25/09/2026
የኢትዮጵያ ደምና ሕብረሕዋስ ባንክ አገልግሎት በበጀት ዓመቱ 605 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ማቀዱን ገለጸ፡፡
________________________
አዲስ አበባ — የኢትዮጵያ ደምና ሕብረሕዋስ ባንክ አገልግሎት በያዝነው የበጀት ዓመት 605 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ ገለጹ።
አቶ ሃብታሙ ከጤና ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፤ ከተያዘው ግብ ለመድረስ ሰፊ የህዝብ ግንኙነትና የንቅናቄ ሥራዎች ታቅደዋል።
ባለፈው የበጀት ዓመት 476 ሺህ ዩኒት ደም መብሰብሰቡን ያስታወሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ዘንድሮ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ከ100 ሺህ ዩኒት በላይ ብልጫ ያለው ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል። በዚህም መሰረት ከሃምሌ 1/2018 ዓ.ም እስከ መስከረም አጋማሽ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ150 ሺህ ዩኒት በላይ ደም መሰብሰብ ተችሏል።
ሆኖም ከመስከረም እስከ ጥቅምት የመጀመሪያ ሳምንት ባለው ጊዜ ልዩ ልዩ ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላት የሚከበሩበት፣ እንዲሁም በትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ትምህርት ገበታቸው የማይገቡበት ወቅት በመሆኑ በተደራጀ መልኩ ደም ለመሰብሰብ ፈታኝ እንደሚሆን ገልጸዋል።
በተለይም የመስቀልና የኢሬቻ በዓላት በሚከበሩበት በዚህ ወቅት የህብረተሰቡ ትኩረት ወደ በዓላቱ በማዘንበሉ ምክንያት የልገሳ መጠኑ እንዳይቀንስ የተለያዩ የደም ልገሳ ዘመቻዎች እየተካሄዱ እንደሚገኝ አቶ ሀብታሙ አስረድተዋል።
በበጀት ዓመቱ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካትና የደም እጥረትን ለማስወገድ በህብረተሰቡ ዘንድ ስለ ደም ልገሳ ያለው ግንዛቤ እንዲዳብር ሰፊ የህዝብ ግንኙነት ሥራዎችን መስራት፤ደም በስፋት በሚገኝባቸው ቦታዎች በተደራጀ መልኩ የተለያዩ ፎረሞችን ማካሄድ፤ወጣቶችን በስፋት ለማግኘት በሚዲያና በሶሻል ሚዲያ አማራጮች መጠቀም በተለይ ከፍተኛ ተከታይ ያላቸውን የቲክቶክ (TikTok) እና የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎችን እንደ አምባሳደር በመጠቀም ህብረተሰቡን የማንቃት ሥራ በጋራ ለመስራት ዝግጅቶች መጀመሩን አቶ ሃብታሙ ገልፀዋል፡፡።
በመጨረሻም አቶ ሀብታሙ ታዬ፤ በደም እጥረት ምክንያት የዜጎች ሕይወት እንዳይጎዳና የህክምና አገልግሎቱ እንዳይስተጓጎል ህብረተሰቡ ደም በመለገስ የበኩሉን ሰብአዊ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።