06/06/2026
የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ አህጉራዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው
በአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራን በተግባራዊ ፖሊሲዎች ለመደገፍ ያለመ አህጉራዊ ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰኔ 4 እና 5 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ያዘጋጀው ይህ ጉባኤ በአካዳሚክ ምርምሮች እና በፖሊሲ አፈጻጸሞች መካከል ያለውን ክፍተት መሙላትን ታሳቢ ያደረገ ነው።
የአፍሪካ ልማትና የተግባራዊ መፍትሄዎች መድረክ (ADIF 2026) የሚል ስያሜ ያለው ጉባኤ “በአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ የሚረዱ ምርጥ ተሞክሮዎችና የፈጠራ መፍትሔዎች” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ነው።
ጉባኤው በአፍሪካ በፍጥነት እያደገ የሚገኘውን የወጣት ማኅበረሰብ፣ በዓመት ከ15 ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድል በመፍጠር አህጉራዊው ፍላጎትን ለመመለስ ከተያዘው ውጥን ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው።
ይህ አዲስ መድረክ ከተለመዱ አህጉራዊ ስብሰባዎች በተለየ፤ የፖሊሲ አፈጻጸምን በማፋጠን በዘርፉ ያለውን የፖሊሲ እና የአሰራር ሂደት ለማቀለጣፈ ያለመ መሆኑን ኢዜአ ከኢሲኤ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በዚህም መሠረት የኢኮኖሚክ ኮሚሽኑ በገንዘብ እጥረት ምክንያት መሬት ያልወረዱ ጥናታዊ ምርምሮችን ወደ ተግባር ለመለወጥ፣ በጥቂት አካባቢዎች ተሞክረው ስኬታማ የሆኑ አነስተኛ የሙከራ ፕሮጀክቶችን ለማስፋት እንዲሁም አህጉር በቀል ምርጥ ተሞክሮዎችን በአገራት አጠቃላይ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ውስጥ በቀጥታ ለማካተት አቅዷል።
አሠራሩ በልማት ላይ የሚፈሱ የአህጉሪቱ ኢንቨስትመንቶች አስተማማኝና ዘላቂ ውጤት እንዲያመጡ ለማድረግ ትልቅ እገዛ ይኖረዋል ተብሏል።
የፎረሙን ውጤታማነትና ተጠያቂነት በተረጋገጠ መልኩ ለመከታተልም፣ ከጉባኤው በፊት፣ በጉባኤው ወቅትና ከጉባኤው በኋላ የሚተገበር የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቷል።
የመድረኩን ቀጣይነትና ትስስር አስተማማኝ ለማድረግ፣ የየዓመቱ መሪ ሀሳቦችን አንዱ ከሌላው ጋር በማስተሳሰር እና ተመጋጋቢ በማድረግ እንደሚዘጋጁ ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በቀጣይ የሚካሄዱት ፎረሞች፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ትግበራን ከአህጉራዊ የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂዎች ጋር ማስተሳሰር ጨምሮ ሌሎች የልማት የትኩረት መስኮችን ታሳቢ በማድረግ እንደሚካሄድ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።
05/06/2026
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ 5ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ በዛሬው ዕለት አካሄደ።
ለካቢኔው በዛሬው በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡
በዚህ መሰረት፡-
1ኛ. የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ አስተዳደር ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ ተፈፃሚ እንዲሆን አፅድቋል።
2ኛ. የመሬት ይዞታ ማስለቀቅና ካሳ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ እንደገና ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ አፅድቋል።
3ኛ. በግል ዘርፍ ለህክምና ተቋማት ግንባታ እና ማስፉፍያ የሚውል መሬት ለማስተላለፍ የቀረበ የዉሳኔ ሀሳብ ላይ ተወያይቶ፣ ተፈፃሚ እንዲሆን አድፅድቋል።
05/06/2026
ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ማለዳ ላይ፤ የመጀመሪያው የወገግታ ጭላንጭል በከፍታማዎቹ የኢትዮጵያ ተራሮች ላይ ፈንጥቆ ጨለማውን ሳይቀድ በፊት ኢትዮጵያውያን ረጃጅም ሰልፍ ተሰልፈዋል። በጅማ፣ በድሬዳዋ፣ በሐዋሳ፣ በባሕር ዳር እንዲሁም ስማቸው በዓለም አቀፍ የዜና ጋዜጣዎች ላይ ፈጽሞ ሊወጣ በማይችሉ ከተሞችና መንደሮች ውስጥ ያሉ ወንዶችና ሴቶች፤ ወሳኝ ተግባር ለመፈጸም በሰልፍ ቆሙ። ድምፅ ሰጡ! ይህንን ታሪካዊ ኃላፊነት ለመወጣት ከሃምሳ አራት ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ተመዝግበው ነበር። ይህ ቁጥር ከአንዳንድ ሀገሮች አጠቃላይ ሕዝብ ቁጥር በላይ ነው። ይህ ምርጫ እውነተኛ ስለመሆኑ ጥያቄ ለሚያነሣ ለማንኛውም አካል ግልጽ እና የማያሻማ ምላሽ ሰጥቷል!
የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከ52,000 ምርጫ ጣቢያዎች መካከል ከ50,188 በላይ የሚሆኑት በሰዓቱ ተከፍተው ቀኑን ሙሉ መራጮችን ሲያስተናግዱ እንደነበር አረጋግጧል። ከ42 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወጣጡ ከ10,438 በላይ ዕጩዎች እና 80 የግል እጩዎች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤት ወንበሮችን ለማሸነፍ ተወዳድረዋል። ይህ በማንኛውም ሊለካ በሚችል መሥፈርት በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቁ እና በውሳኔ አሰጣጥም ሆነ በአስተዳደራዊ ረገድ እጅግ በረቀቀ ሁኔታ ተግባራዊ የተደረገ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ የታየበት ኩነት ነበር።
የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ክቡር ኡሁሩ ኬንያታ የሚመሩትና ከ37 የአፍሪካ ሀገሮች የተወጣጡ 83 ታዛቢዎችን ያቀፈው የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ምርጫውን “ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን በሰፊው በሚደግፍ ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ ውስጥ የተካሄደ” ሲል ገምግሞታል። በቀድሞዋ የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ክብርት ዶክተር ስፔሲዮዛ ዋንዲራ ካዚብዌ የሚመራው የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት፥ በታዘቡባቸው ጣቢያዎች ሁሉ የምርጫ ሳጥኖች በትክክል የታሸጉ መሆናቸውን፣ የፓርቲ ወኪሎች በሂደቱ በሙሉ መገኘታቸውን እንዲሁም ምርጫው አስደናቂ ተቋማዊ፣ አስተዳደራዊና የቴክኖሎጂ ዕድገትን ያሳየ መሆኑን አረጋግጧል። የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ይሄንን ምርጫ «የበርካታ አዳዲስ ምዕራፎች ምርጫ» ሲል ሰይሞታል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በድምፅ መስጠት ሂደት ውስጥ ምንም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳልተመለከተ አረጋግጧል። የሲቪክ ማኅበረሰብ ታዛቢዎች ጥምረት በምርጫ ቦርድ እውቅና ከተሰጣቸው 55 ድርጅቶች 65,299 የታዛቢዎችን በመላ ሀገሪቱ ያሠማራ ሲሆን፥ 99 በመቶ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ያለምንም ዕንቅፋት የመታዘብ ዕድል ማግኘቱን አረጋግጧል። እነዚህ ተዓማኒነት ያላቸው ሀገራዊ እና አኅጉራዊ ተቋማት ያደረጓቸው ግምገማዎችና የሰጧቸው እውነተኛ ፍርዶች ናቸው። እነዚህ ለአፍሪካ ጥላቻ ካላቸው ወይም የአፍሪካን ዴሞክራሲ በውጫዊ መሥፈርቶች ከሚለኩ ተቋማት የተደመጡ ድምፆች አይደሉም።
አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተንታኞች ይሄንን ምርጫ እንደ ንግሥና በዓል አድርገው ያቆሸሹት ሲሆን ውጤቱም አስቀድሞ የተወሰነ ድራማ እንደነበር አድርገው ሊያቀርቡት ሞክረዋል። እነዚህን መግለጫዎች ከእውነታው ፈጽሞ የራቁ፣ በጥናትና ትንተና ላይ ያልተመሰረቱ እንዲሁም ነፃና የታሰበበት ዴሞክራሲያዊ ምርጫቸውን በኩራት ላደረጉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ክብር የማይሰጡ በመሆናቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሙሉ በሙሉ የማይቀበላቸው መሆኑን ያረጋግጣል። አስቀድሞ የተወሰነ ውጤት ቢኖር ኖሮ፤ ከ37 የአፍሪካ ሀገሮች የተወጣጡ 83 ገለልተኛ ታዛቢዎችን፣
05/06/2026
ዛሬ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነ፣ የሕዝባችንን የጤና አገልግሎት በአዲስ ከፍታ ላይ የሚያስቀምጥ አዲስ የዲኤንኤ(DNA)፣ የፎሬንሲክና ስነምረዛ ምርመራ የልህቀት ማዕከል መርቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል።
ሀገራችን ብዙ የውጭ ምንዛሪ የምታጣበት እና የምርመራ ውጤት ለማግኘት በጣም ረጅም ጊዜ ይፈጅ የነበረውን ችግር የሚያስቀር የDNA መረጃ ማከማቻና ማነጻጸሪያ ሲስተም (CODIS)፣ በወንጀል የተጠረጠሩ፣ ወላጅነትን ለማረጋገጥና ተመሳሳይ ምርመራዎችን በዘር መለያ (DNA Profiling) ለመለየት፣ የቤተሰብ ግንኙነትን እስከ ዘር ሀረግ መለየትና ማረጋገጥ እንዲሁም አጠራጣሪ ማንነትን ለማወቅ የሚያስችል የልህቀት ማዕከል ነው።
ይህ ማዕከል የሀገሪቱን የፍትሕ ሥርዓት ምርመራን ውጤታማ በማድረግና በማዘመን፣ በሳይንሳዊ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ የወንጀል ምርመራ ለማካሄድ፣ የመብት ጥያቄዎችን ለመመለስና ለሕዝብ ጤና ጥበቃ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ብሔራዊ የልህቀት ማዕከል ነው።
ሁሌም ቃልን በተግባር ፈፅመን በቁርጠኝነትና በተሻሻለ የስራ ባህል እየሰራን ባለፉት 5 ዓመታት ለጤናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት 4 ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚመጥኑ ሆስፒታሎች በመገንባትና ነባሮቹንም ሆስፒታሎች በማደስና በማስፋፋት ሰፊ ስራዎችን ሰርተን አዘምነናቸዋል፡፡
በከተማ አስተዳደራችን በጤናው ዘርፍ የኢትዮጵያን የዕድገት ተምሳሌትነት እና የከፍተኛ ቴክኖሎጂ ምዕራፍ እያበሰርን ነው! ተጠናክሮም ይቀጥላል።
ከዚሁ ጎን ለጎን የጤና ባለሙያዎቻችንን ትጋት፣ ብቃት እና እምነት ይበልጥ ለማሳደግ ልዩ ትኩረት እንሰጣለን።
ከእቅድ ጀምሮ የልህቀት ማዕከሉ እውን እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደረጋችሁትን በሙሉ በራሴ፣ በከተማ አስተዳደሩ እና በተጠቃሚዎች ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
05/06/2026
የልማት ስራዎች የአንድ ወቅት ብቻ አይደሉም፥ ዘመን ተሻጋሪ እንጂ!
በተለያዩ የልማት ስራዎች ፈር ቀዳጅ የሆነችው አዲስ አበባ፣ ከ7ኛው ሀገራዊ መርጫ ማግስት በተለያዩ የልማት ስራዎች መገለጥዋን ቀጥላለች፡፡
የልማት ስራዎች የአንድ ወቅት ብቻ አለመሆናቸውን የተረዳው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ከዚህ ቀደም በእንግልት እና በኃላ ቀር አሰራር ህዝብ ሲማረርባቸው የነበሩ የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ይስተዋል የነበረውን ችግር በማስቀረት፣ በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ቀልጣፋና የተቀናጀ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ዘመናዊ ተቋማት እየተገነቡ ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
ከዚህም የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዘንድ ለዓመታት የቆየውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ ታላቅ ስራ ሲሆን፤ በተለይም በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተደራሽ መሆኑ ነዋሪዎች ከተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚያገኟቸውን አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በተቀናጅና በተናበበ እንዲሁም በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲያገኙ አድርጓል።
ቀደም ሲል ቀናትና ሳምንታት ይወስዱ የነበሩ ጉዳዮች፥ ዛሬ በመሶብ የአንድ ማዕከል በደቂቃዎች ውስጥ እልባት ማግኘት ችለዋል፡፡ ከሁሉም በላይ አገልግሎቱ ወደ ነዋሪዎች መቅረቡ ነዋሪዎች ረጅም ርቀት ሳይጓዙ ባሉበት ቦታ በተንቀሳቃሽ መሶብ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል።
እነዚህ ማዕከላት በውስጣቸው ከንግድ ፈቃድ ምዝገባ ጀምሮ እስከ መታወቂያና የውልና ማስረጃ አገልግሎቶች ድረስ እጅግ በርካታ ፋይዳ ያላቸውን ዘርፎች አካትተዋል። በተለይም ለአገልግሎት ፈላጊዎች ምቹ የሆኑ የጥበቃ ስፍራዎች፣ ዲጂታል የሰልፍ መቆጣጠሪያዎች፣ የህፃና ማቆያና ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆኑ መሰረት ልማቶችን በመያዛቸው ተገልጋዩ የጊዜ ብክነት እና እንግልት እንዳይገጥመው ታድገዋል፡፡
በአዲስ አበባ የተጀመረውና በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተግባራዊ የሆነው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቁጥሩን ወደ ስምንት ከፍ በማድረግ እንዲሁም በተንቀሳቃሽ አውቶብስ አገልግሎቱን በማስፉት ነዋሪው እፎይታን እንዲያገኘ ማድረግ ተቸሏል።
የልማት ስራዎች የአንድ ወቅት ብቻ አይደሉም፥ ዘመን ተሻጋሪ እንጂ፥ ይቀጥላል!
05/06/2026
በጀት ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት 3 የመሶብ ዲጂታል አንድ ማዕከላት ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ይሆናሉ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በይፋ የመረቁት የመሶብ ዲጂታል አንድ ማዕከል ነዋሪዎችን ለዓመታት ሲያማርር ከኖረው የአገልግሎት አሰጣጥ እንግልትና ከብልሹ አሠራር የሚታደግ መሆኑን ገልጸዋል።
ከንቲባ አዳነች በማዕከሉ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የኮልፌ ነዋሪዎችን ከአገልግሎት አሰጣጥ እንግልትና ከሙስና የሚታደገው የመሶብ ዲጂታል ማዕከል በይፋ ሥራ መጀመሩን አብስረዋል።
ይህ ዘመናዊ የዲጂታል ማዕከል ለአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን ፣ የረጅም ጊዜ የሀገር ግንባታን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተገነባ መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባዋ፤ ነዋሪዎች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚደርስባቸውን ውጣ ውረድ በማስቀረት፣ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ሳያባክኑ የፈለጉትን አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።
በከተማዋ በርካታ የልማት ሥራዎች ቢሠሩም፣ አሁንም ድረስ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚታዩትን እንደ ፈጣን አገልግሎት አለመስጠት፣ እንግልት እና የእጅ መንሻ (ጉቦ) ጥያቄዎችን ከመዋቅሩ ውስጥ መንጭቆ ለማውጣት ማዕከሉ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
ነዋሪዎች ፈጣን፣ ቀልጣፋና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ያለምንም ጉቦ ማግኘት የሚችሉበትን አስተማማኝ ሥርዓት ይፈጥራል ብለዋል ከንቲባ አዳነች።
በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የተጀመረው ይህ የዲጂታላይዜሽን ንቅናቄ በዚህ ብቻ እንደማያበቃ የገለጹት ከንቲባ አዳነች ፣ ሦስት ተመሳሳይ የዲጂታል ማዕከላት የበጀት ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት፣ ተጠናቀው ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።
ሕዝቡ በምርጫው ወቅት ያሳየው ታላቅ ፅናትና ፍላጎት፤ ሰላም፣ ልማት እና አጠቃላይ ሀገራዊ አካሄዶች በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲጓዙ መሻቱን በተግባር ያረጋገጠበት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የዚህን ፅኑ ሕዝብ ጥያቄዎችና ፍላጎቶች በሚመጥን መልኩ ምላሽ መስጠት፣ ሥልጣን ከሚይዘው አካል የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ያለምንም የውጭ ተፅዕኖ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በራሷ ሕዝቦች፣ በሰላማዊና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ማካሄዷ እና በምርጫው ማግስትም እንደነዚህ ያሉ ተጨባጭ ፍሬዎችን ማስመዝገቧ፣ የጀመረችው የብልጽግና ጉዞ ወደ ከፍታ እንደሚመራ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ማሳያ መሆኑን ከንቲባዋ ገልጸዋል።
05/06/2026
በቀድሞው የአዲስ አበባ ከንቲባ አምባሳደር አሊ አብዶ ህልፈተ ህይወት ጥልቅ ሃዘን ተሰምቶኛል።
አምባሳደር አሊ አብዶ 27ኛ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በመሆን እንዲሁም በሱዳን እና በናይጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ሀገራቸውን ያገለገሉ የሃገር ባለውለታ ናቸው።
ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጆቻቸው እና ለመላው ህዝብ መጽናናትን እመኛለሁ።
ፈጣሪ ነብሳቸውን በአጸደ ገነት ያኑር።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ