13/11/2026
የሜላ–ጵዝጎ 23 ኪ.ሜ የገጠር ጠጠር መንገድ ግንባታ በተፋጠነ ሁኔታ እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለሥልጣን የሣውላ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ የተከበሩ አቶ ፍጹም ጳውሎስ ገለጹ
ህዳር 02/2019 ዓ.ም
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጎፋ ዞን በዛላ እና በደምባ ጎፋ ወረዳዎች የሚገኙ 9 ቀበሌዎችን የሚያስተሳስረው የ23 ኪ.ሎ ሜትር የሜላ–ጵዝጎ የገጠር ጠጠር መንገድ የግንባታ ሂደት በመስክ ምልከታ ተገምግሟል።
የመስክ ምልከታው ዋና ዓላማ የፕሮጀክቱን የአሁኑን የአፈጻጸም ደረጃ፣ የሥራ ፍጥነትና ጥራት በቦታው በመገኘት መገምገም እና ቀሪ ሥራዎች በተቀናጀ ሁኔታ እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ መስጠት ነው።
በምልከታው ወቅት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የመንገድ አስተዳደርና ጥራት ቁጥጥር ዘርፍ ኃላፊ ክቡር አቶ እልጉ እንጂ እንደገለጹት፣ የመንገዱ ግንባታ በ45 ቀናት ውስጥ በፍጥነትና በጥራት ተጠናቆ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል።
መንገዱ በዛላ እና በደምባ ጎፋ ወረዳዎች ቀበሌዎችን በማስተሳሰር የአካባቢውን የመጓጓዣ፣ የገበያና የምርት ትስስር እጅግ የሚያጠናክር በመሆኑ፣ ግንባታው መጠናቀቁ የማኅበረሰቡን አጠቃላይ የልማት ተጠቃሚነት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድገው ተገልጿል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለሥልጣን የሣውላ ዲስትሪክት ዋና ሥራ አስኪያጅ የተከበሩ አቶ ፍጹም ጳውሎስ በበኩላቸው፣ የመንገዱ ሥራ በፍጥነትና በጥራት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ ቀደም ሲል ያጋጠሙ የሥራ እንቅፋቶችን በመሻገር ሥራዎቹን እያፋጠኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የዛላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የተከበሩ አቶ ምስራቅ በላቸው፣ በበኩላቸው «መንገድ የልማት ሁሉ መሠረት ነው» በማለት በዞኑ እየተከናወነ ያለው የመንገድ ሥራ እጅግ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል። በመስክ ጉብኝቱ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም በዝርዝር ተገምግሞ፣ ቀሪ ሥራዎች በተፋጠነ ሁኔታ፣ በተፈለገው ጥራትና በተቀናጀ ክትትል እንዲጠናቀቁ የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
የመንገድ ሥራ ሳይት መሐንዲሶችና ባለሙያዎች በበኩላቸው የፕሮጀክቱ ፣ የመንገድ ጠረጋና ጠጠር ማልበስ ሥራው 95 በመቶ ተጠናቆ የድልድይ ግንባታ እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸዋል። በዚህም መሠረት፡- የኤልሴ ድልድይ የመሠረት ድጋፍ (Abutment) እና የመንገድ መጋጠሚያ ሙሌት (Approach fill) ሥራ ተጠናቆ የጣራ ወይም የወለል ሙሌት (Slab) ሥራ ብቻ እንደሚቀረው፣ የላስቴ እና የማላንጋ ድልድዮች ደግሞ የግንባታ ቁሳቁስ (Material) የማምረትና የማዘጋጀት ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑን አስረድተዋል።
በአጠቃላይ በዛላ እና በደምባ ጎፋ ወረዳዎች የሚገኙ 9 ቀበሌዎችን የሚያስተሳስረው የ23 ኪ.ሜ ሜላ-ጵዝጎ የገጠር ጠጠር መንገድ ግንባታ ቀደም ሲል ያጋጠሙ ችግሮችን በመሻገር፣ በየደረጃው በሚገኙ አመራሮች የተቀናጀ ክትትልና በግልጽ በተቀመጠ አቅጣጫ መሠረት በ45 ቀናት ውስጥ በጥራትና በፍጥነት ተጠናቆ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት ለመስጠት በተፋጠነ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል።
በመስክ ምልከታው ወቅት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የመንገድ አስተዳደርና ጥራት ቁጥጥር ዘርፍ ኃላፊ ክቡር አቶ ኢልጎ እንጂ ፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለሥልጣን የሣውላ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ የተከበሩ አቶ ፍጹም ጳውሎስ፤ የክልሉ መንገዶች ባለሥልጣን ግንባታ ዘርፍ ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ መቅደስ ወልቃ፤ የዛላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ምስራቅ በላቸው፤ የወረዳው አስተባባሪ አካላት፣ እንዲሁም የመንገድ ሥራ ሳይት መሐንዲሶችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።