15/05/2020
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 27 ፓርቲዎችን ሰረዘ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እስከ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በቀድሞ ህግ ሰርተፍኬት የነበራቸው እና በቀድሞው ህግ ምዝገባ ጀምረው ለነበሩ 106 ፓርቲዎች በአዲሱ ህግ ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን እንዲያሟሉ በደብዳቤ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ ከቦርዱ ደብዳቤ ከደረሳቸው 106 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 76 የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰነዶችን ያቀረቡ ሲሆን በሕጉ መሠረት ተሟልቶ የቀረበ ስለመሆኑ እየተመረመረ ይገኛል፡፡
ምርመራውም
• ፓርቲዎቹ በደብዳቤ የተገለጸላቸውን ነጥቦች ሁሉንም ማሟላታቸውን ማረጋገጥ ( የህገደንብ ለውጥ ጠቅላላ ጉባኤ ሰነዶች አቀራረብ፣ የመስራቶች ፊርማ … የመሳሰሉት)
• የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕጉ መሠረት ማሟላት የሚገባቸውን የመሥራች አባላት ብዛት ትክክለኛነትን ለመፈተሽ ካቀረቡት የመሥራች አባላት ዝርዝር ናሙና የማውጣት
• ናሙናዎቹ በትክክል ግለሰቦቹ የተፈረሙ መሆናቸውን ወደተፈረሙበት ቦታ በመላክ ማረጋገጥ
• የህገ ደንብ ለውጦችና፣ የጠቅላላ ጉባኤ ሰነዶች በትክክል መያያዛቸውን ማረጋገጥን ያጠቃልላል፡፡
ይህ እንደተጠናቀቀም ሰነዶቻቸው ካስገቡት 76 ፓርቲዎች መካከል ምን ያህሎቹ መስፈርት እንዳሟሉ በቦርዱ ይፋ የሚደረግ ይሆናል፡፡
ነገር ግን የሚጠበቅባቸውን ሰነድ ማስገባት ያልቻሉ እና ጊዜ እንዲራዘምላቸው የጠየቁ 15 [edited] የፓለቲካ ፓርቲዎች ሲኖሩ ከነዚህ ፓርቲዎች መካከል ከስር የተጠቀሱት የ13ቱ አጥጋቢ ምክንያት ባለማቅረባቸው እንዲሰረዙ ቦርዱ ወስኗል፡፡
የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነት ሳያገኙ የተሰረዙ ፓርቲዎች ዝርዝር የሚከተለው ነው
1. የኢትዮጵያውን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ (ኢዴአን) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ፣ ጉባኤ ያላካሄደ
2. የገዳ ስርአት አራማጅ ፓርቲ (ገሥአፓ) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
3. የየም ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ( የብዴን) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ፣ ጉባኤ ያላካሄደ
4. የደንጣ ዱባሞ ክችንችላ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት - የመስራች አባላት ዝርዝርም ያላቀረበ፣ ጉባኤ ያላካሄደ
5. የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረስ ( ኮንግረስ) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
6. የትግሪ ወርጂ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ( ትወብዴድ) - ጠቅላላ ጉባኤ ያላካሄደ
7. የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት (መአህድ) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ፣ ጉባኤም ያላካሄደ
8. የኢትዮጵያን አንድነት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኢአዴድ) - ጠቅላላ ጉባኤ ያላካሄደ
9. የመላው አማራ ህዝብ ፓርቲ (መዐሕፓ) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
10. የኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
11. የደቡብ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኮንግረስ ( ደቡብ ኮንግረስ) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
12. የሸኮና አካባቢው ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ሸአሕዲድ) -ጠቅላላ ጉባኤ ያላካሄደ
13. ነጻነትና ሰላም ለኢትዮጵያ ህብረት ፓርቲ ( ነጻነትናሰላም) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
በሌላ በኩል ሌሎች 14 ፓርቲዎች ደግሞ ከቦርዱ በተደረገው ጥሪ መሰረት ሰነዶቻቸውን ከነአካቴው ያላቀረቡ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር መዋሃዳቸውን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የነዚህ 14 ፓርቲዎች እንዲሰረዙ ቦርዱ ወስኗል፡፡
በመሆኑም ሰነድ ባለማምጣታቸው እንዲሰረዙ የተሰወኑት ፓርቲዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ
2. መላው ኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
3. የከምባታ ሕዝቦች ኮንግረስ
4. የሐድያ ብሔር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት
5. የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት
6. የዲል ወቢ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ
7. የቤንች ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት
8. የስልጤ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
9. የአፋር ሕዝብ ነፃነት ፓርቲ
10. የሱማሌ አንድነት ፓርቲ
11. ነፃነት ለአንድነትና ለፍትሕ ፓርቲ
12. ብሔራዊ ተሀድሶ ለሰላም ልማት
13. የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ህብረት
14. የጋምቤላ ክልላዊ ንቅናቄ
ሁለት ፓርቲዎች ሰነዶችን ማቅረብ አለመቻላቸው በፓርቲው የውስጥ ችግር የተነሳ መሆኑ ስለታመነበት ጠቅላላ ጉባኤያቸውን የኮቪድ ወረርሽን በሚያበቃበት ወቅት አንዲያከናውኑ ቦርዱ ሲወስን ሌሎች ሰነዶቻቸው ግን ከላይ በተጠቀሰው መንገድ እየተገመገሙ ይገኛል፡፡
በልዩ ሁኔታ የሰነድ ካስገቡ ፓርቲዎች ጋር ሰነዶች እንዲታይላቸው የተደረጉ ፓርቲዎች
1. ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ( ኢዴፓ)
2. ወለኔ ህዝቦች ፓርቲ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
28/04/2020
የምርጫ ጊዜን የማራዘም ጉዳይ፡ ብቸኛው ህገ መንግስታዊ የመዉጪያ መንገድ
(በዳ. ቡልቻ)
ምርጫ ቦርድ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የ2012 መደበኛ አገራዊ ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል መግለጹን ተከትሎ የምርጫ ጊዜን ማራዘም የሚቻልበት ህጋዊ ሁኔታና ሥርዓት ላይ በርካታ አስተያየቶች ሲሰጡ ሰንብተዋል፡፡ አሁን ከተፈጠረው ሕገ መንግስታዊ አጣብቅኝ ውስጥ ለመውጣት ሁለት አማራጮች እንዳሉም በሰፊው ሲነገር አይተናል፤ አንብበናል፡፡ አንደኛው፡ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 60 መሰርት ፓርላማውን መበተንና የአደራ መንግስት ማቋቋም የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው፡ በአንቀፅ 93 መሰረት የአስቸከኳይ ጊዜ አዋጅን በማወጅ/የታወገውን በማራዘም/ የምርጫ ጊዜን ማራዘም እንደሚቻል ይመክራሉ፡፡ በኔ አስተያየት ሁለቱም አማራጮች ወይም ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎች መደበኛ የምርጫ ጊዜን ለማራዘም የሚያስችሉ አይደሉም፡፡ ሁለቱም መንገዶች ብዙ ህገ መንግስታዊ ጥያቄዎችን እንደሚያስነሱ አስተያየት ሰጪዎቹም ቢሆኑ ሳያነሱ አላለፉም፡፡
የህገ መንግስቱ አንቀፅ 54(1) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በየአምስት ዓመት ጊዜውን ጠብቆ በሚካሄድ ምርጫ እንደሚመረጡ ይደነግጋል፡፡ የምርጫ ጊዜ የሚራዘምበት ሁኔታና አካሄድ እንዲሁም የማራዘም ስልጣን የማንኛው የመንግስት አካል እንደሆነ ምንም የተገለፀ ነገር የለም፡፡ ሕገ ምንግስቱ ምርጫ በምንም ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ጊዜውን ጠብቆ መካሄድ ያለበት እና በየትኛውም ሁኔታና ምክንያት መራዘም ወይም መተላለፍ አይችልም የሚል አቋም የወሰደ ይመስላል፡፡ ሆኖም ግን አገርቷ ካቅም በላይ በሆነ ሁኔታ እና ምክንያት ጊዜውን ጠብቃ ምርጫ ማካሔድ ካልቻለችስ ምን ይደረጋል? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይገባል፡፡ አሁን አገሪቷን የገጠማት ሁኔታ ዐይነት ማለት ነው፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የዘንድሮን ምርጫ ጊዜውን ጠብቆ ማካሄድ እንደማይቻል ከሞላ ጎደል ሁሉም የተስማማበት ጉዳይ ይመስላል፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ የችግር ወቅትም ቢሆን ምርጫ መራዘም የለበትም ብለው ያካሄዱ ወይም በዝግጅት ላይ ያሉ ሀገሮች አሉ፡፡ ደቡብ ኮሪያን እንደምሳሌ ማነሳት ይቻላል፡፡ ወደ እኛ ጉዳይ ሲመለስ፤ በወረርሽኙ ምክንያት የምርጫው ጊዜ መራዘሙ የግድ ከሆነ፤ ህገ መንግስታዊ ሥልጣን ማክበርና የተቀመጠውን ሥርዓት (ካለ) መከተል የግድ ይላል፡፡ አገሪቷ ችግር ገጥሟታልና የምርጫው ጊዜ ይራዘም በሚል ብቻ የሚኬድበት ጉዳይ ሊሆን አይችልም፡፡ የምርጫ ጊዜን ማራዘም ሕገ መንግስቱ ይፈቅዳል ወይ? የማራዘም ሥልጣንስ የማን ነው? እንዴትና በምን አኳኃን? ለምን ያህል ጊዜ? የሚሉ ጥያቄዎች በማያሻማ መልኩ መመለስ አለባቸው፡፡ ከላይ የቀረቡ ሁለቱ የመፍትሔ ሀሳቦች ለነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መለስ የሚሰጡ አይደሉም፡፡
1. በአንደኛ ደረጃ የቀረበው የሕገ መንግስቱን አንቀፅ 60ን መሠረት ያደረገ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ የስልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሄድ በምክር ቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱን ሊበትን እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ይህ ድንጋጌ በአንድ የሥልጣን/የምርጫ ዘመን ውስጥ ስለሚካሄድን ምረጫ እንጂ ጊዜውን ጠብቆ በየአምስት ዓመቱ ስለሚመጣ መደበኛ ምርጫን የሚመለከት አይደለም፡፡ መጀመሪያውኑ የአንድ መንግስት የሥልጣን ዘመን ከተገባደደ መደበኛ ምርጫን ማካሄድ እንጂ ምክር ቤት ማፍረስም ሆነ አድስ ምርጫ መጥራት አላስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም በአንቀፅ 60 መሠረት የሚካሄድ አድስ ምርጫ በአንድ የምርጫ ዘመን ውስጥ ስለሚደረግ ምርጫን የሚመለከት እንጂ የሥልጣን ዘመኑ ከተገባደደ ቦኃላ የሚከናወን መደበኛ ምርጫን እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ይህንን የህገ መንግስቱን ድንጋጌ መሰረት አድርጎ መደበኛ የምርጫ ጊዜን ማራዘም ኢ-ዲሞክራሲያዊና ኢ-ህገ መንግስታዊ ይሆናል ማለት ነው፡፡
2. በሁለተኛነት እንደአማራጭ የሚነሳው፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በማወጅ ወይም የታወጀውን በማደስ/በማራዘም የምርጫ ጊዜን ማራዘም ይቻላል የሚል ነው፡፡ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 93(1ሀ) ‹የውጭ ወረራ ሲያገጥም ወይም ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የህግ ማስከበር ሁኔታ ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን ፤ ማንኛውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የህዝብ ጤንነትን አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲያጋጥም› የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በማወጅ ‹ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለማስወገድ ተፈላጊ ሆኖ በተገኘ ደረጃ› መንግስት የፖለትካና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን መገደብና ማገድ እንደሚችል ተደነግጓል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ ሁለት ሀሳቦችን ማየት መልካም ይሆናል፡፡ አንደኛው፤ የምርጫን ጊዜ ለማራዘም ተብሎ ብቻ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማወጅ ወይም ማራዘም ሕገ መንግስቱ አይፈቅድም፡፡ ኮሮና ላሁን ከባድ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ችግር ቢሆንም በነሐሴና መስከረም ወራቶች ውስጥ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ሊያሳውጅ/ሊያሳድስ የሚያስገድድ ላይሆን ይችላል፡፡ ሁለተኛውና ዋነኛው ነጥብ ግን፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የዜጎች የመምረጥ መብትን ጭምር ማገድ የሚያስችል ቢሆንም፤ የምርጫ ጊዜን በማራዘም የሥልጣን ዘመኑ ለተገባደደ መንግስት ሕገ መንግስታዊ ሥልጣን የሚያስገኝለት አይደለም፡፡ ሊሆንም አይገባም፡፡ በሌላ አነጋገር አንድ የሥልጣን ዘመኑን የጨረሰ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በማወጅ የሥልጣን ዘመኑን ሊያራዝም የሚችልበት ሕጋዊ አሰራር የለም፡፡
በመሠረቱ እየቀረቡ ያሉት ሁለቱ የመውጪያ ሀሳቦች ሌሎች የህገ መንግስቱን ድንጋጌዎችን ያላግባብ በምትርጎም የቀረቡ እንጂ ለጉዳዩ በቀጥተኛነት አግባብነት ያላቸው ድንጋጌዎች መሠረት ያደረጉ አይደሉም፡፡ ለጉዳዩ አግባብነት ያለው ድንጋጌ አንቀጽ 54/1 ግልፅና የማያሻማ ሆኖ እያለ አግባብነት የሌላቸው ሌሎች አንቀፆችን በመሳብ አግባብነት የሌለው ትርጉም መስጠት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ባጠቃላይ ይህ አንቀፅ ትርጉም የሚያስፈልገው አይደለም፡፡ ምርጫ ጊዜውን ጠብቆ በየአምስት አመቱ መካሄድ እንዳለበት ያስገድዳል፡፡ ማራዘምንም ሆነ ማስተላለፍን በምንም ሁኔታ አልፈቀደም፡፡ የሚሰጡ አስተያየቶች ለጉዳዩ ህገ መግስታዊ መፍትሔ ለመስጠት ከመሻት የመነጩ እንጂ የተገለፁት ድንጋጌዎች አግባብነት ኖሯቸው አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ በራሱ ኢ-ሕገ ምነግስታዊ እና ተቀባየነት የሌለው አካሄድ ነው፡፡
ብቸኛው ህገ መንግስታዊ የመውጪያ መንገድ
አሁን የገጠመውን አጣብቅኝ ሁኔታ ከህገ መንግስታዊ ማዕቀፍና አሠራር ሳንወጣ እንዴት የምርጫ ጊዜን ለተወሰነ ጊዜ በማራዘም፤ ነፃ ፍትሐዊ እና ሰላማዊ ምርጫን ማካሄድ ይቻላል ለሚለው ምናልባትም ብቸኛው መውጪያ መንገድ ሕገ መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌሎች ሕገ መግስታዊ ያልሆኑ (Extra constitutional solutions) እንደፖለትካዊ መፍትሔዎችን ያሉ ሳይጨምር ማለት ነው፡፡
አንድ ሕገ መንግስት ሲቀርፅ በወቅቱ ያልታዩ ጉዳዮች ሲከሰቱ ወይም በየጊዜው በሚፈጠሩ አዳድስ ሁኔታዎችና ለውጦች ለማካተትና ለማስተዳደር ሲባል ሕገ መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ ሕገ መንግስት የማይሻሻል ቋሚ ሰነድ ሳይሆን አገርቷ የደረሰችበትን የዕድገት ደረጃ ጋር ለማስከድ ወይም በየጊዜውም የሚያጋጥሙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመፍታት ሲባል በየጊዜው እየተሻሻለና እያደገ የሚሄድ ወሳኝ ሰነድ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሕገ መንግስቱ ራሱ የማሻሻያ ሥርዓቶችን የሚደነግገው፡፡ ሕገ መንግስታዊ ማሻሻያ ሕገ መንግስት ከሚያድግባቸውና ህገ መንግስታዊነት ከሚጎለብትባቸው መንገዶች አንዱ ነው የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡
በመሆኑም የህገ መንግስቱን አንቀጽ 54 ላይ የተወሰኑ ማሻሻያ በማድረግ መደበኛ የምርጫ ጊዜን ማራዘም የሚቻለበት ሁኔታና ሥርዓት መደንገግ የግድ ይላል፡፡ እዚህ ላይ የምርጫ ጊዜን በሆነ ባልሆነ ምክንያት እንደዋዛ ማራዘም የሚቻልበት ሁኔታ መፈቀድ የሌለበት መሆኑ ይታመናል፡፡ ካገር አቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ሲከሰትና ምርጫን ማካሄድ በምንም የማይቻል መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ መፈቀድ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ያለበለዚያ ይህ በራሱ የሕገ መገመንግስቱን ተገማችነት በመጉዳት ሥርዓቱን ችግር ላይ ሊጥል ይችላል፡፡ በማሻሻያውም የምርጫው ጊዜ ለምን ያህል ጊዜ መራዘም እንዳለበትና የማራዘሙ ሥልጣን የማን መሆን እንዳለበት መወሰን ይገባል፡፡ ጊዜው ቢበዛ ከስድስት ወር መብለጥ እንደሌለበት የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ ያሳያል፡፡ ምርጫው እስክካሄድ በአንቀፅ 60/5/ መሠረት የአደራ መንግስት አገሪቷን ሊያስተዳድራት ይችላል፡፡
ህገ መንግስታዊ ማሻሻያው በህገ መንግስቱ አንቀጽ 105(2) ሥር የተደነገገውን ሥርዓት ተከትሎ መከናወን አለበት፡፡ በዚሁ መሠረት የፌደራል ሁለቱ ምክር ቤቶች በጋራ ስብሰባ በ2/3ኛ ድምፅ እና 2/3ኛ የፌደሬሽኑ የክልል ምክር ቤቶች (ስድስት ክልሎች) በየፊናቸው በሚያካሂዱት ጉባዔ በአብላጫ ድምፅ ማሻሻውን መደገፍ አለባቸው፡፡
-//-
17/04/2020
የኮቪድ-19 ቀውስ በኢትዮጵያ የሚያስከትለውን የፖለቲካ አስተሳሰብ አያያዝ
ኢትዮጵያ በኮቪድ-19 በሽታ ወረርሽኝ ምክንያት ለነሐሴ ታቅዶ የነበረውን ምርጫ ላልተወሰነ ጊዜ አስተላልፋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለች። ሃገሪቱ ወደ መድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ እየተንገ...
13/04/2020
ባለፉት 24 ሰዓታት የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 247 ግለሰቦች መካከል፤ ሶስቱ የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው ተረጋግጧል።
__________
ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ከተረጋገጠባቸው ግለሰቦች መካከል ተጨማሪ አራት ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።
ቫይረሱ የተገኘባቸው ሶስቱም ግለሰቦች ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ የላቸውም።ሶስቱም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ናቸው።
ከግለሰቦቹ መካከል ሁለቱ ወንዶች ሲሆኑ፤ሁለቱም ከበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ እንዳላቸው ገና አልተረጋገጠም።
አንዷ የ23 ዓመት እድሜ ያላት ስትሆን ከበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ እንዳላት ተረጋግጧል።
ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 74 ደርሷል።
ቫይረሱ እንዳለባቸው ከተረገጠባቸው ግለሰቦች መካካል ተጨማሪ አራት ግለሰቦች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን፤ይህን ተከትሎም በአጠቃለይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ወደ 14 ከፍ ብሏል።
በኢትዮጵያ እስካሁን ለ4 ሺህ 110 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸዋል።
11/04/2020
በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 345 ግለሰቦች መካከል አራቱ የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው ተረጋገጠ። ቫይረሱ ተገኝቶባቸው ክትትል እያደረጉ ከሚገኙት መካከል 10 ግለሰቦች አገግመዋል።
___________
እስካሁን ባለው ሂደት በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ለ3,500 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተከናውኗል።
ዛሬ ቫይረሱ የተገኘባቸው አራቱም ግለሰቦች ኢትዮጵያዊያን ናቸው።
ሁለቱ ወንድ ሁለቱ ደግሞ ሴቶች ሲሆኑ ሶስቱ የጉዞ ታሪክ ያላቸው ናቸው።
ከእነዚህም መካከል አንድ የ30 ዓመት ሴትና አንድ የ29 ዓመት ወንድ ኢትዮጵያዊያን ከዱባይ መጥተው በለይቶ ማቆያ ክትትል ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው፡፡
አንድ የ33 ዓመት ሴት ኢትዮጵያዊት ደግሞ የአሜሪካ አገር የጉዞ ታሪክ ያላት ናት።
ሌላኛው ግለሰብ የ42 ዓመት እድሜ ያለው ኢትዮጵያዊ ነው።
ግለሰቡ የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ የሌለው ሲሆን፤ በህመሙ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ እንዳለውና እንደሌለው እየተጣራ ነው።
በሌላ ዜና ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋግጦ ክትትል እያደረጉ ከሚገኙ ግለሰቦች መካከል ተጨማሪ ስድስት ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።
ይህን ተከትሎም በአጠቃላይ ከህመሙ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ወደ 10 ከፍ ብሏል።
በጽኑ ህሙማን ክፍል ክትትል ሲያደርጉ የነበሩት የ65 ዓመት ኢትዮጵያዊት ትናንት ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፤ አሁን ላይ በጽኑ ህሙማን ክፍል ክትትል የሚደረግላቸው ህሙማን የሉም።