28/05/2026
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ከሚዲያዎች ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን የሚዲያ ፎረም አካሄደ
ግንቦት 20 ቀን 2018 (ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል አዲስ አበባ)፡- የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ተደራሽነቱን ይበልጥ ለማሳደግ ይረዳው ዘንድ በዛሬው ዕለቱ የተለያዩ የሚዲያ ባለሙያዎችን ጠርቶ የሚዲያ ፎረም አካሂዷል፡፡
የሆስፒታሉ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር መገርሳ ዓለሙ፣ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ረድዔት ሰለሞን እንዲሁም የአዕምሮ ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ አስከ አሁን ያለውን አጠቃላይ ሂደት በተመለከተ ለጋዜጠኞች ገለጻ አቅርበዋል፡፡
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በተለየ ሁኔታ የሚታወሰው በኮቪድ ወቅት በማገገሚያ ማዕከልነት በማገልገል ባበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲሆን ሆስፒታሉ ከዚያም በተጨማሪ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተከስቶ በነበረው ግጭት ሳቢያ በተወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ የጦር ጉዳተኞችን ተቀብሎ የህክምና እርዳታ ሲያደርግ መቆየቱንም ዶ/ር መገርሳ አንስተዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም በወቅቱ አገልግሎት ሲሰጡ ለነበሩ ክፍሎች የእድሳት ስራ ማካሄድና የአገልግሎት ጥራቱን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ወደ እድሳት ተገብቶ የሱስ ማገገሚያ ተኝቶ ህክምናን ጨምሮ በርካታ አዳዲስ አገልግሎቶችን በማካተት እድሳቱ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ከ90 በላይ ሰብ ስፔሻሊስቶች ያሉትና በሰው ኃይልም ሆነ በመሳሪያ ዘመኑ በሚፈልገው ደረጃ የታጠቀና እንደ አገር የሜዲካል ቱሪዝም አገልግሎት እውን ለማድረግ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ከድጅታላይዜሽንም አንጻር ሆስፒታሉ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ከወረቀት ነጻ ለማድረግ መሰረተ ልማቶችን የሟሟላት ስራ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝና የቅሬታ አቀራረብ ስርዓትም ድጅታል ሆኖ በጽሁፍ፣ በድምጽ እና በፎቶ አስደግፎ ማቅረብ የሚቻልበት ስርዓት መዘርጋቱን አንስተዋል፡፡
ሆስፒታሉ ወደ ተቋሙ የሚመጡትን ብቻ ሳይሆን እንደ ሜቄዶንያ፣ ዲቦራ ፋውንዴሽን፣ ቦርን አጌይን በሚባሉ ድርጅቶችና በአካባቢው ያሉ ትምህርት ቤቶች ድረስ በመሄድ ነጻ የህክምናና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የትምህርት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ዶ/ር ረድኤት ሰለሞን ተናግረዋል፡፡ የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የአእምሮና የአካላዊ ህክምናን አጣምሮ የያዘ ከመሆኑም በተጨማሪ የሆስፒታሉ ስፋትና ወጣ ብሎ የሚገኝ መሆን ለአእምሮ ህመም ታካሚዎች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑ ከሌሎች ሆስፒታሎች ልዩ ያደርገዋል ሲሉ ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የሚዲያ ባለሙያዎችም የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አንስተው በበላይ ኃላፊዎቹ ምላሽና ማብራሪያዎች የተሰጡ ሲሆን የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ከሌሎች ሆስፒታሎች በተለየ የአእምሮና የአካላዊ ህክምናን አጣምሮ መያዙ የታካሚዎችን እንግልትን የሚቀንስና የአእምሮ ህመም ታክሞ መዳን ምጣኔን የሚያሳድግ በመሆኑ የሚበረታታ ተግባር እንደሆነ ተሳታፊዎቹ ጨምረው አንስተዋል፡፡
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በምስራቅ አፍሪክ ብቸኛ የስነ አዕምሮ ህክምና ማዕከል የመሆን ርዕዩን እውን ለማድረግም በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ የካበተ ልምድ ካላቸው ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነቶችን በመፈራረምና ትስስሮችን በማጠናከር እየሰራ እንደሚገኝ ዶ/ር መገርሳ ዓለሙ ተናግረዋል፡፡
በፎረሙ ላይ የተሳተፉ የሚዲያ ባለሙያዎች በሆስፒታሉ ኢክስኪዩቲቭ ዳይሬከተር አስጎብኚነት የሆስፒታሉን አገልግሎት መስጫ ክፍሎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
“የአገልግሎት ጥራት አርማችን!”
26/05/2026
ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1447ኛው ዓመተ ሂጅራ የአረፋ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
በዓሉ የሰላም: የመተሳሰብና የደስታ እንዲሆንላችሁ እንመኛለን።
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በበዓል ወቅት አመጋገባችንን በማስተካከል ለጤናችን ትኩረት እንስጥ እያለ መልካም በዓል እንዲሆንላችሁ ይመኛል።
"የአገልግሎት ጥራት አርማችን!"
21/05/2026
ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ከAHRI ጋር በጤና ምርምር ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ስትራቴጂካዊ የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ‼
ግንቦት 13/2018(አዲስ አበባ)— ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል እና አርማወር ሐንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት (AHRI) በሕክምና ምርምር፣ በክሊኒካል ልህቀት እና በባዮሜዲካል ፈጠራ ዘርፎች በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት በዛሬው ዕለት በይፋ ተፈራርመዋል።
ይህ ስምምነት ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ከፌዴራል የጤና ተቋማት ጋር ያለውን የሥራ ግንኙነት የበለጠ በማጠናከርና ተቋማዊ መስመር በማስያዝ፣ ኅብረተሰቡን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የምርምር ሥራዎችን በጋራ ማከናወን ይችል ዘንድ ታቅዶ የተፈረመ ስምምነት እንደሆነ ተገልጿል።
የስምምነቱ ዋነኛ ዓላማዎች በሁለቱ ተቋማት ዘንድ ያለውን አቅምና ተሞክሮ በማሰባሰብ በተለይም በሚከተሉት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ለመሥራት ነው ተብሏል፦
✅በክሊኒካል አገልግሎት፣ ምርምርና ሥልጠና፦ የጋራ የድኅረ-ምረቃ ፕሮግራሞችን በጋራ ለመቅረጽና ለመተግበር፤
✅ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ጥናቶች፦ የምርምር ውጤቶችን በጥልቀት በመተንተን፣ ለውሳኔ ሰጪ አካላት ጠቃሚ የሆኑ የፖሊሲና የቴክኒክ ሰነዶችን በጋራ ለማዘጋጀት፤
✅የመረጃ ልውውጥ፦ ለተቋማቱ የምርምርና ልማት ፍላጎቶች ወሳኝ የሆኑ ሳይንሳዊ መረጃዎችን በጋራ ማመንጨትና መጋራት።
የተቋማቱ ከፍተኛ አመራሮች ስምምነቱ በኢትዮጵያ የጤና ምርምርና የሕዝብ ጤና አገልግሎት ላይ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍትና ከፍተኛ አገራዊ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ስምምነቱን ወደ መሬት ለማውረድ ሁለቱም ተቋማት በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ተናግዋል።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
"የአገልግሎት ጥራት አርማችን!"
20/05/2026
የአዕምሮ ህመም እንዴት ይታከማል?
የአዕምሮ ህመም መንስኤዎች እና የህክምና ሂደቶች
➡️ Biological(ስነ ህይወታዊ)
➡️ Psychological(ስነ-ልቦናዊ)
➡️ Social(ማህበራዊ ጉዳዮች ) ብለን ከፍለን ማየት እንችላለን::
➡️ Biological(ስነ-ህይወታዊ ህክምና) ስር መድሃኒቶችን እናገኛለን:: የአዕምሮ ህመም መድሃኒቶች እንደየ ህመሙ አይነት ይለያያሉ::
▪️ Anti-depressant የተባሉ የአዕምሮ ህመም መድሃኒቶች ለድብርት፣ ለጭንቀት(Anxiolytic ጭምር ስለሆኑ)፣ ለ Obsessive-Compulsive disorder(ያልተፈለገ ሃሳብ እየመጣ ለሚረብሻቸው) እና ለመሳሰሉ ህመሞች ይታዘዛሉ::
አሰራራቸውም በህመም ወቅት የሚዛባውን የአዕምሮ መልእክት አስተላላፊ ቅመም (Neurotransmitter- በዋነኝነት Serotonin) የተባለውን ማስተካከል ነው::
ህመሙን የማከም አሰራራቸው (Mechanism of action)፣ በሚታዘዙበት የህመም አይነት ሊያመጧቸው በሚችሏቸው የጎንዮሽ ጉዳቶች እና መሰል ጉዳዮች መሰረት የተለያዩ አይነት Anti-depressant አሉ::
▪️ ለሳይኮሲስ ህመም(እንደ ስኪዞፍሬኒያ እና የመሳሰሉት) የሚሰጡ መድሃኒቶች Anti-Psychotic ይባላሉ::
እነዚህ መድሃኒቶች Typical/first generation እና Atypical/Second generation ተብለው ይከፈላሉ:: አሁን ላይ ከበፊቶቹ በተሻለ ብዙም የጎንዮሽ ጉዳት ሳያመጡ ሳይኮሲሱን ማከም የሚችሉ መድሃኒቶችን ማምረት እየተቻለ ነው::
እነዚህም መድሃኒቶች አንድ የሚያደርጋቸው የተዛባን የዶፓሚን ስራን ማስተካከል ላይ መስራታቸው ነው:: በሚዋጥ ወይንም በመርፌ መልክ ሊሰጡ ይችላሉ::
▪️ Mood stabilizer የሚባሉት ደግሞ ለ Bipolar (የስሜት መዋዠቅ) ህመሞች የሚታዘዙ ሲሆኑ ከልክ ያለፈ ድባቴ (Depression) እና መጠን አልባ ደስታ/ፈንጠዝያ (Mania) በማከም የተመጠነ ስሜት እንዲኖረን ያደርጋሉ::
▪️ Attention deficit hyperactivity disorder (ትኩረት የማጣትና የመቅበጥበጥ ችግር) ላለባቸው የሚታዘዙ እንዲሁም የእንቅልፍ ችግር ላለባቸው የሚታዘዙ መድሃኒቶች ናቸው::
ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው- በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት
“የአገልግሎት ጥራት አርማችን”!
19/05/2026
እንዲህም አለ? የሚያስብለው የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የሴቶች ፎረም ዓርዓያነት ያለው ተግባር
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በ2012 ዓ.ም በወቅቱ የጤና ሚኒስትር በነበሩት ክቡር ዶ/ር አሚር አማን ተመርቆ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ከመደበኛ የህክምና አገልግሎቶቹ በተጨማሪ የተለያዩ ሀገራዊ ተልዕኮዎችንም ሲወጣ ቆይቷል፡፡
በዚህ አጭር ጽሁፍ ልናወራ የወደድነው ግን ከኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ሰርክ ተግባር ይልቅ ወደሳበን የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የሴቶች ፎረም ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡
ፎረሙ በ2012 ዓ.ም ተመስርቶ ወደ ስራ የገባ ሲሆን ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ይበል የሚያሰኙ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ የገቢ አቅሙን ለማሳደግ ከሴት ፎረም አባላቱ ከሚሰበስበው የ10 ብር ወርሀዊ መዋጮ በተጨማሪ ለሆስፒታሉ ማህበረሰብ የሻይ ቡና መስተንግዶ እንዲሁም የፎረሙን አባላት ተጠቃሚ ለማድረግ በአነስተኛ ወለድ የተለያዩ የቤት እቃዎችን ገዝቶ በረጅም ጊዜ ክፍያ የማቅረብ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
የሴቶች ፎረም ዓላማው አባላቱን በተለይም አቅም የሌላቸውን መደገፍ እና የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራት ነው፡፡ “የፎረሙን አባላት” የሚለው ይሰመርበትና ይህ በብዙዎቹ ተቋማት በሚገኙ የሴቶች ፎረም አደረጃጀቶች የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡
ይህ ከሆነ የኤካ ኮተቤ የሴቶች ፎረም ምን የተለየ ስራ ሰርቶ ነው? ካላችሁኝ የመጀመሪያው ከ2016- 2018 ዓ.ም ባለው ጊዜ የፎረሙ አባላት ለሆኑ ከባድ ህመም ላጋጠማቸው 7 ሴት ሠራተኞች ለህክምና ወጪ የሚሆናቸውን የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ፣ ከ1ኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ደረጃ 12 ሴት ሰራተኞችን ያስተማረ ሲሆን 1 በዲግሪ 3 ሰራተኞችን ደግሞ በዲፕሎማ አስመርቋል፡፡
ከነዚህ ሁሉ ወይ ጉድ! የሚያሰኘው ተግባር ይህ ነው፡፡ ፎረሙ በተቋሙና በአባላቱ ብቻ ሳይወሰን የፎረሙ አመራሮች የተለያዩ የመለያ ዘዴዎችን በመጠቀም በአካባቢው ምንም ዓይነት ገቢም ሆነ ደጋፊ የሌላቸውን እንዲሁም ደግሞ ወደ ሆስፒታሉ ህክምና ለማግኘት መጥተው ለመድሃኒትም ሆነ ለምርመራ የሚከፍሉት ገንዘብ አጥተው ሲያለቅሱ ያገኟቸውን 25 እናቶች የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡ በዚህ ሳያበቃ ከእነዚህ እናቶች መካከል ለሆነችው ወ/ሮ ትዕግስት ካለባት ተደራራቢ ችግር አንጻር እስከ አሁን ድረስ ልዩ እገዛ እየተደረገላት ትገኛለች፡፡ ወ/ሮ ትዕግስት 12 ዓመት አካባቢ የሚሆነው መቀመጥም ሆነ መቆም የማይችል፣ በፈሳሽ መልክ ካልሆነ በቀር ማኘክ የማይችል ልጅ ያለ አባት ብቻዋን ይዛ የልጇን ህይወት ለማቆየት እየታገለች ያለች እናት ስትሆን ፎረሙ በወር በቋሚነት እያደረገላት ካለው የ1000 ብር ድጋፍ በተጨማሪ በቀጣይም በግል ፍላጎት ላይ ተመስርቶ የፎረሙ አባላት በራሳቸው ተነሳሽነት የተስማሙትን መጠን በወር ለማዋጣት ሃሳቡን ያቀረቡ አካላት እያስተባበሩ ይገኛሉ፡፡
ሌላው የሚያስገርመው ተግባር ከተለያዩ አካባቢዎች ምጥ ይዟቸው ወደ ሆስፒታሉ መጥተው ከወለዱ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸው ጥለዋቸው ለሄዱ ሁለት ህጻናት ቋሚ አሳዳጊ እስኪያገኙ ድረስ በሆስፒታል ቆይታቸው የወተትና የዳይፐር አቅርቦት ከሆስፒታሉ እንዲያገኙ ሲደረግ አሰራሩ የተራዘመ በመሆኑ አፋጣኝ ድጋፍ እንዲያገኙ ከሆስፒታሉ የማህበራዊ ድጋፍ ሰራተኞች ፎረሙ የህይወት አድን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥያቄ ሲቀርብለት አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት 14000 ብር ወጪ አድርጎ ወተት፣ ዋይፕስ እና ዳይፐር እንዲገዛ ማድረጉ ነው፡፡
በተጨማሪም ሆስፒታሉ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንጻር በአካባቢው ነዋሪ ለሆኑ ሶስት አቅመ ደካሞች ቤት አድሶ ሲያስረክብ ፎረሙም ለሶስት እማወራዎች መሶብ ገዝቶ በመስጠት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
ከላይ የተዘረዘሩት ተግባራት ጽሁፉን ለማሳጠር ሲባል ዋናው ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ሆኑ እንጂ ያሉት ሂደቶች እጅግ አሳዛኝና ልብ ሰባሪ እንደሆኑ የፎረሙ አመራርና አባላት በእንባ ጭምር የሚናገሩት ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ የፎረሙን አመራሮች ፍጹም ቅንንት እና ጥንካሬ አለማድነቅ ንፉግነት ይሆናል፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡ “ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው!”
“የአገልግሎት ጥራት አርማችን!”
14/05/2026
የአእምሮ ህመም ታክሞ ሊድን የሚችል በሽታ ነው
ግንቦት 6/2018 ዓ.ም፡ የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የወንዶች የስነ አእምሮ ተኝቶ ህክምናና የሱስ ማገገሚያ ክፍሎች ስራ መጀመርን በዛሬው ዕለት በይፋ አብስሯል፡፡ ሆስፒታሉ የአገልግሎት ጥራቱን ለማሳደግና የሚሰጣቸውንም የህክምና ዓይነቶች ከማስፋት አንጻር ላለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ የዕድሳትና የማስፋፊያ ስራዎችን ሲያካሂድ ቆይቶ አሁን ላይ ወደ ሙሉ አገልግሎት ለመግባት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
በዛሬው ዕለት ስራ መጀመሩ የተበሰረው የወንዶች የስነ አእምሮ ህክምናና የሱስ ማገገሚያ ክፍልም የዚሁ ዕድሳት አካል እንደሆነ በፕሮግራሙ ላይ ተገልጿል፡፡ የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በአዲስ አበባ ከሚገኙ የአእምሮና የፊዚካል ህክምናን አጣምረው ከያዙ ጥቂት ሆስፒታሎች አንዱ መሆኑን የተናገሩት የሆስፒታሉ ኢክስኪዩቲቭ ዳይሬክተርዶ/ር መገርሳ ዓለሙ “የአእምሮ ህመም እንደሌሎች በሽታዎች ሁሉ ታክሞ የሚድን በሽታ መሆኑን እንሰማለን አሁን ደግሞ በሆስፒታላችን እንደዚህ ዓይነት የአዕምሮ ችግር ያለባቸው ወገኖቻችን ታክመው ሲድኑ ማየት ለኛ ትልቅ ዕድል ነው” ሲሉ አንስተዋል፡፡ አያይዘውም ህክምናውን በምንስጥበት ጊዜ ደግሞ አገልግሎት መስጠት ብቻ ሳይሆን ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት ኃላፊነታችንን መወጣት ይገባናል ሲሉ ከአደራ ጭምር አሳስበዋል፡፡
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በምስራቅ አፍሪካ ታዋቂ የሆነ የሥነአዕምሮ ተቋም የመሆን ራዕይ ሰንቆ እየሰራ ያለ ተቋም እንደመሆኑ በዚያው ልክ ደረጃቸውን የጠበቁ የህክምና ቁሳቁሶችን አቅም በፈቀደ መጠን እያሟሉ መሄድ እንደ ተቋምም እንደ መንግስትም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ዶ/ር መገርሳ አንስተዋል።
በመርኃግብሩ ላይ የሆስፒታሉ የበላይ አመራሮች: ጥሪ የተደረገላቸው የማኔጅመንት አባላት የስነ አዕምሮ ክፍል የጤና ባለሙያዎችና የስነአዕምሮ ተኝቶ ታካሚ ወንዶች ተገኝተዋል።
"የአገልግሎት ጥራት አርማችን!"
08/05/2026
የአንድ ተቋም እቅድ ሙሉ የሚሆነው አሳታፊና ሁሉን አቀፍ ሲሆን ነው
ሚያዝያ 29 ቀን 2018፡ የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ከማህበረሰብ ተወካዮች ጋር በተቋሙ የ3ኛ ሩብ ዓመት እቅድ
አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ውይይት አካሄደ፡፡
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ለአካባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ ህክምና
አገልግሎቶችን ከመስጠት ባሻገር የተለያዩ ማህበራዊ ሁነቶችንም ከአካባቢው ማህበረሰብና ከሆስፓታሉ ተኝቶ ታካሚዎች ጋር እንደሚያሳልፍ ተገልጿል። ለአብነት ኢፍጣር እና የትንሳኤ በዓል የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ከተካሄዱ ሁነቶች መካከል ተጠቃሽ እንደሆኑ ተነስቷል።
ከዚህም በተጨማሪ ሆስፒታሉ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃር በትምህርት ቤቶችና ልዩ ልዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በመገኘት የነፃ ህክምናና የጤና ትምህርቶችን እንደሚሰጥ የሆስፒታሉ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መገርሳ ዓለሙ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት አንስተዋል።
የማህበረሰብ ተወካዮቹም በጥንካሬ የሚነሱ ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆኖ እንደ ማህበረሰብ ተወካይነታቸው ከህብረተሰቡ ያሰባሰቧቸውንና በሆስፒታሉ ተገኝተው የታዘቧቸውን ጉዳዮች አንስተው በማኔጅመንት አባላትና በበላይ አመራሩ ምላሽና ማብራሪያ ተሰቷቸዋል።
የማህበረሰብ ተወካዮቹ በእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ወቅት ብቻ ሳይሆን ከእቅድ ዝግጅት ጀምሮ በሚያደርጉት ተሳትፎ በየጊዜው የሚያነሷቸው ነጥቦች ለተቋሙ በትልቅ ግብዓትነት የሚወሰዱ እንደሆኑና ሊበረታቱ የሚገቡ እንዲሁም ደግሞ ወደፊት ሊታረሙ ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች በዝርዝር ያቀረቡበት አግባብ የሚበረታታ በመሆኑ ወደፊትም እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራቱ የሆስፒታሉን በምስራቅ አፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ተቋም ሆኖ የመምራት ራዕይ እውን ለማድረግ የሚያግዝ በመሆኑ ክትትልና ድጋፋቸው አስፈላጊ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የህብረተሰብ ተወካዮቹ በሆስፒታሉ በዕድሳት ላይ ያሉ የህክምና ክፍሎችን
ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን አብዛኞቹ ክፍሎች ለስራ ዝግጁ በመሆናቸው በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ለአገልግሎት ክፍት ስለሚሆኑ ይህንኑ ለህብረተሰቡ በማድረስ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡
“የአገልግሎት ጥራት አርማችን!”
07/05/2026
Eka Kotebe Hospital has Signed Memorandum of Understanding with Ethiopian Public Health Association
May 6/2026. Eka Kotebe Hospital has signed a Memorandum of Understanding (MoU) officially with Ethiopian Public Health Association (EPHA) marking a significant step toward strengthening collaboration in Ethiopia’s public health sector.
The MoU establishes a framework for cooperation in key areas, including joint research initiatives, professional training, and capacity-building programs.
Through this partnership, both institutions aim to enhance the quality of healthcare services and contribute to the advancement of evidence-based public health practices.
Speaking at the signing ceremony, representatives of both organizations emphasized the importance of institutional collaboration in addressing emerging health challenges and improving health outcomes nationwide. The agreement also facilitates the sharing of knowledge, technical expertise, and resources to support sustainable health system development.
This partnership reflects a shared commitment to improving public health and reinforcing coordinated efforts to deliver effective and equitable healthcare services across Ethiopia.
The Ethiopian Public Health Association is a non profitable leading professional association dedicated to promoting public health through research, advocacy, and capacity building.
"Our Reference is Service Standard!"
06/05/2026
ዓለም አቀፍ የእጅ ንፅህና ቀን በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በፓናል ውይይት ተከበረ!
በዓለም አቀፍ ደረጃ የእጅ ንፅህና ቀን ሲታሰብ፤ በጤናችን ላይ የሚያመጣው አስገራሚ ለውጥ ተመላክቷል። በትክክለኛ መንገድ እጅን ማፅድዳት በሽታን ከመከላከል ባለፈ የሕይወት አድን ሚናው ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል።
በውይይቱ ላይ ዶ/ር ሄርጎ አበራ እንዳብራሩት፣ እጅን በሳይንሳዊ መንገድ መታጠብ የሚከተሉትን አስደናቂ ጥቅሞች ያስገኛል፦
የተላላፊ በሽታ ምጣኔን መቀነስ፦ ተላላፊ በሽታዎችን የመተላለፍ ዕድል ከ18% ወደ 2% ዝቅ ያደርጋል።
የበሽታ መከላከል፦ በንክኪና በፈሳሽ የሚተላለፉ በሽታዎችን በ50% ይቀንሳል።
መድኃኒት የመለማመድ ችግር፦ በባክቴሪያዎች ላይ መድኃኒት አለመስራት (Drug Resistance) የሚያመጡ በሽታዎችን እስከ 70% ይከላከላል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሳይንሳዊውን መንገድ ተከትለው እጃቸውን በተገቢው የሚያፀዱ የጤና ባለሙያዎች 30% ቢሆኑም፣ ይህንን ቁጥር በማሻሻል የሕመምተኞችን ደህንነት ይበልጥ ማረጋገጥ እንደሚቻል ተመላክቷል።
በጤና ተቋማት፣ በምግብ ቤቶችና በሥራ ቦታዎች ንፁህ ውሃ፣ ሳሙናና አልኮልን በበቂ ሁኔታ በማቅረብ እጃችንን የማፅዳት ባህላችንን ካሳደግን፣ ጤናማ ማህበረሰብ መፍጠር እንደምንችል ተመልክቷል።
እጅዎን በትክክለኛ ቅደም ተከተል በማፅዳት ራስዎንና የሚወዱትን ሰው ይጠብቁ!
"የአገልግሎት ጥራት አርማችን"