10/06/2026
የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ወረዳን መሰረት ያደረገ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ዝግጅት መድረክ እያካሄደ ነው።
ሐረር — የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ወረዳዎችን ማዕከል ያደረገ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ እና የሁለተኛውን የሦስት ዓመት የጤናው ዘርፍ የመካከለኛ ዘመን የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ዝግጅት መድረክ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
በዕቅድ ዝግጅት መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኢማን ዜይዳን፤ ወረዳዎች የ2019 በጀት ዓመት ዕቅዳቸውን ሲያዘጋጁ ካለፈው በጀት ዓመት አፈጻጸም ጠንካራና ደካማ ጎኖች ተገቢውን ተሞክሮ መውሰድ እንዳለባቸው አሳስበዋል። ዕቅዱ በጤናው ዘርፍ ላይ ተጨባጭ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ በጥናት ላይ ተመስርቶ መዘጋጀት እንዳለበትም ገልጸዋል።
ዶክተር ኢማን አክለውም በወረዳዎች የሚታቀዱ ዕቅዶች የወረዳውን የመፈጸም አቅም ያገናዘቡ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመው፤ በተለይም በጤና ተቋማት የሚገኙትን የሰው ኃይል፣ በጀት እና የህክምና ግብዓቶች ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በእቅድ ዝግጅት ወቅት ያለፉት ዓመታት ተሞክሮዎችን በመቀመር የ2019 ዓ.ም ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ውጤት ተኮር ማድረግ እንደሚገባ ያሳሰቡት ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የመጨረሻ አቅማቸውን በመጠቀም ለዕቅዱ ስኬታማነት በትኩረት እንዲሠሩ አሳስበዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ የዕቅድ፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ አብዱሰመድ አሊ በበኩላቸው፤ እያንዳንዱ ወረዳ በሥሩ የሚገኙ ከጤና ጣቢያ እስከ ጤና ኬላ ያሉ የጤና ተቋማትን ሁሉ ያማከለ እና ከኅብረተሰቡ የሚነሱ መሠረታዊ የጤና ጥያቄዎችን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ዕቅድ ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል። በመድረኩም በአቶ አብዱሰመድ አማካኝነት የዕቅድ ዝግጅት ሂደቱንና አቅጣጫዎችን የሚያብራራ የመወያያ ጽሑፍ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
ለአምስት ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይ ከወጣው መርሃግብር ለማወቅ የተቻለው በዚህ የዕቅድ ዝግጅት መድረክ ላይ የወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች፣ የጤና ጣቢያ ኃላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ የጤና ባለሙያዎችና አመራሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
10/06/2026
የእናቶችና ጨቅላ ህጻናት ሞት ቅኝት እና ምላሽ አሰጣጥ ላይ ትክረት ተደርጎ መስራት እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ።
የእናቶችና ጨቅላ ህጻናት ሞት ቅኝት እና ምላሽ (MPDSR) ስርዓት ዙሪያ የጋራ ፎረም በሐረሪ ክክልል ተካሄደ።
በጋራ የውይይት ፎረሙ የሐረሪ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ ክልሎች እና ምስራቅ ሀረር ጌይ እንዲሁም የድሬ ደዋ መስተዳድር የእናቶችና ጨቅላ ህጻናት ሞት ቅኝት እና ምላሽ አሰጣጥ የሚሰሩ አካላት ተሳትፈዋል።
በጤና ሚኒስቴር የእናቶች ህፃናትና ወጣቶች
መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ማራማዊት አስፋው እንደተናገሩት የእናቶች እና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ዘርፈብዙ ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የእናቶች ሞት ቅኝት እና ምላሽ ስርዓት የፎረም በእናቶችና ህጻናት ሞት ቅነሳ ላይ ዘርፈ ብዙ ለውጦችን አምጥቷል ብለዋል።
ሁሉም ተቋማት ተቀናጅተው መስራታቸው በዘርፉ የተያያዙ እቅዶችን ለማሳካት አስተዋጽኦ እንሚኖረው ጨምረው ገልጸዋል።
የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ኢማን ዘይዳን በበኩላቸው በክልሉ እና አጎራባች ክልሎችን ጨምሮ በምስራቅ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የእናቶችና ህጸናትን ሞት ለመቀነስ ተችሏል፤ብለዋል።
በተለይም በሆስፒታሎች መካከል ያለው ትስስር አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው መሰል ፎረሞች በጋራ ለመስራት አስፈላጊ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በጤና ሚኒስተር የእናቶች እና ህጻናት ስራ አስፈጻሚ የእናቶች ጤና ዴስክ ሃላፊ ሲስተር ዘምዘም መሃመድ በሆስፒታሎች መካከል የሪፈራል አግልግሎት ከተገቢው መረጃ ጋር በማጣመር የጤና አግልገሎትን በተገቢው መልኩ መስጠት የሚቻል ስርዓትን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ፎረሙ የእናቶች ሞትን ለመቀነስ በሆስፒታሎች እና ክልሎች መካከል ግንኙነትን ማጠናከር እንደስቻለ ተናግረዋል።
09/06/2026
የሀረሪ ክልል ጤና ቢሮ የጤናው ዘርፍ የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ስርዓት ማሻሻያ ሪፎርም ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡
የሀረሪ ክልል ጤና ቢሮ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በጤናው ሴክተር አገልግሎትና አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያ (ሪፎርም) ዙሪያ የተዘጋጀ ከፍተኛ የግንዛቤ ማስጨበጫና የምክክር መድረክ አካሄደ።
በመድረኩ ላይ የቢሮው ማኔጅመንት አባላት፣ የሪፎርም ቴክኒካል ኮሚቴዎች እንዲሁም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የሪፎርም ቴክኒካል ኮሚቴ አባላት በጋራ ተሳትፈዋል።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በጤና ሚኒስቴር የብቃትና የሰው ሀብት አስተዳደር ስራ አስፈጻሚ አቶ ሀብታሙ ደምሴ፤ የጤናው ሴክተር የአገልግሎት እና አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያ ሪፎርም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የሪፎርም ስራ ውጤታማ ለማድረግ የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ስራ አስፈጻሚው አክለውም፣ ሪፎርሙ በተቀመጠለት ፍኖተ ካርታ መሰረት በጥራት እንዲተገበር የጤና ሚኒስቴር አስፈላጊውን የሙያና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠው፣ የክልሉ አመራርና የቴክኒክ ኮሚቴው ለሪፎርሙ ስኬታማነት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በዕለቱ በተካሄደው በዚህ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ በሪፎርሙ ዙሪያ ያተኮሩ መነሻ ፅሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የሪፎርም ቴክኒካል ኮሚቴ በመድረኩ ላይ መሳተፉ በሁለቱ አካባቢዎች መካከል ያለውን የጋራ ቅንጅትና የልምድ ልውውጥ ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተመላክቷል።
ተሳታፊዎቹም በቀረቡት ሰነዶች ላይ ከተወያዩ በኋላ፣ የጤና አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የህብረተሰቡን እርካታ ለማረጋገጥ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
08/06/2026
የአፍሪካ የክትባት ሳምንት በክልሉ በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄዎች መከበር ጀመረ።
ሀረር — በክልሉ የሚገኙ እናቶችና ህጻናትን የክትባት ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመው «የአፍሪካ የክትባት ሳምንት» የተለያዩ የግንዛቤ ማዳበሪያ መልዕክቶችን በማስተላለፍና ህጻናትን በማስከተብ በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች መከበር ጀምሯል።
በክልሉ ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከልና ጤና ማበልጸግ ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ሱለይማን በእለቱ እንደገለጹት፤ ጤናማና አምራች ዜጋን ማፍራት የሚቻለው እናቶችና ህጻናት ተገቢውን የክትባት አገልግሎት ማግኘት ሲችሉ ነው። ወላጆችም ህጻናትን በወቅቱ በማስከተብ ጤናማ ትውልድ የመቅረጽ አገራዊና ቤተሰባዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም፣ ህጻናትን ማስከተብ ከተለያዩ ተላላፊ እና ተላላፊ ካልሆኑ ገዳይ በሽታዎች ለመከላከል ፍቱን መፍትሄ በመሆኑ፣ ወላጆች ህጻናት መውሰድ የሚገባቸውን ሁሉንም አይነት የክትባት ዓይነቶች አስጀምረው ማስጨረስ እንደሚገባቸው በጥብቅ አሳስበዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ የክትባት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ሰይፉዲን አሚን በበኩላቸው፤ በሳምንቱ በሚከናወኑ የንቅናቄ ስራዎች ለማህበረሰብ ክፍሎች ስለ ክትባት ጥቅም ሰፊ ትምህርት እንደሚሰጥና ህጻናትን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በእለቱ በተደረገው የማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ አጫጭር የግንዛቤ ማዳበሪያ መልዕክቶችን ለህዝብ በማስተላለፍ ህጻናት ክትባት እንዲወስዱ የተደረገ ሲሆን፣ የክትባት ንቅናቄው በሳምንቱ በሁሉም ወረዳዎች በሚገኙ የጤና ተቋማት ተደራሽ እንደሚሆን ተጠቅሷል።