15/04/2023
ሹዋል ኢድ በሐረሪ ማህበረሰብ መቼና እንዴት ማክበር ተጀመረ ?
የሐረሪ ሹዋል ኢድ ባህላዊ በዓል ታሪካዊ ዳራ
በኑረዲን አብደላ
የሐረሪ ማህበረሰብ በርካታ እስላማዊ ባህላዊ በዓላት በራሳቸው ወግና እሴት የሚያከብራቸው በዓሏት ባለቤት ነው ። ከነዚህም ባህላዊ በዓሏት ውስጥ ለአብነት
- በሙሃረም አሸራ (10ኛው ቀን ) አሹራ ፣
- አሃታኝ መውሉድ ( በረቢ-አወል 12 ተኛው ቀን ) የሚከበረው ነቢ መውሉድ [ የነቢዩ (ዐሰወ)ልደት ]
- ረጀብ 27 ኛው ቀን የኢስራዋ ሚዕራጅ ፣
- በረመዳን 17 ኛው ቀን የበድር ድል መታሰቢያ ዮመል በድር በድሪ-በሪ (በርቲ በርቲ )
- በረመዳን 27 የኸቲመት የሌይለቱል ቀድር ምሽት እና - ሹዋል ወር በ8ተኛው ቀን የሚያከበሩት የሹዋል ኢዲ በዓሏት ጢቂቶች ናቸው ።
ዛሬ በዚህ በሐረሪ ማህበረሰብ ባህላዊ በዓላት አንዱ በሆነው የሐረሪ ባህላዊ ሹዋል ኢድ በዓል ታሪካዊ ዳራ እንቃኛለን
የሹዋል ኢድ አጀማመር
የሹዋል ኢድ ታሪካዊ ጅማሬ በሐረሪ ማህበረሰብ በትውፊት በተገኘው በርካታ መረጃ መሰረት ይህ የሐረሪ የሹዋል ኢድ ጅማሬ በ16 ተኛው ክ/ዘመን የኢማም ኢብራሂም አልጋዚ ሐበሻን ማቃናት ዘመቻ ላይ የነበሩ የኢማሙ ሰራዊት እና ኢማሙ በረመዳን መጨረሻ ወር ለኢድ ፍጥር በዓል ሐረር ከተማ ለመድረስ አልቻሉም ይህ ለዘመናት የሐረሪ አባቶች ፣ አዛውንቶችና የሐገር ሽማግሌዎች በትውፊት ይነገር የነበረ ነው ። ይህንን በተመለከተ የኢማሙን ዘመቻ የዘገበው አረብ ፈቂ
ፈትሁል ሐበሻ ጸሃፊ ሼኽ ሸሐበዲን የኢማሙ በረመዳን ወር ያደረጉት ዘመቻ ውሎ በአዋሽ አካባቢ እንደደረሱ በረመዳን ወር መታመማቸውን ያስነብባል
[ ሙስሊሞች በአገሪቱ ሁሉ ተበተኑ ። ብዙ ወርቅ ፣ ብርና ሐር ሰበሰቡ ። አንዳንዶቹ ምርኮ ሰብስበው ሲመለሱ ሌሎች በተራቸው ለመሰብሰብ ይዘምታሉ ። በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ ኢማም አህመድ ታመሙ ፣ በረመዳን ወር ሕመሙ ጠናባቸው ። ሃያ ቀናት በዚህ ሁኔታ ቆዩ ። ሙስሊሞች በኢማሙ መታመም ያለቅሳሉ ። አላህን በጽኑ ወደ መለመን ገቡ ። ኢማሙ በሕመም ላይ እያሉ ሙስሊሞች ብዙ ትርፋት ሰበሰቡ ። የአዋሽ ወንዝ ውኃ ቀነሰ ። አበሻን የማቃናት ዘመቻ ፣ ገጽ 167-168 ]
የእንግሊዘኛው Futuh al Habash ወይም
The Conquest of Abyssinia ኢማም አህመድ ኢብራሂም አልጋዚ በረመዳን ወር በአዋሽ ወንዝ አካባቢ ቆይታቸውን እንዲህ ያስነባል በፖል ሊስተር ከአረበኛ ወደ እንግሊዝኛ በተተረጎመው
[ Imam Ahmed may Almighty God have merecy upon him, fell sick . The malady worsened during the month of Ramadan and he rested twenty days. The Muslims wept because the Imam was ill, and besought Almighty God for him.
While the Imam was sick, the Muslims accumulated vast b***y. For the flood on the river Awash abated, and its water level fell. Then the Muslim cavalry crossed the river Awash while the Imam remained in his camp. Conquest of Abyssinia, p 166 ]
ከላይ በቀረበው ዘገባው መሰረት ኢማሙና ሰራዊታቸው በረመዳን ወር 935 ዓመተ ሒጅሪያ ወይም በፈረንጆቹ Saturday May 9, 1529 አዋሽ አካባቢ ላይ እንደነበሩ መረጃው ያመለክታል [ እንደ ላይኛው ገጽ 166 ] ። የሐረሪ አባቶችና የሐገር ሽማግሌዎች ትውፊት ኢማሙና ሰራዊታቸው ወደ ሐረር በመመለስ መንገድ ላይ እያሉ የኢድ በዓል በጉዞ ያልፋቸዋል ኢማምና ሰራዊታቸው የሹዋል ወር የመጀሪያዎቹ ቀናትና የኢድ አልፍጥር ( ኢድ ቀን) ከአለፈ በሃሏ ሐረር ይደርሳሉ ፣ ሐረር የደረሰው የኢማም ሰራዊት እና ኢማም የሹዋል ወር የመጀመሪያ ሳምንት ቀናት ጾምን በመጾ በሹዋል ስምንተኛው ቀን በሐረር ሹዋል ጾም ጨርሰው ፈሰጉ አፍጥረው (ጾማቸውን ይፈታሉ ) ሹዋል ስምንተኛው ቀን በሐረር የሹዋል ኢድ አከበሩ ። ይህ የመጀመሪያው ታሪካዊ በሐረር ሹዋል ኢድ መከበር መነሻ ተደርጎ በበርካታ የሐረሪ አዛውንቶች በትውፊት ከጥንት አባቶች እስከ ዛሬው ትውልድ ሲቀባበሉት የመጣ የሐረሪ ትውፊታዊ መረጃ ነው ። በተመሳሳይ የስልጤ ማህበረሰብ የሹዋል ባህላዊ ኢድ እንደ ሐረሪ እንደሚያከብሩ የስልጤ ማህበረሰብ መረጃዎች ያመለክታሉ ፣ የስልጤ ማህበረሰብ እንደ ሐረሪና ሌሎች ብሔሮች በ16 ክ/ዘመን በኢማም አህመድ ሐበሻን ማቃናት ዘመቻ ተሳታፊ ካደረጉ ማህበረሰብ አንዱ መሆኑ የታሪክ መዛግብት ያመለክታሉ የሹዋል ባህላዊ ኢድ አከባበር የስልጤ ማህበረሰብ የጀመረው እንደ ሐረሪዎች ከኢማሙ ዘመቻ ጋር በተያያዘ ነው ወይስ ሌላ ምክንያቶች ወደፊት በታሪክና በአንቶሮፖሎጂ ምሁራን ጥናት የሚጥና ይሆናል ወይም የተጠና ካለም ዝርዝር መረጃው ይቀርባል ። ወደ ሐረሪ የሹዋል ባህላዊ ኢድ አጀማመር ስንመለስ ሌላው የትውፊት መረጃ አመልካች የ18 ኛው የሼኽ ሐሺም ቢን አብዱለዚዝ አል ሐረሪይ (1702-1768) የተባሉ ታላቁ የሐረሪ የሐይማኖት ምሁር የሹዋል ስድስቱን ቀን የጾመ አመቱን ሙሉ ከጾመ ጋር እኩል ምንዳ አለው የሚለውን ሐዲስ በመንተራስና የኢማም አህመድ በዘመቻ ምክንያት በሹዋል 8 ተኛው ቀን ያከበሩትን ባህላዊ የሹዋል ኢድ ሼኽ ሐሺም ሐረሪዎች በዝክሪ ፣ በመንዙማ ፣ በመውሉድ ጡንሱስ (በምሽት) በነቢጋር - አዋች ሹዋል 6 ተኛው ምሽት ፣ 7ተኛ ምሽትና 8 ተኛው ቀን እስከ አስር ሰላት ድረስ በማክበር በዓሉ እንዲጠናቀቅ አስደረጉ ። ይህንን ቀጣይ በዓላት በአርጎበሪ በሼኽ ሐሺም ጎረቤት በሹሉም አህመድና እንዲሁም በአሱሚበሪ 07 ቀበሌ አካባቢ በነበረው ነቢጋር እና በአው አቅበራ እየደመቀ መከበር ተጀመረ ።
በሌላ ተዛማች የሹዋል ኢድ ታሪካዊ አጀማመር በተመለከ የሐረሪ ስነቋንቋና የሐረሪ ማህበረሰብ ባህልና ወግ ላይ በርካታ ጹሁፎችን ያስነበበን ጸሃፊ አሚር አሊ አቂል የሚከተለውን የሹዋል ኢድ መከበር መነሻ ምክንያት በትውፊት ያሰባሰበውን የሚከተለውን ያስነበናል ።
[ በአንድ ወቅት ይኖሩ የነበሩ የሐረር አሚር የአሚሩ ዘመን እና ስሙም በግልጽ ባይታወቅም ይህ አሚር ሹዋል ኢድ እንዳይከበር አዋጅ አውጥተው ያሳውጃሉ በዚህም አዋጅም በሐረር ሹዋል ኢድ እንዳይከበር አስደረገ ነገር ግን ሹዋል ኢድ በሚከበርበት ቀን ኢዱን የሚያከብሩበት የሚጠቀሙበት የድቤ ከረቦ በተአምር ወደ ሚከበርበት የሹዋል ቦታ በመድረስ ያለሰው ራሱ ድቤ እየመታ ቦታው በድቤ ይቀልጣል ፣ ወሬው ለአሚሩ ይደርሳል አሚሩም ሹዋል ኢድ የከለከሉበትን አዋጅ በመሻር ሹዋል ኢድ እንዲከበር በመፍቀድ ያውና ሹዋል ኢድ እስከዛሬ በሐረሪዎች ሳይቋረጥ እየተከበረ ይገኛል ። ሐረሪ - ኻድነት ፣ አሚር አሊ አቂል ፣ ገጽ 92-93 ]
በሐረር ለዘመናት በዘለቀው የሹዋል ኢድ ባህላዊ በዓል እያንዳንዱ የሐረሪ ማህበረሰብ ተሳትፎ በነቂስ ቢኖረውም በአርጎበሪ በኩል በሹሉም አህመድ አካባቢ ለሚደረገው በዓል ድጋፍ የአርጎበሪ አካባቢ ያሉ አፎቻዎች ና ሼኽ ሐሺም አፎቻ ድጋፍ ሲያደርጉ በአሱምበሪ ለአው አቅበራና ለነቢጋር ድጋፍ ያደርጉ የነበሩት በአሱምበሪ አካባቢ የነበሩ አፎቻዎችና ኢናይ አቢዳ አፎቻ ድጋፍ በማድረግ በዓሉ እንዲከበር ያደርጉ ነበር ።
በሐረር የሹዋል ኢድ በዓል የከረቦ ድምቀት ድቤና መንዙማን ታሪካዊ አጀማመር በተመለከተ አንድ ጥናታዊ ዳሰሳ " አዋቻች ሚነት ዋ ኩትዋ ቂያስ ቢሳሎት" ( የቁዱሳን ምንነት እና ያሉበት ልኬት ጥናት ) በሚል ሰኔ 2004 በሐረር ባህልና ቅርስ ቢሮ በተደረገው ዝርዝር ዘገባ ጥናት ላይ ከሼኽ አባዲር በሃሏ አዳዲስ የማህበረሰቡን ኢስላማዊ ባህላዊ እሴት ስኬት ያሳኩ አዋቻች ውስጥ ሁለቱ ተጠቅሰዋል እነርሱም ሸሪፍ አህመድ ( ሹሉም አህመድ) እና አው አቅበራ እነዚህ ሁለቱ ሹዋል ከረቦ (ድቤና መንዙማ) ከሹዋል 6 እስከ ሹዋል 8 በተከታታይ ለሶስት ቀናት የሹዋል ኢድ ከረቦ ( ድቤ ) ያስጀመሩ መሆኑ የጥናቱ ሰነዱ መስረጃ ያመለክታል
በሐረር አርጎበሪ በሹሉም አህመድ አዋች የሚከበረው የሹዋል ኢድ ከረቡ ( የመንዙማ ከበሮ ) በሹዋል 6ተኛና 7ተኛ ከምሽቱ አምስት ሰዓት እስከ ፈጅር ሰላት በሹዋል 8ተኛው ከምሽት ጀምሮ ከጠዋቱ እስከ አስር ሰላት ባለው ስአታት አርጎበሪ መሐል ገበያው ላይ ተከብሮ ይውላል ።
የአሱሚ በሪው ( አው አቅበራ ) ዱሮ ፣ዱሮ በ 07 በርበሪ ዘር አካባቢ በነበረው አዎች ( ነቢጋር ) የሹዋል 6ተኛው ምሽትና የሹዋል 7 ምሽት በነቢ ጋር ቤት በመንዙማ ይደምቅና ሹዋል 8 ቀን ከጠዋቱ እስከ አስር ሰላት ባለው ሰዓታት በአሱሚ በሪ መሐል ገበያ ዱንኳን ተደርጎ እዛው በአሱሚ በሪ በአው አቅበራ መስጂድ አካባቢ በመደቀ መልኩ ይከበር ነበር ። የአሱምበሪ በር መሐል በሹዋል 8ተኛ ቀን ገበያ ላይ የሸራ ዱንኳን በመትከል ማክበር የተጀምረው በዓጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1945 ዓል ወዲህ ማስጀመራቸው አው ላዚም ዩሱፍ አህመድ ኡመር ለHMN ቲቪ ቃለ መጠይቅ ማስረዳታቸው እና ከ07 በርበሬ ሰፈር ከነበረው ነቢ-ጋር የሹዋል ምሽት 6-7ተኛ በነቢጋር በሹዋል 8ተኛው ወደ አሱሚ በሪ ሸራ ድንካን ውስጥ እንዲከበር ያስደርጉ እንደነበረና ነገር ግን በደርግ ስርዓት ከ1971 ዓል ወዲህ ከበርበሬ ሰፈር (07ቀበሌ) ነቢጋር ወደ (አሱሚ በሪ ጋር ) በጆጎል አሱሚይ በሪ በሩ ውስጥ ባለው ክፍል ሹዋል 6ተኛው ምሽት - ሹዋል 7 ምሽቶች እና ሹዋል 8 ቀን በተከታታይ በአሱሚ በሪ ላይ የከረቦ (ዲቤ) መንዙማ ከ1971 ዓል ጀምሮ ማስጀመራቸው የአው ላዚም ዩሱፍ አህመድ ኡመር ቃለመጠይቅ ያስረዳል ።
በሐረሪ ማህበረሰብ ሹዋል ኢድ እጅግ የደመቀና የአማረ ባህላዊ በዓል ሲሆን በዓሉ በማንኛውም እድሜ የሚገኝ ሰው ህጻናት ፣ ወጣቶች ፣ ልጃገረዶች ፣ አዛውንትና ሽማግሌዎች የሚሳተፉበት ነው
ህጻናት [ወዚዞ በሓሬይ] ለከረቦ እንጨት መሰብሰብ ፣
ጥንት የጾታ መደበላለቅ ባለነበረበት ዘመን በቤተሰብ ስምምነት ትዳር የሚመሰረተው በዚህ በዓል ተሻሽሎ ለትዳር የተዘጋጀ ጎረምሳ በሹዋል ኢድ የመረጣትን ኮረዳ ሽማግሌ በመላክ በሐላል ትዳር መመስረት ፣ ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች በባህል ልብሳቸው አምረው ተውበው በዓሉን ማድመቅ ፣ እናቶች አባቶች በሹዋል ኢድ ከረቡ አስፈላጊ ዝግጅት በማድረግ መሳተፍ [ምግብና ቀህዋ(ቡና)] ወዘተ በማቅረብ ፣ በአጠቃላይ የሐረሪ ማህበረሰብ በዚህ በዓል በባህላዊ አልባሳት አጌጠው ፣ በመንዙማ ዝክሪ የሚሳተፉበት ታላቅ ፌሽታ በተጨማሪ በመላው ኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታ በውጭ ሃገራትም የሚኖሩ ሐረሪዎች ከዘመድ አዝማድ በሐረር ከተማ በየዓመቱ በሹዋል ኢድ በነቂስ ተሰባስበው አምረው በሐረር ከተማ ዙሪያ ካሉት ብሔረስቦች ከኦሮሞ ፣ አርጎባ ፣ ሱማሌ ጋር አንድ ላይ በደመቀ ስርዓት በዓሉን ያከብራሉ ።
በሐረሪ ማህበረሰብ የሹዋል ዒድ ባህላዊ በዓል አከባበር ከተጀመረ ጀምሮ እጅግ ለበርካታ አመታት በሐረር ከተማ በልዩ ልዩ ድምቀት በዓላት ቢከበርም እስከዛሬ ወደር ያልተገኘለት እጅግ በደመቀና ሐረር ከተማ በሹዋል ኢድ እንግዶች ጢም ብላ የተጨናነቀችበት በመላው ኢትዮጵያ የሐረሪ ማህበረሰብ አፎቻ ( የሐረሪ በሐላዊ ተቋም ) በስፋት የተሳተፉበት በደርግ ስርዓት በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1973 ዓል በሐረር የተከበረው የሹዋል ኢድ ባህላዊ በዓል እጅግ በአማረና በመደመቀ የዘመናችን ታላቅ የሐረሪ ሹዋል ኢድ በዓል ሆኖ በታሪክ ሰነድ ሆኖ ተሰንዷል ።
የ1973ቱ በደርግ ስርዓት የሐረሪ ሹዋል ባህላዊ ኢድ ያማረበትና ሊሰምር የቻለበት ዋና ዋና አብይ ምክንያቶች
- የሐረር እና የአዲስ አበባ ላቂ አፎቻ በጋራ መስራት
-የሐረሪ ባህል መአከል በ1972 (አዳእ ጋር መመሰረት )
-የሐረሪ ብሄረሰብ ባህላዊ ኪነት ( መስኖይ ) መመስረት
-በሐረሪ አዳዕ ጋር መዕከል በርካታ በጎ አድራጎት ሐረሪዎችን በመላው ኢትዮጵያ መሰባሰብ መቻል
- የዛ ዘመን የሐረሪ ሐገር ሽማግሌዎች አባቶች የተጫወቱት ታላቅ ሚና (የአው ሐጂ ዘከሪያ ሐሚድ ቡድን )
- የዛ ዘመን ወጣቶችን ያሰባሰበው የእስታድ ረመዳን ዱዋሌ ስብስብ የተጫወተው ሚና
-የዛ ዘመን የሐረሪ ሴቶች ማህበር ወጣቶችና እናቶች የተጫወቱት ሚና
-የሐረሪ አዳዕ ጋር በርካታ አርቲስቴቶችን ማሰባሰብ
- እያንዳንዱ ሐረሪ ማህበረሰብ ከግል እስከ ቡድን በበጎፍቃደኝነት በመንቀሳቀስ የ1973 ሹዋል ባህላዊ ኢድ በሐረር ከተማ የመንግስት መስሪያ ቤት ፣ ት/ቤቶች ተዘግተው የእረፍት ቀን እውቅና በማግኘት በይፋ በዓሉ ተከበረ ፣ የ1973 የሐረሪ ሹዋል ኢድ በሐረር በሁለት ታላላቅ መርሃግብር የጠዋቱ ፈረቃ ከ2 ሰዓት - 6 ሰዓት በሐረር ሲኒማ ቤት የባህል ዘፈን ፣ ድራማ ፣ ኪነት ፣ ባህላዊ ጭፈራ ፣ ግጥም ፣ የመስኖይ ባህላዊ ኪነት ዝግጅት ፣ ታዋቂ እንግዶች ንግግር ያደረጉበት ፣ ባህላዊ ምግብና ለስላሳ መጠጥ የቀረበ ሲሆን ፣
ሁለተኛው የሹዋል ባህላዊ ኢድ በሐረር አዋች በሹሉም አህመድና በአው አቅበራ የሚቀርበው መንዙማና ከረቦ (ድቤ) ባህላዊ መንፈሳዊ ዝክር ነው ይህም ከቀኑ 6 ሰዓት እስከ አሥር ሰዓት ላይ እጅግ በተዋበ በአማረ ሁኔታ ማህበረሰቡን በበዓሉ ተሰትፎ በማድረግ የታደመመበት ነበር ። በሐረር 1973 ዓል የሐረሪ ማህበረሰብ የሹዋል ኢድ ባህላዊ ኢድ አንድ ከፍተኛ እድገት ደረጃ ላይ መድረሱና አመልካች ነበር ። የሐረሪ አርቲስቶች የሹዋል ኢድ በዓልን አስመልክቶ እስከዛሬ የዚህ በዓል መገለጫ የሙዚቃና የኪነጥበብ ሥራ የሆነው
"ሹዋል ኢዴይ ኢኝኛሌ ኢዴይ "
የተሰኘው ታላቅ የሙዚቃ ቅንብር ስራ የተሰራውም በ1973 በሹዋል በዓል የግጥም ጸሃፊ በድሪ ዩሱፍ ሊማይ (ጆን ሊማይ) የዜማ ሥራ በድሪ ዩሱፍ ሊማይ የቀረበና እንዲሁም ድምጻዊው እራሱ በድሪ ዩሱፍ ሊማይ የቀረበ ሲሆን ይህ ዘፈን የሐረሪ ሹዋል ኢድ በዓል መገለጫ ምልክት ሆኖ እስከዛሬም ቀጥሏል የዚህ ግጥም ኪነት የሐረሪን ማህበረሰብ ለሹዋል ባህላዊ ኢድ ያለውን ከፍተኛ የላቀ ባህላዊ እሴት አመልካች ነው ። የአርቲስት በድሪ ዩሱፍ ሊማይ ሹዋል ኢዴይ በሐረሪ ቋንቋ ሙሉ ግጥሙ የሚከተለው ሲሆን ትርጉሙ ከታች በቅንፍ በአማረኛ በግርድፉ ቱሩጎሜው የራሴ ነው
ሹዋል ኢዴይ ኢኝኛሌ ኢዴይ
( ሹዋል ኢዳችን የኛ ኢዳችን)
ዚመሳ ተስቲው ተሱሪ ኢዴይ
( በጋራ ደስታን የምታስተናግድ ኢዳችን)
አመት አመትዞውም ነግዲራሽ ኢሊ ኢዴይ
( አመት አመቱም እናከብርሻለን ታላቅ ኢዳችን )
ደድ ዳይ ፊሪ ዙግማን ሐለሻ
( ቀዳሚ የፍቅር አንድነት ፍሬ ያለሽ)
ጉድጉዳ ዋደላን ቲዳብላሽ
(ልጃገረድ ኮረዳና ጎረምሳን የምታገናኚ )
ናግዲራሽ አዜባች ዳድ ማኽቱትን ታቢርናሽ
( ናከበርሻለን ወጣቶች የፍቅር ብርሃን ስላበራሽ )
አዜባች ያጋድሬዛል ኢዳ
( ወጣቶች የሚከበሩት ፌሽታ)
ኡማ ባባች አውዋ አያች
( አያቶች ወላጆች የሚያከብሩት ፌሽታ )
ቢቀሉ አዜባች ይልቦዛል ተስቲ ኢዳ
( እደጉ ተመንደጉ የሚባልበት የደስታ ፌሽታ) ሐለሽ ኢዴይ ዚደድ ዋሬጋ
( አለሽ የኔ ኢድ ያማረ ፍቅር )
ሹሉም አህመድ አው አብቃራ
( እንደ ሹሉም አህመድ እንደ አው አብቃራ [ ሐረር ሹዋል ኢድ የሚከበርበት ታሪካዊ ቦታ] )
ዚዲልቅ ማራኻ ዚማትናሰብ ቶያ
( የከረቦ (ድቤ) መንዙማና የመተጫጨት ሰፈር )
ዚክሪ ከራቡ ኸሹም አብሽር
( ዚክሪ መንዙማ ከረቦ( ድቤ) አብሽር ያማረ)
ተስቲ ቻፍቸፍቲ ኸሹም አብሽር
( የደስታ መንዙማ ውዝዋዜሽም አብሽር ያማረ )
ዋቴ ናጋድራና ኩሊዚናም አብሺር
( ያውና እናከብራለን ሁላችንም አብሽር አምሮብናል )
** *በቅንፍ ያቀረብኩት የራሴን በግርድፉ የቀረበ ትርጉምና የግጥሙ ይዘት ነው ***
የሐረሪ ሹዋል ባህላዊ ኢድ በሐረሪ ማህበረሰብ ውስጥ ከአምስት መቶ አመታት በላይ ከራሱ ባህልና ወግ ተጣምሮ ያሳደገው ይህ ባህላዊ በዓል በውስጡ በያዛቸው በርካታ የማህበረሰቡ እሴት ተዳምሮ በሐረሪ በማይዳሰሱ ቅርስ በ UNESCO ለማስመዝገብ ከ2019 ጀምሮ በሐረሪ ማህበረሰብ እና በሐረሪ ክልል መንግስት የሐረሪ ሹዋል ኢድ እንቅስቃሴ መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን ይህ ባህላዊ ኢድ የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ህብረተሰቡ ይህንን የቱሪስት እንዱስትሪን ለልማት በመጠቀም የአካባቢውን ባህል ፣ ወግ እና እሴት ለትውልድ በማሳወቅና በማሻገር በዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት ተመዝግቦ ለሃገር ሐብትና ለህብርተሰቡ ባህል እድገት ተጠቃሚ ማድረግ በሁላችንም ይጠበቃል ።
19/02/2023
በ20ኛው ክ/ዘ ሐረር ያስተዳደሩት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የሐገር ሽማግሌዎች
በኑረዲን አብደላ
ይህ በፎቶ የምታዩት በ20ኛው ክፍለ ዘመን ሐረር ከተማን ያስተዳድሩ የነበሩት በከፍተኛ የሥራ ቦታ ላይ የነበሩና ታዋቂ የሐረር ሽማግሌዎች ናቸው ከፊት ለፊት የሚታዩት የሚከተሉ ናቸው ።
አሚር ሱፍያን
አሚር ሱፍያን ቢን አሚር አብዱላሂ ቢን አሚር ሙሑመድ
የአሚር አብዱላሂ ሁለተኛው ወንድ ልጅ ናቸው ። አሚር ሱፍያን ኃሏ ላይ በዓጼ ኃ/ሥላሴ ትእዛዝ በመርፌ በጆግላ ሆስፒታል ተመርዝው በተከታታይ ከልጃቸው ጋር የተገደሉ ናቸው ።
ከቢር አህመድ ላዚም
ከቢር አህመድ ላዚም የእስልምና ሐይማኖት መምህርና ሊቅ ናቸው
ቃዲ ሙሑመድ ሙዲር
ቃዲ ሙሑመድ ሙዲር ወይም አው ፈቂ ሙሑሙድ ሙዲር ይባላሉ ። ታላቁ የሐረር የሸሪያ ቃዲ (ዳኛ) ናቸው ። ቃዲ ሙሁመድ የአሚር አብዱላሂን ሴት ልጅ አመቱላ ቢንት አሚር አብዱላሂን ያገቡ የሐረር ታዋቂ ቃዲ ናቸው ።
አው ሐጂ አህመድ አቦኝ
አው አህመድ አቦኝ ወይም ሐጂ አህመድ አቦኝ የሐረርጌይ ታዋቂ ባላባትና ከአርባ አመት በላይ በሥራ ሃላፊነት በተለያዩ ቦታ ላይ በዲዋን ሹም ፣ የጉርጉራ አካባቢ ዶጊኝ ፣ የራስ መኮንን የግል ሃብት ወኪል በመሆን አገልግለዋል ።
አው አብዲሱብሃን ኡመር አሊ
በ19 ኛው ክፍለ ዘመን የሐረር አሚሮች እና የአሚር አብዱላሂ ቤተሰቦች ከሶማሌ ጎሳዎች ከጊሪዎች ያደረጉት የትዳር ትሥሥር በምሳሌነት የሚጠቀሰው በጊስቲ አሚና ገራድ (የጊሪ ሶማሌ ጎሳና) በአው ኡመር አሊ ሞቲ የተደረገው የጋብቻ ትስስር የበለጠ በሐረሪዎችና በሶማሌ ጎሶ ይበልጥ አንድ ላይ ለማስተሳሰር በአሚር ቤተሰቦች በምሳሌነት የሚታይ ትልቅ ትስስር ነበር :: ለዚህ የአሚር ቤተሰቦች ሲያስረዱ አው ኡመር አሊ ሞቲ የአሚር ኡብዱላሂ አጎት እና ቤተሰብ ሲሆኑ ከጊሪ ሶማሌ ባላባት ከገራድ ቤተሰብ የሆኑትን ጊስቲ አሚና ገራድን አግብተው ከሶማሌ ሐረር አምጥተው ኑራቸውና ትዳራቸውን ሐረር ላይ የመሰረቱት አው ኡመር አሊ ሞቲ ትዳሩም ሰምሮ ሰባት ልጆች ይወልዳሉ ከእነሱም አንዱ
አው አብዲሱብሃን ኡመር አሊ አንዱ ታዋቂ የሐረር ሰው ናቸው
አው ሐጂ አብዱላሂ አሊሳዲቅ
በሐረር እስልምና መስተዳደር የዲዋን ሹም ረኢስ አል ሙስሊም ሐረር ፣ ዲፕሎማት ፣ የዓጼ ምኒልክ መንግስት የውጭ ጉዳይ መልክተኛ ፣ በዓጼ ምኒልክ የንግድ ጉንኝነት የአሜሪካ መልክተኛ በመሆን በከፍተኛ ሃላፊነት ለሃገር ያገለገሉ የፖለቲካ ሰው ነበሩ ።
አው ሙሑመድ እድሪስ
የሐረር ታዋቂ የሃገር ሽማግሌ ( አባት )
አው ዩሱፍ በርኸድሌ
አው ዩሱፍ በርኸድሌ በሐረር የሃገር ሽማግሌነት ያገለገሉ ሲሆን በተለይም በዓጼ ምኒልክና በሐረር መካከል በተደረገው ከጨለንቆ ጦርነት ማግስት የሐረርን ህዝብ በመከል ዓጼ ምኒልክ ፊት በመቅረብ ስምምነት ከተፈራረሙት ሐረሪዎች አንዱ ሲሆኑ በመቀጠልም ከአው አህመድ አቦኝና ከሐጂ አብዱላሂ አሊ ሳዲቅ በመቀጠል የዲዋን ሹም በመሆን አገልግለዋል ።
ቃዲ ሐጂ ዮኒስ
የሐረር የሸሪዕ ቃዲ (ዳኛ) የነበሩና በሐረር በድሪ በሪ አካባቢ ይኖሩ የበሩ የታወቁ የዘመኑ ቃዲ ናቸው
የመረጃው ምንጭ
ኡማ ሃኒም ጃሚእ ቃለ መጠይቅ
የሐሪናየሐረር ከተማ ታሪክ 1998
Sixteen letters of ras makonen, sief.m 1974
11/02/2023
ቶጲያ ስለ አሚር ኑር
የተሳሳተ መረጃ
ቁጥር 8
በኑረዲን አብደላ
ስለ አሚር ኑር የተሳሳተ መረጃ
የቶጲያ ጸሃፊ በመጸሃፉ በገጽ 368 ስለ አሚር ኑር የጻፈው የሚከተለው ያስነብቧል
[ ወዚር ሙጃሂድ ከኢማሙ ጀግና ፈረሰኛ ተዋጊዎች መካከል አንዱ የነበረ ሲሆን የኢማሙ የእህት ባል እንደሆነም ይታወሳል ። ቶጲያ ገጽ 368 ]
ለአሚር ኑር አባት ከሆነ ጥቅሱ ትክክል ሲሆን በአውሮፖ አጻጻፍ ስልት Last Name ከሆነ ለአሚር ኑር ስል ሆን
ከላይ በቶጲያ መጸሃፍ እንደቀረበው አሚር ኑር የኢማሙ የእህት ባል እንደሆነ በማድረግ ያስነብቧል ። ይህ የነጃሺ ከዲር ምንያህል የታሪክ ጥናት ደካማና ምንም የምርምር ጥናት በአካል ተገኝቶ ስለ ሐረር ከተማ ፣ ስለ ሐረሪ ማህበረሰብና ስለ ሐረር አሚሮች ያደረገው እንደለሌለ አመልካች ነው ። ስለ አሚር ኑር ቤተሰቦች አሁን ድረስ የ 45 ተኛ ተከታታይ የቤተሰብ አባላት የአይ ከዲጃ በክሪ ( አላህ ለጀነት ይበላቸውና ) ቤተሰብ አሁንም በሐረር አሚር ኑር ወረዳ በቀበሌ 01 በአሚር ኑር ዶሪ ይገኛሉ ።
በአሚር ኑር ቢን ሙጃሂድ እና በኢማም አህመድ ኢብራሂም አልጋዚ (ግራኝ) መካከል ያለውን የቤተሰብ ዝምድና ገናና ታሪክ ነጃሺ ከዲር አለማወቁ የጥናቱ ውጤት ደካማ መሆኑ አመልካች ነው ። ለዚህ ነበር ነጃሺ ወረቤ ወይም አዲስ አበባ ላይ ተቀምጠህ ስለ ገናና የሐረር ታሪክ በመጸሃፍና በGoogle መጻፍ ሳይሆን በአካል በቦታው በመገኘትና ጊዜ በመስጠት ጥናትና ምርምር ዋጋ በመከፈል እንጂ ውጤትና ስኬት ትክክለኛ መረጃ የሚገኘው በሩቅ በቢሮ በወራቤና በአአበባ ቢሮ ጠረጴዛ ላይ የምትጽፈው እንዲህ ለሃሰት ይዳርገሃል ።
ለነጃሺ ከዲር ለአሳሳተው መረጃ ትክክለኛ መረጃ
በኢማም አህመድና በአሚር ኑር ያለው ዝምድና የሚከተለው ነው
ኢሚም አህመድ ኢብራሂም አልጋዚ ለአሚር ኑር ቢን ሙጃሂድ አጎቱ ነው ። አሚር ኑር ቢን ሙጃሂድ የኢማም አህመድ ኢብራሂም አልጋዚ የእህት ልጅ መሆኑ ነው የሚከተለው መረጃዎች ያመልክታሉ ።
History of Harar and Hararis (2015)
[ Dil Wanbera later married Amir Nur bin Mujahid, her husband's nephew, p 69 ]
ከዓጼ ልብነድንግል እስከ ዓጼ ቴዎድሮስ በሚለው ከተክለጻዲቅ መኩሪያ ገጽ 72 የሚከተለው ያስነብባል
[ 1552 ዓል ኑር አህመድ ( ኑር ኢብን ሙጃሂድ ) የሚባል የግራኝ አህመድ የእህቱ ልጅ ተነስቶ የሐረርና ያካባቢው እስላሞችን ሁሉ አለቃ አድርገውት ነበር ። ]
የግራኝ አህመድ ወረራ ተክለጻዲቅ ሞኩሪያ በገጽ 815 የሚከተለው ያስነብባል
[ ኑርን የግራኝ የእህቱ ልጅ መሆኑን ከማረጋገጥ ጋር ....]
በ2007 ሐረር መልኒየም የአሚር ኑር አርባ አራተኛ የልጅ ልጅ የነበሩት አይ ከዲጅ በክሪ( አላህ መርሂም) ሲያስሩዱኝ ከቅድመ አያቶቻቸው የሰሙት አሚር ኑር ከጦር ግንባር ሲመለሱና የኢማም አህመድ እህት የኑር እናት በሐረር አሚር ኡጋ ላይ ህዝብ ፊት እንዲህ ብሎ ነበር አሚር ኑር እናቱን ያናገሯት
[ አዬይ አይ ነስሬይ አይ በቱላ ቀሃት አላመገን ሞተሌሽ ]
ትርጉሜ እምዬ እናት ነስራ የበቱላ ልጅ አላመገን ሞተ
ቶጲያ የተሳሳተ መረጃ በገጽ 369
[ አሚር ኑር ባደረጋቸው ጦርነቶች ምን ያህል እንደተሳካለት ግን ዝርዝር መረጃ አይገኝም ። ምንም እንካን ሁሉንም ሙስሊም ማህበረሰቦች በስሩ ማድረግ ባይሳካለትም በሀረር ሙስሊሞች ላይ ስልጣኑን አደላድሎ ነበር ። ገጽ 369 ]
ከላይ በቀረበው የቶጲያ ጸሃፊ አሚር ኑር ቢን ሙጃሂድ ምንም ስኬት ስራ እንዳልሰራና ዝም ብሎ ጊዜውን ያባከነ ተራ አሚር አድርጎ አቅርቦታል ። ቶጲያ ጸሃፊ ስለ አሚር ኑር ብዙ ምርምና ጥናት አለማደረጉ አመልካች ነው ። አሚር ኑር ቢን ሙጃሂድ በሐረር አሚሮች ታሪክ ስኬታቸው በወርቃማ ታሪክ ካጻፉ ምርጥ ስኬታማ አሚሮች አንዱ ነው ።
ቶጲያ ጸሃፊ ስኬት የሚለውን ቃል ያወቀም አይመስለኝም ። ስኬት የአንድ ማህበረሰብ እድገት ያልነበረን ማስጀመር ፣ የነበረን ማሳደግ ፣ ለመጪው ትውልድ በተከታታይ ሳይጠፋ አሻራ አስርፎ ለስንት ዓመታት የሚዘከር በመንፈሳዊና በቁሳዊ በሚታዩ አሻራዎች ከትውልድ ትውልድ የተሻገረ ታላቅ ስኬት ማስቀጠል ነው ።
የዘመኑ ታሪክ በወርቅ ቀለም በድምቀት አሚር ኑር ቢን ሙጃሂድ ካሳኩት የሚከተለውን መረጃ እናቀርባለን
የጀርመኑ Ulrich Braukamper " the Islamization Harar plateau " በሚለው ጹሁፋቸው አሚር ኑር እስልምናን ስልጣኔውን እንዴት አድርገው ከጥፋት እንዴት አድርገው እንደታደጉት የሚከተለውን ያስነብባል
[ Islam was reduced to small pockets within anon- muslim environment.The most important was the town of Harar which Amir Nur bin Mujahid had ordered to be surrounded by a wall to make it inaccessible to invaders. According to the Oral traditions, Amir Nur , the Adalite initiator of " the secondconquest " ( Sahib al-fathaht- thani )]
ከላይ ዩሪች ብራውካምፐር ጹሁፍ የአሚር የእስልምናን ሐይማኖትና የአዳል ሱልጣኔትን እስልምና ካልሆኑት ሐይላት እንዴት አድርጎ ከጥፋት አድኖ ለዚህ ትውልድ በስኬት እንዳሻገረ በግልጽ አመልካች ነው ለዚህ ታላቅ ስኬት የበረሳደዲን ህዝብ አዳል ሱልጣኔት ለአሚር ኑር ከነበራቸው ታላላቅ የማዕረግ ስምች በተጨማሪ " ሳሂቢ ፋትሁ ታኒ " የሚል ታላቅ ማዕረግ ክብር ተቻራቸው ።
አንባቢያን ልብ በሉ የአሚር ኑር ታሪክ ላይ በበርካታ ቦታ ላይ ይህ በግልጽ እያመለከተ እያለ የቶጲያ ጸሃፊ ይህንን እውነታና የሐረር ታሪክ በመካድ ነው አሉታዊ ለመጻፍ አስራ ሁለት አመት የፈጀበት ።
የታላቁን የአዳል ሐረር አሚር ኑር ታሪክ የሰሜን ክርስቲያን ተቀናቃኞች ሳይቀር ነበር ሐቅን የመሰከሩለት
[1552 ዓል ኑር አህመድ ( ኑር ኢብን ሙጃሂድ ) የሚባል የግራኝ አህመድ የእህቱ ልጅ ተነስቶ የሐረርና ያካባቢው እስላሞችን ሁሉ አለቃ አድርገውት ነበር ። እርሱም የወደቀውን የግራኝ አህመድን መንግስት እንደገና ያቆማል ብለው እስላሞች ሁሉ ተስፋ አደረጉት በጊዜውም የሐረርን ግንብ ስለሠራ ዝናው ባገር ውስጥ ተስፋፋ ። ተከጻዲቅ ሞኩሪያ ፣ ከዓጼ ልብነድንግል እስከ ዓጼ ቴዎድሮስ ገጽ 72 ]
ካላይ በጹሁፉ ከአሚር ኑር ተቀናቃኞች እንደተገለጸው [የሐረርን ግንብ ስለ ሰራ ዝናው ባገር ውስጥ ተስፋፋ] ከተጻፈው ሐረግ የምንረዳው የአሚር ኑር ያከናወኑት ትልቅ ስራ ዝናው ባገር ውስጥ ተስፋፋ የሚል ታላቅ የስኬት ምልክት አመልካች ነው ይህንን ምስክር ከተቀናቃኞቻቸው እውቅና የተሰጠ የአሚሩ ስኬት የስኬት ውጤት ነው ። የቶጲያ የሐሰት መረጃ ለቅላቂና የሱ ደጋፊዎች ይህቺ እውነታ እየመረረች ይውጧቷል ፣ እውነት ሐቅ ቢመርም መዋጥ የግድ ይላልና ።
የአሚር ኑር ሌላው የስልጣኔ
(የሐረር ሳንቲም ገንዘብ) ስኬት
አሚር ኑር በ16ተኛው ክ/ዘመን በሐረር የመጀመሪያው የገንዘብ ሳንቲም ግብይይት ያስጀመሩ አሚር ሲሆኑ ይህንን እውነታ ሙስሊም ያልሆኑ ታሪክ ጸሃፊያን ያረጋገጡት መረጃውም ነው ።
ስለ ሐረር ጥንታዊው ገንዘብና ሳንቲሞች በተመለከተ የሐረር ጥንታዊው ገንዘብ ሣንቲም አጀማመር መቼ ሐረር ላይ ተጀመረ ? ለሚለው ጥያቄ አብዛኛው የውጭ ሃገር ተመራማሪዎችም ሆነ በሃገር ውስጥም የሐረር ጥንታዊው ገንዘብ ሳንቲሞች የተጀመረው በ16ኛው ክ/ዘመን በአሚር ኑር ቢን ሙጃሂድ ዘመን መሆኑን ሁሉም ተመራማሪዎች የተስማሙበት ነው :: ይህንን በተመለከተ አቪሻይ ቢንዶሮር የሚከተለውን ያስነበናል
"(Amir) Nur was the first ruler of Harar who coined local currency, the main one being the mahlak. [Emirate,Egyptian,Ethiopian Avishai Ben-Dror pp 17]"
History of Harar and Hararis
Page 215
[ Amir Nur mint his own coin , the price of durrah rose to two ashrafi ( Ahmed Z.) P 215 ]
ተክለጻድቅ ሙኩሪያ
የግራኝ አህመድ ወረራ
ገጽ 46
[ስለሐረር ጥንታዊው ሳንቲሞች የኢንሪኮ ቺሩሊ ዘገባን ዋቢ በማድረግ የሚከተለውን ያስነብባል“ የወላስሞች መደብ ከ1512 ዓል ወዲህ ከአዳል (ደከር) ወደ ሐረር በዞረበት ብዙ ዓረቦች ከማዶ ከዓረብ አገር እየመጡ ከአዳሎችና ከሱማሌዎች ጋር በኖሩበት ስዓት የሐረር ህዝብ የመገበያያ ገንዘብ እንደነበራቸው ለማስረዳት አቡበከር ኢብን መሐመድ ሻም በአልዊ የሚባለው ዓፄ ገላውዴዎስ በሞቱበት ዓመት በሐረርጌ በተነሳው የረሃብ ጽናት የእህሉን ውድነት ከተረከበት ላይ አንድ መለኪያ (ቁና ) በቆሎ 12 አሽራፍ አንድ መለኪያ አሞሌ ጨው 25 አሽራፍ የበሬ ዋጋ 300 አሽራፍ ከዚህም በላይ ሆነ ሲል ጠቅሷል” እንደገናም መረጃውን በቀጠል ተክለጻድቅ ሙኩሪያ
“የሐረርጌ ሱልጣኖች ወይንም የነ አሚር ኑር ግዛት የመገበያያ ገንዘብ ሊኖረው የቻለው ይኸው ሐረርጌ በዘይላ ወደብ አማካይነት በቀይ ባህር ማዶ ከአሉት ከዘቢድ አረቦችና ቱርኮች ጋር የሥልጣኔ ግንኙነት አድርጎ ሸቀጥ ለሸቀጥ እየተለዋወጠ ንግዱን በማስፋፋቱ ምክንያት ይሆናል” ]
ከላይ የአሚር ኑር በሐረር ሳንቲም ገንዛብ ያስመዘገቡት ወርቃማ ስኬት ይህ ሆኖ እያለ ነው ነጃሺ ከዲር ባላጠናው በማያውቀው ታሪክ በመሰለኝ የጻፈው የቶጲያ ድርሰትና ሐሰት መረጃ አሳፋሪና የወረደ መጸሃፍነው የምንለው ። እኔ እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ለወንድሜ ነጃሺ ከዲር ሻሞ የምጠይቀው አሚር ኑር ይህንን የሳንቲም ግብይይት ሐረር ላይ በ16ኛው ክ/ዘመን ሲያስጀምር አንተ በቶጲያ መጸሃፍ በተደጋጋሚ የስልጤ ቀደምት አባቶች ያልካቸው በወራቤ ወይም በስልጤ ዞን በምን ነበር ግብይት ያደርጉ የነበረው ? በሳንቲም ገንዘብ? ወይስ Bartering ? መልሱ ግልጽ ነው ። በዚህ መስፈርት ነው የአሚር ኑር ስኬት መመዘን የሚገባህ ።
ቶጲያ ገጽ 369
[ ስለ ሙስሊም መሪዎች ከሚነገሩት ብዙ መሰረተ ቢስ የፈጠራ ወሬዎች መካከል አንዱ አሚር ኑር ከአጼ ገላውዴዎስ ጋር ተዋግተው ባቲ ድል ወንበራ የአጼ ገላውዴዎስ አንገት ቆርጠህ ራስ ቅሉን ይዘህ ከመጣህ አገባሃለው ብላው ነበር ነው ። ]
ነጃሺ ከዲር አንተም ተሳስተህ ሌላውንም የተሳሳተ መረጃ እያቀበልክ ነው ፣ መረጃው አንተም በተገቢ አላጠናህም ። ትክክለኛ መረጃ የሚከተለው ነው
[ አሚር ኑር ድል ወንበራ ቢንት አሚር መሕፉዝ ከመጀመሪያ ባለቤቷ ኢማም አህመድ ሞት በሃሏ በኒካህ ተጋቡ ፣ ጋብቻ ከፈጸሙ በሃሏ ድልወንበሯ አሚር ኑርን [መህር] የጠየቀችው የገላዲዎስን ጭንቅላት አምጦቶ እንዲያሳያት ነው የዚህ ምንጭ የሐረሪ ታሪክ ምሁር ዩሱፍ አብዱረህማ ሼኽ በበቂ የ16 ኛው ክ/ዘመን ታሪክ ላይ ዘርዝረዋል ፣ ሌላኛው ምንጭ ግን የሐረሪ የአሚር ኑር ቤተሰቦችም ሆኑ ማህበረሰብ ይህንን ተውፊት መረጃ ሁሉም የሚስማማበት ነው ።
ነገር ግን የክርስቲያ የሃገር ውስጥና የውጭ ታሪክ ጸሃፊያን ይህንን ይህንን ዘገባ ሲዘግቡ [መህር] የሚለውን በግንዛቤ ማነስ ወደ ጥሎሽ በመቀየር በዚያ መልክ የተጻፈ ነው እንጂ ነገሩ የፈጠራ ወሬ አይደለም ፣ ነጃሺም ይህንን ጥናት ስራ ሐረር ላይ ተገኝተህ መረጃ መሰብሰብ ነበረብህ እንጂ እውነትን በሐሰት ማቅረብ ተገቢም አይደለም።
ቶጲያ ገጽ 369
[ አሚር ኑር ባደረጋቸው ጦርነቶች ምን ያህል እንደተሳካለት ግን ዝርዝር መረጃ አይገኝም ። ገጽ 369 ]
የቶጲያ ጸሃፊ ከላይ አስቂኝ የሆነ መረጃና የራሱን አላዋቂነት በግልጽ አመልካች ነው ። የአሚር ኑር የጦር ዘመቻ ከኢማም አህመድ እስከ አሚር ሆኖ በዋለበት የአዳል ሱልጣኔት በበርካታ ቦታ ላይ ኑር ቢን ሙጃሂድ እንደተሳካለት በርካታ ወርቃማ የታሪክ መረጃዎች ያመለክታሉ ። ለአብነት
ፕ/ር ላጲሶ የኢትዮጵያ ታሪካዊ መሰረቶችና መሳሪያዎች ገጽ 141
[1547 ዓጼ ገላውዴዎስና ሁለቱ ታላላቅ የጦር አበጋዞች ራስ ፋኑኤልና ራስ ሐመልማል ከሐረር እስከ ዘይላ [ከበር ሰአደዲን እስከ በር አጀም] ድረስ ማለት ከአዋሽ እስከ ኤደን ባህረሰላጤና እስከ ህንድ ውቅያኖስ ጠረፍ ድረስ በታላላቁ የአዳል አገርና መንግስት ላይ ብዙ ተከታታይ የቅጣት ዘመቻዎችን በማካሄድ በህይወትና በንብረት ታላቅ ጥቃትና ጥፋት አደረሱ መንደሮች ፣ ከተሞችና መስጂዶችን አፈራረሱ ። ....በመጋቢት 1559 በዋጅ ከአዳሉ ኤሚር ኑር የሐረሩ ግምብ መሥራች ጋር ሲዋጋ አጼ ገላውዴዎስ ራሱ ተገደለ ]
ነጃሺ ከዲር ሻሞ የአዳል ሱልጣኔት ተቀናቃኝ ዓጼ በአሚር ኑር መወገድ ዝርዝር መረጃ እንዲህ ሆኖ ሳለ የለም በማለት አይኑን በጨው በማጠብ ይክዳል ።
ከአረብ ፈቂና ከሌሎች
የኑር ቢን ሙጃሂድ ዘገባ ምስክርነት የሚክተለው ይገኛል
[1543 አሚር ኑር ቢን ሙጃሂድ ከአጎቱ ሞት በኋላ ሆነ በፊት በርካታ ግንባር ላይ ተሰልፎ ግዳጁን የተወጣ ጀግና ነው ። አረብ ፈቂ አሚር ኑርን አስፈሪ አንበሳ ብሎ ሲዘግብ ሌሎች ደግሞ ፈትህ ታኒ እና ወሊ ኑር በማለት ጽፈዋል ። አሚር ኑር ከባሌ ጀምሮ በሹምብራ ኩሬ ፣ በደዋሮ ፣ በይፋት ፣ በዋስለና በዋጅ ከአጎቱ ጋር በብዙ ግንባር ተዋግቶ ያሸነፈ የጦር መሪና ጀግና ነው ። በመጨረሻም ከአጎቱ ሞት እና ስልጣ ተረካቢ በመሆን በ1559 በፈጥጋር ከዓጼ ገላውዲዮስ ጋር ጦር ገጥሞ ድልን ተቀዳጅቷል ]
ተክለጻዲቅ ሞኩሪያ
የግራኝ አህሙድ ወረራ ገጽ 815
[ ከተማው ሐረር የወረራ አደጋ እንዳይደርስበት ዙሪያውን እስከዛሬ የሚታየውን ግንብ ማሰራቱን በመልካም አስተዳዳሪነቱና ይኸን ግንብ ከማሰራቱ የተነሳ በእሳላሞቹ ዘንድ እንደ ጻድቅ የሚቆጠር መልካም መስፍን መሆኑን በዘመኑ የነቡሩ ጸሐፊዎች እነ አቡበከር ኢብን መሐመድ ( አልዊ ሰንባል) ያረጋግጣሉ የነርሱም ጹሁፍ አንዳንድ ጊዜ አሚር ወይም ጻድቁ አሚር አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አሚር ሙሚኒን የአማኞች መስፍን ይባላል ። ከግራኝ ሞት ወዲህ ዓጼ ገላውዴዎስን በመግደል የግራኝን ደም ስለተበቀለ ሳሂብ አልፈትህ አልታኒ ሁለተኛው ድል አድራጊ ተብሏል አንደኛው ድል አድራጊ ሳሂብ አል ፈትህ አል አዋል ተብሎ የተሰየመው ግራኝ አህመድ የኢብራሂም ልጅ ነው ። ግራኝ አህመድ ወረራ ፣ ገጽ 815 ]
አስቂኝና በሐሰትና መረጃ የተካነው ነጃሺ ከዲር ከላይ ባቀረበው በገጽ 369 አሚር ኑር ባደረጋቸው ጦርነቶች ምን ያህል እንደተሳካለት ግን ዝርዝር መረጃ አይገኝም ይልና ወረድ ብሎ በገጽ 370 የሚጋጭ ሐሳብ የሚከተለውን
[ የአጼ ገላውዴዎስ ጦርና የፖርቹጋልን ጦር ብዛት እንዲሁም የታጠቀውን ዘመናዊ መሳሪያ ታሳቢ በማድረግ እንደዛም ሆኖ ግን አሚር ኑር የተጎናጸፈው ድል ሲታይ አሚር ኑር ጠንካራ ጦር በማደራጀት ስኬታማ እንደነበር ያመለክታል ። ገጽ 370 ]
ከላይ በአሚር ኑር ገድል ላይ የቶጲያ ጸሃፊ እርስ በእርሱ የሚጋጩ ታሪክ እየጻፈ እንደገና ተመልሶ በአሚር ኑር ወታደራዊ ስኬት ላይ ደግም የፈረደበትን የስልጤ ታሪክ ተቋዳሽ ነበረ እኛም አለንበት ለማለት ያለ ምንም ምንጭና መረጃ የሌለው ያልተቀሰ የሚከተለውን ተረት ያስነቧል
[ የመሐል ደቡብ የስልጤ-ወለኔ ጦር ለአሚር ኑር ድል ከፍተኛ አስተዎጾ ነበረው ። ] አንባቢያን ልብ በሉ ምንጭ መረጃ አልተጠቀሰም ። ነገር ግን ታሪኩን ያለ መረጃ ጠምዝዞ የድሉ ተቋዳሽ በግድ ራሱን አደረገ ።
ነጃሺን የቶጲያ ጸሃፊን የምጠይቀው ፣ አሚር ኑር ጦር አደራጅቶ የመጣው ከምስራቅ ብሄረሰቦች በኩል ነበር በዚሁ በአንተው ቶጲያ ገጽ 213-214 እንዲሁም በ13ኛው ክ/ዘመን የስልጤ ሐረር አካባቢ ለቀን ወደ ጨርጨር ቀጥሎም በገጽ 226 ከ1512-1518 ወደ አሁኑ ስልጤ አካባቢ ሰፈርን በማለት ከሐረር አሚራዊ ስርዓት ውጭ የሆነው አካባቢ መስፈሩን ጽፈህ ተመልሰህ ከዚህ ጋር የሚጋጭ በአሚር ኑር ስር ያልተዋቀረ ያልታቀፉ ሐይል የድሉ ተቋዳሽ ማድረግ ያለ መረጃ ተገቢ ነውን ?
በቶጲያ ገጽ 371
የሀዞሎ ጦርነት አስመልክቶ የሚከተለውን ይጽፋል
[ አሚር ኑርም በቅሎ ወይም ፈረስ እየጋለበ አመለጣቸው ። በአደሬ ትውፊት በጣም መደንገጡን ለማጋነን አህያ እየጋለበ ሀረር ደረሰ የሚለው ግን ትክክል አይመስልም ። ]
ከላይ የቀረበው የአሚር ኑር ገድል ላይ የሌለ የውሸት ትርክት በመጻፍ የሐረርን ታሪክ ያለ እውቀት ለማጠልሸት በታሪክ ያልተጻፈና በሐረሪ ትውፊት ሰምቼ የማለውቀው በሬ ወለደ ቅጥፈት በገሃድ ጽፏል ። በአጠቃላይ ስለ ሃዘሎ የተጻፈው በሁለት ክርስቲያን ገድል ጽሃፊዎች ነው እነርሱም አንዱ ቶጲያ በምንጭነት የጠቀሰው አባ ባህርይ ( ገጽ 82) ሲሆን ሌለኛው በቶጲያ ተረት ያልተጠቀሰው በይልማ ደሬሳ (ገጽ 231-232) ነው ፣ ከላይ የተቀሱት ክርስቲያን ጸሃፊች ስለ አሚር ኑር ጀግነትና ሳይደብቁ ብዙ ሰው እንደፈጀባቸው (እንደጨረሰባቸው) ጠቅሰው በመጨረሻም የክርስቲያንን ደም በሐዞሎ አደፍጦ በጠበቀ ሉባዎች ፈጣሪ ተበቀለልን በማለት በቁጭት የጽፉት ነው ። ነጃሺ በዚህ ጨማምሮበት በጹሁፍ ያልተሰነደ ሐሰት የለቀለቀው ፣ ነጃሺ ከዲር ይህ ትውልድ ታሪኩን አያውቅም ብሎ የመሰለውን ቢለቀልቅ ያዉና እኛ የአባዲር ልጆች እያንዳንዱን ሐሰት መረጃህን አበጥረን እናወጣታለን ።
ወንድሜ እንጂነር ነጃሺ ታላቁ የሐረር አሚር ኑር የሚከተለውን ወርቃማ ስኬት አሳክቷል
-> ሐረር ሳትፈርስና ሳትወድም ለትውልድ በቅርስነት አሚር ኑር ለትውልድ አቆይቷል ዛሬ ሐረር የአለም ቅርስ ሆናለች
->በሐረር የመጀመሪያ ሳቲም " ደረባ አል ሐረር "
-> ወሊ ኑር መስጂድ ገንብቶ ወሊ ኑር እራሱም እስልምና ዲን አስተምሯል መስጂዱ እስከዛሬ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል
-> ጀግነቱ በፈትህ አልሐበሻ በአረብ ፈቂ በዝርዝር ቀርቧል
-> ከአባዲር በመቀጠል የአዋች ተቋሟት እንዲጠናከሩ ታላቅ ጥረት አድርጎታል
-> ሐረርን ከዘበዲ የመን ሊቃውንት ጋር ጥምር በመፍጠር ዲናቸውና ቅርስ ግንባታ እንዲያብብ ለዚህ ትብብር ታላቁን ሊቅ ፈኽረዲን ዮኒስ ከዘቢድ አስመጡ ።
-> አሚር ኑር የሐረር ግንብ አምስት በር አርካን ኢስላም ፣ እርዝመቱን 6666 ኩሩእ (የቁርዓን አያት) ፣ ወዘተ እሴት ባላቸው ግንባታውን አከናውናል ።
-> ሐረርን ከወራሪዎች ጠብቋል
-> ለዚህ ሁሉ ስኬት ኑር ቢን ሙጃሂድ የሚከተለውን ስሞች በማህበረሰቡ ተችራል አሚር ኑር ፣ ወሊኑር ፣ ሳሂብ ፈትሁ ታኒ ፣ አሚርአል ሙሚኒን ወዘተ
ለውድ አንባቢያን በመጨረሻ ታላቁ የሐረር 18ኛው ሊቅ ፈቂ ሐሚድ ስለ አሚር ኑር በሰጠው የእጅ ጹሁፍ ምስክር (Manuscript) ጹሁፌን ደመደምኩኝ ።
ፈቂ ሐሚድ ቢን ሳዲቅ (ፈቂ ሳዲቅ) አልሐረሪ አላህ ለጀነት ይበላቸውና 18ኛው ክ/ዘመን ምሁር በጥንታዊዉ ጹሁፍ ስለ አሚር ኑር የሰጡት አስተያየት
በተጨማሪ (ፈቂ)ደራሲው ስለ ጥሩ ሥነምግባር አገር መሪ (ገዢ) ሚለው ክፍል የሚከተለውን አስነብቧል
ሱልጣን ወይንም አሚሩ የሃገሩ ገዢ በፈሪ ፈጣሪና በስነምግባር በጎነት ( በስብእናቸው) በምሳሌነት ለድርድር የሚጋብዘን እውነተኛና ሐቀኛ መሪ እንደ ኢሚም አህመድ የመሰለ በ949 ዓመተ ሂጅሪያ (1543 እኤአ) የሞተው :: እንዲሁም እንደ አሚር ኑር በ974 ዓመተ ሂጅሪያ (1567 እኤአ) የሞተው እናም እነዚህ መሪዎች ይላል ጸሐፊው “ እነዚህ አሚሮች ሲሞቱ መኖሪያ ቤታችው ውስጥ ምንም አልተገኘም ካለ ሰይፋቸው : ቁርዓን መጽሐፍ : ሲዋክ (ጥርስ መፋቂያ እንጨት) : ሚለብሰው ነጭ ቀሚስ እና መቀበሪያ ነጭ ጨርቅ (ከፈን) ብቻ ነበር ።
ውድ አንባቢያን ለአሚር ኑር የተመሰከረው ይህ ሆኖ እያለ የነጃሺ በቶጲያን ከጻፈው ጋር በሚዛን መዝኑት ።
05/02/2023
የሐረር አመሽና 1950 ዓል
በኑረዲን አብደላ
በሐረር ታሪክ በ1950 በሐረር የአመሽና ሙጋድ ወጣቶች በመደራጀት በ15 አባላት እንቅስቃሴ ጀምረው (በአመሽና በሚል የተደራጁ ) ። ወጣቶች በመጀመሪያ በመማር ማስተማር የበጎሥራ እየተጠናከረ የሐረሪ ማህበረሰብ በማህበራዊ ፣ በቋንቋ ፣ በፖለቲካ ፣ በትምህርት ፣ በሥራ ፣ በባህል ግንባታ ፣ በመዝሙር ፣ በሙዚቃ ፣ በድራማ ፣ በጾታ እኩልነት በርካታ ለማህበረሰቡ ከላይ የተዘረዘሩትን በርካታ ለውጦችን አስመዘገቡ ።
የአመሽና መስራቾች ተብለው በማህበሩ የሚጠቀሱት
በድሪ ባሻ
ሪድዋን አብደላህ
ኢዘዲን ዩሱፍ ሼኽ
አብዱልጋፉር መሐመድ ( አውቁራ)
ያህያ ኢስማኢል (ሩጣቡን)
አህመድ አብዱልዋሂድ
ኸዛሊ መሐመድ
መሐመድ አብዱረሺድ
መሐመድ ኢብራሂም ሱሌይማን
አብዱረህማን አሊ ሼኽ
አህመድ አብዲ ዮኒስ (ዳኢም አሩዝ)
ረሂላ አህመድ አቦኝ
ኪሚያ በድሪ ኢብራሂም
ፍርድውሳ ሐሰን በሺር
አፈንዲ ሐጂ አቡልኼስ
አብዱረህማን ሼኽ አቡበከር
የነዚህ የአመሽና መስራች ፎቶ መኩሪያ መሸሻ ስለ አመሽና በሐረሪ አመጽ በገጽ 158 ላይ የሚገኘው ዋናውን ፎቶ ከመስራቾቹ አንዱ አባ አብዱልኸፉር መሐመድ ( አውቁራ) መረጃውን ስለሰጠኝ ምስጋናዬ የላቀ ነው ። አብዛኛው የአመሽና መስራቾች በሞት ወደ ማይቀረው አኺሯ ሄደዋል አላህ በጀነት ያስደስታቸው ። በህይወት የሚገኙትም ጤናና ኢማን ይስጣቸው ።
ከላይ የአመሽና ወጣቶችን ማህበርና ራዒ እንዲሳካ የደገፉ የሐረሪ አባቶች
አው ሐጂ መሐመድ አዲሽ
አው ዩሱፍ ሸኖ
አው ሐጂ አዱስ አዲሽ
ሼኽ መሐመድ ዱአሌ
አው መህዲ አብዱልወሃብ
አው ሐጂ ሱፍያን መሐመድ
አው አቡበከር አህመድ አቦኝ
አው ኢብራሂም ሱሌይማን
አው አቡበከር አህመድ ፈቂ
05/01/2023
ኢኛ ዘልታ ማን ሃል ዞደቃ ?
ሐረሪ ታሪኹ ዚኸሻ መልቀቃ
ቶጲያ ባያማ ጂጃ ፈረቃ
ሐረሪ ታሪኽ አዱኛ ሪኤውማ አቃ
ቁራስዋ እጂ ኩቱባች ዘሌልባ ፊርቃ
ሐረሪ አቀበላ ታሪኽዞቤ ሮሐቃ
አዱኛ ዛቄው ሐረር ቶጲያ ሼመቃ
ጀዋብ ኑሽ አህላች ኪዝበኛው ነቴውቃ
ሐረሪያች ዚከተቦው ሁጀዋ አቦቃ
ኢርመውጣ አፊቃው ዲንቤ አተቃ
ኢኛ ዘልታ ማን ሃል ዞደቃ ?
ሩህዞቤ ዘይቲቤቅ ዘሌላ ሲቃ
ማልቱ ኢርቤ ዚመለሃ ጪልማ ጨረቃ
ኢርዋ ጨረቃ ዘሞሴው መትናፋ ቢፈረቃ
ኢኛ ዘልታ ማን ሃል ይወቅቲቤ ዞደቃ ?
አላይዞ ያሻዛልቤ ይኹናል አሺቃ
ማንነትዞ አልመኽነዞቤ ዘማንዞሌ አፈቃ
አትለመዱና ዲንዋ አደቤ መሌቃ
ኢማን ቂባጭቤ ቀልቢን ተስዳደቃ
ማጥ ኒባሮት ኢጂቤ አጠበቃ
ታጪና በቀኛ ረሴኤማ ሰደቃ
አሐድ ገበታ ኡኻቱ አልፊሌ ዘትቢቃቃ
ዘመንዞኩት አዞም ኻና መጠቃ
ረህማበርረኹ ከርሲ ጠቢቅ ረቃ
ኢኛ ዘልታ ማን ሃል ይወቅቲቤ ዞደቃ ?
ሃሚስቲ በሪ መሰቤ ዚዳበላች
ሜጠቃሜጠቅቤ መሳ ዚቃነናች
ኢንጪገርኩት ለከም ዘታሻች
ሐረሪያች ዱንያቤ አኻ ዚትፊጣጠናች
መዲነቱል አውሊያ ባድዚዩ ሐረሪያች
ነትዋደድ ነትጋድሪ አንኹን ሸረኛች
ቀርበን ዚታ ዳይሐዋዝ ፋይዳኤላ አህላች
ቀዲም ሔራኩት የትኺሻል ኤቀዳች
ኢኛ ዘልታ ማን ሃል አኻ ዞደቃ ?
አባዋ ኢህዞው ጪሪቅ ዘጬረቃ
ሐረሪነት ሐቡ አዳዋሌ ቢረት ሁንቃ
አማሳይ ነቱቤ ዘልቲጪማለቃ
አግሪ መኽነቤ ጌይሌ ዚትፊላለቃ
ናሩ ኤቡያች ዘማንሌ አለቃ
አኻኽ ሃለና ኢኜሌ ዞደቃ ?
ዊቅሪዞ ከታቢ ኑረዲን አብደላ
ዲሴምበር 30 / 2022
ካናዳ
03/01/2023
አዲሱን የፈረንጅ አመት 2023
በሐረሪ ቁርዓን አጻጻፍ ጀመርነው
የሐረሪ ጥንታዊዉ የእጅ ጹሁፍ የቁርዓን
ኸሊሊ አጻጻፍ የኪነጥበብ የካሊግራፊክ ዘዴ
Harsri Qur'an Manuscript khalili art and Calligraphy
በኑረዲን አብደላ
በዓለማችን በርካታ ጥንታዊዉ የቁርዓን የእጅ ጹሁፍ የአጻጻፍ ዘዴዎችና የየራሳቸውን የኪነጥበብ ቅብ ዲኮሬት በማድረግ የክፍለ አህጉራቸው የራሳቸው መለያ ምልክት ያደሩጉ ሃገራት ይገኛሉ ለአብነት ጥቂቱ
ግብጾችና ቱርኮች መሙሉክ(Mamuluk) ፣
ህንዶች ፖኪስታኖች ቢሃሪ (Bihari)
የየመኖች Alkawakib aldurria(የካዎክብት አምሳያ)
ጥቂቶች ናቸው
በጥንታዊዉ የቁርዓን የእጅ ጹሁፍ የሐረርና የምስራቅ አፍሪቃ እስከ ህንድ ውቅያኖስ እንዲሁም እስከ ዘንዚባር ድረስ የዘለቀውና ለቀጠናው የራሱን አሻራ ያስቀመጠው በሐረር ከተማ በሐረሪዎች በእጅ የተጻፈው የቁርዓን ኪታብ ላይ የቀረበው ጥበብ ኸሊሊ በሚባል የሚጠራው ነው
በሐረር ከተማ በተለያዩ ሃገራት የመሙሉክ አጻጻፍ የተጻፉም አለ ። እንዲሁም አልከዋኪብ ዱሪያ የየመኑ አይነት ላይ የተጻፈ ይገኛል ። ነገር ግን በብዛት በሐረር በቁርዓን ጥበብ ስራ አብዛኛ አሸብርቆና ደምቆ የሚታይው የኸሊሊ የቁርዓን ጥበብ በቀለም ቅብ ፣ በቁርዕን የቀለም ዓይነትና ዲኮረሺን በብዛት ይታያሉ ። በሐረር የሐረሪ ጥንታዊዉ ቁራዓን (ኪታቦች ) ከ25 በላይ የተለያዩ የኸሊሊ የጥበብ ስራና ካለግራፊ የያዙ ጥንታዊዉ የእጅ ጹሁፎች ከሐረር ወጥተው በመላው አለም ተሰራጭተው ይገኛሉ ።
በሐረር ከተማ ጥንት በእጅ ጹሁፍ የተጻፉ Harari Old Quran Manuscripts በብዛትና በጥራት የኸሊሊ እንዲጻፉ የተደረገበት ምክንያቶች ጥቂቶች የሚከተሉት ናቸው
1) የቁርዓን ኪታብ በወፍቅ መልክ ለሚወዱት ቤተሰብ አባላት በስጦታ መስጠት
2) ለሞቱ ለቤተሰብ አባል በወፍቅ መልክ ቁራዓን በማጻፍ በሚቀራው ሰው አጅር (ምንዳ) ማግኘት
3) ለወላጅ አባቶቻቸው ወይም በእድሜ ለገፉ ወዳጅ ዘመድ ስጦታ ኪታብ መስጠት
4) ቁርዓን ኪታብ አጽፈው አዋች ፣ ለቅሶቤት ፣ መውሉድ ቦታዎች በመውሰድ ህዝብ እንዲጠቀምበት ለማስደረግ
5) ለኸይር ስጦታ ቁርዓን አስከትበው ለአዋች በስጦታ መስጠትና ህብረተሰቡ እንዲጠቀምበት ማድረግ
6) በሐረር ከተማ የሚገኙ ትላልቅ ሊቃውንትና ኡለማዎች ፣ እንዲሁም አሚሮች በራሳቸው መኖሪያ ቤት የግል ላይበራሪ በማከማቸት ማህበረሰቡ እንዳስፈላጊነት እንዲጠቅምበት ማድረግ
የሐረሪ የእጅ ጹሁፍ ቁርዓኑ Manuscript ጥራት እጅግ ከፍተኛ ነው ለአብነት የሐጂ ሰኢድ ኢብን አዲሽ ኡመር ዲን የኸሊሊ የምስራቅ አፍሪቃ ቁራዓን ታሪኩን በሌላ ጊዜ እመልሰበታላሁኝ ፣ ነገር ግን አሁን በኪታቡ ላይ ጥራት ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል
በ 290 ገጾችን የያዘ ወይም ያካተተ ነው
32.5 × 22.5 ስፋትና አግድም ያካለለ ነው
በሂጅሪያ በሹዋል ወር 1162 ሂጅሪያ ከታቢው ጨርሰው አዘጋጅተዋል ለሰሩት ስራ[አላህ ለጀነት ይበላቸው አሚን]
መጸሃፉን የከተቡና ያዘጋጁ ሐጅ ያደረጉ ያላህ ባሪያ ናቸው [ሐጃቸውን አላህ ይቀበላቸው አሚን]
በቁርዓኑ የሰፈረበት በአራት ማዘን በሶስት መስመሮች በተሰመረ መስመር ውስጥ ነው ።
እያንዳንዱ ገጽ በ15 መስመሮች ላይ ቁርዓኑ በቀጥታ መስመር ተጽፈው እኩል በሆነ ሃርፎች በጥራት ተቀምጠዋል ።
እያንዳንዱ አያ (ምእራፍ) በቀይና በቢጫ ቀለም የአረበኛ ኸምሳ (٥) በሚመስል ምልክት ተለይተዋል ።
በየገጹ የመጀመሪያና የመጨረሻው መስመሮች ቁርዓኑ በትላልቅ ፊደላት ተጽፈዋል ።
መረጃው የሐረሪን ጥንታዊዉ የቁርአን የእጅ ጹሁፍ ለ PHD ጥናትና መረጃ የሰበሰበችው በአንድ ወቅት የዚህ ጥናት በኮንፈረንስ 2019 የሐሪዎችን ጥንታዊዉ ጹሁፍ ስራ ግንዛቤ ያስጭበጠችን አመሪካዊት Sana Mirazi ምስጋናዬ የላቀ ነው ።
17/12/2022
የህንድ ቱጃር መሐመድ አሊ
GM ኩባኒያ 1888 እኤአ እና ሐረሪዎች
በኑረዲን አብደላ
የህንድ ነጋዴና ቱጃር ወደ ሐረር በ ፈረንጆቹ 1888 ኩባኒያውና አባላቱ ሐረር ይደርሳሉ የኩባንያው ስም GM መሐመድ አሊ ይባላል ። ይህ የመጀመሪያው በሐረር መዳረሻ ያደረገው የንግድ ጉንኝነት የኢትዮ- ህንድ ጉንኘትና የመጀመሪያው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ለማድረግ ወደ ሐረር የመጡ የህንድ ነጋዴዎች ቡድን አባላት ነበሩ [ Indo - Ethiopian relation 1961 R Pankhurst , P 50 ] በሐረር ቆይታቸው በሐረር ጆጎል ውስጥ የመሐመድ አሊ ቤት ተብሎ የሚጠራውና በተለያዩ በህንድ በመጡ የእንጨት ስራ የተገነቡና ዘመናዊ የቀለም ቅብ የተቀቡ ቀለማት ለሐረሪ ማህበረሰብ የአለላ ስፌት ፣ ጌይ ኮልይታ ( የሙሹራ ኮፊያ ) እንዲሁም የሴቶች ጌይ ገናፊ ( የሴቶች ባህላዊ ሱሪ ) የቀለም ዲዛየን ምንጭ የተወሰደበት መሆኑና ስያሜ መሐመድ አሊ ተብሎ አገልግሎት እስከዛሬም እየሰጠ ይገኛል ። የመሐመድ አሊ ኩባንያ በወቅቱ የንግድ ፣ የአነጺነት ሙያና ስራ ፣ የእንጨት ስራ ህንጻ በርና መስኮት ፣ የቤት የግንብ ግንባታ ፣ የቀለም ቅብ ፣ የማሽን ልብስ ስፌት ፣ የሸቀጥ ንግድ ፣ የቡና ንግድ ወዘተ ላይ በመሰማራት በርካታ ሐረሪዎች በዚህ ኩባንያ በመቀጠር ፣ ሙያውን በመማር በኩባኒያው ተጠቃሚ ለመሆን ችለዋል ፣ በፈረንጆቹ በ1890 ኩባኒያው በሐረር ተጠናክሮ አገልግሎት በሚስጥበት ወቅት በኩባኒያው ግቢ የመሐምድ አሊ ኩባኒያ አባላት ህንዶችና የሐረሪ የኩባኒያው ሰራተኞች ስም ዝርዝር የሚከተሉት ናቸው
ከፊትለፊት የተቀመጡት ከግራ ወደቀኝ ስማቸው
1- አው ሐጂ ሸርዋ
2- አው ሐጂ ሸሮ
3 - አው መሐመድ አብዱላሂ ሸሪፍ
4 - አው ፈዘል ( የቤተሰቡ የመጀመሪያው)
5 - አው ሐጂ ቦንባ ( በልጅነት )
6 - አው ሸሪፍ
7 - አው ሐጂ ጉቱ
8 - አው አቡበከር ቡሉቃ
9 - .......ያልታወቁ .....
10 - አው ዩሱፍ
ከሃሏ 2ኛ መስመር ከቀኝ ወደግራ
ቁጥር ሁለት ነጭ ጺም የሚታይባቸው : አው ፉዲ ጌሌ
ቁጥር ስምንት የህዶችን ኮፊያ ያደረጉ ከቢር ካሚል
ከቢር ካሚል ታላቅ ምሁር ናቸው በሐረር ዘመናዊ ትምህርት ቤት ባልተጀመረበት ወቅት በሐረር አሱምበሪ በራሳቸው ቁራን ጌይ ያስተማሩ ከቢር ናቸው ።
ሁሉም ወደ ማይቀረው አኺራ ሄደዋል አላህ ለጀነት ይበላቸው
ለትውልድ የሚቆይ ስራና ታሪክ መስራት ትውልድ እንዲዘክረው ፣ እንድንማርበት የነርሱን ፈለክ እንድንከተል ይረዳል ።
10/12/2022
ሐጂ አብዱረህማን ሐጂ አህመድ አቦኝ
የዘመኑ ታላቅ የሐረሪ ጥበበኛ ሰው
በኑረዲን አብደላ
በሐረር ከተማ ከእናታቸው ሰራ አብደላ ሸሪፍና ከአባታቸው የሐረሩ ባላባት ሐጂ አህመድ አቦኝ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ 1888 ዓል ተወለዱ ።
ሐጂ አብዱረህማን አባታቸው ከወለዳቸው ወንድ ልጆች የመጀመሪያ በመሆናቸው አባታቸው አው አህመድ አቦኝ በልዩ እንክብካቤና ይህንን ልጅ በሐይሞኖታዊና በአለማዊ ትምህርት ጠንክረው እንዲማርላቸው በመመኘት ይህንን ለማሳካት አባታቸው አው አህመድ አቦኝ ከየመን ሐገር ወደ ሐረር መምህራን በማስመጣት ልጃቸውን እንዲማርላቸው እድል አመቻቹላቸው ።
ሐጂ አብዱረህማን እዱልን በመጠቀም ከየመን ከመጡ ሙሁራን መምህራን አረበኛን ፣ የእስልምና ዲን ፣ ስነ ጹሁፍ ፣ ስነፈለክ ፣ የሮማዊያን ስሌት ፣ ሂሳብ ፣ የእጽዋት ሳይንስ ፣ የእጽዋት ባህል መድሃኒት ቅመማ ወዘተ በርካታ ጥበብን ተምረዋል ። ሐጂ አብዱረህማን በተለይ በእጽዋት ሳይንስና በአስትሮኖሚ የአውቃት ሰላት ሰአታትና ደቂቃዎች በቀን ፣ በወርና በአመት መሸንሸን አገልግሎት እንዲሰጥ ከ20 ዓመታት በላይ ምርምር በማድረግ የምርምርምሩን ሰነድ ወደ እንግሊዝ ሐገር በመላክ በእንግሊዝ ሃገር ጥናቱ ምርምሩ ትክክል መሆኑ እውቅና ተሰጣቸው ፣ በርካታ መጸሃፍቶችን አንበውና ምርምር አድርገዋል በርካታ የእጽዋት ህክምና በክሊኒካቸው ተማሚዎችን አክመዋል ፣ በርካታ የአአበባ ዩኒቪርሲቲና የአለማያ ዩንቨርስቲ የእጽዋት ፣ የእርሻ ፣ Horticulture , Bottany, Harar area plants and Horticulture physiology , Genetic structure and Ecological distribution ምርምር ያደረጉበትን ተማሪዎች ለምርምር እርሳቸው ዘንድ ሐረር በመምጣት ጥናት ያደርጉ ነበር ፣ በሐረር ታላቁ ጃሚ መስጂድ ለሙአዚኖች በብረት የጸሃይ የአዛን ጥሪ ምልክትና የአውቃት ሰላት የሰአት ጊዜ ስሌት ሰሌዳን አበርክተዋል ፣ በርካታ የእጽዋት (ጌይ አባት አባቃላ ) የሐረር ባህል መድሐኒቶችን እጽዋት በሐረሪ ባህል ቤቶች ጊቢ እንዲተከሉና እንዲጠበቁ አስደርገዋል ፣ በሐረር ከተማ በሚከበሩ በታላላቅ በዓላት በክብር እንግድነት ንግግር እንዲያደርጉ ይጋበዙ ነበር ፣ በርካታ ቋንቋ ተናጋሪም የሐረሪ ፣ የኦሮመኛ ፣ አማረኛ፣ ሱማለኛ ፣ አረበኛ ፣ አቀላጥፈው ይናገራሉ ፣ የአረበኛ የጹሁፍ ችሎታቸው የሚደነቅ ነበር ለአብነት ከዚህ ጹሁፍ ጋር በራሳቸው እጅ የተጻፈውን ጹሁፍ ፖስት አድርጌዋለሁኝ ።
ሐጂ አብዱረህማን ባጠቃላይ የ20 ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ የሐረሪ ሊቅና የተከበሩ ሙሁር ነበሩ ።
ሐጂ አብዱረህማን ሐጂ አህመድ አቦኝ የአራት ሚስት ባለትዳርና የአስራ ስድስት ልጆች አባት ነበሩ ። በተወለዱ በሰማኒያ ስምንት ዓመታቸው የካቲት 02 / 1976 ዓል ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል አላህ ለጀነት ይበላቸው ።
28/11/2022
ከቢር ጃሚእ አቦኝ
የሐረር 20ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ
የእስልምና ሊቅ
በኑረዲን አብደላ
በሐረር ከተማ በ20ኛው ክፍለ ዘመን በፈረንጆቹ 1950-60ቹ ትልቅ የአላህ ባሪያና የእውቀት ባለቤት
ኢማም ፣ ኸጢብ፣ ሼኽ ፣ ሙጅተሂድ ታላቅ ከቢር ናቸው
በሂሳብ ፣ ጆሜትሪ ቀመር ፣ ባህላዊ የቅመማ መድሃኒት ስሪት ፣ ሃገር በቀል የእጽዋት ቅመማ ፣ የሐረሪ ቤት (ጌይ ጋር ) የጊቢ የባህል እጽዋት ሁሉም በሐረር ሱጉድ አጥ በሪ ቤታቸው ይገኛል ።
ከቢር ጃሚእ አቦኝ በሐረር ከተማ በሐረርና በአካባቢው የተጻፉ ማናቸውም የሃይማኖት ፣ቁርዕን፣ ሐዲስ፣ ፍቅህ ፣ ፣የአራቱ መዝሃብ ድርሳናት ፣ ሲራ ፣ የሰለዋት ፣የሸሪዓ ህጎች ፣ የአረበኛ ቋንቋ ፣የሂሳብና የጥበብ ፣የቤት ግንባታ ፣ የእርሻ ግብርና ስራዎች ፣ የከዋክብትና የጨረቃ ፣ የመድሃኒት ቅመማ ፣ በሐረር ከተማ ሱጉድ አጥ በሪ መኖሪያ ቤታቸው ታላቅ የቤተ መጸሃፍ ስብስብ እስከ እንድሺ አመታት የሚያስቆጡሩ የተለያዩ እስላማዊ መጸሃፍቶች ስብስብ ይገኝ ነበር ፣ ሁሉንም አንበውና አጥንተው ስራ ላይ ያዋሉ ያስተማሩ የዛ ዘመን ታላቅ ሊቃውንት ናቸው ። በርካታ ደረሳዎች የሐረርና የዙሪያው ብሄረሰቦች መጥተው እሳቸው ላይ ቀርተው ተምረዋል እንዲሁም የህክምና ክትትል አድርገዋል ።
በሐረር ከተማ ሌላው ጉዙፍ እንደ ከቢር ጃሚእ አቦኝ የመጸሃፍ ስብስብ ቤተመጸሃፍ የነበራቸው በድሪ በሪ አካባቢ ይኖሩ የነበሩት ፈቂ ዮኒስ አብዶሽ ሌላኛው ናቸው ። ከቢር ጃሚ አቦኝ ስር ከተማሩት ደረሳዎች ውስጥ አንዱ ሼኽ አብዳላሂ አልሐረሪ አንዱ ናቸው ።
በ1915 ተፈሪ መኮንን (ኃ/ሥ) በሐረማያ ሐይቅ መሐል ላይ ጀልባው ተሰንጥቆ ውሃው ሰጠሙ በዚህም በርካቶች ሲሞቱ ተፈሪ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት በህይወት ቢተርፍም በወቅቱ የሐረር ባህል ህክምና አዋቂው ከቢር ጃሚእ አቦኝ ህክምና ክትትል አድርገው ሊሻለው ቻለው ፣ በጠቃላይ ከቢር ጃሚእ አቦኝ የዘመኑ ታላቅ ሙሁርና ጠቢብ ነበሩ ።
ከቢር ጃሚእ አቦኝ በፋሽስት ኢጣሊያ በየካቲት 12 /1929 ዓል ጸረ ግራዛኒ አመለካከት አላቸው ተብለው ከታሰሩት ኢትዮጵያዊያን ውስጥ ከቢር ጃሚእ አንዱ ናቸው ። ከቢር ጃሚና ከሳቸው ጋር እስር ላይ የነበሩት እስረኞች በፋሽስት ኢጣሊያ ወታዶሮች ሊለቀቁ የቻሉበት ምክንያት የሆኑት ከቢር ጃሚእ ለግራዛኒ መንግስት ከፍተኛ የመንግስት ባልስልጣን ሚስት ለነበረችው የጣሊያን ወይዘሮ እስረኞችን በመጎበኘት ላይ ሳሉ ወይዘሮዋ ነስር ደም ሲፈሳት ከቢር ጃሚእ ባላቸው የባህል ህክምና ጥበብ በመርዳት ወይዘሮዋን ወዲያውኑ ነስሩ ቆሞ ከበሽታዋም ተፈውሰች በዚህም የግራዛኒ ባለስልጣናት ከእስር በክብር እንደተፈቱ ይነገራል ። ወደፊት ስለ ሐረር 20ኛው ክ/ዘመን ምሁርና ሊቅ ከቢር ጃሚ አቦኝ የሐረሩ ታላቅ አሊም በሰፊው በአላህ ፍቃድ እንዘግባለን ።