04/06/2026
በካይዘን ጽንሰ ሀሳብ እና በስራ ላይ በሚከሰቱ ብክነቶች ዙሪያ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለተሰማሩ አመራሮች እና ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጠ
አዳማ፣ ግንቦት 27 ቀን 2018 ዓ/ም (ከመልሚ) በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ በዘመናዊ የኮንስትራክሽን ስራ ላይ ደህንነት እና በካይዘን ጽንሰ ሀሳብ ዙሪያ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለተሰማሩ የህንጻ ስራ ተቋራጮች፣ የሙያ ማህበራትና አማካሪዎች በአዳማ ከተማ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
የስልጠናው ዓላማም በካይዘን እና አተገባበር ላይ የተሟላ አረዳድ መፍጠር፣ የስራ ባህልን በማሻሻል የሰራተኞች የስራ ተነሳሽነት መጨመር እና በማያቋርጥ የለውጥ ጎዳና ተቋማትን መገንባት እንዲሁም የስራ ላይ ደህንነትን ትኩረት መስጠት እንደሆነ በመድረኩ ተገልጿል።
በካይዘን የልዕቀት ማዕከል አማካሪ እና ተመራማሪ የሆኑት ወ/ሮ ገነት ደበበ የካይዘን ጥልቅ ዕይታን አስመልክተው ካይዘን ማለት የማያቋርጥ ቀጣይነት ያለው ለውጥ ማምጫ፣ አሳታፊ፣ የበርካታ ጥቃቅን ለውጦች ድምር ውጤት እና ያለ ከፍተኛ መዋለ-ነዋይ የሚሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
ካይዘን ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን ቴክኖሎጂዎችን፣ የአስተዳደር መመሪያዎችን የአሰራር ሂደት ደረጀዎችን ቀጣይነት እንዲኖራቸው እና በእየ ጊዜው አቅማቸውን ከፍ እንዲል ማሻሻያ ማድረግ እንደሆነ አያይዘው ተናግረዋል።
በካይዘን የልዕቀት ማዕከል አማካሪ እና ተመራማሪ የሆኑት አቶ ደረጄ አራጌ በበኩላቸው በስራ ቦታ የሚታዩ ብክነቶችን መለየት እና መከላከል በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ባደረጉት ገለጻ እንዳሉት በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በስራ ሂደት የሚያጋጥሙ አላስፈላጊ ወጪዎችን እና ለስራው ምንም አይነት ዕሴት የማይጨምሩ ነገሮችን ማስወገድ ያስፈልጋል ብለዋል።
በሰራተኛው ላይ የአካል ጉዳት መድረስ፣ በድርጅቱ ላይ የሚከሰቱ የንብረት ውድመቶች እና ስራው ከተጠናቀቀ በዋላ በተጠቃሚው ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ከብክነት መካከል ተጠቃሽ እንደሆኑ አቶ ደረጄ አክለው ገልጸዋል።
በነገው ዕለትም የስራ ቦታ ማደራጀት እና የስራ ቦታ ደህንነት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና እንደሚሰጥ ከስልጠናው መርሀ ግብር ለመረዳት ተችሏል።
04/06/2026
የመንግሰት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የብቃት ማእቀፍ የዝግጅት ምዕራፍ ስራ ተገመገመ
ቢሾፍቱ፣ ግንቦት 27 ቀን፣ 2018 ዓ.ም (ከመልሚ) የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመራሮችና የብቃት ማዕቀፍ ንኡሳን ኮሚቴዎች እንዲሁም የፈደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አመራር በተገኙበት በመንግሰት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የዝግጅት ምእራፍ ስራዎች ተገምግመዋል።
የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ሪፎርሙን አስመልክተው በ11 ወራት ውስጥ በተለያዩ ኮሚቴዎች የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን በእጅጉ አድንቀው እንደተቋም ማከናወን ሲገባ ባልተከናወኑ ቀሪ ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ማጠናቀቅ እንደሚገባ አሳስበው እስካሁን ያልተፈቱ ተግዳሮቶችን ከተቋሙ የቴክኒክ ኮሚቴና ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በጋራ ተናቦና ተረዳድቶ ለመፍታት ከምንጊዜውም በላይ እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በሪፎረሙ አማካኝነት መንግስት የሀገሪቱ ዜጎች የጣሉበትን አደራ በትክክልና በታማኝነት ለመወጣት የድጅታል አሰራር እውን ማድረግ ነው ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ የከተማ ነዋሪዎችን ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ ርካታን በማረጋገጥ ዘላቂነት ያለው ተቋም ገንብቶ ሀገርን ለማሻገር፣ ነጻና ገለልተኛ የሆነ፣ ተጠያቂነት የሰፈነበት፣ ምቹ የሥራ አካባቢን መፍጠር ነው።
በዚህ ሪፎርም ሥራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ለሚገኙ የተቋሙ አመራችና ባለሙያዎች ክብርት ሚኒስትሯ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ሪፎርሙ የተቋም ግንባታ ሀገርንና ትውልድን የሚያሻግር መሆን እንደሚገባው ክብርት ሚኒስትሯ ጠቅሰው ተቋሙ የተለያዩ ዓለማትን የሪፎርም ተሞክሮ በመውሰድ የከተማ ነዋሪዎችን መሠረታዊ ችግር በዘላቂነት የሚፈታ ሪፎርም እንደሆነ ተናግረዋል ፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የክትትልና ድጋፍ ቡድን አባላት እንደተናገሩት ተቋሙ ያዘጋጀውን የብቃት ማዕቀፍና የአደረጃጀት የሰነድ ዝግጅት የአባላቱን ትጋትና ብቃት አድንቀው ቀሪ ሥራዎች ላይ ከፍተኛ አመራሩም ይሁን በጥናት ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ኮሚቴዎች ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ መሠረት ሥራዎች በአስቸኳይ ተጠናቀው ወደተግባር መግባት እንደሚገባ ተናግረዋል።
03/06/2026
የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት፣ ካናዳ፣ ኖርዌይ እና ስዊዘርላንድ በጋራ ባወጡት መግለጫ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም የተካሄደውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ያደነቁ ሲሆን፤ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለእጩዎችና ለሲቪል ማኅበራት ለምርጫው ስኬት ላበረከቱት አስተዋጽኦ እንዲሁም ለአፍሪካ ኅብረትና ለኢጋድ የምርጫ ታዛቢነት ሚና እውቅና ሰጥተዋል።
02/06/2026
ኢትዮጵያውያን መርጠዋል፤ ኢትዮጵያ አሸንፋለች!
ግንቦት 25 2018 ዓ.ም
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ኢትዮጵያ ከዜጎቿ የፈለገችዉን ኹሉ በፈለገችው ጊዜና ኹኔታ የምታገኝ ሀገር ናት፡፡ ለሀገራቸዉ የተጠየቁትን ሁሉ ለመስጠት ወደኋላ የማይሉ ዜጎች ስላሏት በእጅጉ ኮርታለች፡፡ ከዓድዋ እስከ ሕዳሴ ግድብ፣ ከወገን ለወገን መረዳዳት እስከ አረንጓዴ ዐሻራ የዜጎቿን ተሳትፎ ጠይቃ፣ ከመሻቷ በላይ ተሳትክቶላታል፡፡ ዛሬ የተደገመዉም ይኸው ነው፡፡
ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲን ማንበር፣ በግልጽና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መንግሥትን መምረጥ፣ ሕገ መንግሥታዊነትን ፅኑ መሠረት ማስያዝ ትሻለች፡፡ ለዚህ ደግሞ 7ኛዉን ሀገራዊ ምርጫ እንደ ትልቅ አጋጣሚ መጠቀም አስፈልጓት ነበር፡፡
በምላሹም ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለመራጭነት ተመዝግበው የዛሬዋን ቀን ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡ እነሆ የእናት ሀገር ጥሪን በመቀበል ዜጎች በነቂስ ወጥተው ሲመርጡ ውለዋል፤ ሌሊቱንም አጋምሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ዜጎች ለረዥም ሰዓታት ተሰልፈዉ ድምፅ የሰጡበት ልዩ ምርጫም ነው፡፡
ምርጫዉ እንዳይካሄድ ባዳ እና ባንዳ ተቀናጅተዉ ያልቆፈሩት ጉድጓድ፣ ያልደረደሩት እንቅፋት አልነበረም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ለጠራችው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የማይቻል ነገር አልነበረምና በስኬት ተጠናቅቋል፡፡ ኢትዮጵያውን በሰላማዊ መንገድ መርጠው ኢትዮጵያ አሸንፋለች፡፡
የኢትዮጵያን የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ጥሪ ተቀብሎ ከንጋት እስከ ምሽት በመምረጥ ምላሽ ለሰጠው ሕዝብ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐቱ እንዲጸና እና ዜጎች በሰላም እንዲመርጡ ምቹ ዓውድ ለፈጠሩ የፀጥታ አካላት፣ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በየደቂቃዉ ሲያደርሱ ለነበሩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እንዲሁም የምርጫዉን ሂደት ለመሩ፣ ላስተባበሩ እና ለታዘቡ ሁሉ ኢትዮጵያ ታመሰግናለች፡፡
የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ግንቦት 25 2018፣አዲስአበባ፣ኢትዮጵያ