18/09/2026
በኮሌጁ ለትምህርት ደረጃ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ተማሪዎችና ለሌሎች ተመዛኞች ሲሰጥ የቆየው የሙያ ብቃት ምዘና በሰላምና በስኬት ተጠናቀቀ
ወ/ሶ/ግ/ኮ መስከረም 08/2019 ዓ/ም
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርትና ሥልጠና ቁጥጥር ባለሥልጣን ከወላይታ ሶዶ ግብርና ኮሌጅ ጋር በመተባበር ከመስከረም 05/2019 ዓ/ም እስከ መስከረም 08/2019 ዓ/ም ሲያካሂድ የቆየው የሙያ ብቃት ምዘና በሰላምና በስኬት መጠናቀቁን የኮሌጁ ዲን ዶ/ር አሉላ ታፈሰ አስታውቀዋል።
ዶ/ር አሉላ አክለውም፣ ምዘናው በሰላምና በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የባለሥልጣኑ ማኔጅመንት ኮሚቴ አባላትና መዛኞች፣ የኮሌጁ ሙያ ብቃት ምዘና ማስተባበሪያ፣ ትምህርት ክፍሎች፣ የኮምፒውተር ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
የኮሌጁ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ኃላፊና ምክትል ዲን አቶ ታሪኩ ጨመረ በበኩላቸው፣ ምዘናውን የወሰዱት በኮሌጁ የትምህርት ደረጃ ማሻሻያ መርሐ-ግብር በሰብል ልማት፣ በእንስሳት እርባታ፣ በተፈጥሮ ሀብት አያያዝና በእንስሳት ጤና የሙያ ዘርፎች ላይ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች እና በግል ለመመዘን ያመለከቱ ተመዛኞች መሆናቸውን አብራርተዋል።
አቶ ታሪኩ አያይዘውም ፣ ምዘናው የምዘና ዲስፕሊንንና ሥነ-ሥርዓትን በጠበቀ ሁኔታ መካሄዱን ተናግረዋል።
የኮሌጁ ሙያ ብቃት ምዘና ማስተባበሪያ ኃላፊ መምህር በለጠ ቦቴ በበኩላቸው፣ ምዘናውን የወሰዱት የትምህርት ደረጃ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ተማሪዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 333 ተመዛኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ምዘናው የተሰጠው በሰብል ልማት፣ በእንስሳት እርባታ፣ በተፈጥሮ ሀብት አያያዝ፣ በእንስሳት ጤና፣ በመስኖና ፍሳሽ እንዲሁም በሕብረት ሥራ ሂሳብ አያያዝና ኦዲቲንግ ሙያዎች ላይ ላመለከቱ ተመዛኞች መሰጠቱን ተናግረዋል።