08/10/2026
የዳንግላ ወረዳ ም/ቤት የ2019 ጥቅል በጀት 1.5 ቢሊዮን ብር አድርጎ አፀደቀ።
መስከረም 28/2019ዓም ዳንግላ ወረዳ ኮሙኒኬሽን
የዳንግላ ወረዳ ም/ቤት 4ኛ ዙር 43ኛ መደበኛ ጉባኤዉ በሁለት ተከታታይ ቀናት ቆይታው የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ሲመክር ቆይቶ ጉባኤውን አጠናቋል።
በም/ቤቱ 4ኛ ዙር 43ኛ መደበኛ ጉባኤዉ የወረዳውን የ2019 ዓ.ም በጀት አመት ለ26 የበጀት መስሪያ ቤቶች የሚደለደለውን በጀት 887ሚሊዮን 699ሽ 324 ብር ሆኖ ም/ቤቱ አጽድቋል።
ከዚህም ውስጥ ፦ለስራ ማስኬጃ 86ሚሊየን 135ሽ231 ብር ፣ለደመወዝ 769ሚሊየን 950ሽ 514 ብር ፣ለካፒታል መደበኛ በጀት 31ሚለየን 613ሽ 579 ብር እንዲሁም ከህብረተሰብ ተሳትፎ ለካፒታል ስራዎች 179ሚሊየን 914ሽ671 ብር በአጠቃላይ የወረዳው ጥቅል በጀት #1ቢሊየን 518 ሚሊየን 330ሽ 324ብር አድርጎ ም/ቤቱ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል ።
በጀቱ ከመንግሥት ግምጃቤት፣ ከክልል ድጎማ ፣ ከወረዳው የሚሰበሰብ ገቢ ፣ ከውስጥ ገቢ እና ከማህበረሰብ ተሳትፎ የሚገኝ መሆኑን የወረዳው ገንዘብ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ይበልጣል መኳንንት ገልጸዋል።
የዜጎች ሁለንተናዊ ልማት እንዲረጋገጥ የተለያዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶችን አቅዶ ተፈጻሚ ለማድረግ በጀት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የወረዳውን የገቢ አሰባሰብ ስርዓት ማሳደግና በቅንጅት በመስራት በጀቱን ከተለያዩ አላስፈላጊ ወጪዎች በመቆጠብ በተገቢዉ ለታለመለት ዓላማና ተግባር ብቻ መጠቀም እንደሚገባም አቶ ይበልጣል ጠቁመዋል።
ምክር ቤቱ በሁለት ተከታታይ ቀናት ቆይታው በ2018 በጀት አመት በወረዳው የታዩ ውስንነቶች እንዲፈቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
የምክር ቤት አባላት ካነሷቸው ጥያቄዎች በዋናነት ፦በመንገድ ፣በትምህርት ፣በጤና፣በእንሰሳት ሀብት ልማት ፣ በግብርና፣ በስራ እድል ፈጠራ፣በገንዘብ ፣ በህብረት ስራ ማህበራት ፣በሲቪል ሰርቪስ አገልገሎት አሰጣጥ እና በሌሎች ተቋማት የታዩ ውስንነቶች ተነስተው በጥልቀት ተመክረዋል ።
ለተነሱ ጥያቄዎችም አስፈጻሚ አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷቸው በ2019 በጀት አመት በትኩረት እንደሚሰሩ የጋራ መግባባት እና የቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ አረጋግጠዋል ።
የዳንግላ ወረዳ ተቀዳሚ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ወሃቤ ጸጋ በም/ቤቱ በማጠቃለያ መርሃግብር እንዳሉት ወረዳው በ2019 በጀት አመት በተገኘው አንጻራዊ ሰላም በመጠቀም በርካታ የልማት እና የሰላም ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
ይሁን እንጂ አሁንም በተፈጠረው ግጭት ማህበረሰቡ ከመንግሥት ጋር ለመገናኘት የጸጥታ ችግሮች እንቅፋት ሆነዋል ብለዋል።
በ2019 በጀት አመት ህግ እንዲከበር ፣ ስርዓት አልበኝነት ለመግታት ፣ የአርሶ አደሩን ስቃይ እና እንግልት ለማስቀረት በትኩረት ይሰራል ያሉት አቶ ወሃቤ የም/ቤት አባላት ፣የወረዳው አመራሮች እና የመንግስት ሰራተኛው ከጸጥታ አካላት ጎን ሆነው መስራት ይገባል ብለዋል።
የዳንግላ ወረዳ በእንሰሳት ሃብት ልማት፣በግብርና ፣በኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ፣በማዕድን እና በሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶች ተዝቆ የማያል እምቅ ጸጋ ባለቤት በመሆኑ በቁርጠኝነት መስራት አለብን ብለዋል።
በመጨረሻም በወረዳው የተመደበው በጀት በአግባቡ እና በቁጠባ መጠቀም፣ገቢ አሰባሰብን ማዘመን፣ በግብዓት አቅርቦት ቀልጣፋ አገልግሎት ለአርሶ አደሩ መስጠት ፣የኢኒሼቲቭ ተግባራት መፈጸም፣የግዢ ግልጽነትን ማስፈን እና ሰላምን ማረጋጋት ላይ ወረዳው በትኩረት መስራት እንዳለበት የም/ቤት አባላት አሳስበዋል።