06/11/2026
ኦዲት ግኝት የተገኘባቸው ግለሰቦችና ተቋማት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በአጭር ቀናት ውስጥ የመንግስት ሀብት እንዲመልሱ ተገለጸ።
የቶጫ ወረዳ ኦዲት ግኝት አስመላሽ ግብረ-ሀይል የ2019 ዓ/ም 1ኛ ሩብ በጀት ዓመት የኦዲት ግኝት ሪፖርት ላይ መክሯል።
ለመድረኩ የቶጫ ወረዳ ፋይናንስ ኢኮኖሚ ልማት ጽ/ቤት የኢንስፔክሽንና ኦዲት ክትትል ቡድን መሪ አቶ ታዬ ታረቀኝ በ2019 በጀት ዓመቱ በ1ኛ ሩብ ዓመት የተከናወኑ የኦዲት ስራዎች አጠቃላይ ሁኔታንና ከዚህ በፍት በኦዲት ግኝት የታዩ ክፍተቶችን እና ሕገ-ወጥ የሀብት ንክኪዎች ያሉባቸውን አካላት ዝርዝር ሁኔታዎች ለግብረ-ሀይሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
መድረኩን የመሩት የቶጫ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ውበቴ ኡቴ እንደጠቆሙት ፦ ኦዲት ግኝት የተገኘባቸው ግለሰቦችና ተቋማት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በአጭር ቀናት ውስጥ የመንግስት ሀብት እንዲመልሱ በጥብቅ አሳስበዋል ።
መንግስት ለህዝቡ ልማት ስራና አገልግሎት የመደበዉን ሀብት ያለ አግባብ ያጎደለቱ አካላት ላይ የሚደረገው የማስመለስ ስራና በህግ የማስጠየቅ ሰራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በማንሳት ውስን የሆነውን የመንግስትና የህዝብ ሀብት ለታለመለት አላማ ብቻ በማዋል የማህበረሰብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ከየትኛዉም ጊዜ በላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደምሰራ አብራርተዋል ።
አቶ ዉበቴ አክለውም በየደረጃው የሚገኝ አመራርና ባለሙያ በመቀናጀት የኦዲት አሰራሩን ከወትሮ በልዩነት በማጠናከር ያለ አግባብ የሚባክን የመንግስት ሀብትና ንብረት እንዳይኖር ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል ።
የቶጫ ወረዳ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤና የኦዲት ግኝት ግብረ-ሀይል ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ አብዮት አስፋው በበኩላቸው ፦ የህዝብ ሀብት አላግባብ መባከን ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን በማንሳት የተቋማት ኃላፊዎች እና የሚመለከታቸው አካላት የክትትል ስራቸውን አጠናክረው በመቀጠል የባከነዉን የመንግስት ሀብት በአጭር ቀናት ውስጥ ወደ ካዜና እንዲመለስና ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ያለ ምንም ቅድሜ ሁኔታ ሊወሰዱ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመድረኩ የተገኙት ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው በኦዲት ግኝት አመላለስ ዙሪያ የሚታየው የባለ ድርሻ ተቋማት የቅንጅት ጉድለት ፣ ተቋማቱ የተሰጣቸውን ዝርዝር ተግባራት በሚገባ እያከናወኑ አለመሆናቸው፣ እንደዚሁም የመረጃዎች መጣረስ፣ የወጥነትና የጥራት ጉድለት በኦዲት ግኝት አመላለስ ተግባር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቁመዋል።
ግኝቶችን ወደ ውጤት ለመቀየር የቅድመ መከላከል ስትራቴጂ መከተል ይኖርብናል ያሉት የግብረ-ኃይሉ አባላት፤ ከወትሮ በተለዬ ሁኔታ በመቀናጀትና ሀብቱን በማስመለስ የማህበረሰብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚጠብቅባቸዉ ገልጸዋል ።
በመጨረሻም በመድረኩ በኦዲት ግኝት የተገኘውን ጉድለት ለማስመለስ የተከናወኑ ሰራዎችን በመገምገምና በቀጣይ ስራዎች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደርጎ ሃሳብና አስተያየት ታክሎበት ግብረ-ሀይሉ ለወረዳዉ ኦዲተሮች እዉቅናና ምስጋና በመስጠት የውይይት መድረኩ ተጠናቋል።
ዘገባው ፦ የቶጫ ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው።