19/03/2026
ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1447ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል አደረሳችሁ ፡፡
/ምክር ቤት ኮሚኒኬሽን 10/07/2018 ዓ.ም/
በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ሀይማኖታዊ ስነ - ስርዓት የሚከበረው የዒድ አልፈጥር በዓል የሠላም ፣ የፍቅር ፣ የደስታና የመረዳዳት በዓል እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሕዝበ ሙስሊሙ በታላቁ የረመዳን ጾም ወቅት ያሳየውን የመረዳዳትና የመተዛዘን ኢትዮጵያዊ እሴት በማስቀጠል ለተቸገሩና የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ያለዉን በማካፈል በዓሉን በአንድነት መንፈስ በደስታና በፍቅር ልናከብር ይገባል ።
ዒድ ሙባረክ !
የተከበሩ አቶ መኩሪያ ጉርሙ
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ
06/03/2026
የጉለሌ ክፍለ ከተማ የአሽከርካሪ ተሸከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ጉለሌ ቅርንጫፍ ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች " በአሽከርካሪ ተሸከርካሪ አሰራርና መመሪያ እና በአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ስራ ላይ በዋሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች" ላይ ስልጠና ሰጠ ፡፡
/ምክር ቤት ኮሚኒኬሽን 27/06/2018 ዓ.ም/
ስልጠናውን ያስጀመሩት የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ መኩሪያ ጉርሙ ተቋሙ ከዚህ ቀደም የመልካም አስተዳደር ችግሮች ጎልተው የሚታዩበት ተገልጋዩ ብዙ እንግልት የሚያገኝበት በምክር ቤት ጉባኤዎች ችግሮቹ በዘላቂነት እዲፈቱ የተወያየንበት ተቋም ነበር ፤ ዛሬ በሚያስደንቅ ሁኔታ ተቋሙን በቴክኖሎጅ በማዘመን ችግሮቹን ስር ነቀል በሆነ መልኩ እየፈታ የህዝብን እርካታ እየፈጠረ ተቋም ነው ።
ቋሚ ኮሚቴው በአሰራርና መመሪያው ላይ በቂ ግንዛቤ ይዘው እዲደግፉ ስልጠናውን ማዘጋጀቱን ምክር ቤቱ ከፍተኛ አድናቆት እዳለው ገልጸዋል ፡፡
ስልጠናውን የሰጡት የአሽከርካሪ ተሸከርካሪ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዳይሬክተሮች ተቋሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ የአሰራር መንገዶችን በማሸሻልና የተለያዩ የቴክኖሎጅ ሶፍት ዌሮችን በማበልጸግ ለተገልጋዮች የሚሰጠውን አገልግሎት ፈጣን ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋሙ ከዚህ በተሻለ አቅም ስራዎችን እንዲሰራ የምክር ቤቱ የመሰረተ ልማትና ማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ተናግረዋል ፡፡
05/03/2026
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት የመንግስት በጀት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከፋይናንስ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በበጀት ዝግጅት ፣ በኦዲት ግኝት አመላለስ ፣ እና በገቢ አሰባሰብ ዙሪያ ለክፍለ ከተማና ለወረዳ ምክር ቤት የንመንግስት በጀት አስተዳደር ጉዳዮች የቋሚ ኮሚቴ አባላት ስልጠና ሰጠ ፡፡
/ምክር ቤት ኮሚኒኬሽን 26/06/2018 ዓ.ም/
" በጀት " ለአንድ ሀገር እድገት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል ፤ የመንግስትን ውስን ሀብት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ማድረግ ያስፈልጋል ።
በስልጠናው ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ መኩሪያ ጉርሙ የክፍለ ከተማችን እድገትና ብልጽግና የምናረጋግጠው በጀታችን በአግባቡ ስንጠቀምና አስፈጻሚ አካላት በእቅዳቸው መሠረት በጀታቸውን ማዋል ሲችሉ ነው ብለዋል ።
ከበጀት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ብልሹ አሰራሮችንና የኦዲት ግኝቶችን በእግባቡ መፈተሽና ማረም ያስፈልጋል ብለዋል ።
የተሰጠው ስልጠና ቋሚ ኮሚቴዎች አስፈጻሚ አካላትን ድጋፍና ክትትል ሲያደርጉ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ድጋፍና ክትትል እንደያደርጉ ስለሚያግዝ ውጤታማ ስራ ለመስራት እና የመንግስት ውስን ሀብት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ያደርጋል ብለዋል ።
05/03/2026
የፓርላማና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት የጉለሌ ተመራጮች ባለፉት 5 ዓመታት የመረጣቸውን ህዝብ በታማኝነትና በቁርጠኝነት ማገልገላቸውን መራጮች ገለጹ ።
/ምክር ቤት ኮሚኒኬሽን 26/06/2018 ዓ.ም/
የፓርላማና የአዲስ ከተማ ምክር ቤት አባላት የጉለሌ ክፍለ ከተማ ተመራጮች ከሀይማኖት አባቶች ፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከወጣቶች ጋር ባለፉት 5 አመታት የተሰሩ ስራዎችንና እና በቀጣይ መፈታት ያለባቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ ።
የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ መኩሪያ ጉርሙ የፓርላማና የአዲስ አበባ ከተማ የምክር ቤት አባላት የጉለሌ ተመራጮች ባለፉት አምስት አመታት የመረጣቸውን ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲመለሱ በርካታ ስራዎችን መስራታቸውን ገልጸዋል ፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት በክፍለ ከተማችን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች ተሰርተዋል ፤ የኗሪዎችን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮችን በልማት ፕሮጀክቶች ተፈተዋል ፤ በክፍለ ከተማችን የተሰሩ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች የክፍለ ከተማችን ገጽታና የህብረተሰባችን የኑሮ ዘይቤ ቀይረዋል ፤ አሁንም ልማቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወልዴ ወገሴ በክፍለ ከተማው ባለፉት አምስት ዓመታ የተሰሩ ዋና ዋና የልማት ስራዎች አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል ፤ የተቀናጀ የልማት ፕሮጀክቶች ስራዎች ፣ በስራ እድል ፈጠራ ፣ በኮሪደርና በወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ፣ ለሰራተኛው ምቹ የስራ ሁኔታ ከመፍጠር ፣ ፍትሀዊ የልማት ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ የተሰሩ ስራዎችን ሪፖርት አቅርበዋል ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የጉለሌ ተመራጯ ዶ/ር ቤተልሄም ላቀው ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት የጉለሌ ተመራጮች የተከበሩ ዶ/ር ማሾ ኦላና ፣ ዶ/ር ግዛቸው አይካ ፣ ዶ/ር ወርቅነሽ ባለፉት 5 ዓመታት በክፍለ ከተማተማው የተሰሩ የልማቶች ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችን ምላሽ የሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል ። አሁንም ከህብረተሰቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በቀጣይ ጊዚያት ምላሽ እንደሚሰጥ ገልጸዋል ።
7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ፣ ነጻ ፣ ዲሞክራሲያዊ እና አካታች በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ መልክታቸውን አስተላልፈዋል ።
በመድረኩ ላይ መራጩ ህብረተሰብ ባለፉት 5 ዓመታት በተጨባጭ የተሰሩ ስራዎችን በመግለጽ ፤ የክፍለ ከተማ ተመራጮች ለክፍለ ከተማው እድገትና ብልጽግና ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ፤ በቀጣይም በዘላቂነት የሚፈቱ ጥያቄዎችን ምላሽ የሚያስፈልጋቸውን ጥያቄዎች አቅርበዋል ።
05/03/2026
የጉለሌ ክፍለ ከተማን በመወከል የፓርላማና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ተመራጮች ከመረጣቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ማካሄድ ጀመሩ ።
03/03/2026
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት የእውቅና እና የምስጋና ሽልማት ተበረከተለት ።
/ምክር ቤት ኮሚኒኬሽን 24/06/2818 ዓ.ም/
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በ20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በአል አከባበር ላይ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የክፍለ ከተማ ምክር ቤቶች የእውቅና እና የምስጋና ሽልማት አበረከተ ።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት የ20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በክፍለ ከተማችን የኢትዮጲያን ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህል ፣ ወግና ማንነት ባንጸባረቀ መልኩ በድምቀት በማክበርና በማጠቃለያ በዓሉ ላይ ለመሳተፍ ወደ ከተማችን የመጡ እንግዶችን በክብር በመቀበልና በማስተናገድ የላቀ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ መኩሪያ ጉርሙ ከአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ከተከበሩ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር የምስጋና የእውቅና የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል ፡፡
26/02/2026
"ምርጫ" የመንግስት ስልጣን ለመያዝ በድምጽ ብልጫ የሚወሰንብት ወይም የሚመረጥበት መንገድ ነው ፡፡
/ምክር ቤት ኮሚኒኬሽን 19/06/2018 ዓ.ም/
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ፍትህ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች " በኢትዮጲያ የምርጫ ህግ " ላይ ስልጠና ሰጠ ፡፡
ስልጠናውን ያስጀመሩት የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ መኩሪያ ጉርሙ ለ7ኛ ጊዜ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እና በህጋዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ፣ መራጩ ህዝብ በትክክል ያመነበትን ነጻ ፣ ፍትሀዊና አካታች በሆነ መልኩ የሚያስተዳድረውን አካል በዲሞክራሲያዊ መንገድ መምረጥ እንዲችል አጠቃላይ በምርጫ ህጎች ላይ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የምርጫ ህጎችን በመረዳትና በመገንዘብ ምርጫው በሰላማዊና በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል ፡፡
ስልጠናውን የሰጡት የጉለሌ ክፍለ ከተማ ፍትህ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አስማማው ፍቃዱ ስለምርጫ መርሆችና ፣ ስለመራጮች እና ዕጮዎች ምዝገባ ፣ ስለምርጫ ዘመቻ እና መራጮች ቅስቀሳ ፣ ስለፖለቲካ ፓርቲዎችና አባሎቻቸው መብትና ግዴታዎች ፣ ስለ ስነምግባር ጥሰቶች እና ስለሚወሰዱ እርምጃዎች ፣ በምርጫ ወቅት ስለተከለከሉ ተግባራትና ቅጣታቸው ፣ ስለ ድምጽ ቆጠራና ውጤት … ወዘተ ሰፋ ያለ ግንዛቤ ሰጥተዋል ፡፡
በስልጠናው ላይ የተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶችን የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ አባይነሽ ቴኒ እና አቶ አስማማው ፍቃዱ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል ፡፡
18/02/2026
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት ከጉለሌ ክፍለ ከተማ የመልካም አስተዳደር ቅሬታና አቤቱታ አፈታት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች "በቅንጅታ አሰራር ማስፈጸሚያ ማንዋል" ላይ ስልጠና ሰጠ፡፡
/ምክር ቤት ኮሚኒኬሽን 11/06/2018 ዓ.ም/
" ቅንጅታዊ አሰራር " በተቋማት መካከል በመርህ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ የትብብር ሥርዓት መፍጠር ቀጣይነት ባለው መንገድ በተናጠል የጊዜ ብክነት እንዳይደርስና ከተገልጋዮች ፍላጎት ማደግ ጋር በተያያዘ የአገልግሎት አሰጣጥ ስታንዳርዶችን በጋራ በመንደፍና አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት ውጤታ ስራ ለማከናዎን ይረዳል።
" ቅንጅታዊ አሰራር " ተቋማት በቅንጅት እንዲሰሩ በማድረግ ፣ ተሻጋሪ የሆኑ ተግባራትን በጋራ ለማከናወን ፣ የተወሳሰቡ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ፣ ትብብርን ፣ ተግባቦትን እና የሀብት መጋራትን በማጎልበት የዜጎችን ፍላጎት በማሟላት ምላሽ ሰጪነታቸውን እና ውጤታማነታቸውን ለማሻሻል እንደ ሚረዳ በስልጠናው ላይ በስፋት ተገልጿል ።
ቋሚ ኮሚቴዎች አስፈጻሚ አካላትን ድጋፍና ክትትል በሚያደርጉበት ወቅት ቅንጅታዊ አሰራር ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ በስልጠናው ላይ ተገልጿል ።
ስልጠናውን የጉለሌ ክፍለ ከተማ የመልካም አስተዳደር ቅሬታና አቤቱታ አፈታት ጽ/ቤት የቅንጅታዊ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ግርማ ገ/ማርያም የሰጡ ሲሆን ፤ በስልጠናው ላይ የተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶችን የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም ምስጋናው እና የጉለሌ ክፍለ ከተማ የመልካም አስተዳደር ቅሬታና አቤቱታ አፈታት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ እንደሻው ምኒችል ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል ።
18/02/2026
" ድንገተኛ ምልከታ "
/ምክር ቤት ኮሚኒኬሽን 11/06/2018 ዓ.ም/
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት አስፈጻሚ አካላት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የድንገተኛ ምልከታ አደረገ።
ምክር ቤቱ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማት አስተዳደር ጽ/ቤት ፣ የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ጉለሌ ቅርጫፍ ፣ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ጽ/ቤት ፣ የቤቶች ልማት አስተዳደር ጽ/ቤትና የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ተቋማት ላይ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን ተዘዋውሮ ተመልክቷል ፡፡
ምልከታ በተደረገባቸው ተቋማት የተቋሙ አመራሮችና ባለሙያዎች በሰዓቱ በመገኘት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል ፡፡
ተቋማቱ የአገልግሎት አሰጣጥ እንቅፋቶችን በመቅረፍ አሰራራቸውን እየፈተሹ የአገልግሎት አሰጣጣቸውን እያዘመኑ ፈጣን ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን እና ተገልጋይ የማጉላላት እና የመማመላለስ ችግሮች እየቀነሱ መሆኑ በምልከታው ታይቷል ፡፡
በተቋማቱ ላይ የታዩ ውስንነቶች ለተገልጋይ መረጃ የሚሰጥ የመረጃ ዴስክ መረጃ ሰጪ ባለሙያ አለመኖር ፣ የባለሙያ እጥረት ፣ የቢሮ ጥበት … ወዘተ ተስተውለዋል ፡፡
10/02/2026
ሹመት
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት በ13ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤው የቀረበለትን ሹመት መርምሮ አጸደቀ ።
/ምክር ቤት ኮሚኒኬሽን 03/06/2018 ዓ.ም/
1. አቶ ተስፋዬ ፈይሳ ፡ - የጉለሌ ክፍለ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ፅ/ቤት ሀላፊ
2. አቶ ባርኬ ዴቲ ፡- የጉለሌ ክፍለ ከተማ ትምህርት ፅ/ቤት ሀላፊ
በማድረግ ሹመታቸውን አጽድቋል ።
10/02/2026
ምክር ቤቱ የ13ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሄደ።
/ምክር ቤት ኮሚኒኬሽን 03/06/2018 ዓ.ም/
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት የ2018 በጀት ዓመት የ13ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን በዛሬው ዕለት ያካሄደ ሲሆን በአስተዳደሩ የ2018 በጀት አመት የ6 ወር ሪፖርት የምክር ቤት አባላት በየቡድናቸው የተወያዩባቸውን በማቅረብ መልካም አፈፃፀም ያላቸው ተግባራት በማድነቅ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና በዕቅድ ተይዘው ደግሞ በአፈፃፀማቸው ላይ ውስንነት ያሳዩት ተግባራት የእርምት እርምጃ እንዲወሰድና አስተዳደሩ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በስፋት እንዲረጋገጥ መሰራት እንዳለበት ተጠይቋል ።
የጉለሌ ክለተማ አስተዳደር ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወልዴ ወገሴ ምላሽ በመስጠት የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል ።
የክፍለ ከተማው አስተዳደር ባለፉት ስድስት ወራት በነቃ የነዋሪዎች የልማት ተሳትፎ እና የጋራ ድጋፍ የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶችን በማጠናከር የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።
የከተማ ግብርና ፣የሸማቾች እና የንግድ ተቋማትን አቅም በማጠናከር ኑሮ ውድነትን በልዩ ትኩረት ማረጋገጥ ፤ በዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሌብነትና ብልሹ አሰራር በመከላከል የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል ፤ የጉለሌ ልዩ መለያ የሸማና የሸክላ የእደጥበብ ጥበብ ውጤቶችን በስፋት በማስተዋወቅ ክፍለ ከተማችን የቱሪስት መስብ ማድረግ ፤ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ የተማሪዎች የምገባ ማስፋፊያ ግንባታ ማጠናከር ፤ የመስሪያ ቦታዎችን ግንባታና አቅርቦትን በማጠናከር አስተማማኝና ፍትሃዊ የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ማረጋገጥ በትኩረት መስራት ፤ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የተሰሩ የልማት ስራዎችን በባለቤትነት ተከታትሎ በመጠበቅ አጋዥ አድርጎ መስራት።
የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባዔ የተከበሩ አቶ መኩሪያ ጉርሙ በበኩላቸው ምክር ቤቱ በ2018 በጀት ዓመት ውጤታማና ስኬታማ ተግባራት ማከናወናቸውን ገልፀው በተለይም አስፈፃሚ አካላትን በመደገፍና በመቆጣጠር አስፈጻሚ መስሪያቤቶች የሚሰጡትን አገልግሎት የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና እርካታ እንዲረጋገጥ ምክር ቤቱ እንደ ሁል ግዜዉ በትኩረት ከቋሚ ኮሚቴዎች ጋር እንደተሰራ ገልጸዋል ።
10/02/2026
በጉባኤው ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች የአስፈጻሚ ተቋማት አመራሮች ምላሽና ማብራሪያ ፤
/ምክር ቤት ኮሚኒኬሽን 03/06/2018 ዓ.ም/
በመሬት ማኔጅመንት አገልግሎት ዙሪያ የሚነሱና የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ተቋሙ እየሰራ ነው ፤ በእሁድ ገበያዎች ላይ በቂ ምርት የማስገባት ስራ ተሰርቷል ፤ በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት የግብዓት ፍጆታ አቅርቦት እጥረትን ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ ነው ፤ በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ላይ ያሉ የአሰራር ማነቆችን በመፍታት ማህበራቱ ተገቢውን አገልግሎትን እንዲሰጡ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው ፣ በፋይናንስ አሰራር ላይ ከወረቀት ነጻ በሆነ መንገድ በድጅታል አሰራር አገልግሎት እየተሰጠ ነው ፤ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃዎች እየተሰራ ነው ፤ የውሀና የመብራት መቆራረጥን ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ ነው ።