ 99 በመቶ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ያለምንም ዕንቅፋት የመታዘብ ዕድል ማግኘቱን አረጋግጧል። እነዚህ ተዓማኒነት ያላቸው ሀገራዊ እና አኅጉራዊ ተቋማት ያደረጓቸው ግምገማዎችና የሰጧቸው እውነተኛ ፍርዶች ናቸው። እነዚህ ለአፍሪካ ጥላቻ ካላቸው ወይም የአፍሪካን ዴሞክራሲ በውጫዊ መሥፈርቶች ከሚለኩ ተቋማት የተደመጡ ድምፆች አይደሉም።

‎አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተንታኞች ይሄንን ምርጫ እንደ ንግሥና በዓል አድርገው ያቆሸሹት ሲሆን ውጤቱም አስቀድሞ የተወሰነ ድራማ እንደነበር አድርገው ሊያቀርቡት ሞክረዋል። እነዚህን መግለጫዎች ከእውነታው ፈጽሞ የራቁ፣ በጥናትና ትንተና ላይ ያልተመሰረቱ እንዲሁም ነፃና የታሰበበት ዴሞክራሲያዊ ምርጫቸውን በኩራት ላደረጉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ክብር የማይሰጡ በመሆናቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሙሉ በሙሉ የማይቀበላቸው መሆኑን ያረጋግጣል። አስቀድሞ የተወሰነ ውጤት ቢኖር ኖሮ፤ ከ37 የአፍሪካ ሀገሮች የተወጣጡ 83 ገለልተኛ ታዛቢዎችን፣ 65,299 የሀገር ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ታዛቢዎችን ወይም 1,100 ዕውቅና የተሰጣቸውን ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች መጋበዝ ባላስፈለገ ነበር።

‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ሀገራዊ ምርጫ ለተሳተፉ የኢትዮጵያ ዜጎች፣ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ላሠማራቸው ከ350,000 በላይ ኃላፊዎች፣ ሂደቱን ለጠበቁት የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ ግንባታ መጎልበት እና ለሂደቱ መሳካት ያላትን ቁርጠኝነት ላረጋገጡት የአፍሪካ እና ቀጣናዊ የታዛቢ ቡድኖች ምስጋናቸውን ያቀርባሉ!

‎ስለ ኢትዮጵያ ልማት
‎ኢትዮጵያውያን ግንቦት 24 2018 ዓ.ም ውሳኔያቸውን ሲያስቀምጡ፣ ሀገራቸውን በፍጹም የዴሞክራሲ ባህል ውስጥ ለማንበር ነው። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ባላት ጸጋ ልክ የሚያስፈልጋትን ሁለንተናዊ ልማት በፍጥነት እውን የማድረግ ባህል እንዲቀጥል ሕዝባችን ተናግሯል።

‎ባለፉት ዓመታት የታየው እውነት እንደሚያሳየን የኢፌዴሪ መንግሥት የተስፋ ቃል መንግሥት አልነበረም። ይልቁንም በተጨባጭ የሚታዩ ውጤቶች የተመዘገቡበት ውጤት ተኮር መንግሥት ሲሆን፤ እነዚህም ውጤቶች በግልጽ የሚታዩ ናቸው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2017 በጀት ዓመት የ9.2 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ ሲሆን፥ ይሄም በዓለም ላይ ፈጣን ዕድገት ካስመዘገቡ ኢኮኖሚዎች አንዱ ያደርገዋል። ይሄንን መነቃቃት መሠረት በማድረግ በ2018 በጀት ዓመት የኢኮኖሚ ዕድገቱ 10.2 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። ዕድገቱ ግብርናን፣ ኢንዱስትሪንና የአገልግሎት ዘርፎችን በከፍተኛ ደረጃ ያካተተ ሰፊ መሠረት ያለው ቢሆንም፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን ኢንዱስትሪው ለዕድገቱ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይል ሆኖ እየመጣ ይገኛል። ይሄም መንግሥት ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለኢንዱስትሪ ልማት፣ ለዕሴት ጭማሪና ለውጭ ገበያ ተኮር ምርቶች የሰጠውን ቀጣይነት ያለው ትኩረት ያሳያል።

‎እነዚህ ውጤቶች እንዲሁ ግምቶች ብቻ ሳይሆኑ፥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የ100 ቀናት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ሥርዓት አማካኝነት ክትትል የሚደረግባቸው የተጠያቂነትና የታቀደ አመራር ፍሬዎች ናቸው። አጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ 20 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ይህም ከ2016 ዓ.ም. ወዲህ የ100 በመቶ ገደማ ጭማሪ አሳይቷል። የዋጋ ግሽበትም ወደ ታች ማሽቆልቆሉን በመቀጠል አሁን ላይ ወደ አንድ አሐዝ ደረጃ እየተቃረበ ይገኛል፤ ይሄም በቅርብ ዓመታት ውስጥ በቤተሰቦችና በንግዶች ላይ ከባድ ጫና ፈጥሮ ከነበረው ባለ ሁለት አሐዝ የዋጋ ግሽበት አንጻር ትልቅ መሻሻል ነው። ይህ ስኬት የተመዘገበው ዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦትና ሌሎች ስትራቴጂካዊ ቁሳቁሶችን ገበያ ያናጋው የመካከለኛው ምስራቅ ወቅታዊ ጂኦፖለቲካዊ ውጥረት ጨምሮ፣ ውጫዊ ጫናዎች በነበሩበት ወቅት ነው።
‎የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ከተጀመረ ወዲህ መንግሥት ከውጭ ምንጮች ምንም ዓይነት አዲስ የንግድ ብድር ስምምነት ያላደረገ ሲሆን፥ ይሄም የሀገሪቱን የብድር ዕዳ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ አቅልሎታል። ከእነዚህ ቁጥሮች በስተጀርባ ኢትዮጵያውያን በዓይናቸው የሚያዩትና በእጃቸው የሚዳስሱት ተጨባጭ ለውጥ አለ። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለመኖሪያ ቤቶች፣ ለንግድ ተቋማትና ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጨ ይገኛል። ይህ ግድብ በራሳቸው በኢትዮጵያውያን የተደገፈ፣ በኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች የተገነባና ቀጣይነት የነበረውን ውጫዊ ጫናዎችን ተቋቁሞ የተጠናቀቀ ነው። ከሃይድሮ ፓወር ጎን ለጎን፥ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሚገኘውን የአይሻ ሁለት የንፋስ ኃይል ማመንጫ እና በአርሲ ዞን የሚገኘውን የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች፤ በመሳሰሉ ሥራዎች የታዳሽ ኃይል አቅርቦቷን እያሰፋች ሲሆን፥ ይህም የቀጣናዊ ኢነርጂ ትብብርን እያሳደገ የብሔራዊ ኃይል አቅርቦት መረቡን የመቋቋም ዐቅም ያጠናክራል። በአፍሪካ አህጉር ታሪክ ውስጥ ትልቁ የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት አንዱ የሆነው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ ግንባታው ተጀምሯል። እነዚህ ምኞቶች አይደሉም፤ ተጨባጭ ሐቆች ናቸው።

‎ግብርና፣ አምራች ኢንደስትሪና ቴክኖሎጂ
‎በግብርናው ዘርፍ፣ የመንግሥት የምግብ ሉዓላዊነት አጀንዳ ወቅታዊ ለውጦችን ሳይሆን መዋቅራዊ ውጤቶችን እያስገኘ ቀጥሏል። በሶማሌ ክልል የጎዴ ዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካን ለመገንባት ከአሊኮ ዳንጎቴ ግሩፕ ጋር የተፈረመው አጋርነት የዘመኑ ጉልህ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንቶች አንዱ ማረጋገጫ ነው። ፋብሪካው በዓመት 3 ሚልዮን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ የማምረት አቅም እንዲኖረው ታቅዶ እየተገነባ ሲሆን፥ ይሄም ኢትዮጵያን በዓለም ትላልቅ ማዳበሪያ አምራች ሀገራት ተርታ ያሰልፋታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንቦት 9 ቀን 2018 ዓ.ም. የፕሮጀክቱን የግንባታ ሂደት በጎበኙበት ወቅት እንደገለጹት፤ “ይህ ፕሮጀክት በግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ በምግብ ዋስትና፣ በኢንዱስትሪ ዕድገትና በኢኮኖሚ ራስን መቻል ላይ የተደረገ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት ነው” ብለዋል። አስተማማኝ ባልሆነና ውድ በሆነ የማዳበሪያ አቅርቦት ለረጅም ጊዜ ለተገደቡት ኢትዮጵያውያን አምራቾች የዚህ ፕሮጀክት ፋይዳ ፈጣንና ተጨባጭ ነው።

ከዚህ ምርጫ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንቦት 19 ቀን 2018 ዓ.ም. በነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያ ምርቃት ላይ ሲገኙ የታየው ተምሳሌትነት ለቦረና ሕዝብ ትልቅ ትርጉም ነበረው። ይህ ዞን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅበት ስም የሀገርን አንገት ያስደፋ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ሲሆን፤ እርሱም ድርቅ ነው። ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የዝናብ መጥፋት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከብቶችን የገደለ፣ ቤተሰቦች ለውኃ ፍለጋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን እንዲጓዙ ያስገደደ፣ እንዲሁም በእነዚህ የግጦሽ መሬቶች ላይ ለዘመናት ራሳቸውን ችለው የኖሩ ማኅበረሰቦችን ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ እጅ እንዲዘረጉ አድርጎ ነበር። ዓለም የሚያውቃት ቦረና እርሷ ነበረች። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግንቦት ወር ጉብኝት ግን የተለየ ታሪክ አሳይቷል። አሁን ላይ ለአርብቶ አደር ማኅበረሰቦችና ለከብቶቻቸው ንጹሕ ውኃ እያቀረቡ ያሉትን የውኃና የመስኖ መሠረተ ልማቶችን የገመገሙ ሲሆን፥ ከጥቂት ዓመታት በፊት አቧራ ብቻ በነበረው መሬት ላይ የክላስተር እርሻዎችን ጎብኝተዋል፤ በያቤሎ የባህል ማዕከል መርቀዋል፤ እንዲሁም በአየር ንብረት ሁኔታዎች ምክንያት ቀድሞ ተገልሎ ለነበረው ቀጣና ዓመቱን ሙሉ ትስስር የሚፈጥር አውሮፕላን ማረፊያ መርቀው ከፍተዋል።

‎የአምራች ዘርፉም ተመሳሳይ የለውጥ ታሪክ አለው። በግንቦት 2018 ዓ.ም. በተካሄደው 4ኛው ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ላይ፤ መንግሥት ለአራት ዓመታት የተመዘገበውን ቀጣይነት ያለው የኢንዱስትሪ መስፋፋት ውጤቶች አቅርቧል። የአምራች ዘርፉ የግብአት አቅርቦት በዓመት 9 ሚልዮን ቶን ወደ 15 ሚልዮን ቶን አድጓል። የምርት አቅም አጠቃቀም ከ47 በመቶ ወደ 67 በመቶ ከፍ ማለቱን፣ የማኑፋክቸሪንግ ዕድገት ከ4.8 በመቶ ወደ 10.7 በመቶ ማደጉን፣ እንዲሁም ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚቀርበው ፋይናንስ ከ8.1 ቢልዮን ብር ወደ 50 ቢሊዮን ብር ማደጉን ያሳያል። እነዚህ ስኬቶች በሀገር ውስጥ ምርት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንጸባረቁ ይገኛሉ። ኤክስፖው በተጠናቀቀ በሃያ ቀናት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ተጠናቆ ከ80 በመቶ በላይ ጥሬ ዕቃውን ከሀገር ውስጥ የሚያገኘውን ግዙፍ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት «ግራንዲዩር የሴራሚክ ማኑፋክቸሪንግ» ፋብሪካን በሞጆ ከተማ መርቀዋል። ቀደም ሲል በገቢ የሴራሚክ ምርቶች ላይ ጥገኛ የነበረችው ኢትዮጵያ አሁን ላይ የሴራሚክ ምርቶችን ከውጭ ማስገባት ሙሉ በሙሉ ለማቆምና ለውጭ ገበያ የሚሆን ምርት ለማስፋፋት እየተዘጋጀች ትገኛለች።

‎በቴክኖሎጂው ዘርፍም፥ ዘመናዊ ልማት ከጊዜ ወደ ጊዜ በዳታ፣ በፈጠራና በዲጂታል ሥርዓቶች የሚወሰን መሆኑን በመገንዘብ፥ መንግሥት ኢትዮጵያን ሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የኢንዱስትሪ 5.0 ማሕቀፎችን ቀድመው ከተገበሩ ሀገራት ተርታ እያሰለፋት ይገኛል።

‎የጽንፈኝነትን ፖለቲካ ውድቅ ማድረግ
‎በኦነግ ሸኔ ዐማጽያን በንጹሐን ዜጎች ላይ በተለይም በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ዒላማ ተደርገው የተፈጸሙ ጥቃቶችን ተከትሎ፤ የቤተሰብ እና የወዳጆቻቸውን ሕይወት ላጡ፣ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው እና የቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው በአርሲ ዞን ለሚገኙ ወገኖቻችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ መንግሥት ስም የተሰማቸውን ጥልቅ ኀዘን ይገልጻሉ።

እነዚህ ጥቃቶች የሀገሪቱን ብሔራዊ ዕድገት ለማደናቀፍ ከሚሹ አካላት፣ በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የሀገር ውስጥ አማፂ ቡድኖች እና ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ጥላቻ ካላቸው የውጭ ኃይሎች ጋር በጥምረት የተከናወኑ ሲሆኑ፤ ዓላማቸውም በኢትዮጵያ አለመረጋጋትንና የምርጫ መስተጓጎልን ለመፍጠር ሲደረግ የነበረ የጥፋት ውጥን ተከታይ ነው። መንግሥት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያለ አንዳች የፀጥታ ችግር ፍትሐዊና አሳታፊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀ ልዩ ትኩረትና ዝግጅት በማድረግ በቁርጠኝነት ሲሠራ ቆይቷል። በሌላ በኩል የጥፋት ኃይሎች ከባዕዳን ጋር 'ፅምዶ' የሚል ቁርኝት በመፍጠር ዕኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት ሰፊ የጥፋት ዝግጅት ሲያድርጉ ቆይተዋል፣ ሀገራዊ ምርጫው እንዳይከናወን ሰፊ ርብርብ አድርገዋል። በተጨባጭም በቅድመ ምርጫ እና በምርጫ ወቅት የዜጎችን የመምረጥ መብትና ነጻነት ለመጋፋትና ለማደናቀፍ አለን የሚሉትን የጥፋት እጅ ዘርግተዋል።
‎እነዚህ የጠላት ኃይሎች በመደጋገፍና በመናበብ ዐመፅና ሁከት ለማነሳሳት፣ ከተሞችን በሽብር ጥቃት ለማወክ፣ በመንገዶች የደፈጣ ጥቃት በመፈጸም እንቅስቃሴ ለመገደብ እና በተወሰኑ አካባቢዎች ዒላማ አድርገው ነጥሎ ለማጥቃት ተንቀሳቅሰዋል። እንደ ማሳያ የጦር መሣሪያ፣ ተተኳሾችንና ሌሎች ሎጀስቲክሶችን በድጋፍ በማቅረብ በደቡባዊ ትግራይ በሚገኙ አዋሳኝ የአማራ ክልል አንዳንድ ቦታዎች ላይ ትንኮሳ ፈጽመዋል፣ በአማራ ክልል ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን እና ወልድያ ከተሞችን ጨምሮ በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች እና ሲቪሎች ላይ ዒላማ በማድረግ ያካሄደው የሽብር እንቅስቃሴና ዝግጅት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ባደራጃቸው የኅቡዕ ሴሎች አማካኝነት በተመረጡ አከባቢዎች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ተንቀሳቅሰው የነበረ ቢሆንም ይሄን የጥፋት ሴራ እና ድርጊት እንዲከሽፍ ማድረግ ተችሏል።

‎በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል የሸኔ ሽብር ቡድን ከጽንፈኛው ፋኖ ታጣቂ ቡድን ጋር በመናበብ በአንዳንድ አካባቢዎች መንገዶችን በመዝጋት እንቅስቃሴ ለማስቆምና ለማስተጓጎል ፍላጎት የተንቀሳቀሰ ቢሆንም በጸጥታ ኃይሉ በተወሰደበት የተጠናከረ እርምጃ ፍላጎቱን ማሳካት አልቻለም። ቡድኑ በፀጥታ ኃይሉ የተወሰደበትን ርምጃ መቋቋም ባለመቻሉ እና ፍላጎቱን ማሳካት ባለመቻሉ ስስ ዒላማዎች ላይ ያተኮረ ርምጃ በመውሰድ የሃይማኖት እና የብሔር ግጭት ለመቀስቀስ በማለም በአርሲ ዞን አሰኮ እና አካባቢው ጥቃት በመፈጸም ሁሉን አይነት የጥፋት ርብርብ ያደረገ ቢሆንም ሁኔታውን በመቆጣጠር ፀጥታ ኃይላችን በእነዚህ ኃይሎች ላይ የተቀናጀ ርምጃ እየወሰደ ይገኛል።

መንግሥት መሰል ሥጋቶችን በንቃት በመከታተል ላይ ሲሆን፣ በምርጫው ወቅትም በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተቀነባበሩ ተመሳሳይ ዕቅዶችን በስኬት ማክሸፍ ችሏል። በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን፤ ፍርሃትና ክፍፍልን ከሚያጎሉ የሚዲያ ዘመቻዎች ጋር በማስተሣሠር የተቀነባበረው ይህ እኩይ ተግባር፤ በመንግሥት የደኅንነት መዋቅርና ኦፕሬሽኖች አማካኝነት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲስተጓጎል ተደርጓል። ብሔራዊ እና ሃይማኖታዊ ክፍፍልን ለመዝራት የኃይል ጥቃትን እና ውድመትን እንደ መሣሪያ የሚጠቀሙ አካላት በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ በግልጽ ሊወገዙ ይገባል። መሰል ተግባሮች በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት የወደፊት ዕድል እንደሌላቸው ለማሳየት የተቀናጀ ብሔራዊ ምላሽ በመስጠት ወሳኝ ርምጃዎችን ይቀጥላል።

‎በንጹሐን ዜጎች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ አካላት፣ ድርጊታቸውን ምክንያታዊ ለማስመሰል ምንም ዓይነት የፖለቲካ ንግግር ቢጠቀሙ፤ ወሳኝ ዓላማን እያሳኩ ሳይሆን ወንጀል እየፈጸሙ ነው። የፖለቲካ ቅሬታዎች በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት፣ በብሔራዊ ምክክር ሂደት እና በዴሞክራሲያዊ ተቋማት አማካኝነት መፍትሔ ሊያገኙ የሚችሉ እና ሊያገኙ የሚገባቸው ናቸው።


ጽንፈኝነት ግን በኢትዮጵያ ምድር ፈጽሞ ቦታ የለውም!

Photos from Yeka Woreda 09 Prosperity Party ብልጽግና's post 05/06/2026

በጀት ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት 3 የመሶብ ዲጂታል አንድ ማዕከላት ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ይሆናሉ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በይፋ የመረቁት የመሶብ ዲጂታል አንድ ማዕከል ነዋሪዎችን ለዓመታት ሲያማርር ከኖረው የአገልግሎት አሰጣጥ እንግልትና ከብልሹ አሠራር የሚታደግ መሆኑን ገልጸዋል።

ከንቲባ አዳነች በማዕከሉ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የኮልፌ ነዋሪዎችን ከአገልግሎት አሰጣጥ እንግልትና ከሙስና የሚታደገው የመሶብ ዲጂታል ማዕከል በይፋ ሥራ መጀመሩን አብስረዋል።

ይህ ዘመናዊ የዲጂታል ማዕከል ለአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን ፣ የረጅም ጊዜ የሀገር ግንባታን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተገነባ መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባዋ፤ ነዋሪዎች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚደርስባቸውን ውጣ ውረድ በማስቀረት፣ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ሳያባክኑ የፈለጉትን አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

በከተማዋ በርካታ የልማት ሥራዎች ቢሠሩም፣ አሁንም ድረስ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚታዩትን እንደ ፈጣን አገልግሎት አለመስጠት፣ እንግልት እና የእጅ መንሻ (ጉቦ) ጥያቄዎችን ከመዋቅሩ ውስጥ መንጭቆ ለማውጣት ማዕከሉ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

ነዋሪዎች ፈጣን፣ ቀልጣፋና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ያለምንም ጉቦ ማግኘት የሚችሉበትን አስተማማኝ ሥርዓት ይፈጥራል ብለዋል ከንቲባ አዳነች።

በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የተጀመረው ይህ የዲጂታላይዜሽን ንቅናቄ በዚህ ብቻ እንደማያበቃ የገለጹት ከንቲባ አዳነች ፣ ሦስት ተመሳሳይ የዲጂታል ማዕከላት የበጀት ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት፣ ተጠናቀው ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።

ሕዝቡ በምርጫው ወቅት ያሳየው ታላቅ ፅናትና ፍላጎት፤ ሰላም፣ ልማት እና አጠቃላይ ሀገራዊ አካሄዶች በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲጓዙ መሻቱን በተግባር ያረጋገጠበት መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የዚህን ፅኑ ሕዝብ ጥያቄዎችና ፍላጎቶች በሚመጥን መልኩ ምላሽ መስጠት፣ ሥልጣን ከሚይዘው አካል የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ያለምንም የውጭ ተፅዕኖ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በራሷ ሕዝቦች፣ በሰላማዊና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ማካሄዷ እና በምርጫው ማግስትም እንደነዚህ ያሉ ተጨባጭ ፍሬዎችን ማስመዝገቧ፣ የጀመረችው የብልጽግና ጉዞ ወደ ከፍታ እንደሚመራ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ማሳያ መሆኑን ከንቲባዋ ገልጸዋል።

Photos from Adanech Abiebie- አዳነች አቤቤ's post 04/06/2026
04/06/2026

የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ልዩ ድምቀቶች

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የፖለቲካ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን ብቻ አልነበረም፤ ይልቁንም የዜጎች የሀገር ፍቅር፣ ልዩ መስዋዕትነት እና አስገራሚ የሕይወት አጋጣሚዎች በደመቀ ቀለም የተጻፉበት ታሪካዊ መድረክ እንጂ።

በየምርጫ ጣቢያዎቹ የተስተዋሉ አንዳንድ ክስተቶች የምርጫውን ሂደት ከፖለቲካዊ ክንውንነት ባለፈ፣ የሰው ልጅን የፅናት ጥግ እና ለሀገር የመቆርጠጥን ሚስጥር ያሳዩ ነበሩ።

የምርጫ ጣቢያው ታዳሚዎችን ብቻ ሳይሆን መላውን የሀገሪቱን ህዝብ ያስደመመው ክስተት የተመዘገበው በአካል ጉዳት ምክንያት ሁለት እጆቹን ያጣው ወገናችን ነው። እርሱ ግን እጆች ባይኖረኝም መምረጥ እችላለሁ በሚል መንፈስ፣ የምርጫ ወረቀቱን በአፉ በመያዝ ድምጹን በምስጢር ሳጥን ውስጥ ከቷል።

በሌላ በኩል እናትነትና ሀገራዊ ግዴታ ፊት ለፊት የተጋፈጡበት አስደናቂ ታሪክ ተመዝግቧል። አንዲት ጀግና እናት አዲስ ህጻን ልጅ ወደዚህች ምድር ባመጣች በሁለት ሰዓት ልዩነት ውስጥ፣ በምጥና በድካም ዝላ ሳለች ወደ ምርጫ ጣቢያ በመሄድ ድምፅ መስጠጥ ችላለች ።

ለብዙዎች የሰርግ ቀን ከጭፈራ፣ ከፎቶግራፍ ውጭ ሌላ ነገር አይታሰብበትም። ለነዚህ አዲስ ተጋቢዎች ግን የሰርጋቸው ምርጥ ማስታወሻ ወደ ምርጫ ጣቢያ መሄድ ነበር።
የትዳራቸውን መጀመሪያ በሀገር የወደፊት እጣ ፈንታ ውሳኔ የባረኩት እነዚህ ሙሽሮች፣ የዕለቱ ደማቅ ድምቀት ነበሩ።

በዱላ እየተደገፉ፣ በልጆቻቸውና በልጅ ልጆቻቸው እየተመሩ ወደ ምርጫ ጣቢያ የጎረፉት አባቶችና እናቶች ሌላው የምርጫው ውበት ነበሩ።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኮሮጆ ውስጥ የገቡ ድምፆች ብቻ ሳይሆኑ፣ የዜጎች ተስፋና ህያው ታሪኮች የተሰነዱበት ክስተት ሆኖ ያልፋል።


Want your business to be the top-listed Government Service in Addis Ababa?

Click here to claim your Sponsored Listing.

Location

Category

Website

Address

Asmera Street
Addis Ababa