03/06/2026
ኅብረት ሥራና ዴሞክራሲ
።፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣፣
ኅብረት ሥራ ማህበራት የኢኮኖሚ ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ የዴሞክራሲ ትምህርት ቤቶች ናቸው
ዴሞክራሲ ዜጎች በየቀኑ በሚያደርጉት ተሳትፎ፣ በሚያሳዩት ተጠያቂነት፡ በሚፈጥሩት የመተማመን ባህል እና በጋራ ችግሮቻቸውን በመፍታት የሚጠናከር ነው።
ኅብረት ሥራ ማህበራት "የዴሞክራሲ ትምህርት ቤቶች" ተብለው የሚጠሩት
ከኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸው ባሻገር የዴሞክራሲ እሴቶችን ያጎለብታሉ፣ የንቁ ዜግነት ባህልን ያስፋፋሉ፣ የመተማመንና የአብሮነት መንፈስን ያጠናክራሉ።
በኅብረት ሥራ ማህበራት አባላት ጥያቄዎችን ያቀርባሉ፣ አመራሮቻቸውን በምርጫ ይመርጣሉ፣ አፈፃፀማቸውን ይገመግማሉ። ይህ ሂደት ለሚሊዮኖች ዜጎች የዴሞክራሲ ተግባራዊ ልምድ ይፈጥራል።
በተጨማሪም በብዙ አካባቢዎች ሴቶችና ወጣቶች የመጀመሪያ የአመራር ልምዳቸውን የሚያገኙት በኅብረት ሥራ ማህበራት ውስጥ ነው፤ ይህም አካታችነትንና የዜጎችን ተሳትፎ ያጠናክራል።
በአሁኑ ጊዜ እየተተገበረ ያለው የኅብረት ሥራ ማህበራት ዕድገትና ተወዳዳሪነት ሪፎርምም ግልፅነትን፣ ተጠያቂነትን፣ የአባላት ተሳትፎን እና ዘመናዊ አስተዳደርን በማጠናከር ይህንን ዴሞክራሲያዊ ሚና የበለጠ የሚያጎለብት ነው።
ስለዚህ ኅብረት ሥራን ማጠናከር ማለት የኢኮኖሚ ተቋማትን ማጠናከር ብቻ ሳይሆን የዴሞክራሲን መሠረት ማጠናከርማለትም ነው።
30/05/2026
ኀብረት ሥራን ወደ ዘመናዊ ኢኮኖሚ የማሸጋገር የአዲስ ምዕራፍ ጉዞ!
*****
ዛሬ ላይ በዓለማችን የሚገኙ ኀብረት ሥራ ማህበራት
በፈጣን ቴክኖሎጂ የተደገፈ እና ተወዳዳሪ አሰራር ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በሃገራችን የሚገኙ ኀብረት ሥራ ማኀበራትም ከባህላዊ አሰራር ወጥተው ወደ ዘመናዊ አገልግሎት፣ ዲጂታል ስርዓት እና ጠንካራ የቢዝነስ አሰራር እንዲሸጋገሩ እየተሠራ ይገኛል።
የአገልግሎት ጥራትን ማሻሻል፣ ዘመናዊ የቢዝነስ አሰራርና የግብይት ስርዓት መፍጠር፣ የአባላት ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎን ማሳደግ እና ተዓማኒ የብራንድ ገፅታ መገንባት ኀብረት ሥራ ማህበራትን የማዘመንና ማደስ ቁልፍ አቅጣጫዎች ናቸው።
ይህም በመሆኑ ዛሬ ላይ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ማህበራት የአገልግሎት ስርዓታቸውን እና የግብይት አቀራረባቸውን በማዘመን እንዲሁም የብራንድ ገፅታ በመገንባት በገበያ ውስጥ አዲስ ቦታ እየፈጠሩ ይገኛሉ።
ለአብነትም የቁጠባና ብድር ኀብረት ሥራ ማህበራት የዲጂታል አገልግሎታቸውን እያዘመኑ፣ የፋይናንስ አማራጭ አገልግሎቶችን እያሰፉ እና ተደራሽነታቸውን እያሳደጉ ይገኛል። ይህ ደግሞ የአባላትን እምነት ከፍ ከማድረጉ በተጨማሪ የማህበራቱን ካፒታል እያሳደገ ነው።
በግብርና ዘርፍ ከምርት እስከ ግብይት ያለውን ሰንሰለት በማሳጠር የምርት ዋጋ በማረጋጋት ውጤታማ ስራ እየተሠራ ነው። በውጪ ግብይት በተለይ በቡና ዘርፍ አበራታች ውጤት እየመጣ ነው።
እንዲሁም ዘመናዊ የምርት መሸጫ ሱቅ፣ የተሻለ የሸቀጥ አቅርቦት እና ጥራት ያለው አገልግሎት የሸማች ኀብረት ሥራ ማህበራት አዲሱ ገፅታ እየሆነ መጥቷል።
ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ የማህበራቱን ገፅታ በመቀየር፣ ተቀባይነትና ተወዳዳሪነታቸውን እያሳደገ ይገኛል።
ይህን ጅምር ለውጥ ለማስፋትና የበለጠ ለማጠናከር ግን ጠንካራ አመራር፣ የአባላት ንቁ ተሳትፎ፣ ዘመናዊ የቢዝነስ አስተሳሰብ፣ ቴክኖሎጂን የመጠቀም አቅም እና ተከታታይ ስልጠናና ድጋፍ ወሳኝ ናቸው።
በዚህ መልኩ ለውጡ በተግባር ሲደገፍ ኀብረት ሥራ ማህበራት የአባላትን ኑሮ በማሻሻል ብቻ ሳይወሰኑ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚታይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ዘመናዊ እና ተወዳዳሪ ተቋማት እንደሚሆኑ አያጠራጥርም።
ጠንካራ ኀብረት ሥራ የጠንካራ ኢኮኖሚ መሠረት ነው!
26/05/2026
የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1447ኛው የዒደል አድሃ (ዐረፋ) በዓል በሠላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቱን ይገልጻል!!
ዒድ ሙባረክ!
26/05/2026
ምርት ብክነት ቅነሳ ላይ የሚሰራ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
*****
መቀመጫውን በጣሊያን ያደረገው አለምአቀፍ ሜታልሞንት በተሰኘ ኩባንያ የመጀመሪያው ምዕራፍ የተቀናጀ የድህረ-ምርት መሰረተ ልማትና ቴክኖሎጂ አቅርቦት ፕሮጀክት ይፋ ተደርጓል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደሳለኝ ተሻለ ድህረ-ምርት ብክነት የግብርናው ዘርፍ ማነቆ መሆኑን ገልፀው የድህረ-ምርት ብክነት የአርሶ አደር ገቢ፣ የምግብ አቅርቦትና ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የድህረ-ምርት ብክነትን ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የድህረ-ምርት ብክነትን ለመቀነስ፣ እሴት ሰንሰለትን ለማጠናከርና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ ፕሮጀክቱ ሚናው የላቀ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ለጣሊያን መንግስት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የጣሊያን የልማት ትብብር ኃላፊ ዶ/ር ሚቼል ሞረና በበኩላቸው በአለም አቀፍ ደረጃ ከተመረተው ሲሶው ምርት እንደሚባክን አንስተው በኢኮኖሚ ላይ ያለውን ተፅዕኖ ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የድህረ-ምርት ብክነትን በመቀነስ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ገልፀው ኢትዮጵያ ለምታከናውነው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አበርክቶው የላቀ ነው ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የሰብል ምርት ማከማቻ መጋዘን ግንባታ፣ ዘመናዊ የእህል ማበጠሪያ፣ ማድረቂያ፣ መጋዘን ውስጥ ሙቀት መቆጣጠሪያ ማሳሪያዎች በማቅረብ፣ የመሳሪያዎች ጥገና በመስጠት እንዲሁም ለባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት፣ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎች የልውውጥ በማካሄድ ድጋፍ ያደርጋል፡፡
ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ከፍተኛ ምርት አምራች በሆኑ አካባቢዎች ላይ የሚተገበር ይሆናል፡፡
በመድረኩ አጠቃላይ ስለፕሮጀክቱ ዓላማ፣ ስለሚሰራባቸው አካባቢዎች እና ድጋፍ ስለሚሰጥበት ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ተሰጥቶ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ምንጭ:- ግብርና ሚኒስቴር
24/05/2026
"ኩላሊት፣ ጤና፣ ህይወት፣ ተስፋ " በሚል መሪ ቃል በሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ በተዘጋጀው የእግር ጉዞ ላይ የኮሚሽናችን የማኔጅመንት አባላት እና በተቋማችን የተደራጁ አሚጎስ፣ የሁሉ እና አዲሲቱ ኢትዮጵያ እንዲሁም ተደራሽ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራትን በማስተባበር በንቃት ተሳትፎ አድርገዋል።