02/06/2026
የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ አሰጣጡ ሂደት በሰላም መጠናቀቁን በሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የምርጫ ኮማንድ ፖስት አስታውቋል።
የምርጫ ኮማንድ ፖስቱ የድምፅ መስጫ ሂደቱ እስከ ከሌሊቱ 6፡00 ሰዓት ሲከናወን መቆየቱን በሶስቱም ምርጫ ክልል በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ የመስጠት ሂደት ፍጹም ሠላማዊ ሆኖ መጠናቀቁን በሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የምርጫ ኮማንድ ፖስት አስታውቋል።
ድምጽ የመስጠት ስርዓቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ መራጩ ህዝብ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ዕጩዎች እና ታዛቢዎች ላበረከቱት አስተዋጽኦ እና ኃላፊነታቸውን በተገቢው ለተወጡ መላው የጸጥታ አካላት ኮማንድ ፖስቱ ምስጋናውን አቅርቧል።
ድምጽ ቆጠራው በአንዳንድ ጣቢያዎች እየተካሄደ ነው።
ድህረ ምርጫ ያለው ሂደት በተመሳሳይ በስኬት እንዲከናወን ባለ ድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የምርጫ ኮማንድ ፖስት ጥሪውን በድጋሚ አቅርቧል።
ሰላም ለሁሉም !!
ሁሉም ለሰላም!!
26/05/2026
የኢድ አል አድዓ (አረፋ) በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቋል፦ Tofik Mohammed Yuyo
**************************
1447ኛው የኢድ አል አድዓ (አረፋ) በዓል በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የሀረሪ ክልል ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ቶፊቅ መሐመድ እንደገለጹት በዓሉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ለማስቻል ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሰላም አደረጃጀቶችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጎ ወደ ተግባር ተገብቷል።
የሀረሪ ክልል የሰላም፣ የፍቅር፣ የመቻቻልና የአንድነት ተምሳሌት ናት ያሉት አቶ ቶፊቅ የክልሉን ሕዝብ የሰላሙ ባለቤት በማድረግ በተከናወኑ ተግባራት በክልሉ የሚከበሩ የተለያዩ የአደባባይ በዓላትን ከስጋት ነጻ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የኢድ አል አድዓ በዓልም ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ በሰላም እንዲከበር ለማድረግ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ኃላፊው አብራርተዋል።
በዛሬው ዕለትም በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች፣ የሰላም አደረጃጀቶች፣ የጸጥታ አካላት እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በጋራ በመሆን የኢድ ሶላት የሚሰገድበትን ስፍራ ማጽዳታቸውን ገልጸዋል።
ይህም በክልሉ ያለውን የአብሮነትና የመደጋገፍ እሴት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን አቶ ቶፊቅ አክለው ገልጸዋል።
ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ ለ1447ኛው የኢድ አል አድዓ (አረፋ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል።
26/05/2026
የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ የሚሊሻ ጉዳይ ፅ/ቤት ኃላፊ የፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮችና አባሎች፣የወረዳ አመራሮች ፣የሰላም አደረጃጀቶች ፣የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላቶች ለ1447ኛው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በአል የስግደት ቦታዎችን የፅዳት መርሃ ግብር ተካሄደ ፡፡---------------------------
ማክሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ.ም
ለ1447ኛው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በአል የስግደት ቦታ በኢማም አህመድ እስታዲየም እና በሁሉም የስግደት ቦታዎች የፅዳት መርሃ ግብር በዛሬው እለት የተከናወነ ሲሆን
በመርሃ ግበሩ የተገኙት የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶፊቅ መሀመድ የ1447ኛው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በአል በሁሉም ስግደት የሚደረግባቸውን ቦታዎች በአብሮነት በማፅዳት የተባበሩትን የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተወካዮችና የህብረተሰብ ክፍሎች ፣የሰላም አደረጃጀቶች ፣ወጣቶችን በጋራ በማመስገን የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል ፡፡
የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤም ሃይማኖታዊ በዓላትን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል አንድነቱንና ትብብሩን የሚያጠናክርባቸው መልካም እሴቶቻችን ናቸው በማለት እንኳን ለ1447ኛው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በአል ዋዜማ አደረሳችሁ በማለት መርቀዋል ፡፡
አቶ ቶፊቅ መሀመድ አክለውም ለ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ እለት ዋዜማ ላይ እንደመገኘታችን ኃይማኖቶች ለሰላም ፣ለአብሮነት ፣ለአንድነትና ለሀገር ግንባታ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው በክልላችን ላለው ዘላቂ ሰላም የሁላችንም ድርሻ እና ሀላፊነት በመሆኑ በዓሉን ስናከብር ክልላችን በምትታወቅበት የተለመደ የመከባበር ፣የመተዛዘንና የመረዳዳት እሴትን በመተግበር መሆን እንዳለበት እና ከተማችንን ፅዱና ማራኪ ማድረግ እንዳለብን በማህበራዊ ሚዲያ ሀገር ጠል የሆኑ ግለሰቦች የሚያሰራጩትን የተሳሳተ መረጃ እንዲሁም የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ቡድኖች እኩይ ሴራ በማጋለጥ ማህረሰቡ ለሰላማችን ዘብ ሊቆምና 7ኛውን አገራዊ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ በመንገድ ማጠናቀቅ ይገባናል በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ።
በመርሃ ግብሩ የሚሊሻ ጉዳይ ፅ/ቤት ኃላፊ ፣የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሮችና መኮንኖች ፣የወረዳ አመራሮች ፣የሰላም አደረጃጀቶች ፣የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላቶች ፣የሰላና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የማኔጅመንት አባላቶች ፣የሚሊሻ አባላት ተገኝተዋል ፡፡
ሰላም ለሁሉም !!
ሁሉም ለሰላም !!
የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ህዝብ ግንኙነት
19/05/2026
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሀዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲፈጸም የጸጥታና የሰላም አደረጃጀቶች የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት መወጣት ይገባል ተጠየቀ
በሐረሪ ክልል 7ኛው ጠቅላላምርጫ ፍትሀዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲፈጸም የጸጥታና የሰላም አደረጃጀቶች የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት መወጣት እንደሚገባ በብልጽገና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ተናገሩ።
በክልሉ የሚገኙ የሚሊሻና የደንብ ማስከበር አባላት እና በተለያዩ አደረጃጀቶች የሚገኙ የፖሊስ ተባባሪ አካላትና የሰላም አደረጃጀቶች ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በሚያስችል ጉዳይዎች ላይ ውይይት አካሂደዋል።
በመድረኩ የተገኙት በብልጽገና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ እንዳሉት በክልሉ የሚገኙት የሚሊሻ እና ደንብ ማስከበር አባላት እንዲሁም የሰላም አደረጃጀቶች በክልሉ ሰላምና ጸጥታ እንዲረጋገጥ እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ወንጀሎችና ህገ ወጥ ተግባራትን በመከላከል ረገድ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በሚያከናውኑት የተቀናጀ ተግባር አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በክልሉ የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫም ፍትሀዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲፈጸም የጸጥታና የሰላም አደረጃጀቶች ሚና ወሳኝ በመሆኑ አብርክቷቸውን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የሐረሪ ክልል ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ አቶ ቶፊቅ መሀመድ በበኩላቸው በክልሉ የሚገኙ የጸጥታና የሰላም አደረጃጀቶች ወንጀሎችንና ህገ ውጥ ተግባራትን በመከላከሉ ረገድ አመርቂ ተግባራት እያከናወኑ ይገኛሉ።
በክልሉ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሀዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲፈጸም በክልሉ የሚገኙ የጸጥታና የሰላም አስተዋጽዎ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በዚህም የምርጫ ህግ፣ ደንብና መመሪያዎች በማክበር ምርጫው ሰላማዊና በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያተረፈ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን አስተዋጽዎ እንዲያበረክቱ አስገንዝበዋል።
በመድረኩም የተገኙት የጸጥታና የሰላም አደረጃጀቶች በሰጡት አስተያየት ጠቅላላ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
ምርጫው ከጸጥታ ስጋት በራቀ መልኩ በሰላም ከፍጻሜው እንዲደርስ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አክለዋል።
15/05/2026
የሰላምና አብሮነት ኮንፈረንሱ የህዝቦችን አብሮነትና ትስስርን ባጠናከረ መልኩ በስኬት ተጠናቋል
የሐረሪ ክልል፣ ምስራቅ ሀረርጌ ዞን እና ማያ ከተማ አመራሮችና ነዋሪዎችን ባሳተፈ መልኩ ሲካሄድ የቆየው የሕዝብ ለሕዝብ የሰላምና አብሮነት ኮንፈረንስ የተነሱለትን ግቦች በማሳካት በስኬት መጠናቀቁን የክልሉ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ቶፊቅ መሀመድ የኮንፍረንሱን መጠናቀቅ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፦ ''የህዝቦች ሰላምና አብሮነት ለጋራ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ኮንፈረንስ የአብሮነትና የመቻቻል እሴት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ ነው።
የሀረሪ እና የኦሮሞ ህዝቦች እርስ በእርስ የተዋለዱ፣ የተጋመዱና ለአያሌ ዘመናት አብረው የኖሩ ህዝቦች መሆናቸውን ጠቁመው በመድረኩም አንዱ ለሌላው ያለውን የላቀ ፍቅርና መተሳሰብ የታየበት መድረክ እንደነበር ነው የተናገሩት።
ሕዝባዊ ትስስሩን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ የፀና አቋም የተያዘበት ከመሆኑም በተጨማሪ እርስ በእርስ መደጋገፍ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ህዝቡ ያለውን ቁርጠኝነት የገለፀበት መሆኑን ነው የጠቀሱት።
የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎችን፣ ሃደ ስንቄዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ ወጣቶችንና ሴቶችን በንቃት ባሳተፈ መልኩ በተካሄደው ኮንፈረንስ ላይ የተነሱ ጠቃሚ የሰላም እሴቶች በየደረጃው ወደሚገኘው ማህበረሰብ እንዲሰርጽ ለማስቻል በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ለኮንፍረንሱ ስኬታማነት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋናቸውንም አቅርበዋል።
15/05/2026
በሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮና ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ የመንግስት አገልግሎት እና አስተዳደር ሪፎርም ፖሊሲ ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ። **************************
ግንቦት 7 ቀን 2018 ዓ.ም.
በክልል ደረጃ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ለመተግበር ቅድመ ሁኔታዎች ተጠናቆ ወደ ትግበራ ለመግባት በዝግጅት ላይ በመሆኑ ለሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮና ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ ሰራተኞች በጉዳዩ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ በዛሬዉ ዕለት ለመላዉ የተቋሙ ሰራተኞች ስልጠና ተሰቷል።
የስልጠናውን መርሃ ግብር የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ም/ኃላፊ ኮሚሽነር ነስሪ ዘከርያ
በመገኘት ያስጀመሩ ሲሆን በመልእክታቸውም የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ዋና አላማው ግልጽነትንና ተጠያቂነትን እንዲሁም ብዝሃነትን እና አካታችነትን ያረጋገጠ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለተገልጋይ ማድረስ መሆኑን አስረድተው ስልጠናው በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ አፅንኦት ሠተዋል፡፡
በስልጠናዉም የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ፤ ነጻ ገለልተኛና አካታች የሠራተኞች ስምሪት ፤ የስራ አፈጻጸም አመራር ለውጦችና እድገቶች እና የመንግስት ሰራተኞች ብቃት የስራ አመራር ይዘትና አተገባበር ላይ ያተኮረ ሰነዶችን የተቋሙ የለዉጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክተር በሆኑት አቶ ዲኔ አብደላ የቀረበ ሲሆን
1. የመንግስት አገልግሎት አስተዳደር ሪፎርም
2. የስራ አፈፃፀም አመራር ለውጦች
3. የመንግስት ሰራተኞች ብቃት ምዘና ስራ አመራር ይዘትና አተገባበር
4. ነፃ ገለልተኛ አካታች የሰራተኞች ስምሪት በሚል ርዕሶች ጉዳዮች
የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ዋና አላማው ግልጽነትንና ተጠያቂነትን እንዲሁም ብዝሃነትን እና አካታችነትን ያረጋገጠ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት የሚያቀርብ እና ለሀገራዊ የልማት ግቦች ስኬት ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነፃ ፣ ገለልተኛና ብቁ ሲቪል ሰርቪስ ለመገንባት እንደሆነ ተመላክቷል።
በመጨረሻም በቀረበዉ ሰነድ ላይ ከስልጠናዉ ተሳታፊዎች ጋር በስፋት በመወያየት ሀሳብ አስተያየት በመስጠት ስልጠናው ግንዛቤ ተጠናቋል።
ሰላም ለሁሉም !!
ሁሉም ለሰላም !!
10/05/2026
የአብሮነት እሴቶችን በማጎልበት ሰላምና ልማትን ማስቀጠል ይገባል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ
የአብሮነት እሴቶችን በማጎልበት ሰላምና ልማትን ማስቀጠል ይገባል ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።
የሀረሪ ክልል፣የኦሮምያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ ዞንና ማያ ከተማ መስተዳድር የህዝብ ለህዝብ የሰላምና አብሮነት ኮንፍረንስ በመካሄድ ላይ ነው።
“የህዝቦች ሰላምና አብሮነት፤ ለጋራ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ በሚገኘው ኮንፍረንስ የክልሉ፣ዞንና ከተማ መስተዳድሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የህዝብ ለህዝብና የሰላም ኮንፍረንስ ላይ የተገኙት የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ባደረጉት ንግግር የምስራቅ ኢትዮዽያ በተለይም የሐረርጌ ህዝቦች ግንኙነት በኢትዮዽያ ታሪክ ውስጥ እጅግ ልዩና ተምሳሌታዊ ከሚባሉት የማህበራዊ ውህደት አንዱ ማሳያ ነው።
ትስስሩም ሰው ሰራሽ ድንበሮች የማይገድበው በደም፣ በባህል፣ ሃይማኖት፣በንግድና በጋራ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ውህድና ተጠቃሚነት የተጋመደ ጥልቅ ስነ ልቦናዊ አንድነት ማሳያ ነው ሲሉም አክለዋል።
ለዘመናት በችግርም ሆነ በደስታ ጊዜ አብረን የቆየን፣ በጋብቻ፣ በባህልና በታሪክ የተሳሰርን ህዝቦች በመሆኑ ይህንን ጠንካራ ገመድ ይበልጥ ማጥበቅና ለትውልድ ማስተላለፍ የሁላችንም ኃላፊነት መሆን ይገባል ብለዋል።
የሁላችንም ጥንካሬ የሆነውን አብሮነትና አንድነትን በማጠናከር የሰላምና የልማት አምባሳደሮች መሆንም ይገባል ሲሉ አመልክተዋል።
ወጣቶች በአገራችን ለተጀመረው የብልጽግና ጉዞ ፈተና እየሆነ የሚገኘውን፣ የብሔር ጽንፈኝና የጥላቻ ትርክትን በመከላከልና በአብሮነት፣በልማትና ሰላም ስራዎች ላይ በመሰማራት ለሀገር ግንባታ የበኩላቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
አመራሩ፣የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ምሁራንና ሌሎች ባለድሻ አካላት ለዚህ ተግባር የበኩላቸውን አበርክቶ ማድረግ ይጠበቅበታል ሲሉ አስገንዝበዋል።
የህዝብ ለህዝብ ትስስር ማለት ቃል ብቻ አይደለም ያሉት ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ አብሮ መኖር፣አብሮ መስራት፣አብሮ መጠበቅና አብሮ መልማት መሆኑን ገልጸው ይህም የጋራ ተጠቃሚነትን እንደሚያጎለብተው አመልክተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የህዝብ ለህዝብ መድረኩ አብሮነት፣ ሰላም፣ ልማት፣አንድነትና ብሔራዊ መግባባት ከማስቀጠል አንጻር ፋይዳው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
በመድረኩ ላይ የሀረሪ ክልል ፣ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን እና የማያ ከተማ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።