05/10/2026
የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት አጠቃላይ የግምገማ እና የዕቅድ መድረክ አካሄደ
*****
መስከረም 25/2019 ዓ.ም ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በ2019 የትምህርት ዘመን በተሻለ ለመስራት የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ስራ አስፈፃሚ ከአባላቱ፣ ከዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አግልግሎት እና ከጸጥታ አካላት ጋር ውይይት አደረገ። በመድረኩም የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ ካሰች ፈንታ ተሳታፊዎችን በማመስገን ዝግጅቱ የተጀመረ ሲሆን የባለፈውን የ2018 ዓመት ክንውን በመገምገም እና የ 2019 ዓመት ዕቅድ ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
ውይይቱ ተማሪዎች ከሌሎች አካላት ጋር በቅንጅት የመስራት አቅማቸውን ለማጎልበት እና የዩንቨርሲቲውን የጋራ አላማዎችን ለማሳካት ትልቅ ግብአት አንደሆነ ተገልጿል።
በተጨማሪም በግንኙነት እና በትብብር ስራዎች ላይ ጠንካራ መሠረት ለመጣልና ከተለያዩ የዩኒቨርሲቲው አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችላቸውን ነጥቦች አንስተው ተወያይተዋል።
በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፀጥታና ደህንነት ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዳዊት ሹና የተማሪ ፖሊሶችን እያበረከቱ ላለው ታታሪነት እና ለሠላም ማስከበር ስራቸው ምስጋና አቅርበውላቸው፤ የተማሪ ፖሊሶቹ ከዩኒቨርሲቲው ፖሊስ ጋር በመተባበር የካምፓሱን ጸጥታ በመጠበቅ ላይ ለሚያሳዩት ቁርጠኝነት አድናቆት ችረዋል። ከህብረቱ እና ከተማሪ ፖሊሶች ጋር በጋራ በመሆን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲቀጥል በትብብር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
ሌላው ዘግጅቱን የታደሙት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች አግልግሎት ዲን የሆኑት መ/ር ቦሩ በደያ የተማሪዎችን ህብረት ጥረት አድንቀው ከዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ጋር በመሆን ተማሪዎችን ለመደገፍ ያላቸውን ጽኑ ፍላጎትም ገልጸዋል።
የተማሪዎች ፕሬዚዳንት ተማሪ ካሰችም በበኩሏ ህብረቱ በ2019 ዓ.ም የተማሪዎችን መብት ለማስከበር እና ከዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የተረጋጋ የትምህርት አካባቢ ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆኑን በማንሳት መርሃ-ግብሩን አጠናቀዋል ።
ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ