19/03/2026
መልካም የኢድ በዓል!
የረመዳን ጾም ተፈጽሞ፣
የአላህ ችሮታ ታድሶ፣
የኢድ ደወል ሲያስተጋባ፣
የደስታ ብርሃን ፈንጥቆ።
በዓሉን በሰላም አድርሰን፣
በፍቅር፣ በአንድነት አድምቀን፣
የአላህ እዝነት በእኛ ላይ
እንደ ዝናብ ይውረድ ሁልጊዜም።
በዓሉን በደስታ እናክብር፣
በእምነት እና በመልካም ስራ
የኢድ ሙባረክ መልእክት
ለዓለም ሁሉ ይዳረስ!
تقبل الله منا ومنكم صالح الأعمال كل عام وأنتم بخير
28/02/2026
የሀረር ጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች የመልሶ ማልማት ስራ በጨረፍታ
👉 ውስጥ ለውስጥ መንገዶች የመልሶ ማልማት ስራዎች
~ ~ ~
ኢትዮጵያ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ፣ ሰው ሰራሽና ባህላዊ ቅርሶች ባለቤት ስትሆን፤ ከእነዚህም የሀገራችን ብርቅዬ ሀብቶች መካከል አንዱ የሀረር ጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስ ይገኝበታል።
ሀረር ከተቆረቆረችበት ከ7ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ የተለያዩ የከተማነት ቅርፆችን እየያዘች መጥታለች። በከተማነት መዋቅር ከተዋቀረች በኋላ፣ በ13ኛው - 16ኛው ክፍለ ዘመን በከተማዋ ያለ ከልካይ የሚዘልቁ ፀጉረ-ልውጦችን ለመቆጣጠርና ራስን ከጠላት ለመከላከል በማሰብ በአሚር ኑር ቢን ሙጃሒድ ዘመነ መንግስት ግንቡ እንደተገነባ ታሪክ ያስረዳል።
ጀጎል ከተመሰረተበት ዘመን አንስቶ ከአራት መቶ ዓመታት በላይ ሕያው ሆኖ የዘለቀ ሲሆን፤ በ3342 ሜትር ርዝመት ባለው አጥር ተከልሎ በ48 ሄክተር የመሬት ስፈት የተቆረቆረችውና የጥንታዊቷ የሀረር ከተማ እምብርት የሆነውን የሚየካልል ስፍራ ነት።
በዚህም ጀጎል ውስጥ 365 (ሦስት መቶ ስልሳ አምስት) ቀጭንና ጠመዝማዛ መንገዶች አሉ። የሀረር ከተማ በቅርስነት ካስመዘገበቻቸው ዓለም አቀፍ ቅርሶች መካከል እነዚህ የጀጎል የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ተጠቃሽ ናቸው።
ጀጎል ካለው እድሜ አንፃር እና ከማህበረሰቡ የግንዛቤ እጥረት የተነሳ፣ በተለያዩ ጊዜያት ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘቱ ለሰው ሰራሽ አደጋዎችና ለእክብካቤ ጉድለት ተጋልጦ ቆይቷል። ይህም የቀድሞ መልኩንና ቅርፁን ለመግለጽ በሚያዳግት መልኩ እንዲለዋወጥ፣ አልፎም በመፈራረስና በመዘጋቱ ምክንያት ከመንገድነት የመውጣት አደጋ ተጋርጦበት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
ይህንን በቅርሱ ላይ የተጋረጠ አደጋ በመቀልበስና ቅርሱን ተንከባክቦ ለትውልድ ለማስተላለፍ በማሰብ፣ በክልላችን ፕሬዝዳንት በክቡር አቶ ኦርዲን በድሪ የሐሳብ አመንጪነት፣ የመንግስትና የግል ተቋማትን፣ ዳያስፖራውን እንዲሁም ባለሀብቶችን በማሳተፍና በቆራጥ የአመራር ጥበብ የጀጎል የውስጥ መንገዶች ሕያው ሆነው እንዲዘልቁ ተደርጓል። ይህም "የነጠላ ትርክትን ወደ ወል ትርክት" መቀየር የተቻለበት ትልቅ አጋጣሚ ሲሆን፣ የምንጊዜም የዚህ ትውልድ የታሪክ አንጓ እንዲሆን አድርጎታል።
በዚህም በሦስት ዙሮች 13.3857 ኪ.ሜ የጀጎል ኮሪደር መልሶ ማልማት ተችሏል። በአሁኑ ወቅት በያዝነው 4ተኛው ዙር የዓለም አቀፉ የጀጎል ኮሪደር መልሶ ማልማት ስራ 9.0143 ኪ.ሜ በተያዘለት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ ወደ ስራ ተገብቷል።
የተጀመሩ መልካም ስራዎችን ጥራትና ፍጥነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ቅርሱ ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ፣ የአካባቢውን ፀጋዎችና እውቀት በመጠቀም የሀረርን ታሪክና ስልጣኔ ሊመጥን በሚችል መልኩ እየተከናወነ ይገኛል። ይህ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አንዱ አካል ሲሆን፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶቹን የኢኮኖሚ ምሶሶና የቱሪስት መስህብ በማድረግ ለተተኪው ትውልድ ማስተዋወቅ ወሳኝና የማይተካ ሚና አለው። በተጨማሪም የአካባቢው ማህበረሰብም እነዚህን የለሙና በማልማት ላይ የሚገኙ ቅርሶችን በመንከባከብና በመጠበቅ ረገድ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ እናቀርባለን።
"ጀጎል የታሪካችን አሻራ፣ የትውልድ አደራ በቆራጥ አመራር የተገነባው የጀጎል ኮሪደር፤ የትውልድ ኩራት!"
በቅርስ ዳ/ዳይሬክተር የካቲት 22/2018 ዓ.ም
25/02/2026
"ከጥንት ሲፈስ የመጣው ጥበብ፣ በዘመኑ ትውልድ እጅ ደምቆ ይውጣ ትላንትን በክብር፣ ዛሬን በጥበብ፣ ነገን በቅርስ!"
19/02/2026
ታላቁ የጃሚ መስጂድ (Al-Jami Mosque) የታሪክ ዳራ
ክፍል ሁለት
1. ጥንታዊነትና አመሰራረት
የጃሚ መስጂድ በትክክል መቼ እንደተመሰረተ የታሪክ ድርሳናት ቢለያዩም፣ ግንባታው ከ10ኛው ክፍለ ዘመን (ከሺህ ዓመታት በፊት) ጀምሮ በተለያዩ ደረጃዎች እንደተከናወነ ይነገራል። በታሪካዊቷ የሀረር ከተማ (ጁጎል) ውስጥ የሚገኘው ታላቁ የጃሚ መስጂድ (Al-Jami Mosque) የከተማዋ መንፈሳዊ ልብ እና የእስልምና ስልጣኔ መገለጫ ነው። ሀረር አራተኛዋ የእስልምና ቅድስት ከተማ" (The Fourth Holiest City of Islam) ተብላ የምትታወቅ ሲሆን፣ ይህ መስጂድ ደግሞ በከተማዋ ካሉት 82 መስጂዶች ሁሉ ዋነኛውና ትልቁ ነው። በዚህም መስጂዱ የሀረር ጁጎል በዩኔስኮ (UNESCO) በዓለም ቅርስነት እንድትመዘገብ ካደረጉት ዋና ዋና የህንፃ ጥበቦች አንዱ ነው።
2. የስነ-ህንፃ ጥበብ (Architecture)
የሀረር ጃሚ መስጂድ ከሌሎች መስጂዶች ለየት የሚያደርገውና በፎቶግራፎች ላይ በብዛት የሚታወቀው በሁለቱ ነጫጭ ምንአሬዎቹ (Minarets) ነው።
➡️ምንአሬዎቹ፦ ረጅም እና ውብ ቅርፅ ያላቸው ሲሆኑ፣ አንደኛው ከሌላኛው በጥቂቱ ይረዝማል። እነዚህ ምንአሬዎች የሀረር ከተማ መለያ ምልክቶች (Landmarks) ናቸው።
➡️ዲዛይን፦ የመስጂዱ አሰራር የሀረሪ ባህላዊ ቤቶች (Harari Traditional Houses) እና የአረብ ሀገራት ስነ-ህንፃ ጥምረት ይታይበታል። ውስጡ ሰፊ ሲሆን፣ ለአየር ዝውውር እና ለብርሃን ምቹ በሆነ መልኩ ተገንብቷል።
3. ስያሜው (ለምን "ጃሚ" ተባለ?)
"ጃሚ" (Jami) የሚለው ቃል የመጣው "ጀመዐ" (ሰበሰበ) ከሚለው የአረብኛ ቃል ነው። ትርጉሙም "ሰብሳቢ" ወይም "ትልቅ የጋራ መስገጃ" ማለት ነው።
➡️የስያሜው ምክንያት፦ በእስልምና አስተምህሮ ማንኛውም መስጂድ "መስጂድ" ተብሎ ሊጠራ ቢችልም፣ "ጃሚ" የሚባሉት ግን መላው የከተማው ሕዝብ በሳምንት አንድ ቀን ለአርብ (ጁሙዓ) ሶላትና ለዒድ በዓላት በጋራ የሚሰባሰቡባቸው ታላላቅ መስጂዶች ናቸው።
➡️ክብሩ፦ በሀረር 82 መስጂዶች ቢኖሩም፣ ይህ መስጂድ የሁሉንም መስጂዶች የበላይና የከተማዋ ማዕከል በመሆኑ "አል-ጃሚ አል-ከቢር" (ታላቁ ጃሚ መስጂድ) ተብሎ ይጠራል።
4. የሚገኝበት ቦታ (Location)
የጃሚ መስጂድ የሚገኘው በምስራቅ ኢትዮጵያ፣ በሀረሪ ክልል፣ በታሪካዊቷ የሀረር "ጁጎል" ግንብ ውስጥ ነው።
➡️ትክክለኛ ስፍራው፦ በጁጎል መሃል"ፈረስ መጋላ" (Fereas Magala) ተብሎ በሚጠራው ዋናው የገበያና የሕዝብ መሰብሰቢያ አደባባይ ወዳ አርጎባ በር በሚወስድ መንገድ ጁጎል ሆስፒታል (Jugol Hospital) ጎን ይገኛል።
➡️ጎረቤቶቹ፦ መስጂዱ የሚገኘው ከታዋቂው የመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን እና የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሀል የሚገኙት በ100 ሜትር ራዲየስ ውስጥ ነው። ይህ ሁኔታ በሀረር ከተማ የሚገኘውን የሃይማኖቶች አብሮ መኖርና የታሪክ መወራረስ በጉልህ የሚያሳይ አቀማመጥ በተጨማሪም ይህ አቀማመጥ ሐረርን "የመቻቻል ሙዚየም" ያሰኛታል በዚህም በአንድ አካባቢ ቆመው የሦስቱንም ተቋማት ድባብ በአንድ ላይ ማግኘት ይችላሉ።
"ሐረር የመንፈሳዊ እውቀትና የሰላም ምንጭ ሕያው ምስክር"
በቅርስ ዳ/ዳይሬክቶሬት የካቲት 12/2018 ዓ.ም
15/02/2026
የጀጎል አለም አቀፍ ቅርስ ከአምስቱ በሮች አንዱ የሆነው የበድሪ በሪ በር አጭር የታሪክ ዳራና የአሰራር ጥበብ
1. የታሪክ ዳራ
በድሪ በሪ በጀጎል ግንብ በስተደቡብ አቅጣጫ የሚገኝ በር ነው። ስያሜውን ያገኘው በታዋቂው የባድር (Badr) ጦርነት ስም እንደሆነ ይነገራል። ይህ በር በታሪክ በተለይ የሚታወቀው የንግድና የግብርና ምርቶች መግቢያ በመሆኑ ነው።
👉🏻የንግድ መስመር፦ በድሪ በሪ ሐረርን ከደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች (ባሌ፣ አርሲ እና ጨርጨር) ጋር የሚያገናኝ ብቸኛው የንግድ መግቢያ ነበር። ይህ መስመር ከተማዋን ከደጋማው የኢትዮጵያ ክፍል ከሚመጡ የተፈጥሮ ሀብቶች ጋር ያገናኛታል።
👉🏻የመከላከያ ሚና፦ እንደሌሎቹ በሮች ሁሉ፣ በድሪ በሪ ከተማዋን ከጠላት ጥቃት ለመከላከልና የሰዎችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በታቀደ መልኩ የተገነባ ነው።
2. የአሰራር ጥበብ (Architectural Style)
በሩ መጀመሪያ ሲገነባ (በ16ኛው ክፍለ ዘመን በአሚር ኑር አዳኝ አማካኝነት) የታለመው ለውበት ሳይሆን ለመከላከያ (Defense) እና ለቁጥጥር ነበር። በዚህም የበድሪ በሪ አሰራር የሀረሪዎችን እና የጣሊያኖች ጥንታዊና ጥበባዊ የድንጋይ ግንብ ጥበብ ፍንጭ ይሰጣል።
የግንባታ ቁሳቁስና አሰራር፦
👉🏻የድንጋይ (stone): በሩ የተገነባው በአካባቢው በሚገኝና ለመጥረብ በሚመች ድንጋይ ነው። ድንጋዮቹ በጥንቃቄ ተጠርበው አንዱ በሌላው ላይ እንዲያርፉ ተደርገዋል እንዲሁም የድንጋይ አጠራብ (Masonry): በቅስቱ ዙሪያ ያሉ ድንጋዮች (Voussoirs) በትክክለኛ አንግል ተጠርበው የተቀመጡ ናቸው። ይህም በሩን ከሩቅ ሲመለከቱት ወጥና የተስተካከለ ውበት እንዲኖረው ያደርገዋል።
👉🏻የጥንታዊ "ሳሮጅ" (Saroj) ድብልቅ፦ ድንጋዮቹን ለማያያዝ ያገለገለው ድብልቅ ከኖራ (Lime)፣ ከደቀቀ የሸክላ አፈርና ከውሃ የተሰራ ነው። ይህ ድብልቅ ከዘመናዊ ሲሚንቶ በተሻለ ሁኔታ ከድንጋዮቹ ጋር የመዋሃድና ረጅም ዘመን የመቆየት ባህሪ አለው።
ቅርፅ፦
👉🏻በሩ የቅስት (Arch) ቅርፅ ያለው ሲሆን፣ በላዩ ላይ ለዘበኞች መከላከያና መመልከቻ የሚያገለግሉ ትናንሽ ክፍተቶች አሉት።
👉🏻ጥንካሬ፦ ለዘመናት የቆየው ይህ በር፣ የሀረርን የአየር ንብረትና የተፈጥሮ ክስተቶችን ተቋቁሞ እንዲቆይ ተደርጎ በልዩ ጥበብ የታነጸ ነው።
3. የእድሳት ታሪክ
የሀረር ጀጎል ግንብ በ1998 ዓ.ም (እ.ኤ.አ 2006) በዩኔስኮ (UNESCO) የዓለም ቅርስነት ከተመዘገበ በኋላ፣ ጥበቃና እንክብካቤው ይበልጥ ትኩረት አግኝቷል።
👉🏻ዋናው እድሳት፦ በድሪ በሪን ጨምሮ አምስቱም በሮችና ግንቡ በጠቅላላ በየጊዜው ጥቃቅን ጥገናዎች ቢደረጉላቸውም፣ በጎላ ሁኔታ ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ እድሳት የተደረገለት በ1990ዎቹ አጋማሽ እና በ2000ዎቹ መጀመሪያ (በኢትዮጵያ አቆጣጠር) ነው።
👉🏻የቅርብ ጊዜ እንቅስቃሴ፦ የሀረሪ ክልል መንግስት የባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ በቅርስ ጥበቃ የግንቡን ውበት ለመጠበቅና የተሰነጠቁ ክፍሎችን በመጠገን እንዲሁም በስፍራው እየተሰራ በሚገኘው የኮሪደር ልማት ጋር እንዲጣጠም በመብራት የማሸብረቅ ስራዎች ተሠርቷል።
የበድሪ በሪ ልዩነት:-
በድሪ በሪ ከሌሎቹ በሮች ለየት የሚያደርገው "የንግድ መግቢያ" መሆኑ ነው። ስለዚህ አሰራሩ ከጥንካሬው ጎን ለጎን የከተማዋን ባለጸጋነት በሚያሳይ መልኩ ሰፋ ያለና ግርማ ሞገስ ያለው ሆኖ ተሰርቷል።
//ሐረር ታሪካዊቷና ጥንታዊቷ የቅርሶች መገኛ እና የስነ- ጥበብ ማዕከል!!//
በቅርስ ዳ/ዳይሬክቶሬት የካቲት 8/2018 ዓ.ም
07/12/2025
4ተኛው ዙር የጁገል ኮሪደር መልሶ ማልማት ስራ ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ በትኩረት እየተሰራ ነው፦ኢንጅነር አሚር ረመዳን
*****
4ተኛው ዙር የጁገል ኮሪደር መልሶ ልማት ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
4ተኛው ዙር የአለም አቀፉ የጁገል ኮሪደር መልሶ ልማት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን በሀረሪ ክልል ባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ዳይሬክተር ኢንጅነር አሚር ረመዳን አስታወቁ።
ዳይሬክተሩ የመልሶ ልማት ስራውን በ 2 ወራት ግዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን በማስታወስ ጥራትና ፍጥነትን መሰረት ባደረገ መልኩ የመልሶ ልማት ስራው እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የመልሶ ልማት ስራው ቅርሱ ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ በአካባቢው የሚገኙ ፀጋዎችና እውቀትን በመጠቀም እየተከናወነ እንደሚገኝም አክለዋል።
የመልሶ ልማት ስራውን ካሁን ቀደም ተግባራዊ ከተደረጉ የኮሪደር ልማት ስራዎች የተገኙ ልምዶችን በመቀመር ስራዎችን በምሽት ጭምር እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በመጨረሻውና 4ተኛው ዙር የጁገል ኮሪደር መልሶ ልማት ከ 9 ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እድሳት እየተከናወነ ይገኛል።
በአራተኛው ዙር የመልሶ ልማት ስራ አለም አቀፉን የጁገል ቅርስ ሙሉ በሙሉ መልሶ ለማልማት ወደ ስራ መገባቱንም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
4ተኛው ዙር የጁገል ኮሪደር መልሶ ልማት ከ 9 ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ለማልማት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በተገኙበት ዕጣ በማውጣት ወደ ስራ መገባቱ ይታወሳል ።
26/3/18