10/10/2026
"የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት መሸጋገር ይገባል" ዶ/ር አብዱ ሁሴን
ለዘመናት በእርዳታ ጥገኝነት ውስጥ የቆየውን ሀገራዊ አስተሳሰብ በመቀየር፣ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም በመሸፈንና የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የሀገርን ክብርና ነፃነት ማጠናከር ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አብዱ ሁሴን ገለጹ።
«ከተረጂነት ወደ ምርታማነት» በሚል መሪ ሐሳብ እየተተገበረ ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም የመሸፈን ኢኒሼቲቭ አፈጻጸም በመስክ ለመደገፍ በየዞኑ የተሰማራው ቡድን ሪፖርት ዶ/ር አብዱ ሁሴን በተገኙበት ተገምግሟል።
ዶ/ር አብዱ እንደገለጹት፣ በሀገርም ሆነ በአማራ ክልል ለረጅም ጊዜ የቆየውን የተረጂነት አስተሳሰብ ለመቀየር በየደረጃው በተደረገው መግባባት የተጀመሩት ሥራዎች አበረታች ናቸው። በተለይም በምግብ ራስን ለመቻልና ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የተቀረጹ የልማት እርምጃዎችን በተግባር ማሳካት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የአደጋ ስጋት ፈንድ ማሰባሰብ፣ ምርትና እህል በማሰባሰብ ለዕለት ደራሽና ለመጠባበቂያ የሚሆን የእህል ክምችት መያዝ፣ የእህል ማከማቻ መጋዘኖችን ማዘጋጀትና ተገቢውን ድጋፍ ማግኘት የሚገባቸውን ተረጂዎች በብሔራዊ መታወቂያ መረጃ ላይ ተመሥርቶ ማጥራት የሚጠይቁ ተግባራት ናቸው። እነዚህም በተቋማዊና ሥርዓታዊ አሠራር መከናወን እንዳለባቸው አመላክተዋል።
በተጨማሪም፣ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋዎች ለሚጎዳው ማኅበረሰብ በራስ አቅም ድጋፍ ለማድረግ የተሟላ ዝግጅት መኖሩን በየደረጃው በጥብቅ ክትትል ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ዛሬ ለተረጂነት ያልተጋለጠ ማኅበረሰብም በተጋላጭነቱ መጠን ላይ የተመሠረተ የአካባቢ ልማት ካልተከናወነ ለወደፊት ለአደጋ ሊጋለጥ እንደሚችል በመገንዘብ፣ ተጋላጭ አካባቢዎችን ለይቶ የማልማት ሥራ መሥራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ራሳቸውንና ማኅበረሰቡን ከጥገኝነትና ከተረጂነት አስተሳሰብ በማላቀቅ ወደ ራስን መቻል የሚያሸጋግሩ ተግባራትን ማጠናከር፣ የመረጃ ጥራትን ማረጋገጥና የድጋፍ አሰጣጡን በተከታታይ መከታተል እንደሚገባ አሳስበዋል።
በቀጣይም በመስክ በተገኙ ግኝቶች መሠረት በኢኒሼቲቩ የተቀረጹትን የፍኖተ ካርታና የትግበራ ፓኬጆች በግልጽነትና በተቀናጀ አሠራር ለመፈጸም፣ የቴክኒክ ኮሚቴው አባል ተቋማት ቅንጅታቸውን በማጠናከር በየደረጃው ተከታታይ ድጋፍ እንዲያደርጉ አቅጣጫ ሰጥተዋል።