10/10/2026
የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ተግባር ህብረተሰቡን በማሳተፍ ታቅዶ በመሠራቱ በክልሉ የወንጀል ድርጊት መጠን መቀነሱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ወላይታ ሶዶ መስከረም 30/2019 ዓ/ም(ወዞፖመም)በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ እሩብ አመት ከባለፈው ተመሳሳይ ሩብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የወንጀል ድርጊት መቀነሱም ተገልጿል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የበጀት አመቱ የመጀመሪያ ሩብ አመት እቅድ አፈፃፀም ዘርፎች፣ምክትል ዘርፎችና ዳይሮክቶሬቶች በገኙበት ገምግሟል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአዲስ አደረጃጀት ከተዋቀረ ወዲህ የክልሉ ሰላም ማረጋገጥና የወንጀል መከላከል ተግባር የፀጥታ አባላት፣ ህብረተሰቡና የመስተዳድር አካላትን አሳትፎ በመሠራቱ በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስተማማኝ ሠላምና ደህንነት ማስፈን መቻሉን ተገልጿል።
በትራፊክ ፍሰት ቁጥጥር፣በወንጀል ምርመራና በተለያዩ አስተዳደራዊ ስራዎች በሩብ አመቱ የሚያበረታታ ውጤት መመዝገቡ በግምገማው ተነስቷል።
በ2019 ዓ/ም በጀት አመት ቀጣይ ጊዜያት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራባቸው አቅጣጫዎች የተቀመጡ ሲሆን የአባላት አመለካከት፣ፖሊሳዊ ስነ-ምግባርና ከዘመኑ ጋር የሚሔድ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማሳደግ ግንባር ቀደሞቹ ናቸው።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የስራ መመሪያና የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ ያመላከቱት ኮሚሽነር ፍስሃ ጋረደው እንደገለጹት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንና በስሩ ያሉ መዋቅሮች ከሌሎች የፀጥታ ሀይላት ጋር በመሆን ላስመዘገቡት ውጤትና በክልሉ ለሰፈነው ሰላም የፀጥታ አካላት ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
ይህ ሳያዘናጋን በቀጣይ ፖሊሳዊ ቁመናና ስነ-ምግባር ያለው አባል እንዲኖረን በቁርጠኝነት እንሰራለን ብለዋል።
ለቀጣይ መቶ ቀናት በየዘርፉ የሚተገበሩ እቅዶች ከዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር የተዛመዱ ሆነው መቅረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።