18/06/2026
የክረምት በጎ ፈቃድ መርኃ ግብር ወጣቶች በሀገር ልማት ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ እያደረገ ነው
****************
ወጣቶች በሀገር ልማትና ዘላቂ እድገት ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ በማስቻል ረገድ የክረምት በጎ ፈቃድ መርኃ ግብር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ ገለፁ።
የዘንድሮ 2018 ዓ.ም የክረምት በጎ ፊቃድ መርኃ ግብርም በተደመረ አቅም ለመከወን የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም አመልክተዋል፡
የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርኃ ግብር፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችን በማሳተፍ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸውን በርካታ ተግባራት የሚያከናውንበት ትልቅ መድረክ ነው።
መርኃ ግብሩ በተለይም ትምህርት ቤቶች ዝግ በሚሆኑበት የክረምት ወቅት ወጣቶች ጊዜያቸውን፣ እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ለሀገር ጠቃሚ በሆኑ ስራዎች ላይ እንዲያውሉ ለማድረግ ያለመ ነው።
ባለፉት አመታት በአገራችን እየተተገበረ በሚገኘው በዚህ አገር አቀፍ ንቅናቄ ውስጥ ወጣቶች በአረንጓዴ አሻራ፣ ነጻ ህክምና አገልግሎት፣ ደም ልገሳ፣ ትራፊክ አገልግሎት፣ ትምህርት፣ የአረጋዊያንና አቅመ ደካሞች ቤት እድሳትና በሌሎችም በጥቅሉ14 የስምርት መስኮች ላይ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አሕመድ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ እየተተገበረ ያለው የክረምት በጎ ፈቃድ መርኃ ግብር ወጣቶች ዕውቀታቸውና ጉልበታቸው ለሕዝባቸው በሚጠቅም ተግባር ላይ እንዲያውሉ እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም የበጎነት ባህል በሀገራችን እንዲዳብር በማስቻል ረገድ ባለፉት ዓመታት በትኩረት መሰራቱንና ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን አንስተዋል።
በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሰጡት ትኩረትና ያሳዩት አርአያነት ለበርካቶች መነሳሳት መፍጠሩን ስታውቀዋል፡፡
ባጠቃላይ ከለውጡ ወዲህ የበጎ ፈቃድ ተሳታፊዎች ቁጥር በእጅጉ መጨመሩን አረጋግጠዋል።
ለአብነትም በ2010 ዓ.ም 10 ነጥብ 8 ሚሊዮን የነበረው የወጣቶች ተሳትፎ በ2017 ዓ.ም ወደ 25 ሚሊዮን ማደጉን እንዲሁም 13 ነጥብ 6 ሚሊዮን የነበረው የኅብረተሰብ ተጠቃሚነት ወደ 53 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን ጠቅሰዋል።
ይህም በዘርፉ ከፍተኛ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት የተቻለበት መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።
በተያዘው የ2018 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ መርኃ ግብር 14ቱ የስምርት መስኮች እንደተጠበቁ ሆነው፤ በተለይም በአረንጓዴ አሻራ፣ በሰላም ግንባታ፣ በአረጋውያንና አቅመ ደካሞች ቤት እድሳት እንዲሁም በትውልድ ግንባታ ላይ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ሚኒስትር ዴኤታዋ አስገንዝበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።