የፌደራል ተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት-ኢትዮጵያ The Federal Public Defenders Office-Ethiopia

የፌደራል ተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት-ኢትዮጵያ The Federal Public Defenders Office-Ethiopia

Share

Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from የፌደራል ተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት-ኢትዮጵያ The Federal Public Defenders Office-Ethiopia, Addis Ababa.

Justice Media Center plays instrumental roles in disseminating legal issues aimed to improve public awareness legal and judicial issues, policy level decisions, rule of law, human rights protection and good governance in Ethiopia and beyond.

19/04/2025
Photos from የፌደራል ተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት-ኢትዮጵያ The Federal Public Defenders Office-Ethiopia's post 07/04/2025

በአካል በችሎት በሌለበት "የችሎት መድፈር ወንጀል ፈጽሟል።" በማለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀጣዉ የጽ/ቤታችን ተከላካይ ጠበቃ በይግባኝ የስር ፍርድ ቤት ዉሳኔ አስሻረ።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስር የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዉሳኔ የሻረበትን ሙሉ ዉሳኔ ለግንዛቤ ከስር አያይዘነዋል። አዎንታዊና የፍትህና ዳኝነት ስርዓት ለመገንባት የሚያግዙ አስተያየቶች እናበረታታለን።

. . . . . . . . . . . . / / . . . . . . . . . . . . .

የጉዳዩ አመጣጥ በአጭሩ:-

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተከላካይ ጠበቆች ፅ/ቤት ባልደረባ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ በላይ በፅ/ቤታችን አሰራር መሰረት በከባድ ግድያ ወንጀል ለተከሰሰ ተከሳሽ በተከላካይ ጠበቃነት ሙያዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ተመድበዋል።

በተመደቡት መሰረት መዝገቡ በሚሰማበት እለት በቀን 21/06/2017 በችሎት ቀርበው ተሰይመዋል። በዚህም ከሳሽ ዐቃቤ ህግ ጉዳዮን ያስረዱልኛል ያላቸውን 12 ምስክሮች መካከል ስድስቱ በችሎት የቀረቡ ሲሆን ዐቃቤ ህግም የቀረቡት ምስክሮች እንዲሰሙ ያልቀረቡት ምስክሮች በተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰሙ ያሳስባል። የተከሳሽ ተከላካይ ጠበቃም ተከሳሽ የተከሰሰበት ድንጋጌ ከባድ ድንጋጌ ከመሆኑ አንፃርና ከተከሳሽ ጋር ያልተነጋገርን በመሆኑ እና የዐቃቤ ህግ ምስክሮች የሚያስረዱት ጭብጥ ተመሳሳይ በመሆኑ ምስክሮች ተነጣጥለው ሊሰሙ አይገባም በተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰሙ ፍርድ ቤቱን አሳስቧል።

ፍርድ ቤቱም ጉዳዮን ለመስማት ከሰዓት በኋላ 8:00 ሰዓት ላይ ቀጠሮ ይሰጣል። ከሰዓት በኋላ በነበረው ቀጠሮ ተከላካይ ጠበቃው በአጋጠማቸው እክል ምክኒያት ችሎት አልቀረቡም።

ፍርድ ቤቱም ተከላካይ ጠበቃው ችሎት ያልቀረቡ በመሆኑ የዐቃቤ ህግና የግል ተበዳይን አስተያየት ይጠይቃል። ዐቃቤ ህግ ተከላካይ ጠበቃው ቀጠሮ አውቀው ሳይቀርቡ የቀሩ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ እርምጃ እንዲወስድ ያሳስባል። የግል ተበዳይ እናትም ተከላካይ ጠበቃው ከተከሳሽ ጋር ተመሳጥሮ ምስክሮች እንዳይሰሙ አድርጓል ብለው ለችሎቱ ያስረዳሉ።

ፍርድ ቤቱም ተከላካይ ጠበቃው በችሎት ሳይቀርብ በመቅረቱ 06 የዐቃቤ ህግ ምስክሮች እንዳይሰሙ ሆኗል፣ ፍርድ ቤቱም የእለት ስራውን እንዳያከናውን አድርጓል። ይህን ድርጊት ስንመዝነውም ድርጊቱ የችሎት ስራ የማወክ ድርጊት መፈፀማቸውን ያረጋገጠ ስለሆነ ተከላካይ ጠበቃ አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ በወ/ህ አ/ቁ 449/1-ለ ስር ጥፋተኛ ናቸው በማለት ውሳኔ ይሰጣል።

በዚህም ፍርድ ቤቱ ተከላካይ ጠበቃው ጥፋተኛ የተባለበት ድንጋጌ ከአንድ አመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከሶስት ሽህ ብር የማይበልጥ መቀጮ የሚያስቀጣ በመሆኑ በብር 3000 መቀጮ እንዲቀጣ ውሳኔ ሰጥቷል።

የመስሪያ ቤታችን ባልደረባ በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ጉዳዮን ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን በዚህም ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በቀን 10/07/2017 ቅጣቱ እንዳይፈፀም እግድ በመስጠት በቀን 29/07/2017 በጉዳዮ ላይ ውሳኔ ሰጥቷል።

በተከላካይ ጠበቃ በኩል የቀረበው ዋነኛ የቅሬታ ነጥብ
***
1ኛ የችሎት መድፈር ወንጀልን ሊያቋቁም የሚችል ድርጊት አልፈፀምኩም፤

በመሰረቱ የፍርድ ቤት መድፈር ወንጀል ምንነት ከድንጋጌዎ መረዳት የሚቻለው፤
"ማንም ሰው በፍርድ ቤት ምርመራ በሚደረግበት ወይም የፍርድ ስራ በሚከናወንበት ጊዜ፦
ሀ) ፍርድ ቤቱን ወይም የዳኝነት ሥራ በማከናወን ላይ ያለውን ዳኛ በማናቸውም መንገድ የሰደበ፣ ያወከ ወይም በእነዚሁ ላይ ያፌዘ ወይም የዛተ እንደሆነ ወይም
ለ) የፍርድ ቤቱን ሥራ በማናቸውም ሌላ መንገድ ያወከ እንደሆነ፤" የሚል ነው።
ከዚህ ድንጋጌ የምንረዳው አንድ ሰው ፍርድ ቤትን ደፍሯል ለማለት በአካል በችሎት ተገኝቶ የተገለፀውን ድርጊት መፈፀም መቻል አለበት። በድንጋጌው ንዑስ 1 ላይ በመርሆ ደረጃ የተቀመጠው "በፍርድ ቤት ምርመራ በሚደረግበት ወይም የፍርድ ስራ በሚከናወንበት ጊዜ" በማለት በግል የተቀመጠው ድንጋጌ ፍርድ ቤትን ለመድፈር በፍርድ ቤት በአካል መገኘት እና ፍርድ ቤቱ የሚያደርገውን ምርመራ ወይም የፍርድ ስራ ማወክን ይጠይቃል።

ይግባኝ ባይ በእለቱ ባጋጠመኝ የግል እክል ጉዳይ ለዛውም ለመጀመሪያ ግዜ ምስክር ለመስማት በተቀጠረ መዝገብ አለመቅረቤ ከላይ የተገለፀውን ድንጋጌ ተላልፏል ሊባል የሚያስችል አይደለም። ባልቀረብኩበት ችሎት እንዴት አድርጌ ነው ፍርድ ቤን ደፍረሃል ልባል የምችለው?

የድንጋጌው ንዑስ 1/ለ ላይ "የፍርድ ቤቱን ሥራ በማናቸውም ሌላ መንገድ ያወከ እንደሆነ፤" በማለት የተመለከተው ተግባራዊ ለማድረግ በንዑስ አንድ የተገለፀው የድንጋጌው መርሆ እና መሠረታዊ መነሻ ነጥብ እሱም በአካል ፍርድ ቤት መገኘትና የፍርድ ስራ የሚያከናውነውን ችሎት ማወክ ይጠይቃል።

ስለሆነም የተከበረው ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ከወንጀል ህግ መርሆና አላማ ውጭ የወንጀል ህግ ድንጋጌ አ/ቁ 449 ወሰኑንን እጅጉን አስፍቶ፣ በማመሳስል የወንጀል ድርጊትን ፈጥሮ፣ ወንጀል የማድረግ የሀሳብ ክፍል፣ ድርጊትና በሃሳብና በድርጊት መካከል ኮንኮረንስ ባልተፈጠረበት፣ አንድ ወንጀል ተደረገ የሚባልበትን ወንጀልን የሚያቋቁሙ ህጋዊ፣ ግዙፋዊና ሞራላዊ ፍሬ ነገር ተሟለተው ሳይገኙ በአጠቃላይ የወንጀል ህግን መሰረታዊ መርሆዎችን በታቀረነ ሁኔታ የተሰጠብኝን የጥፋተኝነት ውሳኔ እጅጉን ቅር ስላሰኘኝ በመመርመር እንዲሽርልኝ።


2ኛ ከሙያ ነፃነት እና ተጠያቂነት አሰራር አንፃር
አንድ የህግ ባለሙያ የተጣለበትን የሙያ ግዴታ በአግባቡ ለመወጣት የሙያ ነጻነት እና የሙያ ግዴታወን ተላልፎ ሲገኝ ደሞ ሙያ ተጠያቂነት ያለበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይግባኝ ባይ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተከላካይ ጠበቆች ፅ/ቤት ተከላካይ ጠበቃ እንደመሆኔ መጠን ሙያዊ ነጻነት እና ተጠያቂነት አለብኝ፡፡

በእለቱ በገጠመኝ እክል ችሎት አለመቅረቤ መሠረት በማድረግ የስር ፍርድ ቤት ማድረግ የሚገባው አግባብ ያለው የሥነ ሥርዓት አካሄድ በእለቱ በችሎት አለመገኘቴን መሠረት በማድረግ ያልተገኘሁበትን ምክኒያት በችሎት እንዳስረዳ እና ያቀረብኩት ምክኒያት አሳማኝ ሁኖ ፍርድ ቤቱ ያላገኘው ከሆነ አግባብነት ያለውን የተጠያቂነት አሰራር ተከትሎ ለፌደራል ተከላካይ ጠበቆች ፅህፈት ቤት ማሳወቅ ነው።

በዚህም እንደማንኛውም ነፃነትና ተጠያቂነት ያለበት ሙያ የሚያስተዳድረኝ ተቋም የፈፀምኩት ድርጊት በስነ ምግባር ጥሰት የሚያስጠይቀኝ ነው ብሎ ካመነ በፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አማካኝነት የስነ ምግባር ጥሰት ክስ መስርቶብኝ እኔም የህጉን አግባብ ተከትየ ምላሽ በመስጠት ጉባኤው የመሰለውን ይወስናል።

በዚህ ጉዳይ ግን ፍርድ ቤቱ ለዛውም ለጉዳዮ አግባብነት የሌለውን ድንጋጌ ጠቅሶ ነገሩ ከሆነ ከአምስት ቀን በኋላ በቢሮ ተሰይሞ ክስ ሳይቀርብብኝ፣ በሌለሁበትና የመሰማት መብቴ ባልተከበረበት ሁኔታ በወ/ህ/አ/ቁ 449/1/ለ ጥፋተኛ ማለት የተከላካይ ጠበቆች የሙያ ነፃነትን በመጋፋት፣ በኢፊድሪ ህገ መንግስት የተጣለብንን ሙያዊ ኃላፊነት እንዳንወጣ ከማሸማቀቅ ባሻገር የሙያዊ ተጠያቂነት ሥነ ሥርዓት የሚጣረስ ስለሆነ የተከበረው ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ መርምሮ እንዲሽር የሚጠይቅ ነው።

ይግባኝ ሰሚው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ጉዳዮን ከመመርመረ በኋላ በተራ ቁጥር አንድ የተቀመጠተውን የይግባኝ ባይ አቤቱታ ሙሉ ለሙሉ በመቀበል እንደሚከተለው የውሳኔ ሀተታ ሰጥቷል።

ከወ/ህ 449/1/ሀ/ለ ድንጋጌዎች አንፃር ችሎት መድፈር ወንጀል ተፈፅሟል ለማለት ችሎት የሚደፍር ሰው በመርህ ደረጃ ችሎት ውስጥ መኖር ያለበት መሆኑን ከድንጋጌዎች መንፈስ መረዳት ይቻላል።

በችሎት የሌለ ከሆነም ችሎቱን ወይም ዳኛውን በማንኛውም መንገድ የሰደበ፣ ያወከ፣ ያፌዘ ወይም የዛተ እንደሆነ ወይም የፍርድ ቤቱን ስራ በማንኛቸውም ሌላ መንገድ ያወከ እንደሆነ የሚለውን ድንጋጌ በማድረግ የሚፈፀም ወንጀል መሆኑን የሚመለከት እንጅ አንድ ተከራካሪ ወገን ችሎት ሳይቀርብ መቅረት የሰደበ፣ ያወከ ወይም ያፌዘ ወይም የዛተ የሚለውን ድንጋጌ የሚያሟላ አይደለም።

በሌላ በኩል አንድ ተከራካሪ ወገን ችሎት ሳይቀርብ ከቀረ ወይም በምክኒያት ችሎት ካልተገኘ ፍርድ ቤቱ በችሎት መድፈር ወንጀል ከመቅጣት ይልቅ በህጉ አግባብ 94 መሠረት ቀጠሮ መለወጥ አሊያ ሌሎች አማራጮችን መውሰድ እንደሚችል ህጉ መፍትሔ አስቀምጧል።

ከዚህ አንፃር የሥር ፍርድ ቤት ይግባኝ ባይ ለምን ከችሎት እንደቀረ ሳይጠይቅና ሳያጣራ በእለቱ በቀን 21/06/2017 በሌለበት ጥፋተኛ ውሳኔ ሰጥቶ እንደገና ሳይጠሩና አስተያየት ሳይጠየቁ በቀን 05/07/17 ቅጣት መወሰናቸው ህጉን መሠረት ያላደረገ ከመሆኑ በላይ የመሠማት ህገ መንግስታዊ መብቱን የሚጋፋ በመሆኑ በሥር ፍርድ ቤት የተሠጠው የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ የህግም ሆነ የፍሬ ነገር ግድፈት ያለበት ስለሆነ ሊታረም የሚገባ ሁኖ አጊንተነዋል። በመሆኑም የስር ፍርድ ቤት የጥፋተኝነትና ቅጣት ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ ሽሮታል።

በመዝገቡ የልዮነት ኃሳብ ያላቸው ዳኛ የልዮነት ኃሳባቸውን የገለፁ ሲሆን ጭምቅ ኋሳቡም ይግባኝ ባይ ለምን ከችሎት እንደቀረ ምክኒያቱ ስላልታወቀ መዝገቡ ወደ ስር ፍርድ ቤት ተመልሶ የስር ፍርድ ቤት እንደገና አጣርቶ ይወስን የሚል ነው። በህጋችን መሠረት የአብላጫ ዳኞች ውሳኔ ገዥ ውሳኔ ይሆናል።

. . . . . . . . . . . . . . . / / . . . . . . . . . . . . .

ድምፅ ለሌላቸዉ ድምፅ እንሆናለን። የራሳችንን መብት አስከብረን የሌሎች መብት እንዲከበር እንተጋለን!

ሰኞ መጋቢት 29/2017 ዓ.ም

ተ/ጠ/ጽ/ቤት

Photos from የፌደራል ተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት-ኢትዮጵያ The Federal Public Defenders Office-Ethiopia's post 22/03/2025

በአሜሪካ ብሔራዊ ተከላካይ ጠበቆች ማህበር በተዘጋጀ የሁለት ቀናት የበይነ መረብ ስልጠና በስኬት ተጠናቀቀ።

አሜሪካ የተከላካይ ጠበቆች ማህበር (The American National Association for Public Defense /NAPD) የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት በስሩ የሚገኙ ተከላካይ ጠበቆች አቅም እንዲገነቡ በማለም በሰጠዉ ዕድል መሠረት ነዉ የተከላካይ ጠበቆች በዚህ ሐሙስ መጋቢት 11/2017 ዓ.ም - አርብ መጋቢት 12/2017 ዓ.ም በተሰጠ የ2 ቀን በይነ መረብ ስልጠና የተሳተፉት። ስልጠናዉ "Rise Resist Represent" በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሲሆን ተገልጋዮችን ወክሎ በችሎት ክርክር ማድረ ፣ ጥራት ያላቸዉ የሕግ የክርክር ሰነዶች አዘገጃጀት ፣ በተከራካሪ ወገን በሚቀርብ ማስረጃ ተአማኒነት እና የማስረዳት ሸክም ላይ ተከላካይ ጠበቃ መወጣት ስለሚጠበቅበት ሚና ፣ Artificial Intelligence ለፍትህና እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ፣ ተገልጋይ ተኮር አገልግሎት አሰጣጥ ማዕቀፎች ፣ ለተገልጋዮች መብት መከበር የሚያስችሉ ሙያዊ አማራጮች አሟጦ መጠቀም እና ተያያዥ ገዳዮች ላይ የአሜሪካ ተሞክሮ መሠረት ያደረገ ነበር።

የጽ/ቤታችን ተከላካይ ጠበቆች በዚህ ስልጠና እንዲሳተፉ ድጋፍ ያደረጉ የአሜሪካ ተከላካይ ጠበቆች ብሔራዊ ማህበር ዋና ዳይሬክትሬስ ሎሪ ጀምስ ከልብ ለማመስገን እንወዳለን። ለወደፊቱ የኢትዮጵያን ተጨባጭ እዉነታ ታሳቢ ያደረጉ የስልጠና መርሐ ግብሮች በማዘጋጀት የሀገራችን ተከላካይ ጠበቆች በፍትህ ስርዓት እየተጫወቱ የሚገኘዉን የማይተካ ሚና ይበልጥ ለማሳደግ የአሜሪካ ብሔራዊ የተከላካይ ጠበቆች ማህበር ተግባር በምርጥ ተሞክሮነት የሚወሰድ ነዉ።

Want your business to be the top-listed Government Service in Addis Ababa?

Click here to claim your Sponsored Listing.

Location

Telephone

Website

Address


Addis Ababa