Ministry of Irrigation & Lowlands - Ethiopia

Ministry of Irrigation & Lowlands - Ethiopia

Share

The Ministry of Irrigation & Lowlands (MILLs) is FDRE's Ministry established in 2021.

The Ministry of Irrigation & Lowlands (MILLs), is a government institution established in 2021, mainly to ensure sustainable development by expanding irrigation infrastructure and to improve the lives of citizens living in lowland areas.

Photos from Ministry of Irrigation & Lowlands - Ethiopia's post 01/06/2026

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ) በበሻሻ ድምፅ ሰጡ

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በትውልድ ቀያቸው በሻሻ ድምፅ ሰጥተዋል።

Photos from Dr. Abraham Belay-ዶ/ር አብርሃም በላይ's post 01/06/2026
28/05/2026

ስለድምፅ አሰጣጥ ሂደት መረጃ !!

1. እያንዳንዱ መራጭ ድምጽ ለመስጠት ወደ ምርጫ ጣቢያ ሲሄድ የመራጮች ምዝገባ መታወቂያ ካርዱን ለምርጫ ጣቢያው የምርጫ አስፈፃሚዎች ካስረከበ በኋላ/ዲጂታል ከሆነ ካሳየ በኋላ/ የምርጫ አስፈፃሚዎቹ የመራጩን ማንነት ባቀረበው ማስረጃ ይለያሉ፡፡

2. የመራጩ ማንነት ከተለየና ቀደም ሲል ያልመረጠ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ በመራጮች መዝገብ ውስጥ ለፊርማ በተዘጋጀው አምድ ላይ እንዲፈርም ይደረጋል፡፡

3. መራጩ በመዝገብ ላይ ከፈረመ በኋላ አውራ ጣቱን፣ አውራ ጣት ከሌለው ማንኛውንም ሌላ ጣት በተዘጋጀው የማይለቅ ቀለም እንዲቀባ ከተደረገ በኋላ የድምፅ መስጫ ወረቀት ተሰጥቶት ወደ ምስጢር ድምፅ መስጫው ክፍል ይገባል፡፡

4. መራጩ ወደ ምስጢር ድምጽ መስጫው ክፍል ገብቶ የሚመርጠው እጩ መለያ ምልክት በሚገኝበት ባለአራት ማዕዘን ቦታ ላይ ምልክት ካደረገበት ወይም በጣት አሻራው ከፈረመበት በኋላ የድምጽ ማስጫ ወረቀቱን አጥፎ በታዛቢዎች ፊት ለፊት በቅርብ እይታ በግልጽ ስፍራ በተቀመጠው የድምፅ መስጫ ሳጥን ወይም ኮሮጆ ውስጥ ይከታል፡፡

5. የማያነቡና የማይፅፉ መራጮች ከጣቶቻቸው አንዱን ለዚህ በተዘጋጀው ቀለም ከነከሩ በኋላ ከሚመርጡት ዕጩ መለያ ምልክት ትይዩ በሚገኘው ባለ አራት ማዕዘን ክፍት ቦታ ላይ የጣት አሻራቸው እንዲያርፍ በማድረግ ድምፅ ይሰጣሉ፡፡

6. መራጩ የተሰጠውን የድምፅ መስጫ ወረቀት ባግባቡ ሳይጠቀምበት የቀረ ወይም የተበላሸበት እንደሆነ ይህንኑ መልሶ በምትኩ ሌላ በመቀበል ድምፅ ለመስጠት ይችላል፡፡

7. የምርጫ ጣቢያ ኃላፊ ተበላሽቶ ተመላሽ የተደረገውን የድምፅ መስጫ ወረቀት የተለየ ምልክት ወይም የተበላሸ የሚል በጀርባው ላይ አድርጎበት ለዚሁ በተዘጋጀው ሳጥን ውስጥ ይከተዋል፡፡

8. በምርጫ ድምፅ አሰጣጥ ምልክት ለማድረግና የድምፅ መስጫ ወረቀቱን ወደ ድምፅ መስጫው ሳጥን ወይም ኮሮጆ ውስጥ ለመክተት እርዳታ የሚያስፈልገው ማንኛውም መራጭ የሚረዳውን ሰው እራሱ የመወሰን መብት አለው፡፡ ነገር ግን በድጋፍ ፈላጊው የተመረጠው ሰው ዕድሜ 18 አመት እና ከዚያ በላይ ሆኖ እጩ ወይም የእጩ ተወካይ መሆን የለበትም፡፡

9. በምርጫው ዕለት ድምጽ የመስጠት ሂደት ከተጀመረ ሊቋረጥ ወይም ሊቆም አይችልም፡፡ ሆኖም ግን የድምፅ አሰጣጡ ሂደት በተለያየ ምክንያት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ከተቋረጠና ሁኔታው መልሶ መስተካከሉን የምርጫ አስፈፃሚዎች ካመኑ ሁኔታው በቃለ ጉባኤ ተይዞ ወዲያውኑ የድምፅ አሰጣጡ ሂደት ሊቀጥል ይችላል፡፡ በሌላ በኩል የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ የተቋረጠበት ሁኔታ ከአቅም በላይ ሆኖ ሊስተካከል ካልቻለ ሁኔታው በቃለ ጉባኤ ተይዞ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ባለበት አንዲቆም ተደርጎ አጠቃላይ ሁኔታው ለምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት ሪፖርት ይደረጋል፡፡ በዚህ ሁኔታ የተቋረጠ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ቦርዱ በሚወስነው መሰረት በሌላ ጊዜ ይካሄዳል፡፡

10. በድምፅ መስጠት ሂደት የሚቀርብ ተቃውሞን በሚመለከት ድምጽ በመስጠት ላይ ያለ መራጭ የድምጽ መስጫ ወረቀቱን ከመስጠቱ በፊት የእጩ ተወካይ ድምፅ በመስጠት ሂደት ላይ ያለው ሰው የመራጭነት መብት የሌለው ወይም በምርጫ ጣቢያው በመራጭነት ያልተመዘገበ ነው በማለት ተቃውሞ ሊያቀርብበት ይችላል (ሆኖም አቤቱታው እስኪጣራ ድረስ የምርጫ ጣቢያው አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ አቤቱታ የቀረበበት መራጭ በጊዜያዊነት ድምጽ እንዲሰጥ ሊወስን ይችላል)፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አንድ መራጭ የድምፅ መስጫ ወረቀት ቢከለከል እራሱ ወይም ከእጩ ተወካዮች አንዱ ተቃውሞ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ የእጩ ተወካይ ወይም አንድ መራጭ ከላይ ከተገለጹት የመቃወሚያ ነጥቦች ውጭ በምርጫ አስፈፃሚው፣ የእጩ ተወካይ ወይም በሌላ በማንኛውም ሰው አግባብ ያልሆነ ድርጊት በምርጫ ጣቢያው ውስጥ ተፈጽሟል ብሎ ተቃውሞ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ የምርጫ ጣቢያው አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ የቀረበውን አቤቱታ ከተመለከተ በኋላ ተገቢውን ማጣራት አድርጎ አቤቱታ ላቀረበው ሰው ወይም አካል ውሳኔውን ያሳውቃል፡፡

ኢትዮጵያ ትመርጣለች!

Photos from Ministry of Irrigation & Lowlands - Ethiopia's post 28/05/2026

ባለፉት የለውጥ አመታት መንግስት ህዝቡን በማስተባበርና በመምራት እንደሃገር የሚያኮሩን ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ድሎችን አስመዝግቧል፡፡

በእነዚህ በ3ቱም ዘርፎች ለኢትዮጵያ ድል ያስገኘው ታላቁ የኢትዮያ ህዳሴ ግድብ ሃገር በኩራት የምትጠራው ብሄራዊ ፕሮጀክቷ ነው፡፡

ከለውጡ በፊት የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት በዜጎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘ እንደዚሁም ለገንባታው መሳካት ሁሉም የተረባረበበት ሆኖ ሳለ በፕሮጀክት አመራር ውስንነትና በሌሎች ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ግድቡ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደነበር ይታወሳል ፡፡

የለውጡ ምንግስት ግድቡን ለማጠናቀቅ በነበረው ቁርጠኛ ፍላጎት ምክንያት የነበሩ ችግሮችን ፈቶ ተስፋ በመስጠት መላውን ኢትዮጵያውያንን ዳግመኛ በማስባበሩ ኢትዮጵያ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨርሳ ሪቫን ቆርጣለች፡፡

ለኢትዮጵያውያን ይህ የሕዳሴ ግድብ የኩራት ምንጭ፣ በዓለም መድረክ ደግሞ በጽኑ መሠረት ላይ እንድትቆም ያደረጋትም ነው።

የውጡ መንግስት የግድቡን ግንባታ እና ተያያዥ ጉዳዮች በቅርብት በመምራቱ ይህ የሕዳሴ ግድብ ሕዝቦቿን በእኩል ስሜት እና መንፈስ አንድ አድርጎ ያነሳሳ ፕሮጀክት ሊሆን ችሏል፡፡

ይህ ግድብ አገሪቱ ከምታመነጨው ግማሽ በላይ የሆነ የኤሌትሪክ ኃይል፣ 5100 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ሲሆን፣ ሚሊዮኖችን የኤሌትሪክ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ታሳቢ ተደርጓል።

መንግስት በኢነርጂው ዘርፍ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ የአይሻ እና የአሰላ ንፋስ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ በአውሮፓውያኑ 2030 ቢያንስ 90 በመቶ የሚሆነው ሕዝባችንን የኤሌትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ ይገኛል፡፡

Photos from Ministry of Irrigation & Lowlands - Ethiopia's post 27/05/2026

ኢትዮጵያ እንድትመክር እድል ተፈጥሯል!!

በኢትዮጵያ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ ፣ በተለዩ አጀንዳዎች ላይ ሀገራዊ ምክሮችን በማካሄድ፣ ምክረ ሀሳቦችን በማቅረብ እና ለተግባራዊነቱም የመከታተያ ስርዓ በመዘርጋት ለሀገራዊ መግባባት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽንን አቋቁሟል፡፡
ሀገራዊ ምክክር በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የሀሳብ ልዩነቶች ሲፈጠሩ፣ በከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ወቅት፣ ከጦርነት በኋላ በተከሰቱ ሁኔታዎች ወይም ሰፊ የፖለቲካ ሽግግሮች ውስጥ ባሉ በርካታ ባለድርሻ አካላት መካከል መግባባት ለመፍጠር የታለመ በሀገራዊ ባለቤትነት የተያዘ ግልጽ የሆነ ዓላማና ግብ ያለው የምክክር ሂደት ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ በበኩሉ ሀገራዊ ምክክር ማለት በአዋጁና የኮሚሽነሮች ምክር ቤት በሚያወጣው መመሪያ መሠረት በሚለዩ አጀንዳዎች ላይ በተለያዩ አካላት ውይይት እንዲደረግባቸው የኮሚሽኑ ምክር ቤት በፌደራልና በክልሎች የሚያመቻቸው ውይይቶች እንደሆኑ አብራርቷል፡
ኮሚሽኑም በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተጠሩ ልዩነቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በመለት እና ውይይቶቹ የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በመለየት ምክክር እንዲደረግባቸው የማመቻቸት፤የሚካሄዱት ሀገራዊ ምክክሮች አካታች፣ ብቃት ባለውና ገለልተኛ በሆነ አካል የሚመሩ፣ የአለመግባባት መንስዔዎችን በትክክል በሚዳስስ አጀንዳ የሚያተኩሩ፣ ግልፅ በሆነ የአሠራር ሥርዓት የሚመሩ እና የምክክሮቹን ውጤቶች ለማስፈፀም የሚያስችል ዕቅድ ያላቸው እንዲሆኑ በማድረግ ውጤታማ የሆኑ ሀገራዊ የምክክር ሂደት ተግባራዊ የማድረግ ከተሠጡት ሃላፊነቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተቋቋመበትን ግብ ለማሳካት የዝግጅት፣ የምክክር ሂደት እንዲሁም ትግበራና ክትትል አሉት፡፡ በርካታ ምእራፎችን አልፎ አሁን ላይ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት አጀንዳ ሲያሰባስብ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ ኮሚሽኑ በዚህ ሂደት በሀገራችን ኢትዮጵያ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ባልተግባቡባቸው እጅግ መሠረታዊ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የምክክር አጀንዳዎቻቸውን እንዲሰጡ መደላድል ፈጥሯል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ኮሚሽኑ የተሰበሰበውን አጀንዳ አጠናክሮ እና ረቂቅ ቀርፆ በማጠናቀቅ በምክክር ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው ያሻል ያላቸውን አዘጋጅቷል፡፡

Photos from Ministry of Irrigation & Lowlands - Ethiopia's post 27/05/2026

"በምሥራቅ ቦረና ዞን እየታየ ያለው የግብርና ትራንስፎርሜሽን፤ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል ለምታደርገው ጉዞ ትልቅ ማረጋገጫ ነው!" ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ርነ ዐቢይ አሕመድ

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ () "በምሥራቅ ቦረና ዞን እየታየ ያለው የግብርና ትራንስፎርሜሽን፤ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል ለምታደርገው ጉዞ ትልቅ ማረጋገጫ ነው" ሲሉ ገለጹ።
‎ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ባሰፈሩት መልዕክት፣ “በዚህ ወቅት ብቻ ታታሪ አርሶ አደሮቻችን ከ176 ሺህ 223 ሄክታር በላይ መሬት በማልማት፣ ከ3.1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚያገኙ ይጠበቃል” ብለዋል።

ከ101 ሺህ በላይ አባወራዎችን እና እማወራዎችን በማሳተፍ እና ዘመናዊ ትራክተሮችን በመጠቀም፣ በተደራጀ የክላስተር እርሻ አማካኝነት እምቅ አቅማችንን ወደ ምርታማነት እየቀየርን እንገኛለን ሲሉም አክለዋል።
በምሥራቅ ቦረና ዞን ሊበን ወረዳ ከሚገኙት ሰፋፊ የስንዴ ክላስተሮች ጀምሮ እስከ ዋና ዋናዎቹ የጤፍ፣ የበቆሎ እና የቦሎቄ ምርቶች ድረስ የሚታዬው ውጤት፤ የሀገር ውስጥ የምግብ አቅርቦታችንን የማረጋገጥ ጉዞ ላይ ለመገኘታችን ሕያው ምስክር እንደሆነ ነው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

27/05/2026

ለእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1447ኛው የዒድ-አል-አድሃ ( ዓረፋ) በዓል በሰላም አደረሳችሁ!!

26/05/2026

ለመላ እስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለዒድ አል አደሃ አረፋ በዓል በሰላም አደረሳቹ !!

ዒድ ሙባረክ !!

26/05/2026

“ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም!!” በኢትዮጵያ

ባለፉት የለውጥ አመታት መንግስት እጅግ ስር የሰደዱና ውስብስብ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት፣ ለበርካታ ዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲንከባለሉ የመጡ፣ ሃገር የምትጠገን የማትመስልባቸው በርካታ ስብራቶችን ለመጠገን የሚያስችሉ ከእሳቤ ጀምሮ በተግባር የተደገፉ ስራዎችን መንግስት በቁርጠኝነት ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ሃገርን ከተረጂነትና ከልመና የሚያላቅቁ፣ ትውልዱ ቀና ብሎ እንዲሄድ የሚያግዙ፣ ፈጣንና ውጤታማ ስራዎች ተጀምረዋል፡፡ አስደናቂ ውጤትም እያስገኙ ነው። ከእነዚህ ተግባራት አንዱ ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም ኢኒሼቲቭ ነው::

እሳቤው በምግብ ሉዓላዊነት ማዕቀፍ ውስጥ የሰብአዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን በሁለት ዓመታት (2017-2018) ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህ የመንግስት ደፋር ውሳኔ የታሪክ እጥፋትና ጨዋታ ቀያሪ ሲሆን ለአህጉራችን የብልጽግና ተምሳሌት ያደርገናል፡፡

ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ማዕቀፍ የሚፈጸም ቢሆንም ብሔራዊ ደህንነትን፣ ማህበራዊ ፍትሕን፣ ሰብአዊ መብትን አዎንታዊ ሰላምንና ዘላቂ ልማትን የምናሳካበት እሳቤ ነው፡፡ በተፈጥሮአዊና ሰው-ሰራሽ ምክንያቶች ጊዜያዊ ሰብአዊ ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎችን በሀገር-በቀል አቅም መታደግ ማለት ነው፡፡ ይህም ዜጎቻችን በተቸገሩበት ቅጽበታዊና ነባራዊ ሁኔታ በመንግስት አቅምና በማኀበረሰቡ አጋርነት ለኑሮ የማይመቹ አጋጣሚዎችን መሻገር መቻልን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም (የሰብአዊ ድጋፍ ሉዓላዊነት) እሳቤው ከውጭ አካላት የተንጠራራ፣ ጠባቂነትና ጥገኝነት መላቀቅን በዋናነት ቢያመላክትም ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ፣ ቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞን፣ ክልል በቅድመ-ተከተል አንዱ በሌላኛው የአስተዳደር እርከን ከጠባቂነትና ከጥገኝነት መላቀቅንም የሚያካትት ነው፡፡ በዚሁም የተሟላ ክብራችንን፣ ነፃነታችንንና ሉዓላዊነታችንን በአስተማማኝ ለማረጋገጥ የሚደረግ መደላደል እንደሚፈጥርና የሰላማችንና የልማታችን አካል መሆኑን በመረዳት ነው፡፡

መንግስት ይህንን ሁኔታ በቅድሚያ በመረዳት ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም የሚያሳልጡ የፖሊሲና የትግበራ ሕጎችን በመደንገግና ሀገራዊ የትግበራ ፍኖተ ካርታ በመንደፍ ከማንኛቸውም ጊዜ በላይ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡የሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅምን ለማረጋገጥ የሚሰሩ አምስት ፓኬጆችን ወይንም ዋና ዋና ተግባራት

1. የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ
“ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም” (Humanitarian Relief Sovereignty) አጀንዳ ሲነሳ የታሪክ እጥፋትና ጨዋታ ቀያሪ የሚባለው አስተማማኝ፣ ተደራሽና ተገማች የፈንድ ስርዓት ስለሚረጋገጥ ነው፡፡
መሠረታዊ እሳቤው በሀገር-በቀል አቅም ሰብአዊ ድጋፍን ማሟላት የሚቻለው አስተማማኝ የፈንድ አቅም ሲኖር ብቻ ነው የሚል ነው፡፡
የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ ከዚህ በፊት የመንግስት ሚና ብቻ ሆኖ የቆየውን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር የሁሉም ዜጋና ተቋማት ኃላፊነት በማድረግ አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ መፍጠር ነው፡፡ የግልና የማኀበራዊ ተቋማት በስፋት የሚሳተፉበት ነው።

2. የመጠባበቂያ ምግብ ክምችት
የሰብአዊ ድጋፍ መጠባበቂያ ክምችት እንደ አገር ሊያጋጥመን የሚችለውን የግለሰብ፣ የቤተሰብና የማኀበረሰብ የተራዘመ የእህል እጥረትን ለመቋቋምና ለመሻገር የሚያስችል አቅም ነው፡፡ ይህ የክምችት አቅም በአገር ደረጃ 500,000 ሜትሪክ ቶን እንዲያዝ በመነሻ የተያዘ ሲሆን እያንዳንዱ ክልልና የተዋረድ መዋቅር ድርሻውን ተጋላጭ ቢሆንም ባይሆንም ማከማቸት ይጠበቅበታል፡፡

3. የሰብአዊ ድጋፍ ማከማቻ መጋዘኖች
ሁለተኛው ጉዳይ የሰብአዊ ድጋፍ ምግብ እና ምግብ-ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ማከማቻ መጋዘኖች ናቸው፡፡ ለመጠባበቂያና ለዕለት ደራሽ የሚያዙ ክምችቶች በተሟላ ጥራትና ሁኔታ ሊጠበቁ ይገባል፡፡ የብክለትና ብክነት ሁኔታዎች እንዳያጋጥሙ ከፍተኛ ጥንቃቄና እንክብካቤ ይሻል፡፡ የሙቀትና የቅዝቃዜ ሁኔታ፣ የወለል፣ የጣሪያና የግድግዳው አሠራር ለክምችት አደራደር በሚሆን መንገድ በባለሙያ ምክረ-ሀሳብ መሠረት የሚገነባ ይሆናል።

4. የቅጽበታዊ አደጋዎች አገልግሎት
ወጥ የሆነና በማኑዋል የሚመራ የኦፕሬሽን አቅም፣ የሎጅስቲክስ ክምችትና የአስቸኳይ ጊዜ የማስተባበርና የማቀናጀት ስርዓት ተዘርግቶ ተግባራዊ ማድረግ ይፈልጋል፡፡ በቅጽበታዊ አደጋዎች ወቅት ሁሉም ዜጋና ማንኛውም ተቋም በሚመለከተው አካል በሚሰጠው ምክረ-ሐሳብ መሠረት መተባበርና ድርሻውን መወጣት በህግ መሠረት ይገደዳል፡፡

5. የቤተሰብ ኃላፊነትና የማኀበረሰብ አጋርነት
“ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም” የሕዝባችን መልካም ልምምድ መነሻ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህን መልካምና በጐ ልምምድ ለአደጋ ስጋት ስራ አመራር ተልእኮ ለማዋል የሚጠይቀው በማህበረሰብ ደረጃ የአመራር ስርዓቱን ግንዛቤ ማጎልበት፣ የአደረጃጀት ሚና ማስተዋወቅና አሠራሮችን ማበጀት ነው፡፡

Photos from Ministry of Irrigation & Lowlands - Ethiopia's post 26/05/2026

የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መልዕክት

እንኳን ለ1447ኛው የዒድ አል አድሐ በዓል አደረሰን፣ አደረሳችሁ!

ስለዒድ አል-አድሐ “ዐረፋ” በዓል ስናስብ ሦስት ነገሮች ቀድመው ይታወሱናል። መስዕዋትነት፣ መታዘዝ እና መተጋገዝ። አባት ልጁን ለመስዕዋት ያቀረበበት፤ ልጅ የአባቱን ትዕዛዝ የፈጸመበት፤ ሙስሊሞች የመተጋገዝን እሴት ለዓለም የገለጡበት በዓል ስለሆነ “ዐረፋ” በሕዝበ-ሙስሊሙ ዘንድ ትልቅ ትርጉም አለው።

እስማኤል ለነብዩ ኢብራሂም የመጀመሪያ እና ተወዳጅ ልጃቸው ነው። አላህ (ሱ.ወ.) ይሄን ተወዳጅና የመጀመሪያ ልጅ እንዲሠዉለት ሲጠይቃቸው ታዘዙ እንጂ ወደኋላ አላሉም። ለመታዘዝ የሞከሩት ነገሩ ቀላል ሆኖ አይደለም። ልጅን ያህል ነገር መስዕዋት ማድረግ ምኑ ይቀላል? የአባትነት ስሜት ይተናነቃል። የሰይጣን ሹክሹክታ ይፈታተናል። የቤተዘመድን ወቀሳ እና የጎረቤትን አስተያየት መቋቋምም ይከብዳል። ነብዩ ኢብራሒም፥ በዚህ ሁሉ አጣብቂኝ ውስጥ አንድ ሐቅ ተገልጦላቸዋል። ከራስ ስሜት፣ ከሰው ሐሜት እና ከወዳጅ ፍላጎት የሚልቅ ታላቅ ዓላማ እንዳለ አምነዋል። ስለዚህም በፈተና ውስጥ ጸንተው ቆሙ፤ ቆራጥነታቸውም በተግባር ታየ።

ሀገር የምትገነባው ከራስ ጥቅም በላይ በሚያስቡ እና ከግላዊ ፍላጎታቸው በላይ ለመፈጸም በቆረጡ ዜጎች ነው። የሚወዱትን ነገር እንኳን ሳይቀር ለመሠዋት ዝግጁ የሆኑ ዜጎች ሲበዙላት ሀገር ትበረታለች። እስማኤላቸውን ለመስጠት የማያመነቱ ዜጎች የሞሉባት ሀገር ጽኑ ናት።
የለመድናቸው፣ የምንወዳቸው፣ የራሳችን ገንዘብ ያደረግናቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ። ከእነዚህ የሚበልጥ ዓላማ ግን አለ፤ እሱም “ሀገርነት እና ሉአላዊነት” ይሰኛል። ሀገርነት የሚገነባው ከመውሰድ ይልቅ በመስጠት ነው። ሉአላዊነት የሚጸናው በፈተና ሳይወድቁ በመቆም፤ በወጀብ ሳይናወጡ መጓዝ በመቻል ነው።
የእውነት ኢትዮጵያ ሲያልፍላት ማየት የምንሻ ከሆነ ምኞታችን በተግባር ይገለጥ። የሀገር ኩስመና ካሳሰበን ለግዝፈቷ እንድከም። ያጎበጣትን የድህነት ቋጥኝ ለመሸከም ትከሻችንን እናመቻች። ጎተራዋ እንዲሞላ እጃችን አፈር ይንካ። የጠየመ ገጽዋ እንዲፈካ በሥራ ሌት-ተቀን እንሰለፍ። የተቀማ ክብሯ እስኪመለስ ድርሻችንን እንወጣ። ሀገር መውደዳችን ከልብ ከሆነ መስዕዋት ለመሆን አናመንታ።
የዐረፋ በዓል የመታዘዝና የመስዕዋት ብቻ ሳይሆን የመደጋገፍና የመተጋገዝ በዓል ጭምር ነው። በዐረፋ ከሚከናወነው እርድ አንድ ሦስተኛው ለምስኪኖች እንዲሰጥ የእስልምና አስተምህሮ ያዛል። በዐረፋ ሕዝበ-ሙስሊሙ ደስታና ሐዘኑን እየተጋራ በዓሉን ያከብራል። የዐረፋ እለት አንድም ሰው ተከፍቶ አያሳልፍም፤ በዐረፋ ሰሞን ማንም ሰው ተርቦና ተጠምቶ አያድርም። በዓሉ ትርጉም የሚሰጠው ሕዝበ-ሙስሊሙ ያለውን ተካፍሎ ሲያከብረው ነው። ሰዎች አስቸጋሪ ሁኔታን የሚሻገሩበት መፍትሄው መተሳሰብና መተጋገዝ እንደሆነ ከዐረፋ እንማራለን። ሀገርም ከፈተናዎችዋ በላይ እንድትሆን እኒህ እሴቶች ወሳኝ ናቸው።
ዐረፋ ማኅበረሰባዊ በዓል የሚባለው ለዚህ ነው። ሰዎች በግላቸው የሚያከብሩት አይደለም። ቤተሰቡ፣ ጎረቤቱ፣ ሠፈሩ፣ ከተማው የሚያከብረው በዓል ነው። ያላቸውና የሌላቸው፤ የሚችሉና የማይችሉ፤ ታላላቆችና ታናናሾች፤ ባለ ሥልጣናትና ተራ ዜጎች፣ በአንድነት የሚያከብሩት በዓል ነው። ሰው የሚኖረው በቤቱ ውስጥ አይደለም። በማኅበረሰቡ ውስጥ ነው።
ማኅበረሰባዊ ትሥሥርና ትብብር ለዜጎች እና ለሀገር ደኅንነት ወሳኝ ናቸው። ማኅበረሰባዊ ትሥሥር ስለሌሎች እንድናስብ፣ ስለሌሎች እንድንሠራ እና ስለ ሌሎች ዋጋ እንድንከፍል ያደርገናል። ራሳችንን በሌሎች ጫማ ላይ አቁመን እንድናይ ያስችለናል። የሁላችንም ሰላም፣ የሁላችንም ደኅንነት እና የሁላችንም ጥቅም ካልተከበረ በቀር የግላችንን ብቻ ልናስከብር እንደማንችል ያስገነዝበናል። ስለዚህም ማኅበራዊ ግዴታን እንደ ዜግነት ግዴታ ወስደን እንድንሠራ ያደርገናል።
ምርጫ ማኅበራዊና ዜግነታዊ ግዴታዎችን ከምንወጣባቸው የዴሞክራሲ መገንቢያ መሳሪያዎች መካከል ዋነኛው ነው። ያለ ሕዝብ ተሳትፎ ዴሞክራሲ አይሳካም። ያለ ምርጫም የሕዝብ ተሳትፎ ምሉዕ አይሆንም። የዴሞክራሲያችን መሰረት ጥንካሬው የሚለካው በተሳትፎአችን መጠን ነው።
የዘንድሮ ሀገራዊ ምርጫ ሀገረ-መንግሥታዊ ሥርዓታችን የሚጠነክርበት መሰረት ነው። የዴሞክራሲ ልምምዳችን አንድ ደረጃ ከፍ የሚልበት፤ የቀጣይ ዓመታት የሀገራችንን እጣ-ፈንታ የምንበይንበት፤ ከምንም በላይ ብዝሃ-ድምጽ የሚሰማበት የሕግ መወሰኛ ምክርቤት የምንመሰርትበት ወሳኝ አጋጣሚ ነው። በመሆኑም በዓሉን ስናከብር ዜግነታዊ ግዴታችንን ለመወጣት ብቻ ሳይሆን በካርዳችን ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ለማረጋገጥ እየተዘጋጀን እንዲሆን ጥሪዬን አቀርባለሁ።
በድጋሚ መልካም የዐረፋ በዓል እንዲሆን እመኛለሁ!
ዒድ ሙባረክ!!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ግንቦት 18፣ 2018 ዓ.ም

Want your business to be the top-listed Government Service in Addis Ababa?

Click here to claim your Sponsored Listing.

Location

Telephone

Address


Kazanchis
Addis Ababa