28/04/2026
የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቅ/ጽ/ቤት የ9 ወራት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ አካሄደ
"አገልጋይነትን መላበስ መለያችን ሊሆን ይገባል" — አቶ ቤኪ ቱጁ
ሚያዚያ 20/2018 ዓ.ም
የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቅ/ጽ/ቤት የዘጠኝ ወራት ዋና ዋና ተግባራት አፈፃፀም ግምገማ ዛሬ ተካሂዷል። መድረኩን የመሩት የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ቤኪ ቱጁ እንደገለጹት፣ ተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን እያከናወነ ያለው የሪፎርም ስራ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እያሳየ ቢሆንም፣ አሁንም ተገልጋዩ ካለው ፍላጎት አንጻር በቂ አይደለም ያሉ ሲሆን አመራር እና ፈጻሚውም አገልጋይነትን የተላበሱ ቅን የሆኑ እንዲሁም በየዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን የሚፈቱ ባለጉዳይን በአግባቡ በመመሪያና አሰራር መሰረት በቅልጥፍና የሚያስተናገዱ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።
በውይይቱ ወቅት የተነሱ ዋና ዋና ነጥቦች መካከል የተቋሙ ውጤታማነት መለኪያ የአገልግሎቱ ፍጥነት፣ ጥራት እና የተገልጋዩ እርካታ መሆን አለበት።የተገልጋዮች ምልልስና እንግልት ለብልሹ አሰራር በር የሚከፍት በመሆኑ፣ ማንኛውም መስተንግዶ ተገልጋይን ያከበረና ግልጽነት የተሞላበት ሊሆን ይገባል።
በመሆኑም የቀጣይ 70 ቀናት የሚከናወኑ ስራዎችን አቅጣጫ ያስቀመጡ ሲሆን በበጀት ዓመቱ ቀሪ ቀናት ውስጥ ሊሰሩ የሚገባቸውን ስራዎች ቅ/ጽቤቱ በሪፎርም ስራዎቹ የታዩ ውጤቶችን በማጠናከርና ጉድለቶችን በማረም፣ ቀሪ የበጀት ዓመቱ ስራዎችን በላቀ ትጋት ለማከናወን ዝግጁ መሆኑን በመድረኩ ተገልጿል።
12/04/2026
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ፤ እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
የትንሣኤ በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ መዳን ያለውን ፍቅር እስከ መስቀል ሞት የገለጸበትና የሞት ድል የተበሰረበት ታላቅ ዕለት ነው። በመሆኑም በዓሉን ስናከብር በታላቅ ፍቅር፣ በትሕትና እና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባል።
ድጋፍ ለሚሹ ወገኖቻችን ያለንን አጋርነት በተግባር የምንገልጽበት፣ አንዳችን ለሌላችን የደስታ፣ የሰላም እና የአብሮነት ምክንያት የምንሆንበት በዓል እንዲሆንልን እመኛለሁ።
መልካም በዓል!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
09/04/2026
የቦሌ ክተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የጽ/ቤቱ ሠራተኞቹ ማዕድ አጋራ።
ሚያዚያ 01/2018
*****
በሀገር አቀፍ ደረጃ በስፋት እየተተገበረ የሚገኘው የዜጋ ተኮር ተግባራት መካከል አንዱ የሆነው ማዕድ የማጋራት መርሃ-ግብር በዛሬው እለትም በጽ/ቤታችን ተከናውኖ ውሏል።
ይህንን በጎ ተግባር መነሻ ያደረገው የቦሌ ክተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽ/ቤትም መጪውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ ለቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ሰራተኞች ማዕድ አጋርቷል።
ጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ቤኪ ቱጆ በቀጣይም ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል በማለት ሰራተኞች በዓሉን ከቤተሰቦቻቸው ጋር በደስታ እንዲያሳልፉ ለጋሾችን በማስተባበር ድጋፍ መድረጉን ገልጸዋል ።
08/04/2026
የአገልግሎት አሰጣጥን ንቅናቄን በተመለከተ በቦሌ ክ/ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቅ/ጽ/ቤት ውይይት ተደረገ ቀን 29-07-2018 ዓ,ም
በቦሌ ክ/ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቅ/ጽ/ቤት በዛሬው እለት የጽ/ቤቱ ስራተኞች መካከል ውይይት ተደርጓል:: የጽ/ቤቱ ሀላፊ የሆኑት አቶ ቤኪ ቱጆ ባስተላለፉት መልእክት ተቋሙ ከፍተኛ ተገልጋይ የሚበዛበት እና ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች እንደሚሰጡ ጠቁመው ጊዜውን የሚመጥን ጥራት ያለው የሚለካ ተገልጋዩን የሚያረካ አገልግሎት መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል :: አገልግሎቱን እንዳይሳለጥ እና ተገልጋዩ እንዲማረር የሚያደርጉ ምልልሶች እና የሌብነት እና ብልሹ አሰራርን ታግለን መቀነስ እንዳለብን ገልጸዋል::በእለቱም ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት አገልግሎትን አሁን ካለበት ቁመና መሻሻል ያሳየ መሆኑን ከዚህም በይበልጥ መሻሻል እንዳለበት ቁርጠኛ አቋም መያዝ እንዳለበት በመግባባት ተጠናቋል::
02/01/2026
በቦሌ ክ/ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቅ/ጽ/ቤት የባለጉዳይ ቀን በአንድ መዓከል መስተንግዶ በመሰጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን ለአገልግሎት የሚመጡ ባለጉዳዮችን በአሰራር እና በመመሪያው መሰረት አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት እና ምልልስን በመቀነስ የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ አመራሩ በትጋት እየሰራ ይገኛል። ታህሳስ 24/2018 ዓ.ም
26/12/2025
ከቦሌ ብራስ - ኤድና ሞል - ጎላጉል በመገንባት ላይ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የሥራ አፈጻጸም ያለበት ደረጃ ተገመገመ
ግምገማውን የመሩት የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሙህዲን ረሻድ፤ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ከጊዜ ወደ ጊዜ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ገልፀዋል።
ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅም የሚመለከታቸው አካላት በተለመደው ቅንጅት መረባረብ እንደሚጠበቅባቸው ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር እሸቱ ለማ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በአካባቢው የተሳለጠ እንቅስቃሴ እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፣ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየትና የቅርብ ክትትል በማድረግ አየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
አዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን
22/12/2025
የመሬት ፣ ፕላንና ግንባታ ክላስተር ቅንጅታዊ አሰራር መግባቢያ ስምምነት ፊርማ መርሀ ግብር ተካሔደ።
ታህሳስ 13 ቀን 2018 ዓ.ም
በክፍለ ከተማዉ በመሬት ፣ ፕላን እና ግንባታ ዘርፍ የሚሰሩ ተቋማትን የሚያስተባብር ክላስተር ቅንጅታዊ አሰራር መግባቢያ ስምምነት ፊርማ ተካሔደ።
ይህ መግባቢያ ስምምነት የተፈረመው ዋና ዋና የሥራ ተግባራትን በተቀናጀ መልኩ ለማከናወን የጋራ የቅንጅት ስራዎችን በየወቅቱ ለመገምገም እና በየጽ/ቤቱ ያሉትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በጋራ ለመፍታት ያለመ ነው።
15 ተቋማትና ጽ/ቤቶች ያካተተ ሲሆን የቅንጅት አሰራሩን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት በወር አንድ ጊዜ በጋራ በመገናኘት ስራዎችን የሚገመግሙበት እና የተጠያቂነት ስርዓት የሚተገበርበት አሰራር እንደሚተገበር በስምምነቱ ወቅት ተብራርቷል።
ይህ ቅንጅታዊ አሰራር በመሬት፣ ፕላን እና ግንባታ ዙሪያ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት በክፍለ ከተማዉ ፈጣንና አገልግሎትን ለመስጠት እንደሚያግዝ ተገልዷል።
ስምምነቱም የግንባታ ፍቃድ ቁጥጥር ፣የደንብ ማስከበር፣ፕላንና ፣ልማት ፅህፈት ቤቶችን ጨምሮ በጠቅላላ 15 ፅህፈት ቤቶች ተፈራርመዋል።
22/12/2025
ቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ ባለፉት አምስት ወራት ከ382 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገለፀ ፡፡
ታህሳስ 13/04/18
****************************************
ዘመናዊ የመሬት ልማትና አስተዳደር ስርዓት የተዘረጋበት ፤ የላቀ አገልግሎት የሚሰጥበትና የተገልጋይ እርካታ የተረጋገጠበት ተቋም ለመፍጠር ራዕይ ሰንቆ እየሰራ የሚገኘው የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በተያዘው በጀት ዓመት ልዩ ትኩረት ከሰጠባቸው አበይት ተግባራት መካከል አንዱ የገቢ አሰባሰብ ነው፡፡
በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት 49 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን እቅዱን ለማሳካትም በየደረጃው የሚገኙ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የድርሻቸውን እየተወጡ ነው ፡፡
የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኮሙንኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ከቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ መኩሪያ ተስፋዬ ጋር በገቢ አሰባሰብና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ባደረገው ቆይታ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ በበጀት ዓመቱ 410 ሚሊየን 226ሺህ ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ በአምስት ወራት ብቻ አገልግሎት ለውጥን ጨምሮ ከ382 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን ለማወቅ ችሏል፡፡
አንድም መሬት ያለ ልማት ታጥሮ መቀመጥ የለበትም በሚል ከከተማ አስተዳደሩ በወረደው አቅጣጫ መሰረትም ባለፉት አምስት ወራት በተደረገው ልዩ የግንባታ ክትትል ንቅናቄ ከ2011 በጀት ዓመት ጀምሮ በምደባ መሬት ከወሰዱ 173 አልሚዎች 70 አልሚዎች ወደ ትግበራ እንዳልገቡ ማረጋገጥ ተችሏል ያሉት ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ መኩሪያ ተስፋዬ ችግሩን ለይቶ መፍትሔ ለማበጀትም ከአልሚዎቹ ጋር በተደረገ ውይይት በ15 ቀን ውስጥ ወደ ስራ ለመግባት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡
08/12/2025
በዛሬው ቀን 29/03/2018 የቦሌ ክ/ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቅ/ጽ/ቤት የ5 ወር የስራ አፈጻጸም ከአጠቃላይ ሰራተኛ ጋር ግምገማ ተካሄደ::
በቦሌ ክ/ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቅ/ጽ/ቤት የ5 ወር የስራ አፈጻጸም ከአጠቃላይ ሰራተኛ ጋር ግምገማ ተካሄደ::በእለቱም የአራቱም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሮች አፈጻጸማቸውን ያቀረቡ ሲሆን በቀረበው አፈጻጸምም ዙሪያ የቅ/ጽ/ቤቱ ሃላፊ የሆኑት አቶ መኩሪያ ተስፋዬ ጽ/ቤቱ የግማሽ አመቱን እቅድ ለማሳካት ካለው ቁርጠኝነት በመነሳት ቀሪ ታቅደው ከግብ ያልደረሱትን እቅዶች ላይ ያሉ ክፍተቶችን በመለየት ማሳካት የሚቻልበትን መንገድ አቅጣጫ ሰጥተዋል:: በተጨማሪም ገቢን ከማሳደግ መልካም አስተዳደር ከማስፈን እና ብልሹ አሰራር በመታገል ዙሪያ መሰራት ያለባቸውን ተግባራትን በትኩረት በመስራት በሁሉም መስክ ሙሉ የሆነ አፈጻጸም እንዲኖር ማስቻል እንደሚገባ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን በቀረበው አፈጻጸምም ዙሪያ ሰፊ ውይይት በማድረግ ተጠቃሏል::
28/11/2025
• የአገልግሎት አሰጣጥ መማክርት ጉባዔ ተቋቋመ
።።።።።።።።።።።።።።
የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ ቦሌ ቅ/ጽ/ቤት፤ ህዳር 18 ቀን 2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ ቦሌ ቅ/ጽ/ቤት በሚሠጠው አገልግሎት እርካታን ማረጋገጥ ይቻል ዘንድ የአገልግሎት አሰጣጥ መማክርት ጉባዔን በዛሬው ዕለት አቋቁሟል።
በዚህ የመማክርት ጉባኤ ምስረታ ላይ የጽ/ቤት ሀላፊው አቶ መኩሪያ ተስፋዬ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት የመልካም አስተዳደርና የብልሹ አሰራርን ለመቅረፍ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል። በዚህም ጉባኤ ላይ 30 የሚሆኑ ከሲቪክ ማህበራት፣ ከተገልጋይ ፣ ከባለድርሻ አካላት እና ሌሎችም ተወካዮዎች የተገኙበት መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል።
እነዚህም የመማክርት ጉባኤው ጠቅላላ አባላት ሆነው የሚቀጥሉ ሲሆን ከጠቅላላ አባላቱ ውስጥ 7 የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴዎችን በጠቅላላ ዓባላቱ ምርጫ እና ይሁንታ አፀድቋል ።
የአገልግሎት አሰጣጥ መማክርት ጉባኤ የሚያከናውናቸውን ዋና ዋና ተግባራትን የሚያሳይ ሰነድ ለተሳታፊዎች የቀረበ ሲሆን የአገልግሎት አሰጣጥ መማክርት ጉባዔ አመሠራረት እና ጠቀሜታ ዙሪያ በቢሮው የአገልግሎት አሰጣጥ ክትትል እና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ጸጋ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ በመንግስት ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ማሻሻል የሚቻለው ከተቋማቱ ጥረት በተጨማሪ የሲቪክ ማህበራት፣ ባለድርሻ አካላትና ተገልጋዮችን በማሳተፍ መሆኑን ጠቁመው የተገልጋይን እርካታ ለማረጋገጥ ሁሉም አካል የድርሻውን እንዲወጣ ለማስቻል ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል ።