ጉርብትና
።።።።።።።
እሽ ሥንታየሁ እንዴት ዋልክ ቡና ትጠጣለህ? አለችኝ...
አይ አልጠጣም አልኩ። እሷም ይሄን እንድል እና እንዲህ ብላ ከጠየቀችኝም እንዲህ እንደምል ስለምታውቅ ነው ና ቡና ጠጣ ከማለት ይልቅ ትጠጣለህ? ብላ የጠየቀችኝ። ምቀኛ።
እኔ ምለው ምን አረኳት ቆይ ...ባለፈው ለኮሮና በሽታ መድሃኒት ፈውስ ይሆን ዘንድ ዝንጅብል ፌጦ ማር እና ነጭ ሽንኩርት ቀላቅላችሁ ተጠቀሙ ተብሎ ከገዳም አባቶች ታዟል የተባለ ግዜ ምድረ ተከራይን እያንኳኳች በለሊት ቀስቅሳ መዳኒት ተብዬውን በማንኪያ ስታስልስ እኔ መብራት አብርቼ ሳልተኛ ቤት ውስጥ እያለሁ እያወቀች ሳታንኳኳ አለፈችኝ...የተባለውን መድሃኒት በእጦት ምክንያት ሳልወስድ ሞቼ ቢሆን ለሞቴ የተባበረችን እሷ ነበረች። ኪራይ ቀጥታች አላውቅ ለምን እንደደበርኳት እንጃ።
ዛሬ ደግሞ ሁሉንም ኑ ቡና ጠጡ እያለች ደጇ ደግሳ ጠርታ ስታበቃ ለኔ ሲሆን ቡና ትጠጣለህ እንዴ? ማለት ምን ማለት ነው ጎበዝ?
።..
ይቺን ንዴቴን ቤቴ ውስጥ ሆኜ እያብሰለሰልኩ ሳለ ድንገት ጮክ ብለው ደጅ ላይ የተጠሩት ሁሉ በአንድ ላይ ሲስቁ ከማብሰልሰሌ ባነንኩ...እነዚህ ሰዎች በአንድ ላይ ለምን ሳቁ? እኔን ለማናደድ ተልዕኮ አላቸውን? ይሄን ያህል በአንዴ የሚያስቅ ኮሜዲያን እዚህ ግቢ ውስጥስ አለን? ይሄን ያህል በአንዴ የሚያስቅስ ጉዳይ በተለይም በዚህ ሰአት በሃገራችንስ ከየት ተገኘ? የሰው ልጅ እንዲህ በአንዴ ተግባብቶ ይስቅ ዘንድ ሳይንሱስ አግባብ ነው ይላልን? በጣም መሳቅስ ኮሮናን አያስተላልፍም ወይ? እያልኩ በንዴት ጥያቄ አሽጎደጉድ ጀመር።
በድንገት ደሞ እናቴ ትዝ አለችኝ....አቤት የኛ ቤት ንፍሮ እኮ ብይ ብይ ነው እኮ የሚያክለው አልኩ እነሱ ሃሳቤን እየሰሙ ይናደዱልኝ ይመስል። እንደናንተ በመርፌ ቀዳዳ የሚሾልክ የላመ ንፍሮ መሰላችሁ እንዴ የኛ ቤት አልኩ በውስጤ...ደግሞ ንፍሮ ብቻ አይደለም እኛ ቤት አልኩ...በጉ ፣ ጠላው ፣ አረቄው ፣ ድፎው ፣ ብርዙ ምንትሱ አልኩኝ በሃሳቤ በቤቴ ውስጥ ለብቻዬ ቁጭ ብዬ። እነዚህ የሆነች ብናኝ ንፍሮ እና ቡና ነው ያዙ ያዙ ሲባባሉ ያየሁትም የሰማሁት።
ለነገሩ በግ አለያም ዶሮ ባያርዱም ከሚያመሰኩት ኩጫጭ ንፍሮ ጋር አብረው የለቀቀች የዱሮ ተከራይ ሴት እያሙ ስለነበር ያው ድግሱን የፍስግ አድርገውታል። እሷ ደሞ መንቃራ አይደለች እንዴ እያሉ ያሽካካሉ። ቤተክርስቲያን የሚባል ነገር አትወድም እኮ አንች ትላለች ሌላኛዋ ደግሞ....(በሷ ቤት አሁን የሷን ሃሜት እግዚአብሔር የሚወደው ነው የመሰላት) ..ደሞ የምታመጣቸው ወንዶችስ ብዛት ብትይ ብላ ሌላዋ ደሞ ከት ብላ ሳቀች...እሱንማ ተይው ድፍረቷ መቼም አይን አውጣ ነበረች ፡ እኔ ስንት ሰው አከራይቻለሁ እንደ እሷ ጋጠ ወጥ ገጥሞኝ አያውቅም አለች አከራይዋ።
እየውልሽ አንዴ አምሽታ ጥግብ ብላ ሰክራልሽ ከአንዱ ወንድ ጋር እየተወለጋገደች መጣችና በሩን ለሁለት ይቀጠቅጣሉ...አንች ከለሊቱ 6፡30 ሆኗል እኮ እንዴት እንደደነገጥኩ...በዛ ላይ ኧረ መጣሁ ብዬ ተነስቼ እስክከፍት ድረስ ፋታ ሊሰጡኝ መሰለሽ ለሁለት በሩን ሊሰብሩት በቃ.. ምድረ ተከራይ አልቀረ ጎረቤት አልቀረ የምን ጉድ ነው ብለው በየቤቱ ወጥተው ብታይ (ይች ሴትዮ ስታወራ ግነቷ አይጣል) ኧረ ማን ነው ቀስ ብዬ በሩን ክፍት ሳደርግ ተቃቅፈው በር ላይ ቆመዋል...ንድድ ብሎኝ አንች ያምሻል እንዴ ግን ጤነኛ አይደለሽም? በለሊት ሰው ከተኛ በኋላ መምጣትሽ ሳያንስ ደግሞ በስነስርአት አታንኳኩም እንዴ እላታለሁ ፡ ያ ሰካራም ለፍዳዳ ወንዷ ውልግድግድ ባለ አንደበቱ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው?....ም....ምን ታ...ታመጫለሽ ቆይ....ክ....ክፈቺ ተ...ባልሽ አይደል....ዝም ...ብለሽ መክፈት ነው....አሁን...ዞር በይ አትጩሂብን....ቤተ-መን...ግስት ያከራየሻት መ...መሰለሽ እንዴ? አይለኝም። ከዛ ተከራዮቹ በሙሉ ይሄን ሁሉ ነገር በለሊት ተነስተው አይተው ስለነበር ..ልብ አርጉልኝ ይሄን ሁሉ ብልግና ብዬ ምስክር አድርጌ ነገውኑ ቤት ፈልገሽ እንድትወጭ ማነሽ ስላት....ያ ሰካራም ሰውዬ በድጋሜ ተለፋደደብኝ.....
ስሚ ሃ...ሃበሻ እኮ ማለት....ግር ብሎ በተ..ጠራበት የሚገኝ ከ...ከንቱ መንጋ ነው...እነዚህም ምስኪን....የማይዝናኑ ተከራዮችሽ ግርርር ብለው ቢ..መ...ሰክሩልሽ አይገርምም....ግን ነገ አይደለም እስከወዲያኛው ትወጣልሻለች...ለዚህ ትኋናም የወፍ ጎጆሽ....ደና ቤት እንዳ..ላት ውጭልኝ ትላለች እንዴ ማፈሪያ ብሎ አላቀለለኝም መሰለሽ እያለች ውርደቷን ለምድረ ተከራይ ታወራለች።
እኔ ይሄን ሁሉ ዲስኩር ቤቴ ውስጥ ሆኜ እየሰማሁ ፈገግ እላለሁ።
ይሄን ሁሉ ሃሜት ስሰማ ቡና ትጠጣለህ እንዴ ሥንታየሁ? ስትለኝ አይ አልጠጣም ማለቴን ወደድኩት።
ለመሆኑ የኛ ሃገር ህዝብ መች ነው ሃይማኖታዊ በዓልን አውዱን ጠብቀን አክብረን የምናሳልፈው። ልብ በሉ እስቲ ለገና በዓል ቀን በሬዲዮ እና በቴሌቭዥን ካልደሰኮሩልን በቀር በስህተት ስለጌታችን ልደት ሃሳብ ተነስቶ ለ5 ደቂቃ እንኳ አይወራም በቃ ተሰብስቦ መብላት መጠጣት ከርስ መሙላት ብቻ ነው። ለፋሲካ ዕለትም እንዲሁ ኧረ እዚጋ ዱለት አንሷል አንቺ..
ምንድን ነው ቁርጥ ጨምሩላቸው እንጂ ለልጆቹ....ጠላውስ የት ሄደ ስንል እንጅ የምንውለው የጌታን ትንሳኤ ማን ልብ ብሎት።
ዛሬም የወላዲተ አምላክ የቅድስት ብፅዕት ድንግል ማርያም ልደቷ ሳለ...ቢያንስ ለምን ተሰብስበን ደጅ ላይ ንፍሮ ቀቅለን እንደምናከብር እንኳን ሃሳብ አንስቶ እንወያይ ያለ የለም ...እ ቡና ደረሳችሁ? እህ ዝገኝ እንጂ ከንፍሮው ሲባባሉ ብቻ ነው የሰማሁት። በዓላቶቻችን በሙሉ የከርስ መሙያ ...መስከሪያ እና መለፋደጃ ሆነዋል። በተለይም ኃይማኖታዊ በዓላትን ስናከብር በቅጡ መብላት መጠጣቱ እንዳለ ሆኖ ስለ በዓሉ ምንነትና ምክንያት እውቀት እና ሃሳብ እየተወያየን ቢሆን ትውፊቱን በቀጣይ ትውልድ ውስጥም ጠብቆ ለማዝለቅ ያግዛል ባይ ነኝ።
አይ ዘንድሮ አምና እኮ ብታይ በሬ የሚያህል ሙክት አርደን ደጅ ላይ ሰፈራችንን ቀውጢ አርገነው ነበር እድሜ ለኮሮና ዘንድሮ በየግቢያችን ለየብቻ ሰበሰበን....ብላ አከራይዋ ያቆመችውን ወሬ ስትቀጥል...በሉ ደህና እደሩ እኔ ልሂድ እግዜር ይስጥልኝ ብላ አንዷ ተከራይ ወደ ቤቷ ገባች። ከመቅጽበት ቤት ከመግባቷ አከታትላ ታስነጥስ ጀመር...እህህህ ብላ ጉሮሮዋንም ትጠራርግ ጀመር...አሃ ወዳ አይደለም ለካ ቶሎ ብላ ወሬ አቋርጣ ደና እደሩ ብላ የወጣችሁ አልኩ በውስጤ....
ይሄኔ ታድያ አከራይዋ ማነሽ አመለ....አመለ ብላ ተጣራች....
አቤት እትዬ ጸጋ....
ምነው ሰላም አይደለም?
እየሰማሽኝ አይደል እንዴ እያጣደፈኝ ምን ትጠይቂኛለሽ...
ዋ አመለ ከማንም ጋር ስራ ቦታ ስትጋፊ እየዋልሽ ብቻ.....አሃሃሃሃ ብላ ሳቀች።
ከዛ በኋላ የደጁ ጨዋታ ቀዘቀዘ...ይሄ ቅዝቃዜውም ምኑም ዝናቡም ሳል ያመጣል እኮ እየተባባሉ እነሱም በየቤታቸው ገብተው ዘና ብለው ሊስሉና ሊያስነጥሱ ነው መሰል የተጠራው ሰው ሁሉ ወደየቤቱ ክትት አለ.....እድሜ ለኮሮና ስንት ሃሜትና ጨዋታ ቀዘቀዘ።
Wegna chewata wekumneger
In this page we gone see some funny,wise thoughts around our societies and some critics in it.
የእኔ መልዕክት ወደ ፌስቡክ ሰዎች
ምዕራፍ 2
……………
ከባለፈው ምዕራፍ የቀጠለ….
1. በአለም ላይ ሶስት ነገሮች ካሉህ በቂ ነው እነርሱም ፍቅር ፣ ገንዘብ እና እውቀት ናቸው፡፡ አየህ እውቀት ቢኖርህ ገንዘብ ከሌለህ መተግበር አትችል ይሆናል ፣ ገንዘብ ኖሮህ እውቀቱ ከሌለህ ደግሞ የባሰ ከንቱ ነህ እውቀት ፍለጋ ልትባዝን ነው ማለት ነው (ለዛም ነው እኮ የተማረ እምትቀጥረው) ፣ ገንዘብና እውቀቱ ኖሮህ ፍቀር ከሌለህ ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነህ ፣ ፍቅር ገንዘብ ኖሮህ ብቻ አይደለም ሳይኖርህም ሊኖርህ ግድ ነው ፣ የሰውን ልጅ በሙሉ ዘር ፣ ቀለም፣ ሀይማኖትና ፆታ ሳትለይ ማፍቀር አለብህ፡ ያኔ ያለህን እውቀት በገንዘብህ ታግዘህ ለምታፈቅረው የሰው ልጅ በተግባር አንዳች ስራን መስራት ትችላለህ
2. በጎ ህሊና ይኑርህ ፡ ስለነገሮች ያለህ አስተሳሰብ ፡ ሀሳብህን እምትፀንስበት መንገድ በበገ ስፍሪያ ላይ ያዘነበለ ይሁን ፡ ያኔ ክፉውን ነገር እንኳ ወደ በጎነት መቀየር አይሳንህም ፣ በዚህ አለም ላይ ለራስህ ከሚሰማህ ስሜት ውጭ ፣ እራስህ ከምትፈጥረው ሀሳብ በላይ ላንተ ተፅእኖ ፈጣሪ ሰው በፍፁም አይኖርም ፣ አነስታይንን የምታደንቀው ሂትለርን የምትጠላው እኮ እኔ በነገርኩህ መንገድ ብቻ ሳይሆን አንተ ጠቅልለህ በተረዳሃው መጠን ነው፡፡ በጎ መሆን እራስህን እንዳያምህ ይረዳሀል ስንቶች እራሳቸው በፈጠሩት ክፋትና ፍራት ይሰቃያሉና
3. መንጋውን መሆን ስለማትችል መንጋውን አትከተል ፡ ልብ አድርግ አንተ እኮ አንድ ነጠላ ግለሰብ ነህ እንጅ ፡ አንተ ማህበረሰብ ወይንም ህዝብ ልትሆን አትችልም ፡ እንዳንተ አይነት ሰው ተጠራቅ ህብረተሰብ ሊፈጥር ይችላል እንጅ ምንግዜም አንድ ሰው አንድ ነው፡፡ የአንተን የአንድን ሰው ህይወት መኖር ስትጀምር ስለሌላውም ማሰብህ አይቀርም ፣ የአንተን የአንድን ሰው መብት ስታስከብር ስለሌላው መብት ማሰብህ አይቀርም ስለዚህ መጀመሪያ እራስህን መሆን አስቀድም እራሳቸውን ያልሆኑ ለማንም አይጠቅሙምና
4. መስጠትን ውደድ ያለህ ብዙ ነገር ነውና ይዘኸው አፈር ከመቀላቀልህ በፊት ለሚገባውም ለማይገባውም ቢሆን ስጥ፡ በሰጠህ ቁጥር ማሰቢያህ የበለጠ ስራውን ይሰራ ዘንድ ክፍተትንም ያገኛል ፡ በተከፈተውም ቦታ ያላሰብከውን ፀጋ ሊሞላብህ ይችላልና ፡ ስትሰጥ ምስጋናንም ሆነ ሙገሳበን ብሎም ብድርን አንዲመልሱልህ አትሻ ፡ በመስጠትህ ውስጥህ ብቻ ደስ ሊላት ይገባል፡ መስጠትን ደስ ስለሚልህ ብቻ አድርግ እንጂ ከቶውንም ብድር አትጠብቅ
an art something a way to express internal privillages
የሶስቱ ምናብ ወግ
………..በስንታየሁ (ካሌብ) አለማየሁ
በቀን ውሎየና በኑሮየ አግድመት
አለ አይደል አንዳንዴ ምናብ ይታየኛል….
ምን አይነት አትሉም?
ምናብ ‹‹አንድ››…..
ወድቀው በተጣሉ ሰው በናቃቸው ውስጥ
ንፁህ ታላቅ እውነት ….ሲያድግ ይታየኛል
………
ያቀረረች ሴት..አንገት መግቢያ ያጣች
ቀና ብላ ስትሄድ ፀሀይ ሲወጣላት
እልፍ ሰው በገድሏ ሲንበረከክላት
ይታየኛል ምናብ…የመጎስቆል ታምር
የመናቅ ትሩፋት የመረሳት ሚስጥር
….
አምስት አስር ሳንቲም….ስለማምላክ ብለው
ስለለማመኑ ሰው ፊት ስለ ቆሙ
የሰውነትን ስም በቁም የተቀሙ
ሰው የመባል ሀረግ የስም ደሀ የሆኑ
ከሰው በላይ ሆነው የሰውን ምንነት
እየሸነሸኑ እየተነተኑ …ሲነግሩ ይታየኛል
ሰባራው ቅስማቸው ከላያቸው ገፎ
በቁም ስጋቸው ላይ ሰውነት ተነጥፎ
ተራ በተባሉ በተራ ሰብ ምናብ
ሀገር ሲጠጋገን ሲድን ይታየኛል
……
ምናብ ‹‹ሁለት››
አንቱ በተባሉ ከብረው በገዘፉ ትላልቅ ሰው መሀል
ህሊና ሲሟሽሽ እውነት ስሯ ሲደርቅ ህልም ሲስለመለም
በዙፋን መታጠር በአንቱታ መከበብ እጦቱ ይታየኛል
….
በቁስ የታጀቡ በእንቁ የከበሩ
ከሀብታቸው ብዛት ከፍ ብለው ተሰቅለው
ከፍ ብለው የቀሩ
አንደበት ሲያጥራቸው
ቅንጣት ቅንጣቢ…እውቀት ሲመክናቸው
ህዝቤ የሚሉት ህዝብ ከቦ ሲንዳቸው
የናዱት የእንቧይ ካብ ደርሶ ሲፈልጣቸው
ሲቀጠቅጣቸው ….
በደም ያገኙትን ክብርና ስልጣን
በደም ሲቀማቸው
ሰውነትን አጥቶ የሚያገኙት ኩራት
ዘመኑ ሲሟጠጥ ተስፋውን ሲታገት
ይታየኛል ምኩራብ
ይታየኛል ምናብ፡፡
….
ምናብ ‹‹ሶስት››
እግዜሩ ይመጣል
መጥቶም ይታዘባል
ፊተኞች ኋላ ኋለኞች ፊት ሆኑ
ዝቅ ያሉት ከፍ አሉ
ከፍ ያሉት ዝቅ አሉ
ዝቅም ከፍ ያላሉስ ምን ይሁን ተባሉ?
ብሎ ይጠይቃል
ሁሉን እንደማያውቅ እንዳልሰማ ሁኖ
ይህን ደንባራ ህዝብ አውቆ ያደናብራል
በውዥንብሩ ውስጥ ደስ ያለውን መርጦ
ወይ ደግ ወይ ሌባ ሰው
ደሀ ወይ ሀብታም ሰው
ጠቢብ ወይ ማይም ሰው
ሲወስድ ይታየኛል….
መቀላቀላችን መነጣጠላችን በእግዜር ሲደመደም
ምናብ ይታየኛል፡፡
ያንድ ለሊት ግጥም
በስንታየሁ
(……..)
ያንድ ለሊት ግጥም ቆይ ምን ቢል ጥሩ ነው?
ሰአት እየቆጠርክ በጨለመ ቁጥር መተኛት ምንድን ነው?
መተኛት ተፈጥሮው ሲጨልም ብቻ ነው?
ቀን ቀን ሰው አይተኛም?..
በጠራ ሰማይ ስር ክው ባለ ፀሀይ
ሰው አልተኛም ወይ?...እ
በል እንጅ….
ስራውን አቋርጦ ህይወቱን ገድቦ
በጠራራ ፀሀይ ያሸለበ የለም ወይ?...እ
……
ደሞ
ፅልመት ተገን አርገህ…ሴት ማቀፍ ምንድን ነው?
ለማቀፍ ለመሳም ከጋለ ገላዋ ዘሎ ለመላተም
ውበት እያደነቅህ በቀን አይሻልም?
እንዴት ሰው ከሚስቱ ከእጮኛ ይደበቃል
ሚወደውን ነገር በፅልመት ይከድናል
ከአንጀት ከወደዱ በቀንም ይስሟል…
ያቅፏልም ይተኟል
ዝም ብሎ መሸፈን ነገር መደባበቅ
አላግባብ መሽኮርመም ከእውነታ መራቅ
ለምዶብን ነው እንጅ ህይወት ቀኗ ቀን ነው
ብንርቀው የማይርቅ ብርሀን በጃችን ነው
……..
ደሞ
ህልም አየሁ እያልከን ምትቃዠው ምነው?
ልጆችህ…ሚስትህ…እህት ወንዶምችህ..
ምቀኛህ ወዳጅህ…የቤት ጎረቤትህ
ቀየህና አድባርህ መላው ያገርህ ህዝብ
ተኝቶ ሲያንቀላፋ
አንተ የኛ አዋቂ አንተ የኛ ፈላስፋ
ህልም አየሁ ትላለህ?
ህልምና ቅዠትክን መለየት ተስኖህ
እስቲ የታል ህልምህ..?
ለዚ ለተኛ ህዝብ…ሰርክ ላንቀላፋ
የመንፈስ ይሁንታ የምናብ ከፍታ
የህይወቱ ባትሪ የልፋት ስጦታ
የሚሆነው ህልምህ እስቲ ወየት ላይ ነው
ዲካውና ውሉ ቋጠሮው ሚፈታው?
ህልምስ በቀን ማየት…
ለተበደለ ሰው…ፍርድ ለጎደለበት
ፍቅር ለተነሳ አመፅ ለበዛበት
እናት አባት አጥቶ ሰው ለመከነበት
እሚበላው አጥቶ መለመኛ አፉንም ለተነጠቀበት
ለእንዲያ አይነቱ ሰው ነው..ህልም አለኝስ ካሉ
መታለም ካለበት መታየት ያለበት
ህልም ብሎ መጥራት
…….
ሺ…ጎርባጣ ኑሮ…በበሳሳው አልጋ
እረፍትን ፍለጋ እልፍ አመት ብተኛ
እንቅልፍ ድርሽ አይልም
ቢልም ህልም አታይም
ብታይም.
ህልምህን አትፈታም
ብትፈታም
ለተግባር አይጠራም…..
ይለኛል..ያብሰለስለኛል
ያልድ ለሊት ግጥም
ሰርክ እየሞገተ እንቅልፌን ነስቶኛል፡፡
ሳታውቁኝም አውቃችሁኝም ጨቅችቃችሁ መፅሀፍ ነገር ካላሳተምክ ላላችሁኝ ፣ ደስ አይበላችሁ መፅሀፌ እንዳይታተም በከልካዮች ተያዘ ፣ እናንተን ለማናደድ ሳይሆን ንዴቴን በናንተ አሳብቤ ለመግለፅም ጭምር ነው ፣ ግን እቺም ቀን ታልፍና…..አንድ ቀን ፣ ይቺ እማታልቅ አንድ ቀን ትገርመኛለች! እና አንድ ቀን በጥሩ ቀን ያገናኘን እና ጥሩ ሀሳብን በመፅሀፍ እናወጋለን
የካሌብ ማህሌት It is a blog circulating issues around socioeconomic and political bases and further more it is a blog about all artistic areas and philosophical agendas.
ስምና ሁናቴ
…………….
በካሌብ(ስንታየሁ) አለማየሁ
ስም ያው ብዙ ጊዜ መጠሪያ ነው ፣ አንዳንዶቹ ወላጆች ከሁኔታዎች ጋር እያመሳሰሉ ያወጣሉ ፣ አንዳንዶቹ አፋቸው ላይ የመጣውን ደስ ያላቸውን ስያሜ ይሰጡበታል፡፡ በእኛ ሀገር በተለይ አፍ መፍቻ ቋንቋው አማርኛ በሆነበት አካባቢ ስሞቻችን አንዳንድ ግዜ ከአባት ስም ጋር ተገጣጥሞ ትርጉም እንዲሰጥ ፣ እንዲገጥም ፣ መልክት እንዲያስተላልፍ ፣ አንዳንድ ጊዜ ደሞ ተረት መተረቻም ቅኔ መቀኛም ያደርጉታል፡፡
ለምሳሌ እኛ ሰፈር የነበረ አቶ አወቀ የሚባል ሰውዬ ፣ የልጆቹን ስም ከሱ ስም ጋር እንዲገጥም አድርጎ ነው ያወጣሁ፣ መቅደም አወቀ፣ መስጠት አወቀ፣ ወ/ሪት ማታለል አወቀ፣ መሳቅ አወቀ፣ እና ወላጆች አንዳንዴ ሳስበው ለነሱ ከነሱ ጋር የሚሄድ ስም ይሁን እንጂ ምንም አይነት ቃል ይሁን በቃ ዝም ብለው ይለጥፉብናል ፣ በቃ ‹‹ምናባቱ እኔ ለፍቼ ለማሳድገው ደሞ የስም ባለመብት ደሞ እሱ ሊሆን ነው›› ብለውና ‹‹በገዛ ልጃችንና በገዛ ቋንቋችን ማን ነኪ አለን›› ብለው የሚያወጡ ነው እሚመስለው ፣ እውነቴን እኮ ነው! አስቡት እስቲ ማታለል አወቀ ብሎ ስም ማውጣት እስቲ ምን ይሉታል ፣ በቃ ‹‹ ከኔ ስም ጋር ይግጠም ብያለሁ ይግጠም!›› ይላል አቶ አወቀ ፣ እሱ ሳይሰማ እዛ ቤት ለተወለደው ልጅ ፣ ወንድም ይሁን ሴት ስም አይወጣለትም፣ አቶ አወቀ ‹‹በዘራችን እማይገጥም ስም አውጥተን አናቅም›› እያለ እሚኮፈስ ፣ ያወጣው ስም ለወጣለት ልጅ ይመርበትም አይመርበት ፣ ከሱ ስም ጋር ብቻ ገጥሞ ካየ በቃ ‹‹እንዲህ ናቸው የአውቄ ልጆች አ!›› እያለ በየመንገዱ ጉራውን እሚነዛ ሰው ነው፡፡ ወይ የኛ ሰው ብሎ ብሎ እሚኮራበት ቢያጣ በልጁ ስም መንቀባረር ጀመረ! አይ እኛ አስቂኞቹ……
ወደሌላ ስም እንለፍ አብዮት ገነነ ፣ እሳቱ ገነነ፣ ሊያልቅ ሲል ገነነ እሚባሉ መከረኛ ፣ የሆኑ የአባታቸው የአረፍተ ነገር መስሪያ የሆኑ የሚመስለኝ ፣ አንዳንዴም የወላጆጃቸው የማስታወሻ ደብተር ወይም ዲያሪ የሚመስሉኝ ልጆች አሉ፡፡ እንደኔ እንደኔ ወቅት ጠብቀን ለልጆጃችን ስም እንደምናወጣ ሁሉ ፣ ወቅት ጠብቀን ደሞ ብንቀይርላቸው ጥሩ ነው ባይ ነኝ ፣ እኚህ መከረኛ ልጆች በደርግ ጊዜ ፣ በዚያ የኢሀዲግና የደርግ ጦርነት ወቅት ፣ በዚያ በተፋፋመ ጊዜ በመወለዳቸው ፣ ፈርዶባቸው አቶ ገነነም ስም አወጣጥ ይችላሉ መቸም! አብዮት ገነነ ፣ እሳቱ ገነነ እና የመጨረሻው የደርግ-ኢሀዲግ ጦርነት ግዜ የተወለደውን ደግሞ ሊያልቅ ሲል ገነነ ብለው ስም አውጥተዋል፡፡ ዛሬ ታዲያ አቶ አብዮት ስሙን አይወደውም ፣ ሆ እውነቱን እኮ ነው ፣ አስቡት እስቲ አብዮት ብሎ አቶ ፣ አሁን በዘመነ ዲሞክራሲ እና በዘመነ ሰላም ሰው ልጁን አብዮት ብሎ ይሰይማል ፣ እሺ ቆይ ያኔስ ጊዜው ነው ፣ ልጁን አብዮት ብሎ ቢሰይም ግድ የለም ፣ አሁን እሺ ያ ዘመን አልፏል አይደለ እንዴ ምናለበት ስሙን ለምሳሌ ከአብዮት ወደ እውቀቱ ፣ ሰላሙ ፣ ፍክክር ምናምን እያሉ ቢያወጡለት እንዴ እውነቴን እኮ ነው ፣ መቸም ከአባት ስም ጋር እንዲገጥም አደል እሚፈለገው ፣ ይኸው ይገጥማል፡- እውቀቱ ገነነ፣ ሰላሙ ገነነ ፣ ፉክክር ገነነ እያሉ መጥራት ይቻል ነበር ታዲያ ምን ያደርጋል የኛ ሰፈር አባቶች አይሰሙም አቦ!
አቶ ገነነም ልክ እንደ አቶ አወቀ ሁሉ ‹‹በህግ አምላክ ካወጣሁልህ ስም ውልፍች ትልና›› እያሉ በቃ ልጆቻቸው በስማቸው አብዮት አብዮት እየሸተቱና እየከረፉ ተሳቀው በመኖር ላይ ናቸው፡፡
በእርግጥ ስለ ስም ስናወራ በእኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በተለይ እንደ ጀርመን ባሉ ሀገሮችም ስም ከሁኔታና ከተግባር ጋር ተያይዞ ይወጣል፣ ለምሳሌ ጀርመኖች ሸማኔውን ሸማኔ ፣ እቃ ሻጩን እቃ ሻጭ ብለው የሚጠሩበት አጋጣሚ አለ፣ ሌሎችንም እንዲሁ ብዙ በስራቸውና በሁኔታቸው የሚያወጡበት አጋጣሚ አለ ፣ ማለትም ለምሳሌ ሸማኔውን ዌቨር ፣ ሻጩን ሴለር ምናምን እያሉ ይጠራራሉ ማለት ነው ፣ ይሄን ሰምቼ ታዲያ ዘወር ስል እትዬ ብርጣሉና እማማ ወርቂቱ ግብ ግብ ተያይዘው ደረስኩ ፣ ምነው ምን ሆነው ነው ፣ ምን አጋጫቸው ? ስል የእትዬ ብርጣሉ ልጅ ነው ነገረኛው የእማማ ወርቂቱን ልጅ የሸማኔ ልጅ ብሎ ተሳድቦ ነው አሉኝ! እማማ ወርቂቱ እትዬ ብርጣሉን ‹‹እንዴት ብትንቂኝ ነው በይ ብለሽ ብለሽ ልጅሽን ልከሽ የሸማኔ ልጅ ብለሽ ልጄን እምታሰድቢው እረ!›› ብለው ነጠላቸውን ጥለው ገጠሙ፣ ታዲያ አያችሁ ልዩነት? በጀርመን ሽምንና ከተከበረ ስራም አልፎ የተከበረ ስም ሆኖ ሳለ ወዲህ በኛ ሀገር ግን ንቀት ካዘለ ስድብ ተቆጥሮ ጎረቤት እና ዘር ማንዘር ያጣላል ጉድ ነው ሀበሻ!
ብቻ ግን እንተወውና ሰው መቸም እንደባህሉ ነው እሚኖረው ፣ እንደጀርመኖች ደፋር ሆነን ሸማኔውን ሸማኔ ብለን መሰየም ባንችልም ፣ ባይሆን እንደው ገና ለገና ከአባት ስም ጋር እንዲገጣጠም ብለን እባካችሁ ያልሆነ ስም አናውጣ ተመልከቱ ፡- ሳራ ከች አለ ፣ ቀፋፊው ፊቱ፣ አረግርግ ቆመጡ ብሎ ስም ምን ይሉታል እስቲ!
ሳራ ከች አለ! ብሎ ስም ! መጀመሪያውኑ ከች አለ ብሎ ስም አያስቅም ደረሰ እሚለውን ስም በቦሌ ብሄረሰብ ቋንቋ እ…ከች አለ! ወይ መንቀባረር ከዛ እንዳይገጥም ይሁን እንዲገጥም አይታወቅም በቃ ልጆቻቸውን የሆነ ቃል እየለበጡባቸው ወላጆች ይደበራሉ! አሀሀሀሀ ….አስቂኝ ነገር ነን…ሳራ ከች አለ ከምንል ቢቻል አንዴ ሆኗል መቸም የአባቷን ስም መቀየር አንችልም እንጂ ከች አለ እሚለውን ደረሰ በሚል የሀገሬን ለዛ ያለው ቃል መጠቀም ጥሩ ነበር ግን ምን ዋጋ አለው! አንዴ ሆኗል እሱ ነገር ግን ልጂቷን ለዚህ ስም አጋልጦ ከመስጠት ፣ ከአባቷ ስም ጋር መገጣጠሙ እንደ ህገ መንግስቱ የማይናድ ህግ ከሆነ ምን ይደረጋል ፣ በቃ ሳራ ከማለት ስሰራ ፣ ሳነብ ፣ ወይ ደሞ በዛው በለመዱት በቦሌኛቸው ኬክ ስበላ ፣ ፊልም ሳይ ፣ ጌም ስጫወት ምናምን እሚሉ ስሞችን ሰጥቶ ከሳቅን አይቀር በደንብ መሳቅ ነው፡፡ ከዛ በቃ ከአባቷ ስም ጋር ሲገጣጠም ስሰራ ከች አለ፣ ኬክ ስበላ ከች አለ፣ ፊልም ሳይ ከች አለ! አሁን እስቲ ይሄ ስም ነውን ሆ! ወሬ አረግነውኮ በቃ! መቸም አንዴ በዚህ ሀገር ስም ማውጣት ማለት አረፍተ ነገር መመስረትና አማርኛ ፔረድን እድሜ ልክ መሳተፍ ነውና!....ምን ማድረግ ይቻላል አብረን እንሳቃ…….
አንዴ እንዲሁ በስም ጉዳይ ከሆነ መንገድ ላይ ካገኘሁት ሰው ጋር እያወራን እያለ ፣ አሱ እራሱ በስሙ ሁሌም እንደሚበሳጭ ነገረኝ ፣ ምነው ምን ሆንክ ፣ ማን ነው ስምህ ስል ጠየኩት….
እረ ተወው እሱን አሲቂኝ ነው ስሜ ፣ ካልጠፋ አማርኛ እስቲ በናትህ ብሎ ድንገት እንባው ጥርዝዝ አለ…እንዴ ቆይ እንጂ ይሄን ያህል ምን ቢሆን ነው ስምህ እረ ደስ አይልም እንዳታለቅስ ብዬ በግድ አባብዬ ጠየኩት ስሙን ነገረኝ፣ ስሙ ገፊው ኮስትሬ ነው፡፡ እና አንተ ካስጠላህ አታስቀይርም እንዴ ምን አጨናነቀህ ስለው ፣ ‹‹እሱ አይደለ እንዴ እሚደብረው›› ብሎ ቀጠለ ፣ ‹‹አያቴ የማስቀየር መብቴን ይዞት ሞቷል›› አለኝ ፣ እንዴ እንዴት አይነት ነገር ነው ፣ ጭራሽ የሰው መብትም ይዞ መሞት ይቻላል እንዴ! እረ ይቺ ጉደኛ አገር ብዬ ፣ እንዴት ነው ግን አያትህ የማስቀየር መብትህን ይዘውት የሞቱት ፣ መብት አይደለም የሰው ልጁ ልብሱንና ወርቁን ሳይቀር ሲሞት እዚህ ትቶ አይደለ እንዴ እሚቀበረው አልኩት፣ ‹‹አይ አንተ ጥሩ ብለሀል›› ብሎ ቀጠለ ‹‹ይሄ እኮ ባይን የማይታይ የአደራ ቃል ነው ፣ በቃ ማንም የልጅ ልጄ እኔ ስም አውጥቼለት ፣ ደስ ሳይለው ቀርቶ አስቀይሮ አያውቅም፣ እና አደራ ብየሀለው ልጄ ፣ ካስቀየርክ በአዲስ ስምህ ትሞታለህ ፣ ኑሮ አይቀናህም ፣ ብሎ እርግማንም ትንቢትም ቀላቅሎ ነው ነገሮኝ የሞተው ስለዚህ ቃሉን ብሽር ትንቢቱና እርግማኑ የሚደርስ ስለሚመስለኝ እፈራለሁ ፣ እና ይኸው አሁን ማንም ገፌ ፣ ገፎ ፣ ገፊቲ እያሉ ቁልምጫ አይሉት ስድብ እየተጠራሁበት እገኛለው›› ብሎ አጫወተኝ፡፡
አንዳንዴ ደሞ የሚያስቀው ነገር፣ መቸም አንዴ ስለስም ከተነሳ ብዬ ነው ፣ በቃ የሆነ የውጭ ሀገር ስም ነገር ከሆነ ደስታችን አይጣል ነው፣ እነ ዮሀንሶች ጆን ሲባሉ ደስታቸው አይጣል ነው! ፣ እነ ሮቤል ሮበርት ሲባሉ ይፈነድቃሉ! ሌሎችም ያልጠቀስኳቸው ብዙ ብዙ ግን ለምን ፣ አንዱ ጓደኛዬ ምርር ብሎት ያደለውማ ሪሀና ራውል ይባላል እኔ አለው እንጂ ለቁልምጫ እንኳን እማይመች አረገሀኝ እሚል ስም ይዤ ወይኔ! ሆ ብቻ የሆነ ብዙ አስቂኝ ነገር አለው ፣ በመጨረሻ ግን የበኩሌን ልምከራችሁ ፣ አንዳንዴ እኮ ከወጣትም ምክር መቀበል ብፁእነት ነው ፣ እና እኔ እምለው ምን መሰላችሁ ስም ስታወጡ በተለይ ለወላጆች የናንተን ታሪክ እንዲወክል ብቻ አታስገድዱ እሺ ግን ይሄም ይሁን ነገር ግን ልጁ ሲያድግ የመቀየር መብት ይኖረው ዘንድ ህገ መንግስታችሁን ወይንም ህገ ስማችሁን ተቀያሪ ፍሌክሴብል አድርጉት እንጂ ባለፈ ትውልድ እና መንግስት አሰያየም የወጣውን ስም ተሸክሞ የመኖር ግዴታ ያለበት ልጅ የለም፡፡በዚህ እግር ምናለበት መጥፋት የሌለባቸው ስንት ሺህ ቋሚ ቅርሶች አሉን አይደለ እንዴ ፣ እነሱን ካፈረስክ ወዮልክ ብላችሁ ለምን ቃል አስገብታችሁ አትሞቱም!.....አበቃሁ፡፡
Click here to claim your Sponsored Listing.
Location
Category
Telephone
Website
Address
Sarbet
Addis Ababa
1211
