03/06/2026
የአዋሽ ከተማ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት
ሕዝቡ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነቱን በተግባር አረጋግጧል!
ግንቦት 24/2018 ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ በመውጣት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አዲስ ታሪክ ፅፈዋል። ይህ ታላቅ ሕዝባዊ ንቅናቄ የሀገሪቱን የዲሞክራሲ ጉዞ ለማፅናትና ለማስቀጠል ያለውን ፅኑ ፍላጎት በግልፅ ያሳየበት ታሪካዊ አጋጣሚ ሆኖ ይመዘገባል። ሕዝቡ የምርጫ ካርዱን በጥንቃቄ አስቀምጦ በመያዝ በምርጫዉ እለት ድምፅ በመስጠት ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነቱን በተግባር አረጋግጧል።
የፖለቲካ ሥልጣን ምንጭ ሕዝብ ብቻ መሆኑንም ዳግም ለመላው ዓለም በማሳየት፣ ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ ተችሏል። በዚህ ታሪካዊ ሂደት ውስጥ ዋነኛውና ብቸኛው አሸናፊ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ሀገራችን ኢትዮጵያ ብቻ ናቸው። መራጩ ሕዝብ ሳይሰለች ከነጋት 10:00 ሰአት ጀምሮ ረጅም ሰልፎችን በመያዝ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ድምፁን የሰጠው የፓርቲዎችን ድል ለመወሰን ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ክብር ከፍ ለማድረግ ነው። እናቶች፣ አባቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ እድሜ ጠገብ አዛዉንቶች፣ ሙሽሮች ሳይቀሩ በነቂስ ወጥተው ዲሞክራሲን ለማፅናት ያሳዩት ትዕግስት የኢትዮጵያን ብሔራዊ አንድነትና ጥንካሬ ለዓለም ያሳየ ታላቅ የድል ምዕራፍ ነው።
የዘንድሮው የምርጫ ሂደት ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ፣ ስልጡን እና ፍፁም ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መጠናቀቁ ለሀገራችን ትልቅ የሞራል ድል ሲሆን ሕዝቡ ያሳየው የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል፣ መቻቻልና እርስ በርስ የመከባበር እሴት ኢትዮጵያን ሊከፋፍሉና ሊያዳክሙ ለሚፈልጉ ሀይሎች ሁሉ ግልጽ ምላሽ የሰጠ ታሪካዊ ድል ነው። ይህ ስልጡን የዲሞክራሲ ልምምድ አካሄድ ኢትዮጵያ በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ረገድ የደረሰችበትን ጀረጃ በተግባር ያሳየና የሀገሪቱን ገጽታ በዓለም መድረክ ከፍ ያደረገ ልዩ ክስተት ነው።
ይህ ምርጫ ለአዲሲቷና ለበለፀገችው ኢትዮጵያ ጠንካራ መሰረት በመጣል ለነገዋ የበለፀገችና የተረጋጋች ሀገር ጠንካራ መሰረት የጣለ ታላቅ የስኬት ምዕራፍ ነው። 7ኛዉ ጠቅላላ ምርጫ የልዩነት ሳይሆን የኅብረት፣ የብጥብጥ ሳይሆን የሰላም መገለጫ በመሆኑ የሀገሪቱን የነገ ተስፋ ብሩህ አድርጎታል።
በመጨረሻም በተለያዩ ጫናዎች እና ፈተናዎች ሳይበገሩ ድምፄ ዋጋ አለዉ በማለት በታላቅ ሀገራዊ ክብር ፀንተዉ በመቆም በትዕግስት እስከ ሌሊት ተሰልፈው ድምፃቸውን ለሰጡ እና የኢትዮጵያና ህዝቦቿን ታላቅነት በተግባር ላገዘፉ ዜጎች ሁሉ ታላቅ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል።
ኢትዮጵያ መርጣለች!

26/05/2026