31/03/2026
"ከሀገራችን አልፎ ለአፍሪካና ለሌሎችም ሀገራት ጭምር ሞዴል በሆነ ተቋም ውስጥ ህዝብና መንግስትን ማገልገል መቻል ትልቅ ዕድል ነው" ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ርስቱ ይርዳው
*************
መጋቢት 22 ቀን 2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ርስቱ ይርዳው ከሀገራችን አልፎ ለአፍሪካና ለሌሎች ሀገራት ጭምር ሞዴል በሆነ ተቋም ውስጥ ሕዝብና መንግስትን ማገልገል መቻል ትልቅ ዕድል ነው ያሉት በጠቅላይ መምሪያው በተዘጋጀ የአቀባበልና የትውውቅ መርሃ-ግብር ላይ ነው።
ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሀገራችን የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ሪፎርም ውስጥ ግንባር ቀደም የሆነ ለውጥና ዕድገት በማስመዝገብ ዘመኑን የዋጀ የፖሊስ አገልግሎት በመስጠት የሀገር ኩራትና መከታ፤ የህዝባችን የክብር መገለጫ እየሆነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ተቋሙ በልዩ ሁኔታ በተግባሩና በአስተሳሰቡ የገዘፈ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀ፣ ሙያዊ ተልዕኮውን በሚገባ ያወቀና የተረዳ፣ ዜጎች በአለኝታነት የሚተማመኑበት ተወዳዳሪ ተቋም መሆኑን አንስተዋል። በተለይም በሰብዓዊ መብት አያያዙ በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር የተመሰከረለት መሆኑንም ተናግረው ውጤቱም የአመራሩና የመላው ሠራዊት ሀገርን የማገልገል ከፍተኛ ቁርጠኝነት ውጤት እንደሆነም ገልፀዋል።
ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዕድገትና ለውጥ ቀጣይነት ያለው በመሆኑ የተመዘገበው ስኬት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤ በዲስፕሊንና በሙያዊ ክህሎቱ የተመሰገነ እና ከሀገር የተሻገረ ዕውቀት ያለው ሠራዊት ለመገንባት ከፍተኛ አመራሩ በበለጠ በጋራና በትብብር ተቀናጅቶ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።
የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የኦፕሬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ ክቡር አቶ ሙሊሳ አብዲሳ በበኩላቸው፤ ባለፉት ሰባት የሪፎርም ዓመታት በተሰራው ጠንካራ ሥራ በወንጀል ምርመራ ላይ ይቀርብ የነበረውን ከፍተኛ ቅሬታ በመቅረፍ ተጠያቂነት ያለው አሠራር መዘርጋቱን ጠቅሰው፤ ሕግን አክብሮ የሚያስከብር ፕሮፌሽናል የፖሊስ አገልግሎት ለመስጠትና የተመዘገበውን ዕድገት ለማስቀጠል ከፍተኛ አመራሩ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የጠቅላይ መምሪያው ተጠሪ ምክትል ዋና መምሪያዎችና መምሪያዎች የስድስት ወር የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።
28/03/2026
በዜጎች ላይ የ1.7 ቢሊዮን ብር ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩት የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ድርጅት መስራችና ባለቤቶች ላይ ምርመራ ተጠናቆ ክስ መመሥረቱን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ
********************************
የፊንቴክ ኢንቨስትመንት የግል ድርጅት መስራችና ባለቤቶች የሆኑት ዳንኤል ዮሃንስ ኢየሱስ እና ግርማይ ገብረሚካኤል ይህደጎ የተባሉ ተጠርጣሪዎች፣ ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን በመጠቀም ከ1,200 በላይ ዜጎችን በማጭበርበር የ1.7 ቢሊዮን ብር ጉዳት በማድረሳቸው ፖሊስ በ19 ዓይነት የተለያዩ ወንጀሎች ምርመራውን አጣርቶ ለዓቃቤ ሕግ በመላክ ክስ እንዲመሰረትባቸው ማድረጉን ገልጿል።
መጀመሪያ ላይ ክሱ የቀረበው ለአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የነበረ ቢሆንም፣ ወንጀሉ ውስብስብ፣ ከፍተኛ ልምድ የሚጠይቅና ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ ምርመራው በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በኩል በሰፊው ሲጣራ ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅት ተጠርጣሪ ዳንኤል ዮሃንስ ክስ ተመስርቶበት በማረሚያ ቤት ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል የተደረገ ሲሆን፣ ሌላኛው ተጠርጣሪ ግርማይ ገብረሚካኤልን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ክትትል እየተደረገ ይገኛል።
ግርማይ ገብረሚካኤል በአውሮፓውያኑ 2010 የደቡብ አፍሪካ ዓለም ዋንጫ ወቅትም "አስካሉካን" በተባለ ድርጅት ስም ዜጎችን በማጭበርበር በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ይዞ ከሀገር ቢሰወርም፣ በወቅቱ በኢንተርፖል አማካኝነት ተይዞ ለሕግ መቅረቡን የወንጀል ሪከርዱ ያመላክታል።
ተጠርጣሪዎቹ ተጎጂዎችን በ90 ቀናት ውስጥ የመኪና ባለቤት እናደርጋችኋለን በማለት የ950 ሺህ ብር (50%) ቅድመ ክፍያ እንዲፈጽሙና ቀሪውን ገንዘብ ያለወለድ በ5 ዓመት በባንክ ብድር እንደሚጨርሱ በማሳመን ነው ወንጀሉን የፈጸሙት።
ሕዝብን ለማሳመን ሲሉ 148 መኪኖችን ከጅቡቲ በማስገባት 100ዎቹን ለተወሰኑ ሰዎች ማከፋፈላቸውንና ቀሪዎቹን 48 ዘመናዊ መኪኖች በድብቅ መሸጣቸውን ፖሊስ አረጋግጧል።
በተጨማሪም 350 መኪኖች ወደ ሀገር መግባታቸውንና 400 መኪኖች ጅቡቲ ወደብ መድረሳቸውን የሚገልጽ የሐሰት መረጃ ለተጎጂዎች ሲሰጡ እንደነበር በምርመራው ተደርሶበታል።
ተጠርጣሪዎቹ የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ከሆነው የቻይናው BYD ካምፓኒ ጋር ምንም ዓይነት ውል ሳይኖራቸው ውል እንዳላቸው በማስመስልና በመስቀል አደባባይ ከተለያዩ ቦታዎች በትውስት ያሰባሰቧቸውን መኪኖች ድርጅቱ ያስገባቸው በማስመሰል የማጭበርበር ወንጀል ሲፈጽሙ ቆይተዋል።
በጅቡቲ "አልፋቲዞ" የተባለ ድርጅት በማቋቋም መኪኖቹን በ10% ቅድመ ክፍያ ተረክበው፣ ቀሪውን 90% ክፍያ ሳይፈጽሙ ጅቡቲ ላይ መልሰው መሸጣቸውም በምርመራው ተረጋግጧል።
ፖሊስ እንዳረጋገጠው ተጠርጣሪዎቹ ከእያንዳንዱ ተጎጂ ለቅድመ ክፍያ፣ ለመንግሥት ታክስና ለቻርጀር ማሰሪያ በሚል በአጠቃላይ 1 ሚሊዮን 365 ሺህ ብር ተቀብለዋል።
የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ድርጅትን ባልተገባና በተጋነነ መልኩ በማስተዋወቅ፣ በሕገወጥ መንገድ ከተሰበሰበው ገንዘብ ተጋሪ በመሆን የተጠረጠሩት አርቲስቶችና የማስታወቂያ ባለሙያዎች ሰለሞን ቦጋለ፣ ሰራዊት ፍቅሬ፣ ዳንኤል ተገኝ፣ አብርሃም ግዛው፣ ይገረም ደጀኔ፣ መንሱር ጀማል እና ካሊድ ናስር በቁጥጥር ሥር ውለው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ፍርድ ቤቱም በእነዚህ ግለሰቦች ላይ እስከ መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል። እነዚህ ግለሰቦች ዕውቅናቸውን በመጠቀም የሐሰት መረጃዎችን በማሰራጨትና እያንዳንዳቸው 8 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የ"BYD Song Plus" መኪና በስጦታ በመቀበል ወንጀሉን በማሳለጥ ተጠርጥረዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በማጭበርበር፣ በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ (Money laundering) እና በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ የጀመረውን ምርመራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ይህ ውስብስብ ወንጀል ተጣርቶ ክስ እንዲመሰረት ከፖሊስ ጋር በትብብር ለሠራው የፍትሕ ሚኒስቴር እና መረጃ ሲሰጥ ለነበረው ማኅበረሰብ ፖሊስ ላቅ ያለ ምስጋና ማቅረቡን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኢቢሲ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
24/03/2026
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሆነው አዲስ የተሾሙት ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል እርስቱ ይርዳው ከተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ጋር የስራ ትውውቅ መድረክ አካሄዱ።
******************
መጋቢት 15 ቀን 2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሆነው አዲስ የተሾሙት ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል እርስቱ ይርዳው ከተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በዛሬው እለት የስራ ትውውቅ መድረክ አካሂደዋል።
ወደ ኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ እንኳን ደህና መጡ በማለት አቀባበል ያደረጉት በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የኦፕሬሽን ዋና መምሪያ ሀላፊ ክቡር አቶ ሙሊሳ አብዲሳ ሲሆኑ በእለቱም በጠቅላይ መምሪያው በዲጂታላይዜሽን፣ በሰብአዊ መብት አያያዝና በምርመራ ጥራት ዙሪያ የተሰሩ የሪፎርም ስራዎችን በአካል ተዘዋውረው በማስጎብኘት በቀጣይ ሊሰሩ የታሰቡ ስራዎችን ገለፃ አድርገውላቸዋል፡፡
ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉም ከተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በተደረገላቸው አቀባበል እና የስራ ትውውቅ አመስግነው ቀጣይ በተቋሙ በሚሰሩ ስራዎች ዙሪያ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣትና ተግባሩን በውጤት አጅቦ መምራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
19/03/2026
ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ
እንኳን ለ1447ኛው ዒድ አል-ፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ!!!
ዒድ ሙባረክ
18/03/2026
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ልዑካን በአውሮፓ የፖሊስ ተቋም (ዩሮፖል) የሥራ ጉብኝት አደረገ
*********
መጋቢት 9 ቀን 2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምርያ ኃላፊ ተወካይ በክቡር አቶ ሙሊሳ አብዲሳ የተመራ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖች ልዑክ በኔዘርላንድስ ሄግ በሚገኘው የአውሮፓ የሕግ አስከባሪ ኤጀንሲ The European Union Agency for Law Enforcement Cooperation (Europol) ዋና መሥሪያ ቤት በመገኘት ውጤታማ የሥራ ጉብኝት አድርጓል።
የዩሮፖል (Europol) ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የልዑካን ቡድንን በዋና መሥሪያ ቤት ተቀብሎ ካነጋገሩ በኋላ ዩሮፖል በመረጃ አሰባሰብ እና ትንታኔ የደረሰበትን አቅም፣ በተለይም በከባድ እና በተደራጀ የወንጀል ስጋት ትንተና (SOCTA) ላይ ትኩረት ያደረገ ገለፃ እንዲሁም በተልዕኳቸው እና በተግባራቸው ዙርያ ማብራሪያ በመስጠት ልምዳቸውን አካፍለዋል።
የአውሮፓ የስደተኞች መከላከል ማዕከል (EMSC) እያከናወነ ያለውን ተግባር እና በሰዎች የመነገድ እና በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር በሚያሻግሩ ወንጀለኞች ላይ የሚካሄደው ምርመራን አስመልክቶች ለልዑኳን ቡድኑ ገለፃ የተደረገላቸው ሲሆን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ልዑኳን ቡድን በበኩሉ የወንጀል ምርመራ ሥራ እና በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አሁን ላይ የደረሰበትን የመፈፀም አቅምና በተቋሙ እየተከናወኑ ያሉ የለውጥ ስራዎችን ለዩሮፖል ኃላፊዎች በቂ መረጃ ሰጥተዋል::
ዩሮፖል ኃላፊዎችም ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር ያለዉን ፖሊስ ለፖሊስ ግንኙነት የበለጠ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ለልዑኳን ቡድኑ ገልጸዋል::
12/03/2026
“ፋይዳ መታወቂያ በተለያዩ ማንነቶች የሚፈጠሩ ማጭበርበሮችን የሚከላከል እና የሰነድ ትክክለኛነትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ በመሆኑ ለፀጥታና ደኅንነት መረጋገጥ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው” ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል
********************
መጋቢት 3፣ 2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አዛዥ ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ፋይዳ መታወቂያ በሁሉም ዜጎች እጅ ሲዳረስ በተለያዩ ማንነቶች የሚፈጠሩ ማጭበርበሮችን የሚከላከል እና የሰነድ ትክክለኛነትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ በመሆኑ ለፀጥታና ደኅንነት መረጋገጥ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ያሉት የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሸነር ጀነራሎች፣ የክልሎችና የከተማ አስተዳድር የፖሊስ ኮሚሽነሮች እንዲሁም የፖሊስ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በተገኙበት የፋይዳ መታወቂያን በተመለከተ እየተሰጠ ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ ነው፡፡
ክቡር ከሚሽነር ጀነራል አክለውም ኢትዮጵያ የፋይዳ መታወቂያን ወደ ሥራ ማስገባቷ የሰላም እና ፀጥታ ተግባራትን በማዘመን ረገድ ሰፊ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው የዲጅታል መታወቂያን ሁለንተናዊ ጥቅም በመገንዘብ የፖሊስ አባላት የፋይዳ መታወቂያ ተደራሽ እንዲሆን መስራት አለባቸው ብለዋል።
ብሔራዊ መታወቂያ ከተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ራሳቸውን ጠብቀው ለሚኖሩ ዜጎች ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በቅርቡ በሀገራችን እንዲሁም በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የስማርት ፖሊስ ስቴሽንን ስናስመርቅ የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች በጎበኙበት ወቅት ከብሔራዊ ፋይዳ መታወቂያ ጋር የተገናኘ መሆኑን ተመልክተው ኢትዮጵያ በዲጂታለ ቴክኖሎጂው ዘርፍ እያመጣች ያለችውን ለውጥ ማድነቃቸውን ገልጸዋል፡፡
የሀገራችን የፖሊስ ኃይል በማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት እስከ ቀበሌዎችና ወረዳዎች የሚደርስ በመሆኑ ሕብረተሰቡ የፋይዳ መታወቂያ ተጠቃሚ እንዲሆን ሁሉም ፖሊስ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከፀጥታና ደኅንነት አንጻር የፋይዳ መታወቂያ የፊት ገፅታ መልክን የሚያካቲት በመሆኑ የወንጀል ተጠርጣሪን ማንነት በቀላሉ ማወቅ የሚቻልበትን እድል ይፈጥራልም ብለዋል፡፡
ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል አሁን ላይ ከብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት ጋር በመሥራታችን በወንጀል መከላከል፣ በወንጀል ምርመራ እንዲሁም በትራፊክ ቁጥጥር ሥራችን ከፍተኛ ለውጥ እየመጣ ነውም ብለዋል፡፡
ፖሊስ ኦፊሰር የግለሰብ ፋይዳ መታወቂያን ሲጠይቅ ሞባይል ስልኩ ላይ ባለው የዜጎች መተግበሪያ (EFPApp) የግለሰቡን ፋይዳ መታወቂያ ተቀብሎ ባርኮዱን ፎቶ በማንሳት ትክክለኛ መሆን አለመሆኑን መለየት ያስችለዋል ብለዋል፡፡
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር ዮዳሄ አርዓያሥላሴ በበኩላቸው ከዲጅታል ኢትዮጵያ መሠረቶች አንዱ የሆነው የዲጂታል መታወቂያ ከሀገር ፀጥታና ደኅንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን ገልፀው አንድ ግለሰብ በልዩ ሁኔታ ክልል እና ከተማን ቢቀይር ማንነቱን ሊቀይር ስለማይችል በፋይዳ መታወቂያ አማካኝነት የፖሊስ ኦፊሰሩ የግለሰቡን ማንነት ማረጋገጥ የሚችልበትን ሥርዓት ይፈጥርለታል ብለዋል፡፡
የፖሊስ ሥራ ከአሻራ እና ከባዮሜትሪክስ ጋር የተገናኘ በመሆኑ የፋይዳ መታወቂያም የፊት እና የጣት አሻራን ወስዶ ወጥ የሆነ አንድ ማንነትን የሚያሳይ በመሆኑ ከተለያዩ ማንነቶች ተሰባጥሮ የተፈጠሩ የሐሰት ማንነትን መከላከል እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡
10/03/2026
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ አቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ቸርነት ሆርዶፋ የተመራ የልኡክ ቡድን በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የስራ ጉብኝትና በጋራ በሚሰራባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አደረጉ፡፡
************************************************
መጋቢት 01 ቀን 2018 ዓ.ም
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ አቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ቸርነት ሆርዶፋ የተመራ የልኡካን ቡድን በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የስራ ጉብኝትና ውይይት አደረጉ፡፡
በእለቱም የጠቅላይ አቃቤ ህግ ዘርፍ ስር ያሉ ሁሉም የአቃቤያን ህግ ዳይሬክቶሬት ጀነራሎች እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ተወካይ ክቡር አቶ ሙሊሳ አብዲሳ ለልኡካን ቡድኑ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በመቀጠልም ከ2015 ዓ.ም - 2018 ዓ.ም ግማሽ ዓመት ድረስ በሁለቱ ተቋማት በጋራ የተሰሩ ስራዎች ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡
በውይይቱም በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚጠቀማቸውን ቴክኖሎጂዎችን፣ የተጠርጣሪ አያያዝን እና የምርመራ ጥራት በጋራ እየተሰሩ ያሉ ውጤታማ የምርመራ ስራዎች መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን እንዲሁም በስራ ሂደት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ውጤታማ ውይይቶች አድርገዋል፡፡
ከሁለቱም ተቋማት የተነሱትን ሀሳቦችን ለመስራትና የተሻሉ የክስና የምርመራ ሂደቶችን ለማከናወን አሁን ያለውን የፍትህ ስርዓት ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስና በቀጣይም የሚመጡ ክሶችን ተቀብሎ መመርመር ብቻ ሳይሆን ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት የጋራ የኦፕሬሽን ስራዎችን በማከናወን በወንጀል ተሳታፊ የሆኑ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ በመክሰስና በመመርመር መንግስትና ህዝብ ከተቋማቶቹ የሚጠብቃቸውን ተልዕኮ በተገቢው በመወጣት ሁለቱም ተቋማት የጋራ መግባባት ላይ የደረሱ ሲሆን በሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችንም የጋራ ኦፕሬሽን ቡድን በማቋቋም በፍጥነት ለመፍታትና ቀጣይ ተደራሽ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸው ተገልጿል፡፡
በመጨረሻም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ አቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ቸርነት ሆርዶፋ በተነሱ ጉዳዮች ላይ አስተያየትና ማጠቃለያ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡
28/02/2026
"ግዙፍ የምርመራ አንስቲትዩቶችን በመገንባት ለነገ ትውልድ የሚሻገር ታሪካዊ የተቋም ግንባታ ሥራ እየተሰራ ነው" ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል
*****************************
የካቲት 20 ቀን 2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ከለውጡ በፊት ኋላ ቀር የነበረውን የታክቲክና ቴክኒክ የምርመራ ሥራ ዛሬ ላይ ከሀገራችን አልፎ ለሌሎች ሀገራት የሚተርፍ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳደሪና ጥቂት ሀገሮች ብቻ ያላቸውን ዘመናዊ ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም እና ግዙፍ የምርመራ አንስቲትዩቶችን በመገንባት ለነገ ትውልድ የሚሻገር ታሪካዊ የተቋም ግንባታ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አመራርና ባለሙያዎች የሥራ ግምገማ ላይ ነው።
ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል ከለውጡ በፊት በሰዎች ላይ በሚያደርሰው የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በህዝብ ዘንድ አመኔታ ያልነበረው፣ የሚጠላ፣ የሚፈራና በሚደርስበት ጣልቃ ገብነት ምክንያትም ገለልተኛ ሆኖ መስራት ባለመቻሉ የፍትህ ሥርዓት ተዛብቶ ዜጎች በሀገራቸው እኩል ፍትህ ለማግኘት የተቸገሩበት የሰቆቃ ጊዚያቶች ማሳለፉቸውን አስታውሰዋል።
መንግስት በሪፎርሙ የፀጥታ ተቋማትን ግምባር ቀደም የለውጡ አካል በማድረግ በተለይም ሕዝባችን በፍትህ ተቋማት ላይ ሲያነሳቸው ለነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ በተሠራው የለውጥ ሥራ አሁን ላይ የኢትየጵያ ፌደራል ፖሊስ የዜጎችን መብት ለማስከበር ፕሮፌሽናል የሆነ ዘመናዊ የምርመራ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀም፤ በሙያ ብቃታቸው የተመሰከረላቸው እና ማንኛውንም ምርመራ በብቃት የሚያከናውኑ የምርመራ ፖሊስ ኦፊሰሮችን ያፈራ በመሆኑ ከሀገራችን አልፎም ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር ሞዴል የሆነ ተቋም እየተገነባ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በተክኖሎጅና በሰው ኃይል ግንባታ የታየው ከፍተኛ ዕድገት የበለጠ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የተናገሩት ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል የወንጀል ምርመራ ሥራ ሕግና ሥርዓት የሚከበርበት፣ ፍትሕ የሚሰፍንበት በመሆኑ የምርመራ ፖሊስ ኦፈሰሮቻችን ሀገራቸውን ለማገልገል የገቡትን ቃል-ኪዳን አክብረው በሙያዊ ብቃት (Professionalism)፣ የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም በማስቀደም፣ ከሙስናና ብልሹ አሠራር በፀዳ አኳሃን የበለጠ ሕዝብን በዕኩልነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።
27/02/2026
"የፖሊስ አባላትን የመፈፀም አቅም በትምህርትና ስልጠና በማሳደግ የሰብዓዊ መብትን አክብሮ የምርመራ ስራውን በከፍተኛ ብቃት የሚያከናውንና ከዘመኑ ጋር የሚጓዝ ፕሮፌሽናል የሆነ የፖሊስ ኃይል ተፈጥሯል" ክቡር አቶ ሙሊሳ አብዲሳ::
***************
የካቲት 20 ቀን 2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ተወካይ ክቡር አቶ ሙሊሳ አብዲሳ የፖሊስ አባላትን የመፈፀም አቅም በትምህርትና ስልጠና በማሳደግ የሰብዓዊ መብትን አክብሮ የምርመራ ስራውን በከፍተኛ ብቃት የሚያከናውንና ከዘመኑ ጋር የሚጓዝ ፕሮፌሽናል የሆነ የፖሊስ ኃይል ተፈጥሯል ያሉት የኢንተለጀንስ ባለሙያዎች ስልጠና የማጠቃለያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የስራ መመሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።
ክቡር አቶ ሙሊሳ አብዲሳ የኢንተለጀንስ ሙያ በፖሊስ የምርመራ ሥራ ላይ ቁልፍ ሚና ያለው፣ ፖሊስ እና ህዝብን የሚያገናኝ ድልድይ መሆኑን ጠቅሰው ይህን ከባድ ኃላፊነት በቁርጠኝነት ለመወጣት የሚያስችሉ የተለያዩ ትምህርትና ስልጠናዎችን ለኢንተለጀንስ ባለሙያዎቻችን በመስጠት በስምሪታችን የተሳካ፤ ፕሮፌሽናል እስታንዳርዱን የጠበቀና ውጤታማ የሆነ የሕግ የማስከበር ሥራ ማከናወን ተችሏል ብለዋል።
የኦፕሬሽን ክፍሉ ዓለም አቀፍ ተሞክሮና ልምዶችን በመቅሰም፤ የተናበበ የግንኙነትና የመረጃ ልውውጥ አቅም በማዳበርና ፕሮፌሽናል የምርመራ ስልቶችን በመጠቀም ህዝብን በከፍተኛ ዲስፕሊን፣ በእኩልነት፣ በታማኝነትና በቅንነት በማገልገል አኩሪ ተግባር እየፈፀመ መሆኑን የተናገሩት ክቡር አቶ ሙሊሳ አብዲሳ ከዚህም በላይ የምንመኘውን ውጤት ለማስመዝገብ በቀጣይ ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
በመጨረሻም የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በሀገራችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያስከትሉ ልዩ ልዩና ከባድ ወንጀሎችን የሚመረምር በመሆኑ በሙያችሁ ብቁ በመሆን፣ ሕገ-መንግስቱን ማዕከል በማድረግ፣ በዕውቀት፣ በክህሎት በተሟላ ፖሊሳዊ ሥነ-ምግባር በመመራት ራሳችሁን ከሌብነት፣ ከሙስና እና ከብልሹ አሠራር በማፅዳት የሀገራችንና የተቋማችንን ክብር ከፍ የሚያደርግ ሥራ እንድታከናውኑ በማለት አሳስበዋል።
19/02/2026
በሐሰተኛ የባንክ ዋስትና ሰነድ በገዳ ባንክ፣ በኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በሌሎች ድርጅቶች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል በመፈፀም ከ89 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሶ በሕግ ሲፈለግ የነበረውን ተጠርጣሪ ከነግብረ-አበሮቹ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ
****************************************
የካቲት 12 ቀን 2018 ዓ.ም
በሐሰተኛ የባንክ ዋስትና ሰነድ እና በሌሎች ሐሰተኛ ሰነዶች በመጠቀም ህገወጥ የጥቅም ትስስር በመፍጠር የባንክ አሰራርና ሕግን ባልተከተለ መልኩ በገዳ ባንክ፣ በኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በሌሎች ድርጅቶች ላይ ከባድ የሙሰና ወንጀል በመፈፀም ከ89 ሚሊዮን 296 ሺህ ብር በላይ ጉዳት አድርሶ በሕግ ሲፈለግ የነበረውን ተጠርጣሪ ከነግብረ-አበሮቹ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተጠርጣሪዎቹ ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀምና ሐሰተኛ የባንክ የዋስትና ሰነዶችን በማዘጋጀት የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙ ሲሆን በተለይም የጎደር ዋይን ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ ዋነኛው ተጠርጣሪ ጌታሁን መለስ ልይህ ከገዳ ባንክ አገምሳ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አብዲሳ ቶሎሳ ደበሊ ጋር በጥቅም በመመሳጠር፤ የቅርንጫፉን የሥራ ኃላፊ ፊርማና ማኅተም በመጠቀም ለወንጀል ድርጊታቸው ማስፈጸሚያነት ሲገለገሉ መቆየታቸውን ፖሊስ በምርመራው አረጋግጧል።
ተጠርጣሪዎቹ በዚህ የተቀነባበረ የወንጀል ድርጊት ለወደራ ሁለገብ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን የውል ማስከበሪያና የቅድመ ክፍያ ዋስትና በማስመሰል 23 ሚሊዮን 296 ሺህ ብር እንዲሁም ለፈናን መሃመድ በሽር የቀለም ማምረቻ ድርጅት የ20 ሚሊዮን ብር የሐሰት የዱቤ ሽያጭ ዋስትና ሰነድ በማቅረብ፣ በድምሩ 43 ሚሊየን 296 ሺህ ብር የገንዘብ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ያመላክታል።
አበባው መኮንን አረጉ የተባለ ሌላኛው ተጠርጣሪ ከጌታሁን መለስ ልይህ እና ከአብዲሳ ቶሎሳ ደበሊ የተባሉት ተጠርጣሪዎች ከባድ የሙስና ወንጀሉን እንዲፈጽሙ ሁኔታዎችን ያመቻቸ፤ ያግባባና ያገናኘ ሲሆን ጌታሁን መለስ ልይህ በቁጥጥር ስር እስከዋለበት ቀን ድረስ በበላይነት ወንጀሉ እንዲፈፀም ትልቅ ተሳትፎና ከፍተኛ የጥቅም ትስስር የነበረው መሆኑን ፖሊስ በምርመራው አረጋግጧል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጌታሁን መለሰ የተባለው ተጠርጣሪ ከዚህ በፊትም በሐሰተኛ የባንክ ዋስትና ሰነድ በኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ላይ 28 ሚሊየን ብር ጉዳት በማድረስ በፖሊስ ሲፈለግ እንደነበር ተገልጿል። በተጨማሪም ተጠርጣሪው የፍርድ ቤት እግድ የነበረበት ቤቱን በሐሰተኛ ሰነድ እግዱን አስነስቶ ለሦስተኛ ወገን አስተላልፎ 18 ሚሊየን ብር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ጉዳት በማድረስ ክስ ተመስርቶበት እየተፈለገ እንደነበርም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በቀጣይም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ሥር የማዋልና ለሕግ የማቅረብ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጾ ሕብረተሰቡም መሰል ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ሲመለከት በ'EFPApp' ወይም በነፃ የስልክ መስመር 991 ጥቆማ በመስጠት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።