05/07/2025
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃጸም የማጠቃለያ ግምገማ ማካሄድ ጀመረ
*፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
አዳማ፣ ሰኔ 28 ቀን2017 ዓ.ም (ኢ.ፌ.ፖ.ሚ)፦የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት የስራ አፈፃጸም የማጠቃለያ ግምገማ በአዳማ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል::
የኢትዮጽያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ በግምገማው መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ሠራዊቱ ከተሰጠው ተልዕኮ ስፋት አንፃር በሁሉም መስክ ስኬታማ የሥራ አፈፃፀም የታየበት የሥራ ዘመን መሆኑን አንስተዋል።
አያይዘውም አዳዲስ አባላትን በብቃት በማሰልጠንና ነባር አመራርንና አባላትንም አቅም የበለጠ በማሳደግ የወንጀል መከላከል ስራዎች በውጤት እንዲታጀቡ የተደረገበት ዓመት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የሀገር ሰላም ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ከሌሎች የፀጥታና የደኅንነት ተቋማት ጋር በመቀናጀት በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ በርካታ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ሁነቶች ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከወኑ መደረጉንም ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የማጠቃለያ ግምገማው በ2017 የሥራ ዘመን በተልዕኮ አፈጻጸማችን የነበሩ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል የታዩ ድክመቶችን ደግሞ በመቅረፍ ለ2018 በጀት ዓመት የምንዘጋጅበት መድረክ ነው ብለዋል።
በአዳማ የሚከናወነው ዓመታዊ የማጠቃለያ ግምገማ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከግምገማው መጠናቀቅ በኋላም በአዳማ ከተማ የአረንጓዴ አሻራ የማኖር መርሀ-ግብር እንደሚከናወንም ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ ተናግረዋል።
26/06/2025
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ለጠቅላይ መምሪያው ተጠሪ ከሆኑ የስራ ክፍሎች ጋር የ 2017 ዓ.ም የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ አካሄደ ።
23/06/2025
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ በመላው ሀገራችን ስምሪት በወሰደባቸው ቀጠናዎች ያሉትን የፀጥታ ሁኔታዎች ገምግሞ በቀጣይ ትኩረት በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ አስቀመጠ
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም (ኢፌፖሚ)፦የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ በመላው ሀገራችን ስምሪት በወሰደባቸው ቀጠናዎች ያሉትን የፀጥታ ሁኔታዎች ገምግሞ በቀጣይ ትኩረት በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ አስቀምጧል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ግምገማውን በመሩበት ወቅት የፖሊስ ሠራዊቱ ስምሪት በወሰደባቸው ቀጠናዎች ከሌሎች የፌደራልና የክልል ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በፀረ-ሰላም ኃይሎች ላይ ጠንካራ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገልፀው በቀጣይም ይኸው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጠዋል::
ኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡርን ጨምሮ በሁሉም የሀገራችን የመውጫ እና የመግቢያ አውራ ጎዳናዎችን ደኅንነት በመጠበቅ የገቢና ወጭ ምርቶች እንቅስቃሴ የተሳለጠ እንዲሆን በተደረገው እጀባና ቋሚ ጥበቃ ጠንካራ ሥራ መሰራቱን ገልፀዋል።
በመሀል ሀገርና በድንበር የሀገራችን አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰውን የገቢና ወጭ ኮንትሮባንድ፣ ሕገ-ወጥ የሰዎችና የጦር መሳሪያ ዝውውርን እንዲሁም ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ከመግታት አንፃር የተሠራው ሥራ እጅግ በጣም አመርቂ ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑን በመገምገም በቀጣይም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የተለየ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል::
በተለይም በሀገራችን ትላልቅ የልማት አውታሮችና መሠረተ ልማቶች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስ ጠንካራ ስምሪት በመደርጉ ተቋማት ባቀዱት ልክ ዓመታዊ እቅዳቸውን እያሳኩ መሆኑ ተገምግሟል።
በማጠቃለያው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ለተልዕኮ ምቹ የሆነ አደረጃጀት የተፈጠረለት መሆኑንና በቀጣይም በተሻለ ደረጃ ተልዕኮውን መወጣት የሚያስችል ቁመና ላይ መሆኑ በግምገማው ተነስቷል::
10/06/2025
ኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሰሜን ምስራቅ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ መምሪያ አመራርና አባላት የቀጠናውን ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸው ተገለጸ
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ሰመራ; የሰሜን ምስራቅ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ መምሪያ አመራርና አባላት የቀጠናውን ሰላምና ደኅንነት በማረጋገጥ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸው ተገልጿል።
በወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ
የሰሜን ምስራቅ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ድጋፍ አገልግሎት ምክትል መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር መስፍን አዳነ መምሪያው ከአፋር ክልል በተጨማሪ አማራ ክልልን ጭምር የሚሸፍን ሰፊ ቀጠና የያዘ በመሆኑ የፖሊስ ሠራዊቱ በተሰማራበት የግዳጅ ቀጠና ሁሉ ከአጋር የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በፀረ ሰላም ኃይሎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን የድርሻውን እየተወጣ ነው ብለዋል።
ኮማንደር መስፍን አዳነ አያይዘውም በጣና ሀይቅ ላይ መጓጓዣና መዝናኛ አገልግሎት ለመስጠት ወደ ሀገራቾን የገባችው ጣናነሽ 2 ጀልባ ከጋላፊ ጀምሮ በማጀብ፣ ጉዙፍ ማሽነሪዎች፣ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች፣ ሌሎች ገቢ እና የወጭ የሀገር ሀብቶችን ሌት ተቀን በማጀብ እንዲሁም የፌደራል መንገድ ደኅንነት በመጠበቅ የገቢና ወጭ ንግድ እንቅስቃሴ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲካሄድ በማድረግ የመምሪያው አመራርና አባላት ስኬታማ ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
መምሪያው በዘጠኝ ወራት ውስጥ በተሰማራባቸው አካባቢዎች ከ33 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ኮንትሮባንድ መያዙን ጠቅሰው በቀጠናው በተለያየ ጊዜ በሕገ- ወጥ ደላሎች ተታለው አደጋ ላይ ይወድቁ የነበሩ 3000 ዜጎችን ወደ አካባቢያቸው በመመለስ እና አስኮብላዮች ደግሞ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማደረጉን ገልፀዋል።
በሌላ በኩል የመምሪያው አመራርና አባላት የተቋሙን ማህበራዊ ሚዲያ እንደሚከታተሉ እና ተቋሙ እንደሀገር ወንጀልን ለመቀነስና ለመከላከል የገነባውን የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያንም (EFPApp) እንደሚጠቀሙ አንስተው የአካባቢው ማኅበረሰብ የተቋሙን ማህበራዊ ሚዲያ በመከታተል እንደሀገር በተፈፀሙ ወንጀሎችና የወንጀል ስጋቶች ላይ መረጃ እንዲኖረው ከማድረግ ባሻገር EFPAppን ተጠቅሞ በአካባቢው የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በመጠቆም ለወንጀል መቀነስ የድርሻውን እንዲወጣ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
10/11/2023
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የ2016 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀሙ ስኬታማ እንደነበር ገለጸ
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የ2016 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀም ስኬታማ እንደነበር ገለጸ።
በማጠቃለያ ግምገማው ላይ በመገፕት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ክቡር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በሩብ ዓመቱ እንደሀገር ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ስኬታማ ስራዎች የተሰሩበት ወቅት እንደነበር ተናግረዋል።
አያይዘውም ከመስከረም ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ በመላው ሀገራችን ህዝባዊ፣ ሃይማኖታዊና መንግስታዊ ሁነቶች (ዘመን መለወጫ፣ መስቀል፣ መውሊድ እና ኢሬቻ በዓላት) በሰላም ተከብረው መጠናቀቁ ተቋሙ ዘመናዊ ቴክኖለጂዎችን በመጠቀም ረገድ የደረሰበትን ደረጃ ያመላከተበት እና እንደሀገር የፀጥታ መዋቅሩ ያለውን ጥንካሬና ብቃት ያረጋገጠበት ነው ብለዋል።
ክቡር ኮሚሽነር ጀነራሉ አክለውም በየደረጀው ያለው አመራር የተቋሙን ዕቅድ እስከ ፈፃሚ አካላት በማውረድና የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስራዎች ያከናወነበት ወቅት መሆኑን ጠቅሰው የሀገራችንን ሰላም ለማናጋት የሚንቀሳቀሱ የሽብር ኃይሎችን በመመከት እና እንቅስቃሴያቸውን በመግታት በሀገራችን በአራቱም ማዕዘናት ሠራዊቱ መስዋዕትነት እየከፈለ ለሀገራችን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በመጨረሻም ክቡር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ በማስቀመጥ የግምገማ መድረኩን አጠቃለዋል።
በውይይቱ ላይ በሩብ ዓመቱ በሀገር ላይ ጉዳት ያስከተሉ ከ1 ቢሊየን 577 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የገቢ እና የወጪ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዝ መቻላቸውንና በሕገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበር ሕገ-ውጥ 26 ቢሊዮን 867 ሚሊዮን 707 ሺህ ብር እና 99 ሺህ 970 ዶላር ላይ ምርመራ መጣራቱ ተገልጿል።
07/11/2023
“ለሕገ-መንግስቱና ለሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱ ታማኝ በመሆን የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ስራ ተሰርቷል” ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27 ቀን 2016 ዓ.ም
የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት የ2016 በጀት 1ኛ ሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀም የተሳካ እንደነበር ገመገመ።
ግምገማውን የመሩት ክቡር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ሠራዊቱ ተልዕኮ ወስዶ በተሰማራበት በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ለሕገ-መንግስቱና ለሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱ ታማኝ በመሆን የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ስራ ሰርቷል ብለዋል፡፡
የሕዝብን ሰላምና ደህንነት የሚያደፈርሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን የመመንጠር ስራ በተሳካ ሁኔታ መሰራቱን ያነሱት ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ ሠራዊቱ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት፣ የስኳር ፋብሪካዎችን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦችን፣ ድልድዮችን፣ የነዳጅ ዲፖዎች እና ደረቅ ወደቦችን ጨምሮ 575 የሀገራችንን ትልልቅ ተቋማትንና መሰረተ ልማቶች ደህንነት በመጠበቅ የተሳካ ስራ መስራቱን ገልፀዋል፡፡
በኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ያለምንም እንከን መደበኛ ስራውን እንዲሰራ እና ገቢና ወጭ ምርቶችና ሸቀጦች በተገቢው እንዲጓጓዙ ጠንካራ ጥበቃ መደረጉን ገልፀዋል።
በመላው ሀገራችንና በአዲስ አበባ ከተማ የተከበሩ እንደ ስድስቱን የጳጉሜን ቀናት፣ የዘመን መለወጫ፣ መስቀል፣ መውሊድ እና ኢሬቻ ያሉ ህዝባዊ፣ ሃይማኖታዊና መንግስታዊ ሁነቶች በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቁ የሠራዊቱ አስተዋፅኦ የላቀ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በሁሉም የሀገራችን ድንበሮች በርካታ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን በተለይም ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር፣ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመግታት ተችሏል ያሉት ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች በዜጎች ላይ የሚፈፀም እገታን ለመከላከል ከተሰሩ የቅድመ መከላከል ስራዎች በተጨማሪ በአጋቾች ላይ ከፍተኛ ክትትል በማድረግ እና የኦፕሬሽን ስራ በመስራት ሠራዊታችን መስዋትነትን ጭምር በመክፈል የታገቱ ዜጎችን በማስለቀቅ ረገድ ከፍተኛ ስራ መሰራቱንም ገልጸዋል፡፡
ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ በመጨረሻም በሀገራችን በሚገኙ በሁሉም ዩኒቨርስቲዎች የተሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና በሰላም እንዲጠናቀቅም ሠራዊቱ ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ውስጥ አልፎ መስዕዋትነት በመክፈል ማሳካቱን አንስተዋል፡፡
31/10/2023
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ሁለተኛ ዙር የከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መስጠት ጀመረ
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ጅግጅጋ፣ ጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ከፈጥኖ ደራሽ ዋና መምሪያ፣ ከምድር ባቡር መምሪያ እና ፀረ-ኮንትሮባንድ መምሪያ ለተውጣጡ ከፍተኛ እና መካከለኛ የፖሊስ አመራሮች በሱማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የአቅም ማጎልበቻ ሁለተኛ ዙር ሥልጠና መስጠት ጀመረ።
ስልጠናውን ያስጀመሩት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ የተዘጋጀው ስልጠና አሁን ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሰው ሀይል፣ በሎጂስቲክስ እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የደረሰበትን ደረጃ የሚመጥን በብቃት እየመራ ተልዕኮውን መፈፀም የሚችል የአመራር አቅም ለመፍጠር ነው ብለዋል።
ስልጠናው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የታጠቀውን ዘመናዊ ትጥቅ በሚገባ ለማሳወቅ እና ከቴክኖሎጂ ጋር ተግባብቶ የሚሰራ፣ ዘመኑን የሚመጥን ፖሊሳዊ ቁመናን የተላበሰ አመራር ለመፍጠር እንደሆነም ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ ተናግረዋል።
ስልጠናው የአመራርነት ዕውቀት እና ክህሎትን የሚጨምር፣ ከዚህ በፊት የነበሩ ክፍተቶችን የሚሞላ በአጠቃላይ የዘመነ የፖሊስ አገልግሎት አሰጣጥን የሚያሳድግ እንደሆነ ገልፀዋል።
በስልጠናው መከፈቻ ስነ ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ነብዩ ዳኜን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
30/10/2023
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል የጸጥታና ህግ የአቬሽን መምሪያ አመራርና አባላት ከ70 ሄክታር በላይ ያለሙትን የጤፍ ማሳ በተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ተጎበኘ
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም፦
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል የጸጥታና ተቋማት ጥበቃ ዋና መምሪያ አመራርና አባላት ከ70 ሄክታር በላይ ያለሙትን የጤፍ ማሳ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ጎበኙ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዙሪያ የጸጥታናተቋማት ጥበቃ ዋና መምሪያ የአቬሽን ፖሊስ መምሪያ ላይ የተሰማሩ የፓሊስ አመራሮችና አባላት ከህግ ማስከበር ስራቸው ጎን ለጎን ከ70 ሄክተር በላይ የሚሸፍን የጤፍ ማሳ በማልማት እንደሀገር የተጀመረውን የከተማ ግብርና ልማት ከግብ ለማድረስ የድርሻቸውን ከማበርከታቸውም በላይ የሠራዊቱን ቀለብ ለመደጎም የሚያስችል ተግባር ማከናወቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች በጉብኝቱ ወቅት ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ለአቬሽን ፖሊስ መምሪያ የቢሮ አገልግሎት መስጫ የሚሆን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር ያስገነባውን የሰራዊት ቢሮ አስመርቋል።
28/10/2023
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያሳደሳቸውን ካምፖች እና የማዘዣ ማዕከል አስመረቀ
※※※※※※※※※※※※※※※※※※※※※※※※※※※※※※
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም (ኢፌፖሚ)፡- የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ከኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በመተባባር ያስገነባውን የማዘዣ ማዕከል (Command Centre) እንዲሁም ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያሳደሳቸው በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ዋና ዋና የፖሊስ ካምፖችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ክቡር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በራስ ተነሳሽነትና በራስ አቅም እንዲሁም ከፍተኛ ጥረት በማድረግ እንደዚህ ዓይነት ተግባር መከናወኑ የለውጡ ውጤት እንደሆነ ገልፀዋል።
የካምፕ እድሳት መደረጉና ምቹ የስራ አካባቢን ለመፍጠር የምናደርገው ጥረት ለቢሮ ኪራይ የምናወጣውን ወጪ ከማዳን ባለፈ የገቢ ምንጭ የሚያስገኝ እና ለአካባቢው ማህበረሰብም ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
የነበረውን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ውስንነት በማስቀረት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ተቋሙ በማስገባት ከፍተኛ ለውጥ አምጥተናል ያሉት ክቡር ኮሚሽነር ጀነራሉ ዛሬ ላይ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ በሀገሪቱ በየትኛውም አካባቢ ኦፕሬሽን ስራን ለመስራት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ባለቤት መሆኑ ሰላሟ የተረጋገጠች ሀገር ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት የሚያሳካ ተግባር ነው ብለዋል።
ክቡር ኮሚሽነር ጀነራሉ አሁን አድሰን የምንጠቀምባቸው ካምፖች የቀደሞ የፖሊስ መሪዎች ያስረከቡን ሲሆኑ እኛም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመዘርጋት በአግባቡ ይዘን በመገልገል ለመጪው ትውልድ ማስረከብ ይኖርብናል ብለዋል።
ክቡር ኮሚሽነር ጀነራሉ አያይዘውም አሁን በተያዘው መንገድ በየደረጃው ያለው አመራር አርዓያ በመሆን መስራት ከቻሉ ከዘመኑ ጋር ተወዳዳሪ እና ፕሮፌሽናል በሆነ መልኩ የሀገራችንን ሰላም የሚያረጋግጥ የፖሊስ ተቋም መፍጠር እንደሚቻል ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ በበኩላቸው በለውጡ ካከናወናቸው ተግባራት መካካል ለዘመናት ግንባታቸው ተቋርጦ የነበሩ የቢሮዎች እና የሰራዊቱ መኖሪያ ካምፖች በሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ ከፍተኛ ክትትል እና ቁጥጥር ተደርጎ የተወሰኑት መመረቃቸውን እና የተቀሩት ግምባታቸው በፍጥነት በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን ዛሬ ያስመረቅናቸው በአዲስ አበባ ያሉ ዋና ዋና ካምፖች እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች እየተሰሩ ያሉ ካምፖችና ቢሮዎች ተቋሙ ለኪራይ የሚያወጣውን ከፍተኛ ወጪ ማዳን እንደቻሉ ተናግረዋል።
ዛሬው ዕለት የተመረቀው የማዘዣ ማዕከል በሀገራችን በየትኛውም አካባቢ ለኦፕሬሽን ሥራ አጋዥ የሆነ መተግበሪያን ያካተተ በመሆኑ አሁን ላይ ለተልዕኮአችን ትልቅ አቅም ፈጥሯል ብለዋል።
ይህንን ተግባር ለመከወን ከአቻ ተቋማት እና የስራ ክፍሎች ተሞክሮ መወሰዱን ያነሱት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ ሠራዊቱ በሚገባ በመያዝ በባለቤትነት መጠቀም እንዳለበት አሳስበዋል።
በመጨረሻም በካምፖች እድሳት እና የማዘዣ ማዕከሉን በማዘመን ለአገልግሎት እንዲበቃ ላደረጉ አመራሮችና አባላት እንዲሁም ለኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ ለኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እና ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ ላሳዩት አጋርነት እና እገዛ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
28/10/2023
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ በ3.3 ሚሊዬን ብር በላይ በሆነ ወጪ በውስጥ አቅም በአዲስ አበባ ያሉ ዋና ዋና ካምፓችን ዕድሳት በማድረግ አስመረቀ