02/06/2026
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት ተጠናቅቋል - ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
#ጅግጅጋ:- 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በሰጡት መግለጫ÷ በግንቦት 24 ቀን ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ድምጽ ሲሰጥ የዋለው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት ተጠናቅቋል ብለዋል።
በድምጽ ምስጫ ሂደቱ በአዲስ አበባ ከተማ በጣም ረጃጅም ሰልፎች እንደነበሩ አንስተው÷ በሲዳማ፣ ጋምቤላ፣ አማራ፣ ሶማሌ ክልሎች የድምጽ ቆጠራ አለመጠናቀቁን ገልጸዋል።
በዚህም የመራጮች ቁጥር እስካሁን ተጠቃልሎ አለመግባቱን ተናገረዋል።
ቦርዱ የተለያዩ ቅሬታዎች በተለያየ መንገድ ሲያስተናግድ መቆየቱን አንስተው÷ በሕግ ክፍል በኩል በቀጥታ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ የስራ ክፍል አማካይኝነት በቅድመ ማስጠንቀቂያ 6214 ስልክ ቁጥርና በአጭር መልዕክት መቀብያ 7555 የመጡ ጥቆማና ቅረታዎች እንደነበሩ አመልክተዋል።
በዚህም ጥቆማውን በመከተል ከስር ከስር አስፈላጊውን የእርምት ርምጃ ቦርዱ ሲሰጥ መቆየቱን እንዲሁም የማጣራት፣ የማረጋገጥና ማስረጃ ማጠናቀር በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
02/06/2026
የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የውጤት አሰጣጥ የጊዜ ሰሌዳ፦
02/06/2026
ኢትዮጵያውያን መርጠዋል፤ ኢትዮጵያ አሸንፋለች!
#ኢትዮጵያ ከዜጎቿ የፈለገችዉን ኹሉ በፈለገችው ጊዜና ኹኔታ የምታገኝ ሀገር ናት፡፡ ለሀገራቸዉ የተጠየቁትን ሁሉ ለመስጠት ወደኋላ የማይሉ ዜጎች ስላሏት በእጅጉ ኮርታለች፡፡ ከዓድዋ እስከ ሕዳሴ ግድብ፣ ከወገን ለወገን መረዳዳት እስከ አረንጓዴ ዐሻራ የዜጎቿን ተሳትፎ ጠይቃ፣ ከመሻቷ በላይ ተሳትክቶላታል፡፡ ዛሬ የተደገመዉም ይኸው ነው፡፡
ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲን ማንበር፣ በግልጽና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መንግሥትን መምረጥ፣ ሕገ መንግሥታዊነትን ፅኑ መሠረት ማስያዝ ትሻለች፡፡ ለዚህ ደግሞ 7ኛዉን ሀገራዊ ምርጫ እንደ ትልቅ አጋጣሚ መጠቀም አስፈልጓት ነበር፡፡
በምላሹም ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለመራጭነት ተመዝግበው የዛሬዋን ቀን ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡ እነሆ የእናት ሀገር ጥሪን በመቀበል ዜጎች በነቂስ ወጥተው ሲመርጡ ውለዋል፤ ሌሊቱንም አጋምሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ዜጎች ለረዥም ሰዓታት ተሰልፈዉ ድምፅ የሰጡበት ልዩ ምርጫም ነው፡፡
ምርጫዉ እንዳይካሄድ ባዳ እና ባንዳ ተቀናጅተዉ ያልቆፈሩት ጉድጓድ፣ ያልደረደሩት እንቅፋት አልነበረም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ለጠራችው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የማይቻል ነገር አልነበረምና በስኬት ተጠናቅቋል፡፡ ኢትዮጵያውን በሰላማዊ መንገድ መርጠው ኢትዮጵያ አሸንፋለች፡፡
የኢትዮጵያን የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ጥሪ ተቀብሎ ከንጋት እስከ ምሽት በመምረጥ ምላሽ ለሰጠው ሕዝብ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐቱ እንዲጸና እና ዜጎች በሰላም እንዲመርጡ ምቹ ዓውድ ለፈጠሩ የፀጥታ አካላት፣ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በየደቂቃዉ ሲያደርሱ ለነበሩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እንዲሁም የምርጫዉን ሂደት ለመሩ፣ ላስተባበሩ እና ለታዘቡ ሁሉ ኢትዮጵያ ታመሰግናለች፡፡
የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ግንቦት 25 2018፣አዲስአበባ፣ኢትዮጵያ
01/06/2026
ይሄንን ሕዝብ ማገልገል መታደል ነው፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
"ውጣ ውረዶችን አሸንፎ ታሪክ ለሠራው የኢትዮጵያ ሕዝብ" ልባዊ ክብርና ምስጋና አቀረቡ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ታሪካዊ የምርጫ ዕለት ጽናቱን ላሳየውና ተአምር ለሠራው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከልብ የመነጨ ምስጋና አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት፥ "የኢትዮጵያ ሕዝብ አስደናቂም ተአምረኛም ሕዝብ ነው፤ ከፈጣሪ በቀር ሕዝባችንን አሟልቶ ሊያውቅና ሊገመግም የሚችል ማን ነው?" ካሉ በኋላ፣ ሕዝቡ የዳበረ ባህል፣ ሀገር ወዳድና የወል መሻቱን መጠበቅ የሚችል መሆኑን በዘንድሮው ምርጫ ዳግም ለዓለም ማሳየቱን ገልጸዋል።
በዛሬው ታሪካዊ ዕለት የሌሊቱ ብርድና ጨለማ ያላስፈራቸው፣ የቀትሩ ፀሐይና ድንገተኛ ዝናብ ያልበገራቸው፣ እንዲሁም ሠርግ፣ ኀዘንና ወሊድን የመሰሉ ማኅበራዊ ሁነቶች ያላገዳቸው ዜጎች በነቂስ ወጥተው መምረጣቸውን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ረጃጅም ሰልፎች ያላታከታቸው፣ የአካል ጉዳት፣ ሕመም እና እርጅና የሀገር ተስፋን ከመመልከት ያላገዳቸው፣ ጨቅላ ልጃቸውን ማዘል ያላደከማቸውና ከምንም በላይ የጠላት ጩኸትና ማስፈራሪያ ያላስቆማቸው ዜጎች በብዙ ውጣ ውረዶች መካከል ያሳዩት ጽናት ለዴሞክራሲና ለሀገር ሕልውና የተከፈለ በመሆኑ ከልብ የመነጨ ምስጋና እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
ይሄንን ሕዝብ ማገልገል ትልቅ መታደል መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ተመራጮች ያከበራቸውን ሕዝብ መልሰው እንዲያከብሩና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ዋጋ የከፈለውን ይሄንን ሕዝብ በንጽሕና ለማገልገል እንዲበቁ ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
01/06/2026
የኢትዮጵያ ሕዝብ አስደናቂም ተአምረኛም ሕዝብ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ከፈጣሪ በቀር ሕዝባችንን አሟልቶ ሊያውቅና ሊገመግም የሚችል ማን ነው? የዳበረ ባህል፣ ሀገር ወዳድና የወል መሻቱን መጠበቅ የሚችል ሕዝብ መሆኑን በዘንድሮው ምርጫ ዳግም ለዓለም አሳይቷል። በዛሬው ታሪካዊ ዕለት፡-
• የሌሊቱ ብርድና ጨለማ ያላስፈራቸው፣
• የቀትሩ ፀሐይና ድንገተኛ ዝናብ ያልበገራቸው
• ሠርግ፣ ኀዘን፣ ወሊድና ሌሎች ማኅበራዊ ሁነቶች ያላገዳቸው፣
• ረጃጅም ሰልፎች ያላታከታቸው፣
• የአካል ጉዳት ድምጽ ለመስጠት ያልገደባቸው፣
• ሕመም እና እርጅና የሀገር ተስፋን ከማየት ያላገዳቸው፣
• የነገ ሀገር ተረካቢ ጨቅላ ልጃቸውን ማዘል ያላደከማቸው፣
• ከምንም በላይ የጠላት ጩኸትና ማስፈራሪያ ያላስቆማቸው ዜጎች፤
በብዙ ውጣ ውረዶች መካከል (against all odds) ያሳያችሁት ጽናት ለዴሞክራሲና ለሀገር ሕልውና የተከፈለ ነውና ከልብ የመነጨ ምስጋና ይገባቸዋል።
ይሄንን ሕዝብ ማገልገል መታደል ነውና ተመራጮች ያከበራችሁን አክብራችሁ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ዋጋ የከፈለውን ይሄንን ሕዝብ በንጽሕና ለማገልገል ያብቃችሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
01/06/2026
እስከ ለሊቱ 6:00 ተራዝሟል
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በድጋሚ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ከማለዳ 12:00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽት 12:00 ሰዓት የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ የማስፈጸም ሂደት ላይ እንደነበር ይታወቃል። ቦርዱ በሥምሪት ላይ ያለው የክትትል ቡድኑ ያቀረበለትን ሪፖርት ተመልክቶ የሚከተለውን ወሥኗል።
በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 49(4) መሠረት ቦርዱ የምርጫው ነፃና ፍትሐዊነት ይበልጥ ያሰፍናል ብሎ ካመነ የድምፅ መስጫ ሰዓቱን ሊያራዝም እንደሚችል በግልጽ ይደነግጋል። በመሆኑም የድምፅ መስጫ ሂደት ባልተጠናቀቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ድምፅ የመስጠት ሂደቱ እስከ ዕኩለ ለሊት 6:00 ሰዓት ድረስ የተራዘመ መሆኑን ቦርዱ ያሳውቃል።
ማሳሰቢያ: የተመዘገቡ መራጮች መርጠው የተጠናቀቁባቸው ጣቢያዎች ላይ አስፈጻሚዎች የድምፅ ቆጠራ ሂደቱን እንዲያከናውኑ ቦርዱ ያስታውሳል።
01/06/2026
የምርጫ ቦርድ በሰልፍ ላይ ለሚገኙ መራጮች የድምፅ መስጫ ሰዓት መራዘሙን ገለጸ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዕለቱ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ማብቂያ እስከሆነው 12:00 ሰዓት ድረስ በምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው በሰልፍ ላይ የነበሩ መራጮች በሙሉ ድምፅ ሰጥተው እስኪያጠናቅቁ ድረስ ሂደቱ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ይህ ውሳኔ የተላለፈው በምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 4 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ሲሆን፣ ቦርዱ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ የድምፅ መስጫ ሰዓትን ማራዘም እንደሚችል በሕጉ ላይ ተደንግጓል።
01/06/2026
“ስንጨፈጨፍበት የነበረው ቦታ ዛሬ የምርጫ ጣቢያ ሆኖ በነፃነት መርጠንበታል” – የኦብነግ ም/ሊቀመንበር
#ጅግጅጋ:-የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በ7ኛው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ላይ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል።
የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ አህመድ ያሲን ድምፃቸውን ከሰጡ በኋላ በሰጡት አስተያየት÷ ያለፉት 27 ዓመታት ስንጨፈጨፍበት የነበረው ቦታ ዛሬ የምርጫ ጣቢያ ሆኖ በነፃነት መርጠንበታል ብለዋል።
በምርጫው ሂደት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው አብሮ የመሥራት እና የመቀናጀት መንፈስ የሚደነቅ መሆኑንም ምክትል ሊቀመንበሩ ጠቅሰዋል።
ሕዝቡ ያለምንም ማስገደድ እና ጫና የወደደውን እና ያሻውን ፓርቲ በነፃነት እየመረጠ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡
ፓርቲው ለረጅም ጊዜ በምርጫ ሳይሳተፍ መቆየቱን አስታውሰው÷ ዛሬ ለዚህ ታሪካዊ ቀን የበቁት በሀገሪቱ በመጣው አጠቃላይ ለውጥ ምክንያት መሆኑንም አስገንዝበዋል።
01/06/2026
በሶማሊ ክልል በፊቅ ወረዳ ፊቅ ከተማ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እየተካሄደ ይገኛል።
የፊቅ ከተማ ነዋሪዎች እና የተለያዩ ፓርቲዎች ዕጩ ተወዳዳሪዎች ከንጋቱ 12:00 ጀምሮ እየመረጡ የሚገኝ ሲሆን ምርጫው ሰላማዊ ፣የተረጋጋ ና በዴሞክራሲያዊ ሁኔታ እየተካሄደ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
01/06/2026
ለልጆቻችን የነገ ተስፋና እጣ ፋንታ ስንል መርጠናል - የሶማሌ ክልል እናቶች
የሶማሌ ክልል እናቶች ለልጆቻችን የነገ ተስፋና እጣ ፋንታ ስንል ነጻ በሆነ መልኩ ድምጻችንን ሰጥተናል ሲሉ የሶማሌ ክልል እናቶች ገለፁ።
እናቶቹ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገር ይበጃል ለሚሉት ፓርቲ ድምጻቸውን መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ የሕዝብና ሀገርን ጥቅም ያስጠብቃል ያልነውን ፓርቲ ለልጆቻችን መጻኢ እድል ስንል መርጠናል፤ ኢትዮጵያም እየመረጠች ነው ሲሉም ተናግረዋል።