23/03/2026
“ኢዜማ የብሔር ፌዴራሊዝም አወቃቀርን በመተው ዜጎች በእኩልነት የሚኖሩባትን ሀገር ለመገንባት ይሠራል”
- አቶ ኢዮብ መሳፍንት
የኢዜማ ፓርቲ መሪ
++++++++++++++++++++++++++++
#ጋዜጣ ፕላስ | ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የብሔር ፌዴራሊዝም አወቃቀር ወጥታ ዜጎች በእኩልነት የሚኖሩባትንና የጋራ ባለቤትነታቸው የሚረጋገጥባትን ሀገር ለመገንባት እንደሚሠራ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ገለጸ፡፡
የፓርቲው መሪ አቶ ኢዮብ መሳፍንት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የሀገሪቱ ግዛት እኩል የመኖርና የባለቤትነት መብት ያለው እንጅ በየትኛውም ቦታ አንዱ ከሌላው የተለየ ልዩ መብት ሊኖረው አይገባም፡፡
ኢዜማ በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ አሸንፎ ስልጣን ቢይዝ ክልሎች የማንነት፣ የልማት አመቺነት፣ የአስተዳደር ምቹነት እና ኢኮኖሚያዊ ራስን መቻልን መሰረት ባደረጉ 4 መስፈርቶች ይዋቀራሉ፡፡
ይህ አዲሱ የክልሎች አወቃቀር አሁን ካለው አሠራር ጋር ሙሉ ለሙሉ ልዩነት ያለው መሆኑንና ለሁሉም ዜጎች እኩል የባለቤትነት መብት እንደሚሰጥም አቶ ኢዮብ መሳፍንት አስታውቀዋል።
ኢዜማ በምርጫ ማኒፌስቶውም ሆነ በፖሊሲ አማራጮቹ የዜግነት ፖለቲካ ያራምዳል ያሉት የፓርቲው መሪ፤ ሁሉም የባለቤትነት ጥያቄ የሚነሳባቸው "አከራካሪ" ቦታዎች እና የሀገሪቱ ክልሎች የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ንብረት ናቸው ብሎ ያምናል ብለዋል፡፡
የወሰን ክርክሮችና “የእኔ ግዛት” የሚሉ ትርክቶች ለሀገራዊ አንድነትና ሉዓላዊነት ከፍተኛ ስጋት መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ኢዮብ፤ “በዚህ ክልል አንተ መጤ ነህ፣ እኔ ባለቤት ነኝ” የሚሉ ኋላ ቀር አመለካከቶች በአስቸኳይ ሊቆሙ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የባለቤትነት ስሜት መሸርሸር ዜጎች ሀብታቸውን አፍስሰው እንዳይሰሩና የሀገር ሉዓላዊነትን ለመጠበቅ እና ከውጭ ወራሪ ለመከላከል ያላቸውን ተነሳሽነት እንደሚቀንስ የጠቆሙት አቶ ኢዮብ፤ ይህ አይነቱ አካሄድ እንዲታረም ፓርቲያቸው እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
በመዓዛ ማሞ
+++++++++++++++++++++
@ጋዜጣ-ፕላስ #ኢትዮጵያ #ኢዜማ #ምርጫ #ፖለቲካ #7ተኛው #ሀገራዊምርጫ

22/03/2026
22/03/2026
22/03/2026
09/02/2026
09/02/2026
09/02/2026
01/02/2026
01/02/2026