Harari Attorney General /የሐረሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ

Harari Attorney General /የሐረሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ

Share

Harari Attorney General aims to give justice for citizens

22/10/2024

ለዉድ የድህረ ገፃችን ተከታታዮች የሀረሪ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ቢሮ የቀድሞዉ ድህረ ገፅ የተቀየረ ሰለሆነ አዲሱን የድህረ ገፃችን እንድትከታተሉ ስንል በማክበር እንጠይቃለን።

የጠቅላይ አቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነት ዳሬክቶሬት
https://www.facebook.com/profile.php?id=61567193829876&mibextid=ZbWKwL

Photos from Harari Government communication affairs Office's post 19/10/2024
16/10/2024

የአደንዛዥ እፆች እና የህግ ተጠያቂነት በአትዮጵያ
--------------****-------------
የአደንዛዥ እፅ ትርጉም
አድንዛዥ እፅ ማለት ከምግብ እና መጠጥ ውጪ የሆነ ወደ ሰውነት ውስጥ በሚገባ ጊዜ በሰውነት ስራ ላይ አካላዊ ወይም ስነ ልቦናዊ ለውጥ የሚያስከትል ማንኛውም ንጥረ ነገር ነው፡፡ እፆች ህጋዊ የሆኑትን እንደ አልኮል፣ ካፌን እና ትንባሆ እንዲሁም ህጋዊ ያልሆኑ ወይም የተከለከሉ እንደ ካናቢስ፣ ኮኬን እና ሄሮኢን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሳይኮአክቲቭ ንጥረ ነገሮች (Psychoactive drugs) በማዕከላዊ የአዕምሮ ክፍል ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር የሰዎችን አመለካከት እና ባህሪይ ይቀይራሉ፡፡
እነዚህ ንጥረ ነጥሮች በአራት ሊከፈሉ የሚችሉ ሲሆን እነሱም፡- ድብርት ፈጣሪ (Depressants)፣ አነቃቂ ወይም ቀስቃሽ (Stimulants)፣ ሃሉሲኖጅንስ (Hallucinogens) እና ሌሎች (Other) ናቸው፡፡ ድብርት ፈጣሪ ንጥረ ነገሮች የማዕከላዊ አዕምሮ ክፍልን እንቅስሴ ዝቅ በማድረግ ንቃትን ይቀንሳሉ (decrease alertness)፡፡ ቀስቃሽ ንጥረ ነገሮች ደግሞ በተቃራኒው አዕምሮን በማነቃቃት የሰውነትን መነቃቃት ይጨምራሉ (increase the body's state of arousal):: ሃሉሲኖጅንስ በበኩላቸው የሰዎችን ግንዛቤ (perception) በመለወጥ ሰዎች የሌሉ ነገሮችን እንዲሰሙ እና እንዲያዩ ሊያደርጉ ወይም ከእውነት የራቀ ሃሳብ እንዲያስቡ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ የሌሎች (Other) የንጥረ ነገሮች አይነት ስር የሚመደቡት ደግሞ ከላይ የተገለፁት ንጥረ ነገሮች ከአንድ በላዩን ባህሪዎች በአንድ ጊዜ ይዘው ሲገኙ ነው፡፡

የአደንዛዥ እፆች ውጤት/ተፅዕኖ (effects of drugs)
------------------------
አደንዘዥ እፆች በሰዎች ላይ የሚያስከትሉት ውጤት የሰዎችን ሁኔታ ማለትም አካላዊ ሁኔታ፣ እድሜ፣ ፆታ፣ ስሜት፣ አመጋገብ፣ አካላዊ ብቃትና ጤና፣ መጠበቅ (expectation) እንዲሁም እንዴት እና በምን አይነት አካባቢ እንደተወሰዱ መሰረት በማድረግ ከሰው ሰው ሊለያዩ የሚችሉ ሲሆን አንዳንድ ሰዎች ድብርታም፣ ተናዳጅ፣ ቁጡ፣ እንቅልፋም፣የማይነቃቃ (unmotivated)፣ ጭንቀታም ወይም ወሬኛ ይሆናሉ፡፡ በአጠቃላይ አደንዛዥ እፆችን መጠቀም ስሜታዊ እና ማህበራዊ ችግሮችን በማስከተል ሰዎች ከቤተሰባቸው እና ከማህበረሰቡ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳይኖራቸው ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡
በአደንዛዣ እፅ ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች ተጠቃሚዎችን ሲሱ ውስጥ በማስገባት የእፆቹ ጥገኛ ያደርጋሉ፡፡ የአደንዛዥ እፅ ሱስ ማለት አንድ ሰው ራሱን መቆጣጠር እስኪያቅተው ድረስ የሱስ አምጭ ንጥረ ነገሮችን ለመውሰድ ፍላጎት ሲያድርበት እና ችግር የሚያስከትሉ እንደሆነ እያወቀ እነዚህን ንጥረ ነገሮች ሲወስድ ነው፡፡ አደንዛዥ እፆች የሰዎችን ሀሳብ፤ ስሜት፤ እንቅልፍ፤ የምግብ ፍላጎት እና ማህበራዊ ግንኙነትን የመቀየር ውጤት አላቸው፡፡
አእምሮን የሚያነቃቁ አደንዛዥ እፆች በሚወሰዱበት ጊዜ በዋናነት አእምሮ ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር በአካላዊና ስነልቦናዊ ተግባሮች ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ ብዙ ሰዎች የአደንዛዥ እፅ በሚፈጥረው የአእምሮ መነቃቃት እና አመለካከት ለውጥ በመደሰት ይዝናኑበታል፡፡ በመጨረሻም ይህ በመሆኑ ሰዎች ሳያውቁት በተደጋጋሚ በመውሰድ ወደ ልምድ ወይም ሱስ ውስጥ ይገባሉ፡፡

አደንዛዥ እፆችን የተመለከቱ አለም አቀፍ ህጎቸ
----------------------
በአለም አቀፍ ደረጃ አደንዛዥ ዕፆችን መቆጣጠርን በተመለከተ ሶስት ዋና አለም አቀፍ ስምምነቶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም፡፡
1. የናርኮቲክ ንጥረ ነገር ነጠላ ኮንቬክሽን (the Single Convention on Narcotic Drugs of 1961 (as amended in 1972),
2. የሳይኮትሮፒክ ንጥረ ነገሮች ኮንቬክሽን (the Convention on Psychotropic Substances of 1971), እና
3. የተባበሩት መንግስታት ህገ ወጥ የናርኮቲክ እና ሳይኮትሮፒክ እፆችን ላይ የተደረገ ኮንኔክሽን (the United Nations Convention against Illicit Traffic in Narcotic Drugs and Psychotropic Substances of 1988).
እነዚህ ስምምነቶች እርስ በእርስ ተደጋጋፊ እና አንዱ አንዱ የሚያሟሉ ናቸው፡፡

ከእፅ ጋር የተገናኙ ወንጀል ድርጊቶች
-----------------------
ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ አብዛኛው የአለም አገራት የአደንዛዥ እፆችን ጥፋት (offenses) በተለያዩ የወንጀል መለኪያ ቢሆንም በህጎቻቸው ውስጥ አካተው ይገኛሉ፡፡ጥፋቶቹ የአቅርቦት (supply) እንደ እርሻ፣ ማምረት (በፋብሪካ) እና ማዘዋወር እንዲሁም የፍላጎት (demand) እንደ መጠቀም እና መያዝን የሚያካትቱ ናቸው፡፡ ህጎች ተለይተው ጎጂ ናቸው የተባሉ ንጥረ ነገሮችን ወይም አደንዛዥ ዕፆችን ማምረትን፣ ማዘማወርን፣መጠቀም እና መያዝን ወንጀል የሚያደርጉ ሲሆን አተገባበራቸው ከሀገር ሀገር የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁኑና ብሄራዊ ህጎቹ የአለም አቀፍ የህግ ማዕቀፎችን መዋቅር የተከተሉ መሆን አለባቸው፡፡ የተባበሩት መንግስታት የአደንዛዥ እፅና ወንጀል ቢሮ (UNODC) በተባበሩት መንግስታት ስር የአለምን ሰላምና ፀጥታ፣ የሰብዓዊ መብቶች እና እድገትን ለማረጋገገጥ አለምን ከአደንዘዥ እፅ፣ ከወንጀል፣ ከሙስናና ከሽብርተኝነት የመጠበቅ ተልዕኮን ይወጣል፡፡

አደንዛዥ እፆችን የተመለከቱ ህጎች በኢትዮጵያ
------------------------
በሀገራችን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አብዛኛው ወጣት በዚህ ሱስ ወስጥ በመጠመድ ለጤና፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ በመዳረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን በርካታ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለወንጀል ተጠያቂነት በመጋለጥ ላይ ይገኛሉ፡፡
በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ህግ አደንዛዥ እፆችን የተመለከቱ ድንጋጌዎች በሰውና በእንስሳት ጤና ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ነገሮችን ማምረትና በማሰራጨት የሚደረጉ ወንጀሎች ስር ተካቶ ይገኛል፡፡ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 525 ላይ እንደተደነገገው መርዛማ ወይም የናርኮተክና ሣይኮትሮፒክ መድኃነቶችን ወይም እፆችን ማምረት፣ መስራት፣ማዘዋወር ወይም መጠቀም የወንጀል ተጠያቂነቂነትን ያስከትላል፡፡ የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ድርጊቶች በድንጋጌው ስር የተዘረዘሩ ሲሆን እነዚህም፡- ማንም ሰው ልዩ ፍቃድ ሳይኖረው መርዛማ ነገሮችን ወይም ናርኮቲክ ወይም ሳይኮትሮፒክ መድሀኒቶችን ወይም እፆችን ያበቀለ፣ ያመረተ፣ የሰራ፣ የለዋወጠ ወይም የፈበረከ፤ ንጥረ ነገሮቹን ይዞ የተገኘ፣ ወደ ሀገር ያስገባ ወደ ውጪ አገር የላከ፣ ያጓጓዘ፣ ያከማቸ፣ የደለለ፣ የገዛ ለሽያጭ ያቀረበ፣ ያሰራጨ፣ ያዘዋወረ፣ አሳልፎ የሰጠ ወይም ለሌላ ያስገኘ፤ንጥረ ነገሮቹን ለመስሪያነት፣ ማቀነባበሪያነት፣ ማምረቻነት፣ መሸጫነት ወይም ማከፋፈያነት ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሆነበትን ቤቱን ግቢውን ወይም ቦታውን የሰጠ፣ ያከራየ ወይም የፈቀደ ከአምስት ዓመት በማያንስ ፅኑ እስራትና ከአንድ መቶ ሺህ ብር በማይበልት መቀጮ እንደሚቀጣ የወንጀል ህጉ አንቀፅ 525/1 ይደነግጋል፡፡
ቅጣቱን የሚዛከብዱ ሁኔታዎች በአንቀፅ 525/2 ስር የተቀመጡ ሲሆን እነዚህም፡-
 ወንጀሉ የተፈፀመው ለዚሁ ንግድ ወይም በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር አቀፍ ወንጀል ለመፈፀም በተደራጀ የቡድን ወይም የማህበር አባል በሆነ ወይም ይህን ሕገ ወጥ ድርጊት ሙያው አድርጎ በያዘ ሰው እንደሆነ ፤
 ጥፋተኛው የተከለከለውን ህገ ወጥ ነገር ወይም ለዚሁ ዓይነቱ ነገር መጠቀሚያ ቦታ እያወቀ የሰጠው ወይም የፈቀደው በአፍቅሮ ንዋይ፣በወራዳነት ወይም አግባብ በሌለው ሌላ ዓላማ እንደሆነ፤ወይም ተጠቃሚው ህፃን፣ለአካለ መጠን ያልደረሰ ወጣት ወይም አዕምሮው ያልተስተካከለ ወይም የእፅ ሱስ ያለበት እንደሆነ፤
 ወንጀለኛው ወንጀሉን የፈፀመው ሕፃናትን ወይም አዕምሮው ያልተስተካከለ ሰውን ለወንጀል ድርጊቱ አፈፃፀም መጠቀሚያነት በማድረግ እንደሆነ
 ወንጀሉ የተፈፀመው በማረሚያ ቤት፣በትምህርት ቤት ወይም በሌላ ማህበራዊ አገልግሎት ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ ፣ሕፃናት ወይም ወጣት ተማሪዎች ለትምህርት፣ለስፖርት ወይም ለሌሎች ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች በመጠቀሙበት ቦታ እንደሆነ ወይምወንጀለኛው ከዚህ ቀደም በፈፀመው ተመሳሳይ ወንጀል ምክንያት የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎበት የነበረ እንደሆነ ከአምስት አመት በማያንስ ፅኑ እስራት እና ከአንድ መቶ ሺህ በማይበልጥ መቀጮ ይቀጠል፡፡
ስለሆነም ሰዎች አደንዛዥ ዕፆችን የተመለከቱ ክልከላዎችን ባለመተላለፍ እራሱን ከህግ ተጠያቂነት እና ንጥረ ነገሮቹ ከሚያስከትሉት የስነ ልቦና፣ ማህበራዊ እና የጤና ጉዳት ሊጠብቅ ይገባል፡፡

14/10/2024

"ሰንደቃ ዓላማችን ለብሄራዊ አንድነታችን፣ለሉአላዊነታችንና ለኢትዮጰያ ከፍታ" በሚል መሪቃል ጥቅምት 4/2/2017

14/10/2024

የሰንደቅ ዓላማ ሕግ በኢትዮጵያ

1. መግቢያ
ቀደም ሲል የወጡ ሰንደቅ ዓላማን የሚመለከቱ የተለያዩ ሕጎች ተደንግገዉ ይገኛሉ፡፡ ስለ ኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሰንደቅ ዓላማ በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 1 እና 2 የተደነገገ ሲሆን ይህን ሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ተከትለው ቀደም ሲል የወጡ እና በሥራ ላይ ያሉ ሕጎች ሰንደቅ ዓላማን አስመልክቶ የየራሳቸውን ድንጋጌዎች አስፍረዋል፡፡ አሁን ያለው የፌዴራል መንግስት ቅርፅ የሪፐብሊኩ እና የክልሎች ሰንደቅ ዓላማዎች እንዲኖሩ የሚፈቅድ ነው፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ የሰንደቅ ዓላማን ምንነት፣ ታሪካዊ አመጣጥ፣ ስለ ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ ዓርማ እንዲሁም ሰንደቅ አለማ ጋር ተያይዞ የተከለከሉ ተግባራት እና ቅጣት የሚሉትን እንመለከታለን፡፡

2. የሰንደቅ ዓላማ ምንነት
በሀገራችን የሚገኙ አብዛኞቹ መዝገበ ቃላቶች ተመሳሳይ ትርጉም ሰጥተውት የሚገኝ ሲሆን
ሰንደቅ፡ ማለት "ምርኩዝ፣ ምሰሶ፣ በትር፣ ህዝብ "ማለት ሲሆን
ዓላማ፡ "ምልክት፣ የህዝቦች የማንነት መለያ" ማለት ነው፡፡ ይህም ሰንደቅ ዓላማ "የአንድ ሀገር መንግስትና ህዝብ ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ ስልጣን፣ ነፃነት፣ እድገትና ማህበረሰባዊ ትስስር መፍጠሪያ መሳሪያ ነው፡፡" የሰንደቅ ዓላማን ትርጉም ከምልክትነት ከፍ ያለ ነው፡፡ ዜጎች ከሰንደቅ ዓላማው ፊት በቆሙ ቁጥር ልዩ ስሜት ውስጥ የሚገቡት በሀገርና በህዝብ ፊት እንደቆሙ ስለሚቆጥሩ ነው፡፡ ለምሳሌ፡-
• ለሀገራችን ነፃነት የተፋለሙ የጦር ጀግኖቻችን
• ሀገራችንን የወከሉ አትሌቶች በዓለም አደባባይ
የሰንደቅ ዓላማ ከፍ ማለት የህዝብና የሀገር ክብር፣ ነፃነትና ሉዓላዊነት ከፍ ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ሰንደቅ ዓላማ የሀገርና የህዝብ ያለፈ ታሪክ፣ ወቅታዊ ገጽታና የወደፊት ዓላማ ነፀብራቅም ነው፡፡
ለሀገርና ለህዝብ የጠለቀ ፍቅር፣ ክብርና ቁርጠኝነት ያለው ዜጋ የተግባር ልዕልና የሚገለጠውም ሰንደቅ ዓላማውን በሰቀለበት ማማ ከፍታ ነው፡፡ በተቃራኒው የሰንደቅ ዓላማ መውረድ/መረገጥ የሀገርና የህዝብ ሽንፈት ወይም ውርደት ምልክት ነው፡፡
ሰንደቅ ዓላማ የአንድ ሀገርና ህዝብ ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ምልክት (መገለጫ) ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማ የህዝቦች ባህል፣ እምነትና መገለጫ እንዲሆን ተደገርጎ የሚቀረጽ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ፣ የኢንባሲና ቆንስላ ጽ/ቤቶች የሀገሮች ውክልና የሚገለፀው በሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ የኢፌዲሪ ሰንደቅ ዓላማ የሪፐብሊኩ ሉዓላዊነትና የሕዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት መግለጫ ነው፡፡

3. ታሪካዊ አመጣጥ
ሰዎች ከ4000 ዓመታት በፊት ጀምረው የሚገልፃቸውን ምልክት ይጠቀሙ ነበር፡፡ በጥንታዊ ግሪክ ታዋቂ ሰዎች ሲሞቱ፣ ጀግንነት ሲፈፅሙ እና ዘመቻ በሚመሩበት ጊዜ በወቅቱ የብረት ቁራጭ በምልክትነት ያስቀምጡ ነበር፡፡ 2000 ዓመታት በኋላ ከብረት ምልክትነት ቀስ በቀስ ወደ ጨርቅ ባንዲራዎች መጡ፡፡ ከ15ኛው ክ/ዘመን የአውሮፓ ሀገራት ዓለም አቀፍ ዳሰሳ በየሃገራቸው መርከቦች ይህንን ምልክት በመጠቀም በመካከላቸው ሊከሰቱ የሚችሉ ያለ መግባባቶች ለማስወገድ ተጠቅመውበታል፡፡ ቅኝ ገዢዎች፤ በአፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካ እና ኤስያ ነባር ህዝቦችን በስነልቦናም ጭምር የገዢዎቻቸውን አስተሳሰብ እንዲሸከሙ አድርገውበታል፡፡ የሀገሮች መለያ ምልክት (የብሄራዊ ማንነት መገለጫ) እስከ መሆን ደርሷል፡፡ አሁን ላይ ሃገሮች በተለይ በዓለም አቀፍ የባለብዙ ስምምነት አባልነት ላይ ሰንደቅ ዓላማቸውን የሃገራቸው ፖለቲካዊና ማሕበራዊ መገለጫ አድርገው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡

4. ስለ ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ ዓርማ በጠቅላላው
ሰንደቅ ዓላማ የሀገሩና የህዝቡ እኩልነትና አንድነት መገለጫ ነው፡፡ የአንድ ሀገር ህዝብና መንግስት እንደ ህዝብና መንግስት ስለ መኖራቸው፡፡
ብሔራዊ ዓርማ ህዝቦች የሚኖራቸው አጠቃላይ ፍልስፍና፣ የፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም አቅጣጫ ምን እንደሆነ የሚያመለክት ነው፡፡ ከ195 (ዩኤን) ሰንደቅ ዓላማዎች መካከል የ64 ሃገራት ሃይማኖታዊ ምልክትን እንደ ብሔራዊ አርማ አካተዋል፡፡ 48% የክርስትና ሃይማኖት፣ 33% ደግሞ የእስልምና ሃይማኖትን የሚወክል ዓርማን ተጠቅመዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ በኤስያ ከሚገኙ ሌሎች ቡድሂዝምን የመሳሰሉ እምነቶች ተጠቅመዋል፡፡ ሌሎች ሀገራት ለነፃነታቸው ከከፈሉት መስዋእትነት ጋር የሚገናኙ አርማዎችን ይጠቀማሉ፡፡
ብሔራዊ ዓርማ በሰንደቅ ዓላማቸው ላይ ብቻ ሳይሆን እንደሀገር መገለጫ ማህተም አድርገውም ይጠቀሙባቸዋል፡፡ ዓርማውን ህጋዊ ለሆኑ ሰነዶች ሁሉ ጥቅም ላይ ያውሏቸዋል፡፡
ሌሎች ሀገራት ደግሞ ሰንደቅ ዓላማውንና ብሔራዊ ዓርማውን ነጣጥለው ይጠቀማሉ፡፡
ለምሳሌ፡- የአውስትራሊያ ሰንደቅ ዓላማ አምስት ኮከብ ያለው እና በቀይና ነጭ የተደበላለቀ መስቀል በጥቁር ሰማያዊ መደብ ላይ ያረፈ ነው፡፡ በሀገሪቱ ብሔራዊ ሰነዶች ላይ የሚጠቀሙት ዓርማ ግን የካንጋሮና በሀገራቸው ብቻ የምትገኘውን ከንጋሮ ምስል ነው፡፡
የሩስያ ሰንደቅ ዓላማም በተመሳሳይ ሰንደቅ ዓላማቸው ነጭ፣ ሰማያዊና ቀይ ቀለም ያለው ሲሆን ብሔራዊ ዓርማቸው (National emblem) ደግሞ ሁለት ራስ ያለው ንስር፤ ይህም የሁለቱ ሀገራት ብሔራዊ ዓርማ ከሰንደቅ ዓላማቸው የተለየ መሆኑን ያሳያል፡፡
አሜሪካም እንደ አውስትራሊያና ሩስያ ሁሉ ብሔራዊ ዓርማዋ እና ሰንደቅ ዓላማዋ የተለያዩ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አሜሪካንን ወክለው በሚዘጋጁ ሀገራዊ ከሰንደቅ ዓላማው ጋር በመደረብ ሲጠቀሙበት ሰነዶች ላይ የአሜሪካ ብሔራዊ ዓርማ ይታያል፡፡

5. ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ ዓርማ በኢትዮጵያ
ሰንደቅ ዓላማ በኢትዮጵያ ረጅም ዘመን ታሪክ አለው፡፡ ነገስታት የራሳቸውን ምልክት እያተሙበትም ቢሆን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማቱን ጠብቆ ብዙ ዘመናትን ቆይቷል፡፡
"የአሁኑ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ" አሁን ባለው ቅርፅ ስራ ላይ የዋለው በ1880ዎቹ መጨረሻ ላይ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡
 በ1898 ዓ.ም በተሰጠ ትርጉም
አረንጓዴ ---›የተስፋ፣
ቢጫ ---›የብርሃን፣
ቀይ ---›የመስዋዕትነት ምልክት ነው፡፡
 የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አንድ ጊዜ መንፈሳዊ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ፖለቲካዊ ትርጓሜ እየታከለበት ከዘመን ዘመን ተሻግሯል፡፡
 አራት መአዘኑ ሰንደቅ አላማ ከመጽናቱ በፊት ሶስት እርስ በእርስ ባልተያያዙ ቀይ፣ ቢጫና አረንጓዴ ቀለማት ጥቅም ላይ ይውል ነበር፡፡
 ከ1889-1967 ሰንደቅ ዐላማው ከይሁዳ አንበሳ ዓርማ ጋር፡፡ (ይህ ሰንደቅ ዓላማ አሁን ራስ ተፈሪያውያን በብዛት ይጠቀሙበታል፡፡)
 ከ1967-1979 እ.ኤ.አ እና ከ1983-1987 ሰንደቅ ዓላማው ያለምንም ተጨማሪ ዓርማ፡፡
 ከ1975-1987 የደርግን ዓርማ ይዞ ከልሙጡ ሰንደቅ ዓላማ ጎን ለጎን (በጣም አልፎ አልፎ) ፡፡
 ከ1987-1991 የኢህዴሪ ሰንደቅ ዓላማ
 ከ1988 ጀምሮ - የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሰንደቅ ዓላማ
የአድዋ ድል በሰንደቅ ዓላማችን ስር ተንበርክከን ለህዝባችንና ለሀገራችን ክብር ለመዋደቃችን ዐብይ አብነት ነው፡፡ ዛሬ ድህነት መዋጋት የነፃነትና የሰንደቅ ዓላማ ትግል ነው፡፡ ለዚህም ሲባል ብዝሃነትን ያስተናገደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጎለብት ያደርጋል፡፡ አንድና የተዋሀደ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብን መፍጠርን ይጠይቃል፡፡ ይህን ለመፍጠር ሰንደቅ ዓላማችን የሚኖረው በአንድ የማስተባበርና የኢትዮጵያ ብሔርተኝነትን የመገንባት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ሠንደቅ ዓላማ ሀገርና ህዝብን በአንድ ጥቅም ዙሪያ የሚያሰባስብ ምልክት ነው፡፡ ልዩ ልዩ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላቸውን ዜጎች ሳይቀር ለአንድ ዓላማ የሚወክል የጋራ መንፈስ ነው፡፡

5.1 የኢፌዲሪ ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ አርማ ሕጋዊ ትርጉም
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት አንቀፅ (3) “የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሀል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በመሀል ብሔራዊ ዓርማ ይኖረዋል፡፡” ብሔራዊ ዓርማው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ ይሆናል፡፡ የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ በአዋጅ ቁጥር 654/2001 ዓ.ም አንቀፅ (5)፣ ሰንደቅ ዓላማው የሪፐብሊኩ ሉዓላዊነትና የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፍላጎትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነታቸው መገለጫ ምልክታቸው ሆኖ የሚያገለግል ይሆናል፤ አንቀፅ 6(1)፤ ሰንደቅ ዓላማው ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሀል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በክብ ሰማያዊ መደብ ላይ የተቀረፀ ብሔራዊ ዓርማ ይኖረዋል፡፡ ዓርማው በሰንደቅ ዓላማው መካከል ላይ የሚያርፈው የክቡ ዙርያ የአረንጋዴውንና የቀዩን ቀለም ቁመት አጋማሽ አካል ይሆናል፡፡ እነዚህ ቀለማት አግድም የተዋቀሩና እኩል ስፋት የሚኖራቸው ሆኖ የሰንደቅ ዓላማው ወርድ የቁመቱን እጥፍ ይሆናል (አንቀፅ 6(2)፡፡ አንቀፅ 6/4/ሀ ሰንደቅ ዓላማው ቀጥታና እኩል ከሆኑት መስመሮች የተዋቀረ ኮከብ የሚኖረው ሲሆን ቀጥታና እኩል በሆኑ መስመሮች መተላለፊያ ላይ የሚፈነጥቅ ቢጫ ጨረር ይኖረዋል፡፡

5.1.1 የኢፌዲሪ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማቱ ትርጉም፡-
 አረንጓዴው፡- የስራ፣ የልምላሜና የዕድገት ምልክት (አንቀፅ 7/1/)
 ቢጫው፡- የተስፋ፣ የፍትሕና የእኩልነት ምልክት (አንቀፅ 7/2/)
 ቀዩ ፡- ለነፃነትና ለእኩልነት መስፈን የሚደረግ የመስዋእትነትና የጀግንነት ምልክት (አንቀፅ 7/3/) ነው፡፡

5.1.2 የኢፌዲሪ ብሔራዊ ዓርማ ትርጉም
ዓርማው ብዝሀነትን በአግባቡና በብቃት በማስተናገድ፣ የግለሰብ ነፃነቶችና መብቶችን በአግባቡ በማክበርና ለቡድን መብቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት ለኢትዮጵያ ህዝቦች ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መገንባት ነው፡፡ አስተማማኝ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ፤ የኢፌዴሪ መንግስት ከማናቸውም ሃይማኖታዊ ምልክቶች ወይም እምነቶች ጋር የማይያያዝ ወይም የማይወግን መሆኑን ያመለክታል፣ ተቻችሎና ተከባብሮ በነፃነት የመኖር ተስፋቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡
 ቀጥታና እኩል የሆኑት መስመሮች፡- የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም የሃይማኖቶች እኩልነትን (አንቀፅ 8/2/)፣
 ቀጥታና እኩል ከሆኑ መስመሮች የተዋቀረው ኮከብ፣ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመፈቃቀድ የመሰረቱትን አንድነት፣
 ቢጫ ጨረር በመፈቃቀድ አንድነት ለመሰረቱት ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የፈነጠቀውን ብሩህ ተስፋ ይጠቁማል፡፡ (አንቀፅ 8/3/)
 ብሔራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች እና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡

5.2 ለኢፌዲሪ ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ ዓርማ ተገቢውን ሕጋዊ ክብር ስለ መስጠት
የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ እና ለብሔራዊ ዓርማው በአዋጅ ቁ. 654/2001 ተገቢ ክብር መስጠት እንደሚገባ ተደንግጓል፡፡
የመንግስት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በየቀኑ ከጧት 12፡00-ምሽት 12፡00 ሠዓት ሰንደቅ ዓላማውን ይሰቅላሉ፡፡
ሲሰቀልና ሲወርድ ዜጎች ተገቢውን ክብር የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡
የሪፐብሊኩ ሰንደቅ ዓላማ ከፌዴራሉ አባል ክልሎች ሰንደቅ ዓላማ ጋር አብሮ ከመጣ በስተቀኝ በኩል ይሆናል፡፡ ሁለት ከሆኑ ከፍ ብሎ ከመሀል፣ ሁሉም ከሆኑ የክልሎቹ በፊደል ቅደም ተከተል የክልሎቹ ሰንደቅ ዓላማዎች በክልሎቹ ስያሜና በአማርኛ ፊደል ተራ መሰረት ቦታቸውን ይይዛሉ፡፡
የሀገር መሪዎች ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ሠንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ ይውለበለባል፤ የአስክሬን ሳጥኑ በሰንደቅ ዓላማ ይሸፈናል፡፡
የሰንደቅ ዓላማውን ክብር መጠበቅ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ማክበር ነው፡፡
ብሔራዊ ዓርማውን ማክበር የዜጎችን እኩልነትና በመከባበር አብሮ ለመኖር የገቡትን ቃልኪዳን ማክበርም ነው፡፡

6. ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን
ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በኢትዮጵያ በየዓመቱ በአዋጅ ቁጥር 863 /2006 መሠረት ጥቅምት አንደናኛ ሳምንት ዕለተ ሰኞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል፡፡ በየዓመቱ በተለያዩ መሪ ቃል መነሻነት ተከብሮ ይዉላል፡፡ በዚህ መሰረትም ዘንድሮ “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል፡፡

7. የተከለከሉ ተግባራት
በዚህ አዋጅ ቁጥር 23 መሰረት ከዚህ በታች የተመለኩትን ተግባራት መፈፀም የተከለከለ ነው፡፡
1. ሰንደቅ ዓለማውን በዚህ አዋጅ በተደነገገው መሠረት ዓርማውን ሳያካትቱ መጠቀም፤
2. ሰንደቅ ዓላማው ላይ ቃላቶችን መፃፍ ሌሎች ምልክቶችን ወይም ስዕሎችን ለጥፎ መገልገል፤
3. ያረጁ፣ የተበላሹ፣ ቀለማቸው የደበዘዘና የተቀደዱ ሰንደቅ ዓላማዎችን መጠቀም ወይም መገልገል፤
4. ሰንደቅ ዓላማው በወጣበት ሰንደቅ (ምሰሶ) ላይ ማስታወቂያ መለጠፍ፣ ያለአግባብ ሌሎች ሰንደቅ ዓላማዎችን ወይም አርማዎችን ጨምሮ ማውለብለብ ወይም መገልገል፤
5. ህዝብ በተሰበሰበት ቦታ ሰንደቅ ዓላማውን በጽሁፍ ወይም በቃላት፣በድርጊት ወይም በሌላ በማንኛውም አኳኋ መድፈር ወይም ማዋረድ ወይም ጉዳት እንዲደርስበት ማድረግ፤
6. የሰንደቅ ዓላማውን ቀለማት ቅደም ተከተል እንዲሁም የብሔራዊ ዓርማውን መጠን ሳይጠብቁ ማዘጋጀትና መገልገል፤
7. ሰንደቅ ዓላማውን በዚህ አዋጅ ከተጠቀሰው የማውረጃ ጊዜ በላይ ማቆየት፤
8. በስብሰባ ወይም በማናቸውም መሰል ክንውኖች ሰንደቅ ዓላማውን የጠረጴዛ መሸፈኛ ማድረግ፤
9. ሰንደቅ ዓላማን የህንፃ ወይም የሌሎች ቁሶች መሸፈኛ ማድረግ፤
10. ሰንደቅ ዓላማውን በማነኛውም ንግድ መስተወቂያነት መጠቀም፤
11. ሰንደቅ ዓላማው በሚሰቀልበትና በሚወርድበት ጊዜ ተገቢውን ክብር አለመስጠት፡፡
8. ቅጣት
በአዋጁ አንቀጽ 23 ከንዑስ አንቀጽ 2 እስከ 11 ድረስ ተመለከቱትን የተከለከሉ ተግባራት በመተላለፍ ጥፋት የፈፀመ እንደሆነ እስከ ሶስት ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ወይም እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡
ማንኛውም ሰው በአዋጁ አንቀጽ 23 ንዑስ አንቀጽ 1 የተመለከተውን በመተላለፍ ጥፋት የፈፀመ እንደሆነ እስከ አምስት ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ወይም አንድ ዓመት ከስድስት ወር በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ በአዋጁ የተመለከተውን ጥፋት የፈፀመው በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ከሆነ የገንዘብ ቅጣቱ ከሁለት እጥፍ ያላነሰ ይሆናል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 244 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት ማንኛውም ሰው በተንኮል፣ በንቀት ወይም ይህን በመሳሰለ በማናቸውም ሀሳብ በግልጽ የታወቀውን አንድ የአገር ምልክት ማለትም የፌዴራላዊት ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን ወይም ዓርማን እንዲሁም የክልላዊ መንግስት ሰንደቅ ዓላማን ወይም ዓርማን በአዳባባይ የቀደደ፣ የቃጠለ፣ ያጠፋ፣ የደፈረ፣ ያበላሸ፣ የሰደበ ወይም በማናቸውም ሌላ አኳኋን የዋረደ እንደሆነ ከሶስት ወር በማያንስ ቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል፡፡

Photos from Harari Attorney General /የሐረሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ's post 13/10/2024

የሀረሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ ና ከተጠሪ ተቋም የ2017 በጀት ዓመት እቅድ የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት ሪፖርት ግምገማ አካሄዱ******

የሀረሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግና ተጠሪ ተቋም የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያውን የሩብ ዓመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ኃላፊዎችና ማኔጅመንት አባላት በተገኙበት ግምገማ አካሄዷል፡፡

ባለፉት ሶስት ወራት በክልልችን ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በ273 የወንጀል መዝገቦች በተለያዩ የወንጀል ጉዳዮች በሁሉም የክልል ፍ/ቤቶች ውሳኔ የተሰጠ ሲሆን በክልል ደረጃ የወንጀል ክሶችን የማስቀጣት ምጣኔ 96% መሆኑን ተገምግሟል ።
የህዝብ እና የመንግስትን ጥቅምን ለማስጠበቅ መንግሥትን በመወከል መንግስት በተከሰሰበት እና በከሰሰበት 37 የፍትሐብሔር መዝገቦች የህግ ክርክር ሂደት ላይ መሆኑን ተገልፆል ።

በዚህ ሩብ ዓመት ህግ እና ማስረጃን መሠረት በማድረግ 2580 ሰነዶች የተዘጋጁና የተረጋገጡ ሲሆን ዘመናዊ እና ቀልጣፈ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን በመተግበር ለ4,350 ተገልጋዮች አገልግሎት መሰጠት መቻሉን እንዲሁም የገንዘብ አቅም ለሌላቸዉና ልዩ ድጋፍ ለሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎች የጥብቅና አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል እንደተቻለ በሪፖርታቸው ላይ ተብራርቷልዋል፡፡

በክልላችን በተለየዩ የወንጀል ጉደዮች በፍ/ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ የተሰጠባቸው ግለሰቦች ስብዓዊ መብቶቻቸውን ባከበረ መልኩ የማረም እና የማነፅ ተግባር እየተፈጸመ መሆኑን ከተጠሪ ተቋም ሪፖርት ቀርቧል ።

በቀረበው የ2017 የሩብ ዓመት ሪፖርት በበጀት ዓመቱ በቢሮዉ የእቅድ አፈፃፀም ወቅት የታዩ ጥንካሬዎችን፣ ውስንነቶችን እና እያጋጠሙ የነበሩ ችግሮች የተነሱ ሲሆን ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች እንደ አግባብነታቸዉ ተገቢውን ማብራሪያና ምላሽ በመስጠት የግምገማ መድረኩ ተጠናቋል፡፡

Photos from Harari Attorney General /የሐረሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ's post 10/10/2024

በህገወጥ የሰዎች ዝዉዉር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ለወጣቶች ተሰጠ

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝዉዉር በአንድ ሰዉ ብቻ የሚከናወን ወንጀል ሳይሆን እንደ ሰንሰለት የተያያዘ ተግባር ነዉ ያሉት የሀረሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከፍተኛ አቃቤ ህግ ፀገነት ሀይሉ

ለተዉጣጡ የሸንኮር ወጣቶች የተሰጠ ሲሆን አቃቤ ህጓ ሲያስረዱ የህገ-ወጥ የሰዎች ዝዉዉር ሲባል ሰዎች በማስገደድ ወይም በማስፈራራት ፣ጠልፎ ፣አጭበርብሮ ወይም አታሎ ሌሎች መንገድን በመጠቀም መመልመልና ማዘዋወርና ማቆየትን እንደሆነ ተናግረዉ የዚህ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈለገበት አላማ በአሁኑ ሰአት በስፋት የወንጀሉ ተጎጂዎች ሴቶችና ወጣቶች እንደሆኑና ወንጀሉ እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ በመሆኑ ነዉ ብለዋል።
በእለቱ አያይዘዉም በህገ-ወጥ የሰዎች ዝዉዉር እና በሰዎች የመንገድ እና ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣዉ አዋጅ 1178/2012 ዙሪያ ላይ ወንጀሉ የፈፀሙ ግለሰቦች ተባባሪዎች በእስራትና እንደሚያስቀጣ እና በገንዘብ መቀጮ እንደሚያስቀጣ ህጉ በግልፅ እንደሚያስቀምጠዉ አብራርተዋል
በመጨረሻም ወጣቶች በእንደዚህ አይነት ተግባር የተሳተፉ ግለሰቦችን እንዲሁም ደብቀ የያዙም ሰዎችንም ለህግ አካል መጠቆም እንዳለባቸዉ አሳስበዋል።

08/10/2024

ወጣት ወንጀል አድራጊነት በኢትዮጵያ ህግ
መግቢያ
ወንጀል የማህበረሰብን ሰላም እና ደህንነት የሚያናጋ እንደመሆኑ ወንጀል ፈፃሚዎች እንዲታረሙ እንዲሁም ሌሎችም ከመሰል ድርጊት እንዲታቀቡ ወንጀል ፈፃሚዎች በህግ መጠየቃቸው የግድ ነው፡፡ ሆኖም ወንጀል ፈፃሚዎች በተለያየ የእድሜ ክልል የሚገኙ እንደመሆናቸው የሚታረሙበት መንገድ እና የሚወሰደው የእርምት እርምጃ ይህን ያገናዘበ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በዚህም በአዋቂዎች እና በታዳጊዎች ላይ የሚወሰኑ ቅጣቶች እና የእርምት እርምጃዎች የተለያዩ ናቸው፡፡ በዚህ አጭር ፅሁፍ ስለወጣት ወንጀል አድራጊነት ምንነት እና ወጣት ወንጀል አድራጊዎች ጥፋተኛ ሆነው ሲገኙ የሚወሰዱባቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎ እንዳስሳለን፡፡
የወጣት ወንጀል አድራጊነት ምንነት
በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ህግ አንቀፅ 52 እና ተከታዮቹ መሰረት በሀገራችን የወንጀል ተጠያቂነት የሚጀምረው ከ9 አመት ጀምሮ ነው፡፡ በመሆኑም 9 አመት የሞላው ልጅ ወንጀል ውስጥ ገብቶ ቢገኝ የወንጀል ተጠያቂነት ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ እድሜያቸዉ ከ9-15 ዓመት የሆናቸዉ ልጆች ወንጀል ፈፅመው ቢገኙ የሚወሰዱባቸው የእርምት እርምጃዎችም ከመደበኛ ቅጣት የተለዩ የጥንቃቄ እርምጃዎች ብቻ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል እድሜያቸዉ ከ15 አመት በላይ የሆነ ነገር ግን 18 ዓመት በታች የሆኑ ወጣት ልጆች ለአካለ መጠን ያልደረሱ ቢሆንም ወንጀል ፈፅመው ከተገኙ ፍርድ ቤት በልዩ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ሚያስገባቸው ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው በወንጀል ህግ የተመለከቱ መደበኛ ቅጣቶች ይፈፀሙባቸዋል፡፡ በመሆኑም በልዩ ሁኔታ የጥንቃቄ እርምጃ የሚወሰድባቸው ወጣት ወንጀል አድራጊዎች እድሜያቸው ከ9 እስከ 15 አመት ያሉ ልጆች ናቸው፡፡
ወጣት ወንጀል አድራጊዎችን በተመለከተ የሚፈፀሙ ሥነ-ሥርአቶች
የወጣት ወንጀል አድራጊዎችን በተመለከተ ተፈፃሚ የሚሆነው ሥነ ሥርአት ከአዋቂ ወንጀል ፈፃሚዎች የተለየ ነው፡፡ ወጣት ወንጀል አድራጊዎች ወንጀል ውስጥ ገብተው ሲገኙ ወዲያውኑ አቅራቢያው ወደሚገኝ ፍ/ቤት እንዲቀርቡ መደረግ አለበት፡፡ ከቀረቡም በኋላም ያቀረባቸው አካል ወይም ፖሊስ የወንጀሉንና የምስክሮቹን ዝርዝር ለፍርድ ቤቱ እንዲገልፅና አስፈላጊ በሆነ ጊዜም አቤቱታ እንደደንቡ መሠረት እንዲያቀርብ ይጠበቃል፡፡ ፍርድ ቤቱም የቀረበውን ከመዘገበ በኋላ ፖሊስ ምርመራውን የሚፈፅምበትን ሁኔታ የሚገልጽ መምሪያ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ከወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 172/1/ እና /2/ ድንጋጌ መረዳት ይቻላል፡፡ ወጣት ወንጀል አድራጊን በተመለከተ እንደአዋቂ በመደበኛ ምርመራ እና ክስ ሂደት ሳይሆን አቤቱታው ቀጥታ በፍርድ ቤት ክትትል ስር የሚታይ ነው፡፡ ሂደቱም ከመደበኛው ሂደት ተለየ ነው፡፡ ይኸውም፡-
• የተያዘ ሰው በ48 ሰዓት ውስጥ ወደ አቅራቢያው ፍርድ ቤት የመቅረብ ሕገ-መንግስታዊ መብት ያለው ሲሆን ወጣት ወንጀል አድራጊን ግን በወ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 172(1) መሰረት ፖሊሱ፣ ዐቃቤ ህጉ፣ ወላጁ ወይም ሞግዚቱ ወዲያውኑ እንዲያቀርበው ይጠበቃል፡፡
• በመርህ ደረጃ ማንኛውም የተከሰሰ ሰው ለሕዝብ ግልፅ በሆነ ችሎት የመሰማት ሕገ-መንግስታዊ መብት አለው፡፡ የተከራካሪውን የግል ሕይወት፣ የሕዝብ ሞራል ሁኔታና የሀገሪቱን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ብቻ ክርክሩ በዝግ ችሎት ይከናወናል፡፡ በወጣት ወንጀል አድራጊዎች የወንጀል ፍትህ ሥርአት ውስጥ ግን ነገሩ በሙሉ የሚሰማው በዝግ ችሎት ውስጥ እንደሆነ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 176/1/ ላይ ተመልክቷል፡፡
• የወጣት ወንጀል አድራጊዎች ጉዳዮች በሙሉ መደበኛ ባልሆነ አካሄድ እና መግባባት በሰፈነበት ድባብ መካሄድ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት ከወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 176/2/ ድንጋጌ መረዳት ይቻላል፡፡ ወጣቱ ሀሣቡን በነፃነት እንዲገልፅ መፍቀድ፣ በጥሞና ማዳመጥ፣ ክፍት የሆኑ ጥያቄዎችን መጠየቅ እንዳለበት ያሳያል፡፡
• የወጣት ወንጀል አድራጊዎቹ ወላጅ ወይም ቤተዘመድ ባልተገኙ ጊዜ ወይም እነሱም ቀርበው ወጣቱ ከ1ዐ ዓመት በላይ በሆነ ፅኑ እስራት ወይም በሞት በሚያስቀጣ ወንጀል በተከሰሰ ጊዜ ፍ/ቤቱ ጠበቃ ሊመድብለት እንደሚገባ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 174 ላይ ተመልክቷል፡፡
• ወጣት ወንጀል አድራጊው ሊሰማው የማይገባ ነገር በማስረጃነት የቀረበ ወይም ትችት የሚሰጥበት በሆነ ጊዜ ሊሰማው የማይገባው ነገር በሚነገርበት ጊዜ ከችሎቱ ክፍል እንዲወጣ የሚደረግ ስለመሆኑ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 175 ላይ ተመልክቶ ይገኛል፡፡
ችሎቱ በሚካሄድበት ጊዜም የቀረበው አቤቱታ ወይም ክስ ማመልከቻ ለወጣቱ ተከሣሽ ተነቦለት እንዲረዳው መደረግ አለበት፡፡ ክሱን ሙሉ ለሙሉ ያመነ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ በወ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 176(4) መሰረት ወዲያውኑ የጥፋተኝነት ውሣኔ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ወጣት ተከሣሽ አቤቱታውን ወይም ክሱን ያላመነ እንደሆነ ለአቤቱታው ወይም ለክሱ የመጡትን ምስክሮች ፍ/ቤቱ ይጠይቃል፡፡ ፍርድ ቤቱ ምስክሮቹን በጥያቄ ከመረመረ በኋላ በተከሳሹ በኩል መስቀለኛ ጥያቄ ሊጠየቅ ይችላል፡፡ በተጨማሪም ወጣቱ ወይም እንደራሴው ወይም ጠበቃው ማንኛውም ምስክር እንዲጠራለት ማድረግ ይችላል፡፡ ከእነዚህ ሂደቶች መረዳት እንደሚቻለው አንድ ጊዜ አቤቱታውን ካቀረበ በኋላ አቤቱታውን ወይም ክሱን ደግፎ ክርክር የሚያደርግ ተከራካሪ ወገን ወይም ዐቃቤ ህግ የማይገባ መሆኑና ፍርድ ቤቱም ራሱን እንደከሣሽም እንደ ዳኛም በመሆን ሂደቱን እንደሚመራ ነው፡፡ ከዚህ በኋላም ወጣት ወንጀል አድራጊዎች በክሱ ጥፋተኛ ሆነው ያልተገኙ እንደሆነ ፍ/ቤቱ ወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 177/1/ መሰረት ወዲያውኑ በነፃ መልቀቅ አለበት፡፡ ይሁንና ወጣቶቹ በክሱ ወይም አቤቱታው ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ እንደሆነ ለወጣቶቹ የሚጠቅም ውሣኔ ለመስጠት እንዲያስችለው ስለወጣቶቹ ጠባይና ስለቀድሞ ጥፋት ለመጠየቅ ማንኛውንም ድርጅት፣ ማንኛውንም ሰው ወይም እንደራሴ ፍርድ ቤቱ መጥራት ይችላል፡፡ በፍርድ ቤቱ የተጠሩት ሰዎች ቃል ከተሰማ በኋላ የወጣቶቹ ወገን መልስ መስጠትና ስለጠባዩ ምስክሮች መጥራት ይችላል፡፡ ፍርድ ቤቱ ምስክሮቹን ከጠየቀ በኋላ የከሣሽ ወገን ስለቅጣቱ በቃል እንደሚያመለክት በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 177/2/ እና /3/ ላይ ተመልክቶ ይገኛል፡፡
በወጣት ወንጀል አድራጊዎች ላይ የሚወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎችና ቅጣቶችበወጣት ወንጀል አድራጊዎች ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች ግብ ወጣቶቹን ከገቡበት የተሳሳተ መንገድ እንዲወጡ እና መልካም ዜጎች ሆነው ጥሩ አስተሳሰብን እንዲያዳብሩ ከዚያም ሠላማዊና ለሕግ ተገዥ የሆኑ ዜጎች እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡ በመሆኑም በወጣት ወንጀል አድራጊዎች ላይ ሊወሰዱ የሚችሉ የመፍትሄ እርምጃዎች በወንጀል ህጉ አንቀፅ 158-168 የተመለከቱት ብቻ እንደሆኑ በአንቀፅ 53 ተደንግጓል፡፡ እነዚህ የጥንቃቄ እርምጃዎች ምንም አይነት የቅጣት ይዘት ሳይኖራቸው የወጣቶቹን መመለስ አላማ ያደረጉ እርምቶች ናቸው፡፡ እነዚህም፡-
• ለአካለመጠን ያልደረሰው ወጣት ጥፋተኛ ህክምና የሚያስፈልገው ሲሆን በተለይም የአዕምሮ ደካማነት፣ የአዕምሮ እድገቱ የዘገየ፣ አዕምሮው የታመመ፣ የሚጥል በሽታ ያለበት፣ በአልኮል ሱሰኝነት የተጠመደ ወይም በናርኮቲክና ሳይኮትሮፒክ ነገሮች ወይም በሌሎች የሚያፈዙ እፅዋት የተመረዘ ሆኖ ሲገኝ በወንጀል ሕግ አንቀፅ 158 መሰረት ፍርድ ቤት ተገቢ ወደ ሆነው የህክምና ተቋም እንዲሄድ ሊያዝ ይችላል፡፡ በፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ወጣት ወንጀል አድራጊው ወደህክምና ተቋም የሚላክ ከሆነ ከህክምናው ጋር ትምህርት እና ስልጠና እንዲካተት ሊያደርግ ይችላል፡፡ የህክምና ጊዜው የተላከበት የህክምና ባለስልጣን ወይም ባልደረባ ያስፈልጋል እስካለው ድረስ የሚቆይ ይሆናል፡፡
• ለአካለመጠን ያልደረሰው ወንጀል አድራጊ አስተዳደጉ በጎ ካልነበረ፣ በንዝህላልነት የተተወ ወይም ጠባዩ ወደመጥፎ ስራ ያዘነበለ ወይም የሚያዘነብል ሲሆን በወንጀል ሕግ አንቀፅ 159 መሰረት በጠባቂ ስር ሆኖ ቁጥጥር እየተደረገበት ትምህርት እና አስተዳደግ እንዲያገኝ ይታዘዝለታል፡፡ ጠባቂ የሚሆኑ ዘመዶች ከሌሉት ወይም ዘመዶች ኖረው ችሎታ የሌላቸው እንደሆነ ብቁ ለሆነ ሰው ወይም ህፃናትን ለመጠበቅ እና ለመቆጣጠር ለተቋቋመ ድርጅት እንዲሰጥ ያዛል፡፡ ይህ በሆነ ጊዜ ተረካቢዎቹ ሀላፊነታቸውን ተከታትለው የሚያስፈፅሙ ስለመሆኑ ፍርድ ቤት ቀርበው በፅሑፍ በማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ወደ ትምህርት ቤት አዘውትሮ እንዲሄድ፣ ወይም የሙያ ስራን እንዲለምድ፣ ከአንዳንድ ሰዎች ከመገናኘት ወይም ከአንዳንድ ስፍራ ከመድረስ እንዲከለከል፣ በተወሰኑ ጊዜያት ከጥበቃ ባለስልጣኖች ፊት እንዲቀርብ ወይም ሪፖርት እንዲያቀርብ እና የመሳሰሉ ግዴታዎች ሊታዘዙ ይችላሉ፡፡ ጠባቂዎቹ የተጣለባቸውን የማሳደግና የማስተማር ሀላፊነት ካልተወጡ ፍርድ ቤቱ የጠባቂነት ስልጣናቸውን የሚወስድባቸው ይሆናል፡፡
• ፍርድ ቤት ተገቢ መስሎ በታየው ጊዜ ለአካለ መጠን ያልደረሰውን ልጅ በወንጀል ሕግ አንቀፅ 160 መሰረት መውቀስ ወይም መገሰፅ ይችላል፡፡ ወቀሳውም ለአካለ መጠን ያልደረሰው ወንጀል አድራጊ የፈፀመውን የወንጀል ድርጊት እንዲረዳው እና ለወደፊት ከእንዲህ አይነቱ ተግባር እንደቆጠብ በጎ ተግባር እና መልካም ፀባይ ለማምጣት ያለመ መሆን ይኖርበታል፡፡ ፍርድ ቤት በወቀሳ እና በተግሳፅ የሚያልፈው የወንጀሉን ቀላልነት እና የወንጀል ፈፃሚውን የመረዳት ችሎታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ግን ከሌሎች የጥንቃቄ እርምጃዎች ጋር ተጣምሮ ሊተገበር ይችላል፡፡
• በትምህርት ቤት ወይም በመኖሪያ ቤት ተወስኖ እንዲቆይ በወንጀል ሕግ አንቀፅ 161 መሰረት ትዕዛ ሊሰጥ የሚችል ሲሆን ይህም የሚደረገው ፍርድ ቤቱ ወጣት ወንጀል አድራጊው በቀላሉ የሚታረም መስሎ ከታየው እና የሚቆይበትን ጊዜ በመወሰን እና በእረፍት ጊዜው የሚያከናውነውን ተግባር በመስጠት ነው፡፡
• የወጣት ጥፋተኛው የቀድሞ ታሪኩን፣ ፀባዩን እና መጥፎነቱን እንዲሁም የወንጀሉን ከባድነት እና አፈፃፀሙን በማየት በወንጀል ህግ አንቀፅ 162 መሰረት ወንጀል አድራጊዎችን ለማረሚያ እና ለማስተማሪያ በተቋቋመ ተቋም እንዲገባ ፍርድ ቤቱ ሊያዝ ይችላል፡፡ በዚህ ሂደት ወጣት ጥፋተኛው ጠቅላላ ትምህርት፣ ግብረገብነት፣ የመተዳደሪያ ልዩ ሙያ የሚያገኝበትን (ልዩ መልመጃ) እንዲሁም ወደማህበራዊ ኑሮው እንዲመለስና በቅንነት እየሰራ እንዲኖር አስፈላጊ የሆኑትን ሁሉ እንዲማር ያደርጋል፡፡
• በዚህ መልኩ ሚሰጥ ትእዛዝ የሚቆይበት ግዜ መገለፅ ያለበት ሲሆን ቢያንስ አንድ አመት ቢበዛ አምስት አመት እንጂ ለአካለመጠን ከደረሰ በኋላ ተፈፃሚነት የለውም፡፡
ፍርድ ቤቱ መርጦ የወሰነው የጥንቃቄ እርምጃው የማያስተምር አይነት ከሆነ መለወጥ ይችላሉ፡፡ የእርምት እርምጃ ተፈፀመው ውጤት አልባ ሆነው ሲገኙ የእስራት ወይም የመቀጮ ቅጣት ተፈፃሚ የሚሆኑ እንደሆነ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 166 ድንጋጌ መረዳት ይቻላል፡፡

Want your business to be the top-listed Government Service in Harar?

Click here to claim your Sponsored Listing.

Location

Telephone

Address


Shankor
Harar