14/12/2021
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የቀድሞ ሰልጣኞች ለመከላከያና ህዝባዊ ሰራዊቱ ድጋፍ አደረጉ
ታህሳስ 05/2014ዓ.ም
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የቀድሞ የአትሌቲክስ ሰልጣኞች ግምታቸው 40,000 ብር (አርባ ሺህ ብር ) የሚያወጣ ፓስታ፣ዘይትና የንፅህና መጠበቂያ የቁሳቁስ ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አድርገዋል ።
አካዳሚው ሰራተኞቹን አስተባብሮ ካዘጋጀው ስንቅና ቁሳቁስ ጋር በአንድ ላይ ለመከላከያ እና ህዝባዊ ሰራዊት ወደ ግንባር እንዲላክላቸው ለአካዳሚው አስረከቡ፡፡
ድጋፉ በአሰልጣኝ ተሾመ ከበደ አስተባባሪነት የተሰበሰበ ሲሆን እሳቸውን ጨምሮ ኢትዮጵያን በተለያዩ የአለም አትሌቲክስ መድረኮች ሀገራቸውን ያስጠሩ አትሌት ጌትነት ዋለ፣ አትሌት አብርሃም ስሜ ፣አትሌት ዘርፌ ወንድማገኝ እንዲሁም አትሌት መልኬነህ አዘዝ እና አትሌት መልካሙ ዘገየ ድጋፉን አድርገዋል፡፡
አትሌቶቹ በሰጡን አስተያየት የሃገራቸው ጉዳይ የሚመለከታቸው እና የሚያሳስባቸው በመሆኑ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዳደረጉ በመግለፅ በቀጣይም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል ፡፡
14/12/2021
በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የዓለም አቀፉ የውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን አዘጋጅነት /አቡዳቤ/ በሚካሄደው ሻምፒዮን ላይ ኢትዮጵያ ለመሳተፍ ወደ ስፍራው አቅንተዋል፡፡
(ታህሳስ5/2014 ዓ .ም አዲስ አበባ)
በ15ኛው የአለም ውሃ ዋና ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በአራት ዋናተኞች የሚትወክል ሲሆን ሻምፒዮንዉ ከዴሴምበር 16 እሰከ ዴሴምበር 21 ይካሄዳል፡፡
ኢትዮጵያን የሚወክሉ ሁለት ሴትና ሁለት ወንዶች በድምሩ አራት አትሌቶች ወደ ስፍራው አቅንተዋል፡፡ በሴቶች ራሄል ፍስሃ እና ብርሃን ደመቀ ተካፋይ ሲሆኑ በወንዶች አቻላ እኛኮቤና ጥላሁን አያል ኢትዮጵያን ይወክላሉ፡፡
ለስድስት ቀናት በሚካሄደው ሻፒዮና ላይ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ስምንት አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን በአርባ አራት አይነት ውድድሮች ይፎካከራሉ፡፡
አራት ስፖርተኞችን ጨምሮ ሰባት አባላትን የያዘው የልኡክ ቡድን በውሃ ዋና ስፖርት ከሚያደርጉት ተሳትፎና ተፎካካሪነት በተጨማሪ አሁን ሃገራችን ኢትዮጵያ ያለችበት ትክክለኛ ሁኔታ የውጭ መገናኛ ብዙሃን እንደሚሉት ያለመሆኑን ለማሳወቅ የሚያስችል ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡
12/12/2021
በስፖርት የህግ ማዕቀፎች ላይ የተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተጠናቀቀ ።
ታህሳስ 03/2014 ዓ.ም
በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት በስፖርት ልማት ዘርፍ ሀገራዊ የስፖርት ሪፎርም እና በተለያዩ የህግ ማዕቀፎች ዙሪያ ለአመራሮች ለሁለት ቀናት ሲሰጥ የቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተጠናቋል ።
በመድረኩ በ2012 ዓ.ም የተጠናው ሀገራዊ የስፖርት ሪፎርም ፕሮግራም ጨምሮ ሪፎርሙን መሠረት በማድረግ የተዘጋጁ የተከለሰ ብሔራዊ የስፖርት ፖሊሲ ረቂቅ ፣ ረቂቅ የስፖርት አዋጅ እና የሀገር አቀፍ ስፖርት ማህበራት ስለሚቋቋሙበት መመሪያ ቀርቦ ግንዛቤ ተፈጥሮባቸዋል ።
የመድረኩ ተሳታፊ አመራሮች በሰጡት አስተያየት የቀረቡት ሰነዶች እና የህግ ማዕቀፎች አሁን ከአለው መዋቅራዊ አደረጃጀት እና ስልጣንና ተግባር ጋር የተጣጣመ መሆን ይገባዋል ብለዋል ።
በተጨማሪም ስፖርቱን ከባህል ጋር በማስተሳሰር ሁለቱም ዘርፎች ተደጋግፈው የሚያድጉበት እና ውጤት በሚያመጡበት ሁኔታ ሊሰራ እንደሚገባ ተመላክቷል ።
በስፖርት ማህበራት ላይ የሚታየው የአደረጃጀት እና የአሠራር ችግሮች ዴሞክራሲያዊ የተላበሱ እንዲሆኑ እና የህዝብ አመኔታ እንዲኖራቸው እንደሚሰራም ተጠቁሟል ።
በአጠቃላይ በቀረቡት ሰነዶች ስፖርቱ ያለበትን ሁኔታ ለመረዳት አስችሎናል ስለሆነም ወቅቱ የሚጠይቀው ፍጥነትና ጥራት በመሆኑ በስፖርቱ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት ወደ ውጤት በመቀየር ሀገርና ህዝብን ከፍ ለማድረግ እንደሚሰሩ አመራሮቹ ቁርጠኝነታቸውን ገልፀዋል ።
የተዘጋጁ የህግ ማዕቀፎችም አስፈላጊውን ግብዓት በማሰባሰብ እና የሚጠሩ ጉዳዮችን በማጥራት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲፀድቁ ይደረጋል ተብሏል ።
11/12/2021
ስፖርቱ ካለበት ውስብስብ ችግር ለማላቀቅ በዘርፉ የተጀመሩ የሪፎርምና የለውጥ ፕሮግራሞችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተገለፀ ።
ታህሳስ 02/2014 ዓ.ም
በሀገራችን ስፖርትን ባህሉ ያደረገ ትውልድ ለመፍጠር እና በስፖርቱ የላቁ ስፖርተኞችን በማፍራት ውጤት ለማስመዝገብ ሰፋፊ የስፖርት የልማት ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም የተሰሩ ስራዎች ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ እና ከህዝቡ ፍላጎት አኳያ ሲመዘን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ።
በመሆኑም የስፖርት ዘርፍ ከህዝቡ ፍላጎት እና ለሀገሪቱ ማበርከት ከሚገባው አስተዋጽኦ እና ካለበት ውስብስብ የመዋቅራዊና አሠራር ችግሮች ለማላቀቅ ስር ነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልግ በመታመኑ ሀገራዊ የስፖርት ሪፎርም ጥናት ፕሮግራም ተዘጋጅቷል ።
ይህን የሪፎርም ፕሮግራም ጨምሮ በስፖርት ፖሊሲው እና በሌሎች የስፖርት የህግ ማዕቀፎች ላይ ለአመራሮች የጠራ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችል መድረክም በቢሸፍቱ እየተካሄደ ይገኛል ።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ መድረኩን ሲከፍቱ እንደተናገሩት አንድ አመራር የሚመራውን ተቋም በአግባቡ ለመምራትና በስራው ውጤታማ ለመሆን በተቋሙ የሚገኙ የህግ ማዕቀፎችን ተንቅቆ መገንዘብ ይኖርበታል ብለዋል ።
የዚህ መድረክ ዋና ዓላማም አመራሩ የለውጥ ሀሳቦችን እና የህግ ማዕቀፎችን አውቆ እና ተገንዝቦ ለተግባራዊነቱ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መሆኑን ገልፀዋል ።
የባህልና ስፖርት የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ስፖርቱን ለማስፋፋት እና በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ በስፖርቱ ዘርፍ በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይስተዋላሉ ብለዋል ።
በመሆኑም ዘርፋ ካለበት ውስብስብ ተላቆ ስፖርት ለሁለንተናዊ ልማትና አገራዊ እድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የተጀመሩ የሪፎርምና የለውጥ ፕሮግራሞችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
በዛሬው ዕለት ሀገራዊ የስፖርት ሪፎርም ፕሮግራም ሰነድ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መምህር እና የጥናቱ አባል በሆኑት አቶ ሳሙኤል ስለሺ እና ዶ/ር ዘሩ በቀለ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል ።
የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ሀገራዊ የስፖርት ሪፎርም ፕሮግራም ሰነድ ፣ የተከለሰው ብሔራዊ የስፖርት ፖሊሲ ሰነድ ፣ የስፖርት ህግ ረቂቅ ሰነድ እና ሌሎች ሰነዶች ቀርበው ውይይት የሚካሄድባቸው ይሆናል ።
መድረኩ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳን ጨምሮ የዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታዎች ፣ የተጠሪ ተቋማት አመራሮች ፣ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የጤና ፣ የባህልና ስፖርት ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ፣ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት እና የሚኒስቴር መ/ቤቱ ዳይሬክተሮች ተሳትፈዋል ።
10/12/2021
18ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን ተከበረ፣
=====================================
በዕለቱ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የደም ልገሳ መርሐ ግብር ተካሂዷል ።
ታሕሣሥ 1/2014ዓ.ም
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሠራተኞች ከተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች ጋር በመሆን በዓለም አቀፍ ለ18ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ17ኛ ጊዜ የሚከበረውን የፀረ-ሙስና ቀን “በሥነ-ምግባር የታነጸ አመራር ከሙስና ለጸዳች ኢትዮጵያ!” በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ በሲምፖዚየም አክብረዋል ፡፡
በዕለቱ ንግግር ያደርጉት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንዳሉት ከሦስት ዓመት በፊት ሙስና ወይም ብልሹ አሠራር በሀገራችን ከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞ ካስከተሉ ምክንያቶች እንደነበር ጠቁመው ፤ በአሁኑ ሰዓት የለውጥ አመራሩ ሌብነትን ዋነኛ ጠላታችን መሆኑን በማመን ሕዝባዊ ፣ የተደራጀና ተቋማዊ ትግል እንዲደረግበት ግልፅ አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል ብለዋል ፡፡
በመሆኑም ሁሉም ሰራተኛ ለሀገር ህልውና ከሚያደርገው አስተዋጽኦ ባሻገር የተጀመረውን የብልሹ አሠራርና የሌብነት ትግል አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል ።
በዕለቱ የፀረ- ሙስና መታገያ ስልቶች የሚያዳብሩ አሠራሮችና አቅጣጫዎችን የሚያመላክቱ ፅሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል ።
በፕሮግራሙ በርካታ ሠራተኞች የተሳተፋበት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የደም ልገሳ መርሐ ግብር ተካሂዷል ፡፡
10/12/2021
ጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ1.6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ::
ማሰልጠኛ ማዕከሉ ለጀግናው ሀገር መከላከያ ሰራዊት የአይነትና፣ቁሳቁስና የገንዘብ የአደረገውን ድጋፍ ቢሾፍቱ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት አስረክቧል፡፡
ማዕከሉ ያደረገው ድጋፍ ከሰራተኞች የተሰበሰበ የአንድ ወር ደሞዛቸውን ፣ 4-ሰንጋዎች፣ ፓሰታ፣ ማር፣ አሳቱና፣ ሞኮሮኒ፣ ብርድልብስ፣ አንሶላ፣ ጤፍ፣ሩዝ፣በሶ፣ በአጠቃላይ መጠናቸው 1,678,000.00 ብር በላይ የሚያወጡ ቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን አሳይቷል ፡፡
በድጋፍ ርክክቡ ላይ የኢትዮጵያ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳን ጨምሮ፣ሌሎች ሚኒስቴር ዲኤታና የተለያዩ ሃላፊዎች በተገኙበት ርክክብ ተደርጓል፡፡
07/12/2021
ዓለም አቀፍ የመቻቻል ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ይገኛል ።
ህዳር 28/2014 ዓ.ም
የመቻቻል ቀን በዓለም ለ24 ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ12ኛ ጊዜ " መቻቻል ለሰላም ፣ ለአብሮነትና ለጋራ እድገት " በሚል መሪ ቃል በየደረጃው ሲከበር እና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ሲካሄድ ቆይቷል ።
በዛሬው ዕለትም የመቻቻል ቀን የማጠቃለያ ፕሮግራም በብሔራዊ ቲያትር በሲምፖዚየም እና በተለያዩ ዝግጅቶች እየተካሄደ ይገኛል ።
ሲምፖዚየሙን የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳ በይፋ የከፈቱት ሲሆን በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የባህልና ቋንቋ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ወርቅነሸ ብሩ ቀኑን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል ።
በሲምፖዚየሙ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳን ጨምሮ ሚኒስትሮች ፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች የክልልና ከተማ መስተዳድር የቢሮ ኃላፊዎች ፣ የሚኒስቴር መ/ቤቱ እና የተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች ተገኝተዋል ።
04/12/2021
የኢትዮጵያ ዳርት ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ ፡፡
ህዳር25 / 2014 ዓ/ም
ፌዴሬሽኑ ባካሄደው 18ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የ2013ዓ/ም የእቅድ ክንውን ሪፖርት ፣ የኦዲት ሪፖርት፣ የ2014 በጀት አመት እቅድ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዳርት ፌዴሬሽን ተሻሽሎ የተዘጋጀውን ረቂቅ የመተዳደሪያና መቋቋሚያ መመሪያ ደንብ በመወያየት አጽድቋል ፡፡
በተጨማሪም ከሁለገብ ኦንላይን ሶሊሽን ኃ/የተ/የግል ማህበር ጋር ለመስራት የሶስት አመት የጋራ መግባቢያ ውል ስምምነት ፊርማ ስነ ስርዓት ተካሂዷል ፡፡
የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ቢልልኝ መቆያ ባደረጉት ንግግርም የዳርት ስፖርት ለማሳደግ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከጠባቂነት መንፈስ በመላቀቅ በአህጉራዊና አለም አቀፍ ውድድሮች ለመሳተፍ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል ፡፡
ለጉባኤው በቀረበው የ2013ዓ/ም ሪፖርት በክልሎች የዳርት ስፖርት የታዳጊ ስልጠና ፕሮጀክቶች ማደጉ ፣ ከመንግስት ከሚሰጠው የድጎማ በጀት በተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት የተለያዩ የበጀት መጠየቂያ ሰነዶችን በማዘጋጀት ተጨማሪ ገቢ ማግኘት መቻሉ ፣ ስፖርቱ በክልሎች ህዝባዊ መሰረት አደረጃጀትና ተሳትፎ እንዲያድግ እገዛ መደረጉ በጥንካሬ ቀርቧል ፡፡
በተጨማሪም አለም አቀፍ ዳርት ፌዴሬሽን አመታዊ የአባልነት ክፍያ ባለመከፈሉ ምክንያት በበጀት አመቱ በሚደረጉ አለም አቀፍ ውድድሮችና ግንኙነቶች ላይ ተጠቃሚ መሆን አለመቻልና የታቀደው የእቅድ ክንውኖችን ለማጠናቀቅ በአመቱ የተመደበው የድጎማ በጀት በቂ አለመሆኑ በቀረበው ሪፖርት በድክምት ተነስተዋል ፡፡
በዳርት ስፖርት የስልጠና ጣቢያ ቁጥርን በማሳደግ ተተኪዎችን ማፍራት ፣ በዳርት ስፖርት የላቁ ኤሊት ስፖርተኞችን ቁጥር ማሳደግ ፣ የውድድር እድል በማስፋት በአህጉርና አለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ የሚያስችል ብሔራዊ ቡድን መምረጥ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ የገቢ አቅም ማሳደግ ፌዴሬሽኑ በ2014 በጀት አመት ሊያከናውናቸው ከያዛቸው ዋና ዋና ተግባራት ናቸው ፡፡
በመጨረሻም ኦሮሚያ ክልል የ2014ዓ/ም የኢትዮጵያ ዳርት ሻምፒዮና አስተናጋጅ እንዲሆን በመምረጥ ጉባኤው ተጠናቋል ፡፡
04/12/2021
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠረጴዛ ቴኒስ ክለብ በ1ኛ ዙር የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ውድድር አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን አጠናቀቀ፡፡
ህዳር 26/2014 ዓ/ም
በኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስፌዴሬሽን አዘጋጅነት ከህዳር 19-26 /2014 ዓ/ም ሲካሄድ በቆየው1ኛ ዙር የክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠረጴዛ ቴኒስ ክለብ የዋንጫ አሸናፊ በመሆን ተጠናቀቀ::
በአዲስ አበባ አዲስ ከተማ ወጣቶች ስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል በተካሄደው 1 ዙር የክለቦች ሻምፒዮና ውድድር 6 ክለቦች የተሳተፉ ሲሆን በ18 ዓመት ፣ ከ 21 አመት በታችና ከ21 አመት በላይ በሁለቱም ፆታ 116 ስፖርተኞች ተሳትፈዋል፡፡
ከ18 ዓመት በታች በነጠላ ታዳጊ ሴቶች እና ወንዶች ውድድር ኦሮሚያ ፖሊስ የዋንጫ እና የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ሲሆን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
ከ21 አመት በታች በነጠላ ሴቶች ውድድር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1 ደረጃን ሲይዝ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ2-3 ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ከ21 አመት በታች በነጠላ ወንዶች ውድድር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ1-2 ያለውን ደረጃ በመያዝ የዋንጫና የብር ሜዳሊያ ሲያሸንፉ ኢትዮ ንግድ ባንክ የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ነው፡፡
ከ21 አመት በላይ በነጠላ ሴቶች ውድድር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዋንጫ እና የነሀስ ሜዳሊያ አሸናፊ ሲሆን ኢትዮ ኢሌክትሪክ የብር ሜዳሊያ ተሸላሜ ሆኗል፡፡
ከ21 አመት በላይ በነጠላ ወንዶች ውድድር ኢትዮ ንግድ ባንክ ከ1-2 ያለውን ደረጃ ሲይዝ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 3ኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡
ከ18 አመት በታች በድብልቅ ውድድር 1ኛ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 2ኛ ኢትዮ ንግድ ባንክ 3ኛ ኦሮሜያ ፖሊስ በመሆን አጠናቀዋል፡፡
ከ 21 አመት በታች ድብልቅ ውድድር ኢትዮ ንግድ ባንክ አሸናፊ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ 2-3 ያለውን ደረጃ ሲይዝ ከ21 አመት በላይ ኢትዮ ንግድ ባንክ የብርና የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክ የዋንጫ አሸናፊ ሆኗል፡፡
ከ18 አመት በታች የሴቶች ጥንድ ውድድር ኦሮሚያ ፖሊስ 1ኛ ፣ ከ2-3 የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ፤ ከ18 አመት በላይ ወንዶች ኦሮሚያ ፖሊስ የወርቅና የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ሲሆን የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የነሀስ ተሽላሚ ሆኗል፡፡
ሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በምትካፈልባቸው በምስራቅ አፍርካ እና በአፍሪካ ሻምፒዮና ለመሳተፍ የሚያስችል እጩ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ አላማ ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
በውድድሩ ማጠቃለያ ላይ የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ የስራ አስፈፃሚን ጨምሮ የተለያዩ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡