Ethiopian Civil Aviation Authority

Ethiopian Civil Aviation Authority

Share

Ecaa envisions to become Africa's Aviation Hub by 2033

27/05/2026

ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1447ኛዉ የዒድ አል-አድሃ አረፋ በዓል በሰላም አደረሳችሁ እያለ በዓሉ የደስታ እና የጤና እንዲሆንልዎ የኢትዮጽያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡

Photos from Ethiopian Civil Aviation Authority's post 08/05/2026

የአውሮፕላን አደጋ ቢከሰት በፈልጎ ማዳን ተግባራት ዙሪያ የምክክር መድረክ ተዘጋጀ

የአውሮፕላን አደጋ ቢከሰት ፈጥኖ በመድረስ የሰው ህይወትን መታደግ በሚያስችሉ መሰረታዊ የፈልጎ ማዳን ጉዳዮች ዙሪያ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ፡፡

ዛሬ ሚያዚያ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ለግማሽ ቀን በተካሄደው የምክክር መድረክ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርና የውይይት መድረኩ ሰብሳቢ አቶ ዮሀንስ አበራ ‘የፈልጎ ማዳን ስራ ሰብዓዊነት የተላበሰ ምንም ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ አጀንዳ የሌለው መሆኑን የተናገሩ ሲሆን በአየር ትራንስፖርት ዘርፉም አንድ ሀገር ጠንካራ የፈልጎ ማዳን አቅም ከሌላት የበረራ ደህንነት ጥያቄ (safety concern) የሚያስነሳ፣ በአለም አቀፍ አቪዬሽን ማህበረሰብ ዘንድ ቅቡልነትን የሚያሳጣ መሆኑን በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ አደጋዎች ቢከሰቱ የፈልጎ ማዳን ስራን በአስተባባሪነት እንደሚያከናውን በአዋጅ ስልጣን የተሰጠው ሲሆን ይህን ትልቅ ኃላፊነት ከኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከክልል የፀጥታ ኃይሎች፣ በየደረጃው ያሉ የደህንነት ተቋማት፣ ከጤና ሚንስቴር፣ ከግል አየር መንገዶችና ከብሔራዊ አየር መንገዱ፣ ከማህበረሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲቲዩት፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጥምረት የሚከናወን ነው፡፡

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አንድ የአውሮፕላን አደጋ በተከሰተ በሁለት ሰዓታት ጊዜ ውስጥ መድረስ ከተቻለ የበርካታ ሰዎችን ህይወት የማዳን እድሉ ከፍ እንደሚል የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ የፈልጎ ማዳን ስራ ብርቱ ጥረት እንደሚጠይቅ የማሌይዢያ አውሮፕላን አደጋ እና መሰል ሌሎች ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በማንሳት አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአየር ትራንስፖርት እድገትን እያስመዘገበ ሲሆን ይህን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎች መሰራት እንዳለበት የገለፁት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ንጉሴ ሲሆኑ በአሁን ወቅት በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የሚነሱና የሚያርፉ አውሮፕላኖች ፤የሀገራችንን አየር ክልል አቋርጠው የሚያልፉትን ጨምሮ በኢትዮጵያ አየር ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አውሮፕላኖች ቁጥር በዓመት እስከ 250 ሺህ እንደሚደርስ ም/ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

ከተሳታፊዎች በፈልጎ ማዳን ተከታታይነት ያለው ውይይቶች ማድረግ እንደሚገባ፣ በሚዲያ የኮሚዩኒኬሽን ስራዎች መሰራት እንዳለበት፣ የእያንዳንዱ ባለድርሻ አካላት ሀላፊነቶችና ግዴታዎች ተለይተው መቀመጥ እንዳለባቸውና ሌሎች መሰል ገንቢ ሀሳቦች ቀርበዋል፡፡

የፈልጎ ማዳን ስራ ከፍተኛ የሰው ሀይልና የማቴሪያል አቅም የሚጠይቅ እንደመሆኑ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍልን ተሳትፎ የሚጠይቅ ሀገራዊ ተግባር ነው፡፡ ለህብረተሰቡም ይህን ግንዛቤ ለመፍጠር የመገናኛ ብዙሀን ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ በውይይቱ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

05/05/2026
Photos from Ethiopian Civil Aviation Authority's post 30/04/2026

የአለም አቀፍ ድርጅቶች የስራ ሃላፊዎች የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን የስራ እንቅስቃሴ ተመለከቱ
ከዋና ዳይሬክተሩና ማኔጅመንታቸው ጋር በጋራ መክረዋል

የአለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት ቀጣና ዳይሬክተር ሚስ ሉሲ ምቡጉአ እና የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን (AFCAC) ዋና ፀሀፊ ሚስ አደፉንኬ አደየሚ ዛሬ መጋቢት 22 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ተገኝተው ከዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዮሀንስ አበራና የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው አቶ ዮሀንስ ስለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጠቅለል ያለ ግንዛቤ የሚሰጥ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ወቅታዊና ዋንኛ የተቋሙ የትኩረት አቅጣጫ በሆነው የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ቀጣይ ኦዲት ዙሪያ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ላይ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ማባብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በተለይ ከሚስ ሉሲ ጋር በነበራቸው ውይይት ከወራት በፊት በኦዲት ዝግጅቱ ዙሪያ ድጋፍ ለማድረግ የመጡትን የአለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የቀጣናው ልዑካን በማስታወስ ከፍተኛ እገዛ እየተደረገላቸው እንደሆነ ከምስጋና ጋር የገለፁት አቶ ዮሀንስ በቀጣይም ትብብራቸው እንደማይለያቸው ያላቸውን ፅኑ እምነት ገልፀዋል፡፡

ሚስ ሉሲ በበኩላቸው እስከ ኦዲቱ መጨረሻው ዕለት የቀጣናው ቢሮ ድጋፍ እንደማይለያቸው ተናግረው ቀደም ሲል ተቋሙ ካስመዘገበው 89.55 ኦዲት ከፍ ያለ ነጥብ ለማስመዝገብ በትጋት መስራት ይገባችኋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የአሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽና ዋና ጸሀፊ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በመግለፅ በተለይ በአየር ትራንስፖርት ዘርፉ ብዙ በጋራ ልንሰራባቸው የሚያስችሉ የትብብር መድረኮች ይኖራሉ ብለዋል፡፡

ሁለቱ ታላላቅ የአቪዬሽን በተለያዩ የተቋሙ የቁጥጥር አካላት፤ ማለትም በኤሮድሮም ሴፍቲና ስታንዳርድ፣ በአውሮፕላን ምዝገባና የበረራ ብቃት ማረጋገጫ ሰርቪላንስ እና በአቪዬሽን ባለሙያዎችና የትምህርት ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬቶች በመዘዋወር የስራ እንቅስቃሴያቸውን የጎበኙ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ ድጋፍ በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ ሁሉ ከጎናቸው እንደሚቆሙ በፅኑ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን የዋናው መስሪያ ቤት ህንፃ ጎብኝተዋል፡፡

Photos from Ministry of Transport and Logistics - Ethiopia's post 29/04/2026
29/04/2026

የአለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር (IATA) ኮንፈረንስ ዛሬ ይከፈታል

የአለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር (IATA) 'Elevating Aviation Safety, Connectivity, and Operational Efficiency in Africa’ በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ አለም አቀፍ ኮንፈረንስ ዛሬ ሚያዚያ 21 ቀን 2018 ዓ.ም ይጀመራል፡፡

ለሁለት ቀናት የሚቆየውን ኮንፈረንስ ያዘጋጀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ሲሆን የካርጎ ሴፍቲን ማሳደግ፣ የአየር መንገዶችንን እርስ በእርስ ቁርኝት ማጎልበትና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ማሳደግ በሚሉ ዓበይት ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ በርካታ ንግግሮች በዛሬው ዕለት በአለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት የቀጠናው ዳይሬክተር ሚስ ሉሲ ምቡጉዋን ጨምሮ ከዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ድርጅቶች ማለትም ከአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን (AFCAC) ፣ የአፍሪካ ኤርላይን ማህበር(AFRAA)፣ የደቡብ አፍሪካ ሀገራት አየር መንገዶች ማህበር(AASA) አመራሮች ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ንግግሮችን የሚያቀርቡ ሲሆን መድረኩን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚንስትር ክቡር ዓለሙ ስሜ (ፒ.ኤች.ዲ) እንደሚከፍቱት ይጠበቃል፡፡

የአለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ጋር በግራውንድ ኦፐሬሽን ዙሪያ በጋራ ለመስራት በሚያስችላቸው የመግባቢያ ሰነድ ረቂቅ ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን አቋም የሚያመላክቱ ፕረዘንቴሽን በአየር ኦፐሬተሮች ብቃት ማረጋጫ ሰርቪላንስ ዳይሬክተር እንደሚቀርብም ይጠበቃል፡፡ ኮንፈረንሱ በነገው ዕለትም ቀጥሎ ይውላል፡፡
(የእለቱን ዝርዝር የኮንፈረንስ ውሎ ይዘን እንቀርባለን)

Photos from Ethiopian Civil Aviation Authority's post 28/04/2026

ኢትዮጵያና ሞዛምቢክ በአቪዬሽን ዘርፍ በትብብር ለመስራት ተስማሙ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣንና የሞዛምቢክ ሲቪል አቪዬሽን ሬጉሌሽን ባለስልጣን በተለያዩ የአቪዬሽን መስኮች በጋራና በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ሚያዚያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር ዋና መሰብሰቢያ አዳራሽ በሁለቱ አካላት መሀከል ከተካሄደው የፊርማ ስነስርዓት ለመረዳት እንደተቻለው የትብብር ማዕቀፉ በኤርናቪጌሽን እና ኤርፖርቶች፣ በአውሮፕላን ኦፐሬተሮች ሴፍቲ ኦቨርሳይት እና ሰርቬይላንስ ፣ በአውሮፕላኖች ተስማሚነትና ብቃት ምዘና ፣ በሴፍቲ ማኔጅመንት ሲስተም እና በስቴት ሴፍቲ ፕሮግራሞች፣ በዘላቂ አቪዬስን ፊዩልና ሌሎች አምስት ተጨማሪ የአቪዬሽን የሙያ ዘርፎችን ያካትታል፡፡

ፊርማውን በኢትዮጵያ ወገን የፈረሙት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሀንስ አበራ ሲሆኑ በሞዛምቢክ በኩል ደግሞ የሲቪል አቪዬሽን ሬጉሌሽን ሊቀመንበርና ሚስተርዋና ስራ አስፈፃሚ ኢማኑኤል ሆዜ ኮንቼ ቻቬዝ ናቸው፡፡

የሞዛምቢክ ሲቪልአቪዬሽና ሬጉሌሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ኢማኑኤል ከኢትዮጵያ በኩል ሰው እንዲመደብና ከሀገራቸው የአቪዬሽን አካላት ጋር የጋራ ኮሚቴ በማቋቋም በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎችንና ስብሰባዎችን በቅንጅት እንዲያመቻቹ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ዋና ዳይሬከተሩም ሀሳቡን ተቀብለው ሰው እንደሚመድቡ ተናግረው እግረመንገዳቸውን ከሞዛምቢክ የሲቪል አቪዬሽን ሬጉሌሽን ባለስልጣን ጋር በጋራ መስራት በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡

በፊርማው ስነስርዓት ላይ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል ተስፋዬን ጨምሮ ሌሎች የክፍል ዳይሬክተሮች ተገኝተዋል፡፡

Photos from Ethiopian Civil Aviation Authority's post 28/04/2026

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የILS (Instrument Landing System) መሳሪያ ተከላ ለማከናወን ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት በሚያከናውናቸው የተለያዩ የማስፋፊያ ስራዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ፡፡

በዋና ዳይሬክተሩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው ውይይት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሃንስ አበራ የአየር ትራንስፖርት ደህንነትን ለማስጠበቅና የምንሰጠውን አገልግሎት ለማዘመን የምንሰራቸው ስራዎች የሃገራችን የአቬሽን እድገት ላይ ጉልህ ሚና ያላቸው በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በእኔነት ስሜት ሊረባረቡ ይገባል" ያሉ ሲሆን በክረምት ወራትና የአየር ንብረቱ አስቸጋሪ በሚሆንበት ወቅት አውሮፕላኖች ያላንዳች ችግር ለማረፍ እንዲችሉ የሚረዳቸው ዘመናዊ መሳሪያዎች(Instrument Landing System/ILS) የመግጠም ስራ ያለምንም የጊዜ መጓተት ሊከናወን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

አቶ ዮሃንስ አያይዘውም ባለስልጣን መስሪያቤቱ የሚከናወነው ይህ የማስፋፊያና የአየር ትራንስፖርት ዘርፈን የማዘመን ስራ የአውሮፕላኖችን ደህንነት የማስጠበውና በቀጣይ ለሚደረገው የአለም አቀፍ የአቪዬሽን ተቋም (ICAO) ኦዲት ዝግጅት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡

የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የኤርናቪጌሽን አገልግሎት ዘርፍ ም/ዋናዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ንጉሴ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት ባለስልጣን መስሪያቤቱ በቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት በሚያደርገው የማስፋፊያ ስራዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው የጋራ ውይይት በቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ሁለት(2) የአውሮፕላን ማረፊያ ሜዳዎች በክረምት እና ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ በሚኖርበት ወቅትና አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ በማፈራረቅ ለመጠቀም የተዘጋጁ እንደመሆናቸው አንደኛው ማረፊያ በጥገና ወይም በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎት በማይሰጥበት ሁኔታ ላይ ሌላኛውን ለመጠቀም ያስችላል ብለዋል፡፡

አቶ መንግስቱ አያይዘውም የአየር ንብረት በማይኖርበት ሁኔታ ውስጥ (ሰማዩ በጉም ተሸፍኖ አውሮፕላን ማሳረፍ በማያስችልበት ወቅት) አብራሪውን መሬት ድረስ የሚያሳርፍ Instrument landing system/ILS የተሰኘ መሳሪያ በአንደኛው የአየር ማረፊያ ላይ ለመገንባት ሰፊ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው ከዚህ በፊት Category ||| የተሰኘ ዘመናዊ መሳሪያ ተተክሎ ክረምት ከመግባቱ በፊት አገልግሎት እንዲሰጥ ዝግጅት የተጠናቀቀ ሲሆን በሁለተኛው የማረፊያ ሜዳ ላይ ይህንን መሳሪያ መትከል በማስፈለጉ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር (ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ..) የጋራ ውይይት በባለስልጣን መደስሪያ ቤቱ መካሄዱን አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በየዕለቱ ከሚያስተናግዳቸው ስድስ መቶና ከዚያ በላይ በረራዎች በተጨማሪ የኢትዮጵያን የአየር ክልል አቋርጠው የሚያልፉ (Overe Flight) ቁጥር በጣም እየጨመረ በመሆኑ ይህንን የሚመጥን ስራ መሬት ላይ መስራት በማስፈለጉ ይህ የማስፋፋት ስራ ሌሎች እየተሰሩ ካሉ የራዳርና የኮሙዩኒኬሽን ስራዎች ጋር ተዳምሮ የሃገራችንን የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያራምድ ነው፡፡

23/04/2026

በፌዴራል መንግስት የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ውስጥ ተቋማዊ የአሰራር ለውጥ ማምጣትን ማዕከል ያደረገ ሲሆን ሪፎርም እየተተገበረ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣንም የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ቀርፆ ለመተግበር ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡ በሪፎርሙም ዙሪያ በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረኮች ተከናውነዋል፡፡ ሀኖም ግን የሪፎርሙን መሰረታዊ አላማዎች ሁሉም ሰራተኛ በደምብ ተረድቶት (internalize) ማድረግ እንደሚገባው ታሳቢ በማድረግ የሪፎርሙን ሰባት አበይት ዓላማዎች እንደሚከተለው ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ዋና ዋና አላማዎች
መንግስት የሀገራችን የሲቪል ሰርቪስ ተቋማትና ባለሙያዎች ብቃት ያላቸው፣ ጊዜውን የሚዋጁና ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆኑ ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ዋና ዓላማ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን እንዲሁም ብዝሃነትን እና አካታችነትን ያረጋገጠ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት የሚያቀርብ እና ለአገራዊ የልማት ግቦች ስኬት ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነፃ፣ ገለልተኛና ብቁ ተቋም መገንባት ነው፡፡
የሪፎርሙ ዋና ዋና አላማዎች ከዚህ እንደሚከተለው ይቀርባሉ።

1. ቀልጣፋና ተደራሽ የመንግሥት አገልግሎት አቅርቦት ሥርዓት መዘርጋት፤

የመንግሥት አገልግሎቶችን ለዜጎችና ለተገልጋዮች ምቹና ተደራሽ እንዲሆኑ በማድረግ በአነስተኛ ወጪና ጊዜ ጥራት ያለው ውጤት ማስመዝገብ ላይ ያተኩራል። ይህም አላስፈላጊ ቢሮክራሲን በማስቀረትና አሠራሮችን በማሳለጥ የተገልጋዩን እርካታ የሚያረጋግጥና ለሀገራዊ ልማት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ቀልጣፋ የአገልግሎት አቅርቦት ሥርዓት መገንባትን ያለመ ነው።

2. ውጤታማ የመንግሥት አደረጃጀትና አስተዳደር ሥርዓትን ማሳለጥ፤

የመንግሥት ተቋማት ተልዕኮና ተግባር ተደራራቢነትን በማስቀረት፣ ግልጽና ተናባቢ የሆነ አደረጃጀት በመፍጠር የሥራ ሂደቶች ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርጋል። ይህም ውሳኔ አሰጣጥን በማሳለጥና የሀብት ብክነትን በመቀነስ፣ ተቋማት ለተሰጣቸው ኃላፊነት ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሚችሉበትን ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት ላይ ያተኩራል።

3. የመንግስት ሰራተኞች የብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ስርዓት መገንባትና የማስፈጸም አቅምን ማሳደግ፤

በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በዕውቀትና በክህሎት ላይ የተመሠረተ የሥራ ስምሪት እንዲኖር፣ ግልጽና ደረጃውን የጠበቀ የብቃት ምዘና ሥርዓት በመዘርጋት የሠራተኛውን የማስፈጸም አቅም ቀጣይነት ባለው ሥልጠና ማሳደግ ላይ ያተኩራል። ይህም ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች ብቻ ኃላፊነት የሚረከቡበትን አሠራር በማረጋገጥ፣ ተቋማዊ ግቦችን በላቀ ጥራትና ፍጥነት ለማሳካት የሚያስችል ጠንካራ የሰው ሀብት መገንባትን ያለመ ነው።

4. ብዝኃነትንና አካታችነትን ያረጋገጠ ሲቪል ሰርቪስ ግንባታን ማፋጠን፤

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሀገሪቱን ብዝኃነት የሚያንፀባርቁና ለሁሉም ዜጎች እኩል ዕድል የሚሰጡ እንዲሆኑ በማድረግ፣ ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችንና ልዩ ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በውሳኔ ሰጪነትና በሥራ ስምሪት ውስጥ ማሳተፍ ላይ ያተኩራል። ይህም የተለያየ ዕውቀትና ተሰጥኦ ያላቸው ዜጎች በጋራ የሚሰሩበት አካታች የሥራ አካባቢ በመፍጠር፣ ተቋማዊ ተቀባይነትንና ማኅበራዊ ፍትህን ማረጋገጥን ያለመ ነው።

5. የዲጂታል ሲቪል ሰርቪስን በመገንባት ቅቡልነት ያላቸው አገልግሎቶችን ማሳለጥ፤

የመንግሥት አገልግሎቶችንና ውሳኔ አሰጣጥን ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመደገፍ ደንበኞች ፈጣን፣ ግልጽና ወጥ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል። ይህም በእጅ ንክኪ የሚፈጠሩ ስህተቶችንና ቢሮክራሲን በማስቀረት፣ የተቋሙን ተዓማኒነት የሚያሳድግና ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን መሠረት ያደረገ ቀልጣፋ አሠራር መገንባትን ያለመ ነው።

6. ነጻና ገለልተኛ ሲቪል ሰርቪስ ግንባታ፤

የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆነው በሙያዊ ብቃትና በሕግ የበላይነት ላይ ብቻ ተመስርተው ለሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ላይ ያተኩራል። ይህም የመንግሥት ሠራተኛው የፖለቲካ ለውጦች ባጋጠሙ ቁጥር ሳይናወጥ ሥራውን በገለልተኝነትና በታማኝነት እንዲያከናውን በማስቻል፣ የተቋማትን ቀጣይነትና ተዓማኒነት ማረጋገጥን ያለመ ነው።

7. የሲቪል ሰርቪስ ገቢር ነበብ አመራር እና ተቋም ግንባታን ማፋጠን፤

በተግባር ላይ የተመሰረተና ውጤት ተኮር የሆነ አመራር በመገንባት፣ ተቋማት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት መወጣት እንዲችሉ የማስፈጸም አቅምንና ተቋማዊ ባህልን ማሳደግ ላይ ያተኩራል። ይህም አመራሩ ከንድፈ-ሀሳብ ባለፈ ለውጥ አምጪ ተግባራት ላይ እንዲረባረብ በማድረግ፣ ጠንካራ፣ ተገማችና ስኬታማ ተቋማትን መገንባትን ያለመ ነው።

Want your business to be the top-listed Government Service in Addis Ababa?

Click here to claim your Sponsored Listing.

Location

Telephone

Address


Ethiopia International Air Port
Addis Ababa
1000