08/10/2026
ቢሮው ከጥቅምት 01/2019 ዓ.ም ጀምሮ ለሚደረገዉ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባላት ምዝገባ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ዉይይት አደረገ ፡፡
አአ ጤና ቢሮ መስከረም 28/ 2019 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ከጥቅምት 01 እስከ ህዳር 30/2019 ዓ.ም ለሚያደርገዉ የአባላት ምዝገባ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዉይይት ያደረገ ሲሆን ህብረተሰቡን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ ለማድረግ በቅንጅት መሰራቱ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳመጣ በዉይይቲ ተጠቁሟል ።
በቢሮ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ኢብራሂም ተካ ባለፉት ዓመታት በርካታ የከተማችን ነዋሪዎችን በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ በማድረግ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሰራቱን ገልፀዉ
የጤና መድህን አላማው በመረዳዳት እና በመደጋገፍ መርህን ያደረገ መሆኑን አንስተዉ አባላት በዓመት አንድ ጊዜ በሚያዋጡት መዋጮ እንደ ህመማቸው አይነት ያለ ስጋት አመቱን ሙሉ አገልግሎቱን ለማግኘት እንደሚያስችላቸውና በቀጣይ በሚደረገዉ ምዝገባ ሁሉም ባለድርሻ አካል ኃላፊነቱን እንዲወጣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አክለዉም በዘንድሮዉ አገልግሎቱን ይበልጥ ለማሻሻል የከተማ አስተዳደሩ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ መመደቡንና የማህበረሰቡን የጤና አገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያግዙ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙና ነጋዴዉ ማህበረሰብም ከንግድ ፈቃድ እድሳት ጋር በተያያዘ የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲወጣ ከአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ እና ከንግድ ቢሮ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በኢትዮጲያ ጤና መድህን አገልግሎት የአዲስ አበባ ክላስተር ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ አይካ በበኩላቸው የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን መርህ የመረዳዳት ባህልን የሚያጎለብት መሆኑን እና አባላት ባላቸው ገቢ መጠን በመክፈል የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት ለውጤታማነቱ በቅንጅት እና በትብብር እንዲሰረም ጥሪ አቅርበዋል።