01/06/2026
ለሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት አስፈላጊ የሆኑ የግብዓቶች ዝርዝር መመሪያ ማጠናቀቂያ አውደ ጥናት ተካሄደ
ኢትዮጵያ ውስጥ ማንኛውም ዓይነት የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ፈጣን፣ የተቀናጀ እንዲሁም ሕይወት አድን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች የግብአቶች ዝርዝር መመሪያ ለማጠናቀቂያ አውደ ጥናት (ወርክሾፕ) ከግንቦት 18 - 22, 2018 ዓ.ም ተካሂዷል።
በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነት ዳይሬክቶሬት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ግብአቶች አቅርቦት አስተዳደር ዲቪዥን አስተባባሪ አቶ ቢቂላ ዲሪባ እንደገለጹት፤ አሁን ላይ እየተዘጋጀ ያለው የግብአት ዝርዝር መመሪያ ድንገተኛ አደጋዎች ከመከሰቱ በፊት የሚደረግ የቅድመ ዝግጁነት ስራ አካል ነው። ዋናው ዓላማው አደጋ ከመከሰቱ በፊት ለእያንዳንዱ የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ምን ዓይነት ግብአቶች እንደሚያስፈልጉ አስቀድሞ መለየት፣ ሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው ወጥ መመሪያ ማውጣት እንዲሁም የአቅርቦት ሰንሰለት ዘላቂነትን ማረጋገጥ ነው። አስተባባሪው አክለውም፥ ይህ ወጥ የሆነ አሰራር መዘርጋቱ ሊከሰቱ ለሚችሉ አደጋዎች ምላሽ መስጠ የሚያስችል ጠንካራ፣ ተቋማዊ እና ዘላቂ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ግብአቶች አቅርቦት ሥርዓት መገንባት ነው።
አውደ ጥናቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ግብአቶች አቅርቦት ሥርዓትን ለማዘመን፣ የግብአት ድግግሞሽ እና ብክነትን ለመቀነስ፣ ወጥ የሆነ የምላሽ ሂደት እንዲኖር ለማድረግ እንደሚረዳ ተሳታፊዎች አጽንኦት ሰጥተዋል። በተጨማሪም መመሪያው ተቋማት አንድ አይነት የምላሽ አሰጣጥ እንዲከተሉ በማድረግ ቅንጅታዊ አሠራር ለመፍጠር እንደሚረዳ ተመላክቷል።
በአውደ ጥናቱ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከሕብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት፣ ከኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን፣ WHO፣ Project Hope፣ JSI፣ UKHSA፣ CHAI፣ ከክልሎች እና ከሆስፒታሎች የተውጣጡ፣ በቀጥታ የስራው ባለድርሻ የሆኑ አካላት ተሳትፈዋል።
ይህ መመሪያ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ግብአቶች ዝግጁነትን የሥራ ባህል ለማድረግ መሠረታዊ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል።
https://ephi.gov.et/ለሕብረተሰብ-ጤና-ድንገተኛ-አደጋዎች-ምላ/
31/05/2026
በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ደህንነትን ለማጠናከር የሚያስችል የአንድ ጤና የቴክኒክ የሥራ ቡድኖች ማነቃቂያ አውደጥናት ተካሄደ::
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በብሔራዊ የአንድ ጤና (One Health) ሴክሬታሪያት አማካኝነት በኢትዮጵያ ያሉ የጤና ስጋቶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የዝግጁነትና ምላሽ አቅም ለማጠናከር ያለመ የቴክኒክ የሥራ ቡድኖች (TWGs) ማነቃቂያ ወርክሾፕ ከግንቦት 20–21 ቀን 2018 ዓ. ም አካሂዷል።
በአውደጥናቱ የመንግሥት ተቋማትን፣ የልማት አጋሮችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በአንድ ጤና አቀራረብ በማሰባሰብ ከአስተዳደር፣ ከቅንጅት፣ ከተጠያቂነት እና ዘላቂነት ጋር የተያያዙ ችግሮች ላይ ተወያይቷል።
በዝግጅቱ ላይ የብሔራዊ የአንድ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶ/ር ፈይሳ ረጋሳ የሰው፣ የእንስሳት እና የአካባቢ ጤና ሥርዓቶችን በተቀናጀ መንገድ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
“ዋና ግባችን ለጊዜው ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ፣ ከወረርሽኞች ውጪም በየዕለቱ የሚሰራ እና ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ጠንካራ የሥራ ሥርዓት መገንባት ነው፣” ብለዋል።
የአውደ ጥናቱ ቁልፍ ውጤቶች የመመሪያ ሰነዶችን (Terms of Reference - TORs) በማሻሻል የሥራ ኃላፊነቶችንና የሪፖርት ማቅረቢያ መዋቅሮችን ግልጽ ማድረግ፣ የተጠያቂነት ሥርዓቶችን ማጠናከር፣ እንዲሁም ለቴክኒክ የሥራ ቡድኖች ቋሚ ሰብሳቢዎችና ምክትል ሰብሳቢዎችን በመሾም እና መደበኛ የመግባቢያ መድረኮችን በመፍጠር እንደገና ማነቃቃትን ያካትታሉ።
በአውደ ጥናቱ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከሕብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት፣ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን እንዲሁም እንደ FAO፣ Resolve to Save Lives፣ UKHSA፣ JSI፣ Core Group Partners Project፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር እና Project HOPE ያሉ አለማቀፍ አጋሮች ተሳትፈውበታል::
ተሳታፊዎች በሰው፣ በእንስሳት እና በአካባቢ ጤና መስኮች መካከል የሚከሰቱ አዳዲስ የጤና ስጋቶችን ለመቋቋም በቅጽበት የመረጃ ልውውጥን ማሻሻል፣ ሀብት ማሰባሰብ እና የተቀናጀ ምላሽ መስጠትን ለማጠናከር ቃል ገብተዋል።
ይህ የተሳካ አውደጥናት የአንድ ጤና አቀራረብን በኢትዮጵያ ውስጥ ተቋማዊ ለማድረግ እና የዘርፎች መካከል ትብብርን ለሰዎች፣ ለእንስሳት እና ለአካባቢው ጤና መደበኛ የሥራ ባህል ለማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ታይቶበታል::
https://ephi.gov.et/ጤና-ደህንነትን-ለማጠናከር-የሚያስችል-የ/
EPHI Concludes One Health TWGs Revitalization Workshop to Strengthen Ethiopia’s Health Security
The Ethiopian Public Health Institute (EPHI), through the National One Health Secretariat, has successfully concluded a two-day Technical Working Groups (TWGs) Revitalization Workshop held from May 28–29, 2026, aimed at strengthening Ethiopia’s preparedness and response to interconnected health threats.
The workshop brought together government institutions, development partners, and stakeholders to address challenges related to governance, coordination, accountability, and the sustainability of the One Health approach.
Speaking at the event, Dr. Feyisa Regassa, Chairperson of the National One Health Secretariat, emphasized the need to integrate human, animal, and environmental health systems.
“Our ultimate objective is to pivot away from temporary fixes and build a resilient, everyday operational mechanism that endures well beyond active outbreaks,” he said.
Key achievements of the workshop included refining draft Terms of Reference (TORs) to clarify mandates and reporting structures, strengthening accountability mechanisms, and revitalizing Technical Working Groups through the appointment of dedicated chairs and co-chairs and the establishment of regular communication platforms.
The workshop also reinforced collaboration among key stakeholders, including the Ministry of Health, Ministry of Agriculture, Environmental Protection Authority, Ethiopian Wildlife Conservation Authority, and international partners such as FAO, Resolve to Save Lives, UKHSA, JSI, core group partners project , Ethiopia Red Cross Society and Project HOPE.
Participants committed to enhancing real-time information sharing, resource mobilization, and coordinated responses to emerging health threats at the human-animal-environment interface.
The successful workshop marks an important step toward institutionalizing the One Health approach in Ethiopia, making cross-sector collaboration a routine practice for protecting the health of people, animals, and the environment.
https://ephi.gov.et/ጤና-ደህንነትን-ለማጠናከር-የሚያስችል-የ/
31/05/2026
የምርምር ስነምግባር፣ የጥናታዊ ፅሁፎች ቅድመ ምርምር ግምገማና እዉቅና አሰጣጥ ቦርድ አሰራር እና የ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጥናታዊ ፅሁፎች መቀበያ ደህረ ገፅ ትዉዉቅና ስልጠና ተሰጠ፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምርምር ሥነ-ምግባር እና ህትመት መከታተያ ጽ/ቤት ከግንቦት 20 አስከ 22/2018 ዓ.ም የምርምር ጽሁፍ ስነ ምግባርን አስመልክቶ ባዘጋጀው የምርምር ጽሁፎች ጋር የተያያዙ የሥነ ምግባር ጉዳዮችን አንስቶ የተወያየ እንዲሁም አገልግሎቱን በማዘመንና ዲጂታላይዝ በማድረግ የግምገማ ሂደቱን የሚከወንበትን ድረ-ገጽንም አስተዋዉቋል።
የኢንስቲትዩቱ የምርምር ሥነ-ምግባር እና ህትመት ጽ/ቤት ዳይሬክተር ዶ/ር ማህደር ሚሊዮን በመድረኩ ላይጽ/ቤታቸው የተለያዩ የምርምር ጽሑፎች ከኢንስቲትዩቱም ሆነ ከሌሎች አጋር ተቋማት የሚመጡን የምርምር ስነምግባር ፋቃድ ጥያቄ በመገምገም ወደ ሥራ የሚያስገባ ጽ/ቤት መሆኑን ጠቅሰዉ በክልሎች ለሚገኙ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶችና ጤና ቢሮዎች ለሚገኙ ባለሙያዎች የምርምር ጽሁፍን ሥነ-ምግባር አስመልክቶ የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሆኑን አብራርተዋል:: የስልጠናው አላማም ከጽህፈት ቤታቸው ጋር በጋራ የሚሰራ ቦርድ (IRB) ፕሮፖዛሎችን የሚገመግምና አጽድቆ ምርምሮችን ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚያደርግ ቦርድ ያላቸው ተቋማት ለሌሎች ልምድ የሚያካፍሉበት እና የሌላቸው ደግሞ የሚያቋቁሙበትን ሁኔታ መነሻ እውቀት እንዲቀስሙ ለማስቻል ሲሆን በመድረኩ ተቋማዊ የምርምር ጽሁፎች የግምገማ ቦርድ (Institutional Review Board) የሌላቸው የክልል የሕብረተሰብ ጤና ተቋማት የምርምር ስነምግባር መክታተያ ቦርዱ ማቋቋም የሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይም ምክክር ተካሂዷል::
በምክክር መድረኩ አዳዲስ ከሥነ ምግባር የተያያዙ ጉዳዮችን ዲጂታላይዝ በማድረግ የምርምር ፍቃድ ጽሑፎችንና ጥያቄ የሚላኩትም ድህረ ገፅ የሚተዋውቅበት መድረክ እንደሆነ ገልጸዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው በመስኩ በሙያ ልምዳቸው እና እውቀታቸው ከፍተኛ ልምድ ባካበቱ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች የተሰጠ ሲሆን የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የክልል ጤና ቢሮዎች እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች ተመራማሪ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታልየኢንስቲትዩቱ የምርምርሥነ-ምግባር እና ህትመት ጽ/ቤቱ ከተቋቋመ ጀምሮ በርካታ የምርምር ፁሑፎችን ገምግሞ ፍቃድ የሰጠና የአለም አቀፍ የምርምር ግምገማና ፍቃድ አሰጣጥ ስርዓትን በመከተል ከStratgic initiative for Developing Capacity in Ethical Review ( SIDCER) በ 2023 እ.ኢ.አ እዉቅና የተሰጠዉ ተቋም መሆኑ ይታወሳል::
https://ephi.gov.et/የምርምር-ስነምግባር፣-የጥናታዊ-ፅሁፎች/
25/05/2026
በአፍሪካ ስለተከሰተው ኢቦላ ቫይረስ በሽታ እና በኢትዮጵያ እየተደረጉ ያሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች
ግንቦት 17 ፣ 2018 ዓ.ም
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በግንቦት 09 ፣ 2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ (DRC) እና በዩጋንዳ በቡንዲቡግዮ (Bundibugio) ቫይረስ ዝርያ የሚመጣ የኢቦላ ቫይረስ በሽታ መከሰቱን ያሳወቀ ሲሆን እስከ ትላንት ግንቦት 16፣ 2018 ድረስ በእነዚሁ ሀገራት በአጠቃላይ ከ101 በላይ የሚሆኑ በላቦራቶሪ የተረጋገጡ ታማሚዎች እና ከ900 በላይ ንክኪ ያላቸው ተጠርጣሪዎች የህክምና ክትትል ላይ ይገኛሉ።
የኢቦላ ቫይረስ በሽታ ከፍተኛ የስርጭት እና የሞት ምጣኔ ያለው በሽታ ሲሆን ከሰው ወደ ሰው በንክኪ በቀላሉ ይተላለፋል።
እስከዛሬ ድረስ በሃገራችን ኢትዮጵያ ምንም አይነት በኢቦላ ቫይረስ በሽታ የተጠረጠረ ወይም የታመመ ሰው አልተገኘም።
ምንም እንኳን በሽታው ከተገኘባቸው አገራት ጋር ቀጥተኛ የድንበር ግንኙነት ባይኖረንም የበሽታውን አደገኛነት በመገንዘብ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና የአፍሪካ በሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል (Africa CDC) የወረርሽኙን መከሰት ይፋ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ፦
- በሁሉም አለም አቀፍ የየብስ መግቢያ እና መውጫ ኬላዎች የልየታ እና የቅኝት ስራዎች በማጠናከር ፣
- በአለም አቀፍ አየር ማረፊያዎች የተጠናከረ ክትትል በማድረግ ፣
- የጤና ተቋማት ዝግጁ በማድረግ እንዲሁም የላቦራቶሪ አቅምን በማሳደግ
- እንዲሁም አስፈላጊው የህክምና ግብአት አቅርቦት ላይ የተጠናከረ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እየተከናወነ ይገኛል።
Website: ephi.gov.et
25/05/2026
የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር መረጃዎችን ከመነሻቸው በጤና ተቋማት አገልግሎት ለሚሰጡ የጤና ባለሙያዎችን አቅም በመገንባት የጤና መረጃዎችን ጥራት ማስጠበቅ እንደሚቻል ተገለጸ፡፡
የኢትዮጰያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቅኝትና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክቶሬት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቅኝትና በሽታ ኢንተለጀንስ ዲቪዥን የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ተግባራትን ለማከናወን በመረጃ መነሻነት አገልግሎት በሚሰጡ የጤና ተቋማት ላይ ለሚስሩ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች የመረጃ ጥራትን አስመልክቶ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጠ፡፡
የስልጠናው ዋና ዓላማ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ መረጃዎችን ጥራትና ወቅታዊነት ለማስጠበቅ መረጃዎችን ከመነሻቸው ከጤና ተቋማት በደረጃ ለሚመለከተው አካል ተደራሽ ለማድረግ፣ ባለሙያዎች ጥራት ያላቸውን መረጃዎች የማሰባሰብ፣ የማደራጀት ፣ የመተንተንና መተንተን በየደረጃው ለእቅድ፡ ለውሳኔ መጠቀም እና ሪፖርት የማድረግ ተግባራትን ለማሻሻል የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና ነው፡፡
አቶ ደረጄ መሬ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቅኝት ባለሙያና የስልጠናው አስተባባሪ ለጤና ባለሙያዎች የተሰጠውን የአቅም ግንባታ ስልጠና አስመልክቶ እንደገለጹት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከልን የልህቀት ማዕከል ከማድረግ አንጻር በሀገር አቀፍ ደረጃ መረጃን በማዘመን እና ዲጂታላይዝ የማድረጉ ጉዳይ በርካታ ስራ የተሰራ በመሆኑ አመርቂ ውጤት እተመዘገበ ይገኛል ብለዋል፡፡
የመረጃ ጥራትን ለማስጠበቅ መረጃዎች ከሚነሱበት በጤና ተቋማት እንደ ሀገር የመረጃ አሰባሰብ፣ አያያዝ፥ ጥራት አጠባበቅና ለውሳኔ መጠቀም የቅድመ አስፈላጊነት ጥናት በማደረግ፥ ከባላድርሻ አካላት ጋር በመወያየት እና የቅድመ የአፈጸም መመሪያዎችን በማጠናቀቅ ለተመረጡ ተቋማት በኦሮሚያ፤ በአዲስ አባባ፣ በድሬዳዋ፣ በሲዳማ፣ በማእክላዊ ኢትዮጲያ አና በደቡብ ኢትዮጲያ የፓይለት/የሙክራ/ትግበራ እየተስራ መሆኑንና የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ስራ ላይ ለሚሰሩ ለተመረጡ ሆስፒታል እና ጤና ጣቢያ ባለሙያዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ከመሆኑም በላይ በቀጣይ በአገር አቀፍ ደረጃ ስልጠናውን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አቶ ደረጄ አያይዘው አብራርተዋል፡፡
የመረጃ አሰባሰብ፣ አደረጃጀት፣ጥራት አጠባበቅን፣ መረጃዎችን በኤክሴል እና በDHI2 እንዴት እንደሚያዝ፣ እንዴት እንደሚተነተንና ሪፖርት እንደሚደረግ አጠቃላይ በጤና ተቋማት መደረግ ስለሚገባቸው የመረጃ ጥራት ስራዎች በስፋትና በጥልቀት ስልጠና የተሰጠ ሲሆን የጤና ባለሙያዎችም ባገኙት እውቀት እና ክሕሎት በመጠቀም ከጤና ተቋማት ተሰብስበው የሚወጡ መረጃዎች ተአማኒነተቸው፣ ወቅታዊነታቸው፣ አደረጃጀታቸውና ምሉእነታቸው እንዱሁም በሚፈለገው ደረጃ ጥራታቸው የተጠበቀ መረጃዎች ለሚመለከታቸው ማመንጨት፣ መያዝ፣ መጠቀም እና ማጋራት ባለድርሻ አካላትና ለውሳኔ ሰጪ ተደራሽ በማድረግ ተገቢውን የምላሽ ስራ ይሳለጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
25/05/2026
ኢንስቲትዩቱ በላብራቶሪ አቅም ግንባታ እና ጥራት ማስጠበቅ
በጤናው ዘርፍ የላብራቶሪ አቅም ግንባታ እና ጥራት ማስጠበቅ (Laboratory Capacity Building and Quality Assurance) የሕክምና አገልግሎት ጥራት፣ የታካሚዎች ደህንነት እና የሕዝብ ጤና ጥበቃ ዋና መሠረት ነው። የላብራቶሪ ምርመራ ውጤት ሐኪሞች ለሚሰጡት ውሳኔ ከ70 በመቶ በላይ ድርሻ እንዳለውም ይገመታል። ለዛም ነው ላብራቶሪ የህክምናው ዘርፍ የጀርባ አጥንት ነው የሚባለው፡፡ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም የላብራቶሪ አቅምን ለመገንባትና ጥራትንም ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በላብራቶሪ አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት የላብራቶ ጥናት ትግበራ ዲቪዢን ሃላፊ አቶ አዋድ መሃመድ እንደሚናገሩት የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሪፈራል እና ሪፈረንስ ላብራቶሪ ዳይሬክቶሬት በየጊዜው አዳዲስ ምርመራዎችን እያስተዋወቀ ይገኛል፡፡ በዚህ አመትም በጣም ብዙ የላብራቶሪ ምርመራዎችን ማስተዋወቅ ተችሏል። ብዙ ገንዘብና ግዜ የሚወስዱ በውጪ ሀገር የሚሰሩ የላብራቶሪ ምርመራዎችን በዝቅተኛ ዋጋ ለህብረተሰቡ ማቅረብ ችሏል፡፡ ለህብረተሰብ ጤና አስተዳደር የሚያስፈልጉ ምርመራዎችንም በየጊዜው እያስተዋወቀ ይገኛል፡፡
እነዚህ የሪፈራል እና ሪፈረንስ ላብራቶሪዎች ከጥራት አኳያ ሲታዩ በISO 15189 የጥራት እውቅና የተሰጣቸው ናቸው፡፡ ISO 15189 ደግሞ ለሜዲካል ላብራቶሪ የተዘጋጀ አለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ነው። በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያሉት የሪፈራል ላብራቶሪዎች ሁሉም ይህንን የጥራት መስፈርት አሟልተዋል፡፡ ይህም ላብራቶሪዎቹ በየትኛውም አለም ተቀባይነት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡
አሁን ላይ ደግሞ አንቲ-ዶፒንግ (Anti-Doping) ምርመራ በሀገር አቀፍ ደረጃ ማድረግ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል:: ይህም በቅርቡ የሚጀመር ይሆናል፡፡ ብዙ ጊዜ አትሌቶች ይህን ምርመራ የሚያደርጉት በውጪ ሀገር ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን ይህን ምርመራ በሀገር ውስጥ ማድረግ ተችሏል፡፡ ስለዚህ ወደፊት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገራትም ጭምር ምርመራ ለማድረግ የሚያስችል አቅም ተገንብቷል፡፡
ሌላው የላብራቶሪ አቅም ግንባታ ስራ የሚሰራው አጠቃላይ የላብራቶሪ አገልግሎት ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ድጋፍ ማድረግ ሲሆን እንደ ኢትዮጵያ የላብራቶሪ አገልግሎት ጥራትን በሶስት መንገዶች እንዲጠበቅ ይደረጋል፡፡ አንደኛው ለጤና ተቋማት የተዘጋጁ የጥራት መጠበቂያ ስረአትን ተግባራዊ በማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ በዋነኝነት ለሆስፒታል ላብራቶሪ የተዘጋጀውን የጥራት ማስጠበቂያ ፕሮግራም ተግባራዊ እንዲደርጉ በማድረግ ሲሆን ሶተኛውና የመጨረሻው የክልል ሪፈራል ላብራቶሪዎች እና ሀገር አቀፍ ሪፈራል ላራቶሪዎች የአለም አቀፍ ስታንዳርድ ማለትም የ15185 (15189) ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚያወጡት የምርመራ ውጤት ታማኝነት እንዲኖረው የሚያረጋግጥ ስራ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በዋናነት ይሰራል፡፡
ስለዚህ አጠቃላይ የክልል፣ ሆስፒታል፣ የፌደራል ሆስፒታሎች ላብራቶሪዎች ላይ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩ የላብራቶሪ ጥራት ተግባራዊ እንዲሆን ድጋፍ ያደርጋል። በተዋረድ ደግሞ የክልል ሪፈራል ላብራቶሪዎች የራሳቸውን እና በስራቸው ያሉ ፋሲሊቲዎችንድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ ኢንስቲትዩቱ የክልል ሪፈራል ላብራቶሪዎችን ወይም የህዝብ ጤና ኢንስቲትዩቶችን ይደግፋል፡፡
ስለዚህ እነሱ ደግሞ በተዋረድ ወደ ታች ላለው ላብራቶሪ ተመሳሳይ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ ኢንስቲትዩቱም አቅም በየቦታው እየገነባ ነው ያለው፡፡ የክልል ሪፈራል ላብራቶሪዎች ደግሞ በተዋረድ የድጋፍ ስራቸውን ይሰራሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ጥራትን ለማስጠበቅ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ይሰራል፡፡
ስለዚህ እንደ ሀገር በኢትዮጵያ የISO 15189 የጥራት ደረጃን ያሟሉ ወደ 75 የሚሆኑ ላብራቶሪዎች አለም አቀፍ እውቅና አግኝተዋል። ነገር ግን አሁን ካሉት 4,500 በላይ ላብራቶሪዎች ቁጥር አንፃር ሲታይ ገና ነው፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይ ወደፊት ብዙ ስራ መሰራት እንዳለበት የሚጠቁም ነው። እንዲያም ሆኖ ኢትዮጵያ የላብራቶሪ ጥራት ቁጥጥር ስረአትን ተግባራዊ በማድረግ እና የISOን እውቅና በማምጣት በአፍሪካ አራተኛ ደረጃ ይዛለች፡፡
ይህም እንደ አፍሪካ ኢትዮጵያ በጣም ጥሩ ደረጃ ላይ እንደምተገኝ ያሳያል፡፡ ነገር ግን ደግሞ ባጠቃላይ ሲታይ የጥራት ቁጥጥር ስረአት ወይም ደግሞ የጥራት ደረጃ አሁንም ገና የሚቀረው መሆኑን ያሳያል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ደረጃ በአፍሪካ ጥሩ ቢሆንም እንደ ሀገር ካሉት የላብራቶሪዎች ብዛት አንጻር አሁንም በጣም ብዙ መስራት ይጠበቃል፡፡
አቶ አዋድ እንደሚሉት ሌላው ከላብራቶሪ ጥራት ጋር ተያይዞ ያለው ፕሮግራም የውጪ ጥራት ምዘና (External Quality Assessment) ሲሆን ይህም ላብራቶሪዎች የሚሰሯቸው ስራዎች ታአማኒነታቸውን የሚከታተል ስረአት ነው፡፡ በዚህም ውስጥ ሶስት አይነት ስረአቶች አሉ፡፡ አንደኛው እንዲሞከሩና በትክክል ይሰራሉ ወይስ አይሰሩም የሚለውን ለማየትና ጥራታቸውን ለማረጋገጥ እንደ ሀገር ከውጭ ኮንትራት ተደርጎ የሚመጣ የውጪ ጥራት ምዘና ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰራ ፒቲ ፓናል አለ። ስለዚህ እነዚህን በመጠቀም የላብራቶሪ አቅማቸውን ከጥራት አንጻር መመዘኛ ስረአት ሲሆን ላብራቶሪዎቹ በትክክል አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንና አለመሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንደኛው ድጋሚ ማረጋገጥ ወይም (Re-checking) ስረአት ሲሆን ይህም ላብራቶሪዎች የሰሩትን ናሙና ወይም ስላይድ በትክክል ነበረ ወይ የሰሩት የሚለውን ነገር በድጋሚ የማረጋገጥ ስራ የሚሰራበት ነው፡፡ ።
ሶስተኛው ደግሞ ኦንሳይት ኢቫሉዌሽን (On-site evaluation) ነው። ላብራቶዎች እየሰጡት ያለው አገልግሎት ከጥራት አንፃር ልክ ነበረ ወይ የሚለውን አጠቃላይ ስረአቱን ክትትል የሚደረግበት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሶስት መንገዶች በመከተል ላብራቶሪዎች የሚሰጡት አገልግሎት ጥራቱን የጠበቀ የተጠበቀ መሆኑን፣ እምነት የሚጣልበት መሆኑን እና በትክክለኛው ጊዜ መውጣት መቻሉን ለማረጋገጥ የኢትጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከክልል ሪፈራል ላብራቶሪዎች ጋር በመሆን ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ በተዋረድ በአብዛኛው የክልል ሪፈራል ላብራቶሪችንና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶችን አቅም ከማሳደግ አንጻር አጠቃላይ ድጋፍ ያደርጋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ አንደኛው በኢንስቲትዩቱ እየተሰራ ያለ ስራ አለ። በናሽናል ደረጃ የኢኪውኤ (EQA) ሳምፕል ለማምረት የሚያስችል እቅድ ተይዟል፡፡ የህንፃ ግንባታው ተከናውኗል፡፡ ይህም ወደፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ ብዙ ተሳታፊዎችን በዚህ ስረአት ውስጥ ማስገባት ያስችላል፡፡ በተጨማሪ ደግሞ ከዋጋ አንጻርም ሲታይ በጣም ብዙ የሚታደግ ስራ ነው።
23/05/2026
የመሰረታዊ ፊልድ ኢፒዲሞሎጂ (Frontline-FETP) ሰልጣኝ የጤና ባለሙያዎች ተመረቁ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከሚገኙ የተለያዩ የወረዳ ጤና ተቋማት የተውጣጡና ለ3 ወራት መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ (Frontline-FETP) ስልጠናቸውን ሲከታተሉ የቆዩ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች ግንቦት 15 ቀን 2018 ዓ.ም በጅማ ከተማ ተመረቁ።
የምርቃት ፕሮግራሙን ያዘጋጀው የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከል የቅድመ ዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ከኢንስቲትዩቱ ብሔራዊ የስልጠና ማዕከል ጋር በመተባበር ሲሆን ስልጠናው 3ኛ ዙር የጠናቀቁ መሆናቸው ተገልጿል።
የስልጠናው ዋና ዓላማ የጤና ባለሙያዎችን የእውቀትና የክህሎት አቅም በማሳደግ፣ በሕብረተሰብ ጤና ላይ አደጋ የሚፈጥሩ የተለያዩ ወረርሽኞችንና ክስተቶችን ቀድሞ ለመለየት፣ መረጃዎችን በወቅቱ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ለማድረግ እና የምላሽ ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ነው።
በምርቃት ስነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወሰን ጨመሰ እንደገለጹት፤ ይህ ስልጠና በጤናው ዘርፍ ከሚሰጡ ሌሎች ስልጠናዎች ለየት የሚያደርገው በተግባር ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነው:: ባለሙያዎቹ ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም፣ በጥራት ላይ የተመሰረቱና ለውሳኔ ሰጪ አካላት መረጃዎችንና መፍትሔዎችን በማቅረብ የሕብረተሰቡን የጤና ችግሮች በአፋጣኝ ለመፍታት እንደሚረዳም ተናግረዋል።
የኢንስቲትዩቱ የቅድመ ዝግጁነት ዳይሬክቶሬት ባለሙያና የስልጠናው አስተባባሪ አቶ አወል ዳውድ በበኩላቸው፤ የሕብረተሰብ ጤና አደጋን በሙሉ አቅም ለመከላከልና ለመቆጣጠር በአገር አቀፍ ደረጃ ስልጠናውን ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። በተደረገው ከፍተኛ ጥረትም የመረጃ ወቅታዊነት፣ ጥራት እንዲሁም የምላሽ ስራዎች ላይ አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከል ባለሙያ አቶ ጃፈር ከዛሊ እና የብሔራዊ ስልጠና ማዕከል ባለሙያ ወ/ሪት እናኑ ሁነኛው ተመራቂዎች ወደ ስራ ቦታቸው ሲመለሱ ስለሚኖራቸው ኃላፊነትና ተግባራት ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ከሰልጣኞች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶችም ተገቢውን ምላሽ ሰጥተዋል።
ሰልጣኝ ባለሙያዎቹ በበኩላቸው በስራ ቦታቸው የተሰጧቸውን የፊልድ ፕሮጀክቶች አጠናቀው በጽሁፍና በፊትለፊት ገለጻ (Presentation) አማካኝነት መገምገማቸውን ጠቅሰው፣ ስልጠናው በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ውጤታማ ሥራዎችን ለማስመዝገብና ለሕብረተሰቡ የሚሰጡትን የዕለት ከዕለት የጤና አገልግሎቶች በተሻለ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ አቅም እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ስልጠናውን በብቃት ተከታትለው ያጠናቀቁና በአማካይ 70 ከመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡ 28 የኮርሱ ተሳታፊ የጤና ባለሙያዎች የእውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል።
https://ephi.gov.et/በደቡብ-ምዕራብ-ኢትዮጵያ-…ine-fetp-ሰልጣኝ-የጤ/
23/05/2026
ኢትዮጵያ የወረርሽኝ በሽታዎችን በራስ አቅም መለየትና ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም እያጎለበተች ነው
ኢትዮጵያ የወረርሽኝ በሽታዎችን በራስ አቅም መለየትና ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም እያጎለበተች መሆኗን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገበ::
ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የጤና ተቋማትን በማዘመን በበሽታ መከላከልና አክሞ ማዳን ሥርዓት አቅምን ማጎልበት ያስቻለ ስኬታማ የፖሊሲና የሪፎርም እርምጃ ወስዳለች።
ይህም የጤና ተቋማትን የሕክምና ግብዓት በማሟላት የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ማጠናከር ያስቻለ ምኅዳር መፈጠሩን ገልጸዋል።
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የናሙና መመርመሪያ አለመኖር፣ የኦክስጅን ማከማቻ ፕላንትና የሆስፒታሎች የፅኑ ህሙማን ክፍሎች ክፍተት ወሳኝ ትምህርት መወሰዱን ተናግረዋል።
በዚህም የኢትዮጵያን የወረርሽኝ በሽታዎችን በራስ አቅም መለየትና ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም ማጎልበት ያስቻለ ሥራ መሰራቱን አንስተዋል።
ለአብነትም ኢትዮጵያ የነበራትን ሶስት የኦክስጅን ማምረቻ ፕላንት ወደ 83 በማሳደግ በየ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ተገልጋዮች የሚጠቀሙበትን ምኅዳር መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል።
የፅኑ ህሙማን ሕክምና ክፍል ያላቸው ሆስፒታሎች ከ70 በላይ እንዳልነበሩ በማስታወስ፤ በአሁኑ ወቅትም ወደ 198 ሆስፒታሎች ማሳድግ መቻሉን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በጤና ዘርፍ የተከናወኑ ውጤታማ የሪፎርም እርምጃዎች ኢትዮጵያ የወረርሽኝ በሽታዎችን በራስ አቅም መለየትና ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም ማጎልበት እያስቻላት ነው ብለዋል።
ለዚህም በቅርቡ ተከስቶ የነበረውን የማርበርግ ወረርሽኝ ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም መለየትና መከላከል ያስቻለ ውጤታማ ሥራ መሰራቱን አስረድተዋል።
በወቅቶች መፈራረቅ ሳቢያ የሚከሰቱ የወባና መሰል በሽታዎችን ሥርጭት መግታት የሚያስችል የበሽታ ልየታና ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋቱንም አንሰተዋል።
በትምህርትና ስልጠናም የበሽታ ሥርጭትን ቅድመ መከላከልና አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ብቁና ፕሮፌሽናል ሙያተኛ በማሰማራት ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ውጤታማ የቅኝት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
Ministry of Health,Ethiopia
Ethiopian Public Health Institute
22/05/2026
የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቅኝት መረጃዎችን በዲጂታል ሥርዓት ለማዘመን የሚያስችል የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጠ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) በሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቅኝትና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክቶሬት ስር በሚገኘው የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝትና በሽታ ኢንተለጀንስ ዲቪዥን ከኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ ስልጠና ማዕከል ጋር በመተባበር ከግንቦት 10 እስከ 14/2018 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የወረርሽኝና የሕብረተሰብ ጤና አደጋ መረጃዎችን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያስችል ሀገር አቀፍ የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጠ።
የስልጠናው ዋና ዓላማ በሁሉም የጤና ተቋማት ውስጥ ወቅታዊ፣ ምሉዕ እና ጥራቱን የጠበቀ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ መረጃን በዲጂታል መንገድ ማሰባሰብ፣ ማደራጀትና መተንተን የሚያስችል አቅም መገንባት ነው። ይህም ውሳኔ ሰጪ አካላት ፈጣንና ውጤታማ የወረርሽኝ መከላከልና ምላሽ ሥራዎችን ለመስጠት የሚያስችላቸውን መረጃ በወቅቱ እንዲያገኙ ያደርጋል።
አቶ ማንደፍሮ ከበደ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቅኝትና በሽታ ኢንተለጀንስ ዲቪዥን ኃላፊ በመክፈቻ ንግግራቸው ወቅት እንደገለጹት፤ ሀገሪቱ የምትከተለውን የወረርሽኝ መረጃ ልውውጥ ሥርዓት ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ የዲጂታላይዜሽን ሥራው ወሳኝ መሆኑን፣ ለዚህም በዘርፉ ለተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና በተለያዩ ዙሮች እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ማንደፍሮ አክለውም፣ ሰልጣኞቹ በመረጃ አሰባሰብ፣ በጥራት ቁጥጥር፣ በትንተና፣ በሪፖርት አቀራረብ፣ በግብረ-መልስ አሰጣጥ እና ለውሳኔ ሰጪዎች ሪፖርት በማድረግ ረገድ ሰፊ እውቀትና ክህሎት ማግኘታቸውን ገልጸው፤ ለቀጣዩ የComprehensive PHEM DHIS2 ሥርዓት ሙሉ ትግበራ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
አቶ መሐመድ አህመድ የኢንስቲትዩቱ ብሔራዊ የስልጠና ማዕከል ዳይሬክተር በስልጠናው ማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት የኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ ስልጠና ማዕከል በርካታ መደበኛና ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ (CPD) ስልጠናዎችን በመስጠት አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቁመው፣ መረጃን ከማዘምን ጋር ተያይዞ ወቅቱ የዲጂታላይዜሽን ሽግግር ላይ በመሆኑ ተከታታይነት ያለው ሞጁል እስታንዳርድ የሆነ የዲጂታላይዝ የሙያ ብቃትን መሰረት ያደረገ ለጤና ባለሙያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠ ስልጠና መሆኑን እና በቀጣይ ስልጠናውን በተሻለ ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ይህንን የዲጂታላይዜሽን ሽግግር ውጤታማ ለማድረግ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና ከፕሮጀክት ሆፕ (Project HOPE) ጋር በቅርበት እየሰራ ይገኛል። ኢንስቲትዩቱ ለሥርዓቱ ማስፈጸሚያ የሚሆኑ በርካታ ኮምፒውተሮችንና የኤሌክትሮኒክስ ግብዓቶችን ለጤና ተቋማት ያሰራጨ ሲሆን፣ ስልጠናውም ከድርጅቶቹ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑን ከመድረኩ መረዳት ተችሏል።
በስልጠና ፕሮግራሙ ላይ የሁሉም ክልሎች እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች፣ እንዲሁም የመከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ ጤና መምሪያ ጤና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
ሰልጣኞች ስልጠናውን በጥሩ ውጤት ያጠናቀቁ በመሆናቸው የእውቅና ሰርተፍኬት የተቀበሉ ሲሆን፣ በቀጣይም ወደ የመጡበት ተቋም በመመለስ ያገኙትን ስልጠናውን እውቀትና እና ክህሎት ስልጠናውን ላላገኙ ሌሎች የጤና ባለሙያዎች በተዋረድ (Cascade) የመስጠትና ሥርዓቱን በየደረጃው የማስፈጸም ኃላፊነት ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
https://ephi.gov.et/የሕብረተሰብ-ጤና-አደጋ-ቅኝት-መረጃዎችን/
22/05/2026
የሠራተኞች ጤንነትና ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑ ተገለጸ፤ 30 የሚሆኑ የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች ስልጠና አጠናቀው ተመርቀዋል::
ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር በመተባበር በመጀመሪያ ዕርዳታ አሰጣጥ ላይ ያሰለጠናቸውን 30 ባለሙያዎችን ዛሬ በይፋ አስመርቋል።
በየዓመቱ የሚከበረውን ዓለም አቀፉን የሥራ አካባቢ ደህንነት እና ጤንነት ቀንን ምክንያት በማድረግ በተከናወነው በዚህ ፕሮግራም ላይ፤ ለሠራተኞች በመሰረታዊ መጀመሪያ ዕርዳታ ዙሪያ ተገቢውን እውቀትና ክህሎት ማስጨበጥ ጤናማና ምቹ የሥራ ቦታን ለመፍጠር ትልቅ መሠረት መሆኑ ተገልጿል። ይህም ለሠራተኛው ደህንነት ብቻ ሳይሆን ለተቋሙ ውጤታማነትም ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ተመላክቷል።
የኢንስቲትዩቱ የብቃትና የሰው ሀብት አስተዳደር ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ እልፍአገር ተተካ በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የሥልጠናው ዋና ዓላማ ሠራተኞች በሥራ ቦታቸው ላይ ሊደርሱ ከሚችሉ አደጋዎች ቀድመው እንዲጠነቀቁና አደጋ ቢደርስ እንኳን ፈጣንና ትክክለኛ እርምጃዎችን መውሰድ እንዲችሉ ግንዛቤ ማስጨበጥ መሆኑን አብራርተዋል።
"የሥራ አካባቢ ጤንነትና ደህንነት ጉዳይ ከሠራተኞች የሥራ ውጤታማነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ በሠራተኞች አዋጅ እና መመሪያዎች ላይ ተካቶ እየተሠራበት ይገኛል" ያሉት ወ/ሮ እልፍአገር፤ ከዘወትር ሥራዎች ጋር ተያይዘው ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና እክሎችን ለመከላከል ቅድመ ጥንቃቄን የዘወትር ልምድ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ተወካይ አቶ ከበደ እንዳልካቸው በበኩላቸው በመሰረታዊ የመጀመሪያ ዕርዳታ አሰጣጥ ላይ ሰፊ ማብራርያ የሰጡ ሲሆን፤ ኢንስቲትዩቱ ለሠራተኞቹ ደህንነት ትኩረት በመስጠት ይህንን ሥልጠና ማዘጋጀቱ የሚደነቅ ተግባር መሆኑንና በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል። አቶ ከበደ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ መረጃዎችን በማጣቀስ መሠረታዊ የሕይወት ክህሎት ትምህርት ያካፈሉ ሲሆን፤ በዕለቱ ተመራቂዎች አማካኝነትም ተግባራዊ የመጀመሪያ ደረጃ ዕርዳታ አሰጣጥ ሂደት ለታዳሚው ቀርቧል።
በተጨማሪም ስለ ደህንነት ሳይንሳዊ መሠረታዊ እሳቤዎችና አተገባበሮች በአቶ ታደሰ ገረመንፈስ አማካኝነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ጽሑፍ ቀርቦ የጋራ ውይይት ተካሂዶበታል።
ኢንስቲትዩቱ ለሁለተኛ ጊዜ ባከበረው በዚህ ዓለም አቀፍ የሥራ አካባቢ ጤንነትና ደህንነት ቀን መርሃ ግብር ማጠቃለያ ላይ፤ ሥልጠናቸውን ላጠናቀቁ 30 ሠራተኞች የሰርተፊኬትና የዕውቅና አሰጣጥ እንዲሁም የቃለ-መሐላ ሥነ-ሥርዓት ተፈጽሟል።
https://ephi.gov.et/የኢንስቲትዩቱ-ባለሙያዎች-የሠራተኞች-ጤ/