FDRE Ministry of Justice/ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር

FDRE Ministry of Justice/ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር

Share

Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from FDRE Ministry of Justice/ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር, Government Organization, Bambis, Jomo Kenyatta Avenue, Addis Ababa.

Our mission is to ensure that quality laws are enacted and implemented in order to build an effective and efficient criminal, civil, and administrative justice system that protects the interests of the Ethiopian government and people.

05/06/2026

በሌሎች ሰዎች መብቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እና የሚያስከትሉት የወንጀል ተጠያቂነት

መግቢያ
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕግ-መንግሥት ክፍል ሶስት ስር ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተደነገጉ ሲሆን እንዚህ መብቶች ማንኛውም ሰው በእኩልነት የተጎናጸፏቸው ናቸው። በዚህም ማንኛውም ሰው በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕግ-መንግሥትም ሆነ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በተደረጉ ስምምነቶች በተጎናጸፋቸው መብቶች የመጠቀም መብት ያለው ሲሆን በመብቱ የሚጠቀም ማንኛውም ሰው ደግሞ የሌላውን መብትና ነጻነት ባከበረ መንገድ መሆን አለበት። የአንድ ሰው መብት በማንኛወም አካል ከሕግ አግባብ ውጭ የተደፈረ እንደሆነ የወንጀል ተጠያቂነትን እንደሚስከትል በወንጀል ሕጉ እና በሌሎች ሕጎች ተመልክቶ ይገኛል። በዚህ ጽሑፍ በወንጀል ሕጉ የተደነገጉ በሌላ ሰው መብቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የሚያስከትሉትን ተጠያቂነት በአጭሩ እንመለከታለን፡፡

በሲቪል መብቶች በነጻ የመጠቀም መብትን መከልከል
በመርህ ደረጃ የሲቪል መብቶች ሰው በመሆን ብቻ የሚገኙ በመሆኑ ገደብ ሊጣልባቸው የማይቻል ከመሆኑም በላይ በነዚህ መብቶች ለመጠቀም ለማንም ምንም አይነት ክፍያም ሆነ ውለታ ማድረግ አይጠበቅም። በ1996 ዓ.ም በወጣው ወንጀል ሕግ አንቀጽ 601 ላይ እንደሰፈረው ማንም ሰው በዛቻ፣ በኃይል ድረጊት፣ በማታለል ወይም ሕግ ወጥ በሆነ በሌላ መንገድ፡-
• ሌላ ሰው በሕግ-መንግሥቱ ወይም በሌሎች ሕጎች ከተሰጡ የሲቪል መብቶች አንዱን በተለይም የወላጅነትን ወይም የሞግዚትነትን፣ የመክሰስን ወይም ፍርድ ቤት መብቱን እንዳይጠቀምበት የከለከለ ወይም
• ሌላው ሰው ከእነዚህ መብቶች በአንዱ በተወሰነ አኳኃን እንዲጠቀምበት ያስገደደ እንደሆነ
ድርጊቱ በሌላ ግልጽ ድንጋጌ የሚያስቀጣ ካልሆነ በስተቀር ከሶስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እሥራት ወይም በመቀጮ ሊቀጣ እንደሚችል በወንጀል ሕጉ ላይ ተደንግጎ ይገኛል። ሌላው ከሲቪል መብቶች በነጻ የመጠቀም መብት ክልከላ ጋር በተያያዘ የሚነሳው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 467 ላይ የመምረጥና የመመረጥ መብትን የመንካት ሲሆን ይህንን መብት የከለከለ ሰው ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እሥራት ወይም በመቀጮ እንደሚቀጣ ተደንግጎ እናገኛለን።

የመዘዋወር ነጻነት መብትን መድፈር
የመዘዋወር ነጻነት መብት በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት ላይ ከተረጋገጡ መብቶች መካከል አንዱ ሲሆን በኢትዮጵያ ሕግ-መንግሥት ተካተው ከሚገኙ መብቶች መካከልም አንዱ ነው። በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕግ-መንግሥት አንቀጽ 32 ላይ እንደተቀመተው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ አገሪቱ ውስጥ የሚገኛ የውጭ ዜጋ በመረጠው የአገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከአገር የመውጣት ነጻነት አለው። በመሆኑም ማንም ሰው በሕግ ሥልጣን ሳይኖረው ሌላው ሰው በኢትዮጵያ ውስጥ በነጻ እንዳይዘዋወር የከለከለ እንደሆነ በቀላል እሥራት ወይም በመቀጮ እንደሚቀጣ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 602(1) ስር ተመልከቷል።

በነጻነት የመዘዋወር መበትን የከለከለው ወይም የደፈረው የመንግሥት ሠራተኛ በሆነ ጊዜ ሥልጣን አላግባብ መገልገል በመሆኑ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9(1) መሠረት ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እሥራት እና ከሶስት ሺ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከአስር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት እና ከአስር ሺ ብር በማይበልጥ መቀጮ የሚቀጣ መሆኑ ተደንግጓል።

የሥራ ነጻነት መብትን መጣስ
በሌላ ሰው መብቶች ላይ ከሚፈጸሙ የወንጀል አይነቶች አንዱ የሥራ ነጻነት መብትን መጣስ ሲሆን ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ በአገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኡኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሰማራት እና ለመተዳደሪያ የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት እንዳለው በሕግ-መንግሥቱ አንቀጽ 41(1) ላይ በግልጽ ተደንግጓል። የሥራ ነጻነት መብት በሕገ-ገመንግሥቱ የተረጋገጠ በመሆኑ ማንም ሰው ሌላው ሰው በዚህ መብት እንዳይሠራብ ሊከለክለው አይችልም።
በዚህ መሠረትም ማንም ሰው በዛቻ፣ በኃይል ድረጊት፣ በማታለል ወይም በሌላ ሕግ-ወጥ መንገድ ሌላውን ሰው፡-
• አንድ የተወሰነ ሥራ ወይም የሥራ ሁኔታ እንዲቀበል ወይም አሰሪው የሥራ ሁኔታዎችን እንዲቀበል ወይም እንዲያሻሽል በማሰብ ሥራ አንቢ እንዲል ወይም እንዲያቆም ያስገደደ
• ከላይ የተመለከቱትን ለመፈጸም ዓላማው የሆነውን አንድ ቡድን ወይም ማኅበር እንዲቀላቀል ወይም የአንድ ቡድን አባል እንዲሆን ያስገደደ ወይም ከእንደዚህ አይነቱ ቡድን ወይም ማኅበር እንደፈለገው ወይም በፈለጋው ጊዜ እንዳይወጣ የከለከለ አንደሆነ የሥራ ነጻነት መብትን በመጣስ ወንጀል ተጠያቂ ይሆናል።
ይህ የወንጀል ድርጊት በግል አቤቱታ የሚቀርብ ክስ ሲሆን ቅጣቱም ከሶስት ወር በማያንስ ቀላል እሥራት ወይም በመቀጮ እንደሆነ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 603(1) ላይ ተመልክቷል።

የመጻጻፍ ወይም የግንኙነት ግላዊነት መብትን መድፈር
በኢ.ፌ.ድ.ሪ ሕግ-መንግሥት በምዕራፍ ሶስት ስር ከተደነገጉ ሰብዓዊ መብቶች መካከል የመጻጻፍ ነጻነት እና የግላዊነት መብት ሲሆን ይህ መብት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ጥበቃ ከተደረገላቸው መብቶች መካከልም አንዱ ነው። ይህ መብት በሕግ-መንግሥቱ ጥበቃ የተደረገለት በመሆኑ በዘፍቃድ ወይም ከሕግ አግባብ ውጭ ሊጣስ አይችልም፡፡ ጥሶ የተገኘ ማንም ሰው የወንጀል ተጠያቂነት እንዳለበት በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ ላይ ተመልከቷል።
በዚሁ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 606 ላይ እንደሰፈረው ማንም ሰው በሕግ ሳይፈቀድለት፡-
• የእርሱ ያለሆነውን የሥራ (የመስሪያ ቤት) የጉዳይ ማስፈጸሚያ ወይም የግል የሆነ ዝግ ወይም ግልጽ የደብዳቤ (የፖስታ) ወይም የመጻጻፍ፣ የቴለግራም፣ የስልክ፣ የኤሎክትሮኒክ ወይም የቴሌኮሚኒኬሽን ወይም የማናቸውም ሌላ ዘዴ የሚደረግ ግንኙነትን፤ የንግድ ወይም የግል የሆነ የተዘጋ ደብዳቤን ወይም አንድን ጥቅል፤ የታሸገን ጥቅል ዕቃን ወይም ማናቸውንም የተላከ ነገር አስቦ የከፈተ ወይም ውስጡ ያለውን ነገር ያወቀ እንደሆነ ወይም
• ለዕርሱ ያልተላከውን እንደዚህ አይነቱን ደብዳቤ ወይም የታሸገ ጥቅል በስሕተት ወይም በቸልተኝነት በመክፍት አንዳንድ ነገሮችን ከአወቀ በኋላ ለሌላ ሰው ያሳወቀ ወይም ጥቅም ያገኘበት እንደሆነ የግል አቤቱታ ሲቀርብበት ከአንድ ሺ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ወይም እንደነገሩ ሁኔታ ከሶስት ወር በማይበልጥ ቀላል እሥራት እንደሚቀጣ ተደንግጓል።
በሌላ በኩል ማንም ሰው አስቦና ሕግ ወጥ በሆነ መንገድ አንድን ደብዳቤ ወይም የሚላክ ዕቃ ወደ ተላከበት አድራሻ እንዳይደርስ ያቋረጠ ወይም ያስቀረ፣ ወደ ሌላ አድራሻ እንዲደርስ ያደረገ ወይም ያወደመ እንደሆነ የወንወጀል ተጠያቂነት ያለበት በመሆኑ ድርጊቱ የበለጠ ቅጣት በሚያስከትል ሌላ የሕግ ድንጋጌ የሚያስጠይቅ ካልሆነ በቀር በወንጀል ክስ አቅራቢነት ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እሥራት እንደሚቀጣ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 606(2) ስር ተደንግጎ ይገኛል። በዚሁ የወንጀል ሕግ እንደተመለከተው በመንግሥት ሠራተኞች ስለሚፈጸሙ የሥራ ሚስጥርን ስለመግለጽ፣ በአደራ በተሰጠ ዕቃ ያለአግባብ ስለማዘዝ እና በሥራ ተግባር ስለሚፈጸም የመውሰድና የመሰወር ወንጀሎች በተመለከተ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 መሠረት በሙስና ወንጀል ተጠያቂ ይሆናሉ።

ማጠቃለያ
በአጠቃላይ በፌደራሉ ሕገ-መንግሥት የተረጋገጡና ጥበቃ የተደረገላቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሕግ አግባብ ካልሆነ በስተቀር ሰዎች በመብቶቹ እንዳይጠቀሙ ለማገድም ሆነ ለመከልከል የማይቻል ሲሆን ሰዎች እነዚህን መብቶች እንዳይጠቀሙ አድርጎ መገኘት የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚያስከትል ሊታወቅ ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ

የፍትሕ ሚኒስቴርን የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆችን እና ድረ-ገፅን ይቀላቀሉ
Website
https://www.justice.gov.et
Facebook
https://www.facebook.com/MOJEthiopia/
(x) Twitter
https://x.com/MOJEthiopia
YouTube channel
https://youtube.com/...3701...
Telegram
https://t.me/fdreattorneyGeneral_external

Photos from FDRE Ministry of Justice/ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር's post 05/06/2026

በአገልግሎት አሰጣጠጥ እና በተገልጋዮች አያያዝ ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ
************************
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የተገልጋዮች ዳይሬክቶሬት ከንቃተ ሕግና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር በአገልግሎት አሰጣጥ እና በተገልጋዮች አያያዝ ዙሪያ ለተቋሙ ኤክስኪዩቲቭ ሴክሬተሪዎች፣ ፕሮቶኮል ባለሙያዎች፣ ለመረጃ ዴስክ ሠራተኞች፣ ለቢሮ ረዳቶች እና ለስካነር ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተሰቷል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ ክብርን መሠረት ያደረገ ማህብረሰብ ተኮር፣ተደራሽና ተዓማኒ የፍትሕ ሥርዓት ለመገንባት የሰነቀውን ራዕይ ዕውን ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እያከናወናቸው ካሉ ተግበራት መካከል አንዱ የተቋሙን የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል ነው፡፡

የዚህ ሂደት አንዱ አካል በሆነው በዚህ የስልጠና መርሐ-ግብር ላይ ሰልጣኞች አገርና ሕዝብን ማገልገል ትልቅ እድል መሆኑን በመገንዘብ ሥራቸውን በትጋት በማከናወን ለሁሉም ሥራዎቻቸውና አሰራሮች በዋናነት መለኪያ የሚሆነው የተገልጋዮች እይታ መሆኑን በመረዳት የተቋሙን እሴቶች በጠበቀ መልኩ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡

ስልጠናው በዋናነት የተገልጋዮች አገልግሎት ምንነት፣ የተገልጋዮች አይነትና አያያዝ፣ ተቋሙ ከሠራተኛው የሚጠብቀው ሃላፊነት፣ ተገልጋዮችን በአግባቡ የማስተናገድ ስልቶች፣ ተባብሮ መስራት፣ በሥራ ቦታ ሊኖር ስለሚገባው የሙያ ሥነ-ምግባር እንዲሁም በሥራ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን እንዴት በአግባቡ መፍታት እንደሚቻል የሚመለከቱ ጉዳዮች ተዳሰዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴርን የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆችን እና ድረ-ገፅን ይቀላቀሉ
Website
https://www.justice.gov.et
Facebook
https://www.facebook.com/MOJEthiopia/
(x) Twitter
https://x.com/MOJEthiopia
YouTube channel
https://youtube.com/...3701...
Telegram
https://t.me/fdreattorneyGeneral_external

03/06/2026

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግሥት አወቃቀር
መግቢያ
ሕገ መንግሥት የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ ሲሆን እንደየአገራቱ ሁኔታ አገራቱ የሚመሩበትን መሠረታዊ ጉዳዮች የሚያካትት ሕግ ነው፡፡ ይዘቱም እንደየአገራቱ ሁኔታና ፍላጎት የሚለያይ ነው፡፡ በአገራችንም በ1987 ዓ.ም የወጣውን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት በሥራ ላይ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ጽሑፍም የዚህን ሕገ መንግሥት አወቃቀር በአጭሩ የሚዳስስ ይሆናል።

የሕገ መንግሥቱ ዋና ዋና ይዘት
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግሥት በ11 ምዕራፎች ስር የተደራጁ 106 አንቀጾች ያሉት ሲሆን መሠረታዊ ክፍሎች እንደሚከተለው የተዋቀሩ ናቸው።

1. አጠቃላይ ድንጋጌዎች፡- ይህ ክፍል የአገሪቱን መንግሥት ሥያሜ (የኢትዮጵያ ፌዴራላዊና ዴሞክራሳዊ ሪፐብሊክ)፣ የኢትዮጵያ ግዛት ወሰን፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር፣ የሥራ ቋንቋ እና ስለዜግነት የተመለከቱ ጉዳዮችን የሚያካትት ነው።
2. የሕገ መንግሥት መሠረታዊ መርሆዎች፡- ይህም የሕዝብን ሉዓላዊነት፣ የሕገ መንግሥቱን የበላይነት፣ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን መከበር፣ የመንግሥት እና የሃይማኖት መለያየትን እና የመንግሥት አሠራርና ተጠያቂነትን ይደነግጋል።

3. መሠረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች፡- ይህ ክፍል ሰብአዊ መብቶች ማለትም የህይወት፣ የአካል ደህንነትና ነፃነት መብት፣ የተያዙ፣ የተከሰሱ፣ በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብት፣ የክብርና የመልካም ሥም መብት፣ የእኩልነት መብት፣ የግል ሕይወት የመከበርና የመጠበ መብት እና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚያካትት ነው፡፡ በተጨማሪም ዲሞክራሲያዊ መብቶች ማለትም የአመለካከትና ሀሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብት፣ የመጀራጀት መብት፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት፣ የመዘዋወር መብት፣የዜግነት መብት፣ ፍትሕ የማግኘት መብት፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት፣ የንብረት መብት፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህል መብቶችን፣ የአካባቢ ደህንነት መብት፣ የልማት መብት የመሳሰሉትን የሚደነግግ ሲሆን የሴቶች ፣ የህጻናት፣ የሠራተኞች እና የብሔር ብሔረሰቦች መብቶችም በዚሁ ክፍል ተካተው ይገኛሉ፡፡

4. የመንግሥት አወቃቀር፡- ይህም የፌዴራል መንግሥትን አባላት ወይም ክልሎች፣ የአከላለል ለውጦችን እና ርዕሰ ከተማ (አዲስ አበባ) ይደነግጋል።

5. የሥልጣን አወቃቀር እና ክፍፍል፡- ይህ ክፍል የፌደራልና የክልል መንግሥታትን አወቃቀር፣ ሥልጣንና ተግባር ይደነግጋል።
 በአወቃቀር ደረጃ የፌደራሉም ሆነ የክልል መንግሥታት ሕግ የአውጪ፣ የሕግ አስፈፃሚ እና የዳኝነት ሥልጣን እንዳላቸው ይደነገግጋል፡፡
 በሥልጣንና ተግባር ረገድ የፌደራልና የክልል መንግሥታት ያላቸው ሥልጣንና ተግባር በዝርዝር ተደንግጓል፡፡ ለአብነትም
የፌዴራል መንግሥት ሕገ መንግሥቱን የመጠበቅ፣ ዬመከላከል፤ የአገሪቱን አጠቃላይ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና የልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ዕቅድ የማውጣት፣ የማስፈፀም፤ የመሬት፣ የተፈጥሮ ሀብትና የታሪክ ቅርሶች አጠቃቀምና ጥበቃን በተመለከተ ሕግ የማውጣት፣ የአገሪቱን የፋይናንስ የገንዘብ የውጪ ኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን የማውጣት፣ የማስፈፀም እና የመሳሰሉ በርካታ ኃላፊነቶች (አንቀጽ 51) የተሰጡት ሲሆን
ክልሎች ደግሞ በሕገ መንግሥቱ ለፌዴራሉ መንግሥት በተለይ ወይም ለፌዴራሉ መንግሥትና ለክልሎች በጋራ በግልፅ ያልተሰጠ ሥልጣን የክልል ሥልጣን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ለምሳሌ ራስን በራስ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ ክልላዊ መስተዳድር የማዋቀር፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመገንባት፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥትን የመጠበቅ፣ የመከላከል፤ የክልል ሕገ መንግሥትና ሌሎች ሕጎችን የማውጣትና የማስፈፀም፤ የፌዴራሉ መንግሥት በሚያወጣው ሕግ መሠረት መሬትና የተፈጥሮ ሀብትን የማስተዳደር፤ ለክልሉ በተወሰነ የገቢ ምንጭ የክልል ግብርና ታክስ የመጣል፣ የመሰብሰብ፣ የክልሉን በጀት የማውጣትና የማስፈፀም… (አንቀጽ 52) የመሳሰሉ ኃላፊነቶች ተሰጥቷቸዋል፡፡

6. የፌዴራል ምክር ቤቶች፡- የፌዴራሉ መንግሥት ሁለት ምክር ቤቶች ያሉት ሲሆን እነዚህም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ናቸው።
 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስር ስለ ምክር ቤቱ አባላት፣ የምክር ቤቱ ሥልጣንና ተግባር፣ የፖለቲካ ሥልጣን (በምክር ቤቱ አብላጫ ድምፅ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅቶች የፌዴራሉ መንግሥት የአስፈፃሚ አካል እንደሚያደራጁ እና እንደሚመሩ)፣ ስለሕግ አፀዳደቅ፣ ስለምክር ቤቱ ስብሰባና የሥራ ዘመን፣ የምክር ቤቱ ውሳኔዎችና የሥነ ሥርዓት ደንቦች፣ ስለምክር ቤቱ መበተን አንቀጽ 54- 60 ተደንግጓል።
 የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስር ስለ ምክር ቤቱ አባላት፤ የምክር ቤቱ ሥልጣንና
ተግባር (ለምሳሌ፡- ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ፣ የብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት በተመለከተ በሚነሱ ጥያቄዎች ላይ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የመወሰን፣ በክልሎች መካከል ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሔ የመፈለግ…) ሥልጣን እንዳለው ከመደንገጉ በተጨማሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት መብት፣ ውሳኔዎችና የሥነ ሥርዓት ደንቦች፤ ስለ በጀት፣ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ሥልጣን፤ የስብሰባና የሥራ ዘመን፤ በሁለቱም ምክር ቤቶች አባል መሆን የማይቻል ስለመሆኑ ከእንቀፅ 61-68 ተደንግጎ ይገኛል።

7. ስለ ሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት፡- ፕሬዚዳንቱ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ርዕሰ ብሔር እንደሆኑ፤ ስለ ፕሬዚዳንቱ አሰያየም (በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ አቅራቢነት በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ከተደገፈ ፕሬዚዳንት እንደሚሆን) እና የፕሬዚዳንቱ ሥልጣንና ተግባር (ምሳሌ የሁለቱን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ የመክፈት፣ የውጪ አገር አምባሳደሮችንና የልዩ መልዕክተኞችን የሹመት ደብዳቤ የመቀበል፣ በሕግ መሠረት ይቅርታ የማድረግ…) (ከአንቀጽ 69- 72) ደንግጓል።

8. የሕግ አስፈፃሚ አካል፡- ስለአስፈፃሚነት ሥልጣን (የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የአስፈፃሚነት ሥልጣን የጠቅላይ ሚኒስቴሩና የሚኒስቴሮች ምክር ቤት እንደሆነ እና ተጠሪነታቸው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሆነ)፤ የጠቅላይ ሚኒስቴሩ አሰያየም (ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል እንደሚመረጥና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያገኘው የፖለቲካ ድርጅት ወይም ያገኙት የፖለቲካ ድርጅቶች የሥልጣን ዘመንን እንደሚረከቡ)፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣንና ተግባር (የአገሪቱ ርዕሰ መስተዳደር፣ የሚኒስቴሮች ምክር ቤት ሰብሳቢና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እንደሆነ፣ የሚኒስቴሮች ምክር ቤትን እንደሚመራ፣ እንደሚያስተባብር እና እንደሚወክል፣ የሚኒስቴሮች ምክር ቤት ያወጣውን ፖሊሲዎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና ውሳኔዎችን ተፈፃሚነት እንደሚከታተል…)፤ ስለ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ (በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተለይተው የተሰጡትን ተግባሮች እንደሚያከናውን እና ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በማይኖርበት ጊዜ ተክቶ እንደሚሰራ እንዲሁም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስቴሩ እንደሆነ)፤ ስለ ሚኒስቴሮች ምክር ቤት፣ የሚኒስቴሮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር (ለምሳሌ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወጡ ሕጎችና የተሰጡ ውሳኔዎች በሥራ መተርጎማቸውን የማረጋገጥ፣ መመሪያዎችን የመሥጠት፣ የፌደራሉን መንግሥት አመታዊ በጀት የማዘጋጀት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማቅረብ፣ ሲጸድቅ ተግባራዊነቱን የማረጋገጥ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የልማት ፖሊሲዎችን እና ስትራቴጂዎቸን የመንደፍ፣ የማስፈፀም፣ የጦርነት ጉዳዮችን ጨምሮ በማናቸውም ጉዳዮች ላይ የሕግ ረቂቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማቅረብ…) የመሳሰሉ ኃላፊነቶች እንዳሉት ይደነግጋል፡፡ (አንቀጽ 72-77)

9. የፍርድ ቤቶች አወቃቀር እና ሥልጣን፡- ይህ የሕገመንግስቱ ክፍል የፌዴራል እና የክልል ፍርድ ቤቶችን ሥርዓት ያስቀምጣል።
 ስለ ነፃ የዳኝነት አካል፤ የዳኝነት ሥልጣን (በፌዴራልም ሆነ በክልል የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ እንደሆነ፣ በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ የዳኝነት አካል ከማንኛውም የመንግሥት አካል፣ ከማንኛውም ባለሥልጣንም ሆነ ከማንኛውም ሌላ ተፅዕኖ ነፃ እንደሆነ፣ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌዴራሉን መንግሥት የዳኝነት አካል የሚያስተዳድርበትን በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ እንደሚያስወስና ሲፈቀድለትም እንደሚያስተዳድር…) እና የፍርድ ቤቶች ጣምራነትና ሥልጣን፤ ስለዳኞች አሿሿም፤ ስለ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አወቃቀር፤ ሕገ መንግሥቱን ስለመተርጎም፤ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሥልጣንና ተግባር ከአንቀጽ 78-85 ሽፋን አግኝተዋል።

10. የብሔራዊ ፖሊሲ መርሆዎች እና ዓላማዎች፡- የውጪ ግንኙነት መርሆዎች፤ የመከላከያ መርሆዎች፣ የፖለቲካ ነክ ዓላማዎች፣ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና የባሕል ነክ ዓላማዎች እና የአካባቢ ደህንነት ጥበቃ ዓላማዎችን ከአንቀጽ 85 እስከ 92 አካቶ ይገኛል።

11. ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች፡- ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ የፋይናንስ ወጪን እና ገቢን በሚመለከት፣ የፌደራል መንግሥት የታክስና የግብር ሥልጣን፣ የክልል መስተዳድሮች የታክስና የግብር ሥልጣን፤ የጋራ የታክስና የግብር ሥልጣን፤ ተለይተው ስላልተሰጡ የታክስ እና የግብር ሥልጣኖች፣ የታክስና የግብር አጣጣል መርሆዎች፣ ስለ ዋናው ኦዲተር፤ ስለ ምርጫ ቦርድ፤ ስለ ሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን፤ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሀሳብ ስለማመንጨት፣ ሕገ መንግሥቱን ስለማሻሻል እና የመጨረሻ ሕጋዊ እውቅና ስላለው የመንግሥቱ ቅጂ (የአማርኛው ቅጂ የመጨረሻ ሕጋዊ እውቅና ያለው ሰነድ እንደሆነ) ይደነግጋል።

ማጠቃለያ
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግሥት ከአገሪቱ መንግሥት ሥያሜ ጀምሮ የፌዴራልና በክልል መንግሥት ሥልጣንና ተግባራት፣ የመንግሥት ሥልጣን የሚያዝበትንና አገር የምትተዳደርበትን ሥርዓት፣ የሰዎችን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እና ሌሎች ጉዳዮችን ዝርዝር ያካተተ መዋቅር አለው።
በንቃተ ሕግና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ

Photos from FDRE Ministry of Justice/ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር's post 02/06/2026

ከአለም አቀፍ የንግድ ምክር ቤት የግልግል ዳኝነት ፍርድ ቤት (ICC International Court of Arbitration) ፕሬዝዳንት ጋር ስልታዊ ትብብር ለመመስረት የሚያስችል ውይይት ተደረገ
*****************************
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ ከዓለም አቀፉ የንግድ ምክር ቤት (ICC) የግልግል ዳኝነት ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሳሎሞን ጋር በበይነ-መረብ (Virtual) ውጤታማ ውይይት አድርገዋል።

በአገራችን አጠቃላይ ምርጫ እየተካሄደ በሚገኝበት ታሪካዊ ዕለት የተደረገው ይህ ውይይት፤ ኢትዮጵያ ከፍርድ ቤቱ ጋር ያላትን ግንኙነት በክርክር ሂደት ላይ ብቻ ከማተኮር ባለፈ ወደ ስትራቴጂካዊ ተቋማዊ አጋርነት ለማሸጋገር ያለመ ነው። ሚኒስትር ዴኤታው የመራጭነት ድምጽ ሰጥተው በቀጥታ በውይይቱ ላይ መገኘት በመቻላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፤ እ.አ.አ. በ2026 የተሻሻለው የ ICC የግልግል ዳኝነት ደንብ ሥራ ላይ በዋለበት በዚሁ ዕለት ውይይቱ መደረጉ ድርብ ታሪካዊ ምዕራፍ በመሆኑ የእንኳን ደስ አሎት መልዕክት ለፕሬዝዳንቷ አስተላልፈዋል።

አገራችን የዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ክቡር አቶ በላይሁን፤ በሪፎርም ሥራዎቻችን የተደረጉ የሕግ እና መዋቅራዊ ማሻሻያዎች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለው ዓለም አቀፍ ትስስር፣ እንዲሁም አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ መሆኗና የመሳሰሉት ምቹ ሁኔታዎች ኢትዮጵያን በዘርፉ ተመራጭ ያደርጓታል ብለዋል።

በቅርቡ ተግባራዊ የሚደረግ ብሔራዊ የአማራጭ አለመግባባት መፍቻ (ADR) ፍኖተ-ካርታ መዘጋጀቱን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በዋና ዋና የሪፎርም አምዶቹ ውስጥ የ ICC እና የፕሬዝዳንት ክላውዲያ ትብብር እና ድጋፍ ከፍ ያለ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል። በዋናነትም የመንግስትን ዓለም አቀፍ የክርክር ጉዳዮች የሀገር ውስጥ የሕግ ባለሙያዎች በብቃት መያዝ እንዲችሉ የአቅም ግንባታ፣ የልምድ ልውውጥ እና ነጻ የትምሕርት ዕድሎችን በማመቻቸት ረገድ አስተዋጾ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ፕሬዝዳንት ክላውዲያም በበኩላቸው በውይይቱ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን ተራማጅ የሪፎርም ሥራዎች ለመደገፍ ቃል ገብተዋል። የረጅም ጊዜ ዝግጅት የማይፈልጉ እና በአስቸኳይ/በቅድሚያ ሊተገበሩ ይችላሉ ያሏቸውን ማለትም ለመንግስት የሕግ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት እና ለሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መንግስት ተቋማት ልዑካን ቡድን የልምድ ልውውጥ መድረክ ማመቻቸት ላይ በቀጥታ ድጋፍ ማድረግ የሚቻል መሆኑን አረጋግጠዋል። ሌሎች የድጋፍ እና የትብብር መስኮችም በቀጣይ ደረጃ በደረጃ እየተለዩ ተግባራዊ እንደሚደረጉ ጠቁመዋል።

ይህን ተስፋ ሰጪ ጅምር ወደ ተግባር ለመለወጥ እና እ.አ.አ. እስከ 2026 ማጠናቀቂያ ድረስ ይፋዊ የመግባቢያ ስምምነት (MoU) ለመፈረም ከ-ICC አፍሪካ ኮሚሽን ጋር በጋራ የሚሰራ የቴክኒክ የሥራ ቡድን በአስቸኳይ እንደሚቋቋም ተገልጿል። ይህ አጋርነት ኢትዮጵያን በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የግልግል ዳኝነት መዳረሻ ለማድረግ የሚደረገውን ጉዞ በእጅጉ ያግዛል።

የፍትሕ ሚኒስቴርን የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆችን እና ድረ-ገፅን ይቀላቀሉ
Website
https://www.justice.gov.et
Facebook
https://www.facebook.com/MOJEthiopia/
(x) Twitter
https://x.com/MOJEthiopia
YouTube channel
https://youtube.com/...3701...
Telegram
https://t.me/fdreattorneyGeneral_external

Photos from FDRE Ministry of Justice/ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር's post 31/05/2026

መንግሥት ለባህላዊ ፍትሕ ሥርዓቶች ትኩረት በመስጠት የሕግ ማዕቀፎችን እና ተቋማዊ ድጋፎችን እያጠናከረ መሆኑ ተገለፀ
****************************
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከUnited Nations Development Programme እና Hague Institute for Innovation of Law ጋር በመተባበር በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰሜን ሸዋ ዞን ልዩ ስሙ በልቼ ቀበሌ ሥራ ለጀመረው ሞዴል ባህል ፍርድ ቤት የቢሮ ዕቃዎች እና ለሽማግሌዎች የአቅም ግንባታ የሥልጠና ወጪ ድጋፍ አደረገ።

በሞዴል የባህል ፍርድ ቤቱ የሥራ ማስጀመሪያ እና ለሽማግሌዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ፕሮግራም ላይ የፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሃንን ጨምሮ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፣ የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ፣ የደብረብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ እንዲሁም ሌሎች የፌዴራልና የክልል አመራሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት እና ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ እንደተመላከተው ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች ለዘመናት በሀገራችን ውስጥ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታትና ማህበራዊ አንድነትን በማጠናከር ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል። በተለያዩ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ጥናቶችም እነዚህ ሥርዓቶች በማህበረሰቡ ዘንድ ሰፊ ተቀባይነትና ታአማኒነት እንዳላቸው መረጋገጡ ተጠቅሷል።

በዚህ መነሻነትም መንግሥት ለባህላዊ ፍትሕ ሥርዓቶች ትኩረት በመስጠት የሕግ ማዕቀፎችን እና ተቋማዊ ድጋፎችን እያጠናከረ መሆኑ ተገልጿል። እየተገባደደ በሚገኘው በሦስት አመቱ የፍትሕ ትራንሰፎርሜሽን ታቅደው ሲተገበሩ ከቆዩት አስሩ አምዶች ውስጥ አንዱ እና ውጤት እያስገኘ የሚገኘው የመሠረተ ማኅበረሰብ ፍትሕ አገልግሎት አንዱ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም የአማራ ክልልን ጨምሮ ዘጠኝ ክልሎች ለባህላዊ ፍትሕ ሥርዓቶች የሕግ እውቅና መስጠት መቻላቸው ተጠቁሟል።

የባሕል ፍርድ ቤቶች ፍትሕን ወደ ሕዝቡ በማቅረብ፣ ወጪና ጊዜን በመቆጠብ፣ ቀላልና ለማህበረሰቡ የተለመደ ሂደት በመከተል የእውነት ፍለጋን እና የተበላሹ ማህበራዊ ግንኙነቶችን መጠገን የሚያስችሉ ውጤታማ የፍትሕ ሥርዓቶች መሆናቸው እና ከግጭት መፍታት ባለፈም ዘላቂ ሰላምንና ማህበራዊ መተሳሰብን በማጠናከር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተወስቷል።

በአማራ ክልል በ1,170 ቀበሌዎች የባህል ፍርድ ቤት ዳኞች ምርጫ መካሄዱ የተገለጸ ሲሆን፣ ሴቶች በግጭት አፈታትና በማህበራዊ እርቅ ሂደቶች ያላቸውን ጉልህ ሚና በማገናዘብ ከ400 በላይ ሴት ሽማግሌዎች መመረጣቸውም ተጠቅሷል።በሰሜን ሸዋ ዞን ብቻ በ94 ቀበሌዎች 470 ሽማግሌዎች የተመረጡ ሲሆን፣ በ20 ቀበሌዎች የማስቻያ ቦታዎች መዘጋጀታቸው ተገልጿል።

በፕሮግራሙ መጨረሻም ለተመረጡ ሽማግሌዎች የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ሰሥልጠና በይፋ የተጀመረ ሲሆን፣ ይህ ተነሳሽነት ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶችን በማጠናከር ፍትሕን ለማህበረሰቡ ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ እና በማህበረሰብ ደረጃ የሚከሰቱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተመላክቷል።

የፍትሕ ሚኒስቴርን የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆችን እና ድረ-ገፅን ይቀላቀሉ
Website
https://www.justice.gov.et
Facebook
https://www.facebook.com/MOJEthiopia/
(x) Twitter
https://x.com/MOJEthiopia
YouTube channel
https://youtube.com/...3701...
Telegram
https://t.me/fdreattorneyGeneral_external

Photos from FDRE Ministry of Justice/ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር's post 30/05/2026

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዐት እና የማስረጃ ሕጉን ለማስፈጸም የሚረዱ ተግባራትን ለማከናወን የሥራ ቡድኖች ተቋቁመው ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደረገ
*************************
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዐት እና የማስረጃ ሕጉ በሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት ሕጉ የወጣበትን ዓላማ ሊያሳካ በሚያስችል መልኩ ተግባራዊ መደረግ ያለበት መሆኑን በመገንዘብ ሕጉን ለማስፈጸም የሚረዱ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ለማከናወን የማስፈጸሚያ ሕጎች አርቃቂ የሥራ ቡድንና የሥልጠና ሰነድ ዝግጅት የሥራ ቡድን በማቋቋም እንዲሁም የሥራ መመሪያ በመስጠት ቡድኖቹ ወደ ሥራ እንዲገቡ አድርጓል።

የማስፈጸሚያ ሕጎች አርቃቂ የሥራ ቡድን የፍትሕ ሚኒስቴር በሕጉ እንዲያወጣቸው የሚጠበቁትን የተለያዩ መመሪያዎች የሚያዘጋጅ ሲሆን፤ የሥልጠና ሰነድ ዝግጅት የሥራ ቡድን በወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዐት እና የማስረጃ ሕጉ ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለፍትሕ አካላት ለሚሰጠው ሥልጠና ጥቅም ላይ የሚውል ደረጃውን የጠበቀ የሥልጠና ሰነድ የሚያዘጋጅ ይሆናል።

በተያያዘም ህጉን በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ታትሞ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትም እየተከናወኑ መሆኑ ታውቋል፡፡

በቀጣይም በተዘጋጀ ዝርዝር የማስፈጸሚያ እቅድ መሰረት በፌዴራል እና በክልሎች ለሚገኙ የፍትሕ አካላት በወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዐት እና የማስረጃ ሕጉ ላይ ሥልጠና በመስጠት ወደ ስራ እንዲገባ የሚደረግ ይሆናል።

የፍትሕ ሚኒስቴርን የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆችን እና ድረ-ገፅን ይቀላቀሉ
Website
https://www.justice.gov.et
Facebook
https://www.facebook.com/MOJEthiopia/
(x) Twitter
https://x.com/MOJEthiopia
YouTube channel
https://youtube.com/...3701...
Telegram
https://t.me/fdreattorneyGeneral_external

Photos from FDRE Ministry of Justice/ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር's post 29/05/2026

ማስታወቂያ

ንቃተ-ሕግ 29/05/2026

የተከበራችሁ የፍትሕ ሚኒስቴር የፌስቡክ ገፅ ተከታዮች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለ2019 ዓ.ም ለሕብረተሰቡ ንቃተ ሕግ ለመስጠት የፍላጎት ዳሰሳ ለማድረግ ያተዘጋጀውን መጠይቅ ከዚህ በታች የተዘጋጀውን ሊንክ በመጫን እንድትሞሉ እየጠየቀ ተቋማችን የማህበረሰብ ተሳትፎን እና ንቃተ-ህግን በአዲስ ዕይታ ለመቃኘት እያደረገ ባለው ሂደት ተሳታፊ እንድትሆኑ ይጋብዛል፡፡

ንቃተ-ሕግ የ2019 ዓ/ም በጀት ዓመት ለሕብረተሰቡ የሚሰጥ የንቃተ ሕግ ፍላጎት ዳሰሳ ጥናት መጠይቅ- ፍትሕ ሚኒስቴር በአዋጅ ቁጥር 943/2008 (በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀፅ 40) በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መ.....

Photos from FDRE Ministry of Justice/ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር's post 28/05/2026

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ሕግ ሥነ- ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አወጣጥ ሒደት ዉስጥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተጫወቱት ሚና ምስጋና ቀረበ
************************
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፍትሕ ዘርፉን ከመደገፍ አንፃር በተከናወኑ ተግባራት እና በቀጣይ ትኩረት ሊደረግባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ሎሜ በደዎን ጨምሮ የመንግስት ረዳት ተጠሪ፣ የሕግና ፍትሕ ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት፣ የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሐና አርአያስላሴ፣ ሚኒስትር ዲኤታዎች ፤የተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች እና ሌሎች የተቋሙ አመራሮች በተገኙበት ግንቦት 20 ቀን 2018 ዓ.ም ውይይት ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ሎሜ በደዎ እንደገለፁት የፍትሕ ስርዓቱን ለማዘመንና ተደራሽ ለማድረግ ብሎም የጎደለውን ለመሙላት በምክር ቤቱ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየቱን ገልፀው የተሰሩ ስራዎችን በዚህ ልክ በየምዕራፉ በመፈተሽ የተገኙ ውጤቶችን እያላቁ መሄድ የሚኖረው ትርጉም የጎላ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

አያይዘዉም በምክር ቤቱ ከፀደቁ 1400 በላይ ሕጎች ዉስጥ 200 ያህሉ ከለዉጡ ወዲህ የወጡ መሆናቸዉን ጠቁመዉ ከእነዚህ ሕጎች ዉስጥ የወንጀል ስነ-ሥርዓትና የማስረጃ አዋጅ 1410/2018 ዋነኛዉ መሆኑን ያነሱት ምክትል አፈ-ጉባኤዋ ህጉ ከመፅደቁ በፊት የወሰደዉ ጊዜ ቀላል የማይባልና የምክር ቤት አባላቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሰፊ ጊዜያቸዉን ሰጥተዉና ሰፊ ዉይይት በማድረግ የሕዝብን የፍትሕ ጥያቄ ለመመለስ በሚያስችል መልኩ ሊወጣ መቻሉን አንስተዉ ለዚህ አዋጅ መሳካት አስተዋፅኦ ያደረጉ የሕግና ፍትሕ ቋሚ ኮሚቴ፣ ለፍትሕ ሚኒስቴርና ለሌሎች የምክር ቤቱ አባላት ብሎም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋና በማቅረብ በቀጣይም የበቁና ወቅቱን የዋጁ ሕጎች ለማዉጣት ሰፋፊ ጥረት የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሐና አርአያስላሴ በበኩላቸዉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተደረጉ የፍትሕ ማሻሻያ ስራዎች በተለይም የሕዝቡን ውክልና ያረጋገጠና የአስፈፃሚ አካላት ሚና በሕግ የተገደበ መሆኑንና የሕዝቡን ውክልና ያረጋገጠ በማድረግ ረገድ ምክር ቤቱ የነበረው ሚናና ያበረከተው አስተዋፅኦ እጅጉን የጎላ እንደነበር ገልፀዋል ።

አክለውም ምክር ቤቱ በፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ በተለይም የባሕላዊ የፍትሕ ስርአት እውቅና እንዲያገኙና እንዲተገበሩ በማድረግ የነበረው ክትትል፣ የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ሕጉ በፌደራልና በክልሎች እንዲተገበሩ በማድረግ ሂደት የነበረው ሚና ፣ መሠረታዊ የሕግ ማሻሻያዎች የተደረጉበት እና በተለይም በቅርቡ የፀደቀውን የወንጀል ስነ-ስርዓትና የማስረጃ ሕግ እንዲወጣ ምክር ቤቱ ያደረገው አስተዋፅኦ እጅጉን የሚያኮራ እንደነበር በመግለፅ ለዚህም ከፍተኛ አክብሮትና ምስጋና አቅርበዋል።

በተጨማሪም የወንጀል ስነ-ስርዓትና የማስረጃ ሕግ ይዞት የመጣውን የወንጀል ፍትሕ ፓሊሲ በተሟላ መልኩ ለመተግበር የሚያስችል ዝርዝር የአፈፃፀም ዕቅድ ወጥቶ ወደስራ መግባቱ ተገልፆል።

በዉይይቱ ላይ የህሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፍትሕ ዘርፉን ከመደገፍ አንፃር የነበረዉ ሚና፣የተገኙ ዉጤቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በሚመለከት በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግስት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ አማካኝነት ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን፤ የምክር ቤቱ ሚና በሆኑት የህግ ማውጣ፣ ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም በዉክልና ዙሪያ ያከናወኗቸዉን ተግባራት በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን በነዚህ ተግባራት ዙሪያ ምክር ቤቱ የነበረዉ ሚና እጅጉን የሚበረታታና መሬት የረገጠ እንደነበር አንስተዋል፡፡

በጥቅሉ በቀጣይ የተሻለ የሕግ አወጣጥ ሂደትን በመከተልና አሰራሩን ዲጂታላይዝ በማድረግ በህብረተሰቡ ዘንድ ተዓማኒነት ያለው የፍትሕ ስርዓት ለመገንባት የሕዝቡን የሕግ ግንዛቤ ለማሳደግ የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተገለፀ ሲሆን፤ የሚወጡ ሕጎች ጥራታቸዉን የጠበቁና አሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ ሒደት ዉስጥ የምክር ቤት ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመላክቷል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴርን የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆችን እና ድረ-ገፅን ይቀላቀሉ
Website
https://www.justice.gov.et
Facebook
https://www.facebook.com/MOJEthiopia/
(x) Twitter
https://x.com/MOJEthiopia
YouTube channel
https://youtube.com/...3701...
Telegram
https://t.me/fdreattorneyGeneral_external

27/05/2026
Want your business to be the top-listed Government Service in Addis Ababa?

Click here to claim your Sponsored Listing.

Location

Telephone

Address


Bambis, Jomo Kenyatta Avenue
Addis Ababa
P.O.BOX1370

Opening Hours

Monday 09:00 - 17:00
Tuesday 02:30 - 17:30
Wednesday 09:00 - 17:30
Thursday 09:00 - 17:30
Friday 02:30 - 17:00