12/04/2026
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የፋሲካን ማዕድ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ታደሙ
ሚያዝያ 04/2018 ዓ.ም
በመላው ኢትዮጵያ በክርስትና ጥላ ውስጥ በሚገኙ ቤተ-እምነቶች ያሉ ክርስቲያኖች የትንሳኤን በዓል በተስፋ፣ በመስዋዕትነት እና በአዲስ መነሳት መንፈስ በአንድነት ያከብራሉ።
ከሳምንታት የፆም፣ ጥሞና እና ራስን የመመልከት ጊዜ በኋላ ፋሲካ በእውነተኛ አምልኮ፣ መንፈስን አድሶ፣ ቤቶችንም በደስታ ይሞላል። በዘመድ አዝማድ መጠያየቅ እና ማዕድ መካፈልም ፍቅርን ያዳብራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ዓመታዊውን የፋሲካ መዐድ ማጋራት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በአንድነት ፓርክ በጋራ መታደማቸው ለእውነተኛው የአንድነት መንፈስ ጉልህ ማሳያ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡
በዓለ ትንሳኤው በመላው ኢትዮጵያ የእምነት፣ ቤተሰባዊነት እና የመታደስ መንፈስ የሚታይበት ጊዜ ነው። ሁላችንም በዚህ የትንሳኤ መንፈስ ዛሬም፣ ነገም፣ ሰርክ ቤታችንን፣ ልባችንንም ለተቸገሩ ወገኖች እንክፈት! መልካም በዓል ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፏል።
12/04/2026
የትንሳኤ በዓልን ስናከብር እርስ በራስ በመረዳዳት እና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር ተናገሩ!
የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በአብርሆት ቤተ መጻህፍት አቅመ ደካማ አረጋውያንን ጾም የማስፈሰክ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ማዕድ ያጋሩት የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እና የአብርሆት ቤተ መጻህፍት ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር የጾሙን ወቅት በጸሎት ያሳለፉ አረጋውያን በትንሳኤ እለት በትውፊቱ መሰረት በሌሊት የማስፈሰክ መርሃ ግብር በአብርሆት ቤተ መጻህፍት ባለፉት አመታት ሲካሄደ መቆየቱን አስታውሰው ይህን መሰሉ በዓልን አብሮ የማክበር መርሃ ግብር ሊስፋፋ እና ሊጠናከር የሚገባው ነው ብለዋል።
ህብረተሰቡ በዓልን ሲያከብር በአከባቢው ያሉ አቅመ ደካሞችንና ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ ወገኖችን በማሰብ እርስ በእርስ በመረዳዳት እና በመደጋገፍ ሊሆን እንደሚገባም ነው አፈ ጉባኤዋ የተናገሩት።
11/04/2026
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ፤ እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
የትንሣኤ በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ መዳን ያለውን ፍቅር እስከ መስቀል ሞት የገለጸበትና የሞት ድል የተበሰረበት ታላቅ ዕለት ነው። በመሆኑም በዓሉን ስናከብር በታላቅ ፍቅር፣ በትሕትና እና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባል።
ድጋፍ ለሚሹ ወገኖቻችን ያለንን አጋርነት በተግባር የምንገልጽበት፣ አንዳችን ለሌላችን የደስታ፣ የሰላም እና የአብሮነት ምክንያት የምንሆንበት በዓል እንዲሆንልን እመኛለሁ።
መልካም በዓል!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
11/04/2026
አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልቃድር በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የተገነቡ የመኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች አስረከቡ ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎችን የቤት ባለቤት ለማድረግና ሰብዓዊ ክብራቸውን ለመጠበቅ እየተገበራቸው ባሉ የተለያዩ አማራጮች ዛሬ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አዳዲስ የመኖሪያ ቤቶች ተመርቀው ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ክብርት ቡዜና አልቃድር፣ በክፍለ ከተማው አስተዳደርና በከተማው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ትብብር የተገነባውን ጂ+3 የመኖሪያ ሕንጻ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል። ይህ ሕንጻ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በመንግሥት አስተባባሪነትና በባለሀብቶች ተሳትፎ የተገነባ መሆኑ ተገልጿል።
ከዚሁ የምረቃ መርሃ-ግብር ጎን ለጎን፣ በልማት ምክንያት ከመኖሪያቸው ለተነሱና በገላን ጉራ ሳይት ዕጣ ለወጣላቸው 25 የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ይፋዊ የቁልፍ ርክክብ ተከናውኗል። ለተነሺዎቹ የተላለፉት እነዚህ ቤቶች ሙሉ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተሟሉላቸው አካባቢዎች የተገነቡ፤ የነዋሪዎችን ሰብዓዊ ክብርና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ከግምት ውስጥ ያስገቡ መሆናቸው ተመልክቷል።
አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልቃድር በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የከተማ አስተዳደሩ ከለውጥ ወዲህ በመኖሪያ ቤት ግንባታ ዘርፍ ፈጣንና ጥራት ያለው እመርታ እያስመዘገበ መሆኑን ጠቁመዋል። በተለይም ሁሉም በደስታ በሚያከብረው የበዓላት ወቅት ነዋሪዎችን ወደ አዲስ ቤት ማስገባት መቻሉ ልዩ እርካታ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
የዕድሉ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው፣ በበዓሉ ዋዜማ የቤት ባለቤት በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል ።
11/04/2026
የአዲስ አበባ ከተማ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ባለሀብቶችን በማስተባበር በየካ ክፍለ ከተማ ያስገነባቸውን የመኖሪያ ቤቶች ለተጠቃሚዎች አስተላለፈ።
በዕለቱ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ጃንጥራር አባይ ከተማ አስተዳደሩ ለቤት ልማት ከፍተኛ ሀብት በመመደብ በቤት ልማት ከፍተኛ ስራ መስራቱን ገልጸዋል።
በተለይ ባለፉት የለውጥ አመታት ከተማ አስተዳደሩ በርካታ ቤቶችን በማልማት ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍን ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስተራችን በጀመሩት ከተማን መልሶ በማልማት የማደስ ስራ ቀና ልብ ያላቸውን ባለሀብቶች በማስተባበር ከፍ ሲል ህንጻ ዝቅ ሲል ቪላ የሆኑ ቤቶችን በመገንባት ተጠቃሚዎች ህይወታቸውን በደስታ እንዲያሳልፉ ለማድረግ በርካታ ስራዎችን እንደተሰሩም ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።
ሰው ተርፎት ብቻ ሳይሆን የሚሰጠው ካለው ላይ በመቀነስ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር ሁሉም መረዳዳት ቢችል ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል ብለዋል።
መጨረሻም በዚህ የቤት ግንባታ የተሳተፉት ዮት ኮንስትራክሽን እና ግንባታውን ሲከታተሉ ለበሩ ለኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አመራሮች እንዲሁም የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮችን በማመስገን ለቤት ተጠቃሚዎችም እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል ።
11/04/2026
“እንደ-አዲስ” ልዩ ኘሮግራም!
ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጋር።
ዛሬ ምሽት 3 ሰዓት ይጠብቁን
11/04/2026
እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን!
ሁልጊዜም በበዓላት ወቅት እንደምናደርገው፣ ዛሬ በትንሣኤ በዓል ዋዜማ በከተማችን የተለያዩ አካባቢዎች በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር የገነባናቸውን 215 ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች፤ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ ለአቅመ ደካሞች፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአገር ባለውለታዎችና ለልማት ተነሺዎች ከሙሉ የቤት ቁሳቁስና ከበዓል መዋያ ጋር አበርክተናል።
በከተማችን የበጎ ፈቃድ ተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተና ባህል እየሆነ መምጣቱ የሚያስደስት ነው። ይህንን በጎ ተግባር በተለያየ መልኩ ለደገፋችሁ ልበ ቀና በጎ ፈቃደኞች፣ ተቋማትና አመራሮች በሙሉ በተለይም ከ 80 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ላደረገው የኦሮሚያ ባንክ በተጠቃሚዎች ስም ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
የትንሣኤ በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ በፍቅር ራሱን እስከ መስቀል የሰጠበት እና በትንሣኤ የምሥራች የተበሰረበት ነው። በመሆኑም በዓሉን ስናከብር በትሳኤን ዓላማ እና ምሳሌነት መሰረት በታላቅ ፍቅር እና መተሳሰብ ሊሆን ይገባል። ድጋፍ ለሚሹ ወገኖቻችን ያለንን መተሳሰብ በተግባር የምንገልጽበት፣ አንዳችን ለሌላችን የደስታ፣ የሰላም እና የአብሮነት ምክንያት የምንሆንበት በዓል እንዲሆንልን እመኛለሁ።
መልካም በዓል!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ