09/04/2026
በዲጂታል ዘመን የእጅ ስልክዎ የባንክ ሂሳብዎ መሆኑን ያውቃሉን⁉️
+++++++++++++++
ባንበት በዚህ ዘመን የዲጂታል አገልግሎቶች እንደ ሀገር እያደገ ይገኛል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የዲጂታል ማጭበርበርን ለመከላከል የሚያስችሉ የጥንቃቄ መልዕክት ሲተላለፉም ይሰተዋላል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባወጣው መረጃ እንዳመላከተው በዲጂታል ዘመን ስልክ እንደ ባንክ ሂሳብ እያገለገለ መሆኑን ጠቅሶ፣ ደንበኞች በጥቃቅን ስህተቶች የዘመናት ጥሪታቸውን ለዘራፊዎች አሳልፈው እንዳይሰጡ አሳስቧል።
ሚስጥራዊ ቁጥሮችን ለሌላ አካል አሳልፎ መስጠት ለማጭበርበር ዋነኛው መንገድ እየሆነ መጥቷል ብሏል።
ደንበኞች ሊተገብሯቸው የሚገቡ ስድስት ቁልፍ ነጥቦችን እንደሚከተለው ዘርዝሯል፤
• ሚስጥራዊነትን መጠበቅ፦ ማንኛውም ደንበኝ የባንክ ሂሳብ ቁጥሩን፣ የሞባይል ባንኪንግ የይለፍ ቃልና በስልክ የሚላኩ የአንድ ጊዜ የማረጋገጫ ቁጥሮችን (OTP) ለማንኛውም አካል አሳልፎ መስጠት የለበትም።
• አጠራጣሪ ጥሪዎች፦ ባንኩ በስልክ ደውሎ ሚስጥራዊ ቁጥር እንደማይጠይቅ ያስታወሰው መግለጫው፣ ደንበኞች በማይታወቁ አካላት የሚላኩ ሊንኮችን እንዳይከፍቱ አስጠንቅቋል።
• የይለፍ ቃል ጥንካሬ፦ የሞባይል ባንኪንግ የይለፍ ቃል ቢያንስ ስድስት ድጂትና በቀላሉ የማይገመት መሆን እንዳለበት ተመልክቷል።
• የማህበራዊ ሚዲያ ወጥመዶች፦ በሽልማት፣ በስራ ማስታወቂያ ወይም በቴሌግራም/ዋትስአፕ በኩል የሚላኩ የማረጋገጫ ቁጥሮችን ለሌላ አካል መስጠት ለከፍተኛ ዝርፊያና ለወንጀል ተጋላጭ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ደንበኞች ስልካቸውን ለጥገናም ሆነ ለሌላ ጉዳይ ለሰው ሰጥተው ሲቀበሉ አጠራጣሪ መተግበሪያዎች (Apps) አለመጫናቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አሳስቧል። ይህ የጥንቃቄ መልዕክት የወጣው በዲጂታል የክፍያ አማራጮች ላይ የሚታዩ የማጭበርበር ድርጊቶችን ለመግታት ባንኩ እያደረገ ያለው ጥረት አካል መሆኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች እነዚህን መመሪያዎች በመተግበር ገንዘባቸውን ከማንኛውም የሳይበር ጥቃትና ዝርፊያ እንዲከላከሉ ጥሪውን አስተላልፏል።
07/04/2026
ህብረተሰቡ ጥራትና ደህንነታቸው ያልተረጋገጡ ምርቶችን እንዳይጠቀም ባለስልጣኑ አሳስቧል
++++++++++++++
በበዓላት ሰሞን ሸማቾች ግብይት ሲፈጽሙ ደረጃቸውን ባልጠበቁ፣ የደረጃ መስፈርቶችን የማያሟሉ፣ ጥራትና ደህንነታቸው ያልተረጋገጡ ምርቶችንም ከመሸመትና ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አሳስቧል።
በበዓላት ሰሞን የሚታየውን የገበያ እንቅስቃሴ በመጠቀም፣ ህገ-ወጥ ነጋዴዎችና ግለሰቦች የተለያዩ የማታለል ስልቶችን ሲከቱ ይሰተዋላል። በዚህ ወቅት ሸማቾች ግብይት ሲፈጽሙ ከአጭበርባሪዎችና ካልተገቡ የንግድ ስርዓቶች ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል።
በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ዱከም፣ሰበታ፣ ቡራዩ፣ ሱሉልታ፣ ለገጣፎ፣ ገላን በሚገኙ 570 የንግድ ተቋማት ላይ ባደረገው ፍተሻ አስገዳጅ የጥራትና የገላጭ ጽሁፍ መስፈርቶችን (CES 73) ያላሟሉ ሕገወጥ ምርቶች በገበያ ላይ መገኘታቸውን ገልጿል።
እነዚህም 32 የገበታ ጨው፣19 የምግብ ዘይት፣6 የለውዝ ቅቤ፣6 የማር የምርት አይነቶች፣ የከረሜላ፣ የዱቄትና የህፃናት ተጨማሪ ምግቦች ደረጃቸውን ያልጠበቁ ሆነው በገበያ ቁጥጥር ወቅት ተደርሶበታል።
ህብረተሰቡ ጥራትና ደህንነታቸው ያልተረጋገጡ የሚከተሉትን ምርቶች እንዳይጠቀም ባለስልጣኑ አሳስቧል።
የገበታ ጨው (32 ዓይነቶች) ፦ ሰይፋ፣ ቲና፣ እሙሹ፣ ቃሊ፣ አዮዲን፣ እኑ፣ አራዳ፣ ንጉስ፣ ሀሮት፣ ኩል፣ አሜን፣ ሰቦኑማ፣ እቱ፣ መክሊት፣ ዳግም፣ መርሰን፣ ኒሀል፣ ሊቅ፣ ስካይ፣ ናፊ፣ አቤ፣ ሳሮማ፣ ፀሐይ፣ ማሩ፣ ንጉስ፣ እንቁ፣ ሰኒ፣ ሚያዋ፣ ስኬት፣ ሔራል፣ ቤዝ እና ገዳ
የምግብ ዘይት (19 ዓይነቶች) ፦ ምስራቅ ፀሐይ፣ ቃል፣ አፍራን፣ ኒያ፣ ሪሃ፣ ኤአይ ሻኪር፣ ኤ1-ኑር፣ ጥራ፣ ረዲ፣ አያን፣ ሳፊያ፣ እሰይ የተጣራ ፣ አማን፣ ላምሮት ኬኬ፣ እድገት፣ ራኒያ፣ ሸገር፣ ሀይላለ እና ፍፁም የተጣራ
የለውዝ ቅቤ ፦ ሀራ ፣ ሶራ፣ ብሉ፣ ስዊት ክሬም፣ ሉሲ እና ስንቅ
ማር ፦ ቤዛ፣ ውብሸት የማር ጠጅ ፣ ጂጂ፣ አምባሰል እና የኢሉባቦር ማር
ከረሜላ ፦ : ቡርቃ ሎሊፖፕ፣ አዩ ፓፕ፣ አፍሪ እና ዴሉክሴ ከረሜላዎች፤
ህብረተሰቡ ስለሚገዛው ምርት ትክክለኛ መረጃ እንዲኖረው ማንኛውም ምርት ወደ ገበያ ከመውጣቱ በፊት የሚከተሉትን አስገዳጅ የገላጭ ጽሁፍ (CES 73) መስፈርቶች ማሟላት እንዳለበት አሳስቧል
• የገላጭ ጽሁፍ፦ በግልጽ የሚታይ፤
• የአምራች መረጃ፦የድርጅቱ ስም እና ሙሉ አድራሻ መገለጽ አለበት፤
• የምርት ዝርዝር፦ የምርቱ የወል ስም፣ የክብደት መጠን፣ የተመረተበትና የሚያበቃበት ቀን፤
• መለያ ቁጥር (Batch Number)፦ ችግር ቢገኝ ምርቱን ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል መለያ፤
• የጥራት ምልክት፦ አስገዳጅ የደረጃ ምልክት መለጠፍ፡፡
እነዚህ መስፈርቱን የማያሟሉ፣በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያልተመዘገቡ፣ ጥራትና ደህንነታቸው ያልተረጋገጡ ሕገ-ወጥ የምግብ ምርቶች በመሆናቸው ህብረተሰባችን እንዳይጠቀማቸው አስጠንቅቋል።
#ሐሰተኛየብርኖቶች #የጥንቃቄመልዕክት #ሀሰተኛመረጃ
06/04/2026
ብሔራዊ ባንክ በሕገ-ወጥ የገንዘብ አስተላላፊዎች ላይ የሰጠው ማስጠንቀቂያ
++++++++++++++
- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መጋቢት 25 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው ይፋዊ መግለጫ፤ 23 የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ያለባንኩ እውቅና እና ፈቃድ እየሰሩ መሆኑን ገልጿል።
እነዚህ ተቋማት ከመጀመሪያው ፈቃድ የሌላቸው ወይም ቀደም ሲል የነበራቸው ፈቃድ በሕገ-ወጥ ተግባራት ምክንያት የተሰረዘ መሆኑን ባንኩ አረጋግጧል።
ኅብረተሰቡ የገንዘብ ደህንነቱን ለመጠበቅና በሕገ-ወጥ ተግባራት ውስጥ እንዳይሳተፍ በእነዚህ ድርጅቶች በኩል ገንዘብ ከመላክ እንዲቆጠብ ባንኩ አሳስቧል። በኢትዮጵያ ውስጥ የገንዘብ ዝውውር አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ የሌላቸው ናቸውም ብሏል።
እነዚህም ድርጅቶች አዱሊስ መኒ ትራንስፈር፤ አማና ኤክስፕረስ፤ አዋሽ ዳይሬክት፤ ባካኣል መኒ ትራንስፈር፤ ሆልደን ግሎባል፤ ኦሊምፒክ ፋይናንሻል ግሩፕ ፤ ታአጅ መኒ ትራንስፈር፤ ዋይዝ ትሬዲንግ መኒ ትራንስፈር፤ ወርልድ ዳይሬክት ሊንክ እና ሌሎችም እንደሚገኙበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡
ማንኛውም የውጭ ሀገር የገንዘብ ዝውውር በሕጋዊ የባንኮችና እውቅና ባላቸው የገንዘብ አስተላላፊ ወኪሎች በኩል ብቻ መከናወን እንዳለበት ተገልጿል።
በሀና እጅጋየው
#ጥንቃቄ
03/04/2026
"የትራንስፖርት አገልግሎት ይቆማል" በሚል የሚሰራጨው መረጃ ሐሰተኛ መሆኑ ተገለጸ
+++++++++++++++
- "የትራንስፖርት አገልግሎት ይቆማል" በሚል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ስምና ሎጎ የሚሰራጨው መረጃ የተሳሳተና ሐሰት መሆኑን የንግድና ቀጣናው ትስስር ሚኒሰቴር አስታወቀ።
በነዳጅ አቅርቦት ችግር ምክንያት "የትራንስፖርት አገልግሎት ይቆማል" በሚል የተሰራጨው መረጃ ተገቢነት የሌለውና መንግስት የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቆም ያስተላለፈው ምንም ዓይነት ትዕዛዝ የለም ተብሏል።
የትራንሰፖርት አገልግሎቱ እንደተለመደው ይቀጥላል። ነዳጅን በተመለከተ የሚወጡ አዲስ መረጃዎች በተደራጀው የሁኔታዎቸ መከታተያ ልዩ ክፍል ይፋ ይደረጋል።
በመሆኑም ህብረተሰቡ ከማይታወቁ ምንጮች የሚወጡ መረጃዎችን ባለማጋራት የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት እንዲከላከል ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ገልጿል።
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በነዳጅ ማዲያዎች ቅድሚያ አገልግሎት የሚያገኙ ተቋማትን ተቋማትን ይፋ አደርጓል ይታወሳል።
#ጥንቃቄ
31/03/2026
የጥራት ጉድለት የታየበት የፌኒቶይን መድኃኒት በአስቸኳይ እንዲመለስ ታዘዘ
+++++++++++++++
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የባህር ዳር ቅርንጫፍ፣ ሜዲካመን ባዮቴክ ሊሚትድ በተባለ ኩባንያ የተመረተ ለሚጥል በሽታ (Epilepsy) መቆጣጠሪያ የሚያገለግለውን የፌኒቶይን 100 ሚሊ ግራም (Phenytoin 100 mg) ታብሌት መድኃኒት የጥራት ችግር ስላለበት ከጤና ተቋማት በአስቸኳይ እንዲሰበሰብ በደብዳቤ ማዘዙን አስታወቀ።
የቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ለሁሉም የጤና ተቋማት በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንደገለጸው፣ በአምራቹ የተመረቱት የዚህ መድኃኒት ባቾች በሙሉ የጥራት ደረጃውን ባለማሟላቱ ተመላሽ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
ይሁን እንጂ እስካሁን መድኃኒቱን የመለሱ ቢሆንም፣ መድኃኒቱን ያልመለሱ ተቋማት ያላቸውን ቀሪ መጠን በደብዳቤ ገልጸው እስከ መጋቢት 18 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ እንዲያሳውቁ ጥብቅ ማሳሰቢያ ቢሰጥም፣ እስካሁን ድረስ አንዳንድ የጤና ተቋማት አለመመለሳቸውን አገልግሎቱ ገልጿል።
ይህንን ትዕዛዝ ተላልፈው መድኃኒቱን ተመላሽ የማያደርጉ ተቋማት ለሚከሰት ለጤና መታወክ ሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በመረጃው እንዳመላከተው በተጠቀሰው ባች የተመረተው ምርት ከ19ኙም የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እንዲሰበሰቡ አሳስቧል። ዜጎች ለሚጥል በሽታ መድኃኒት ሲጠቀሙ በጤና ባለሙያ የታዘዘላቸውና ጥራቱ የተረጋገጠ መሆኑን እንዲያረጋግጡ ይመከራል።
በሀና እጅጋየሁ
#ተጠንቀቁ
24/03/2026
ሚኒስቴሩ “OK” የተሰኘው በረኪና የጥራት መስፈርትን ባለማሟላቱ ሕዝቡ እንዳይጠቀም አሳሰበ
++++++++++++++++
- የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር “OK” በሚል የንግድ ስም ወደ ገበያ የሚቀርበው የበረኪና ምርት፣ አስገዳጅ የሆነውን የኢትዮጵያ የጥራት ደረጃ መስፈርት የማያሟላና ለጤና ጠንቅ መሆኑ ስለተረጋገጠ ሕብረተሰቡ ምርቱን ከመጠቀም እንዲቆጠብ አሳሰበ።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዛሬ መጋቢት 14 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፣ በገበያ ላይ ባደረገው የኢንስፔክሽንና የክትትል ሥራ በምርቱ ላይ ወካይ ናሙና በመውሰድ የእይታና የላቦራቶሪ ምርመራ አድርጓል።
በዚህም መሰረት በምርቱ ማሸጊያ ላይ የአምራቹ ስም፣ አድራሻ እና ብሔራዊ የደረጃ ምልክት የማይታይባቸው መሆኑ ተረጋግጧል ብሏል።
ከእይታ ፍተሻው ባለፈ በተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራ፣ ምርቱ በውስጡ የያዘው የሶዲየም ሃይድሮክሳይድ መጠን እና የመረጋጋት ሁኔታ፣ አስገዳጅ የሆነውን የኢትዮጵያ የጥራት ደረጃ እንደማያሟላ ተገልጿል።
ይህም ምርቱ ለታለመለት አገልግሎት የማይውልና የጥራት ጉድለት ያለበት መሆኑን ያሳያል ተብሏል።
ሚኒስቴሩ የሕዝብን ጤና፣ ደኅንነትና ጥቅም ለማስጠበቅ ባለው ሥልጣን መሠረት፣ ምንጩ የማይታወቀውና የጥራት ችግር ያለበት ይህ ምርት በገበያ ላይ እንዳይሰራጭ በየደረጃው በሚገኙ የክልልና የከተማ አስተዳደር የንግድ ቢሮዎች በኩል ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ አዟል።
ማንኛውም ነጋዴ፣ በንግድ ሱቆችም ሆነ በሱፐር ማርኬቶች ውስጥ ይህንን ምርት ሲሸጥ ቢገኝ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።
#ተጠንቀቁ
21/03/2026
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በጠና ታመዋል በሚል እየተጋሩ ያሉ ምስሎች ሐሰተኛ መረጃዎች ናቸው
+++++++++++++++++
- በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ‘’የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በገጠማቸዉ የጤና መታወክ ምክንያት በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች፣ አቡ ዳቢ በሚገኝ ሆስፒታል ህክምና ላይ ናቸው ‘’በሚል እየተሰራጨ ያለው መረጃ ሐሰተኛ መሆኑን የፕሬስ መረጃ ማጣሪያ አረጋግጧል።
በአንድ የህክምና ማዕከል ሲታከሙ የሚያሳዩ ምስሎችም በማህበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት እየተሰራጩ ይገኛሉ።
እየተሰራጩ ያሉ ምስሎችን በተመለከተ በሰው ሰራሽ አስተውሎት(AI)ን በመጠቀም ባደረግነው የመረጃ ማጣራት በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ እንዲሁም በፌስቡክ የተጋሩ ምስሎች በGoogle AI /ጉግል ኤ አይ /የተፈበረኩ እንደሆነ ማረጋገጥ ችለናል።
በዚህም መሰረት ህብረተሰቡ መሰል የተሳሳቱ መረጃዎችን ሳይደናገር ፣ መረጃዎችን ከሚያዛቡ አካላት በመጠበቅ መረጃን ከምንጩ መውሰድ እንዳለበት የፕሬስ መረጃ ማጣሪያ አሳስቧል።
በሀና እጅጋየሁ
#ተጠንቀቁ
18/03/2026
የአራት ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት ስምምነት ተፈረመ
++++++++++++++
-አሊኮ ዳንጎቴ በኢትዮጵያ ለሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ የሚውል የ4.2 ቢሊዮን ዶላር የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት ስምምነት ከቻይናው ጂሲኤል ግሩፕ ጋር ለ25 ዓመታት የሚቆየው ተፈራርሟል።
አሊኮ ዳንጎቴ ከቻይናው ጂሲኤል ግሩፕ ስምምነቱን በናይጄሪያ ሌጎስ ፈርመዋል።
የዘጋርዲያን፣ የብሉምበርግ የዜና ወኪልና አፍሪካ ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘገባ እንዳመላከተው፣ ስምምነቱ በ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለሚገነባውና በዓመት 3 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ የማምረት አቅም ላለው ፋብሪካ ስራ ሲጀምር ያልተቋረጠ የኃይል ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግል ተገልጿል።
አሊኮ ዳንጎቴ በስምምነቱ ወቅት እንደገለጹት፣ አፍሪካ ጥሬ ዕቃን ወደ ውጭ በመላክ ያለቀላቸውን ምርቶች የምታስገባበትን አካሄድ በመቀየር በራስ የመተማመን አቅሟን ማሳደግ ይኖርባታል ብለዋል።
የዳንጎቴ ግሩፕ 60 በመቶ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ 40 በመቶ ድርሻ ያላቸው ይህ ፕሮጀክት እኤአ እስከ 2029 ዓ.ም ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ይጠበቃል።
የማዳበሪያ ፋብሪካው ከካሉብ የጋዝ ስፍራ በማውጣትና 108 ኪሎሜትር የማጓጓዣ ቱቦ በመጠቀም በአመት 3 ሚሊዮን ቶን አምርቶ እንደሚያቀርብ መገለፁ ይታወሳል።
ይህ የማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምረቃ ላይ ይፋ ካደረገችው የ30 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ዕቅድ ውስጥ አንዱ ነው። በተጨማሪም GCL በኢትዮጵያ የ2.5 ቢሊዮን ዶላር የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ማቀዱ ይታወሳል።
#የተፈጥሮጋዝ #ቻይና #ጂሲኤል #ኢትዮጵያ #ዳንጎቴ #አዳበሪያ #ኢንቨስትመንት #ኢኮኖሚ
17/03/2026
የኢትዮጵያን የትራንስፖርት ዘርፍ ወደ ኤሌክትሪክና የተፈጥሮ ጋዝ የማሸጋገርና የነዳጅ ቁጠባ ሀገራዊ ጥሪ
++++++++++++++++
በአሁኑ ወቅት በመካከለኛው ምሥራቅ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የዓለም የነዳጅ ገበያ ለአደጋ በተጋለጠበት ወቅት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአራት ዓመታት በፊት የነዳጅና የሌላ ማበረታቻ እንዲያገኙ ያደረጉት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ፖሊሲ፤ ዛሬ ላይ ሀገርን ከፈተና የሚታደግ ብልህና አርቆ አሳቢ ውሳኔ መሆኑ በተግባር ተረጋግጧል።
ወቅታዊውን ዓለም አቀፍ ጫና ለመቋቋምና የሀገርን ኢኮኖሚ በዘላቂነት ለመታደግ የሚከተሉት አራት ዋና ዋና ነጥቦች በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ በመንግሥትና በግል ተቋማት ዘንድ ተግባራዊ እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል።
የቴክኖሎጂ ሽግግርና የኃይል አጠቃቀም
• የኤሌክትሪክ መኪናዎች ባህል፦ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን መጠቀም እንደ ሀገራዊ ባህል በትኩረት ማዳበር።
• ከነዳጅ ወደ ኤሌክትሪክ ሽግግር፦ በነዳጅ እና በኤሌክትሪክ የሚሠሩ (Plug-in Hybrid) ተሽከርካሪዎች ነዳጅን በመተው የኤሌክትሪክ ኃይልን ብቻ እንዲጠቀሙ ማስቻል፤ እንዲሁም በነዳጅ የሚሠሩትን ወደ ኤሌክትሪክ እና ተፈጥሮ ጋዝ የመቀየር ሥራን ማጠናከር።
• ከባድ ተሽከርካሪዎች፦ እስከ 20 ቶን የሚጭኑ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ኤሌክትሪክ፤ ከ20 ቶን በላይ የሆኑት ደግሞ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ እና ኤሌክትሪክ እንዲቀየሩ መንግሥት እና የግል ዘርፍ በቅንጅት እንዲሠሩ ማድረግ።
2. የመንግሥት እና የሕዝብ ትራንስፖርት ሚና
• የመንግሥት ተሽከርካሪዎች፦ በክልል እና በፌዴራል ደረጃ ያሉ ሁሉም የመንግሥት እና የፕሮጀክት ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ኤሌክትሪክ እንዲዘወሩ በማድረግ የተጀመረውን ሀገራዊ ዕቅድ ወደ ሙሉ ትግበራ ማሸጋገር።
• የሕዝብ ትራንስፖርት፦ ባቡሮችን፣ ባሶችን እና ሌሎች የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶችን በስፋት እና በአግባቡ መጠቀም፤ አገልግሎቱም በወጣለት ታሪፍ እና መርሐ-ግብር ያለ መቆራረጥ እንዲሰጥ በትብብር መሥራት።
3. የአጠቃቀም እና የአነዳድ ባህል ለውጥ (Eco-Driving)
• የግል ተሽከርካሪዎች ገደብ፦ ከአንድ ቤት ውስጥ ብዙ መኪናዎችን ይዞ መንገድ ከመውጣት ይልቅ፤ በጋራ የመጠቀም ልምድን ማዳበርና ተግባራዊ ማድረግ።
• አረንጓዴ ጉዞዎች፦ በከተማ ውስጥ የሚደረጉ አጫጭር ጉዞዎችን በእግርና በብስክሌት የማድረግ ባህልን ማሳደግ።
• የአነዳድ ክህሎት (Eco-driving)፦ ነዳጅንና የካርቦን ልቀትን የሚቀንሱ፣ ከሞኖፖሊነት የጸዳ የ"Eco-driving" የአነዳድ ስልጠና ለተሽከርካሪ አሽከርካሪዎች መስጠትና ልምዱን ማዳበር።
4. የጥራት ቁጥጥር እና የአካባቢ ጥበቃ
• ጥገናና መለዋወጫ፦ ወቅታዊ የመኪና ጥገናን ማጠናከርና ኦሪጅናል መለዋወጫዎችን መጠቀም።
• የጭስ ልኬትና ስታንዳርድ፦ የጭስ ልኬት መመሪያን በተሟላ ሁኔታ (100%) መተግበርና ሁሉም ተሽከርካሪዎች በኢትዮጵያ ስታንዳርድ የጸደቁ የነዳጅና ጭስ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ማድረግ።
ማጠቃለያ
ይህ የትብብር ጥሪ የሀገርን የውጭ ምንዛሬ ለማዳን፣ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስና ዜጎች በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መዋዠቅ እንዳይጎዱ ለማድረግ የታለመ ነው። የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን የአመራር ራዕይ ይበልጥ ለማሳካትና ሀገርን ከጥገኝነት ለማላቀቅ ሁላችንም በኃላፊነት ስሜትና በቁርጠኝነት እንድንነሳ እናሳስባለን።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር
15/03/2026
የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ታሪፍ ላይ ማሻሻያ ተደረገ
+++++++++++++
በወቅታዊ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ የተደረገውን የዋጋ ማስተካከያ ተከትሎ በአዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎት ታሪፍ ላይ ማሻሻያ ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
የታሪፍ ማሻሻያው ከነገ ሰኞ መጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል። ጭማሪው የከተማ አውቶብስ አገልግሎትን ጨምሮ በሚኒባስ፣ በሚዲባስና የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን ይመለከታል።
12/03/2026
በመሠረተ ልማት ምክንያት የሚቋረጥ አገልግሎት የለም - መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት
++++++++++++++++++
- ሰሞኑን የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስመልከት ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ በቦሌ ቅርንጫፍ ሲስተም የለም የሚል መረጃ በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተጋራ ይገኛል። መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በሚመለከት "ሲስተም የለም" ተብሎ የተጋራው መረጃ ትክክል አይደለም ተብሏል።
በቦሌ ቅርንጫፍ ከአገልግሎት ጋር ተያይዞ በመሠረተ ልማት ምክንያት የሚቋረጥ አገልግሎት አለመኖሩን የቀድሞ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ገልጸዋል።
ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት ማብራሪያ መሶብ ላይ ኤሌክትሪክ ወደ ማዕከሉ የሚገባው በሁለት መንገድ ነው፤ አንደኛው ከተቋረጠ አንደኛው መስመር ላይ ይሰራል። ጀነሬተር አለ፣ ይህንኑ አገልግሎት እንዳይቋረጥ የሚያግዝ ፓወር ወይም ኃይል አምቆ የሚይዝ አማራጭ ተዘርግቷል። በኃይል መቋረጥ ምክንያት የሚቆም አገልግሎት ምንም ሲሉ ገልጸዋል።
የቴሌኮም መሠረተ ልማት እንደ ሌላው ቦታ በአንድ መስመር ብቻ ሳይሆን ‹‹ሪደንደንት›› ሆኖ የሚያገለግል ነው። ስለሆነ የሚቆራረጥ ነገር የለም። የተቋማትን ሲስተም በተመለከተ መሶብ የራሱ ሲስተም የለውም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ያለማው የመሶብ ሲስተም ተቋማትን አገናኝቶ (integrate) አገልግሎት በአንድ ላይ እንዲሰጥ የሚያደርግ ፕላትፎርም (platform) እንጂ የተቋማቱን ሲስተም የሚተካ አይደለም።
ለምሳሌ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የራሱ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሚመጣ ሲስተም፤ ገቢዎች ሚኒስቴር እንደዚሁ ነው። ሌሎችም በተመሳሳይ ከፌዴራል ተቋማት በቀጥታ የሚመጣ የአገልግሎት ሲስተም ነው።
ተቋሙ የተፈለገበትን ምክንያት እንደ ሀገርም ጤናማ ‹‹ሲቪል ሰርቫንት›› መፍጠር ስለሆነ አዲስ መሶብ ላይ ያለው የሠራተኛ ዲሲፕሊን ትልቅ ትኩረት የሚሰጠውና ብልሹ አሠራርን ከመቅረፍ አኳያም ራሱን የቻለ አስተዋጽኦ እንዳለው ለመግለጽ ነው። የእኛም ክትትል እንደተጠበቀ ሆኖ ሲስተም ላይ ያሉት ጉዳዮች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ጉዳዮች ስለሆኑ አብዛኛው ለብልሹ አሠራር የሚጋለጥ አይደለም።
ስለዚህ ከተገልጋዮች የቀረበውም ሆነም በማህበራዊ ትስስር ገጾች የተጋራው መረጃ ተገቢነት የሌለው መሆኑን በመረዳት፤ህብረተሰቡ በእንደዚህ ዓይነት መረጃዎች ሳይደናጋገር፣ መረጃን ከሚያዛቡ አካላት በመጠበቅ ወደ መሶብ በመሄድ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ የአዲስ መሶብ አሳስቧል።
በሀና እጅጋየሁ
#የአንድማዕከልአገልግሎት #መሶብ #ኢትዮጵያ #ቀልጣፋአገልግሎት