07/10/2026
"ዕዙ ተልዕኮውን በድል እየተወጣ ነዉ" የ11ኛ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ
በደቡብ ወሎ ዞን መካነ ሰላምና አካባቢው በግዳጅ ላይ የተሰማራው የ11ኛ ዕዝ ከአካባቢው የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የጽንፈኛውን ቡድን የጥፋት ሴራ በማክሸፍ ሰላምን እያረጋገጠ እንደሚገኝ የዕዙ የኦፕሬሽን ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ ተናገሩ።
የዕዙ ሠራዊት በቁርጠኝነትና በጽናት በመካነ ሰላምና አካባቢው ተደብቆ የሕዝብን ሰላም ለማደናቀፍ በሚጥረው ጽንፈኛ ቡድን ላይ አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ምክትል አዛዡ ገልጸዋል።
ከምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም የተወጣጣው ጽንፈኛ ቡድን የባንዳነት ተልዕኮዉን ለመፈጸም ወደ ደቡብ ወሎ ሠርጎ ለመግባት የሞከረበት ዋና ዓላማ የተለመደውን የዘረፋ ተግባር ለመፈጸም እንደሆነም አስረድተዋል።
ጽንፈኛው ቡድን ከአባቱ ከወያኔ ተልዕኮ ተቀብሎ በጎጃምና በወሎ አዋሳኝ አካባቢዎች ሰላምን ለማደፍረስ የሚያደርገውን ጥረት ሕብረተሰቡ በሚገባ የተረዳው መሆኑን የገለጹት ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ፤ ሕዝቡ ከሠራዊቱና ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር መረጃ በመስጠትና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የሠራዊቱን ምት መቋቋም ያልቻለው ይህ የጽንፈኛ ቡድን የሰላም እጁን እስካልዘረጋ ድረስ የትም ይግባ የት ሠራዊቱ ተከታትሎ የመምታትና ሰላምን የማረጋገጥ ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የዕዙ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም የደቡብ ወሎ ዞን የመካነ ሰላምና የአካባቢው ሕዝብ ለዕዙ ሠራዊትና ለጸጥታ ኃይሉ እያደረጉ ላሉት ድጋፍ ምክትል አዛዡ ምስጋና አቅርበዋል። ዘገባው የዕዙ የሠራዊት ሥነ-ልቦና ግንባታ ነው።
አማራ ኮሙኒኬሽን