31/07/2025
የድርሻችንን ተወጥተናል!!
ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት የ 2017 የአረንጏዴ አሻራ መርሀ-ግብር አከናውኗል::
በዛሬው እለት ከማለዳው አስራ ሁለት ሰዓት ጀምሮ በአንድ ጀንበር 700 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል በተያዘው ውጥን መሰረት "በመትከል ማንሰራራት” የሚለውን መሪ ቃል በማንገብ የፅ/ቤቱ ኃላፊ ወ/ሮ ሳምራዊት አማን በተገኙበት እንዲሁም ሁሉም የአካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት ባለሙያዎች በወረዳ 4 አቃቂ ወንዝ ዳርቻ በመገኘት አሻራቸውን አኑረዋል::
ወቅታዊ እና በአካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት የሚሰጡ አገልግሎቶችንና መረጃዎችን ለማግኘት ሲፈልጉ ይህን የማህበራዊ ሚዲያ ገፅ ይከተሉ !
07/07/2025
የአካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት የጉድጏድ ቁፋሮ መርሀ ግብር አካሄደ::
የ2017 የአረንጓዴ አሻራን ቅድመ ዝግጅት በማስመልከት በቀን በ30/10/2017 ዓ.ም በወረዳ 04 ልዩ ስሙ ኢ.ኬ.ቲ ጀርባ ባለውወንዝ ዳርቻ የጉድጏድ ቁፋሮው ተደርጏል::
በጉድጏድ ቁፋሮው ላይም የፅ/ቤቱ ቡድን መሪዎች , ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል::
ወቅታዊ እና በአካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት የሚሰጡ አገልግሎቶችንና መረጃዎችን ለማግኘት ሲፈልጉ ይህን የማህበራዊ ሚዲያ ገፅ ይከተሉ !
18/06/2025
የድምፅ ብክለትን ማድረስ የሚያስከትለው የሕግ ተጠያቂነት ምንድን ነው?
******************************************
በኢትዮጵያ የድምፅ ብክለትን ማድረስ ከ1 ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር መቀጮ ወይም ከ1 ዓመት እስከ 10 ዓመት እስር ሊያስቀጣ ይችላል፡፡
በተጨማሪም ለጥፋቱ የዋለው ንብረት እንደሚወረስ ብክለቱን ግለሰቡ /ተቋሙ/ እንዲያቆም ወይም ተገቢውን ካሣ እንዲክስ ፍርድ ቤቶች ሊወሰኑ እንደሚችሉ በአካባቢ ብክለት መቆጣጠሪያ አዋጁ አንቀጽ 16 ተደንግጓል።
ከተፈቀደው ድምፅ በላይ በመጠቀም ማስታወቂያ ያስነገረ ደግሞ በማስታወቂያ አዋጁ አንቀጽ 34(ሐ) መሰረት ከ20 ሺህ እስከ 150 ሺህ ብር ቅጣት ሊጣልበት ይችላል።
የድምፅ ብክለት ከአየር ብክለት ቀጥሎ በዓለማችን ሁለተኛው የአካባቢ ብክለት ዓይነት ነው፡፡
ብክለትን የሚፈጥሩት ድምፆች ከመጠን ያለፉ በመሆናቸው መደበኛውን የሕይወት እንቅስቃሴ ይጎዳሉ፣ እንቅልፍ ይነሳሉ፣ ውይይቶችንና መግባባትን ይቀንሣሉ፤ በአጠቃላይ የአኗኗር ሁኔታን በመረበሽ ተግዳሮት ይሆናሉ፡፡
በኢትጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 44 መሰረት ዜጎች ጤናማ እና ንፁህ የሆነ አካባቢ ውስጥ የመኖር መብት አላቸው። አንቀጽ 92 መንግሥት ጤናማ እና ንፁህ አካባቢ እንዲኖር የአቅሙን ጥረት የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ይደነግጋል።
በ1952 ዓ.ም የወጣው የፍትሐ ብሔር ሕግ በቁጥር 1225 እና በተከታዮቹ ላይ ማንኛውም ሰው ጎረቤቶቹን እንዲያስብ አስጠንቅቋል።
በይዞታችሁና በንብረታችሁ ስትጠቀሙ ከመጠን አልፎ የጎረቤታችሁን ጥቅም እንዳይቀንስ ወይም እንዳይጎዳ ጥንቃቄ አድርጉ ብሏል።
በተለይ ጢስ፣ ጥላሸት፣ ጎረቤት ሊታገሰው ከሚችለው በላይ ሽታ፣ ጩኸት፣ ንውፅታ (የድምፅ ብክለት) ጎረቤት ላይ መፍጠር እንደማይቻል ደንግጓል።
የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 300/1995 አንቀፅ 11 አካባቢ በካይ ከሚባሉት ነገሮች መሐል በሚደርሱበት አካባቢ በማንኛውም መጠን ጥራቱን በመለወጥ ጥቅሙን የሚቀንስ፣ የሚያጓድል ወይም በሰው ጤና ወይም በሌሎች ሕያዋን ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ወይም ሊያደርሱ የሚችሉ ድምፅና ንዝረቶችን የሚያመነጩ ነገሮችን እንደሚያካትት ይደነግጋል።
ብክለት ማለት ደግሞ በሕግ የተቀመጠውን ማንኛውንም ግዴታ፣ ማዕቀብ ወይም ገደብ በመጣስ የአካባቢያዊ ባህሪን በመለወጥ በሰው ጤና፣ በጎነት ወይም በሌሎች ሕያዋን ላይ አደገኛ የሆነ ወይም ሊሆን የሚችል ሁኔታ ነው።
በአዋጁ አንቀጽ 3 ላይ እንደተደነገገው ማንም ሰው የተቀመጠውን የአካባቢ ጥበቃ ደረጃ በመተላለፍ በድምፅም ሆነ በሌሎች ነገሮች አካባቢን መበከል ወይም እንዲበከል ማድረግ አይፈቀድለትም።
ሁሉም ሰዎች የድምፅ ብክለት ለሚፈጥረው መረበሽ ተጋላጭነታቸው እኩል አይደለም። በተለይም የመኖሪያ ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች የአምልኮ ስፍራዎች ወይም ተጠቃሚዎች ምቾትን እንደሚያገኙባቸው የሚገመቱ ሥፍራዎች ለድምፅ ብክለት ጉዳት ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ነው።
በመሆኑም የሚፈቀደውን ከፍተኛ የድምፅ መጠን በአካባቢው አይነት እና ደረጃ ለይቶ መመሪያው አስቀምጦታል።
የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መለኪያ መሠረት ለመኖሪያ አካባቢ ማታ 55 ቀን 45 ዴሲብል፣ ለንግድ አካባቢ ማታ 65 ቀን 55 ዴሲብል እንዲሁም ለኢንዱስትሪ አካባቢ ምሽት 75 ቀን 70 ዴሲብል በላይ ድምፅ አካባቢን ይበክላል ብሏል።
በማስታወቂያ ሰበብ የድምፅ ማጉያ መሣሪያ በመጠቀም ከተቀመጠው የድምፅ መጠን ገደብ በላይ ተጠቅሞ አካባቢን መበከል በማስታወቂያ አዋጁ 759/2004 አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 7 ላይ ሕገ ወጥ ሥራ በመሆኑ ተከልክሏል።
Via Addis Ababa City Administration Environmental protection Authority - የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ በለስልጣን ቴሌግራም ገፅ
✍🏼 ወቅታዊ እናጠቃሚመረጃዎችን ለማግኘት ይህንን ገፅ ይከተሉ ! አለማወቅ ከህግ ተጠያቂነት አያድንም እና መረጃውን ሼር በማድረግ ያግዙ🫵🏼
10/06/2025
የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል “ጽዱ ኢትዮጵያ” በሚል መጠሪያ ሁለተኛው ሀገራዊ ንቅናቄ ተጀምሯል።
የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የሚሳካው በየደረጃው ያሉ የሚዲያና የኮሙኒኬሽን አካላት ጉዳዩን በባለቤትነት ሲመሩ መሆኑ ተገለጸ
ጽዱ እና ምቹ ኢትዮጵያን ለትውልድ የማስረከብ ጉዞው የሚሳካው በየደረጃው ያሉ የሚዲያና የኮሙኒኬሽን አካላት ጉዳዩን በጥልቀት ተገንዝበው ለማኅበረሰብ በማስረዳት እና ሥራዎችን በባለቤትነት ሲመሩ መሆኑ ተገልጿል።
ንቅናቄዉ በአካባቢ ጥበቃ ጽዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያን በመፍጠር ለመጪው ትውልድ ሀለንተናዊ ምቹ ሀገር የማስረከብ ጥረት አካል መሆኑ ተመላክቷል።
የንቅናቄው ማስጀመሪያ አካል የሆነው የሚዲያ አካላት ሚናን የሚመለከት የፓናል ውይይት በትናንትናው ዕለት ተካሂዷል።
በፓናል ውይይቱ የተሳተፉት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ “የአካባቢ ጥበቃ ከሀገርም አልፎ ዓለም አቀፍ ጉዳይ ስለሆነ በአጀንዳ የተመራ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሥራ እንደሚያስፈልግ” ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ባለፉት ሰባት ዓመታት በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ትርጕም ባለው መልኩ ማሳደጉንም አቶ ተስፋሁን ገልጸዋል።
በከተሞች የተጀመሩ የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማቶችም ጽዱ እና ንጹሕ አካባቢ የመፍጠሩ አካል መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
ከእንጦጦ ጀምሮ የአዲስ አበባ ወንዞችን በማልማት እና በማከም አጠቃላይ የከተማዋን ተፋሰሶች የማጽዳት ተጨባጭ እንቅስቃሴ መጀመሩም ለዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የከተማ ኮሪደር ልማቱ ወደ ተለያዩ ከተሞች ተስፋፍቶ የፍሳሽ ሥርዐቱን በማሻሻል፣ ጽዱ የመናፈሻ ቦታዎችን በመፍጠር፣ ለኑሮ ምቹ ያልኾኑ አካባቢዎችን ገጽታ በመቀየር ጽዱ ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ የማስረከብ ጥረቱን ከፍ ማድረጉን ገልፀዋል።
ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ደረቅ ቆሻሻን በአግባቡ ይዞ በመጠቀም ንጹሕ አካባቢ መፍጠር እና ንጹሕና ታዳሽ ኃይል ማመንጨት እንደሚቻል ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ እንደሚሆንም አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጅ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ አንድ ጊዜ ተሠርቶ የሚጠናቀቅ ፕሮጀክት ባለመሆኑ ማኅበረሰቡ ባህል እስኪያደርገው ድረስ ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽኑ አጀንዳ አድርጎና ባለቤት ኾኖ እንዲሠራበት አሳስበዋል፡፡
የኪነ ጥበብ ዘርፉም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት አስተሳሰብ የመቅረጽ ሚናውን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል::
✍🏼 ዘገባው የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን እና AMN ነው::
ወቅታዊ እና በአካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት የሚሰጡ አገልግሎቶችንና መረጃዎችን ለማግኘት ሲፈልጉ ይህን የማህበራዊ ሚዲያ ገፅ ይከተሉ!
29/05/2025
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት ለሴቶች እና እናቶች ድጋፍ አደረገ ::
የአካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት ከሴቶች እና ህፃናት ጋር በመሆን በክፍለ ከተማው ስር ለሚገኙ አቅም ለሌላቸው 20 ለሚሆኑ እናቶች እና ሴቶች ምርጫዬ ሀይል ቆጣቢ የተሰኘ ምድጃ በፅ/ቤቱ ካለው አየር ንብረት ለውጥ እና አማራጭ ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ቡድን አማካኝነት ድጋፉን አድርጏል ::
ድጋፉን ያስረከቡት የአካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ ሳምራዊት አማን ከሴቶች እና ህፃናት ፅ/ቤት ጋር በመሆንነው::
ወቅታዊ እና በአካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት የሚሰጡ አገልግሎቶችንና መረጃዎችን ለማግኘት ሲፈልጉ ይህን የማህበራዊ ሚዲያ ገፅ ይከተሉ !
28/05/2025
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት ከውሀ እና ኢነርጂ ባለስልጣን ጋር በተባበር በክፍለ ከተማው ስር ለሚገኙ ሴቶች ስልጠና ተሰጠ::
ስልጠናው የተሰጠው ከተለያዩ የወዳደቁ ተረፈ ምርቶች ከሰል ለማምረት የሚያስችሉ የብሪኬት ከሰል ማምረቻ ማሽኖች እንዴት በቀላሉ የብሪኬት ከሰል ማሞረት እንደሚቻል ለሴቶች የትምህርት እና ግንዛቤ ስልጠናው ተሰቷል::
ስልጠናውን 38 ሴቶች እንዲወስዱና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተደረገ ሲሆን የአካባቢ ብክለትንም ከመከላከል አንፃር ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑንም በመገንዘብ ፅ/ቤቱ በቀጣይም መሰል ተግባራትን አጠናክሮ የሚቀጥልበት ይሆናል::
🙏🏻 ለምስሉ ጥራት ይቅርታ እንጠይቃለን
ወቅታዊ እና በአካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት የሚሰጡ አገልግሎቶችንና መረጃዎችን ለማግኘት ሲፈልጉ ይህን የማህበራዊ ሚዲያ ገፅ ይከተሉ ! ቤተሰብ ይሁኑ!
03/05/2025
ከፍተኛ የካርቦን ክምችት የሚይዙትን ዛፎች የምትለይ ሳተላይት ወደ ህዋ መጠቀች
40 ጫማ ርዝመት ያለው አንቴና የተገጠመላት አዲስ ሳተላይት ወሳኝ ተልዕኮ አንግባ የዓለምን ደኖች ለመቃኘት ወደ ህዋ ተልካለች።
በጃንጥላ ቅርጽ የተነደፈችው እና በኤርባስ የተሰራችው ሳተላይቷ በ413 ማይል (665 ኪሎ ሜትር) ከፍታ ላይ ምድርን በቀን ከ15 እስከ 16 ጊዜ ትዞራለች ተብሏል።
ሳተላይቷ ከቁጥቋጦዎች ጀምሮ ያሉትን ጨምሮ በዓለም አቀፍ የደን ሽፋን ላይ ዝርዝር መረጃዎችን እንደምትሰበስብ ተገልጿል።
በተጨማሪም እነዚህ ደኖች ምን ያህል ጥቅጥቅ ያሉ እንደሆኑ፤ በተለይም በደን ጭፍጨፋ እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዴት እየተለወጡ እንደሚገኙ መረጃ ትሰጣልች ሲል ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።
የኤርባስ ኩባንያ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ራልፍ ኮርዴይ እንዳብራሩት፥ አብዛኞቹ ሳተላይቶች የጫካውን ገፅታዎች ብቻ መለየት የሚችሉ ናቸው።
አዲሷ ሳተላይት ግን የጫካውን ዋና እና አንኳር ቦታ ለይታ ታያለች፤ ብሎም በዛፍ ውስጥ ምን ያህል ካርቦን እንደሚከማች ጥልቅ መረጃ ትሰጣለች ብለዋል።
✍️ ምንጭ- የአ/አ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን Fb ገፅ እና
- ዋሽንግተን ፖስት
ወቅታዊ እና በአካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት የሚሰጡ አገልግሎቶችንና መረጃዎችን ለማግኘት ሲፈልጉ ይህን የማህበራዊ ሚዲያ ገፅ ይከተሉ ! ቤተሰብ ይሁኑ!
29/04/2025
የአቃቂ ቃሊቲ አካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት የ 9 ወር ስራ አፈፃፀም ግምገማ አካሄደ
በግምገማው የፅ/ቤቱ ሀላፊ ወ/ሮ ሳምራዊት አማን መክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በአካባቢ ብክለት ክትትል ቁጥጥር , በማአድን አስተዳደር እና ቁጥጥር ዘርፍ , በብዝሀ ህይወት እና ስነ- ምህዳር ቡድን እንዲሁም በአየር ንብረት እና አማራጭ ኢነርጂ ዘርፍ የተሰሩ ጥሩ ስራዎችን እንዲሁም በክፍተት የተያዙ ስራዎችን የገመገሙ ሲሆን ስራዎቹ ሲሰሩ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመቅረፍ የተሄደበትን ርቀት አድንቀው በትለይም የህይወታችን ዋስትና የሆኑት ወንዞቻችን ላይ የሚደረጉትን ብክለቶችን ብትኩረት ቁጥጥር እንዲደርግ አቅጣጫ የሰጡ ሲሆን በቀጣይ ባለሙያዎች በቅንነት ስራቸውን እንዲከውኑ አሳስበዋል ::
በአካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት የሚሰጡ አገልግሎቶችንና መረጃዎችን ለማግኘት ሲፈልጉ ይህን የማህበራዊ ሚዲያ ገፅ ይከተሉ ! ቤተሰብ ይሁኑ!
08/04/2025
የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ አካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት የ 6 ወር ስራ አፈፃፀም ምዘና አካሄደ ።
በዛሬው ዕለት በ30/07/2017 ዓ/ም የአቃ/ቃ/ክ/ከተማ አካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት ከቅሬታና መልካም አስተዳደር ፅ/ቤት፣ከፕላን ኮሚሽን እና ከፐ/ሠ/የሠው ሃብት ልማት ፅ/ቤት ከተቋቋመ ኮሚቴ ጋር በመሆን የ2017 ዓ/ም የ6 ወር የስራ አፈፃፀም ምዘና አካሂዷል ። የምዘና ሂደቱ ከላይ ባለው ፎቶ መሠረት ሲሆን ከምዘና ኮሚቴው በአብዛኛው በጥንካሬ የተገለፁ አስተያየቶች የተሠጡ ሲሆን በክፍተት የተነሡም ውስን አስተያየቶችም ስላሉ በቀጣይ በትኩረት ፅ/ቤቱ የሚሰሠራባቸው ይሆናል።
በአካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት የሚሰጡ አገልግሎቶችንና መረጃዎችን ለማግኘት ሲፈልጉ ይህን የማህበራዊ ሚዲያ ገፅ ይከተሉ ! ቤተሰብ ይሁኑ!
04/04/2025
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን
የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር…/2014 ዓ/ም …የቀጠለ
ክፍል ሶስት
የበካይ ነገሮች አያያዝና አወጋገድ ስርዓት
10. ደረቅ ቆሻሻ
1. ደረቅ ቆሻሻ ከሰው ወይም ከእንስሳት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚመነጭ ወይም የሚፈጠር ሲሆን አያስፈልጉም፣ አይጠቅሙም ወይም አገልግሎታቸውን ጨርሰዋል ተብለው የሚጣሉ ነገሮች ስብስብ ነው፡፡
2. በይዘቱም ከተለያዩ መኖሪያ ቤቶች፣ ከንግድ ሱቆች እንዲሁም የህዝብ አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ከሚወጡ ቆሻሻዎች ማዘጋጃ-ቤታዊ ቆሻሻዎች ጀምሮ የግብርና ውጤት፣ የፋብሪካ እና የማዕድን ደረቅ ቆሻሻዎችን እና ተረፈ ምርቶችን ያጠቃልላል፡፡
3. ደረቅ ቆሻሻ የሚያካትታቸው ከመኖሪያ ቤትና ከተለያዩ ተቋማት የሚወጡ ተረፈ ምርቶች፣ የጠርሙስ ስብርባሪ፣ አገልግሎቱን የጨረሱ ጣሳ፣ ፕላስቲክና የፕላስቲክ ከረጢቶች፣ ያገለገለ የተሸከርካሪ ጎማ፣ የግንባታ እና የህንጻ ፍርስራሾች እና ሌሎቹንም ያካትታል፡፡
11. ደረቅ ቆሻሻ አያያዝ
1. ደረቅ ቆሻሻን በመሰብሰብ ፣በማጓጓዝ፣ በጥቅም ላይ በማዋል ወይም በማስወገድ ተግባር ላይ የሚሰማራ ማንኛውም ሰው ከሚመለከተው መስሪያ ቤት በቅድሚያ ፈቃድ ማግኘት አለበት፡፡
2. ማንኛውም ቆሻሻ የሚያመነጭ ሰው ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጀ ቦታ ከሚመለከተው አካል በሚሰጠው ፈቃድና የአወጋገድ ዘዴ መሰረት ማስወገድ አለበት፤
3. ማንኛውም ደረቅ ቆሻሻ የሚያመነጭ ሰው /ተቋም፣ አደገኛ ቁሶችን ወይም ቆሻሻ ከማስወደጉ በፊት በተገቢ ሁኔታ በተዘጋጀና አካባቢን ወይም የአካባቢ አካላትን በማይበክል ሁኔታ ማስቀመጥ አለበት፤
4. ማንኛውም ከኢንዱስትሪ የሚወገዱ ደረቅ ቆሻሻዎችን ወይም ተረፈ ምርቶችን ከአደገኛ ኬሚካል ጋር ቀላቅሎ ማስወገድ የለበትም፤
5. ማንኛውም የጤና ተቋም በሽታ አስተላላፊ ተህዋስያን ወይም ኬሚካል ጋር ንክኪ ያለውን ደረቅ ቆሻሻ ለዚሁ ተብሎ በአግባቡ በተዘጋጀ እና ደረጃዉን በጠበቀ ማቃጠያ ብቻ ማቃጠል አለበት፤
6. ማንኛውንም ቆሻሻ ከሚመለከተው አካል ፈቃድ ሳይዝ ቆሻሻን ማመንጨት፣ ማስቀመጥ፣ ማከማቸት፣ ማጓጓዝ፣ ማምከን ወይም ማስወገድ የተከለከለ ነው፤
7. ማንኛውም ሰው በተቻለ መጠን አነስተኛ ቆሻሻ የሚፈጥር የአጠቃቀም ዘዴ ወይም የአመራረት ሂደት መከተል አለበት፤
8. ማንኛውም ሰው ከተፈጠረው ቆሻሻ ተመልሶ በጥቅም ላይ ሊውል የሚችለውን ለይቶ ጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ አለበት፤
9. ማንኛውም ሰው መወገድ ያለባቸውን የቆሻሻ አይነቶችን አነስተኛ ቦታ እንዲይዙ አድርጎ ማጨቅና ሊያስከትሉት የሚችሉትን ጉዳት ስነ-ህይወታዊ ወይም ኬሚካላዊ በሆነ መንገድ ማስቀረትና ጥቅም ላይ ማዋል አለበት፤
10. ማንኛውም ሰው ደረቅ ቆሻሻ ባልተፈቀዱ ቦታዎች ማለትም በየመንደሩ፣ በየመንገዱ፣ በጎርፍ መውረጃ ቱቦዎች ፣በፓርኮች፣ በአውቶቡስ ፌርማታዎች፣ በስፖርት ሜዳ፣ በወንዞችና በወንዝ ዳርቻዎች ወዘተ መጣል የለበትም፤
11. ማንኛውም የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ላይ የተሰማራ ሰው ተረፈ ምርቶችን ለጤና ወይም ለአካባቢ ጎጂ ባልሆነ ሁኔታና ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀ የተለየ ማጠራቀሚያ ዕቃ ማከማቸት አለበት፤ ይህ አማራጭ ከሌለ በራሱ ኃላፊነት ወደ ተፈቀደ ማስወገጃ ሥፍራ ማድረስ ወይም ወደ ቀልዝነት የሚለወጥበትን መንገድ ማመቻቸት አለበት፤
12. ከግንባታና ልዩ ልዩ ሥራዎች ሂደት የሚመነጭ አፈር ፍርስራሽና ሌሎችም መሰል አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ባልተፈቀዱ ቦታዎች መድፋት የተከለከለ ነው፤
13. ማንኛውም የቆርቆሮ ጣሳ ወይም ጠርሙስ አምራች ወይም አስመጪ ጣሳው ወይም ጠርሙሱ ከአገልግሎት በኋላ መልሶ ጥቅም ላይ የሚውልበትን ዘዴ መዘርጋትና መተግበር አለበት፤
14. ውፍረቱ 0.03 ሚ.ሜ እና ከዚያ በታች የሆነ በስብሶ ከአፈር ጋር የማይዋሃድ ፕላስቲክ ማምረትም ሆነ መሸጥ የተከለከለ ነው፡፡
12. ስለ አደገኛ ቆሻሻ
1. የአደገኛ ደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ዕቅድ ዝግጅት፡-
ሀ) በአዲስ አበባ የሚገኝ እያንዳንዱ ክፍለ ከተማ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የአደገኛ ደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ዕቅድ ማዘጋጀትና መተግበር አለበት፤
ለ) እያንደንዱ ክፍለ ከተማ የአደገኛ ደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ዕቅድና የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ማዘጋጀት አለበት፤
ሐ) እያንዳንዱ ክፍለ ከተማ በውስጣቸው የሚገኙትን ማህበር ባዘጋጁት ዕቅድና ዘገባ ላይ ተመስርቶ አጠቃላይ የክፍለ ከተማውን ዕቅድና ዘገባ ማጠናቀር አለበት፡፡
13. ፍሳሽ ቆሻሻ
1. ከመኖሪያ ቤት የሚወጣ ፍሳሽ ቆሻሻ
ሀ) ከመኖሪያ ቤት የሚወጣ ፍሳሽ ማለት የልብስ እጣቢ፣ የመታጠቢያ ቤት እጣቢ፣ ከምግብ ማብሰያ አካባቢዎች የሚወጣ እጣቢ፣ የሽንት ቤት ፍሳሽ የመሳሰሉትን ፍሳሾች ይጨምራል፤
ለ) እነዚህ ፍሳሾች በሴፕቴክ ታንክ ተጠራቅመው ሴፕቲክ ታንኩ በሚሞላበት ወቅት መመጠጥና ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣኑ ባዘጋቸው የፍሳሽ ማጠሪያ ጣቢያ ሊጣራ ይገባል፤
ሐ) ፍሳሶቹን ከሴፕቴክ ታንክ ውጭ በቱቦ ከግቢ ውጭ በማስወጣት ወደ መንገድና ወደ አካባቢው መልቀቅ የተከለከለ ነው፤ በመንገድ ዳር የሚገኘው የክረምት ውኃ መውረጀ ቱቦ ወይም ድሬኔጅ አገልግሎቱ የጎርፍ ውሃ ወይም የዝናብ ውሃ ማስተላለፊያ ስለሆነ ይህን ቱቦ ለሌሎች ፍሳሾች ማስተላለፊያነት መጠቀም የተከለከለ ነው፤
መ) ኬሚካል ነክ ፍሳሾችን ተገቢውን የማከሚያ ዘዴ ሳይጠቀሙ ወደ ጎርፍ ማስወገጃ መልቀቅ የተከለከለ ነው፡፡
2. ከኢንዱስትሪ የሚወጣ ፍሳሽ ቆሻሻ
ሀ) ከማንኛውም ኢንዱስትሪ የሚለቀቁ ፍሳሽ ቆሻሻዎች ተገቢው ህክምና ተደርጎላቸው አካባቢ ሊሸከመው የሚችለው ደረጃ ላይ ሳይደርሱ በአቅራቢያ ወደሚገኘው የፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦ ወይም ወደ ማንኛውም የአካባቢ አካላት መልቀቅ የተከለከለ ነው፡፡
ለ) ከቆዳ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች፣ ከቀለም ፋብሪካዎች፣ ከዘይት ፋብሪካዎች፣ ከፓስታ ፋብሪካዎች፣ ከህጻናት ምግብ ቀማሚ ፋብሪካዎች፣ ከጎማ ፋብሪካዎች፣ ከስጋ ማቀነባበሪያዎች፣ ከጨርቃጨርቅ፣ ከፕላስቲክ፣ ከመድኃኒት፤ፋብሪካዎችና ከመሳሰሉትና ሌሎች የተለያዩ ፋብሪካዎችን የሚወጡ ፍሳሻ ቆሻሻዎች የፍሳሽ ዓይነት እንደ ፋብሪካው ዓይነት የተለያየ ስለሆነና የወጣውም ደረጃ በዚሁ መሰረት ስለሆነ በደረጃው በወጣው መስፈርት መሰረት መድረስ የሚገባቸው ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት መለቀቅ የለባቸውም፡፡
3. ከጤና ተቋማት የሚወጣ ፍሳሽ ቆሻሻ
ሀ) የጤና ተቋማት ሆስፒታሎችን፣ የጤና ጣቢያዎችን፣ ከፍተኛና መካከለኛ ክሊኒኮችንና የጤና ኮሌጆችን የሚያጠቃልል ነው፡፡
ለ) ከነዚህ ተቋማት የሚወጣ ፍሳሽ ቆሻሻዎች በአብዛኛው በሽታ አስተላላፊ ህዋሳትን ተሸካሚ እንዲሁም የተለያዩ በካይ ኬሚካሎችን የያዙ ስለሚሆኑ በተገቢው መንገድ ሳይታከሙ ወደ አካባቢ መለቀቅ የለባቸውም፡፡
4. ከነዳጅ ማደያዎችና ከጋራዦች የሚወጡ ፍሳሽ ቆሻሻዎች
ሀ) ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚፈጠሩ ፍሳሽ ቆሻሻዎች በውስጣቸው የተቃጠለ ዘይት ግሪስ እና ሌሎች ኬሚካሎችን የያዙ ስለሆኑ በጥንቃቄ ሊያዙ የሚገባቸውና እነዚህ በካይ ነገሮች ከውሃው ሳይለዩ ወደ አካባቢ መልቀቅ በህግ የተከለከለ ነው፡፡
ለ) የመኪና ማጠቢያ ፍሳሽ ሳይጣራ ወደ ማንኛውም የአካባቢ ክፍል መልቀቅ ክልክል ነው፡፡
ሐ) ከአገልግሎት መስጫ ተቋማት የሚወገደውን የተቃጠለ ዘይት በተመለከተ በመሬት ላይ መድፋት ፈጽሞ የተከለከለ ሲሆን የተቃጠለ ዘይት ክዳን ባለው ፕላስቲክ ማጠራቀምና መያዝ አለበት፡፡
መ) ምግብና መጠጥ ይዞ በቆየ ፕላስቲክ ማጠራቀምና መያዝ የተከለከለ ነው፡፡
ሠ) የተቃጠለ ዘይት መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል አካባቢን፣ አየርንና ውሃን በማይበክል መልኩ መሆን ይኖርበታል፡፡
5. ከንግድ ተቋማት የሚወጣ ፍሳሽ ቆሻሻ
ሀ) በንግዱ ህብረተሰብ አካባቢ በተለያየ ሁኔታ የሚጠራቀም ጊዜያቸው ያለፈባቸው ፈሳሽ ኬሚካሎች አያያዝ በጥንቃቄ ሊሆን ይገባል፡፡
ለ) አደገኛ የሆኑ ፈሳሽ ኬሚካሎች በፕላስቲክ መያዣ መጠራቀም የሚገባቸው ሲሆን ይህም በቀዝቃዛ ቦታ ክዳን ባለው መያዣ እንዲሁም በተዘጋጀላቸው ቀዝቃዛና በሲሚንቶ በተለሰነ ቦታ እስከሚወገዱ ድረስ አንዱ ኬሚካል ከሌላኛው በማይነካካበትና በማይቀላቀልበት መንገድ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡
ሐ) ሌሎቹም ጥቅም ላይ መዋል የማይችሉና አደገኛ ያልሆኑም ኬሚካሎች ቢሆኑ በተገቢው መንገድ ተይዘው መወገድ በሚገባቸው መንገድ በባለሙያ በመታገዝ ወደ አካባቢ ደረጃ ከመጡ በኋላ ማስወገድ ይገባል፡፡
መ) ፍሳሾችን በመንገድ ዳር ወይም በቱቦ ውስጥ ወይም በአፈር ላይ ወይም ወደ አየር ወይም ወደ ውሃ አካላት መልቀቅ የተከለከለ ነው፡፡
14. አየር ብክለት
1. ከእንዱስትሪ፤ ከሃይል ማመንጫ፤ ከተሽከርካሪዎች፤ ከአደገኛ ነገሮች፣ ከአምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ከመሳሰሉት የሚመነጩ አየር የሚበክሉ የበካይ ነገሮች ብናኝ/ጭስ/ ክርፋት ወይም ሽታ መጠን በአካባቢው ከሚፈቀደው ደረጃ በላይ መሆን የለበትም፡፡
2. ፈቃድ ካልተሰጠ በስተቀር ማንኛዉም ሰው ለአየር ከወጣለት የጥራት ደረጀ በላይ በካይ ነገሮች ብናኝ፣ ጭስ፣ ሽታና የመሳሰሉት ነገሮች ወደ አካባቢ አየር መልቀቅ ክልክል ነው፡፡
3. ቆሻሻ በሚቃጠልበት ጊዜ ሌሎች በካዮች ይፈጥራሉ እነሱም ካርቦን ዳይ-ክሳይድ፤ካርቦን ሞንኦክሳይድ፤ ናይትሮጅ-ዳይ ኦክሳይድ የመሳሰሉትና ብናኝ ንጥረ ቅንጣቶች በካዮች ይፈጥራሉ፤ስለዚህ ቆሻሻ ሲቃጠል የሚወጣው ጭስ አየርን በመመረዝ ለብክለት መንስኤ ስለሚሆን ከኢንዱስትሪ፤ ከሃይል ማመንጫ፤ከአግልግሎት ሰጭ ተቋማትና ከመኖሪያ ቤት የሚወጡ ቁሳቁሶችን መጣል ወይም ሜዳላይ ማቃጠል የተከለከለ ነው ፡፡
15. የእይታ ብክለት
1. ፈቃድ ካልተሰጠ በስተቀር ማንኛውም ሰው እይታን ከተፈቀደ የምልከታ ደረጀ በላይ በካይ ነገሮች ብናኝ፣ ጭስ ፣የመሳሰሉት ነገሮች አካባቢ መበከል፤ ጉዳት ማድረስ ክልክል ነው፤
2. በልማት ምክንያት ለህንጻ ስራ፣ ለመንገድ ስራ፣ ለማስታወቂያ ስራ ተብሎ የሚቀመጥ ማንኛውም አንጸባራቂ ነገር በሰውና በአካባቢ ላይ ጉዳት የሚያደርስ ሊያደርስ በሚችል መልኩ መጠቀም ወይም ማስቀመጥ መስቀል የተከለከለ ነው፡፡
30/03/2025
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን
የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር…/2014 ዓ/ም
ክፍል ሁለት
ስለ አካባቢ ደረጃዎች እና ብክለት ቁጥጥር
5. የአካባቢ ደረጃዎች
የአካባቢ ደረጃዎች ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ሁኔታዎች ሊገለጹ ይችላሉ፡-
1. ለሰው ልጅ ጤንነት ስለአካባቢ ደህንነት እንዲሁም ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚውል አግባብ ያለው የውሃ ጥራት፤
2. ለሰው ልጅ ጤንነት ህይወትና ጤንነት፤ ለእንስሳት ለተክሎች ተስማሚ የሆነ የአየር ጥራት ደረጃና ወደ አፈር የሚጨመሩ ኬሚካሎች አይነትና መጠን የሚወስኑ የአፈርደህንነትን የሚጠብቅ የአፈር ጥራት ደረጃ፤
3. ወደ አፈር የሚጨመሩ ኬሚካሎች አይነትና መጠን የሚወስኑ የአፈር
ደህንነት የሚጠብቅ የአፈር ጥራት፤
4. ለኢንዱስትሪ፤ ለግንባታ ቦታዎች፤ ለተሸከርካሪዎች ለአውሮፕልኖች፤ ለልዩ ልዩ መሳሪያዎች ለንግድ ተቋማትና ለሌሎች ድምጽ አመንጭ ነገሮች የድምጽ መጠን ደረጃ፤
5. የአደገኛ ነገሮች አመራረትና አያያዝ፤ አጠቃቀም ከቦታ ቦታ የማጓጓዝ
የብቃት ደረጃ፤
6. ወደ ውሃ አካላት ወደፍሳሽ መስመሮች፤ ወደ ከተማ ፍሳሽ ማጣሪያ መስመር፤ እንዲሁም ወደ ግለሰብ ፍሳሽ ማጣሪያ መስመር የሚለቀቁ የፍሳሽ ደረጃ፤
7. ለአካባቢ ደህንነት ለሰው ልጅ ጤንነት የሚስማማ የሽታ፤ የእይታ መጠን ደረጃ፡፡
6. የውሃ ጥራት ደረጃ
ለቤት ውስጥ አገልግሎት፤ ለኢንዱስትሪ ለመዝናኛ እና እንደስፈላጊነቱ ለሌሎች ተግባሮች ጥቅም ላይ የሚውል ውሃን የሚመለከት ይሆናል፡፡
7. የአየር የጥራት ደረጃ
1. ለሰው ልጅ ህይወትና ጤንነት፤ አስፈላጊ የሆነ ዝቅተኛ ሆነ የአየር ጥራት ደረጃ፤
2. ለእንስሳት ለተክሎች እንዲሁም በንብረት ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል የበካይ ነገሮች መጠንን፤
8. የፍሳሽ ለአካባቢ ተስማሚ ደረጃ
1. ወደ ውሃ ወይመር ወደ መሬት የሚለቀቀው፤ የሚደፋው ፤ የሚቀበረው ወይም ወደ ፍሳሽ መስመር እንዲገባ የሚፈቀደው ፍሳሽ፤
2. በፍሳሽ መስመር በፍሳሽ ማጣሪ ጣቢያ ከተጣራ በኋላ ወደ ውኃ ወይም መሬት የሚለቀቅ ፍሳሽ፤
9. ፍሳሽ ወደ ፍሳሽ መስመር ስለመልቀቅ
ማንኛውንም ፍሳሽ ወደ ፍሳሽ መስመር ለመልቀቅ የሚፈልግ ሰው በህግ ስልጣን ከተሰጠው አካል ፈቃድ ካልተሰጠው በስተቀር የፍሳሽ መስመሩን መጠቀም አይችልም፡፡ ከዚህ በታች ከተዘረዘሩትን የፍሳሽ የጥራት ደረጃዎች የማያሟላ ፍሳሽ ወይም ሌላ ነገር ወደ ፍሳሽ መስመር መልቀቅ ወይ ማስገባት እንዲለቀቅ ወይም እንዲገባ ማድረግ ይከለክላል ፡፡
1. በፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ላይ ሊጣራ የሚችል ወይም የማጣሪያ ጣቢያውን ስራ የሚያውክ ወይም ማጣሪያ ሂደት ላይ ችግር የሚፈጥር ፍሳሽ፤
2. ከፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ተጣርቶ የሚወጣ ፍሳሽ የጥራት ደረጃ በመቀነስ
ወይም በማጓደል በመንስት የወጣውን ደረጃ እንዳያሟላ ያደርጋል ተብሎ
የሚገመት ፍሳሽ፤
3. በራሱ ወይም ከሌላ ንጥረ ነገር ጋር በማዋሀድ መርዛማ ኬሚካል በማመንጨት በመስመር ጥገና ላይ በሚሰሩ ማንሆል ውስጥ ገብተው በሚሰሩ ሰራተኛች ላይ ጉዳት ያደርሳል ተብሎ የሚገመት ፍሳሽ፤በቴክኖሎጅ በመጠቀም ማስወገድ አለበት፤
4. በራሱ ወይም ከሌላ ንጥረ ነገር ጋር በማዋሀድ በፍሳሽ መስመር ወይም በማጣሪያ ጣቢያ ወይም የተጣራው ፍሳሽ በሚለቀቅበት ውሃ እና አፈር ላይ ጉዳት ያደርሳል ተብሎ የሚገመት ፍሳሽ፤ከሆነ ጉዳት በማያደርስ አሰራር ተጠንቶ መወገድ ይገባዋል፤
5. የፍሳሽ ሙቀት ፍሳሽ መስመሩ ጋር በሚገናኝበት ቦታ ላይ ሲለካ ከመቶ ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የበለጠ ፍሳሽ፤ መለቀቅ የለበትም፤
6. ፍሳሽ ፒኤች ከ5.5 ከአነሰ ወይም ከ10.0 የሚበልጥ ከሆነ፤
7. በፍሳሽ መስመር ውስጥ የሚቀጣጠል ወይም የሚፈነዳ ወይም መርዛማና አደገኛ ጋዝ ወይም ትነት ያመነጫል ተብሎ የሚገመት ከሆነ፤
8. ከአንድ መቶ ድግሪ ሴንቲ ግሬድ በታች የሆነ ሙቀት ሊተኑ የያዙ ነገሮች በውስጡ የያዘ ፍሳሽ ፤
9. ዘይት፣ ጨዋማ፤ የተቀጣጠለ የሞተር ዘይት ወይም ሳሙና ነክ የሆኑ እና
ሌሎች መስመሩን ሊዘጉ የሚችሉ ወይም ማጣሪያ ጣቢያውን በትክክል እንዳይሰራ ሊያደርጉ የሚችሉ በውስጡ የያዘ ፍሳሽ፡፡ …
29/03/2025
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን
የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አፈጻጸም መመሪያ
መጋቢት/2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የአዲስ አበባ ከተማ የሀገራችን ዋና መዲና የአፍሪካ መቀመጫ የአለም አቀፍ ድርጅቶችና ኤምባሲዎች የሚገኙበት ከተማ እንደመሆኗ መጠን የከተማዋ የህዝብ ብዛት እድገትም ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እየጨመረ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ የአካባቢ ብክለት በከተሞች አካባቢ እጅግ የከፋ ችግር ሆኖ በመታየቱ፤
ይህንን ችግር ለማቃለል የከተማው አስተዳደር ያወጣውን የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር ደንብ ለመተግበር ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈፃሚ አካላት እንደገና ለማደራጀት ሥልጣንና ተግባራቸውን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 74/2014 አንቀፅ 15 ንዑስ አንቀፅ (2) ተራ ፊደል (ሠ) መሰረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡
ክፍል አንድ
1. አጭር ርዕስ
ይህ መመሪያ "የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር…../2014ዓ/ም" ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
2. ትርጓሜ
የቃሉ አግባብ ሌላ ትርጉም የማይሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ መመሪያ ውስጥ፡-
1. “አስተዳደር”ማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው፡፡
2. “ከተማ”፡- ማለት አዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡
3. “ባለስልጣን”ማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከማዕከል እስከ ክ/ከተማ ያለውን መዋቅር ያካተተ ነው፡፡
4. “አካባቢ”፡- ማለት በመሬት ፤በከባቢ አየር፤በአየር ሁኔታና በአየር ንብረት በውሃ በህያዋን ፤ በድምጽ፤ በሽታ፤ በጣዕም በማህበራዊ ጉዳዮች እና በስነ ውበት ሳይወሰን በተፈጥረዊ ሁኔታዎች ወይም በሰው አማካነኝነት ተሻሽለው ወይም ተለውጠው የሚገኙ ነገሮች በጠቅላላ ያሉበት ቦታ እንዲሁም መጠናቸው ወይም ሁኔታቸው የሰው ወይም የሌሎች ሕዋን በጎ ሆነታና የሚነኩ መስተጋብሮቻቸው ድምር ነዉ፡፡
5. “በካይ” ማለት ፍሳሽ፣ ጠጣር ወይም ጋዝ የሆነ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ፡
ሀ) ያረፈበትን የአካባቢ ክፍል ጥራት በመለወጥ ጠቀሜታ የመስጠት አቅሙን የሚያጓድል፤
ለ) በሰው ጤና ወይም በሌሎች ህያዋን ላይ ጉዳት የሚያደርስ ወይም ሊያደርስ የሚችል መርዝን፣ ክርፋትን፣ ጨረርን፣ ድምጽን፣ ንዝረትን፣ ሙቀትን ወይም ሌላ ክስተትን የሚያመነጭ ማንኛውም ነገር ነው ፡፡
6. “ቆሻሻ”፡-ማለት ተጠቅመንበት ያለፈ ሆኖ በአካባቢ ወይም በሰው ደኀንነት ወይም ጤና ላይ ጉዳት ያደርሳል ተብሎ የሚታመን ማንኛውም ነገር ነው፡፡
7. “አደገኛ ቆሻሻ”፡- ማለት ተፈላጊነት የሌለው ሆኖ በአካባቢው ወይንም በሰው ድህንነት ወይም ጤና ላይ ጉዳት ያደርሳል ተብሎ የሚታመን ማንኛውም ነገር ነው ፡፡
8. “አደገኛ ነገር”፡- ማለት በሰው ጤና ወይም በአካባቢ ላይ ጉዳት የሚያደርስ ጠጣር፣ፈሳሽ ወይም ረቂቅ ህዋስ ነው፡፡
9. “መልቀቅ”፡- ማለት በውል ታስቦም ይሁን ሳይታሰብ በካይን ወደ ማንኛውም የአካባቢ ክፍል መጨመር ነው፡፡
10. “አስወጋጅ”፡- ማለት በአደገኛ ቆሻሻ ማስወገድ ስራ ላይ የተሰማራ ማንኛውም ሰው ማለት ነው፡፡
11. “አመንጪ”፡- ማለት ማንኛውም ቆሻሻ የሚያመነጪ ሰው ወይንም ድርጅት ሲሆን አመንጪው ባልታወቀበት ሁኔታ አደገኛ ቆሻሻውን በማወቅ ወይንም ባለማወቅ በይዞታው ስር አድርጎ የሚገኝ ነው ፡፡
12. “ጉድፍ”፡- ማለት የጠትሙስ ስባሪ፣ የብረት ፣ የሲጋራ፣ የፕላስቲክ ወይም የወረቀት ቁርጥራጭን፣ የጨርቅ እራፊን፣ የምግብ ትራፊን እና የእፅዋት ቅሪትን ጨምሮ የተጣለበትን ቦታ ውበት ወይም ንፅህና የሚያሳጣ የሚጠቅምም ይሁን የማጠቅምም ማንኛውም ነገር ነው ፡፡
13. “ሰው” ማለት የተፈጥሮ ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው ማለት ነው፡፡
14. በዚህ መመርያ በወንድ ፆታ የተገለጹ አገላለጾች ለሴት ጾታም ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡
3. የተፈጻሚነት ወሰን
ይህ መመሪያ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክልል ውስጥ በሚገኙአካባቢ ሊበክሉ የሚችሉ ነገሮችን በማመንጨት ወይም በመልቀቅ በአካባቢ ደህንነት ላይ ብክለት እና ሌሎች አሉታዊ ተጽዕናዎችን ሊያስከትሉ የሚችሉና ይችላሉ ተብለው በሚገመቱ ሁሉም ፋብሪካዎች፤ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡
4. ዓላማ
1. ግልጽ የስራ መመሪያ በማውጣት የአካባቢን ብክለት አደጋን በተሟላ ሁኔታ በመጠበቅ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹና ተስማሚ የመኖሪያና የስራ አካባቢ ማድረግ፤
2. የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር ተግባርን ፍትሃዊና ተጠያቂነት ያለበት ግልጽና ቀልጣፋ አሰራር በመዘርጋት፤ አስቀድሞ በመከላከል ላይ ማተኮርና ተበክሎ ሲገኝም መርህን መሰረት በማድረግ አጥፊዎችን ተጠያቂ ማድረግና የደረሰውን ጉዳት ወደ ቀድሞ ሁኔታ የሚመለስበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡