08/06/2026
ትናንትን እያከምን ነገን ዛሬ እየገነባን አስተማማኝ ሰላማችንን እናረጋግጣለን!
ለዘመናት ሲዘራ የኖረው አሉታዊ ትርክት የነበረውን የማህበረሰብ ትስስር እና አብሮነት ሲሸረሽረው ቆይቷል፡፡ በሕዝብ መካከል መከፋፈል፣ መጠራጠር፣ ጥላቻና ተቃርኖ እየፈጠረ በተደጋጋሚ ወደ ግጭት የሚያመራውም ከወል ትርክቶች ይልቅ ተናጠላዊ ትርክቶች ጎልተው በመውጣታቸው ነው፡፡
ህብረ ብሔራዊነትን ከአንድነት አጣጥሞ የሚሄድ የፖለቲካ ሥርዓት ስላልነበረን በአንድ ዘመን በማንነት መኩራት ነውር ነበር፡፡ በኋላ ደግሞ በተቃራኒው ኢትዮጵያ የሚለውን ስም መጥራት እንደ ስህተት ተቆጠረ፡፡
እንዲሁም የአስተሳሰሩን ፀጋዎች ተዘንግተውና ተረስተው ቆዩ፡፡ በዚህም ምክንያት ለሀገራዊ አንድነት መዳከም ትልቁን ሳንካ ፈጠረ። ከዚህም ባሻገር የተለያዩ ሕዝቦችና ማንነቶች በሀገራቸው ባይተዋር ሆነው፣ የጥቂቶች የበላይነት የሰፈነበት አገዛዝ ሀገራዊ አንድነት ሲያዳክም ቆይቷል፡፡
ከለውጡ በፊት የነበረው አግላይ ስርዓት ብዙሀኑን ከፖለቲካና ከኢኮኖሚ ሂደት ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ በማድረግ የጥቂቶችን አምባገነናዊ ሥርዓት አስፍኖ ነበር።
ህዝቦች በክልላቸው ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸው ተገፎ በሞግዚት እንዲተዳደሩ ከማድረጉ ባሻገር የነበረው ስርዓት ዋናና አጋር፣ ልማታዊና ኪራይ ሰብሳቢ፣ ጠባብና ትምክህተኛ፣ ወዘተ. የሚሉ ከፋፋይ ትርክቶችን በመከተል ብዙሀኑን አግልሎ ቆይቷል፡፡
በሀገር በቀሉ የመደመር ፍልስፍና ሁሉም ዜጎች በሀገራቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እኩል ተሳታፊና ፍትሀዊ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ስርዓት በመዘርጋቱ ህዝብን በሀገሩ ላይ ባይተዋር አድርገው የቆዩ በርካታ ስብራቶች እየተጠገኑ ነው፡፡
ሁሉም ችግሮች በውይይት እና በድርድር እንዲፈቱ፣ ሁሉም ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ፣ የህግ የበላይነት እንዲከበር፣ የሀሳብ የበላይነት ገዢ እንዲሆን በብልፅግና ፓርቲ የተወሰዱ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ሀገራችንን ከግጭት አዙሪት በማውጣት አስተማማኝ ሰላሟን ዘላቂ ለማድረግ ፅኑ መሰረተ ናቸው፡፡
አሰባሳቢው የብሔራዊነት የወል ትርክት እንዲገነባ ሀገራዊ እሴቶችን በመጠቀም፣ ሌሎችንም አቅሞች በማስተባበር እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትም ከሁሉም፣ በሁሉም፣ ለሁሉም የሆነች፣ ተጋላጭነትን ያስወገደች ሉዓላዊት ሀገር ለመገንባት ያለንን ተጨባጭ ህልም እና ቁርጠኝነት አመላካች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያዊያን ከጠዋቱ 12:00 እስከ ሌሊቱ 7:00 እረጃጅም ሰልፎችን ታግሰው ፣ መምረጥ አትችሉም ላሏቸው ኋላቀሮች ዛቻና ማስፈራሪያ ጆሮ ሳይሰጡ ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በስኬት ማጠናቀቃቸውም ሰላምን በሰላማዊ መንገድ ለማምጣት የተጀመረው ርብርብ ስር እንዲሰድ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ ሀቅ ሆኗል::
የውይይት ባህልን ለማዳበር እየተሰሩ ከሚገኙ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ባሻገር 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሀዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ መጠናቀቁ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምን ለማረጋገጥ ለሚደረገው አበረታች ጥረት ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል።
ኢጋድ ፣ የአፍሪካ ህብረት ፣ የአውሮፓ ህብረት እና መሰል ቀጠናዊና አህጉራዊ ተቋማት ጭምር የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት የተናገሩለት ፣ ህዝባችን በነፃነት ያካሄደው ፣ በሁሉም መመዘኛዎች ሂደቱም ጭምር ፍትሀዊ የነበረው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ከፍተኛ የህዝብ ቅቡልነትንም አግኝቷል።
ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ሀሳባቸውን ለህዝባችን አቅርበዋል። ህዝባችን ደግሞ በካርዱ ይበጀኛል ያለውን መርጧል።
የህዝባችን ድምፅ እየተገነባ ለሚገኘው የውይይት ባህል መዳበር ፅኑ መሰረት ነው። የህዝብ ድምፅ ሉዓላዊ ነው ፤ በሁሉም ይከበራል።
መልካም የስራ ሳምንት ይሁንላችሁ! ይሁንልን!
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት
07/06/2026
19ኛው የኢትዮጵያ የግማሽ ማራቶን ውድድር በአዲስ አበባ፡
መነሻ እና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ያደረገው የግማሽ ማራቶን ውድድር በወንዶች 455 እና በሴቶች 183 በድምሩ 638 አትሌቶች ተሳትፈዋል።
06/06/2026
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የመንግሥትና የፓርቲ መደበኛ ሥራዎች አፈጻጸም ግምገማ ተካሄደ።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ፣ የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ካባ መብራቱና የክፍለ ከተማው ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መብራቱ ደሴን ጨምሮ የክፍለ ከተማና የወረዳዎች ጠቅላላ አመራሮች በተገኙበት የመንግሥትና የፓርቲ መደበኛ ሥራዎች አፈጻጸም ግምገማ ተካሂዷል።
በመድረኩም በዋናነት የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ፣ የመልካም አስተዳደር ሥራዎች፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም የፓርቲና የፖለቲካ ስራዎች አፈጻጸም ዙሪያ ጥልቅ ግምገማ ተካሂዷል።
በግምገማው ላይ በተለይም ከሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሂደት ጎን ለጎን መደበኛ የመንግሥትና የፓርቲ ሥራዎችን ያለምንም መዘናጋት በዕቅድ መሠረት ማከናወን መቻሉ እንደ ጠንካራ አፈጻጸም ተጠቅሷል።
በግምገማው ማጠቃለያም ከምርጫው ማግስት ጀምሮ ለሕዝብ የተገባውን ቃል በተግባር ለማሳየት፣ አገልግሎቶችን በጥራትና በፍጥነት ለማድረስ እንዲሁም የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን የበለጠ ለማጠናከር የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
06/06/2026
ምርጫው አካል ጉዳተኞች ከመቼውም ጊዜ የላቀ ተሳትፎ ያደረጉበት ነው - ፌዴሬሽኑ
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አካል ጉዳተኞች ከመቼውም ጊዜ በላቀ ደረጃ ተሳትፎ ያደረጉበት ነው አለ።
ፌዴሬሽኑ ምርጫውን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ እንዳለው ከአባል ማህበራት ጋር በመተባበር የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና የተደራሽነት ሁኔታ በቅርበት ሲታዘብ ቆይቷል፡፡
በዚህም በምርጫው 275 አካል ጉዳተኞች በዕጩነት መቅረባቸውንና ይህም በ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ከነበረው 99 የዕጩዎች ቁጥር አንጻር ሲታይ ከፍተኛ መሻሻል የታየበት ነው ብሏል።
165 ሺህ የሚገመቱ አካል ጉዳተኞች በመራጭነት መመዝገባቸውን የገለጸው ፌዴሬሽኑ አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሁም ደንቦችንና መመሪያዎችን የተከተለ እንደነበር አንስቷል፡፡
ፌዴሬሽኑ በመግለጫው የምርጫ አስፈጻሚዎች ለአካል ጉዳተኞች ከወትሮው የተሻለ ሁኔታዎችን የማመቻቸትና ቅድሚያ የመስጠት ሥራዎችን አከናውነዋል ነው ያለው።
በቀጣይም አካል ጉዳተኞች ፖለቲካዊ መብቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀሙ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ ለምርጫ ቦርድና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ምስጋና አቅርቧል።
06/06/2026
የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ አህጉራዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው
በአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራን በተግባራዊ ፖሊሲዎች ለመደገፍ ያለመ አህጉራዊ ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰኔ 4 እና 5 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ያዘጋጀው ይህ ጉባኤ በአካዳሚክ ምርምሮች እና በፖሊሲ አፈጻጸሞች መካከል ያለውን ክፍተት መሙላትን ታሳቢ ያደረገ ነው።
የአፍሪካ ልማትና የተግባራዊ መፍትሄዎች መድረክ (ADIF 2026) የሚል ስያሜ ያለው ጉባኤ “በአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ የሚረዱ ምርጥ ተሞክሮዎችና የፈጠራ መፍትሔዎች” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ነው።
ጉባኤው በአፍሪካ በፍጥነት እያደገ የሚገኘውን የወጣት ማኅበረሰብ፣ በዓመት ከ15 ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድል በመፍጠር አህጉራዊው ፍላጎትን ለመመለስ ከተያዘው ውጥን ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው።
ይህ አዲስ መድረክ ከተለመዱ አህጉራዊ ስብሰባዎች በተለየ፤ የፖሊሲ አፈጻጸምን በማፋጠን በዘርፉ ያለውን የፖሊሲ እና የአሰራር ሂደት ለማቀለጣፈ ያለመ መሆኑን ኢዜአ ከኢሲኤ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በዚህም መሠረት የኢኮኖሚክ ኮሚሽኑ በገንዘብ እጥረት ምክንያት መሬት ያልወረዱ ጥናታዊ ምርምሮችን ወደ ተግባር ለመለወጥ፣ በጥቂት አካባቢዎች ተሞክረው ስኬታማ የሆኑ አነስተኛ የሙከራ ፕሮጀክቶችን ለማስፋት እንዲሁም አህጉር በቀል ምርጥ ተሞክሮዎችን በአገራት አጠቃላይ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ውስጥ በቀጥታ ለማካተት አቅዷል።
አሠራሩ በልማት ላይ የሚፈሱ የአህጉሪቱ ኢንቨስትመንቶች አስተማማኝና ዘላቂ ውጤት እንዲያመጡ ለማድረግ ትልቅ እገዛ ይኖረዋል ተብሏል።
የፎረሙን ውጤታማነትና ተጠያቂነት በተረጋገጠ መልኩ ለመከታተልም፣ ከጉባኤው በፊት፣ በጉባኤው ወቅትና ከጉባኤው በኋላ የሚተገበር የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቷል።
የመድረኩን ቀጣይነትና ትስስር አስተማማኝ ለማድረግ፣ የየዓመቱ መሪ ሀሳቦችን አንዱ ከሌላው ጋር በማስተሳሰር እና ተመጋጋቢ በማድረግ እንደሚዘጋጁ ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በቀጣይ የሚካሄዱት ፎረሞች፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ትግበራን ከአህጉራዊ የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂዎች ጋር ማስተሳሰር ጨምሮ ሌሎች የልማት የትኩረት መስኮችን ታሳቢ በማድረግ እንደሚካሄድ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።
05/06/2026
ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የተሰጠ መግለጫ
ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ማለዳ ላይ፤ የመጀመሪያው የወገግታ ጭላንጭል በከፍታማዎቹ የኢትዮጵያ ተራሮች ላይ ፈንጥቆ ጨለማውን ሳይቀድ በፊት ኢትዮጵያውያን ረጃጅም ሰልፍ ተሰልፈዋል። በጅማ፣ በድሬዳዋ፣ በሐዋሳ፣ በባሕር ዳር እንዲሁም ስማቸው በዓለም አቀፍ የዜና ጋዜጣዎች ላይ ፈጽሞ ሊወጣ በማይችሉ ከተሞችና መንደሮች ውስጥ ያሉ ወንዶችና ሴቶች፤ ወሳኝ ተግባር ለመፈጸም በሰልፍ ቆሙ። ድምፅ ሰጡ! ይህንን ታሪካዊ ኃላፊነት ለመወጣት ከሃምሳ አራት ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ተመዝግበው ነበር። ይህ ቁጥር ከአንዳንድ ሀገሮች አጠቃላይ ሕዝብ ቁጥር በላይ ነው። ይህ ምርጫ እውነተኛ ስለመሆኑ ጥያቄ ለሚያነሣ ለማንኛውም አካል ግልጽ እና የማያሻማ ምላሽ ሰጥቷል!
የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከ52,000 ምርጫ ጣቢያዎች መካከል ከ50,188 በላይ የሚሆኑት በሰዓቱ ተከፍተው ቀኑን ሙሉ መራጮችን ሲያስተናግዱ እንደነበር አረጋግጧል። ከ42 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወጣጡ ከ10,438 በላይ ዕጩዎች እና 80 የግል እጩዎች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤት ወንበሮችን ለማሸነፍ ተወዳድረዋል። ይህ በማንኛውም ሊለካ በሚችል መሥፈርት በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቁ እና በውሳኔ አሰጣጥም ሆነ በአስተዳደራዊ ረገድ እጅግ በረቀቀ ሁኔታ ተግባራዊ የተደረገ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ የታየበት ኩነት ነበር።
የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ክቡር ኡሁሩ ኬንያታ የሚመሩትና ከ37 የአፍሪካ ሀገሮች የተወጣጡ 83 ታዛቢዎችን ያቀፈው የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ምርጫውን “ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን በሰፊው በሚደግፍ ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ ውስጥ የተካሄደ” ሲል ገምግሞታል። በቀድሞዋ የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ክብርት ዶክተር ስፔሲዮዛ ዋንዲራ ካዚብዌ የሚመራው የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት፥ በታዘቡባቸው ጣቢያዎች ሁሉ የምርጫ ሳጥኖች በትክክል የታሸጉ መሆናቸውን፣ የፓርቲ ወኪሎች በሂደቱ በሙሉ መገኘታቸውን እንዲሁም ምርጫው አስደናቂ ተቋማዊ፣ አስተዳደራዊና የቴክኖሎጂ ዕድገትን ያሳየ መሆኑን አረጋግጧል። የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ይሄንን ምርጫ «የበርካታ አዳዲስ ምዕራፎች ምርጫ» ሲል ሰይሞታል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በድምፅ መስጠት ሂደት ውስጥ ምንም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳልተመለከተ አረጋግጧል። የሲቪክ ማኅበረሰብ ታዛቢዎች ጥምረት በምርጫ ቦርድ እውቅና ከተሰጣቸው 55 ድርጅቶች 65,299 የታዛቢዎችን በመላ ሀገሪቱ ያሠማራ ሲሆን፥ 99 በመቶ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ያለምንም ዕንቅፋት የመታዘብ ዕድል ማግኘቱን አረጋግጧል። እነዚህ ተዓማኒነት ያላቸው ሀገራዊ እና አኅጉራዊ ተቋማት ያደረጓቸው ግምገማዎችና የሰጧቸው እውነተኛ ፍርዶች ናቸው። እነዚህ ለአፍሪካ ጥላቻ ካላቸው ወይም የአፍሪካን ዴሞክራሲ በውጫዊ መሥፈርቶች ከሚለኩ ተቋማት የተደመጡ ድምፆች አይደሉም።
አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተንታኞች ይሄንን ምርጫ እንደ ንግሥና በዓል አድርገው ያቆሸሹት ሲሆን ውጤቱም አስቀድሞ የተወሰነ ድራማ እንደነበር አድርገው ሊያቀርቡት ሞክረዋል። እነዚህን መግለጫዎች ከእውነታው ፈጽሞ የራቁ፣ በጥናትና ትንተና ላይ ያልተመሰረቱ እንዲሁም ነፃና የታሰበበት ዴሞክራሲያዊ ምርጫቸውን በኩራት ላደረጉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ክብር የማይሰጡ በመሆናቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሙሉ በሙሉ የማይቀበላቸው መሆኑን ያረጋግጣል። አስቀድሞ የተወሰነ ውጤት ቢኖር ኖሮ፤ ከ37 የአፍሪካ ሀገሮች የተወጣጡ 83 ገለልተኛ ታዛቢዎችን፣ 65,299 የሀገር ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ታዛቢዎችን ወይም 1,100 ዕውቅና የተሰጣቸውን ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች መጋበዝ ባላስፈለገ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ሀገራዊ ምርጫ ለተሳተፉ የኢትዮጵያ ዜጎች፣ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ላሠማራቸው ከ350,000 በላይ ኃላፊዎች፣ ሂደቱን ለጠበቁት የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ ግንባታ መጎልበት እና ለሂደቱ መሳካት ያላትን ቁርጠኝነት ላረጋገጡት የአፍሪካ እና ቀጣናዊ የታዛቢ ቡድኖች ምስጋናቸውን ያቀርባሉ!
ስለ ኢትዮጵያ ልማት
ኢትዮጵያውያን ግንቦት 24 2018 ዓ.ም ውሳኔያቸውን ሲያስቀምጡ፣ ሀገራቸውን በፍጹም የዴሞክራሲ ባህል ውስጥ ለማንበር ነው። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ባላት ጸጋ ልክ የሚያስፈልጋትን ሁለንተናዊ ልማት በፍጥነት እውን የማድረግ ባህል እንዲቀጥል ሕዝባችን ተናግሯል።
ባለፉት ዓመታት የታየው እውነት እንደሚያሳየን የኢፌዴሪ መንግሥት የተስፋ ቃል መንግሥት አልነበረም። ይልቁንም በተጨባጭ የሚታዩ ውጤቶች የተመዘገቡበት ውጤት ተኮር መንግሥት ሲሆን፤ እነዚህም ውጤቶች በግልጽ የሚታዩ ናቸው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2017 በጀት ዓመት የ9.2 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ ሲሆን፥ ይሄም በዓለም ላይ ፈጣን ዕድገት ካስመዘገቡ ኢኮኖሚዎች አንዱ ያደርገዋል። ይሄንን መነቃቃት መሠረት በማድረግ በ2018 በጀት ዓመት የኢኮኖሚ ዕድገቱ 10.2 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። ዕድገቱ ግብርናን፣ ኢንዱስትሪንና የአገልግሎት ዘርፎችን በከፍተኛ ደረጃ ያካተተ ሰፊ መሠረት ያለው ቢሆንም፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን ኢንዱስትሪው ለዕድገቱ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይል ሆኖ እየመጣ ይገኛል። ይሄም መንግሥት ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለኢንዱስትሪ ልማት፣ ለዕሴት ጭማሪና ለውጭ ገበያ ተኮር ምርቶች የሰጠውን ቀጣይነት ያለው ትኩረት ያሳያል።
እነዚህ ውጤቶች እንዲሁ ግምቶች ብቻ ሳይሆኑ፥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የ100 ቀናት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ሥርዓት አማካኝነት ክትትል የሚደረግባቸው የተጠያቂነትና የታቀደ አመራር ፍሬዎች ናቸው። አጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ 20 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ይህም ከ2016 ዓ.ም. ወዲህ የ100 በመቶ ገደማ ጭማሪ አሳይቷል። የዋጋ ግሽበትም ወደ ታች ማሽቆልቆሉን በመቀጠል አሁን ላይ ወደ አንድ አሐዝ ደረጃ እየተቃረበ ይገኛል፤ ይሄም በቅርብ ዓመታት ውስጥ በቤተሰቦችና በንግዶች ላይ ከባድ ጫና ፈጥሮ ከነበረው ባለ ሁለት አሐዝ የዋጋ ግሽበት አንጻር ትልቅ መሻሻል ነው። ይህ ስኬት የተመዘገበው ዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦትና ሌሎች ስትራቴጂካዊ ቁሳቁሶችን ገበያ ያናጋው የመካከለኛው ምስራቅ ወቅታዊ ጂኦፖለቲካዊ ውጥረት ጨምሮ፣ ውጫዊ ጫናዎች በነበሩበት ወቅት ነው።
የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ከተጀመረ ወዲህ መንግሥት ከውጭ ምንጮች ምንም ዓይነት አዲስ የንግድ ብድር ስምምነት ያላደረገ ሲሆን፥ ይሄም የሀገሪቱን የብድር ዕዳ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ አቅልሎታል። ከእነዚህ ቁጥሮች በስተጀርባ ኢትዮጵያውያን በዓይናቸው የሚያዩትና በእጃቸው የሚዳስሱት ተጨባጭ ለውጥ አለ። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለመኖሪያ ቤቶች፣ ለንግድ ተቋማትና ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጨ ይገኛል። ይህ ግድብ በራሳቸው በኢትዮጵያውያን የተደገፈ፣ በኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች የተገነባና ቀጣይነት የነበረውን ውጫዊ ጫናዎችን ተቋቁሞ የተጠናቀቀ ነው። ከሃይድሮ ፓወር ጎን ለጎን፥ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሚገኘውን የአይሻ ሁለት የንፋስ ኃይል ማመንጫ እና በአርሲ ዞን የሚገኘውን የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች፤ በመሳሰሉ ሥራዎች የታዳሽ ኃይል አቅርቦቷን እያሰፋች ሲሆን፥ ይህም የቀጣናዊ ኢነርጂ ትብብርን እያሳደገ የብሔራዊ ኃይል አቅርቦት መረቡን የመቋቋም ዐቅም ያጠናክራል። በአፍሪካ አህጉር ታሪክ ውስጥ ትልቁ የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት አንዱ የሆነው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ ግንባታው ተጀምሯል። እነዚህ ምኞቶች አይደሉም፤ ተጨባጭ ሐቆች ናቸው።
ግብርና፣ አምራች ኢንደስትሪና ቴክኖሎጂ
በግብርናው ዘርፍ፣ የመንግሥት የምግብ ሉዓላዊነት አጀንዳ ወቅታዊ ለውጦችን ሳይሆን መዋቅራዊ ውጤቶችን እያስገኘ ቀጥሏል። በሶማሌ ክልል የጎዴ ዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካን ለመገንባት ከአሊኮ ዳንጎቴ ግሩፕ ጋር የተፈረመው አጋርነት የዘመኑ ጉልህ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንቶች አንዱ ማረጋገጫ ነው። ፋብሪካው በዓመት 3 ሚልዮን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ የማምረት አቅም እንዲኖረው ታቅዶ እየተገነባ ሲሆን፥ ይሄም ኢትዮጵያን በዓለም ትላልቅ ማዳበሪያ አምራች ሀገራት ተርታ ያሰልፋታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንቦት 9 ቀን 2018 ዓ.ም. የፕሮጀክቱን የግንባታ ሂደት በጎበኙበት ወቅት እንደገለጹት፤ “ይህ ፕሮጀክት በግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ በምግብ ዋስትና፣ በኢንዱስትሪ ዕድገትና በኢኮኖሚ ራስን መቻል ላይ የተደረገ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት ነው” ብለዋል። አስተማማኝ ባልሆነና ውድ በሆነ የማዳበሪያ አቅርቦት ለረጅም ጊዜ ለተገደቡት ኢትዮጵያውያን አምራቾች የዚህ ፕሮጀክት ፋይዳ ፈጣንና ተጨባጭ ነው።
ከዚህ ምርጫ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንቦት 19 ቀን 2018 ዓ.ም. በነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያ ምርቃት ላይ ሲገኙ የታየው ተምሳሌትነት ለቦረና ሕዝብ ትልቅ ትርጉም ነበረው። ይህ ዞን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅበት ስም የሀገርን አንገት ያስደፋ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ሲሆን፤ እርሱም ድርቅ ነው። ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የዝናብ መጥፋት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከብቶችን የገደለ፣ ቤተሰቦች ለውኃ ፍለጋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን እንዲጓዙ ያስገደደ፣ እንዲሁም በእነዚህ የግጦሽ መሬቶች ላይ ለዘመናት ራሳቸውን ችለው የኖሩ ማኅበረሰቦችን ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ እጅ እንዲዘረጉ አድርጎ ነበር። ዓለም የሚያውቃት ቦረና እርሷ ነበረች። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግንቦት ወር ጉብኝት ግን የተለየ ታሪክ አሳይቷል። አሁን ላይ ለአርብቶ አደር ማኅበረሰቦችና ለከብቶቻቸው ንጹሕ ውኃ እያቀረቡ ያሉትን የውኃና የመስኖ መሠረተ ልማቶችን የገመገሙ ሲሆን፥ ከጥቂት ዓመታት በፊት አቧራ ብቻ በነበረው መሬት ላይ የክላስተር እርሻዎችን ጎብኝተዋል፤ በያቤሎ የባህል ማዕከል መርቀዋል፤ እንዲሁም በአየር ንብረት ሁኔታዎች ምክንያት ቀድሞ ተገልሎ ለነበረው ቀጣና ዓመቱን ሙሉ ትስስር የሚፈጥር አውሮፕላን ማረፊያ መርቀው ከፍተዋል።
የአምራች ዘርፉም ተመሳሳይ የለውጥ ታሪክ አለው። በግንቦት 2018 ዓ.ም. በተካሄደው 4ኛው ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ላይ፤ መንግሥት ለአራት ዓመታት የተመዘገበውን ቀጣይነት ያለው የኢንዱስትሪ መስፋፋት ውጤቶች አቅርቧል። የአምራች ዘርፉ የግብአት አቅርቦት በዓመት 9 ሚልዮን ቶን ወደ 15 ሚልዮን ቶን አድጓል። የምርት አቅም አጠቃቀም ከ47 በመቶ ወደ 67 በመቶ ከፍ ማለቱን፣ የማኑፋክቸሪንግ ዕድገት ከ4.8 በመቶ ወደ 10.7 በመቶ ማደጉን፣ እንዲሁም ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚቀርበው ፋይናንስ ከ8.1 ቢልዮን ብር ወደ 50 ቢሊዮን ብር ማደጉን ያሳያል። እነዚህ ስኬቶች በሀገር ውስጥ ምርት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንጸባረቁ ይገኛሉ። ኤክስፖው በተጠናቀቀ በሃያ ቀናት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ተጠናቆ ከ80 በመቶ በላይ ጥሬ ዕቃውን ከሀገር ውስጥ የሚያገኘውን ግዙፍ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት «ግራንዲዩር የሴራሚክ ማኑፋክቸሪንግ» ፋብሪካን በሞጆ ከተማ መርቀዋል። ቀደም ሲል በገቢ የሴራሚክ ምርቶች ላይ ጥገኛ የነበረችው ኢትዮጵያ አሁን ላይ የሴራሚክ ምርቶችን ከውጭ ማስገባት ሙሉ በሙሉ ለማቆምና ለውጭ ገበያ የሚሆን ምርት ለማስፋፋት እየተዘጋጀች ትገኛለች።
በቴክኖሎጂው ዘርፍም፥ ዘመናዊ ልማት ከጊዜ ወደ ጊዜ በዳታ፣ በፈጠራና በዲጂታል ሥርዓቶች የሚወሰን መሆኑን በመገንዘብ፥ መንግሥት ኢትዮጵያን ሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የኢንዱስትሪ 5.0 ማሕቀፎችን ቀድመው ከተገበሩ ሀገራት ተርታ እያሰለፋት ይገኛል።
የጽንፈኝነትን ፖለቲካ ውድቅ ማድረግ
በኦነግ ሸኔ ዐማጽያን በንጹሐን ዜጎች ላይ በተለይም በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ዒላማ ተደርገው የተፈጸሙ ጥቃቶችን ተከትሎ፤ የቤተሰብ እና የወዳጆቻቸውን ሕይወት ላጡ፣ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው እና የቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው በአርሲ ዞን ለሚገኙ ወገኖቻችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ መንግሥት ስም የተሰማቸውን ጥልቅ ኀዘን ይገልጻሉ።
እነዚህ ጥቃቶች የሀገሪቱን ብሔራዊ ዕድገት ለማደናቀፍ ከሚሹ አካላት፣ በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የሀገር ውስጥ አማፂ ቡድኖች እና ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ጥላቻ ካላቸው የውጭ ኃይሎች ጋር በጥምረት የተከናወኑ ሲሆኑ፤ ዓላማቸውም በኢትዮጵያ አለመረጋጋትንና የምርጫ መስተጓጎልን ለመፍጠር ሲደረግ የነበረ የጥፋት ውጥን ተከታይ ነው። መንግሥት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያለ አንዳች የፀጥታ ችግር ፍትሐዊና አሳታፊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀ ልዩ ትኩረትና ዝግጅት በማድረግ በቁርጠኝነት ሲሠራ ቆይቷል። በሌላ በኩል የጥፋት ኃይሎች ከባዕዳን ጋር 'ፅምዶ' የሚል ቁርኝት በመፍጠር ዕኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት ሰፊ የጥፋት ዝግጅት ሲያድርጉ ቆይተዋል፣ ሀገራዊ ምርጫው እንዳይከናወን ሰፊ ርብርብ አድርገዋል። በተጨባጭም በቅድመ ምርጫ እና በምርጫ ወቅት የዜጎችን የመምረጥ መብትና ነጻነት ለመጋፋትና ለማደናቀፍ አለን የሚሉትን የጥፋት እጅ ዘርግተዋል።
እነዚህ የጠላት ኃይሎች በመደጋገፍና በመናበብ ዐመፅና ሁከት ለማነሳሳት፣ ከተሞችን በሽብር ጥቃት ለማወክ፣ በመንገዶች የደፈጣ ጥቃት በመፈጸም እንቅስቃሴ ለመገደብ እና በተወሰኑ አካባቢዎች ዒላማ አድርገው ነጥሎ ለማጥቃት ተንቀሳቅሰዋል። እንደ ማሳያ የጦር መሣሪያ፣ ተተኳሾችንና ሌሎች ሎጀስቲክሶችን በድጋፍ በማቅረብ በደቡባዊ ትግራይ በሚገኙ አዋሳኝ የአማራ ክልል አንዳንድ ቦታዎች ላይ ትንኮሳ ፈጽመዋል፣ በአማራ ክልል ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን እና ወልድያ ከተሞችን ጨምሮ በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች እና ሲቪሎች ላይ ዒላማ በማድረግ ያካሄደው የሽብር እንቅስቃሴና ዝግጅት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ባደራጃቸው የኅቡዕ ሴሎች አማካኝነት በተመረጡ አከባቢዎች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ተንቀሳቅሰው የነበረ ቢሆንም ይሄን የጥፋት ሴራ እና ድርጊት እንዲከሽፍ ማድረግ ተችሏል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል የሸኔ ሽብር ቡድን ከጽንፈኛው ፋኖ ታጣቂ ቡድን ጋር በመናበብ በአንዳንድ አካባቢዎች መንገዶችን በመዝጋት እንቅስቃሴ ለማስቆምና ለማስተጓጎል ፍላጎት የተንቀሳቀሰ ቢሆንም በጸጥታ ኃይሉ በተወሰደበት የተጠናከረ እርምጃ ፍላጎቱን ማሳካት አልቻለም። ቡድኑ በፀጥታ ኃይሉ የተወሰደበትን ርምጃ መቋቋም ባለመቻሉ እና ፍላጎቱን ማሳካት ባለመቻሉ ስስ ዒላማዎች ላይ ያተኮረ ርምጃ በመውሰድ የሃይማኖት እና የብሔር ግጭት ለመቀስቀስ በማለም በአርሲ ዞን አሰኮ እና አካባቢው ጥቃት በመፈጸም ሁሉን አይነት የጥፋት ርብርብ ያደረገ ቢሆንም ሁኔታውን በመቆጣጠር ፀጥታ ኃይላችን በእነዚህ ኃይሎች ላይ የተቀናጀ ርምጃ እየወሰደ ይገኛል።
መንግሥት መሰል ሥጋቶችን በንቃት በመከታተል ላይ ሲሆን፣ በምርጫው ወቅትም በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተቀነባበሩ ተመሳሳይ ዕቅዶችን በስኬት ማክሸፍ ችሏል። በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን፤ ፍርሃትና ክፍፍልን ከሚያጎሉ የሚዲያ ዘመቻዎች ጋር በማስተሣሠር የተቀነባበረው ይህ እኩይ ተግባር፤ በመንግሥት የደኅንነት መዋቅርና ኦፕሬሽኖች አማካኝነት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲስተጓጎል ተደርጓል። ብሔራዊ እና ሃይማኖታዊ ክፍፍልን ለመዝራት የኃይል ጥቃትን እና ውድመትን እንደ መሣሪያ የሚጠቀሙ አካላት በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ በግልጽ ሊወገዙ ይገባል። መሰል ተግባሮች በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት የወደፊት ዕድል እንደሌላቸው ለማሳየት የተቀናጀ ብሔራዊ ምላሽ በመስጠት ወሳኝ ርምጃዎችን ይቀጥላል።
በንጹሐን ዜጎች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ አካላት፣ ድርጊታቸውን ምክንያታዊ ለማስመሰል ምንም ዓይነት የፖለቲካ ንግግር ቢጠቀሙ፤ ወሳኝ ዓላማን እያሳኩ ሳይሆን ወንጀል እየፈጸሙ ነው። የፖለቲካ ቅሬታዎች በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት፣ በብሔራዊ ምክክር ሂደት እና በዴሞክራሲያዊ ተቋማት አማካኝነት መፍትሔ ሊያገኙ የሚችሉ እና ሊያገኙ የሚገባቸው ናቸው።
ጽንፈኝነት ግን በኢትዮጵያ ምድር ፈጽሞ ቦታ የለውም!