13/11/2026
በቻግኒ ከተማ አስተዳደር የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ እና በተኪ ምርት አዘገጃጀት ዙሪያ የምክክር መድረክ ተካሄደ።
ዉይይቱ ደረቅ ቆሻሻን ከምንጩ ጀምሮ በተገቢዉ ሁኔታ መለየት፣መሠብሰብ፣ማጓጓዝ፣መልሶ መጠቀምና የማስወገድ ስርዓትን ማጠናከር ላይ እና ተኪ ምርት አዘገጃጀት ዙሪያ ያተኮረ ነዉ።
የፕላስቲክ ምርቶች በአካባቢ፣በጤናና በከተማ ዉበት ላይ የሚያስከትሉትን ተፅዕኖ በመለየት የፕላስቲክ ምርትን ማስቆምና ተገቢዉን የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ተመላክቷል።
በመድረኩ የተገኙት የአዊ ብ/አስ/አካባቢ ጥበቃ ተጠሪ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ብዙነሽ ይሁኔ፣የፕላስቲክ ምርቶች በአፈር ውስጥ ሳይበሰብሱ ከመቶ ዓመት በላይ መቆየት የሚችሉ በመሆናቸው ውሃን የመበከል፣ ብዝሃ ሕይወት የመጉዳት፣ በምርትና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያደርሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዜጎች የፕላስቲክ ምርቶችን ባለመጠቀም ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ውጤታማ እንዲሆን ጠይቀዋል።
የፕላስቲክ ተኪ ምርት አምራች ማህበራት ወደ ስራ ለማስገባ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በሀገር ደረጃ የፕላስቲክ ከረጢቶችን ማምረት፤ ወደሀገር ማስገባት፤ መሸጥ እና መጠቀም የሚከለክለውን አዋጅ ቁጥር 1383/2017 ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር የሚታዩ ውስንነቶች ለመቅረፍ ከቁጥጥር ባሻገር ተኪ ምርቶችን የማስፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ኃላፊዋ ገልጸዋል።
በብሄአሰብ አስተዳደሩ የፕላስቲክ ከረጢት የሚያስከትለውን የአካባቢ ብክለት ተጽዕኖ ለመግታት አዋጁን መሠረት ያደረገ የመከላከል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ቻግኒ ኮሙኒኬሽን