22/09/2026
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት 1ኛ የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ባለ ሰምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ።
ዜና፣መጅሊስ፣መስከረም 12/2019 ዓ.ል. አ.አ
በጠቅላላ ጉባኤው ላይ በክብር እንግድነት የአዲስአበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት ሥራ አስፈፃሚና የልማትና ማህበራዊ ጉዳይ አስተባባሪ ኡስታዝ አዩብ ደርባቸው ፣የከፍተኛም/ቤቱ ሥራ አስፈፃሚና የሐጂ ዘርፍ ተጠሪ ሸህ ኑር ሁሴን ሙስጠፋ፣የከፍተኛ ም/ቤቱ ሥራ አሰፈፃሚና የህግ ዘርፍ ተጠሪ ሸህ ዙቤር ሪድዋን፣የከፍተኛ ም/ቤቱ ስራ አሰፈፃሚና የፕሮጀክት ማስተባበሪያ ሀላፊ ኡሰታዝ ሁሴን ሰኢድ፣የቂርቆስ ክ/ከተማእና የወረዳ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት አመራሮች የቅላላ ጉባኤ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የእለቱን ጠቅላላ ጉባኤ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈቱት የቂርቆስ ክፍለ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ስራ አስፈፃሚ ኡስታዝ ሙሀመድ ሙስጠፋ በምርጫ ወደ ሀላፊነት ከመጣን በኋላ የመዋቅር ዝርጋታ በማድረግ ለክፍለ ከተማው ሙስሊም ማህበረሰብ የሚጠቅሙ ተግባራትን ለማከናወን ተሞክሯል ሲሉ ተናግረዋል::
ዋና ስራ አስፈፃሚው እንዳሉት በማህበራዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርገን በመስራት የአቅመ ደካሞችን ቤት መገንባት፣ የኡድህያ መርሀግብር ማከናወን እንዲሁም የማዕድ ማጋራት ያከናወንን ሲሆን በክፍለ ከተማችን የሚገነቡ ኢስላማዊ ተቋማት የሙስሊሙን እሴት እና የከተማዋን ገፅታ ባማከለ መልኩ እንዲሠሩ ክትትል እያደረግን በቀጣዩ የሥራ ዘመን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትብብር እንሰራለን ብለዋል።
በክብር እንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት አመራር እና ሥራ አስፈፃሚ ኡስታዝ አዩብ ደርባቸው የእለቱ ጉባኤ ባለፈው የስራ ዘመን የሰራችሁትን ስራ የምትገመግሙበት እንዲሁም የቀጣዩን አመት እቅድ የምትወያዩበት ና ውሳኔ የምታስተላልፉበት እድል የሚፈጥር ነው በማለት ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን ተመኝተዋል። :
የከፍተኛ ም/ቤቱ አመራር የሆኑት ሸህ ዙበይር ሬድዋን ለጉባኤው አባላት ከፍተኛ ምክር ቤቱ ባሳለፍነው አመት የተለያዩ ህጎችን እና መመሪያዎችን ሲያወጣ መቆየቱን አስታውሰው በዘንድሮ አመት የወጡት ህጎችን መሰረት አድርገን ውጤታማ ስራ የምንሰራበት መሆን አለበት ብለዋል።
የከፍተኛ ምክር ቤቱ የስራ አስፈፃሚ አባል እና የፕሮጀክት ክፍል ተጠሪ ኡስታዝ ሁሴን ሰኢድ ይህ ጉባኤ ከፍተኛ ምክር ቤቱ የተለያዩ ህጎችን ባፀደቀ ማግስት የሚካሄድ መሆኑ የተለየ የሚያደርገው ሲሆን የወጡት እቅዶች ስራችንን በተሻለ መልኩ ለመስራት ያግዛል ሲሉ ገልፀዋል::
የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ መጅሊስ ዋና ፀሀፊ የነበሩት ሸህ ሁሴን በሽር ተቋምን ተረክቦ ማስተዳደር ትልቅ ሀላፊነት እንደሆነ አንስተው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ መጅሊስን የተረከቡ አመራሮች የተሻለ ነገር እንዲሰሩ የሁላችንም ድጋፍ ሊጨመርላቸው ይገባል ብለዋል::
በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ክፍለ ከተማዎችን በመወከል የተገኙት እና መልእክት ያስተላለፉት ኡስታዝ አብዱራዛቅ ሙሀመድ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ትልቅ ሀላፊነት ያለበት መጅሊስ እንደሆነና የመንግሰት ትላልቅ ፕሮጀክቶች የሚከናወኑበት እንደመሆኑ የክፍለ ከተማው መጅሊስ ከመንግሥት ጋር በመሆን የከተማውን ገፅታ በሚያጎሉ የልማት ስራዎች ላይ መሳተፍ ይኖርበታል ብለዋል::
በጠቅላላ ጉባኤው የ2018 ዓ.ል የስራ ፈፃፀም ሪፖርት በክፍለ ከተማው መጅሊስ የስራ አስፈፃሚ አባል ኑር አህመድ መንሱር የ2019 ዓ.ል የስራ እቅድ የአስተዳደራዊ ጉዳይ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ኢስሀቅ አብዱልአዚዝ እንዲሁም የኦዲት እና ኢንስፔክሽ የ2019 እቅድ በፅሁፍ ቀርበዉ ሰፊ ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ሦስቱም አጀንዳዎች የጠቅላላ ጉባኤ አባላት በግብዐትነት ያቀረቡት ሀሣብን ጨምሮ በሙሉ ድምፅ ፀድቀዋል።
በጉባኤው ማጠቃለያ ላይም የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ባለ 8 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ጉባኤው በስኬት ተጠናቋል:
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት