30/10/2026
"ዘላቂ የኢንዱስትሪ እድገትን ለማረጋገጥ የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ማጠናከር ወሳኝ ነው።"
ክቡር አቶ ጎሹ እንዳላማው የባሕርዳር ከተማ ከንቲባ
ጥቅምት 20/2018ዓ/ም(ባሕርዳር ከተማ ኮሙዩኒኬሽን) የባሕር ዳር ከተማ ስራና ክህሎት መምሪያ በከተማዋ በሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ዘላቂ የኢንዱስትሪ ሰላምን ለማስፈንና የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነትን ለማጠናከር ያለመ የምክክር መድረክ አካሄደ።
በዕለቱ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የባሕርዳር ከተማ ከንቲባ የተከበሩ አቶ ጎሹ እንዳላማው እንደገለፁት የከተማዋን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነትን በጤናማ መንገድ ማጠናከር እና ኢንዱስትሪውን የመሪነት ሚና እንዲይዝ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ባሕር ዳር በአሁኑ ወቅት በለውጥ ሂደት የምትገኝ ከተማ መሆኗን ያነሱት ክቡር ከንቲባው ይህንን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በየደረጃው ያሉ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋትና የሥራ አካባቢያቸውን ምቹ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በከተማዋ በአሁኑ ወቅት ከ300 በላይ የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች ምርት በማምረት ላይ መሆናቸውን የገለፁት ክቡር ከንቲባው ከ700 በላይ የሚሆኑት ደግሞ መሬት ወስደው በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ ያሉ ሲሆን በአጭር ጊዜ ወደስራ እንዲገቡ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
አያይዘውም ኢንዱስትሪዎች የኢኮኖሚው መሪና የሥራ ዕድል ፈጠራ ዋነኛ ምንጭ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ጎሹ የከተማዋን ውስጣዊና ውጫዊ ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ በመጠበቅ ዘርፉ የተቀመጠለትን አገራዊ ግብ እንዲመታ በትኩረትና በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ በአሠሪና ሠራተኛ መካከል ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን በውይይትና በምክክር በመፍታት በሥራ ቦታዎች ላይ አስተማማኝ የኢንዱስትሪ ሰላም መፍጠር ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት መሆኑን ገልፀዋል።
በክልሉ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚሰጧቸው ሥልጠናዎች በቀጥታ በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ካለው የሠራተኛ ፍላጎት ጋር የተጣጣመ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የአብክመ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተፈሪ ታረቀኝ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት አምራች ኢንዱስትሪዎች የአገር ውስጥ ገበያን እንዲቆጣጠሩ፣ ጥራት ያለው ምርት እንዲያመርቱና ውጤታማ የሰው ሀይል ስምሪት እንዲኖራቸው በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የአሰሪና ሠራተኛን መብትና ግዴታ ማክበር ለኢንዱስትሪ ልማት መፋጠን ያለው ሚና ሰፊ መሆኑ ጠቁመዋል።
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-የባሕርዳር ከተማ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ገጽ ይወዳጁ:-